ከሰማይ መጥቻለኹ!
የክርስቶስ ኢየሱስ ቅድመ ህላዌ በወንጌላት
ክፍል ኹለት
የዮሐንስ ወንጌል ስለ ክርስቶስ ቅድመ ህልውና በግልጽ ከሚናገሩ የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መኻከል በቀዳሚነት የሚጠቀስ መኾኑ፣ አጥባቂያኑም ለዘብተኞቹም ምሁራን የሚስማሙበት ጒዳይ ነው [1]። ይህ ደግሞ በዐዲስ ኪዳን መርሐ ጥናት(New testament scholarship) ዘርፍ ያሉት ሊቃውንት አመለካከት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የክርስቶስን አምላክነት የማይቀበሉ የሌላ ሃይማኖት መምህራን አቋምም ጭምር ነው። ለማሳያነት ያኽል፣ የኢየሱስን አምላክነት በመቃወም ከብዙ የክርስትና የነገረ መለኮት ምሁራን ጋራ በርካታ ክርክሮችን የሚያደርጉት እንዲሁም በቶሮንቶ ካናዳ የሚገኘው የእሥልምና መረጃና የዳዕዋ ዓለም ዐቀፍ ማእከል ፕሬዚዳንት የኾኑት ዶክተር ሻቢር አሊ፣ ምንም እንኳ ኢየሱስ በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት “አምላክ” መባሉን ባይቀበሉም፣ የዮሐንስ ወንጌል ልክ እንደ ዕብራውያን መልእክት እና የጳውሎስ መልእክታት፣ የኢየሱስን ቅድመ ህላዌ ያለ አንዳች አሻሚነት የሚመሰክር መጽሐፍ መኾኑን ገልጸዋል [2]። እኒህ ዕውቅ የእሥልምና ዐቃቤ እምነት ወደዚህ ድምዳሜ የደረሱበት አንዱ ምክንያትም የዮሐንስ ወንጌል እጅግ በግልጽና በማያወላዳ መልኩ የክርስቶስን ቅድመ ህላዌ ደጋግሞ ከመግለጹ አንጻር መኾኑ እሙን ነው። እኛም በዚህ መጣጥፍ ይህንን እውነት የሚመሰክሩ ጥቂት ምንባባት ላይ ብቻ ተወስነን ጥናታችንን እንቀጥላለን።
ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት ነበር
“ዮሐንስ በማግስቱም፣ ኢየሱስ ወደ ርሱ ሲመጣ ዐይቶ እንዲህ አለ፤ “ዕንኾ! የዓለምን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፤ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበር ከእኔ ይልቃል’ ያልኹት ርሱ ነው።” (ዮሐ 1:29-30) [ዐ.መ.ት]
ከላይ በሰፈረው የዐማርኛ ምንባብ ያለ አንዳች ማብራሪያ የምረዳው ነገር፣ ኢየሱስ ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት በቅድመ ህልውና መኖሩን ነው። ይህም ኾኖ ሳለ፣ በርካታ የክርስቶስን ቅድመ ትሥጒት (pre incarnate) የማይቀበሉ ፀረ ሥላሴአውያን “ከእኔ በፊት ነበር” የሚለው ዐረፍተ ነገር የደረጃ ብልጫን እንጂ በጊዜ መቅደምን አያመለክትም ይላሉ[3]። ነገር ግን መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ ክፍል እየተናገረ ያለው ስለ ጊዜ እንጂ ስለ ደረጃ ብልጫ አለመኾኑ ቢያንስ አራት መሠረታውያን ነጥቦች ያስረዳሉ።
አንደኛ:- በርግጥ “በፊት” (ጽርኡ: “ፕሮቶስ” πρῶτος) የሚለው ቅጽል የደረጃ ብልጫን የሚያመለክትባቸው ጥቂት የዐዲስ ኪዳን ምንባባት አሉ[4]። ነገር ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ይህንን ቅጽል 13 ጊዜ ያኽል የተጠቀመው ሲኾን ዅልጊዜ የጊዜ ብልጫን ብቻ የሚያመለክት ነው(ዮሐ.1፥41፤ 2፥10፤ 7፥51፤ 8፥7፤ 10፥40፤ 12፥16፤ 15፥18፤ 18፥13፤ 19፥32፤ 19፥39፤ 20፥4፤ 20፥8፤ 1ኛ ዮሐ. 4፥19)። ስለዚህ ወንጌላዊው “በፊት”(ጽርኡ፡ “ፕሮቶስ” πρῶτος) የሚለውን ቃል ዅልጊዜ የጊዜ ብልጫን ለማመልከት የሚጠቀም ከኾነ፣ የዮሐንስ 1፥30 ገለጻም የጊዜ ቅድሚያን አመልካች የማይኾንበት አግባብ እጅግ ጠባብ ነው።
