ከሰማይ መጥቻለኹ! – የክርስቶስ ኢየሱስ ቅድመ ህላዌ በወንጌላት – ክፍል 1

ከሰማይ መጥቻለኹ!

የክርስቶስ ኢየሱስ ቅድመ ህላዌ በወንጌላት 

ክፍል አንድ 

ወንድም ሚናስ


አብዛኞቹ የነገረ መለኮት ምሁራን የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ቢያንስ በተወሰነ ደረጃም ቢኾን፣ ስለ ክርስቶስ ቅድመ ህልውና[1] እንደሚያናገሩ ያምናሉ፤ ለምሳሌ የክርስትናን ነገረ መለኮት በመተቸት  እና በብዙ መጻሕፍቶቻቸው ተነባቢነትን ያተረፉት ባርት ሄርማን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በፊል.2፥5-11 እና በሌሎች መልእክታቱ ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት በመለኮትነት ይኖር እንደ ነበር ገልጾአል የሚል አቋም አላቸው[2] እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል “ኢየሱስ ቅድመ ህላዌ ያለው፥ ከእግዚአብሔር ጋር እኵል የኾነ አካል ተደርጎ ተገልጾአል” ብለውም ጽፈዋል [3]። ነገር ግን ሄርማን ልክ እንደ አብዛኞቹ ለዘብተኛ ሊቃውንት፥ የዐዲስ ኪዳን ነገረ ክርስቶስ በጊዜ ኺደት እየዳበረ የመጣ ትምህርት መኾኑን ይናገራሉ፤ ከዚህም አንጻርም የመጀመሪያ ዘመን ክርስቲያኖች የክርስቶስን ቅድመ ህላዌ ይቀበላሉ የሚል እምነት የላቸውም፤ በሄርማን ገለጻ መሠረትም በምስስለ ወንጌላት[4] የምናገኘው ክርስቶስ በጳውሎስ መልእክታት ላይ ዳብሮ እና ጐልብቶ ተገልጾአል ይላሉ፤ ይኹን እንጂ ይህ ዕሳቤ ቢያንስ ኹለት መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉበት በርካታ ሊቃውንት ይናገራሉ።

አንደኛ:- የጳውሎስ መልእክታት ከምስስለ ወንጌላት በፊት የተጻፉ  ቀዳማይ የዐዲስ ኪዳን ድርሳናት ናቸው[5]፤ ይህም ማለት ምስስለ ወንጌላት የተዘጋጁት የክርስቶስ ቅድመ ህላዌ የተገለጸባቸው (የጳውሎስ መልእክታት) መዛግብት በመላው አገረ ሮም ከተነበቡ እና ከታወቁ በኋላ ማለት ነው፤ ይህንን እውነት ባርት ሄርማን እንኳን እንዲህ ሲሉ ያረጋግጣሉ “የተወሰኑ ክርስቲያኖች ጳውሎስ በ50 ዓ.ም ገደማ መልእክታቱን ከመጻፉ በፊትም ኢየሱስ ቅድመ ህላዌ እንዳለው ያምኑ ነበር”[6]። ከዚህ የተነሣም ምስስለ ወንጌላት ገና ሳይጻፉ የጳውሎስ መልእክታት የክርስቶስን ቅድመ ህልውና የሚያወሱ ምንባባት መሸከፋቸው እንቆቅልሽ እንደኾነባቸውም ራሳቸው (ባርት ሄርማን) ተናግረዋል[7]። 

