ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ለምን አጋንንትን በእግዚአብሔር መንፈስ ያወጣል?

 


36. ማቴዎስ 12፡28 ላይ ኢየሱስ «እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግስት ወደ እናንተ ደርሳለች፡፡» ብሏል፡፡ ታዲያ ኢየሱስ አጋንንትን በእግዚአብሔር መንፈስ የሚያወጣ ከሆነ ምኑ ነው የሚገርመው? ኢየሱስ “በራሴ” አላለ “በእግዚአብሔር መንፈስ” ነው ያለው፡፡ ተዓምሩስ የማነው? ታዲያ አምላክ ሁሉን ቻይ አይደለምን? ነቢያት በእግዚአብሔር መንፈስ ተዓምራት አሳይተው የለምን? ኢየሱስ በፈጣሪ እገዛ ተአምር ቢሰራ ምን ይለየዋል?

ኢየሱስ የመሲህነት አገልግሎቱን ይፈፅም በነበረበት በሥጋው ወራት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አገልግሏል፡፡ ነገር ግን ከሰማያት የወረደ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ መሆኑ ከሌሎች ነቢያት ልዩ ያደርገዋል፡፡ የሚያስወጣቸው አጋንንት እንኳ ይህንን በማወቅ ሲንቀጠቀጡና ሲገዙለት እንመለከታለን (ማርቆስ 5፡1-10፣ ሉቃስ 4፡41)፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አጋንንትን የማስወጣት አገልግሎት የተጀመረው በጌታችን መሆኑን እንመለከታለን፡፡ በብሉይ ዘመን እንዲህ ያለ ሥልጣን የነበረው ነቢይ ስለመኖሩ የተጻፈ ቃል የለም፡፡ ይህም ኢየሱስን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ኢየሱስ አጋንንትን ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹም በስሙ እንዲያስወጡ ሥልጣንን መስጠቱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያረጋግጣል (ማቴዎስ 10:1፣ ማርቆስ 6፡7፣ 16፡17፣ ሉቃስ 9፡1፣ 10:17፣)፡፡ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በኢየሱስ ስም ሰዎችን ከአጋንንት እስራት ነፃ የማውጣት አገልግሎት ቀጥሏል (የሐዋርያት ሥራ 8፡7፣ 16፡16-18፣ 19፡11-17)፡፡ እዚህ ጋ የአሕመዲን ሃይማኖት ጀማሪና ነቢይ የነበሩት ሙሐመድ በአጋንንት ላይ ስልጣን እንዳልነበራቸውና እንዲያውም በአንድ ወቅት አስማት ተሰርቶባቸው ሲሰቃዩ እንደነበር የገዛ መጻሕፍታቸው የተናዘዙትን መጥቀስ ተገቢ ይመስለናል፡-

“አይሻ እንዳስተላለፈችው ላቢድ ቢን አል-አስማ የተባለ ከበኒ ዙራይቅ ወገን የሆነ እና የአይሁዶች ተባባሪ የነበረ ሰው በነቢዩ ሙሐመድ ላይ አስማት (Magic) በመስራቱ ሳብያ ሙሐመድ ሚስቶቻቸው በሌሉበት ከሚስቶቻቸው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት እየፈፀሙ እንደሆነ በአዕምሯቸው ውስጥ እስኪታያቸው ድረስ የአስማቱ ኃይል በእሳቸው ላይ መስራት ችሎ ነበር፡፡”[8]

እውነተኛ ነቢይ ሰዎችን ከሰይጣን እስራት ነፃ ያወጣል እንጂ እንዴት ሰይጣን እንዲህ ባለ ሁኔታ ሊጫወትበት ይችላል? ነቢዩ ሙሐመድ በጣም አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እሳቸውም ሆኑ ተከታዮቻቸው ከሰይጣን ጋር እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡-

“የአላህ መልእክተኛ ሲናገሩ እንዲህ አሉ፡- ከእናንተ መካከል ሰይጣን ያልተመደበበት የለም፡፡ ሱሃባዎቹም የአላህ መልእክተኛ ሆይ በእርስዎም ላይ ሰይጣን ተመድቦበዎታልን? ብለው ጠየቁ ሲመልሱ አዎን! ተመድቦብኛል ነገር ግን አላህ በእርሱ ላይ እረዳኝና ተቃወምኩት ከሃይሉ እኔ ነጻ ነኝ አሁን የሚያዘኝ ወደ መጥፎ ስራ ሳይሆን ወደ መልካም ስራ ነው፡፡ አብዱላህ ኢብን መሱድ የዘገበው ሐዲስ ነው፡፡”[9]

“ሰይጣን ተመድቦብኛል ግን ወደ መልካም ነገር ነው የሚመራኝ” ብሎ ማለት የሰይጣንን ባሕርይ ያለማወቅ ነው፡፡ ምናልባት ነቢዩ መልካም እንደሆነ የተናገሩት ምግባራቸው ክፉ ቢሆንስ? ሰይጣን የያዘው ሰው ክፉው መልካም፤ መልካሙ ደግሞ ክፉ መስሎ ሊታየው ይችላል፡፡

“የአላህ መልእክተኛ ከእናንተ የትኛውም ሰው ከመኝታው ሲነሳ ውዱ ያድርግ አፍንጫው ውስጥ ውሃ እያስገባ እያስወጣ ሦስቴ በመደጋገም ይጠበው፡፡ ምክንያቱም ሰይጣን በአፍንጫው የላይኛው ክፍል ሌሊቱን ሙሉ አድሮ ሊሆን ይችላልና አሉ፡፡  አቡ ሁሬይራ የዘገቡት ሐዲስ ነው፡፡”[10]

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