ኹለተኛ:- “ከእኔ በፊት ነበር” የሚለው ሐረግ ሊወክል የሚችለው የጊዜ ቅድሚያን እንጂ የደረጃ ብልጫን አይደለም፤ ምክንያቱ ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስ አስቀድሞ “ከእኔ ይልቃል” በማለት የደረጃ ብልጫን ተናግሮአልና። ስለዚህ “ከእኔ በፊት ነበር” የሚለው እንዲሁ የደረጃ ብልጫን አመልካች ከኾነ፣ የዐረፍተ ነገሩ ትርጒም እንደሚከተለው ይኾናል፦ “ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቃል ምክያቱም (ὅτι) ከእኔ ስለሚልቅ” ይህ ደግሞ አላስፈላጊ የቃላት ድግግሞሽን ያስከትላል። መጥምቁ ኢየሱስ ከርሱ እንደሚልቅ የተናገረበት ምክንያት ከርሱ በጊዜ ስለሚቀድም ነው። ኹለቱም ሐረጐች ደረጃን አመልካች ከኾኑ፣ “ስለ” “ምክንያቱም” ለሚሉት የዐማርኛ ቃላት ዐቻ የኾነው የጽርእ መስተጻምር ( ὅτι “ኦቲ”) መግባቱ ትርጒም አልባ ይኾናል።
ሦስተኛ:- መጥምቁ “ከእኔ በኋላ የሚመጣው” በሚል ጊዜን አመልካች ገለጻ ንግግሩን መጀመሩን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ስለዚህ “ከእኔ በኋላ” የሚለው ጊዜን አመልካች ከኾነ፣ በዚሁ ዐረፍተ ነገር ውስጥ “ከእኔ በፊት ነበር” የሚለውም ጊዜን ሳይኾን ደረጃን የሚያመለክትበት አግባብ አይኖርም።
ከአብ ዘንድ መጥቶአል
“ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለኹ፤ አኹን ግን ዓለምን ትቼ ወደ አብ እኼዳለኹ”(ዮሐ.16፥28) [ዐ.መ.ት]
በዮሐንስ 16፥28 ኢየሱስ ከአብ ወጥቶ ወደ ዓለም እንደመጣ እና ዓለምን ትቶ ደግሞ እንዲሁ ወደ አብ እንደሚመለስ ተናግሮአል። ከላይ ባለው ምንባብ( እንዲሁም በዮሐ.13፥3) ኢየሱስ ዓለምን ትቶ ወደ አብ እንደሚመለስ የሚናገር ቀጥተኛ ፍቺን ያነገቡ መኾናቸው ኹሉንም አንባቢያን የሚያስማማ ከኾነ፣ እንዲሁ በዚያው ምንባብ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱን መናገሩ፣ ተምሳሌታዊ ገለጻን ሊያመለክት አይችልም። ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱን የገለጸበት ሐረግ ቀጥተኛ ፍቺ ከሌለው፣ ወደ አብ እንደሚኼድ የተናገረውም ቀጥተኛ ፍቺ ሊኖረው አይችልም። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ይህንን ከተናገረ በኋላ፣ የደቀ መዛሙርቱ ምላሽ የኢየሱስ ንግግር ተምሳሌታዊ ሳይኾን ቀጥተኛ ትርጒም እንዳለው እንረዳለን፦ “ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አሉ፤ “አኹን ያለ ምሳሌ በግልጽ እየተናገርኽ ነው” (ዮሐ.16፥29)። በተጨማሪም በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ፣ የወልድን ከሰማይ ወይም ከእግዚአብሔር