የመጀመርያው ፍጡር ወይስ የአርዮሳውያን ፈጠራ? ክፍል ፩

የመጀመርያው ፍጡር ወይስ የአርዮሳውያን ፈጠራ? ክፍል ፩

በወንድም ዳዊት


በጥንቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ የአስተምህሮ ችግር ፈጥረው ከነበሩት ሐሳውያን አንዱ የነበረው አርዮስ ከሚታወቅባቸው አስተምህሮዎች መካከል ዋነኛው ኢየሱስ በባሕርዩ ከአብ ያነሰ የአብ የመጀመርያው ፍጡር ነው እንዲሁም ከአብ ጋር በአብሮነት ያልነበረበት ጊዜ ነበረ የሚለው ነው። በዘመናችን የአርዮስን ፈለግ ተከትሎ የተደራጀው “የይሖዋ ምስክሮች” ወይም “የመጠበቂያ ግንብ” በመባል የሚታወቀው የሐሳውያን ማሕበር ልክ እንደ አርዮስ ሁሉ ኢየሱስ ፍጡር ነው በማለት ያስተምራል። በዚህ ጽሑፍ እነዚህ ወገኖች የሐሰት ትምህርታቸውን ለማጽናት የሚጠቅሷቸውን ጥቅሶች አንድ በአንድ እናያለን። ጥቅሶቹ በዋናነት ሁለት ሲሆኑ የመጀመርያው እንደሚከተለው ይነበባል፦

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል” ቆላስይስ 1፥15-16።

እነዚህ ወገኖች ቃላቱን በራሳቸው የትርጓሜ ስልት ሰፍተው ኢየሱስን ጅማሬ ያለው ፈጣሪ ብለው ከእውነት ወንጌል ተገንጥለው የራሳቸውን ሰው ሠራሽ ትምህርት በአደባባይ መስበካቸውን ማየት የተለመደ ነው። በቆላስይስ መጽሐፍ “በኩር” (Firstborn) ተብሎ የተተረጎመው ቃል በግሪኩ ንባብ πρωτότοκος (ፕሮቶቶኮስ) የሚል ሲሆን ሰፊ ትርጉም እንዳለው አለማወቃቸው እነዚህን ወገኖች ለተሳሳተ ትርጓሜ ዳርጓቸዋል። “በኩር” የሚለው ቃል “መጀመሪያ የተወለደ” ከሚለው በተጨማሪ እንደየአገባቡ ሥልጣንን፣ የበላይነትን፣ ተወዳጅነትንና ልዩ የሆነ ግንኙነትን ያመለክታል። በቆላስይስ ላይ የተጻፈውን በአውድ ስንመለከት እንዲህ ይላል፦

“…በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል” ቆላስይስ 1፥15-16።

አንደኛ፦ ከዚህ ክፍል እንደምንረዳው ኢየሱስ ክርስቶስ የሁሉ ነገር ፈጣሪና አስገኝ ከሆነ ከእርሱ ውጭ የተሠራ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም። ስለዚህ “እርሱ ከፍጥረታት በፊት ፍጡር ነው” የሚል ፈሊጥ ከየትም ሊመጣና ሊያዛልቅ አይችልም። ክርስቶስ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ከሆነ እርሱን የፈጠረ አካል አለ ማለት ትርጉም አይሰጥም። “ሁሉን ፈጥሯል” ተብሎለት እርሱ ራሱ ፍጡር ነው ከተባለ እራሱንም ፈጥሯል የሚል ኢ-አመክንዮአዊ ንግግር ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ጉዳዩ እንደዚያ እንዳልሆነ ለማሳየት በሌላ ስፍራ “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” በማለት ዘግቶታል (ዮሐንስ 1:3)። ከተፈጠረው ሁሉ ያለ ኢየሱስ የተፈጠረ ምንም ነገር ከሌለ እርሱ ፍጡር ሊሆን አይችልም፤ ራሱን ሊፈጥር አይችልምና። ይህንን የተረዳው የመጠበቂያ ግንብ ማሕበር New World Translation (የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም) በተሰኘ የተጣመመ ትርጉሙ ቆላስይስ 1:15-16ን ሲተረጉም “because by means of him all other things were created” በማለት ተርጉሞታል። ይህንኑ ትርጓሜ በአማርኛ ሲያስቀምጥ “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ…” ብሎታል። ይህ በዋናው የግሪክ ንባብ ውስጥ የሌለና ሐሳዌው ማሕበር የራሱን አስተምህሮ ለመደገፍ የጨመረው በቃለ እግዚአብሔር ላይ የተሠራ ድፍረት ነው።

