ሕይወት ሰጪው ክርስቶስ

ሕይወት ሰጪው ክርስቶስ


በዚህ ጽሑፍ ምላሽ የሰጠንበትን ጥያቄ ከዚህ ቀደም የዳሰስነው ቢሆንም የበለጠ ማብራርያ ለመስጠት ዕድል የሚሰጥ መጣጥፍ ስለተመለከትን በድጋሜ አንስተነዋል። ጥቅሶችን ያለ አውድ አቀጣጥሎ በመጻፍ የሚታወቅ አንድ ሙስሊም ተሟጋች ቀጣዩን ጽፏል።

ሙስሊም፦

«ሰላምም በእኔ ላይ ነው፡በተወለድሁ ቀን፣ በምሞትበትም ቀን፣ ሕያው ኾኜ በምቀሰቀስበትም ቀን፡፡» ቁርኣን 19፥33

“ሄአውቶ” ἑαυτῷ ድርብ ተውላጠ ስም ሲሆን “ራስ”own self” ማለት ነው፥ አንድ ምንነት የራሱ ፈቃድ፣ ማንነት፣ እኔነት፣ አንተነት፣ እርሱነት እንዳለው አመላካች ነው፦

መልስ፦

ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ የክርስቶስን ሕይወት በተመለከተ ሙስሊሞች የሚያምኑትን የሚጻረር ነው። የክርስቶስን ስቅለትና ሞት የሚያምኑ አንዳንድ ሙስሊሞች ቢኖሩም አብዛኞቹ ሙስሊሞች እንዳልተሰቀለና እንዳልሞተ ነው የሚያምኑት። ይህ ጥቅስ ግን ስለ ልደቱ፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ነው የሚያወራው። ነገር ግን አብዛኛው ሕዝበ ሙስሊም ክርስቶስ እንደተወለደና፣ ሳይሞት ወደ ሰማይ እንዳረገ ከዚያም ለመሞት ዳግመኛ ወደ ምድር ተመልሶ እንደሚመጣ ቢያምንም ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ለመሞት ዳግመኛ ወደ ምድር ይመለሳል የሚል ትምህርት በቁርአን ውስጥ አይገኝም። የቁርአን ደራሲ ቢያንስ ይህንን ጥቅስ በጻፈበት ጊዜ ይህ እምነት ቢኖረው ኖሮ ወደ ሰማይ አርጎ ዳግመኛ ለመሞት ይመጣል የሚለውን ይህንን ትልቅ ነጥብ ባልዘነጋ ነበር። 

ይህ ሙስሊም ጸሐፊ “ግሪክ እችላለሁ” የሚል መልእክት ማስተላለፍ እንደፈለገ በሚያሳብቅ ሁኔታ ግልጽ የሆነውን ቃል በግሪኩ ከጠቀሰ በኋላ እንደተለመደው አልተገናኝቶ ጥቅሶችን ወደ መደርደር ይሄዳል። “ሄአውቶ” የሚለው ቃል ወደ ራስ ጠቋሚ ተውላጠ ስም መሆኑን ለማሳየት ተከታዮቹን ጥቅሶች ጠቅሷል፦ ያዕቆብ 1፥14፣ ፊልጵስዩስ 2፥3፣ ዮሐንስ 8፥44፣ ዮሐንስ 11፥51፣ ሉቃስ 7፥39። በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ዋናው ቋንቋ የሚጠቀሰው ቃሉ አከራካሪ ሲሆን፣ በትርጉሞች ውስጥ በበቂ ሁኔታ ሳይወከል ሲቀር ወይንም ምሑራዊ ትንታኔ የሚሻ ሲሆን እንጂ ዝም ብሎ ያለ ምንም ምክንያት ቃላትን አምጥቶ መደንቀር ብስለት የማጣት ምልክት ነው። በማስከተል እንዲህ ይላል፦

ሙስሊም፦

ፈሪሳዊ በራሱ ያሰበው የራሱ ፈቃድ፣ ማንነት፣ እኔነት፣ አንተነት፣ እርሱነት ስላለው ነው፥ ስለዚህ እያንዳንዱ “በራሱ” ምኞት የሚመኘው፣ እያንዳንዱ ባልንጀራው “ከራሱ” ይልቅ እንዲሻል በትሕትና የመቁጠር ዐቅም ያለው፣ ፈሪሳዊ በራሱ ማሰብ የቻለው ፈጣሪ ሕይወትን ለሁሉም ስለሰጣቸው ነው። ፈጣሪ እያንዳንዱ ሕያው ነገር በራሱ እዲኖር ሕይወትን ይሰጣል፦