መምጣቱን የሚያሳዩ ዐያሌ ምንባባት አሉ። በዮሐንስ ወንጌል ላይ ብቻ ቢያንስ አርባ ጊዜ ከአብ ዘንድ እንደ መጣ የሚያሳዩ ክፍሎችን እናገኛለን(ዮሐ. 3:13፤ 16-17፤ 6፥33፣ 38፣ 44፣ 46፣ 50-51፣ 62፤ 8፥23፣ 38፣ 42፣ 57-58፤ 16፥3-58)። ይኹን እንጂ የክርስቶስን ቅድመ ህላዌ የማይቀበሉ ፀረ ሥላሴአውያን፣ ኢየሱስ ከአብ ዘንድ መምጣቱ ወይም መላኩ፣ ቅድመ ህልውናውን የሚያመለክት ከኾነ፣ መጥምቁ ዮሐንስም በእግዚአብሔር እንደ ተላከ ተገልጾአልና(ዮሐ.1፥6) ርሱም(መጥምቁ ዮሐንስ) ቅድመ ህላዌ አለው ብላችኹ ታምኑ ዘንድ ግድ ይላችኋል በማለት ይሞግታሉ[5]። ለዚህም አራት ሙግቶችን በማቅረብ የፀረ ሥላሴአውያኑ ክርክር አሳማኝ አለመኾኑን እናመለክታለን።
አንደኛ:- መጥምቁ ዮሐንስ በእግዚአብሔር የተላከ (ጽርእ: ἀποστέλλω) ቢኾንም (ዮሐ.1፥30፣3፥20) ፣ እንደ ኢየሱስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ አልመጣም( ἐξέρχομαι)። መጥምቁ ዮሐንስ በእግዚአብሔር መላኩን ለመግለጽ ወንጌላዊው የተጠቀመው የጽርእ ግስ “ἀπεσταλμένος” “አፔስታልሜኖስ” የሚል ሲኾን፣ መነሻን ሳያሳይ ተልእኮን ብቻ ሊያመለክት ይችላል[6]። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱ የተገለጸበት ግስ ἐξέρχομαι “ኤክኤርኾማይ” የሚል ነው፤ ቃሉም በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት 218 ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለ ሲኾን፣ ይህንን ግስ በመጠቀም ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱን የገለጸ ወይም የተገለጸ አንድም ምድራዊ ፍጥረት የለም። በተለይ “ከእግዚአብሔር ወጥቻለኹ (ἐξῆλθεν) አኹን እዚህ ነኝ (ἥκω) ”(ዮሐ.8፥42) የሚለው ሐረግ ክርስቶስ በሥጋ ከመምጣቱ በፊት በቅድመ ህልውና ደረጃ መኖሩን ያለ አንዳች አሻሚነት የሚያመለክት ነው።
ኹለተኛ:- “መጥቻለኹ” “ወጥቻለኹ” በማለት የተተረጐመው የጽርእ ግስ ἐξέρχομαι “ኤክ ኤርኾማይ” የሚል ሲኾን፣ “ኤክ” ማለትም “ከ” እና έρχομαι “ኤርኾማይ” ማለትም “መውጣት” ከሚሉ የኹለት ቃላት ጥምር ነው። ይኸውም ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ መኼድን ወይም ደግሞ መውጣትን (“out of,” “out from,” “from”) የሚያመለክት ነው። ታዲያ ἐξ “ኤክ” የሚለው ቅድመ ቅጥያ ἀπὸ “አፖ” (ባማርኛ “ከ” ) ከሚለው መስተዋድድ (preposition) ጋር አንድ ዐይነት ትርጒም ሲኖረው፣ በዚህ ምንባብ ግን ወንጌላዊ ኹለቱንም ተመሳሳይ ፍቺ ያላቸውን ቃላትን በመጠቀም ክርስቶስ “ከ (ἀπὸ)እግዚአብሔር መውጣቱን (ἐξ)” ይናገራል። ጸሓፊው፣ እነዚህን ተመሳሳይ ኹለት ቅድመ ቅጥያዎችን (prefix) በመጠቀም ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱን በአጽንዖት እና በአንክሮ ለማመልከት ፈልጐ ካልኾነ፣ አላስፈላጊ የቃላት ድግግሞሽ ናቸው።
