አምላክ የማይፈተን መሆኑ ተነግሮ ሳለ ኢየሱስ አምላክ ቢሆን ኖሮ በሰይጣን ይፈተን ነበር?

 


47. ኢየሱስ በሰይጣን ተፈትኗል መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ አምላክ በሰይጣን እደማይፈተን ይናገራል፡፡ «ማንም ሲፈተን “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፡፡ እርሱም ማንንም አይፈትንም፡፡» (ያዕቆብ 7:13) በተቃራኒው «ከዚህ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በዲያብሎስ ይፈትን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፡፡» (ማቴዎስ 4:1)፡፡ አምላክ የማይፈተን መሆኑ ተነግሮ ሳለ ኢየሱስ አምላክ ቢሆን ኖሮ እንዴት በሰይጣን ይፈተን ነበር? ታድያ ኢየሱስ በሰይጣን እየተፈተነ አምላክ ነው ይባላልን? አንድም ቦታ ላይ የኢየሱስ “ሰዋዊ ባህሪ ተፈተነ” አይልም፡፡ ታድያ ኢየሱስ አምላክ አለመሆኑን አያሳይምን?

ያዕቆብ ላይ የተጻፈው ቃል እግዚአብሔር ኃጢአትን ወይም ክፋትን እንዲያደርግ የሚገፋፋው ባሕርይ በውስጡ እንደሌለ የተነገረ በመሆኑ ከእርሱ ውጪ የሚገኝ አካል ሊፈትነው እንደማይሞክር ለማሳየት እንደ ማስረጃ ሊጠቀስ የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ሐሳብ ቁጥር 14ን ጨምረን ስናነብ ግልፅ ይሆናል፡- “ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም፡፡[1] ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” (ያዕቆብ 1፡13-14)፡፡

ስለዚህ ያዕቆብ እየተናገረ ያለው ከውስጥ በክፉ ምኞት ምክንያት ስለሚፈጠር ፈተና ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍፁምና ቅዱስ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ አይፈተንም፡፡ ነገር ግን ሰዎች እግዚአብሔርንና መንፈሱን እንደተፈታተኑ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ተጽፏል (መዝሙር 106፡4፣ ዘጸአት 17፡1-2፣ ዘኁልቁ 14፡22፣ ዕብራውያን 3፡8-9፣ የሐዋርያት ሥራ 5፡9)፡፡

እንደ አብ እና እንደ መንፈስ ቅዱስ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መለኮት በመሆኑ ክፋትን እንዲያደርግ የሚገፋፋው ባሕርይ በውስጡ የለም፡፡ ስለዚህ በክፉ አይፈተንም፡፡ ነገር ግን እስራኤላውያን በምድረ በዳ እግዚአብሔርን እንደ ተፈታተኑት ሁሉ ሰይጣን በምድረ በዳ ተፈታትኖታል፡፡ እርሱ ግን ፈተናውን በማሸነፍ ሰይጣንን አሳፍሮታል፡፡ ወልድ ፍፁም ሰው በመሆን ወደ ምድር እንደመጣም መዘንጋት የለብንም፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሶች ችላ ብለን አምላክ በምንም መንገድ ሊፈተን እንደማይችል ብንቀበል እንኳ ኢየሱስ በሰዋዊ ባሕርዩ በሰይጣን ሊፈተን ይችላል፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ የኢየሱስ በሰይጣን መፈተን ከያዕቆብ 7፡13 ጋር የሚጣረስበት መንገድ የለም፡፡

ጠያቂያችን እንደተለመደው ቁርጥራጭ ጥቅሶችን መዘው ከማውጣት ይልቅ ሙሉውን የያዕቆብን መጽሐፍ በማስተዋል ሆነው ቢያነቡት ኖሮ ያዕቆብ ስለ ኢየሱስ አምላክነት የጻፈውን ማየት ባልተሳናቸው ነበር፡-

የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ያዕቆብ 1፡1)፡፡

ያዕቆብ የእግዚአብሔር አብ እና የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የኢየሱስን ፈጣሪነት ባይቀበልና ፍጡር እንደሆነ ቢያምን ኖሮ ፈጣሪና ፍጡርን አንድ ላይ በማጣመር የሁለቱም ባርያ መሆኑን ባልተናገረ ነበር፡፡ ይህ የማይገባው ሙስሊም ካለ “የአላህ እና የሙሐመድ ባርያ ነኝ” በማለት መናገር ይችል እንደሆን እንጠይቀዋለን፡፡ “ወንድሞቼ ሆይ፥ በክብር ጌታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን እምነት ለሰው ፊት በማድላት አትያዙ” (ያዕቆብ 2፡1)፡፡

እስኪ ይህንን አባባል ለያሕዌ ከተነገረው ከዚህ ቃል ጋር ያነፃፅሩት፡- “እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘለዓለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ፡፡ ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኃያል” (መዝሙር 24፡7-8)፡፡