ኢየሱስ የራሱ ልጅ የራሱ አባት ነውን?
ለኢየሱስ ብቻ አስተምህሮ የተሰጠ ምላሽ
በአማን እንዳለ
በብዙ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ ኢየሱስ ወልድ መሆኑንና አባቱ እግዚአብሔር አብ ደግሞ ላኪው እንደሆነ ተናግሯል (ዮሐንስ 3፡16-17፣ 5፡23-24፣ 5፡36-37፣ 6፡38-40፣ 7፡28-29፣ 8፡16-18፣ 8፡42፣ 10፡36፣ 11፡42፣ 12፡49፣ 14፡10-11፣ 14፡24፣ 15፡9፣ 16፡27-28፣ 17፡3፣ 17፡8፣ 17፡18፣ 17፡21-23። ማቴዎስ 11፡27፣ 10፡40፣ 15፡13፣ 21፡37፣ 23፡34፣ 24፡36፣ 26፡39፣ 26፡53። ማርቆስ 9፡37፣ 12፡6፣ 13፡32፣ 14፡36። ሉቃ 4፡18-19፣ 4፡43፣ 9፡48፣ 10፡16፣ 10፡22፣ 20፡13፣ 22፡29፣ 24፡49። ራዕይ 2፡27፣ 3፡5፣ 3፡21)። ማንኛውም ሰው በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ክፍሎች ሲያነብ የኢየሱስ አባት ራሱ ኢየሱስ ነው፤ ልጁም ደግሞ ያው ራሱ ኢየሱስ ነው የሚል መረዳት ከቶ ሊኖረው አይችልም። “የኢየሱስ ብቻ” አስተምህሮ ግን ይህንን ግልጽና የማያሻማ እውነት በመለወጥ ኢየሱስ የራሱ አባት የራሱ ልጅ እንደ ሆነ ይናገራል። እነዚህን ወገኖች “ኢየሱስ አብ ከሆነ ኢየሱስ የማን አባት ነው?” እንዲሁም “ኢየሱስ ወልድ ከሆነ የማን ልጅ ነው?” ብለን ስንጠይቃቸው መልሳቸው ኢየሱስ የራሱ አባት የራሱም ልጅ ነው የሚል ነው። አባትና ልጅ የሚሉት ቃላት ግንኙነትን አመልካች በሆኑበት ሁኔታ አንዱ ማንነት ለራሱ አባት ለራሱ ልጅ ነው ብሎ ማለት ትርጉም ይሰጣልን? ውድ አንባቢያን፣ እናንተ በአንድ ጊዜ ለራሳችሁ አባት ተብላችሁ እናንተው ደግሞ ተመልሳችሁ ለራሳችሁ ልጅ ናችሁ ብትባሉ ምላሻችሁ ምን ይሆን? እንዲህ ያለው መረዳት አያዎ (Paradox) በመሆኑ ምክንያት የሚፈጥረው የአስተምህሮ መናጋት የሚያሳስባቸው አንዳንድ ወገኖች ነገሩን ለማድበስበስ ጥረት ቢያደርጉም የቤተ እምነቱ ቀጥተኛ አስተምህሮ ይህ መሆኑን የቤተ እምነቱ መምህራን የሚጽፏቸው ጽሑፎችና የመድረክ ትምህርቶቻቸው ያሳያሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ የኢየሱስ ብቻ አስተምህሮን በቀደምትነት ያመኑትና የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ተብላ የምትጠራውን ቤተእምነት የመሠረቱት የቀድሞ ሊቀመንበር ቄስ ተክለማርያም ገዛኸኝ “ቃሉ ይናገር” በሚለው መጽሐፋቸው በትምህርት 9 ላይ ስለአብና ወልድ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦
“1ጢሞ.3፡16 በሥጋ የተገለጠው አምላክ አብ ነው ወይስ ወልድ? ብለው ለሚጠይቁ መልሱ አንድ አምላክ ብቻ ስላለ በሥጋ ገጽታና በመንፈስ ገጽታ ማለትም መንፈስና ሥጋ ሆኖ በአንድ አካል የተገለጠው አማኑኤል የተባለው አንዱ ፈጣሪያችን አብ ብቻ ነው። ስሙም ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎአል።”
በእርግጥ ይህ ድፍረት የተሞላበት ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሐሰት ትምህርት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራዕይ ቢነበብ ለኀጢአታችን የሞተልን አብ እንደሆነ በአንድም ቦታ አይነግረንም፤ ወይም ደግሞ ኢየሱስ አንድም ጊዜ እርሱ ራሱ አብ እንደሆነ ወይም በሥጋ ገጽታው ወልድ በመንፈስ ገጽታው ደግሞ አብ እንደ ሆነ አላስተማረንም። ይህንን አባባላቸውን ይሁን ብለን ብንወስድ እንኳን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሊሞት ሲል ነፍሱን/መንፈሱን አብ እንዲወስደው ለምኗልና እንደ “ኢየሱስ ብቻ” አስተምህሮ ትንታኔ ኢየሱስ አብን (መንፈሱን) ለአብ ሰጠ ብለን እንረዳ? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ እርገቱን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦
“ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት።” (ዮሐ 20፡17)
