ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንደሚሉት አምላክ ከሆነ እንዴት መንግስት ሰማያት የማስገባው “እኔ አይደለሁም” ሲል ይናገራል?
48. የዘብዴዎስ ልጆች እናት ሁለቱ ልጆቿን በመንግስት ሰማያት በቀኝና በግራው ያስቀምጥላት ዘንድ ኢየሱስን ጠይቃ እንዲህ ሲል መልሶላታል «ኢየሱስም “በእርግጥ እኔ የምጠጣውን የመከራ ፅዋ ትጠጣላችሁ”ነገርግን በቀኝና በግራዬ እድትቀመጡ የማደርገው እኔ አይደለሁም ይህ ቦታ የሚሰጠው አባቴ ላዘጋጀላቸው ነው፡፡ (ማቴዎስ 20፡23) ታድያ ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንደሚሉት አምላክ ከሆነ እንዴት መንግስት ሰማያት የማስገባው “እኔ አይደለሁም” ሲል ይመልሳል? ክርስቲያኖች እንደሚሉት ከሆነ ለበርካታ ጊዚያት የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ የተሳነው “ሥጋ ለብሶ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ስለመጣ” ነው፡፡ “ነገር ግን በዚህኛው ጥቅስ እየሱስ “እኔ አይደለሁም” ሲል እንደማይችል የተናገረው ስጋ በለበሰበት ጊዜ ሳይሆን በመጭው ዓለም በመንግስተ ሰማያት ነው፡፡ ታድያ አምላክ ከሆነ እርሱስ ለምን እንደ አብ ገነት ማስገባት ይሳነዋል?
መንግሥተ ሰማያት በማስገባት ረገድ የመጨረሻውን ብያኔ የሚሰጠው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቀደም ሲል በማስረጃዎች አስደግፈን ገልጠናል፡፡ ነገር ግን ይህ ጥቅስ መንግሥተ ሰማያት ስለማስገባት የሚናገር አይደለም፡፡ ለኢየሱስ የቀረበለት ጥያቄ የሥልጣን ጥያቄ እንጂ መንግሥተ ሰማያት የመግባት ጥያቄ ባለመሆኑ አሕመዲን ያልተባለውን ሐሳብ በራሳቸው ፈጥረው ማስገባታቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ አስተያየት የመስጠት አቅምም ሆነ ዝግጅት እንደሌላቸው ያመለክታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በእስራኤል ላይ ነግሦ ይገዛል የሚል እምነት ስለነበራቸው (የሐዋርያት ሥራ 1፡6-8) ንጉሥ እንደመሆኑ በቀኝና በግራ የሚቀመጡ ሰዎች ይኖራሉ፤ ስለዚህ ያንን ቦታ ለመያዝ መሽቀዳደማቸው ነው፡፡ ጌታችን ወደ ምድር ተመልሶ ለአንድ ሺህ ዓመት እንደሚነግሥ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ራዕይ 20)፡፡ በዚህ ወቅት በግራና በቀኝ የሚቀመጡትን የመወሰኑ የሥራ ድርሻ የአብ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ የሥላሴ አካላትን የግብር ክፍፍል (Function) የሚያሳይ እንጂ የመለኮታዊ ባሕሪ መበላለጥን የሚያሳይ አይደለም፡፡