ኹለተኛ:- ሉቃስ የጳውሎስ የቅርብ አርድእትና የጒዞ ጓድ ከመኾኑ አንጻር[8]፥ ቢያንስ የሉቃስ ወንጌል ከጳውሎስ የተለየ የነገረ ክርስቶስ ትምህርት አለው የሚለው ዕሳቤ ቅቡልነት ያለው አይመስለንም፤ በሉቃስ የሚገኘው  ነገረ ክርስቶስ ምናልባት ከጳውሎስ መልእክታት በተለየ ዐውድ የተገለጸ ሊኾን ቢችልም፣ ከጳውሎስ ዕይታ  ግን ተጻራሪነት አለው ማለት አዳጋች ይመስለናል። በተጨማሪም በምስስለ ወንጌላት፣ የክርስቶስ ቅድመ ህላዌ ባይገኝ እንኳ፣ እስካልተቃረ ድረስ ሊያስገርመን አይገባም:- የኢየሱስን ቅድመ ህላዌውን ባይጠቅሱ እንኳን፥ መለኮትነቱን በሌላ አግባብ ሊገልጹበት የሚችሉበት መንገድ ሰፊ ነውና። ይኹን እንጂ ምስስለ ወንጌላት የክርስቶስን ቅድመ ህላዌ በበቂ ኹኔታ አስተምረዋል ብለን እናምናለን፤ በዚህ መጣጥፍም ይህንን የሚያመለክቱ ጥቂት ምንባባት ላይ ብቻ እናተኵራለን።

በመጀመሪያ የምንመለከተው፥ ጌታ ኢየሱስ ምድራዊ ተልእኮን ለመፈጸም መምጣቱን በተደጋጋሚ በገለጸባቸው ምንባባት ላይ ነው። ይህ ሙግት ግን “መጣ” የሚለው ገለጻ ዅሉ ቅድመ ህልውናን ያጸናል በሚል ላይ የተመሠረተ አይደለም። ምስስለ ወንጌላት በተደጋጋሚ መጥምቁ ዮሐንስን “መጣ” በሚል ግስ ገልጸውታል (ማቴ. 11፥18፤ 21፥32፤ ማር. 9፥12–13፤ ሉቃስ 7፥3)፤ ይህ ማለት ግን መጥምቁ ዮሐንስ ቅድመ ህልውና አለው ማለት አይደለም። ይልቁንም ኢየሱስ መምጣቱን የተናገረባቸው ክፍሎች ዐላማን ለመፈጸም፣ ዕቅድን ከግብ ከማድረስ ጋር የተያያዙ መኾናቸውን ዐቢይ በማድረግ ነው። ለምሳሌ ያኽል ክርስቶስ በአንድ ቦታ እንዲህ ብሎአል፦

“የሰው ልጅ የጠፋውን (τὸ ἀπολωλός) ሊፈልግና (ζητῆσαι) ሊያድን (σῶσαι) መጥቶአል” (ሉቃስ.19፥10)

ይህ ገለጻ ያህዌ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ከተናገረው በቀጥታ የተወሰደ ሲኾን፥ ትንቢቱ እንዲህ ይነበባል፦ 

