አምላክ አምላክ አለውን?
6. አምላክ አምላክ አለውን? ከላይ በጠቀስናቸው የክርስትና ሃይማኖት አስተምሮዎች ውስጥ ቀጥተኛና ግልፅ በሆነ መልኩ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን አላስተማረም፡፡ ለዚያም ነው በክርስቶስ አምላክነት ዙርያ የማይነጥፉ ጥያቄዎች የሚነሱት፡፡
ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በግልፅ እና በማያሻማ ሁኔታ አስተምሯል፡፡[3] ይህ ባይሆን ኖሮ ሐዋርያቱ አምላክነቱን ተቀብለው ባላመለኩት ነበር፡፡ አሕመዲን ግን የሰው ልጅ የማይከራከርበት እና የማይለያይበት አንድም እውነታ እንደሌለ መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በጣም ግልፅ ሊባሉ የሚችሉ ነገር ግን ሙስሊሞች በተለያዩ አንጃዎች በመከፋፈል እርስ በርሳቸው የሚከራከሩባቸውና የሚፋለሙባቸው አስተምህሮዎች አሉ፡፡ አሕመዲን የሚከተሉት የሰለፊ (ወሃቢ) ጎራ አላህ እንደ ሰው እጅ፣ እግር፣ ዓይን፣ አፍንጫ፣ ወዘተ. ያለው አምላክ መሆኑን ያስተምራል፡፡ ሌሎች ሙስሊሞች ደግሞ አላህ በዚህ መልኩ ሊገለፅ የማይችል ረቂቅ መሆኑን ያምናሉ፡፡ በቁርአን ውስጥ እጅግ ግልፅ ከሚባሉት ትምህርቶች መካከል አንዱ የመሐመድ የመጨረሻ ነቢይነት ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚክዱ፣ ጥቅሱን በተለየ መንገድ የሚተረጉሙ አሕመዲያ በመባል የሚታወቁ ሙስሊሞች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ትምህርታቸው የተነሳም በሌሎች ሙስሊሞች ከፍተኛ ስደት ይደርስባቸዋል፡፡ ዒሳ እንዳልተሰቀለና ወደ ሰማይ እንደተወሰደ ቁርኣን እንደሚናገር በሱኒ ሙስሊሞች ዘንድ በፅኑ ቢታመንም የአሕመዲያ ሙስሊሞች መሰቀሉን ነገር ግን በመስቀል ላይ አለመሞቱን ያስተምራሉ፡፡ ብዙ ሙስሊሞች ቁርአን ዘለዓለማዊ የአላህ ቃል መሆኑን የሚያምኑ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ በጊዜ ውስጥ የተፈጠረ ቃል መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህ ርዕስ ሙስሊሞችን በመከፋፈል ለክፍለ ዘመናት ሲያገዳድላቸው ኖሯል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የቁርአንንና የሐዲሳትን ግልፅነት ቢጠየቁ አሕመዲን በአዎንታ እንደሚመልሱ ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን “ግልፅ” የተባሉት ጉዳዮች ሙስሊሞችን ለክፍፍልና እርስ በርስ ለመገዳደል ዳርገዋል፡፡ ግልፅ በሆኑት ጉዳዮች ላይ መለያየት የሰው ልጆች ባሕርይ በመሆኑ በግልፅ የተቀመጠውን የኢየሱስን አምላክነት የሚክዱ ግለሰቦችና ቡድኖች መገኘታቸው ሊያስደንቀን አይገባም፡፡
አሕመዲን ይቀጥላሉ፡- እስቲ አሁን ደግሞ የሚከተሉትን ማገናዘቢያዎች ከስሜታዊንት በፀዳ መልኩ ለማስተዋል እንሞክር፡፡ ኢየሱስ አምላክ እንዳለው በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ ተገልጿል ፦
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (1ኛ ጴጥሮስ1:3)
ስለ እናንተ እያመሰገንሁ ስጸልይ ስለ እናንተ ማሳሰብን አልተውም፤ የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ፡፡ (ወደ ኤፌሶን 1:16-17)
ለወደደንና ከኃጢአታችን በደሙ ነፃ ላወጣን፣ አምላኩንና አባቱን እንድናገለግል መንግስትና ካህን ላደረገን ለእርሱ ክብርና ኃይል ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን አሜን” (የዮሐንስ ራእይ 1:6)፡፡
(ከነዚህ ጥቅሶች በተጨማሪ ጸሐፊው 2ቆሮንቶስ 11፡31፣ ሮሜ 15:5-6፣ ኤፌሶን 1:3፣ ማርቆስ 12:29፣ ዮሐንስ 20:17፣ ማርቆስ 15:34፣ ማቴዎስ 27:46 እና 2ቆሮንቶስ 1:3 ጠቅሰዋል፡፡)
ኢየሱስ አምላክ እያለው እንዴት ራሱ አምላክ ይሆናል? አምላክ ሌላ አምላክ አለው? ክርስትያኖች የሚያመልኩት አምላክ እራሱ አምላክ አለው ማለት ነውን?
በክርስትና ትምህርት መሠረት ኢየሱስ ፍፁም ሰው ፍፁም አምላክ መሆኑን ቀደም ሲል ገልፀናል፡፡ ፍፁም ሰው እንደመሆኑ አብ አምላኩ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ፍፁም አምላክ እንደመሆኑ ደግሞ ከአብ ጋር እኩል ነው፡፡ ኢየሱስ በሰውነቱ አምላክ የለሽ (Atheist) አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላም እንደምንመለከተው ብዙዎቹ ጥያቄዎች ይህንን እውነታ ካለመረዳት የመነጩ መሆናቸውን እናስተውላለን፡፡