“ከቶዉንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም” ይላል፡፡ ኢየሱስ ግን ታይቷል፡፡ ኢየሱስ አምላክ እንዳልሆነ አያሳይምን?
90. በመጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ታይቶ እንደማይታወቅ በ1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡1፤ 1ኛ ዮሐንስ መልእክት 4፡12፤ ዮሐንስ 1፡18 እና ዮሐንስ 5፡57 ላይ ተገልጧል፡፡ ለአብነት ያህል በ1ኛ ጢሞ 6፡16 ላይ “እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘለዓለም ኃይል ይሁን፤ አሜን” ይላል፡፡ እንዲሁም በዮሐንስ 1፡18 ላይ “ከቶዉንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፡፡” ይላል፡፡ ኢየሱስ ግን ታይቷል፡፡ ተዲያ አምላክ የማይታይ ከሆነ ኢየሱሱ አምላክ እንዳልሆነ አያሳይምን?
ለዚህ ጥያቄ በተለያዩ መንገዶች መልስ መስጠት ይቻላል፡፡ የመጀመርያው የኢየሱስ ሰብዓዊ ባሕርይ እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩ በሰዎች ዓይን አልታየም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን አሕመዲን የጠቀሷቸው ጥቅሶች እግዚአብሔር በምንም ዓይነት ሁኔታና መንገድ አልታየም ከሚለው የተሳሳተ ትርጓሜ ሲፋቱ ሁለተኛና ይበልጥ ጠንካራ የሆነ ምላሽ እናገኛለን፡፡ እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔርን ሙሉ በሆነው መለኮታዊ ክብሩ ማንም ማየት እንደማይችልና በዚያ ሁኔታ እንዳልታየ የሚናገሩ ሲሆኑ ውሱን በሆነ ሁኔታ እንዲሁም በራዕይ እግዚአብሔርን ያዩት ሰዎች ስለመኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ በበርካታ ቦታዎች ላይ ይናገራል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
“ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ፡፡ እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም፡፡” (ዘጸአት 24፡9-11)
“እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በፊቴ ሞገስ ስላገኘህ በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር አደርጋለሁ አለው፡፡ እርሱም፦ እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ… ደግሞም፦ ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ፡፡ እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም፡፡” (ዘጸአት 33፡17-23፣ ኢሳይያስ 6፡1-4)፡፡
ጸሐይ ከመሬት በብዙ እጥፍ እንደምትበልጥና ትንሽዬ የጸሐይ ቅንጣት መሬት ላይ ብትወድቅ ይህችን ፕላኔት ሙሉ በሙሉ የማጥፋት አቅም እንዳላት ይነገራል፡፡ አፅናፈ ዓለማትን ሁሉ የፈጠረው ሃያሉ አምላክ ምንኛ ታላቅና የሚያስፈራ ይሆን! እግዚአብሔር ግርማው የሚያስፈራ እጅግ ታላቅ አምላክ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሙሉ ክብሩን አይተው መትረፍ አይችሉም፡፡ ለሰው አቅም ሊመጥን በሚችልበት ሁኔታ ለሰዎች የታየባቸው ጊዜያት እንደነበሩ እነዚህ ጥቅሶች ቢናገሩም ይህ “መታየት” ከታላቅነቱና ከግርማው ጋር ሲነፃፀር እንዳለመታየት ይቆጠራል፡፡ ይህ “ማየት” የእስክሪፕቶ ጫፍ የምታክለውን የጸሐይ ቅንጣት በማየት ጸሐይን እንዳየን የመናገር ያህል ከማየት የሚቆጠር አይደለም፡፡
በዚህ መሠረት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አምላክነቱ በተወሰነ ደረጃ ቢታይም ነገር ግን ፊልጵስዩስ 2 ላይ እንደተጻፈው ወልድ ወደ ምድር ሲመጣ መለኮታዊ ክብሩን በመተው ስለነበር ሙሉ የሆነው መለኮታዊ ግርማው በሰዎች ዓይን አልታየም፡፡