ኢየሱስ ክርስቶስ – የዓለማት ፈጣሪ

ኢየሱስ ክርስቶስ – የዓለማት ፈጣሪ

ለሙስሊም ሰባኪ ስሁት ሙግት ምላሽ


የክርስትና ተቃዋሚዎችና የሐሰት መምህራን ከሚታወቁባቸው ተግባራት መካከል አንዱ የቅዱሳት መጻሕፍትን ጥቅሶች በመቆራረጥ ከአውድ ማፋታት ነው።  ይህ ተግባር ሁሉንም የሐሰት መምህራን የሚያመሳስላቸው ሲሆን የቃላትንና የዓረፍተ ነገሮችን ትርጉም ከተጻፉበት አውድ ብሎም ከአጠቃላይ የቅዱሳት መጻሕፍት ሐሳብ ገንጥሎ በማውጣት አዲስና እንግዳ የሆነ ትምህርት ይፈጥራሉ። የዘመናችን ሙስሊም ሰባኪያን እንዲህ ያለ ተግባር በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ሲፈጽሙ ማየት የተለመደ ነው። እነኚህ ወገኖች በተሳሳተ ትርጓሜ ላይ የተመሠረተ ተቃውሞ እያቀረቡ መሆናቸውን ለመረዳት የጥቅሶችን ዙርያ ገባ ማንበብ ጥሩ መፍትሄ ነው። በዚህ ጽሑፍ የቅዱሳት መጻሕፍትን ጥቅሶች በመከታተፍ በክርስትና ላይ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የሚታወቅን የአንድ ሙስሊም ሰባኪ ሙግት እንፈትሻለን።

አብዱል እንዲህ ሲል ይጀምራል፦

ዘመናትን ባደረገበት

የዘመናችን የባይብል ምሁራን፦ “የዕብራውያን ደብዳቤ ተናጋሪ እና ጸሐፊ ማን እንደሆነ ዐይታወቅም” በማለት ይናገራሉ፥ አንዳንዶች፦ “የዕብራውያን ደብዳቤ ተናጋሪ እና ጸሐፊ ጻውሎስ ነው” ሲሉ፣ ጥቂቶች ደግሞ “አቂላ እና ጵርስቅላ ናቸው” ሲሉ፣ አንዳንድ፦ “አጵሎስ ነው” የሚል መላምት ሰንዝረዋል። ሆነም ቀረ የዕብራውያን ደብዳቤ የነቢይ ወይም የፈጣሪ ንግግር ሳይሆን አንድ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ለዕብራውያን ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ ነው፥

መልስ፦

የዕብራውያን ጸሐፊ ማንነት አወዛጋቢነቱ የታወቀ ቢሆንም በመጀመርያይቱ ቤተክርስቲያን ውስጥ አገልጋይ በነበረና ጢሞቴዎስን የመሳሰሉ የታወቁ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የቅርብ ወዳጅ በነበረ ሰው የተጻፈ መሆኑን የሚክድ የለም (ዕብ. 13፡23)። እስከ ዘመነ ተሓድሶ ድረስ ለ1500 ዓመታት ያሕል ጸሐፊው ጳውሎስ እንደሆነ ቤተክርስቲያን ተቀብላ የኖረች ቢሆንም (ጠርጡልያኖስ የበርናባስ ጽሑፍ ሊሆን እንደሚችል ሐሳብ መስጠቱን ሳንዘነጋ) የግሪክ ቋንቋ አጠቃቀሙን በማጥናት ከጳውሎስ ጽሑፎች ጋር አለመመሳሰሉ ብዙዎች የጳውሎስ ጽሑፍ እንዳልሆነ እንዲገምቱ አድርጓቸዋል። ነገር ግን የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ (150 – 215 ዓ.ም) እና ኦሪጎን (185 – 253 ዓ.ም) እንደተናገሩት ሐዋርያው ጳውሎስ ጽሑፉን በእብራይስጥ ያዘጋጀ ሲሆን ቅዱስ ሉቃስ ወደ ግሪክ ተርጉሞታል። እውነታው ይህ ከሆነ ደግሞ አጻጻፉ ለየት ለማለቱ ጥሩ ምክንያት አለ ማለት ነው። የሆነው ሆኖ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊያን ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው መካከል የመጀመርያይቱ ቤተክርስቲያን አካል ያልሆነና የሐዋርያት ወዳጅ ያልነበረ ሰው የለም። በምሑራን የተሰጡት ግምቶች ሁሉ ጽሑፉን በሐዋርያዊ ሥልጣን ስር የሚያስቀምጡ ናቸው። ጸሐፊው ሐዋርያው ጳውሎስ መሆኑን ለማመን ጥሩ ምክንያቶች ቢኖሩም የቀደመችዋ ቤተክርስቲያን አባል ያልሆነና ሐዋርያት የማያውቁት አንድም ሰው በእጩነት አልቀረበም። ስለዚህ ከተባሉት ቅዱሳን ሰዎች መካከል ማንም ቢጽፈው በሥልጣናዊነቱ ላይ አንዳች ለውጥ አያመጣም። ዋናው ቁምነገር የጸሐፊው ማንነት ሳይሆን የመልእክቱ ባለቤት ማንነት ነው። እርሱ ደግሞ በሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲሠራ የነበረው ጌታ መንፈስ ቅዱስ ነው።

