ደቀመዛሙርቱ በማቴዎስ 15፡12 ላይ “ኢየሱስ ኃያሉ አምላክ ነው” ብለው ቢያምኑ ኖሮ እንዴት “አወቅህን?” ብለው ይጠይቁታል?

 


70. በማቴዎስ 15፡12 ለይ “በዝያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው ፈረሳውያን “ይህን ቃል ሰምተው እንደተሰናከሉ አወቅህን?” አሉት” ይላል፡፡ ደቀመዛሙርቱ “ኢየሱስ ኃያሉ አምላክ ነው” ብለው ቢያምኑ ኖሮ እንዴት “አወቅህን?” ብለው ይጠይቁታል? አምላክ መሆኑ ከታመነ ሁሉን አዋቂ ነውና “አወቅህን” ተብሎ ይጠየቃልን?

ኢየሱስ አእማሬ ኩሉ ስለመሆኑ ቁጥር 10 ላይ ማስረጃዎችን ሰጥተናል፡፡ ሐዋርያት እዲህ ያለ አነጋገር በመጠቀም መጠየቃቸው ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው የሚገልፅ እንጂ የኢየሱስን ሁሉን አዋቂነት መጠራጠራቸውን የሚያሳይ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ሐዋርያት የኢየሱስን ማንነትና ተልዕኮ በትክክል የተገነዘቡት ከትንሳኤው በኋላ በመሆኑ በዚህ ወቅት ትክክለኛ ማንነቱን ሳይገነዘቡ ቀርተው እንዲህ ያለ ንግግር ቢጠቀሙ የሚያስገርም አይደለም፡፡ ይህ ሐዋርያቱ የእርሱን ትክክለኛ ማንነት በሙላት እንደልተገነዘቡ የሚያሳይ እንጂ ኢየሱስ ሁሉን አዋቂ አለመሆኑን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ከትንሳኤው በኋላ ግን ሁሉን አዋቂ አምላክ መሆኑን ተገንዝበው ሲመሰክሩና ተገቢውን ክብር ሲሰጡ እንመለከታለን (ዮሐንስ 20፡28፣ 21፡17)፡፡