ዕብራውያን 1፡4-5 ላይ ኢየሱስ ከመላእክት ጋር መነፃፀሩ ልጅነቱ ምሳሌአዊ መሆኑን አያሳይምን?

 


30. ዕብራውያን 1:4-5 እንዲህ ይላል፡- «ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ እርሱም ከመላዕክት እጅግ የላቀ ሆኖአል፡፡ እግዚአብሔር «አንተ ልጄ ነህ» እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ወይስ ደግሞ “እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፡፡» ያለው ከመላዕክት ከቶ ለማን ነው? » በዚህ ጥቅስ ላይ «ዛሬ ወልጄሀለሁ» ሲለው “ዛሬ” የሚለው ቃል የሚያሳየን ይህ አገላለጽ “ዓለም” እና “ጊዜ” ከተፈጠረ በኋላ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜ ፍጡር ስለ ሆነ ጊዜ ከመፈጠሩ በፊት “ትናንት ዛሬ ነገ ወዘተ የሚሉና ጊዜን አመልካች የሆኑ ቃላት አልነበሩምና፡፡ “ዛሬ” ተብሎ የተገለፀው ቀን ከመወለዱ በፊት ነበርን? እንዲሁም “የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ “የእግዚአብሐር ልጅ” የመባልን ስም ከመውረሱ በፊት ምን ነበር? እንዲሁም “እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” ይላል፡፡ “እኔ አባት እሆነዋለሁ” ሲል “አባቱ ነኝ” ማለት እንዳልሆነ ልብ ብለዋል? “እሆነዋለሁ” ማለት የወደፊት ጊዜን አመለካች አይደለምን? እንዲሁም ጥቅሱ “እኔ አባት እሆነዋለሁ፡ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፡” ያለው ከመላዕክት ከቶ ለማን ነው?” ይላል፡፡ በጥቅሱ ላይ “ያለው ከመላዕክት ከቶ ለማን ነው? ሲል «ያለው በማለት መግለፁ ምንን ያመለክታል? “ያለው” ሲል በተምሳሌታዊ አገላለጽ (symbolical exprerssions) “ልጄ ነህ” ማለት እንጂ በተግባር መወለዱን አያመለክትም፡፡ ይህ ባይሆንማ ኖሮ በጭራሽ ከመላዕክት ጋርም ባልተነፃፀረ ነበር፡፡

የዕብራውያን ጸሐፊ ኢየሱስን ከመላእክት ጋር ያነፃፀረበት ምክንያት የመልእክቱ ተቀባዮች የኢየሱስ ታላቅነት ከመላእክት የላቀ መሆኑን ማወቅ ስለሚገባቸው ነው፡፡ እነዚህ አማኞች ከአይሁድ እምነት የመጡ፣ በመላእክት መካከለኛነት የሚያምኑና መላእክትን ወደ አማልክትነት ደረጃ ያስጠጉ በመሆናቸው ጌታችን የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ፣ የመላእክት ፈጣሪና የእነርሱ ጌታ መሆኑን ከብሉይ ኪዳን ክፍሎች በመጥቀስ ማስረዳት አስፈላጊ ነበር፡፡ ስለዚህ የዕብራውያን ጸሐፊ ንፅፅሩን እንዲያደርግ ያስገደደው የተደራሲያኑ አመለካከት እንጂ የኢየሱስን ዘለዓለማዊ የአብ ልጅነት የመቃወም ሐሳብ ኖሮት አይደለም፡፡ “ዛሬ ወልጄሃለሁ” የሚለው አነጋገር ጊዜን አመላካች አይደለምን? በዚህ ላይ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ ኦሪጎን እና አትናቴዎስን የመሳሰሉት የቤተ ክርስቲያን አባቶች እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ በመሆኑ “ዛሬ” የተባለው እግዚአብሔር የሚኖርበትን ዘለዓለም አመላካች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር “ዛሬ” በሰውኛ አነጋገር ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊነት መታየት ስላለበት ይህ አባባል የኢየሱስን ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር ልጅነት እንደሚያመለክት አትተዋል፡፡[5] ቁርኣን እንኳ የሰውና የአላህ የጊዜ አቆጣጠር እንደሚለያይ ይናገራል (ሱራ 22፡47)፡፡

የቅርብ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐታቾች (Commentators) ደግሞ ይህ ንግግር ኢየሱስ በትንሣኤው ወቅት የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ ለፍጥረት መረጋገጡን የተመለከተ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚህ መረዳት መሠረት “ዛሬ ወልጄሃለሁ” ማለት ከዚህ ቀደም ልጅ አለመሆንን የሚያመለክት ሳይሆን ኢየሱስ ከሠራው ታላቅ ሥራ የተነሳ አብ ደስ መሰኘቱን የገለፀበት መንገድ እና የባርያን መልክ ይዞ በመምጣቱ ምክንያት የተሸፈነውን መለኮታዊ ልጅነቱን ዳግመኛ በማቀዳጀት ለፍጥረት ሁሉ ማረጋገጫ የሰጠበት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሮሜ 1፡3-4 እንደ ማስረጃ ይጠቀሳል፡፡

አሕመዲን “እኔ አባት እሆነዋለሁ” ሲል “አባቱ ነኝ” ማለት እንዳልሆነ ልብ ብለዋል? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን መላእክት በብሉይ ኪዳን ውስጥ “የእግዚአብሔር ልጆች” ስለተባሉ ከዚህ ጥቅስ በመነሳት የኢየሱስ ልጅነት እንደ እነርሱ ሁሉ ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት እንደሌለው ለመሟገት የሚሞክር ሰው የዕብራውያን ጸሐፊ ነጥብ የኢየሱስ ልጅነት ከመላእክት የተለየና የላቀ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሆነ ዘንግቷል፡፡ “እኔ አባት እሆነዋለሁ” የሚለው አነጋገር አብ የኢየሱስ አባት መሆኑ የማይቋረጥና ቀጣይነት ያለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንን አነጋገር በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ተከታዮቹን ጥቅሶች ልብ በሉ፡-

ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” (ራዕይ 21፡7፡፡

በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአማኝ አምላክ እንደሚሆን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ይህ አባባል እስከ መጨረሻው የፍርድ ቀን ድረስ ኢየሱስ የአማኞች አምላክ አይደለም የሚል ትርጉም የለውም፡፡

“ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ” (ዘጸአት 6፡7)፡፡

ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ከዚያ ቀደም የእስራኤል አምላክ አልነበረም ተብሎ ሊተረጎም አይችልም፡፡ ጠያቂያችን የጠቀሱትንም ጥቅስ በዚህ መልኩ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