ሌላው ይህ አብዱል ቅዱሳት መጻሕፍትን ያቃለለ መስሎት “መልእክት” ከሚለው ቃል ይልቅ “ደብዳቤ” የሚል ቃል ተጠቅሟል። ነገር ግን የገዛ ቁርአኑ رِسالة “ሪሳላህ” ተብሎ መጠራቱን ያስተዋለ አይመስልም። “ሪሳላህ” የሚለው የአረብኛ ቃል “ኤፒስቶሌ” እንደሚለው የግሪክ ቃል ሁሉ “መልእክት፣ ደብዳቤ” የሚል ትርጉም ያለው ቃል ነው። ከዚህ አባባል በመነሳት ቁርአንም “ደብዳቤ” በሚል ቃል ሊጠራ ይችላል ማለት ነው። ቁርአን “አላህ” የተባለ ማንነቱ የማይታወቅ አካል “ጅብሪል” ለተባለ ማንነቱ ለማይታወቅ አካል የሰጠው፤ “ጅብሪል” ደግሞ ለሙሐመድ የነገረው፤ ሙሐመድ በተራው ለግል ጸሐፊያኑ የነገራቸው ደብዳቤ ነው ቢባል ትክክል ይሆናል። ለእያንዳንዱ ዘርፍ ሙያዊ ቃላት አሉ። እነዚህ ሙያዊ ቃላት በተግባቦት ውስጥ አስፈላጊ ናቸው። ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚጠቀሱበት የራሳቸው አጠራር አላቸው። ክርስቲያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች መደበኛ በሆነው ተግባቦት ውስጥ እነዚህን ቃላት ቢመርጡ የተሻለ ነው። ሙስሊሞች “ደብዳቤ” የሚለው ቃል ለቁርአን እንደማይመጥን እንደሚያስቡት ሁሉ ክርስቲያኖችም ይህ ቃል ለመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እንደሚመጥን አያስቡም፤ ስለዚህ ትክክለኞቹን ቃላት መምረጥ ለሁላችንም የተሻለ ነው።

አብዱል ይቀጥላል፦

ይህ ደብዳቤ መክፈቻው ላይ እንዲህ ይላል፦

ከጥንት ጀምሮ አምላክ በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ። Πολυμερῶς καὶ πολυτρόπως πάλαι ὁ Θεὸς λαλήσας τοῖς πατράσιν ἐν τοῖς προφήταις

ዕብራውያን 1፥1

እዚህ ጥቅስ ላይ “አምላክ” ለሚለው የገባው ቃል “ቴዎስ” Θεὸς ሲሆን ከጥንት ጀምሮ ይህ አንድ አምላክ ለእስራኤላውያን በነቢያቱ፦ “ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም” እያለ ከተናገረ በኃላ ዘመናትን ባደረገበት በልጁ በዘመኑ መጨረሻ ተናገረ፦

ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን ባደረገበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን። ἐπ’ ἐσχάτου τῶν ἡμερῶν τούτων ἐλάλησεν ἡμῖν ἐν Υἱῷ, ὃν ἔθηκεν κληρονόμον πάντων, δι’ οὗ καὶ ἐποίησεν τοὺς αἰῶνας·

