ኢየሱስ አምላክ ከሆነ እግዚአብሔር ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስና በኃይል ለምን ቀባው?
9. የሐዋርያት ሥራ 10:38እግዚአብሔር የናዝሬቱ ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስና በኃይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ስልጣን ስር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ፡፡” ይላል በመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በአንድም ስፍራ ላይ “እግዚአብሔር” ባይባልም ክርስቲያኖች “ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው” ይላሉ፡፡
አሕመዲን ግልፅ ቅጥፈት ስለፈፀሙ እዚህ ጋ እናስቁማቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በአንድም ስፍራ ላይ “እግዚአብሔር” አልተባለም ብለዋል፡፡ ኢየሱስ እግዚአብሔር የተባለበትን አንድ ጥቅስ እናሳያቸው፡- “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ… ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን” (ዮሐንስ 1፡1፣ 14)፡፡ ስለዚህ ጠያቂው በመጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በአንድም ስፍራ ላይ “እግዚአብሔር” አልተባለም ማለታቸው አንባቢያንን ለማሳሳት ሆነ ብለው የዋሹት ውሸት ነው አለበለዚያም ደግሞ ባለማወቅ የተናገሩት ነው፡፡ ሆነ ብለው ከዋሹ መንፈሳዊ ትምህርት የማስተማር የሞራል ብቃት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ባለማወቅ ከተናገሩ ደግሞ ይህንን ቀላል እውነታ ማወቅ የተሳነው ሰው ጥልቅ የሆኑ ሥነ መለኮታዊ ጉዳዮችን ለመወያየትም ሆነ ክርስትናን ለመተቸት የሚያስችል ብቃት ሊኖረው አይችልም፡፡
- ? እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበረ” በሚለው ጥቅስ “እርሱም” እና “እርሱ” የሚሉት ቃላት ኢየሱስን ለመግለጽ በጥቅሱ ውስጥ ስለተገለፁ እንዲሁም ክርስቲያኖች ኢየሱስን “እግዚአብሔር ወልድ” ስለሚሉት ቃላቶቹን በእግዚአብሔርም” ብንተካው “እግዚአብሔርም (እርሱም) እግዚአብሔር (ከእርሱ) ጋር ስለነበረ ይሆናል፡፡ ስንት እግዚአብሔር ሆኑ? ክርስትያኖች ሦስት የሆኑትን “አንድ” ቢሉ እውን ሦስትነታቸውን ትተው አንድ ይሆናሉን? በዚህ ጥቅስ ”እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን በኃይል ቀባው ” የሚለውን ብናጤን ፣ እግዚአብሔር (አብ) ፣ ኢየሱስ (እርሱንም ክርስቲያኖች “እግዝአብሔር ነው “ይላሉ፡፡) እና መንፈስ ቅዱስ (እንደሚሉት እርሱም ከሥላሴዎች አንዱና ራሱም እግዚአብሔር ነው፡፡) ይህ ማለት ከሦስቱ ስላሴዎች እና ራሳቸውም እግዚአብሔር ከሆኑት ፣ አንደኛው እግዚአብሔር ሁለተኛውን እግዚአብሔርን በሦስተኛው እግዚአብሔር ቀባው ማለት ነው፡፡ ይህ ትክክለኛ እሳቤ ነው ብለው አእምሮዎን ማሳመን ይችላሉን?
ጠያቂው መልሰው መላልሰው የሥላሴን አስተምህሮ በመዘንጋት እግዚአብሔር በመለኮትም በአካልም ነጠላ መሆኑን እንደ ቅድመ ግንዛቤ በመያዝ ይሞግታሉ፡፡ በሥላሴ አስተምህሮ መሠረት አንድ አምላክ ብቻ ነው ያለው፡፡ የአንዱ አምላክ ሦስቱ አካላት እያንዳንዳቸው አምላክ ተብለው ቢጠሩም ነገር ግን አንዱን ግፃዌ መለኮት የሚካፈሉ ሦስት አካላት እንጂ የሦስት መለኮታት ድምር ባለመሆናቸው ሦስት አማልክት ወይም ሦስት እግዚአብሔሮች አይደሉም፡፡ ጸሐፊው ለዚህ የክርስትና ትምህርት ጆሯቸውን ባይደፍኑና እስላማዊ አስተምህሯቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለመጫን ባይሞክሩ ኖሮ ባልተደናገሩ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አገልግሎቱን ይፈፅም የነበረው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነበር፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ “ክርስቶስ” የሚለው ማዕርግ ትርጉም አልባ ይሆን ነበር፡፡ “ክርስቶስ” ወይም “መሲህ” ማለት የተቀባ ማለት ሲሆን የኢየሱስን ንግሥና፣ ክህነት እና ነቢያዊ አገልግሎት የሚገልፅ ነው፡፡ ክርስቶስ በምድር ላይ እንደ አገልጋይ በነበረበት ጊዜ መሲሃዊ አገልግሎቱን ይፈፅም ስለነበር በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቀብቷል፡፡ ጸሐፊው ምክንያታዊ ሙግት ከማቅረብ ይልቅ የቃላት ጫወታ በመጫወት የአንባቢያኑን ስሜታዊ ውሳኔ መጠየቃቸው የረባ ቁምነገር ያዘለ አይደለም፡፡