የጠፋውንም (Τὸ ἀπολωλὸς)  እፈልጋለኹ ( ζητήσω)…ስለዚህ መንጋዬን አድናለኹ (σώσω) ”(ሕዝ.34፥16, 22)፤

በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ያህዌ ወደፊት የጠፉትን እንደሚፈልግና፣ በጐቹን እንደሚያድን የገለጸ ሲኾን፣ ኢየሱስ ደግሞ ይህንን  ለመፈጸም እንደ መጣ ይናገራል ፤  ይህ ደግሞ ክርስቶስ ከሰማይ የመጣ አካል እንደኾነ ያለ ጥርጥር ያመለክታል። በተጨማሪም በዚህ ምንባብ፣ ጌታችን “የሰው ልጅ” የሚል ቅጽል መጠቀሙን ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ የዚህ ቅጽል የብሉይ ኪዳን ምንጭ ትንቢተ ዳንኤል 7፥13–14 ሲኾን፣ ነብዩ ዳንኤል “የሰው ልጅ” የሚመስል “ከሰማይ” እንደ “መጣ”፣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም በመቅረብ ዘላለማዊ መንግሥትን እንደ ተቀበለ ይናገራል፤ ክርስቶስም ይህንን ፅንሰ ሐሳብ ታሳቢ በማድረግ፣ የጠፉትን በመታደግ በዘላለማዊ መንግሥቱ ሐሴት ያደርጉ ዘንድ ከሰማይ መምጣቱን እየተናገረ መኾኑ ክፍለ ምንባቡ አስረጅ ነው። በአንድ ስፍራም ጌታችን ኢየሱስ በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ የሚገኘውን ይህንን ምንባብ ባጣቀሰ መልኩ፦ “የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይኾን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአል” (ማቴ. 20፡28፤ ማር. 10፥45) በማለት ተናግሮአል፤  በዚህ የጌታችን ንግግር፣ በዳንኤል 7፥13-14 ላይ ያሉት ሦስቱ ግሳዊ ቃላት(verbal allusion) ማለትም “የሰው ልጅ” “መጣ” እና “ማገልገል” በኹለቱ የወንጌላት ክፍል ላይ መጠቀሱን ልብ ይሏል፤ ኢየሱስ በዳንኤል 7፥13-14 ላይ የሚገኘውን ምንባብ በሚያስታወስ መልኩ  “መጥቶአል” በማለት በሦስተኛ መደብ ስለ ራሱ በመናገር ፥ ከሰማይ እንደ መጣ እየገለጸ እንደኾነ ለመረዳት አዳጋች አይደለም። 

ሌላው በምስስለ ወንጌላት (በተለይ በማርቆስ እና ሉቃስ) ላይ የክርስቶስን ቅደመ ህላዌ አመልካች አመልካች የኾነው፣ ርኵሳን መናፍስት ኢየሱስን ገና ከርቁ እንደሚያውቁት፣ ዐይተውም እንደሚፈሩት በተደጋጋሚ መገለጹን ዐቢይ በማድረግ ነው፤ በአንድ የወንጌል ክፍልም አንድ ክፉ መንፈስ ኢየሱስን ከሩቁ እንዳየውና እንዲህ እንዳለው እናነባለን፦ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ኾይ፤ ከእኛ ምን ትሻለኽ? ልታጠፋን መጣኽን ? እኔ ማን እንደ ኾንኽ ዐውቅኻለኹ ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነኽ!”(ማር.1፥24፤ሉቃ.4፥34 ) ኢየሱስም ዝም እንዲልና ከሰውዬው ለቅቆ እንዲወጣ ሲያዘው በዚሁ ክፍል ይነበባል፤ ይህ ትረካም በማርቆስ እና ሉቃስ ላይ የምናገኘው የመጀመሪያ የኢየሱስ ተኣምር ነው፤ እንዲህ ዐይነት ክስተቶች በወንጌላት በተደጋጋሚ የሚገኙ ሲኾን ኢየሱስ ግን “ማንነቱን ስለሚያውቁ  እንዲናገሩ አይፈቅድላቸውም ነበር”(ማር.1፥34)።  

በተለይ በኹለት የወንጌላት ምንባባት ላይ በአንድ ግለሰብ ላይ ያደረ ራሱንም “ሌጌዎን” ብሎ የሚጠራ የእልፍ ርኵሳን መናፍስት አለቃ ገና ከርቁ ኢየሱስን እንዳየው እና ወድቆ እንደሰገደለት እንዲህ ተዘግቦአል፦ “ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፥በታላቅ ድምፅም እየጮኸ፦ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ኾይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤኻለኹ (ὁρκίζω) አለ” (ማር.5፥6-7)። ከእነዚህ ዘገባዎች በግልጽ የምንረዳው ኹለት መሠረታዊ ነጥቦች አሉ፤ ይኸውም:- (1ኛ.) ክርስቶስ ገና  የፈውስ አገልግሎት ከመስጠቱ እና ሰዎችን ከአጋንንት እሥራት ነጻ የማውጣት መንክራት (ተኣምራት) መከወን ከመጀመሩ በፊት ኢየሱስን ያውቁት ነበር:- ምድራዊ ሰዎች ግን ይህንን ሊያውቁ አልተቻላቸውም። (2ኛ.) አጋንንት ኢየሱስ ይተዋቸው ዘንድ “ይዤኻለኹ” በማለት የተናገሩት ቃል ὁρκίζω “ኦርኪዞ” የሚል ሲኾን፣ ይህ ቃል በሌላ የዐዲስ ኪዳን ምንባብ አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውሎአል፤ በዛ ክፍልም  የአይሁድ አጋንንት አስወጪዎች፣ የመንፈሳዊ ዓለም አካላት(ክፉ መናፍስት ቢኾኑም) ከሰዎቹ ይወጡ ዘንድ  እንዲህ በተናገሩበት ምንባብ ነው፦ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዝዛችኋለኹ (ὁρκίζω)”(ሐዋ.19፥13) 