ሁለተኛ፦ የአረፍተ ነገሩን የሰዋሰው አወቃቀር ስንመለከተው ለተፈፀመው ድርጊት ክርስቶስ መነሻ (source) ወይም እራሱ አድራጊ እንደሆነ ያመለክታል እንጂ ክርስቶስን በድርጊቱ ውስጥ አያጠቃልለውም። ከዚህ ቀደም በሌላ ጽሑፍ እንደገለጽነው ἐν (ኤን) በግሪክ ቋንቋ መስተዋድድ ስትሆን፣ ትርጉሟ “በ…፣ ከ…፣ …ጋር” የሚሉትን የሚወክል ነው። ነገር ግን ἐν ከተቀባይ ሙያ (Dative) ጋር ከመጣችና የምትገልፀው ስለ አንድ የሆነ አካል ከሆነ ትርጉሟ በሁለት ተከፍሎ ይታያል። አንደኛ፣ እየተገለፀ ያለው አካል በራሱ ሕይወት ወይም ሕልውና የሌለው ነገር (inanimate) ከሆነ፣ ይህ አካል ለተፈፀመው ድርጊት መጠቀሚያ (instrument, means) እንጂ እራሱ የድርጊቱ ፈፃሚ አይደለም። ሁለተኛው ግን እየተገለፀ ያለው አካል ሕልውና ያለው (animate) ከሆነ ለተፈፀመው ድርጊት ይህ አካል መነሻ (source) ወይም እራሱ አድራጊው ነው ማለት ነው። እንግዲህ ቆላስይስ 1:15-16  ላይ እየተገለፀ ያለው አካል ኢየሱስ ነው። የተፈፀመው ድርጊት ደግሞ “መፍጠር” ነው።  ኢየሱስ ደግሞ ሕልውና ያለው (animate) ስለሆነ በዚህ ክፍል ἐν ከተቀባይ ሙያ (Dative) ጋር ስለመጣች የአረፍተ ነገሩ ትርጉም ኢየሱስ እራሱ የድርጊቱ ፈፃሚ ወይም ፈጣሪ መሆኑን ያስረዳል።  (Jeremy Duff, New Testament Greek, p. 49)።

መጽሐፉ ክርስቶስ “ከፍጠረት ሁሉ በፊት በኩር” የተባለበትን መነሻ ሲገልጽ “የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና…” የሚል ምክንያት በማስቀመጥ ፈጣሪ ስለሆነ መሆኑን ነገረን እንጂ የተፈጠረ ስለሆነ ነው አላለንም። ስለዚህ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” ሲባል ከፍጥረታት በፊት የነበረ፣ ዘላለማዊ አምላክ፣ ሁሉ የተፈጠሩበት፣ የፍጥረት ገዢ፣ ከፍጥረቱ ውስጥ የማይመደብ አልፋ እና ኦሜጋ ለማለት ነው። ቅዱሳት መጽሐፍት ይህንን የሚናገሩ ሆነው ሳሉ የመጠበቂያ ግንብ ማሕበር በዚህ መጠን ስሁት ትርጓሜ ሰጥቶ የአርዮስን ዱካ መከተሉ ለምን ይሆን? መጽሐፍ እንደሚል፦ “ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና።” (1ቆሮ. 16:22)።

ይቀጥላል…


መልስ ለአርዮሳውያን