ሦስተኛ:- የዮሐንስ ወንጌል በግልጽ መጥምቁ ዮሐንስ ከሰማይ አለመምጣቱን ሳያወላዳ ይናገራል(ዮሐ.3፥13)፤ በዚሁ ምዕራፍ ቊጥር 31 እንዲህ ይላል፦ “ከላይ የሚመጣው ከኹሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚኾነው የምድር ነው፥ የምድሩንም ይናገራል፤ ከሰማይ የሚመጣው ከኹሉ በላይ ነው።” ኢየሱስ “ከላይ የመጣ” “ከዅሉ በላይ የኾነ” መኾኑን ሲገልጽ መጥምቁ ዮሐንስ ግን እንደ እኛ “ከምድር የኾነ” “የምድርንም የሚናገር” ነው። ይህ ደግሞ ወደ አራተኛው ነጥብ ይመራናል።
አራተኛ:- በዮሐንስ ወንጌል እንዲሁም በሌሎች የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት “ከሰማይ”(ἐκ τοῦ οὐρανοῦ) መምጣቱን የተናገረ ወይም የተነገረለት ከክርስቶስ ኢየሱስ ውጪ ማንም የለም(ዮሐ 3፥13፣ 31፤ ዮሐ.6፥33፣ 41፣ 42 51)። አማኒያን አብ ከሰማይ የሰጠንን በረከት ብንቀበልም (ዮሐ3፥27፤ ዮሐ 6:65)፣ አንዳንዶችም የአብን ድምፅ ከሰማያት ቢሰሙም(ዮሐ. 12፥28)፣ የትኛውም ምድራዊ ፍጥረት ከሰማይ አልመጣም። በዐዲስ ኪዳን መጻሕፍትም ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጪ “ከሰማይ” መውረዱን(ጽርእ: ἀναβαίνω “አናባይኖ”) የተናገረ አንድም ምድራዊ ፍጥረት የለም። አንዳንድ ፀረ ሥላሴአውያን “በጐ ስጦታና ፍጹም በረከት ከሰማይ ይወርዳሉ”(ያዕ 1፥17) የሚለውን በመያዝ ሚስት እና ልጆች ከሰማይ እንደሚወርዱ ተጠቅሶአል፤ ይህ ማለት ግን ልጆች እና ሚስቶች ቅድመ ህልውና አላቸው ማለት አይደለም፤ በተመሳሳይም ኢየሱስ ከሰማይ እንደወረደ መናገሩ ከሰማይ የመጣ አካል መኾኑን አያሳይም ሲሉ ይደመጣል። ነገር ግን በጥቅሱ እና በዐውዱ ውስጥ ሚስትና ልጆችን የሚጠቊም አንዳች ነገር የሌለ ሲኾን፥ በዐውዱ መሠረትም ከሰማይ እንደሚወርድ የተጠቈመው የአምላክ ጥበብ ነው (ያዕ.1፥15) [7]። ጥበብ ደግሞ አካላዊ ማንነት አይደለምና፣ ከሰማይ ይወርዳል ቢባል እንኳ ከተምሳሌታዊ ገለጻነት የዘለለ አንድምታ አይኖረውም።
ዓለም ሳይፈጠር ከአባቱ ጋር ነበር
“እንግዲህ አባት ኾይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ”(ዮሐ.17፥5) [ዐ.መ.ት]
ከላይ ያለውም ምንባባት ያለ አንዳች ሰዋስዋዊ ወይም ዐውዳዊ ማብራሪያ በግልጽ የክርስቶስን ቅድመ ህላዌ የሚገልጽ ምንባብ መኾኑ ባያጠያይቅም፣ የጌታችን የኢየሱስን ቅድመ ትሥጉት (pre incarnation) የማይቀበሉ ጸሓፊያን እና መምህራን “በነበረኝ ክብር” የሚለው ገለጻ በተስፋ ቃል ደረጃ የተነገረ፣ ኾኖም ግን በመጻኢ ጊዜ ተፈጻሚ የሚኾን ነገርን የሚያመለክት መኾኑን ይናገራሉ። ለዚህም በዚሁ በዮሐ.17 ላይ የኢየሱስ ጸሎት ዋቢ በማድረግ ይከራከራሉ። ለምሳሌ “የሰጠኸኝን ሥራ ፈጸምኹ”(ቊ. 4) ቢልም የመስቀሉ መከራ ግን ገና ከፊቱ ነበር፤ “እኔ በዓለም አልቈይም” (ቍ. 11) ቢልም ይህንን ሲናገር ግን ገና በምድር ነበር፤ “ወደ ዓለም ልኬአቸዋለኹ”(ቊ.18) ብሎ ቢናገርም በትክክል ግን ይህ ተልእኮ የተፈጸመው ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ነው(ዮሐ.20)፤ እንዲሁም “የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለኹ”(ቍ.22) ቢልም