ኢየሱስ አብ ነውን?
ወንድም ዳዊት
ክፍል ፩
ክርስትና በዘመናት ያሳለፋቸው ውጣ ውረዶች የአረማውያን ነገሥታት ማሳደድና የጣዖት አምላኪያን መብዛት ብቻ ሳይሆን በዘመናት የተነሱ የኑፋቄ ቡድኖችም ይጠቀሳሉ። ይህኛው ተግዳሮት ከጣዖት ይበልጥ የከፋ፣ ከሚያሳድድ ጠላት ይልቅ እጅግ ጨካኝ ሰንኮፍ ነው። ከእነዚህ የሐሰት ትምህርቶች አንዱ በጥንቷ ቤተክርስቲያን ሰባልዮሳዊነት፣ በዘመናችን ደግሞ በኢትዮጵያ አጠራሩ “የሐዋርያት” ቤተክርስቲያን፣ በዓለም አቀፍ ስሙ Oneness Pentecostalism፣ በተለምዶ Only Jesus በመባል የሚታወቀው ነው። ክርስቲያኖች የሥላሴ አስተምህሮ ታሪካዊነቱ የተመሠከረ፣ ቀጥተኛዋ ሃይማኖት የምታስተምረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት እንደሆነ ቢናገሩም በዘመናችን ያሉ ሰባሊዮሳውያን ይህንን ትምህርት ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም። እነኚህ ወገኖች የቃላትን ትርጉም ከትክክለኛ ትርጓሜና አውዳቸው በመጎንተል (በማስወጣት) መተርጎማቸው ለዚህ ትልቅ ችግር ዳርጓቸዋል። በብዙ ዘርፎች ለክርስትናው ዓለም ትልቅ ጠላት የሆነውና የኑፋቄ ቡድኖች ሁሉ የሚጠቀሙት የተሳሳተ አካሄድ ጥቅሶችን በመቁረጥ የሚከናወን አውድን ያልጠበቀ ሥነ-አፈታት ነው። ከዚህ ጽሑፍ በጀመር በተከታታይ ክፍሎች እነዚህ ወገኖቻችን ሥላሴን በመቃወም ኢየሱስ አብ ነው ብለው ለሚያነሷቸው ጥቅሶች መልስ እንሰጣለን።
“እኔና አብ አንድ ነን”
(ዮሐ 10:30)
“እኔና አብ አንድ ነን” የሚለው የኢየሱስ ንግግር “አንድ አካል ወይም ማንነት ነን” እያለ ነው በማለት በስፋት በእነዚህ ወገኖች ይጠቀሳል። በግልጽ እንደሚነበበው ኢየሱስ በዚህ ቦታ “እኔና አብ አንድ ነን” አለ እንጂ “እኔ አብ ነኝ” አላለም። ስለዚህ ከዚህ ጥቅስ በመነሳት ኢየሱስ አብ ነው ማለት አይቻልም። እስኪ በዝርዝር እንመልከት፦
ዮሐ10፥30 ላይ የሚገኘውን ክፍል ብቻውን ቆርጦ ማንበብ ሙሉ ትርጉም አይሰጥም፤ ኢየሱስ በዚህ ክፍል መልስ እየሰጠ ያለው አንተ ክርስቶስ ነህ ወይ? ለሚለው የአይሁድ ጥያቄ ነው። መልሱን ሲጀምር፦ “እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል” በማለት ነበር። ኢየሱስ አብ ነው ከተባለው እነዚህ ወገኖች ኢየሱስ አብ ነው ለማለት ከሚጠቅሱ ጥቅስ ከፍሎ ብሎ በተቀመጠው መሠረት በአብ ስም እንደሚሠራ መናገሩ ምን ትርጉም ይሰጣል? ኢየሱስ በምድር ላይ ሲመላለስ የሠራውን ሁሉ የሠራው በአብ ስም ከሆነ እንዴት እርሱ አብ ነው እንለዋለን? አብስ እንዴት የራሱ ልጅ ይሆናል? እንዴትስ አብ ስራውን በአባቴ ስም ሠራሁት ይላል? በመቀጠል እዚያው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ስለ በጎቹ ማንነት ከተናገረ በኋላ እንዲህ ይላል፦
“የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።”
(የዮሐንስ ወንጌል 10፥29)
እነዚህ ወገኖች ይህንን እውነታ ማሰብ ባይፈልጉም እዚህ ጋር ኢየሱስ የበጎቹ ተቀባይ አብ ደግሞ በጎቹን ለኢየሱስ ሰጪ ሆነው በቃሉ ላይ ተገልጠዋል። በመስጠትና በመቀበል መካከል ቢያንስ ሦስት አካላት መኖራቸው ግድ ነው፤ ሰጪ፣ ተቀባይና ሁለቱ የሚቀባበሉት ሌላ ሦስተኛ አካል። በቁጥር 29 ላይ ይህ ሃቅ ሊታበል በማይችል ሁኔታ ተቀምጧል። ሰጪው አብና ተቀባዩ ኢየሱስ የተለያዩ ሁለት አካላት ናቸው። እንዲህ ካልሆነ ግን አብ በጎቹን ለራሱ ሰጠ ልንል ነውን?
