ማርያም ከመፀነሷ በፊት ኢየሱስ ነበርን? ከነበረ የትና እንዴት?
81. ማርያም ከመፀነሷ በፊት ኢየሱስ ነበርን? ከነበረ የትና እንዴት? እርሷ ከመንፈስ ቅዱስ ስትፀንስ እርሱ የት ነበር? ስትፀንስ ያ የነበረዉ ጠፋ ሊባል ነዉ? ወይስ ኢየሱስ እንደሚወለድ የሚገልጽ የአምላክ ቃል ብቻ ነበር? እስቲ በደንብ ያዉጠንጥኑት!
አሕመዲን የገዛ ጥያቄያቸውን በደንብ ያውጠነጠኑት አይመስልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከአብ ጋር በሰማይ ይኖር እንደነበር በግልፅ ይናገራል (ዮሐንስ 1፡1-3፣ 3፡13፣ 6፡33-48፣ 6፡62፣ 8፡42፣ 56-58፣ 13፡3፣)፡፡
ዮሐንስ 1፡1 ላይ የተገለፀለው “ሎጎስ” (ቃል) አንዳንዶች እንደሚሉት ልበ እግዚአብሔር ውስጥ የተወሰነ ሐሳብ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የነበረ ልዩ አካል ነው፡፡ ይህንንም ለማመልከት ሐዋርያው “ሁቶስ” (እርሱ) የሚለውን የግሪክ ተባዕታይ ተውላጠ ስም (Musculine Pronoun) እና “ዘንድ” ተብሎ የተተረጎመውን “ፕሮስ” የሚለውን ድርጊት ገላጭ (Proposition) ተጠቅሟል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም ከአብ ጋር የነበረ፣ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ የሥላሴ አካል እንጂ በቅድስት ድንግል ማርያም ማህፀን በተፀነሰ ጊዜ መኖር የጀመረ አይደለም፡፡