በዛች ቅጽበት ግን ሐዋርያቱ ምንም ዐይነት ክብር አልተቀበሉም ነበር። ከዚህ የተነሣም ኢየሱስ “ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር” ሲል በተስፋ ቃል ደረጃ የነበረውን ክብር ፍጻሜነቱን ያገኝ ዘንድ እየጠየቀ ነው ይላሉ። በአጠቃላይ ልክ አማኒያን ዓለም ሳይፈጠር መመረጣቸው (ኤፌ.1፥4) ዓለም ሳይፈጠር በፊት መኖራቸውን እንደማያመለክት ኹሉ፣ ርሱም ዓለም ሳይፈጠር በፊት በተስፋ ቃል ደረጃ የነበረውን ያንን ክብር በተጨባጭ ደረጃ ያገኝ ዘንድ መናገሩ፣ ከማርያም ከመወለዱ በፊት በአካልነት ይኖር እንደነበር አያመለክትም በማለት ይሞግታሉ[8]።
ነገር ግን ይህ ሙግት ግን ሰዋስዋዊ እና ታሪካዊ ትርጒምን መሠረት ያደረገ ሥነ አፈታት አይደለም። ለዚህም ሦስት ወሳኝ መሠረታውያን ነጥቦችን በአስረጅነት እናቅርብ።
አንደኛ:- ኢየሱስ “በነበረኝ ክብር አክብረኝ” ሲል “በነበረኝ” ለሚለው የገባው የጽርእ ግስ εἶχον “ኤይኾን” ሰዋስዋዊ መደቡ የማያቈርጥ ዐላፊ ግስ (Imperfect verb) ሲኾን “ካለፈ ጊዜ ጀምሮ የነበረን የአኗኗር ኹኔታን የሚያመለክት” ግስ ነው[9]። ይኸውም ኢየሱስ ሰው ከመኾኑ በፊት የነበረውን ያንን ክብር በድጋሚ ያገኝ ዘንድ አብን እየጠየቀ እንደኾነ ያመለክታል። በተቃራኒው ደግሞ በዮሐ.17 ላይ ባለፈ ጊዜ የተዘረዘሩትና በመጻኢ ጊዜ ተፈጻሚነትን የሚያመለክቱት ግሶች በማያቈርጥ ዐላፊ ግስ አልተቀመጡም[10]። በትልልቅ የትምህርት ተቋማት የሚዘጋጁ የጽርእ ሰዋስው መጻሕፍትም በተስፋ ቃል የተነገሩ ወይም ቅድመ ውሳኔን (predestination or foreknowledge) የሚያመለክቱ ምንባባት በማያቈርጥ ዐላፊ ግስ መቀመጣቸውን ሲገልጹ አይስተዋልም[12]:-ቢያንስ የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ ይህንን አያውቅም[13]።
ኹለተኛ:- “ከአንተ ጋር በነበረኝ” በሚለው ሐረግ ላይ “ዘንድ/ ጋር” ለሚለው የዐማርኛ ትርጒም የገባው ቃል παρὰ “ፓራ” የሚል የጽርእ መስተዋድድ ሲኾን፥ ከተቀባይ ሙያ (dative case) ጋር የመጣ ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ የዮሐ.17፥5 ገለጻን ጨምሮ፣ παρὰ “ፓራ” የሚለውን መስተዋድድ ከተቀባይ ሙያ ጋር ዐሥር ጊዜ የተጠቀመ ሲኾን ዅልጊዜ ከአንድ በላይ የኾኑ አካላት ዐብሮነትን/መስተጋብርን የሚያመለክት ነው(ዮሐ. 1፥39፤ 4፥40፤ 8፥38፤ 14፥17, 23, 25,፤ 17፥5፤ 19፥25፤ እና ራእይ. 2፥13)። ስለዚህ “ከአንተ ጋር በነበረኝ” ሲል፣ አካል የኾነውን ማንነቱን እንጂ ስመ ርቀት (abstract noun) የኾነውን ወይም አካል ያልኾነውን ክብሩን አይደለም። παρὰ “ፓራ” ከተቀባይ ሙያ ጋር ሲመጣ አካላዊ መስተጋብርን እንደሚያመለክት በሌሎች የወንጌላዊው ምንባባት ላይ ብቻ ሳይኾን፣ የዮሐ. 17፥5 ገለጻን በንጽጽር ስንመለከት ኢየሱስ እየተናገረ ያለው በቅድመ ህልውና በአካልነት ስለነበረው ክብሩ መኾኑን እንገነዘባለን፦
“…በአንተ ዘንድ (παρὰ σεαυτῷ ) አክብረኝ…”
“…ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር (παρὰ σοί) በነበረኝ ክብር”
ፀረ ሥላሴአውያን፣ ክርስቶስ “በአንተ ዘንድ አክብረኝ” ማለቱ ከሞቱ እና ከትንሣኤው በኋላ በአካልነት ከርሱ (ከአብ) ጋር ስለሚኖረው ክብር እየተናገረ መኾኑን ያምናሉ። ስለዚህም በተመሳሳይ በዚሁ ረድፍና ሐረግ “ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ጋር በነበረኝ ክብር” የሚለውም ሐረግ በአካልነት ስለ ነበረው ክብር እንጂ በተስፋ ቃል ደረጃ ስላለው ክብር እያወራ አይደለም። በዐጭሩ በዮሐንስ ገለጻ παρὰ “ፓራ” ከተቀባይ ሙያ(dative case) ጋር ሲመጣ ከአንድ በላይ የኾኑ አካላትን ዐብሮነት የሚገልጽ ብቻ ነው።
ሦስተኛ:- ከ35 እስከ 107 ዓ.ም እንደኖረ የሚነገርለት የሐዋርያው ዮሐንስ ደቀመዝሙር እና የአንጾኪያ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የኾነው ቅዱስ አግናጥዮስ የዮሐንስ 17፥5 ምንባብን በማጣቀስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም በአካልነት ከአባቱ ጋር ይኖር እንደነበር ወደ ማግኔዥያ በላከው ጦማር እንዲህ ላይ እንዲህ ይናገራል፦
“ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘመናት (αἰώνων) በፊት (πρὸ) ከአብ ጋር (παρὰ πατρὶ) የነበረ (ἦν) በዘመኑ መጨረሻም የተገለጠ ነው[13]”
ከላይ ያለውን ምንባብ ከዮሐ.17፥5 ጋር በማነጻጸር እንመልከተው፦
“አባት ኾይ፤ ከዓለም በፊት (πρὸ) ከአንተ ጋር (παρὰ σοί) በነበረኝ (εἶχον) ክብር በአንተ ዘንድ አክብረኝ” (ዮሐ.17፥5)
እንግዲህ በኹለቱም ምንባባት παρὰ “ፓራ” ከተቀባይ ሙያ ጋር ቀርቦአል፥ በኹለቱም ሐረጎች πρὸ የሚል መስተዋድድ አለ፥ በኹለቱም ምንባባት የክርስቶስን ኑረት ለመግለጽ የማያቈርጥ ዐላፊ ግስ የኾኑት “εἶχον” “ኤይኾን” እና ἦν “ሂን” በ1ኛ እና 3ኛ መደብ ተጠቅሰዋል። ይህ ደግሞ በአጋጣሚ የኾነ ሳይኾን የዮሐ.17፥5 ምንባብ በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የክርስቲያን ቅድመ ህላዌን አመልካች ምንባብ ተደርጐ ስለሚወሰድ ነው። የዮሐንስ አርድእት የኾነው፣ ቅዱሱ አባት አግናጥዮስ የማግኔዤያ አማኒያን አስቀድመው የሚያውቁትን የዮሐ.17፥5 ምንባብ በመጠቀም የክርስቶስን ቅድመ ህልውናን እየተናገረ እንደኾነ ብዙ ምሁራንን ያስማማል[14]።
በአጠቃላይ አራቱም ወንጌላት ስለ ጌታችን እና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ህልውና በተደጋጋሚ ዘግበዋል። የመጀመሪያ ዘመን ቤተክርስቲያንም ቅዱሳት መጻሕፍትን ማእከል በማድረግ ይህን እውነት ለዘመናት ስታስተምር ኖራለች። እኛም በዚህ መጣጥፍ የተወሰኑትን ምንባባት በጥቂት ቢኾን ለመዳሠሥ ሞክረናል። የክርስቶስን ቅድመ ህልውና ለማይቀበሉ ወገኖቻችንን ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ የተዘገበውን፣ በሐዋርያትና ሐዋርያት አበው የተመሰከረውን ይህንን ርቱእ ትምህርት ያምኑ ዘንድ ጥሪያችን ነው።
የኅዳግ መዘክር
[1] Maurice Casey, Is John’s Gospel True? (London: Routledge, 1996), 30.