እንግዲህ ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው ኢየሱስ ለጥያቄያቸው መደምደሚያ መልስ የሆነውን “እኔና አብ አንድ ነን” የሚለውን ንግግር የተናገረው። ቃሉን በአንክሮ ስንመለከት ጌታ ኢየሱስ አብንና እርሱን “አንድ ነን” በሚል የብዙ ቁጥር መቋጫ መግለጡን እንመለከታለን። ይህንን አዲስ ኪዳን በተጻፈበት በጽርዑም ሆነ በየትኛውም ቋንቋ ብንመለከት ተመመሳሳይ ውጤት እናገኛለን። ለምሳሌ፦
“I and my Father ARE one.”
ἐγὼ καὶ ὁ πατὴρ ἕν ἐσμεν.
ኤጎ ካይ ሆ ፓቴር ሄን ኤስሜን
ከላይ ካሉት ሁለቱ ቋንቋዎች እንደምንመለከተው ኢየሱስ ራሱንና አብን ያስቀመጠው ከአንድ በላይ አካል በሚገለጽበት የብዙ ቁጥር መግለጫ ነው። ይህ ደሞ የጽርዑ ἐσμέν (ኤስሜን) የሚለው ቃል εἰμί (ኤይሚ) ለሚለው የነጠላ ቁጥር ገላጭ አበዢ ሆኖ የሚያገለግል አንደኛ መደብ ብዙ ቁጥር አመልካች (first person plural indicative) ነው። ስለዚህ አብና ወልድ አንድ መሆናቸውን በሌላ አባባል We are one ማለቱን እንረዳለን እንጂ አብ ወልድ ነው እንድንል የሚያንደረድር እሳቤ አያሲዘንም።
ስለዚህ በዚህ በዮሐንስ 10፥30 ላይ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው፦ በጎቹን ከእርሱም ሆነ ከአብ እጅ ማንም መንጠቅ እንደ ማይችል እርሱና አብ አንድ እንደሆኑ በማሳወቅ በባሕርይ እኩል መሆናቸውን ግልፅ አድርጓል (ዮሐ. 10፡30)፡፡ ይህ አንድነት የኃይል አንድነትን የሚገልፅ ነው፡፡ አብና ኢየሱስ በኃይል አንድ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ማንም በጎቹን ከአብ እጅ መንጠቅ እንደማይችል ሁሉ ከኢየሱስም እጅ መንጠቅ የማይችለው። ስለዚህ ይህ ክፍል እግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ የሆነው ኢየሱስ በአካል/ማንነት አንድ ወደ መሆንና ወደ ነጠላነት መቀየራቸውን አይናገርም። ከዚህ ይልቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ቁጥር ገላጭ ቃል በመጠቀም ከአብ ጋር ያለውን ልዩነት ግልጽ አድርጓል።
ይቀጥላል