ዕብራውያን 1፥2

ሁሉን ወራሽ” ማለት ኢየሱስ ያለውን “ነገር ሁሉ” ከራሱ ያገኘው ሳይሆን አምላክ በጸጋ እና በስጦታ የሰጠው ወይም ያወረሰው ነው፥ ለኢየሱስ የተሰጠው ነገር ሁሉ ለአማኞችም እንደሚሰጥ ጳውሎስ ተናግሯል፦

ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል።ሮሜ 8፥32 ከእርሱ ጋር ደግሞ “ሁሉን ነገር” እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?

ሉቃስ 10፥22

መከራ ብንቀበል “ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን”

ሮሜ 8፥17

ከእርሱ ጋር ደግሞ “ሁሉን ነገር”ይሰጠናል” ካለ ኢየሱስ የሚወርሰው “ሁሉ ነገር” አንጻራዊ ነው።

መልስ፦

ክርስቶስ ሁሉን ወራሽ የተባለበት ምክንያት ሁሉ ነገር በእርሱና ለእርሱ የተፈጠረ በመሆኑ ምክንያት ነው፦

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል” (ቆላስይስ 1፡15-16)።

ከላይ በሚገኘው ጥቅስ መሠረት ክርስቶስ ጌታችን ሁሉን የፈጠረ ጌታ ነው። ፍጥረት ሁሉ የተፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው። ሁሉ የተፈጠረው በእርሱ ከሆነ ወራሽነቱ የአብ አንድያ ልጅ በመሆኑ ምክንያት በዘመን ፍጻሜ የራሱ የሆነውን እንደሚጠቀልል የተነገረ እንጂ ውሱንነትን የሚያመለክት አይደለም። የአብ ሆኖ የልጁ የኢየሱስ ያልሆነ ምንም ነገር የለም፦

“እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ” (ዮሐንስ 16፡14-15)።

ለአብ ያለው ሁሉ የኢየሱስ ከሆነ ኢየሱስ የሚወርሰው የራሱ የሆነውን እንጂ የራሱ ያልሆነውን አይደለም ማለት ነው። “መውረስ” የሚለው ቃል ፍጥረታዊ ሰው ከወላጁ የሚወርሰው ዓይነት ሳይሆን ፍጥረትን ሁሉ ጠቅልሎ የማስገዛት ትርጉም ያለው አባባል ነው። የእኛ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ወራሾች መሆን ደግሞ በክርስቶስ በማመናችን ምክንያት ያገኘነው የልጅነት መብት እንጂ ወራሽነታችን ልክ እንደ ክርስቶስ ነው ወይም ከክርስቶስ ጋር የተካከልን ነን የሚል ትርጉም የለውም። ልጅነታችን የባሕርይ ልጅ በሆነው በክርስቶስ በኩል ያገኘነው እንደሆነ ሁሉ ወራሽነታችንም በእርሱ በኩል ያገኘነው እግዚአብሔር አብ ስለ ልጁ ክብርና ፍቅር ሲል የሰጠን መብት እንጂ የተገባን ሆኖ አይደለም። ክርስቶስ ግን የአባቱ የሆነው ሁሉ የእርሱ ስለሆነ ፍጥረትን ጠቅልሎ በመግዛት ትርጓሜ ወራሽነት ተነግሮለታል። አማኞች በክርስቶስ በማመናቸውና በመከራ ውስጥ ለክርስቶስ በመታመናቸው ምክንያት ከክርስቶስ ጋር አብረው ይነግሣሉ (ራዕይ 5፡9-10፣ 20:6፣ 22:5)። ይህ ክርስቶስን በአማኞች ደረጃ ላይ አያስቀምጠውም ወይም አማኞችን ወደ ክርስቶስ ደረጃ ከፍ አያደርጋቸውም።

ይህ አብዱል ወራሽ  መኾን ኢየሱስን አምላክ እንዳይኾን ያደርገዋል የሚል ከሆነ በቁርኣን መሠረት አላህም ወራሽ በመኾኑ አምላክ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡-

