አምላክ የማይሞት ከሆነ እና ኢየሱስ ከሞተ እንዴት አምላክ ይሆናል?

 


8. አምላክ የማይሞት መሆኑ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 1:17፣ ሮሜ 1:21-23፣ ሮሜ 1:25 እና 1ኛ ጢሞቴዎስ 6:16 ላይ ተገልጿል፡፡ ኢየሱስ ሟች ነው፤ አምላክ የማይሞት ከሆነ ኢየሱስ ሟች መሆኑ አምላክ አለመሆኑን አያሳይምን? ኢየሱስ ሲሞት “ሰውነቱ” ነው ወይስ “አምላክነቱ” ነው የሞተው? በሰውነቱ ከሞተስ እንዴት ሰው የዓለምን ኃጢአት ሊሸከም ይችላል? የአምላክ ወደ ምድር መምጣት ያስፈለገው ሰው ሊሸከመው ስለማይችል ነው ብለው ክርስትያኖች ያምኑ የለም? አቋሞን በማስረጃ ቢያስደግፉ?

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የሞትን ትርጉም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት በአዳም ኃጢኣት ምክንያት የመጡ ሁለት ዓይነት ሞቶች አሉ፡፡ የመጀመርያው ሞት የመንፈስ ሞት ነው፡፡ የመንፈስ ሞት ማለት በኃጢኣት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው (ዘፍጥረት 2፡15-17፣ 3፡22-24፣ ኢሳይያስ 59፡2፣ ዕንባቆም 1፡13፣ ኤፌሶን 2፡1-5)፡፡ ሁለተኛው የሞት ዓይነት ደግሞ አካላዊ ሞት ነው፡፡ አካላዊ ሞት የነፍስ ከሥጋ መለየት እንጂ የህልውና ማክተም አይደለም (ዕብራውያን 12፡22-24፣ ያዕቆብ 2፡26፣ ራዕይ 6፡9-11)፡፡ ጠያቂው “ሞት” የሚለውን ቃል የህልውና ማክተም አድርገው የተረጎሙት ይመስላል፡፡ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሁለቱም የሞት ዓይነቶች የህልውና ማክተምን ስለማያስከትሉ ጠያቂያችን እየተናገሩ ባሉበት መንገድ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልሞተም (ህልውናው አላከተመም)፡፡ ኢየሱስ መለኮት እንደመሆኑ መጠን ህልውናው ሊያከትም አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ኢ-ሟቲነት ሲናገር ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ሌሎች ፍጥረታት በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ቢሆን እንጂ ህልውናቸው ሊጠፋ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሞት ማለት የህልውና ማክተም ተደርጎ እስካልተተረጎመ ድረስ የኢየሱስ መሞት እግዚአብሔር ኢ-ሟቲ መሆኑን ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር አይጣረስም፡፡ ምክንያቱም የኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርይ መኖር ያቆመበት ጊዜ አልነበረምና፡፡

የሰው ልጆች ሁሉ ኃጢአተኞች በመሆናቸው ምክንያት የሌላውን ኃጢአት የመሸከም ብቃት የላቸውም፡፡ ኢየሱስ ግን ንፁህና ኃጢአት አልባ በመሆኑ የሌሎችን ኃጢአት የመሸከም ብቃት አለው፡፡ አምላክ በተሠግዎ ወደ ምድር መምጣት ያስፈለገበት ምክንያት ፍፁም የሆነና ከኃጢአት የራቀ ሰው በመታጣቱ ነው (ኢሳይያስ 59፡13-17)፡፡ ኢየሱስ ኃጢአታችንን የተሸከመው በክቡር ሥጋው ነው (1ጴጥሮስ 2፡24)፡፡ ኃጢአታችንን ያስተሰረየው ደግሞ ቅዱስ ደሙን በማፍሰስ ነው (ሮሜ 3፡25፣ 5፡9፣ ኤፌሶን 1፡7፣ ራዕይ 1፡4-5፣ 1ጴጥሮስ 1፡18-19፣ ዕብራውያን 9፡22)፡፡ ይህ ሥጋና ደም የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የማንነቱ አካል በመሆኑ ኃጢአታችንን የመሸከም ብቃት አለው፡፡

 

 

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