ራዕ 1፡1 ላይ “እግዚአብሔር ለሱ የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ” ይላል፡፡ ታዳያ አምላክ ቢሆን ሁሉን አዋቂ መሆን አልነበረበትምን?

 


56. የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ራዕይን” እንዲህ በማለት ይተረጉማል ፦ “ራዕይ”፦ ሰው ሳያንቀላፋ በተመስጦ የሚያየውና የእግዚአብሔር ቃል የሚገለጥበት፡፡ ራዕይ ከህልም ይለያል፡፡ ራዕይ እግዚአብሔርን ለሚያውቁ የእግዚአብሔር መንፈስ ላደረባቸው ይሠጣል” ይላል፡፡ የዮሐንስ ራዕይ 1:1 ላይ «ቶሎ መሆኑን የሚገባውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳይ እግዚአብሔር ለእርሱ የሰጠዉ የኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ ይህ ነው፡፡» ይላል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚያምኑት ኢየሱስ አምላክ ከሆነ ሁሉንም ያውቃል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር ለሱ የሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ራዕይ ይላል፡፡ ታዳያ አምላክ ቢሆን ሁሉን አዋቂ መሆን አልነበረበትምን? ራዕይ ሊሠጠው ይገባ ነበርን? እርሱስ ቢሆን የሦስቱ ሥላሴዎች አባል አይደለምን?

አሕመዲን የጠቀሱትን መዝገበ ቃላት ልብ ብለው ቢያነቡት ኖሮ ራዕይን እንዲያዩ የሚሰጠው በምደር ላይ ለሚገኙት ሰብዓውያን እንጂ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ለሚኖሩት አለመሆኑን በተገነዘቡ ነበር፡፡ ይህ ቃል ኢየሱስ ራዕይ ማየቱን ሳይሆን ራዕዩን ለባርያው ለዮሐንስ እንዲያሳይ አብ እንደሰጠው የሚናገር ነው፡፡ አንዱ የሥላሴ አካል ከሌላው መቀበሉ ከአንዱ ግፃዌ መለኮት ውጪ ከሚገኝ ሌላ አካል እስካልተቀበለ ድረስ አምላክነቱን ሊያጠራጥር አይችልም፡፡ ጠያቂያችን እንደልማዳቸው ቆራርጠው ባያነቡ ኖሮ በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጡ ብዙ ሐሳቦችን ባገኙ ነበር፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የሚከተሉትን ነጥቦች እናስተውላለን፡- 

 

  • ኢየሱስ መልአኩን እንደላከ ተነግሯል (ቁ.1)፡፡ መላእክት የፈጣሪ እንጂ የፍጡራን ናቸውን? ከፈጣሪ በስተቀርስ ሊያዛቸውና ሊልካቸው የሚችል አካል አለን?
  • ከደመና ጋር እንደሚመጣ እና የወጉትም እንደሚያዩት ተነግሯል (ቁ.7)፡፡ ይህ ዳንኤል በራዕይ ያየው የምድር ሕዝቦች ሁሉ የሚገዙለት፣[2] የማያልፍ ዘለዓለማዊ ግዛት ያለው የሰው ልጅ መሆኑን ያሳያል (ዳንኤል 7፡13-14)፡፡ የወጉት እንደሚያዩት መነገሩ ደግሞ ያሕዌ እግዚአብሔር “ወደወጉኝ ወደ እኔ ይመለከታሉ” በማለት የተናገረውን የሚገልፅ በመሆኑ ኢየሱስ ያሕዌ መሆኑን ያሳያል፡፡[3]
  • ቁጥር 7 ላይ ኢየሱስ እንደሚመጣ ከተናገረ በኋላ ቁጥር 8 ላይ፡- ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፦ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል” በማለት ኢየሱስ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ መሆኑን ያስረዳል፡፡
  • ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እርሱ መሆኑን ተናግሯል (ቁ.17)፡፡ ይህንን ሊናገር የሚችለው ብቸኛው አካል ያሕዌ እግዚአብሔር ነው፡- “የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም” (ኢሳይያስ 44፡6)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአንዱ ግፃዌ መለኮት አካል ባይሆን ኖሮ ይህንን ባልተናገረ ነበር፡፡

አሕመዲን የኢየሱስን አምላክነት ለማስተባበል የጠቀሱት ጥቅስ ከአውድ የተገነጠለና በተሳሳተ መንገድ የተተረጎመ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የሆነውና ስለ በደላችን ነፍሱን አሳልፎ የሰጠው ገናናው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ መሆኑን እንድናረጋግጥ ዕድል ስለፈጠሩልን ጠያቂያችንን ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