“ከከተማም ኑሮዋን (ምቾቷን) የካደችን (ከተማ) ያጠፋናት ብዙ ናት፡፡ እነዚህም ከእነሱ በኋላ ጥቂት ጊዜ እንጅ ያልተኖረባቸው ሲኾኑ መኖሪያዎቻቸው ናቸው፡፡ እኛም (ከእነርሱ) ወራሾች ነበርን” (ሱራ 28፡58)፡፡

“ዘከሪያንም «ጌታዬ ሆይ! ብቻዬን አትተወኝ፡፡ አንተም ከወራሾች ኹሉ በላጭ ነህ ሲል» ጌታውን በተጣራ ጊዜ (አስታውስ)” (ሱራ 21፡89)፡፡ And [mention] Zechariah, when he called to his Lord, “My Lord, do not leave me alone [with no heir], while you are the best of inheritors.” (Sura 21:89)

“እኛ ምድርን በእርሷም ላይ ያለውን ኹሉ እኛ እንወርሳለን፡፡ ወደኛም ይመለሳሉ” (ሱራ 19፡40)፡፡

አብዱል ወራሽነት ከአምላክነት ደረጃ ዝቅ የሚያደርግ እንደሆነ የሚያምን ከሆነ አምላኩ እውነተኛ አምላክ ላይኾን ነው! ሙስሊም ሰባኪያን በክርስትና ላይ አንድ ተቃውሞ ሲያነሱ በገዛ ገመዳቸው እንዲህ እንደሚታነቁ አውቀው ቢጠነቀቁ ለእነርሱ የተሻለ ነው።

አብዱል ይቀጥላል፦

ኮስሞስ” κόσμος ማለት “ዓለም” ወይም “ጽንፈ ዓለም”universe” ማለት ነው፥ ይህም ኮስሞስ የሚለው ቃል ሥነ-ፍጥረትን”cosmology” ያሳያል፦

ዓለም” ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ”። ἐρεύξομαι κεκρυμμένα ἀπὸ καταβολῆς.

ማቴዎስ 13፥35

[አብዱል ግሪክ ማንበብ ስለማይችል κόσμου (ኮስሙ) የምትለዋን ወሳኝ ቃል ረስቷታል።]

እንዲህ ቢሆንስ፥ “ዓለም” ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር። ἐπεὶ ἔδει αὐτὸν πολλάκις παθεῖν ἀπὸ καταβολῆς κόσμου·

ዕብራውያን 9፥26

እነዚህ ጥቅስ ላይ “ዓለም” ለሚለው የገባው ቃል “ኮስሞስ” κόσμος ነው፥ ነገር ግን ዕብራውያን 1፥2 ላይ የገባው ቃል “ኮስሞስ” κόσμος ሳይሆን “አይኦን” αἰών ነው። “አይኦን” αἰών ማለት “ዘመን” ማለት ነው፥ ለምሳሌ፦ የብሉይ ዘመን ፍጻሜ ሲሆን “በዘመናት ፍጻሜ” ተብሎ ተቀምጧል፦

በዘመናት ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። νυνὶ δὲ ἅπαξ ἐπὶ συντελείᾳ τῶν αἰώνων εἰς ἀθέτησιν τῆς ἁμαρτίας διὰ τῆς θυσίας αὐτοῦ πεφανέρωται.