ጌታ ኢየሱስ በዚህ ስፍራ ወደ አባቱ እንደሚያርግ በማያሻማ መልኩ ተናግሯል። ሌላኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ደግሞ ስለ ዕርገቱ እንዲህ ይለናል፦
“ይህንንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ እነሆ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ ደግሞም የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምንቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።” (ሐዋ 1፡9-11)
አብ የኢየሱስ የውስጡ ማንነት ነው ብለን ካልን እነዚህን ሁለት ምንባባት ይዘን ኢየሱስ ያረገው ወደ ውስጡ ነው ልንል ነውን? ወደ አባቴ ነው የማርገው ያለው ወልድ ያረገው ወደ ማይታየው የራሱ ገጽታ ወይንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ውስጥ በተደጋጋሚ ከሰማይ ስለልጁ ወደ መሰከረው ወደ አባቱ? የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የምንመለከተውን ዓይነት አገላለጽ በወንጌላዊው ማርቆስ ዘገባ ውስጥም እናገኛለን።
“ደመናም መጥቶ ጋረዳቸው ከደመናውም የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ድምጽ መጣ።” (ማር 9፡7)
“ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱም ላይ ሲመጣ አየ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።” (ማቴ 3፡16-17)
እነዚህን የመሳሰሉ አብ ለወልድ ያለውን ፍቅር የገለጸባቸው ብዙ ምንባባት እንዳሉ ሁሉ ወልድም ለአብ ያለውን መውደድ የገለጸባቸው ምንባባት ይገኛሉ (ዮሐ. 14፡31)። ስለዚህ አብና ወልድ በመካከላቸው ፍቅር አላቸው፤ ይህ ፍቅር ደግሞ በመጨረሻ ለእኛም ተገልጧል። አባት በልጁ ሥራ እንደሚደሰት፣ ደግሞም እደሚወደው እየተናገረ ሳለ ሐሰተኞች “የኢየሱስ ብቻ” መምህራን ግን ይህ ንግግር ከውስጥ ሆኖ ከማይታይ ማንነት ለሚታየው ማንነት የተነገረ ነው በማለት ይቀጥፋሉ። መውደድና ደስ መሰኘት የሚባሉ ነገሮች በሁለት አካላት መካከል የሚሆንን ስሜት አመላካች ሲሆኑ ኢየሱስ ራሱ አብ ራሱ ደግሞ ወልድም ከሆነ መጽሐፍ ቅዱሳችን በዚህ መልኩ ለምን ተጻፈልን? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን።
“በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ አባት ሆይ የሰማይና የምድር ጌታ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕጻናት ስለገለጥህላቸው አመሰግንሃለው። አዎን አባት ሆይ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኗልና። ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም ከወልድም በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።” (ማቴ 11፡25-27)
በዚህ ቦታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድና ብዙ ተዓምራት ያደረገባቸው ከተሞች ማንነቱን ባለማወቃቸው ከነቀፋቸው በኋላ ምንም እንኳን ይህ ቢሆንም በራሳቸው ጥበብ እናውቃለን የሚሉት እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ሳይረዱ ነገር ግን የተናቁና ተራ ተደርገው ከሚታዩት የማሕበረሰብ ክፍሎች የወጡት ደቀ-መዛሙርት የእርሱን እውነተኛ ማንነት እንዲገነዘቡ የአባት ፈቃድ እንደሆነ ይናገራል። በዚህ መሠረትም አባት የራሱ ቅዋሜ ማንነት ያለው አካል መሆኑን ከሚያሳዩ ባሕርያተ-አካል (Elements of Personhood) ውስጥ አንዱን ከአብ ጋር አቆራኝቶ ይነግረናል። ስለዚህ አብ ፈቃድ አለው። “ፈቃድ አለው” የሚለው ገላጭ ዐረፍተ ነገር አንድ ነገር እንዲሆን ወይም ደግሞ እንዳይሆን የመፍቀድና የመከልከል ሙሉ ችሎታን የሚያመለክት ነው። በዚህም ምንባብ አዋቂዎችና ጥበበኞች የተሰወረባቸው (ፈቃዱ ያልሆነላቸው) እንዲሁም ደግሞም ሕጻናት ተብለው የተጠሩት አካላት