ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ “አምላክ” ከሆነ አምላክ ከፍ ያደርጋል ወይንስ ከፍ ይደረጋል? ፊልጵስዩስ 2፡9

 


58. ፊልጵስዩስ 2፡9 ስለ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጿል፡፡ “ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፡፡ ስሙ ሳይሰጠውና ከፍ ከመደረጉ በፊትስ ምን ነበር? ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ “አምላክ” ከሆነ አምላክ ከፍ ያደርጋል ወይንስ ከፍ ይደረጋል? ከስም ሁሉ በላይ የሆነው ስምስ ምንድነው? “የአምላክ ልጅ” መባል? ይህ ከስም ሁሉ በላይ የሆነው ስም ሳይሰጠው በፊት ኢየሱስ ምን ነበር? ይህ ስሙን ከማግኘቱ በፊት ጊዜ እንደነበረ አያሳይምን?

ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአታችን ሊዋጀን የባርያን መልክ ይዞ ወደ ምድር በመምጣቱ ምክንያት ራሱን እንዳዋረደና ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላ አብ ከፍ ከፍ እንዳደረገው ነው ይህ ጥቅስ የሚናገረው፡፡ ነገር ግን ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በምን ሁኔታ እንደነበር አሕመዲን እንደልማዳቸው ቆርጠው የጣሉት የጥቅሱ ቀዳማይ ክፍል ይገልፃል፡- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ በእናንተ ዘንድ ይሁን፡፡ እርሱ በባሕርዩ አምላከ ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቆጠረውም፡፡ ነገር ግን የባርያን መልክ ይዞ በሰውም አምሳል ተገኝቶ ራሱን ባዶ አደረገ፡፡ ሰው ሆኖ ተገልጦ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡ እስከ ሞት ያውም በመስቀል ላይ እስከመሞት ታዛዥ ሆነ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ከፍ አደረገው ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፡፡ ይኸውም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው፡፡” (ፊልጵስዩስ 2፡5-11 አ.መ.ት.)፡፡

አሕመዲን የኢየሱስን አምላክነትና ከአብ ጋር እኩል መሆን ያለምንም ብዥታ እንዲህ ባለ ሁኔታ ጥርት አድርጎ ከሚናገር ክፍል ውስጥ አንዷን አረፍተ ነገር በግብር አባታቸው መቀስ ቆርጠው በማውጣት የኢየሱስን አምላክነት ለማስተባበል ይሞክራሉ፡፡ በእውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ቅጥፈት በእጅጉ አስደንጋጭና ሕሊና ካለው ሰው የማይጠበቅ ነው፡፡ ይህ ተግባራቸው ሰውየው የዋኀንን ለማወናበድ ምን ያህል የቆረጡና ለጥፋት ራሳቸውን የሸጡ እንደሆኑ ያሳያል፡፡