ዕብራውያን 9፥26

መልስ፦

αἰών የሚለው ቃል “አዮን” እንጂ “አይኦን” ተብሎ አይነበብም። አብዱል በእንግሊዝኛ የተከተበውን እየተመለከተ ቢጽፍም በቋንቋው ምንም ዓይነት ስልጠና እንደሌለው ግልጽ ነው። በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ቃላት የሚተረጎሙት በአውድ እንጂ በቁም አይደለም። የአብዱል ትልቁ ስህተት ቃላት በአውድ እንደሚፈቱ ባለማወቅ ሙግት ለመሥራት መሞከሩ ነው። ለምሳሌ “ዓለም” የሚለው የአማርኛ ቃል እንደየ አገባቡ ይህችን ፕላኔ፣ የሰው ልጆች የሚኖሩበትን ሥርዓት እንዲሁም በሌሎች ብዙ መንገዶች ሊተረጎም ይችላል። “ዘለዓለም” ሲባል ደግሞ ጊዜን አመልካች ሆኖ ይመጣል። “አዮን” የሚለው ቃል እደየ አውዱ የተለያየ ትርጉም እንዳለው ሁሉ “ኮስሞስ” የሚለው ቃል እንደየ አውዱ የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል። ለምሳሌ ያህል 1 የጴጥሮስ መልእክት 3፡3 ላይ “ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ” በሚለው ውስጥ የሴት ልጅ ጌጣ ጌጥን ለማመልከት የገባው “ሽልማት” የሚለው ቃል በግሪኩ “ኮስሞስ” የሚለው ነው። Oxford Dictionary ላይ እንደተገለጸው በእንግሊዝኛ “ኮስሞቲክስ” የሚለው ቃል ከዚሁ የተገኘ ነው። የአዲስ ኪዳን ግሪክ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጹት ይህ ቃል እንደየ አገባቡ ወደ ስምንት የሚሆኑ ትርጉሞች አሉት። ስለዚህ “ኮስሞስ” የሚለው ቃል አንድ ብቸኛ ትርጉም ያለው ይመስል “ዓለም” የሚለውን ትርጉም ብቻ በማሸከም “አዮን” የሚለው ቃል ደግሞ “ዓለም” የሚል ትርጉም የሌለው በማስመሰል ማቅረብ የጸሐፊውን አላዋቂነት የሚያሳይ ነው። ትክክለኛው አካሄድ ቃላትን በውሱን መልኩ ለመተርጎም የሚያስችል አውዳዊ ማስረጃ መኖር አለመኖሩን ማረጋግጥ እንጂ ከግል ድምዳሜ በመነሳት በውሱን ሁኔታ መተርጎም አይደለም። ቀጥሎ እንደምንመለከተው ዕብራውያን 1፡2 ላይ “አዮናስ” የሚለውን ቃል “ዓለማት” ብሎ ለመተርጎም የሚያስችል በቂ አውዳዊ ምክንያት አለ። አብዱል ይቀጥላል፦

ኢየሱስ ሲገለጥ ፍጻሜ ያገኘው ዘመን በሙሴ የተጀመረው የብሉይ ኪዳን ዘመን ነው፥ “በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ሲል የተፈጸመው ዘመን በሙሴ ተጀምሮ የነበረው ነው፦

የዘመናት መጨረሻ” የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። εἰς οὓς τὰ τέλη τῶν αἰώνων κατήντηκεν.

1 ቆሮንቶስ 10፥11

እዚህ አንቀጽ ላይ “ዘመን” ለሚለው የገባው ቃል “አይኦን” αἰών መሆኑን ልብ አድርግ! በተጨማሪ፦

1 ጴጥሮስ 1፥21 ላይ “በዘመኑ መጨረሻ”

ማርቆስ 1፥15 ላይ “ዘመኑ ተፈጸመ”

ገላትያ 4፥4 ላይ “የዘመኑ ፍጻሜ”

የሚሉትን ተመልከት!አምላክ አዲሱ የአዲስ ኪዳን ዘመን ያደረገው በኢየሱስ ነው፥ “ባደረገበት” የሚለው የግሪኩ ቃል “ኤፖኤሴን” ἐποίησεν ሲሆን ኢየሱስ አሥራ ሁለቱን ተከታዮቹን “ሐዋርያ” ለማድረጉ ጥቅም ላይ ውሏል፦

አሥራ ሁለት “አደረገ”። καὶ ἐποίησεν δώδεκα,

ማርቆስ 3፥15

እዚህ አንቀጽ ላይ “አደረገ” ለሚለው የገባው ቃል በተመሳሳይ “ኤፖኤሴን” ἐποίησεν ነው፥ ስለዚህ ብዙ የባይብል ቨርዥኖች፦ “ዘመናትን ባደረገበት”through whom He made the Ages” ብለው አስቀምጠውታል። ዋቢ ቨርዥኖች ተመልከት፦

    • Berean Literal Bible,
    • Literal Standard Version,
    • New Heart English Bible,
    • Weymouth New Testament,
    • Young’s Literal Translation

አምላክ በክርስቶስ ያደረገው አዲሱ ዘመን የመታደስ ዘመን ነው፥ “ነገር ሁሉ የሚታደስበት ዘመን” “የመታደስ ዘመን” የሚሉ ቃላት ይህንን ጉልኅ ማሳያ ነው፦

ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት ዘመን” ድረስ ሰማይ ይቀበለው ዘንድ ይገባልና።

የሐዋርያት ሥራ 3፥21

እነዚህም “እስከ መታደስ ዘመን” ድረስ የተደረጉ።

ዕብራውያን 9፥10

መልስ፦

አብዱል ሁለት ነገሮችን እያደባለቀ ነው። የዕብራውያን ጸሐፊ ስለ ዘመነ መግቦት (dispensation) ለመግለጽ “በዚህ ዘመን መጨረሻ”  በማለት የተናገረውንና ፍጥረተ ዓለምን ለማመልከት “ዓለማትን በፈጠረበት” በማለት የተናገረውን አንድ በማስመሰል እያቀረበ ነው። በሁለቱም ሁኔታዎች ጊዜን ለማመልከት ቢፈልግ ኖሮ የመልእክቱ ጸሐፊ ተመሳሳይ ቃል በተጠቀመ ነበር። ነገር ግን የዘመን መጨረሻ ለማለት “ኤስካቱ ቶን ሄሜሮን” ያለ ሲሆን “ዓለማትን በፈጠረበት” ሲል ደግሞ “ዲ ሁ ኤፖዬሴን ቶውስ አዮናስ” በማለት ነው። ቀደም ሲል እንደገለጽነው “አዮን” የሚለው ቃል እንደየ አገባቡ የተለያዩ ትርጉሞች ያሉት ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደተገለጸው ጊዜና በጊዜ ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታትን በሙሉ አንድ ላይ ለመግለጽ ጥቅም ላይ ይውላል። የዕብራውያን ጸሐፊ በዚሁ መጽሐፍ ምዕራፍ 11፡3 ላይ “ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን” ብሎ ሲል ፍጥረተ ዓለሙን ለመግለጽ የተጠቀመበት ቃል “አዮናስ” የሚል ተመሳሳይ ቃል ነው።

ከላይ እንደሚነበበው አብዱል ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ዘመናትን ባደረገበት” እንደሚሉ ከተናገረ በኋላ መጥቀስ የቻለው አምስቱን ብቻ ነው። ነገር ግን ካሉት ወደ ሃምሳ የሚጠጉ የእንግሊዝኛ ትርጉሞች መካከል ጊዜን በሚያመለክት ሁኔታ የተረጎሙት ሩብ እንኳ አይሞሉም። ከነዚህ መካከል አብዛኞቹ ክርስቶስ የጊዜ ፈጣሪ መሆኑን በሚያመለክት ሁኔታ ተርጉመዋል። ይህንን ትርጓሜ የተጠቀሙት ደግሞ የቃል በቃል (Literal) ትርጓሜን የሚጠቀሙ ትርጉሞች እንጂ አውድን ያገናዘበ ትርጉምን የሚከተሉቱ አይደሉም። ዋና ዋና የሚባሉት ትርጉሞች በሙሉ አንድ ዓይነት ትርጓሜን የተከተሉ ሆነው ሳሉ ጥቂት የቃል በቃል ትርጓሜን የተከተሉ ትርጉሞችን መርጦ መሞገት የተሟጋቹን አቋም ደካማ ያደርገዋል። “ኤፖዬሴን” የሚለው “በፈጠረበት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል እንደ ማንኛውም ቃል የተለያዩ ትርጉሞች ያሉት ሲሆን በአውድ ይወሰናል። ከአውዳዊ ፍቺዎቹ መካከል አንዱ “ፈጣሪነትን” የሚያሳይ ሲሆን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በዚሁ መንገድ ተተርጉመዋል። ለምሳሌ ያህል ማቴዎስ 19፡4፣ ማርቆስ 10፡6፣ ሉቃስ 11፡40፣ የሐዋርያት ሥራ 4፡24፣ 7፡50፣ 17፡24፣ ራእይ 14፡7 የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት ለማመልከት ይኸው ቃል ጥቅም ላይ ውሏል። የዕብራውያንን መጽሐፍ ስናነብ ይህንኑ ቃል በተለያዩ መንገዶች የሚጠቀም ሲሆን እዚሁ ምዕራፍ 1:7 ላይ የመላእክትን አፈጣጠር ለማሳየት ጥቅም ላይ ውሏል። ምዕራፍ 12:27 ላይ ደግሞ “የተፈጠሩ” ተብሎ ተተርጉሟል። በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደተመለከተው ከቃሉ ትርጉሞች መካከል አንዱ መፍጠር የሚል ነው። ጥያቄያችን መሆን ያለበት አውዳዊ ፍቺው ፈጣሪነትን በሚያመለክት መንገድ እንዲተረጎም ይፈቅዳል ወይስ አይፈቅድም? የሚል ነው። ይህንን ጽሑፍ የጻፈው አብዱል ልፋ ቢለው እንጂ የዕብራውያን ጸሐፊ እዚሁ ምዕራፍ 1:10-12 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ፈጣሪ እንደሆነ ሊታበል በማይችል ሁኔታ ይናገራል፦ “ደግሞ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማዮችም የእጆችህ ሥራ ናቸው፤ እነርሱም ይጠፋሉ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጎናጸፊያም ትጠቀልላቸዋለህ ይለወጡማል፤ አንተ ግን አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል።” ፍጥረት የእግዚአብሔር አብ የእጅ ሥራ እንደሆነ ሁሉ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስም የእጅ ሥራ ነው። የዕብራውያን አንድ ዋና ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስ የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ በመሆኑ ምክንያት ከመላእክት የላቀ መሆኑን ማሳየት ሆኖ ሳለ በአውዱ መሠረት ሊተረጎም የሚገባውን አንድ ሐረግ ይዞ መሟሟት ሞጋቹ የምዕራፉን ሐሳብ እንዳልተረዳ የሚያሳይ ከንቱ ልፋት ነው።