ከዚህ የምንረዳው በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ὁρκίζω “ኦርኪዞ” የሚለው ቃል ከሰማይ የመጡ የመንፈሳዊ ዓለም አካላት የሚገለጹበት መኾኑ ሲኾን፣ የሌጌዎኑ አለቃም፣ ኢየሱስ ይተዋቸው ዘንድ ὁρκίζω “ኦርኪዞ” በሚል ቃል መለመኑ ኢየሱስ ልክ እንደ እነርሱ ከመንፈሳዊ ዓለም የመጣ አካል መኾኑን ከመገንዘቡ አንጻር ነው [9]። 

በሦስተኝነት ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት በአካልነት ይኖር እንደነበር የምንመለከተው ደግሞ ካህኑ ዘካሪያስ በሉቃስ ወንጌል ላይ ከተነበየው ትንቢት በመነሣት ሲኾን ክፍሉ እንዲህ ይነበባል፦ “ከአምላካችንም በጐ ምሕረት የተነሣ፣ ይኸውም በጨለማ ለሚኖሩት፣ በሞት ጥላ ውስጥም ላሉት እንዲያበራ፣ እግሮቻችንንም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመራ፣ ይጐበኘን ዘንድ (ἐπισκέψεται ἡμᾶς) የንጋት ፀሓይ (ἀνατολὴ) ከሰማይ (ἐξ ὕψους) መጣልን” (ሉቃ. 1:78-79)። 

ከላይ ባለው ምንባብ “ይጐበኝ ዘንድ” ለሚለው ትርጒም የገባው የጽርእ ግስ (ἐπισκέψεται “ኤፒስኬፕሴታይ”) መቶ ስድሳ (160) ጊዜ በሰባ ሊቃናት ትርጒም፥ ዘጠኝ ጊዜ ደግሞ በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጥቅም ላይ የዋለ ነው፤ ዅልጊዜም የግሱ ባለቤት ኾኖ የሚቀርበው አካላዊ ማንነት ብቻ ነው (ዘፍ . 21፥1፤ ዘጸ. 32፥34፤ ኢዮ 2፥11፤ መዝ. 8፥4፤ ማቴ. 25፥36, 43)፤ ይህም ማለት  “የንጋት ፀሓይ (ἀνατολὴ)” የሚለው መጠሪያ አካላዊ ማንነትን የሚወክል ቅጽል ነው፤ በተለይም ግሱ (ἐπισκέψεται “ኤፒስኬፕሴታይ”) በዐሥር የብሉይ ምንባባት ላይ እግዚአብሔር ሕዝቡን መጐብኘቱን ከባርኮት (blessing) ጋር በተያያዘ መልኩ ተገልጾአል(ዘፍ. 50፥24, 25፤ ዘጸ. 3፥16፤ 4፥31፤ 13፥19፤ ዘፍ 1፥6፤ መዝ. 80፥፤ ኤር 29፥10፤ 32፥41፤ ዘካ . 2፥7) ይህ ገለጻም በካህኑ ዘካርያስ ንግግር በድጋሚ የሚታይ ሲኾን፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘ ከገለጸ (ሉቃ.1፥68) ከጥቂት ቍጥሮች በዃላም፣ የንጋት ፀሓዩ እንዲሁ ሕዝቡን እንዲሁ እንደጐበኘ በመናገር የመሲሑን መለኮትነት ይመሰክራል(ሉቃ.1፥78)። “የንጋት ፀሓይ”( ἀνατολὴ “አናቶሌ”)  ቅርንጫፍ (צֶמַח “ጻማዕ” ) ለሚለው የዕብራይስጥ ቃል ዐቻ ሲኾን፣ መሲሑን አመልካች መጠሪያ መኾኑ በቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ ተጽፎ እናገኛለን (ኤር. 23፥5፤ ዘካ. 3፥8፤ 6፥12)፤ በዐውዱ መሠረትም እንዲሁ ይህ የንጋት ፀሓይ ኢየሱስ መኾኑ እሙን ነው(ሉቃ. 1፥69 እንዲሁም ሉቃ.1፥31–33 ይመልከቱ)። 

ቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ  ይህ የንጋት ፀሓይ(መሲሑ) የሚመጣበትን ምድራዊ የዘር ሐረግ ሲያመለክቱ ይስተዋላል፤ ለምሳሌ፦ “ኮከብ  ከያዕቆብ ይወጣል (ἀνατελεῖ ἄστρον ἐξ Ἰακώβ)” (ዘኍልቍ 24፥17) በማለት መሲሑ ከያዕቆብ ወገን የሚመጣ መኾኑን ተገልጾአል፤ በተጨማሪም ነብዩ ዘካርያስ ይህ የንጋት ፀሓይ “ከሥር (ὑποκάτωθεν) ይወጣል (ἀνατελεῖ) ” በማለት ከዳዊት ዘር እንደሚመጣ ያመለክታል(ዘካ. 6፥12)፤ በተቃራኒው ደግሞ የመጥምቁ ዮሐንስ አባት ዘካርያስ ይህ የንጋት ፀሓይ “ከላይ (ἐξ ὕψους “ኤክ ሁፕሱስ”) እንደሚወጣ ይናገራል፤ በብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት አንድም ጊዜ መሲሑ “ከላይ (ἐξ ὕψους “ኤክ ሁፕሱስ”) እንደሚመጣ አልተገለጸም፤ ይልቁንም “ከላይ” ለሚል የተተረጐመው የጽርእ ቃል (ὕψος “ሁፕሶስ”) የያህዌ ማደሪያ የኾነ፣ ሕዝቡንም የሚመለከትበት ስፍራው መኾኑ በተደጋጋሚ የተገልጸ ሲኾን (2ኛ ሳሙ.22፥17፤መዝ.18፥16)፣ የዳዊት ዘር የኾነው መሲሕ ከዚህ ማደርያ እንደሚመጣ ግን በብሉያት መጻሕፍት ተጽፎ አናገኝም፤ ይህንን አስመልክቶ ሲሞን ጋዘርኮሌ የተባሉ የዐዲስ ኪዳን ምሁር ሲናገሩም  “ነብዩ ዘካርያስ የመሲሑን መምጫ ‛ከሥር’ የሚለውን ትንቢታዊ ቃል፣ በሉቃስ ወንጌል ‛ከላይ’ በሚል መቀየሩ ክርስቶስ ቅድመ ህልውና ያለው ሰማያዊ ማንነት መኾኑን ለማመልከት  ኾን ተብሎ በጸሓፊው  የተደረገው ነው፤ ሉቃስ የመሲሑን ቅድመ ህላዌ ማመልከት ባይፈልግ ኖሮ ‛ከሥር’ የሚለው “ከላይ” በሚል የሚለወጥበት ምንም ዐይነት አግባብ አይኖርም ነበር”[10] ይሉናል። “ከላይ (ἐξ ὕψους “ኤክ ሁፕሱስ”) የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ብቻ ሳይኾን፣ ወንጌላዊው ሉቃስ በወንጌሉ መጨረሻ ላይ  መንፈስ ቅዱስ የሚመጣበት ሰማያዊ ስፍራ እንደኾነ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦

