1ኛ ቆሮንቶስ 15:29 መሰረት ክርሥቲያኖች “ለሞቱ ሰዎች” ብለው ነው እንዴ የሚጠመቁት?

 


96. 1ኛ ቆሮንቶስ 15:29 “ትንሳኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሱ ከሆነ ፣ ሰዎች ለእነሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ?” ይላል፡፡ እነማን ናቸው “ለሞቱ ሰዎች” ብለው የሚጠመቁት? ክርሥቲያኖች “ለሞቱ ሰዎች” ብለው ነው እንዴ የሚጠመቁት? ወይስ ምን? እነማንስ ናቸው?

ይህ ጥያቄ የኢየሱስን ማንነት ከተመለከተው የመጽሐፉ ርዕስ ጋር በምን ይገናኛል? ጠያቂው እንደ ምንም ብለው የጥያቄዎቹን ብዛት 303 ለማድረስ የፈለጉ ይመስላል፡፡ ለማንኛውም ማንየአዲሱ መደበኛ ትርጉም የግርጌ ማጥኛ ለዚህ ጥያቄ ጥሩ መልስ ሰጥቷል፡፡

ለሞቱ ሰዎች የሚጠመቁት የሚለው ግሥ የአሁን ጊዜ መሆኑ በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ለሙታን ሲሉ ይጠመቁ እንደነበር ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ጳውሎስ ስለዚህ ልማድ ተጨማሪ ማብራርያ ባለመስጠቱ ይህንን ሐሳብ ለማብራራት ብዙ ተሞክሯል፡፡ ከእነዚህ ሦስቱ የሚከተሉት ናቸው፡- (1) በሕይወት ያሉ አማኞች ሳይጠመቁ ለሞቱ አማኞች ይጠመቁ ነበር፤ ይህንንም የሚያደርጉት ባለመጠመቃቸው የሚጎድልባቸው ነገር እንዳይኖር በማለት ነው፡፡ (2) ክርስቲያኖች የሙታንን ትንሳኤ ተስፋ በማድረግ ይጠመቁ ነበር (3) በሞት የተለዩ ክርስቲያኖችን ስፍራ ለመሙላት ሲሉ ክርስቲያኖች ይጠመቁ ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ሰዎችን ያነሣው እግረ መንገዱን ነው፡፡ ይህ ልማድ የተነሳው ተቀባይነት ስላለው ሳይሆን የሙታን ትንሳኤ እንዳለ ለማስረዳት ነው፡፡ ምናልባትም የዚህ ሐረግ ትርጉም ስውር እንደሆነ ይኖራል፡፡[1] ጳውሎስ ግን ይህንን ሐሳብ የጠቀሰው በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ ሰዎች ለሙታን እየተጠመቁ የሙታን ትንሳኤን መካዳቸው በራሳቸው ልምምድ መሠረት እንኳ ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት ያህል እንጂ ተግባሩን በመደገፍ አይደለም፡፡ የአዲስ ኪዳን የጥምቀት ፅንሰ ሐሳብም ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡

ኡስታዝ ከዚሁ ሐሳብ ሳይወጡ ሙስሊሞች ለሞቱት ዘመዶቻቸው ሲሉ ለምን ሰደቃ እንደሚያደርጉና ሐጅ እንደሚፈፅሙ እንዲያስረዱን እንጠይቃቸዋለን፡፡