በማስከተል አብዱል ሌላ መናኛ ሙግት ያቀርባል፦

ዓለማትን በፈጠረበት” ቢባል እንኳን ችግር የለውም፥ ምክንያቱም “ዓለም” የሚለው ቃል “ዘመን” የሚለውን ለማመልከት በዕብራውያን 9፥26 ላይ ስለገባ እና “መፈጠር” የሚለው ቃል “መታደስ” የሚለውን ለማመልከት ስለሚገባ ነው፦

አቤቱ ንጹሕ ልብን “ፍጠርልኝ”የቀናውንም መንፈስ በውስጤ “አድስ”

መዝሙር 51፥10

ፍጠርልኝ” ሲል “አድስልኝ” ለማለት እንደሆነ ከተረዳን ዘንዳ “በፈጠረበት” ሲል “ባደሰበት” በማለት መረዳት ይቻላል፥ ስለዚህ ዕብራውያን 1፥2 ስለ ዘፍጥረት ፍጥረት በፍጹም አይናገርም። “

መልስ፦

መዝሙር 51:10 በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም 50:12 ላይ የሚገኝ ሲሆን καρδίαν καθαρὰν κτίσον ἐν ἐμοί (ካርዲያን ካተራን ክቲሶን ኤን ኤሞይ) በማለት ነው የሚነበበው። በግልጽ እንደሚታየው በዚህ ቦታ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ክቲሶን” የሚል ነው። መዝሙረኛው እየጸለየ ያለው የቀደመው የኃጢአት አስተሳሰቡ ተለውጦ አዲስ አስተሳሰብ እንዲፈጠርለት ነው። አብዱል የማይመሳሰሉ ክፍሎችን አንድ ላይ እየሰፋ ነው። ስለ ፍጥረተ ዓለም የሚናገረውን የአዲስ ኪዳን ጥቅስ ስለ ውስጥ አስተሳሰብ በሚናገር ሌላ የብሉይ ኪዳን ጥቅስ ለመፍታት መሞከሩ ስለ ስነ አፈታት (Hermeneutics) ምንም ነገር እንደማያውቅ ያሳያል። በማስከተል እንዲህ ይለናል፦

አይኦን” αἰών የሚለውን “ዓለም” በሚል ቢመጣ እንኳን “ዓለም” የሚለው ቃል የብሉይን ሕግ ለማመልከት መጥቷል፦

ነገር ግን “ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት”ማቴዎስ 22፥40 በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም “ተሰቅለዋል”

