ኢየሱስ የተደረገና የተገኘ አምላክ ነውን? ከአርዮሳውያን ለተቀዳ የሙስሊሞች ሙግት የተሰጠ ምላሽ

ኢየሱስ የተደረገና የተገኘ አምላክ ነውን?

ከአርዮሳውያን ለተቀዳ የሙስሊሞች ሙግት የተሰጠ ምላሽ

Yeshua Apologetics


ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሙስሊሞች ዘንድ በስፋት ከተለመዱት ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይህ ነው። አንድ ሙስሊም ሰባኪ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተደረገ አምላክ ነው ይለናል (ሐዋ 2:36)። እንዲያ ከሆነ አምላክን አምላክ አደረገው ማለት አይሆንምን? በኒቂያም ጉባኤ ላይ እንደምናየው ከሆነ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ እውነተኛ አምላክ ማለታቸውስ ምንን ያሳያል? ኢየሱስ የተፈጠረ ነው ያልነውም ዝም ብለን አይደለም።

በእውነቱ እንደ ጥያቄ ያነሳቸው ነጥቦች ለጥያቄ ብቁም ያልሆኑ ናቸው። እስቲ ነጥብ በነጥብ እንመልከታቸው፦

አንደኛ፦ መጽሐፍ ቅዱስን ስንፈታ ስለምን እና ተደራሲያኑን እነማን ናቸው የሚለውን መለየት መቻል አለብን። ስለዚህ ወደ ሐዋርያት ሥራ 2:36 ጥቅስ ላይ ስናልፍ እንዲህ ይላል፦

“እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።”
— ሐዋርያት 2፥36

ይህ ሙስሊም “እንዳደረገው” የሚለው በመውሰድ ነው “የተደረገ አምላክ ነው” እያለን ያለው። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱሱ ክፍል የሚለን ሌላ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ቤት ሁሉ ይወቅ ማለቱ ጌትነቱ አሁን ጀመረ ማለት አይደለም። እግዚአብሔር አብ የናዝሬቱን ኢየሱስን መሲህ፣ የጌቶች ጌታ እና የነገሥታት ንጉሥ አድርጎ መሾሙና ሹመቱን ደግሞ ለዓለም ይታይ ዘንድ ኃይሉንና ሥልጣኑን በግልፅ በመናገር እርሱን ገልጦታል ማለት እንጂ በተቀበለበት ሰዓት ኢየሱስ ተደረገ (ተፈጠረ) ማለት አይደለም። ታዲያ ለምን “አደረገው” አለን? ይህንን ለማወቅ ተደራሲያኑን ማወቅ ይኖርብናል። እነማን ናቸው የሚለውን ስንመለከት፦ በጭካኔ የገረፉትንና ሰቅለውት የነበረውን ያንን መሢህ እግዚአብሔር በሰማይና በምድር ውስጥ ያሉ ሁሉ ይንበረከኩለት ዘንድ የተሸፈነውን ስልጣኑንና ክብሩን ሁሉን በመግለጥ አሳየ ወይም በግልጠት ኢየሱስ አምላክም ጌታም መሆኑን የማረጋገጥን ሥራ አደረገ ማለት ነው። ምሳሌ ብዙ ጊዜ ጉድለት ቢኖርበትም እንዲሁ ጭላንጭል ወገግታ ትሆን ዘንድ አንድ ምሳሌ ልጠቀም።