Dunn, Christology in the Making, 240. Ehrman, How Jesus Became God, p. 248.
[2] Shabir Ally, Is Jesus God? The Bible Says No, p. 9–11.
[3] Anthony F. Buzzard and Charles F. Hunting, The Doctrine of the Trinity: Christianity’s Self-Inflicted Wound, p. 204.
[4] ማቴ. 20፥27፣ 22፥38፤ ማር 6፥21፣ 10፥44፣ ሉቃ 11፥26
[5] Anthony F. Buzzard and Charles F. Hunting, The Doctrine of the Trinity: Christianity’s Self-Inflicted Wound, p. 202, 322.
[6] BDAG, p.120-21.
[7] Peter H. Davids, The epistle of James: A commentary on The Greek Text, NIGTC (Grand Rapids: Eerdmans, 2002), p. 122
[8] Anthony F. Buzzard and Charles F. Hunting, The Doctrine of the Trinity: Christianity’s Self-Inflicted Wound, p. 216- 17
[9] Daniel Wallace, Greek Grammar Beyond the Basics, p. 542
[10] ዮሐ.17፥4 “አኹን ፈጸምኹ”(τελειώσας) የዋህ ዐላፊ ነው፤ ዮሐ.17፥11 “እኔ በዓለም አልቈይም”(εἰμὶ) የአኹን ጊዜ ነው፤ ዮሐ.17፥18 “ወደ ዓለም ልኬአቸዋለኹ”(ἀπέστειλα) የዋህ ዐላፊ ነው፤ ዮሐ.17፥ 22 “የሰጠኸኝን ክብር ሰጥቻቸዋለኹ” (δέδωκα) በቅርብ ዐላፊ ጊዜ የተገለጸ ነው።
[11] ዶክተር ዳንኤል ዋላስ (Daniel B.wallace) ቅድመ ውሳኔን ወይም መጻኢ ድርጊትን የሚያመለክቱ የዋህ ዐላፊ እና የቅርብ ዐላፊ እንዲሁም የአኹን ጊዜ ግሶችን ሲዘረዝሩ የማያቈርጥ ዐላፊ ግስ ግን አንድም ጊዜ አልጠቀሱም(Greek grammar beyond the basics, p. 563-64, 581።
[12] በቅዱሳት መጻሕፍት ቅድመ ውሳኔን(predestination ወይም foreknowledge) የሚያመለክቱ ምንባባትን ለመመልከት ጥረት ያደረግን ሲኾን በማያቈርጥ ዐላፊ ግስ የተገለጸ አንድም ምንባብ አላገኘንም። ኤር.1፥5 “ዐወቅኹኽ”(ἐπίσταμαί) የአኹን ጊዜ ግስ፤ “ለየኹኽ”(ἡγίακά) እና “ሾምኹኽ”(τέθεικά) ቅርብ ዐላፊ ግስ ፤ ማቴ.13፥35 “የተሰወረው”(κεκρυμμένα) የቅርብ ዐላፊ ፤ ማቴ.20፥23. እንዲሁም ማቴ.25፥34 “የተዘጋጀው”(ἡτοίμασται) የቅርብ ዐላፊ ፤ ሮሜ.8፥29-30. “አስቀድሞ ያወቃቸው”(προέγνω) “አስቀድሞ የወሰናቸው”(προώρισεν) የዋህ ዐላፊ፤ 2ኛ.ቆሮ 5፥1 “አለን”(ἔχομεν) የአኹን ጊዜ፤ ኤፌ.1፥4. “መርጦናል”(ἐξελέξατο) እና “አስቀድሞ ወሰነን”(προορίσας) የዋህ ዐላፊ ፤ 2ኛ.ጢሞ 1፥9 “ተሰጠን”(δοθεῖσαν)፤ 1ኛ.ጴጥ.1፥20 “አስቀድሞ የታወቀው”(προεγνωσμένου) የቅርብ ዐላፊ፤ ራእይ.13፥8 እና 17፥28 “የታረደው”(ἐσφαγμένου) እና “የተጻፈው”(γέγραπται) የቅርብ ዐላፊ ግስ ናቸው።
[13] Ignatius, Epistle of Ignatius to the Magnesians 6:2
[14] Edward L. Dalcour, A Definitive Look at Oneness Theology: In the Light of Biblical Trinitarianism, p.130