የተገለጠላቸው (ፈቃዱ የሆነላቸው) የአብ ፈቃድ ምን ዓይነት እንደሆነ እንረዳለን። በተመሳሳይ መልኩ ወልድ የሚታወቅበትን ማንነት ለሰዎች መግለጥ በአብ ፈቃድ ላይ የሚወሰን እንደ ሆነ ሁሉ አብም የሚታወቅበትን የአብ ማንነት መግለጥ በወልድ ፈቃድ ላይ የተገደበ ነው። ከወልድ በቀር እና ወልድም ከሚፈቅድ በቀር አብን ማንም ማወቅ አይችልምና። ስለዚህ በዚህ ክፍል አብ የሚታወቅበት ማንነት የራሱ ሲሆን በንጽጽር ወልድም የሚታወቅበት ማንነት የራሱ የወልድ ነው። አብ ወልድ የሚታወቅበትን የወልድ ማንነት ለወደደው ሰው እንደፈቃዱ የሚገልጥ ሲሆን አብ ደግሞ የሚታወቅበትን ማንነት ወልድ እንዲሁ በፈቃዱ ለሰዎች ይገልጣል። ስለዚህ አብና ወልድ የሚታይና የማይታይ ገጽታዎች ሳይሆኑ ሁለት ማንነቶችና እራሳቸውን “እኔ” ብለው መናገር የሚችሉ በሌሎች ቅዱሳን ሰዎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ” በመባል የተጠሩ ሁለት አካላት ናቸው።
አካል (person) ማለት በአማርኛውም ሆነ በኢንግሊዝኛ ሙዳየ ቃላት አያሌ ትርጉሞች ያሉት ሲሆን ከትርጉሞቹ መካከል ደግሞ እራሱን “እኔ” በማለት መግለጽ የሚችል፤ በሌሎችም ደግሞ “እርሱ” እየተባለ የሚጠራ ስሜት፣ ፈቃድ፣ እውቀት ያለው ማለት ነው። ለምሳሌ መላዕክት መናፍስት ስለሆኑ የሚታይና የሚዳሰስ አካል የላቸውም፤ ነገር ግን ስሜት፣ ፈቃድ፣ እውቀት ያላቸው ስለሆኑ አካል እንላቸዋለን፤ ስለዚህ አካል የምንልበትን አግባብ መረዳት አስፈላጊ ነው። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ዕድሜ ጠገብ በሆነው ዕውቅ የመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው የአካልን ምንነት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦
“አካል በቁሙ ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ያለው፤ ራሱን የቻለ ለራሱ የበቃ፤ እኔ የሚል ህላዌ ነባቢ፤ ቁመት ቁመና፤ የባሕርይ የግብር የስም ባለቤት፤ እገሌ የሚባል…. ከራስ ጠጉር እስከ እግር ጥፍር ባጥንት በዥማት በሥጋ በቁርበት፣ ተያይዞና ተሸፍኖ ያለው በአንድነት አካል ይባላል። አካለ ጎዶሎ እንዲሉ። እኔ ማለትም የሚገባ ዕውቀት ቀዋሚነት ላላቸው ለማይሞቱና ለማይጠፉ ለሦስት ብቻ ነው፤ ለአምላክ፣ ለመለአክ፣ ለነፍስ . . . አካል መባሉም በነፍስ ዕውቀትና በነፍስ አካልነት ነው፤ እንጂ በራሱ በገንዘቡ አይደለም፤ በገንዘቡስ የነፍስ መሣሪያ እንደ መኾኑ ሥጋ ገላ ይባላል… (ግጥም) ከዚህ ቤት ያለች ሸክላ ሠሪ፤ ድኻ ናት አሉ ጦም ዐዳሪ፤ ምን አስተማራት ጥበቡን፤ ገል ዐፈር መኾኑን (ገላ)። መሣሪያነቱም በዚህ ይታወቃል፤ ርሷ ስትለቀው በመውደቁ እንዲሉ።” (መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤ 1948 ዓ.ም፤ አ.አ፤ ገጽ 218)።
ስለዚህ አካል የሚለው ቃል ግዘፍ አካልን ከማሳየት ባለፈ እኔነትን የሚያሳይ ነው። በሥላሴ ትምህርት ውስጥ ሦስት አካላት ስንል ሦስት እጅ እግር ያላቸው የተቀመጡ ወይም የቆሙ ነገሮች አድርገን መረዳት አይገባንም። አካል ስንል አብ የራሱ ማንነት አለው፤ በዚህ ማንነቱ አብ ራሱ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ እንዲሁ ወልድ የራሱ አካል አለው ስንል ከአብ እና ከመንፈስ ቅዱስ ልዩ (Distinict) የሆነበት “እርሱ” የሚባልበትን ማንነት (ስሜት፣ ፈቃድ፣ እውቀት) ገንዘቡ አድርጓል ማለታችን ነው። ስለ መንፈስ ቅዱስም በተመሳሳይ ሁኔታ ልንገነዘብ ይገባል።
ስለዚህ በቅዱሳት መጽሐፍትም ሆነ ስነ ቋንቋዊ በሆኑ ቀመሮች አብና ወልድ ቄስ ተክለማርያም ገዛኸኝና ሌሎች ሐሰተኛ መምህራን እንደሚናገሩት አንድ አካላት ሆነው ውጪአዊና ውስጣዊ ገጽታዎች ሳይሆኑ ሁለት አካላት እንደሆኑ እንረዳለን። የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያስተምረው የእነዚህ ሐሳውያን ትምህርት በቅዱሳት መጻሕፍት ድጋፍ የሌለውና ህሊናው በትክክል ለሚሠራ አሳቢ ሰው ትርጉም የማይሰጥ ዘመን አመጣሽና ሰው ሠራሽ ትምህርት መሆኑን ተገንዝበን ልንርቀውና ልናወግዘው ይገባል።