እርሱም ሕይወትን እና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና። የሐዋያት ሥራ 17፥25

በተመሳሳይ ወልድ “በራሱ” የራሱ ፈቃድ፣ ማንነት፣ እኔነት፣ አንተነት፣ እርሱነት ያለው ነው፥ ይህ ማንነት ከ-“ራሱ” ምንም ማድረግ ስለማይችል የፍጡር ማንነት ነው፦

እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም። ዮሐንስ 5፥30

መልስ፦

ሙስሊሙ ጸሐፊ ጥቅሱን ከአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ ክርስቶስ እንዲሁም ከምዕራፉ አውድ ውጪ ገንጥሎ ወስዷል። ሐሳቡን ስለማይደግፍለት አንዷን ጥቅስ እንኳ አሟልቶ የመጥቀስ ድፍረት አናይበትም። እርሱ ቆርጦ ያስቀረውን ቀጣይ የጥቅሱን ክፍል ጨምረን ስናነብ ነገሩ ሁሉ ግልጽ ይሆናል፦ “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከራሱ አንዳች ማድረግ ያልተቻለው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ወደ ምድር ስለመጣ መሆኑን በግልጽ በተናገረበት ሁኔታ “ፍጡር ስለሆነ ነው” የሚል ድምዳሜ መስጠት አላዋቂነት ነው። በሌላ ስፍራ እንደተነገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርዩ ከአብ ጋር የተካከለ መለኮት ሆኖ ሳለ ራሱን በማዋረድ ዝቅ ብሎ መጥቷል፦

“በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣ በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ።” (ፊል. 2፡5-8 አመት)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለአባቱ በፍጹም ታዛዥነት ስለተመላለሰ ነው ይህንን ያለው እንጂ በባሕርዩ አምላክ ስላልሆነ ወይም ፍጡር ስለሆነ ፈፅሞ አይደለም። ሙስሊሙ ጸሐፊ አጠቃላዩን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መረዳት ቸግሮታል ቢባል እንኳ ቢያንስ አንዷን ጥቅስ አሟልቶ ማንበብ አለመቻሉ አስገራሚ ነው።

ሙስሊም፦

አዳም ከአፈር ከተፈጠረ በኃላ ሕያው እንዲሆን መንፈስ ቅዱስ እንደተነፋበት ሁሉ ኢየሱስም ከማርያም ተፈጥሮ ሕያው እንዲሆን መንፈስ ቅዱስ ወደ ማርያም ማኅፀን መጥቷል። ከእርሷ የተፀነሰው ፅንስ ሕያው የሆነው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና፦

መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል። ሉቃስ 1፥35

ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና። ማቴዎስ 1፥20

መልስ:-

ሙስሊሙ ጸሐፊ በጥቅሶቹ ውስጥ ያልተባለ እንግዳ ነገር ነው እየተናገረ ያለው። የእግዚአብሔር ልጅ በነቢያት እንደተተነበየው በድንግል ማህፀን አድሮ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ሲመጣ የሂደቱ ከዋኝ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል። ይህንን ሂደት ከአዳም መፈጠር ጋር የሚያመሳስለው አንዳችም ነገር የለም። አዳም ሕያው ነፍስ እንዲሆን የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያስፈለገው ሲሆን ሁለተኛ አዳም ተብሎ የተጠራው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱ ሕይወት ሰጪ መንፈስ ነው፦

“እንዲሁ ደግሞ። ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።” So also it is written: “The first man, Adam, became a living person.” The last Adam was a life-giving spirit. (1ቆሮ. 15፡45)።

ስለ ሁለተኛው አዳም ሲናገር መጽሐፉ በተጻፈበት የፅርዕ ቋንቋ «መሆንን» የሚያሳይ አገላለጽ ስለሌለ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ የሚለው የሁለተኛው አዳም ባሕርይ እንደሆነ እንገነዘባለን። የፊተኛው አዳም ሕያው ለመሆን የአምላክ መንፈስ ያስፈለገው ሲሆን የኋለኛው አዳም ግን ለፊተኛው አዳም ለራሱ ሕይወትን የሰጠ መንፈስ ነው። እንዲህ እንደተባለ፦

“ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።” (ዮሐ. 1፡3)

በቁርአን መሠረት እንኳ ዒሳ የአላህ ቃልና መንፈስ ተብሎ ሳለ በአንድም ቦታ ላይ በቃሉና በመንፈሱ ሕያው ተደረገ አልተባለም። መንፈስም ቃልም ያው አንዱ ዒሳ ነው (ቁርአን 4፡171)። ይህ ሙስሊም ጸሐፊ እንኳንስ በመጽሐፍ ቅዱስ በቁርአን ራሱ ክርስቶስ በመንፈስ ተፈጠረ የሚለውን እምነቱን ሊያረጋግጥ አይችልም። ይልቅ በቁርአን መሠረት ከዒሳ የሚወጣው መንፈስ ሕይወት ሰጪ ነው(ቁርአን 3፡49)።

ሙስሊም፦

አብ የራሱ ማንነት፣ እኔነት፣ አንተነት፣ እርሱነት እራሱን የቻለ ሕይወት አለው፦

ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን። ዮሐንስ 6፥57

ወልድ ወደ ህልውና የመጣው ከአብ የተነሳ ነው፥ ወልድ የራሱ እኔነት እንዲኖረው አብ ሕይወትን ሰጠው፦

አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። ዮሐንስ 5፥26

ወልድ ሕይወትን በስጦታ ያገኘ ሃልዎት ከሆነ ሕይወት ከመሰጠቱ በፊት ሕይወት አልባ ስለሆነ በባዶነት የተቀደመ ነው፥ ሕይወት የተሰጠው ማንነት እና ምንነት መነሻ እና ጅማሮ ስላለው ፍጡር ነው።

መልስ፦

በጥንት የቤተክርስቲያን አበው መሠረት ይህ የክርስቶስን ቅድመ ዓለም ከአብ መገኘት ወይም ዘላለማዊ ልደት (eternal generation) የሚያሳይ ነው። የጌታችን ከአብ መገኘት ዘላለማዊ እንጂ በጊዜ ውስጥ የተፈፀመ ባለመሆኑ ፍጡር አያስብለውም። በሙስሊሞች እምነት እንኳ የአላህ ባሕርያት (attributes) መገኛቸው አላህ ቢሆንም ፍጡራን አይደሉም። በርግጥ ክርስቶስ የአብ ባሕርይ ነው ማለት ሳይሆን መገኛቸው አላህ የሆኑ ባሕርያቱ ፍጡራንና በጊዜ የተገደቡ ካልተባሉ ኢየሱስ በዘላለማዊነት ከአብ ተገኘ የሚለው አገላለጽ ኢየሱስን ፍጡር ሊያደርገው እንደማይችል ለሙስሊሞች ግንዛቤ ለመስጠት ያህል ነው። ሌላው ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ የሚገባው ጉዳይ ጥቅሱ በተለያየ መንገድ ሊተረጎም የሚችል መሆኑ ነው። እስኪ የተለያዩ የአማርኛ ትርጉሞች እንዴት እንዳስቀመጡት እንመልከት፦

“ምክንያቱም አብ ራሱ የሕይወት ምንጭ እንደ ሆነ፣ እንዲሁም ወልድን የሕይወት ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል” (1980 ትርጕም)

“አብ በገዛ ራሱ የሕይወት መገኛ እንደ ሆነ ሁሉ፤ እንዲሁም ወልድ በገዛ ራሱ የሕይወት መገኛ ይሆን ዘንድ አድርጎታል” (ሕያው ቃል)

“አብ ከእርሱ ዘንድ ሕይወት እንዳለው፣ እንዲሁ ደግሞ ለልጅ ሰጠው ሕይወት ከእርሱ ትሆን ዘንድ” (1879 ትርጕም ቃል)

በነዚህ ትርጉሞች መሠረት የክርስቶስ ንግግር የሰው ልጆችን ድነት የተመለከተ እንጂ የራሱን ህላዌ የተመለከተ አይደለም። ስለዚህ ወልድ ለሰው ልጆች ድነት እንዲሆን አብ እንዳደረገው እንጂ ለገዛ ህላዌው መሠረት የሚሆን ሕይወት ተቀበለ ማለት አይደለም። የሚገርመው ነገር የይሖዋ ምስክሮች ትርