ኢየሱስ ጅማሬ ከሌለዉ ለምንድነዉ ቅደም ተከተልን በሚገልጽ ቃላት አባት እና ልጅ ተብለው የተጠሩት?

 


80. ኢየሱስ ጅማሬ፤ ፍጥረት እና ዉልደት ከሌለዉ እንደ ክርስትና እሳቤ አንዱ “አምላክ” (ኢየሱሱ) “ልጅ/ወልድ” ሲባል ሌላኛዉ አምላክ (አብ) “አብ/አባት” ተብሏል፡፡ ታዲያ ለምንድነዉ ቅደም ተከተልን በሚገልጽ ቃላት የተጠሩት? “አባት” እና “ልጅ” ቅደም ተከተል ከሌላቸዉ ለምን እንዲህ ያለ መጠሪያ ኖራቸዉ? ካልሆነ ስያሜያቸዉን መቀያየር እንችላለንን?

አብና ወልድ የተባሉበት ምክንያት ኢየሱስ በዘለዓለማዊ መገኘት ከአብ የተገኘ በመሆኑ ነው (ለጥያቄ ቁጥር 74 የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ)፡፡ እነዚህ ቃላት በመካከላቸው የሚገኘውን ጥብቅ ቁርኝት የሚገልፁ የትስስር ቃላት (Relational Terms) እንጂ የጊዜ ቅደም ተከተልን የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የዘለዓለም አባት”[1] ተብሎ የተጠራ ቢሆንም (ኢሳይያስ 9፡6) ነገር ግን ወልድ እንጂ አብ አይደለም፤ ስለዚህ ስያሜያቸውን በማቀያየር ኢየሱስን የአብ አባት ልንል አንችልም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ስያሜያቸው የተቀያየረበት ቦታ የለም፡፡