አንድ ታዋቂ ያልነበረ ነገር ግን በጣም በዕውቀቱ የሚተማመን የነበረ አንድ ሰው ነበር። ያንን ሰው ጓደኛው ለምን ዕውቀትህን አትገልጥም በማለት ይነዘንዘው ነበር። ልጁ በእንቢታ በማለፍ ይተወው ነበር። የሆነ ጊዜ ግን ጓደኛው የልጁን ተሰጥዖ በብዙ ሕዝቦች ይታወቅ ዘንድና ዕውቀቱ ይገለጥ ዘንድ አደረገው። በዚያም ልጅ ብዙዎች ተደነቁ፤ አከበሩትም። እንግዲህ ከምሳሌው እንደምንረዳው “አደረገው” መባሉ ያንን በዓለም ያልታየ የተደበቀ የነበረውን ታላቅ ምስጢር በመግለጥ ተናገረ ማለት እንጂ አዲስን ዕውቀት በመስጠት አስጀመረው ማለት አይደለም። ጥቅሱ እግዚአብሔር አብ “ጌታም ክርስቶስም” መሆኑን በትንሣኤው ማሳየቱን የሚናገር እንጂ መለኮት ያልነበረን አካል መለኮት ማድረግን የሚያሳይ አይደለም። የዚህ ንግግር ባለቤት ተደራሲያኑ እንደሆኑ ግሪኩ ሲያስቀምጥ “πᾶς οἶκος Ἰσραήλ (መላው የእስራኤል ሕዝብ) ይላል። ስለዚህ ያላከበሩት ያ ታላቅ ንጉሥ እንደከበረ እየተናገረ መሆኑን ልናስተውል ይገባል።

ሁለተኛ፦ በኒቂያው የሃይማኖት መግለጫ ላይ “…ከአምላክ በተገኘ አምላክ ከእውነተኛ አምላክ በተገኘ…” የሚለው ክርስቶስን ጅማሬ ያለው አያደርገውም ወይ?” ከላይ እንደ ተጠየቀው በኒቂያው የሃይማኖት መግለጫ ላይ በገረፍታ ላነበበው ይሄ ጥያቄ መፈጠሩ የሚያስገርም አይደለም። የተገኘ እና የተፈጠረ ለሚለውን አጠር አድርጌ ላሳይ፦ “ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ፥ ከአብ ጋር በመለኮት አንድ በሆነ (ὁμοούσιον τῷ Πατρί/ ሆሙስዮን ቶ ፓትሪ)” በሚለው አውደ ሐሳብ ላይ “በተገኘ” የሚለው ቃል ላይ አንደኛ ወልድ ፍጡር መሆኑን አያሳይም። ሁለተኛ ደግሞ ወልድ በሀልወቱ በሆነ ጊዜ የመጣ መሆኑን አያሳየንም። እነዚህን ሁለት ሐሳቦች ከማብራራቴ በፊት ግሪኩን ቃል በቃል እንመልከተው፦

“…τὸν ἐκ τοῦ Πατρὸς γεννηθέντα πρὸ πάντων τῶν αἰώνων, Φῶς ἐκ Φωτός, Θεὸν ἀληθινὸν ἐκ Θεοῦ ἀληθινοῦ, γεννηθέντα οὐ ποιηθέντα, ὁμοούσιον τῷ Πατρί…”

በዚህ አንቀጽ ላይ “Φῶς (ፎስ/ብርሃን) ἐκ Φωτός, Θεὸν ἀληθινὸν (ቴዎን አሌቲኖን/እውነተኛ አምላክ) “ፎስ ኤክ ፎቶስ” በቀጥታ ስንተረጉመው “ከብርሃን ብርሃን” የሚል ፍታቴ አለው። ይህም የሚገልጸው አብ ብርሃን እንደሆነ ሁሉ (1ዮሐ. 1:15፣ መዝ. 27:1) ወልድም ብርሃን ነው (ዮሐ. 8:12፣ 2ጢሞ. 6:13-16) ማለታቸው መሆኑን እናያለን። ቀጥለን ደሞ “Θεὸν ἀληθινὸν ἐκ Θεοῦ ἀληθινοῦ የሚለው አንቀጽ ደግሞ አብ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ሁሉ (ኤር.10፡10፣ ዮሐ. 17:3) ወልድም ደግሞ እውነተኛ አምላክ መሆኑን (1ዮሐ. 5:20፣ ራዕይ 6:10፣ 3:7) የሚያትት አንቀጸ ሐረግ ነው። እንጂ ኢየሱስ ተፈጠረ ከዛ አብ አደረገው ማለት አይደለም ህጉም እንደዛ እንድንተረጉም አይፈቅድም።