ገላትያ 6፥14

ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት” ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥

ቆላስይስ 2፥20

ዓለም” ተሰቀለ ሲባል “ጽንፈ ዓለም” ተሰቀለ ማለት ሳይሆን የመጀመሪያውን ትምህርት ሕግ እና ነቢያት አክትመው ሁለተኛው ኪዳን “በ”-ክርስቶስ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፦

አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል።

ዕብራውያን 8፥13

ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር።

ዕብራውያን 8፥7

ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል።

ዕብራውያን 10፥9

መልስ፦

ሲጀመር ገላቲያ ላይ “ዓለም” ለሚለው ቃል ጥቅም ላይ የዋለው ቃል “ኮስሞስ” የሚል እንጂ “አዮን” የሚል አይደለም፤ የሆነው ሆኖ በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እነዚህ ቃላት የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ለማሳየት ጥቅም ላይ አልዋሉም። ሙስሊሙ ሰባኪ የግል ፈጠራውን እያወራ ነው። ሁለተኛ ሐዋርያው እየተናገረ ያለው ስለ ዓለማዊ አስተሳሰብ እንጂ ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግጋት አይደለም። የብሉይ ኪዳን ሕግጋት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጡ ሰማያዊ ሕግጋት እንጂ ዓለማዊ አይደሉም፤ በዚህ ቃልም አይገለጹም። ይህንን ጥቅስ በዚህ መንገድ የተረዳ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ የለም። በሦስተኛ ደረጃ ማቴዎስ 22:40 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል” ብሎ ሲል ፈጣሪን መውደድና ባልንጀራን መውደድ የሚሉት ትዕዛዛት የሁሉም ትዕዛዛት ማጠቃለያዎች ናቸው ለማለት እንጂ ገላትያ 6:14 ላይ አማኞች ከዓለማዊ አስተሳሰብ መለየታቸውን ለማሳየት ሐዋርያው እንደተናገረው ዓይነት “መሰቀል” አይደለም። በሁለቱም ላይ መሰቀል የሚል ቃል ጥቅም ላይ ስለዋለ ብቻ የሁለቱን ትርጉን አንድ ማድረግ ሙስሊሙ ሰባኪ የቃላትን አውዳዊ አጠቃቀም ፈጽሞ እንደማያውቅ ማሳያ ነው። የተጻፈውን በትክክል አንብቦ የመረዳት አቅም እንኳ የሌለው እንዲህ ያለ ሰው ደግሞ ቃሉን የመተርጎም ምንም ዓይነት ብቃት እንደሌለው ግልፅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መንገድ መተርጎም በቃሉ ላይ ወንጀል መፈጸም ነው። አብዱል አላዋቂነቱን ይበልጥ ግልጽ እያደረገ ነው።

ከዚህ በማስከተል አብዱል በሌሎች ጽሑፎቻችን ምላሽ የሰጠንባቸውን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ ተልኮ ስለመምጣቱ የሚናገሩ ከርዕሱ ጋር የማይገናኙ ጥቅሶችን እየደረደረ መያዣ መጨበጫ የሌላውን አሰልቺ ዲስኩር ይደሰኩራል። ምላሻችንን ስናጠቃልል የዕብራውያን የመጀመርያው ምዕራፍ ሙሉ ሐሳብ የክርስቶስን አምላክነትና ፈጣሪነት ማሳየት በሆነበት ሁኔታ አንድ ሰው ቁጥር ሁለት ላይ የተጻፈውን ሐሳብ ለማስተባበል መሞከሩ ትርጉም አልባ ከንቱ ልፋት ከመሆን በዘለለ ፋይዳ የለውም። የኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪነት በአንድ ጥቅስ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ በስፋት የተነገረ ሐሳብ ነው፦

“በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። … ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” (ዮሐንስ 1:1-3፣ 9-11)።

“እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል” (ቆላስይስ 1:15-17)።

“ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን” (1ቆሮንቶስ 8:6)።

ክብር ሁሉ የፍጥረት ጌታና ፈጣሪ ለሆነው ለአብ ልጅ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን! አሜን!


መሲሁ ኢየሱስ