“ድንግል አምላኳን ወለደች” የሚለዉ ከየት መጣ? ከጉባኤ?

 


89. ሉቃስ 2፡6-7 ላይ “በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው” ይላል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ድንግል አምላኳን ነዉ የወለደችዉ? ጥቅሱ “ወንድ ልጅ” ነዉ የሚለዉ? ኢየሱስን ስትወልድ ማርያም “አምላኬን ወለድኩ” ብላ ነበር ያሰበችዉ ወይስ “ወንድ ልጅ”? ታዲያ “ድንግል አምላኳን ወለደች” የሚለዉ ከየት መጣ? ከጉባኤ? በሐዋርያት ዘመንስ ይህ ‹‹ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች›› የሚለዉ እምነት ነበርን? ታዲያ ከየት መጣ? ከጉባኤ!! የሚከተለዉ ይህንን ያረጋግጣል፡- ቤተክርስቲያን በ431 ዓ.ል በኤፌሶን በተካሄደዉ ጉባኤ ድንግል ማርያም ቴዎቶኮስ (የአምላክ) እናት መሆዋን እንደ ሃይማኖት ህግ አወጀች፡፡ (ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዉ አብ ቃል እና የዓለም መድሃኒት፤ በኢት/ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጽ/ጠ/ጽ/ቤት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ የተዘጋጀ፤ አዲስ አበባ ፤ ማስተር ማተሚያ ቤት ገፅ 159)

ጠያቂያችን በጠቀሱት በዚያው ክፍል ውስጥ ኢየሱስ የዓለም መድኃኒት እና ጌታ መሆኑ ስለተነገረ ድንግል ፈጣሪዋን እንደወለደች መነገሩ ትክክል ነው (ሉቃስ 2፡10-11)፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ የሚወለደው ልጅ አምላክ መሆኑን መሲሁ ከመወለዱ ከ700 ዓመታት በፊት ትንቢት ተናግሯል (ኢሳይያስ 9፡6)፡፡ ስለዚህ “ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች” የሚለው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እስከሆነ ድረስ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተጠቀሰው እውነት ኦፊሴላዊ በሆነ ጉባኤ እውቅና በመስጠት እንደ እምነት አቋም መያዟ ስህተቱ ምኑ ላይ ነው?