ሦስተኛ፦ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ መወለድ እና መፈጠር የሚል ጥያቄ ቀርቧል። ቅድም በኒቂያው ጉባኤ ላይ አንድ ወሳኝ ነጥብ በትልቁ ተስሎ እናገኛለን “.በተፈጠረ ሳይሆን በተወለደ/γεννηθέντα οὐ ποιηθέντα” በዚህ አንቀጽ ላይ እንደ ቅድሙ ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን ሰፋ አድርገን እንመልከት፦ በተፈጠረ (ፖዬቴንታ/ποιηθέντα) የሚለውን እና በተወለደ (ጌኔቴንታ/γεννηθέντα) ወልድ ከአብ ተወለደ እንጂ አልተፈጠረም። ፖዬቴንታ/ποιηθέντα የሚለው የግሪክ ቃል መፈጠር ከሚለው ይልቅ መሰራት ወደ ሚለው ትርጉም ይቀርባል። ይሄ ማለት “ከእውነተኛ አምላክ በተገኘ አምላክ” የሚለው አንቀጽ ውስጥ አምላክ አምላክን ሰራ(ፈጠረ) የሚል ስሑት ሐሳብ እና ትርጓሜ እንደ ሙስሊሙ ወዳጄ እንዳይመጣ ወልድ የተሰራ(ፖዬቴንታ/ποιηθέντα) ሳይሆን የተወለደ (ጌኔቴንታ/γεννηθέντα) መሆኑን በዛው አናቅፅ ላይ ተቀምጦና ተገልጾልን እንመለከታለን። ጌኔቴንታ/γεννηθέντα የሚለው የግሪክ ቃል ጌናኦ/γεννάω ወይም ጌኖስ/γένος የሚለውን ይገልጻል። ጌናኦ/γεννάω የሚለው የጽርዕ(የግሪክ) ቃል መወለድን፣ ከአብራክ መውጣትንና ከአንድ አካል መገኘትን ወዘተ የሚያመላክት ትርጓሜ ሲኖረው ጌኖስ/γένος የሚለው ቃል አብዝሃኛውን ጊዜ አይነትን፣ መደብንና ባህሪን ወዘተ የሚገልጽ ቃል ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔር አምላክ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የምድር አራዊትን በሚፈጥርበት ጊዜ እንደየባሕሪያቸው (ወገን፣ ዓይነት፣ ምድብ) አድርጎ ሲፈጥራቸው እንመለከታለን፦

“እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ(ጌኖስ/γένος) አደረገ፤ እንስሳውንም እንደ ወገኑ(ጌኖስ/γένος) ፤ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ (ጌኖስ/γένος) አደረገ እግዚአብሔር ያመልካም እንደሆነ አየ።” —ዘፍ 1፥25

ስለዚህ የአርዮስ መሳት እኛ ወልድ ከአብ ተወለደ ስንል በግሪኩ ጌኖስ/γένος ማለታችን እንደሆነ አለማወቁ ነው። ይህ ማለት ወልድ ከአብ ጋር አንድ መደብና ባህርይ አለው ማለት እንጂ በጊዜ ውስጥ መኖር ጀመረ ማለት አይደለም። አንቀጹን እንደ አርዮስ <<ደካማ እናቶች ዘንድ ሄዶ አንቺ ልጅ ከመውለድሽ በፊት እናት ትባይ ነበርን?>> ብሎ እንደ ሰውኛ የመወለድ ዓይነት ትርጓሜ ሰጥተን በሆነ ጊዜ የመጣ የሚለውን ስሑት አረዳድ መውሰድ የምንችልበት አንዳች ምክንያት የለም። የወልድ ልጅነት ዘለዓለማዊ ልጅነት (Eternal Begetting of the Son) ነው እንጂ Adopted ወይም በሆነ ጊዜ የተከሰተ ልጅነት አይደለምና።

ስለዚህ ሙስሊም ወገኖቻችን እንዳነሱት ጥያቄ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ (ሞኖጌኔስ ቴዎስ/μονογενής θεός) እንጂ የተፈጠረ የተደረገ አለመሆኑን በዚህ መልኩ እናውቃለን ማለት ነው።

እግዚአብሔር የቃሉን መረዳት በሙላት ይግለጥልን!


ለተጨማሪ ንባብ ተከታዮቹን መጣጥፎች ይመልከቱ፦

መሲሁ ኢየሱስ