 “እኔም አባቴ የሰጠውን ተስፋ እልክላችኋለኹ፤ እናንተ ግን ከላይ (ἐξ ὕψους) ኀይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቈዩ”(ሉቃ.24፥49)።

ይህ  የጌታችን ንግግርም በዕለተ ጴንጤቆስጤ  ደቀ መዛሙርቱን ለማበረታታት  የመጣውን መንፈስ ቅዱስን የሚያመለክት ነው፤ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር በሉቃስ ውስጥ “ከላይ (ἐξ ὕψους)” የሚለው ሐረግ የተገለጸው በወንጌሉ መግቢያ የመሲሑን (ሉቃ.1፥78)  በወንጌሉ መጨረሻ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን የመጡበትን ስፍራ ለማመልከት (ሉቃ.24፥49) ሲኾን፥ አንድ ቃል በአንድ መጽሐፍ መግቢያ እና መዝጊያ የሚቀመጥ ከኾነ፣ ጸሓፊው በቃላቱ ላይ ማስተላለፍ የፈለገው ተጒዳኝ (correlated) ሐሳብ እንደሚኖር የሥነ አፈታት ምሁራን ይናገራሉ፤ ይኸውም የጸሓፊው ሉቃስ ሐሳብ  ሲጠቀለል መሲሑ ሕዝቡን ሊጐበኘ ከሰማይ እንደ መጣ (ሉቃ1፥78)፥ ምድራዊ አገልግሎቱንም ፈጸሞ  ወደ ሰማይ እንደኼደ ፣ እንዲሁ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ በመምጣት ከአማኒያን ጋር ጸንቶ ይኖራል የሚል ነው። 

በአጠቃላይ በምስስለ ወንጌላት የክርስቶስ መለኮትነት በሚገባ የተዘገበ ሲኾን፥ ቅድመ ህላዌውን አስመልክቶ እንደ ጳውሎስ መልእክታት እና ዮሐንስ ወንጌል ያኽል በተደጋጋሚ ባይጠቀስም በበቂ መጠን ያኽል ተብራርቶአል የሚል እምነት አለን፤ በቀጣይ ደግሞ የዮሐንስ ወንጌል ላይ መሠረት በማድረግ የመጣጥፉን ክፍል የምንደመድም ይኾናል።


የኅዳግ መዘክር

[1] ቅድመ ህላዌ ስንል ኢየሱስ ከማርያም ከመወለዱ በፊት አካላዊ ማንነት ነበረው ማለታችን ሲኾን፣ ይህ ሙያዊ ቃል በእንግሊዘኛው preexistence በመባል ይታወቃል። 

[2] Ehrman, How Jesus Became God, ገጽ 262

[3] ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 248

[4] “ምስስለ ወንጌላት” ማለት “ተመሳሳዮቹ ወንጌላት” ወይም Synoptics Gospels ማለት ሲኾን፥ የማርቆስ፣ የማቴዎስ፣ የሉቃስ ወንጌላትን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውል ሙያዊ ቃል ነው።

[5] በለዘብተኛ ሊቃውንት ዘገባ መሠረት የጳውሎስ መልእክታት ከ49-65 ዓ.ም የተጻፉ ሲኾን፥ ምስስለ ወንጌላት ግን ከ65-85 ዓ.ም እንደተጻፉ ይታመናል።

[6] Ehrman, How Jesus Became God, ገጽ 237

[7] ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ  237

[8] ሐዋ.16፥11-40 ፤ ሐዋ.21፥26

[9] Marcus, Mark 1–8, ገጽ 187–88፤  Collins, Mark, ገጽ 169.

[10] Simon Gathercole  “The Heavenly ἀνατολή (Luke 1:78–9).”, ገጽ 482


መሲሁ ኢየሱስ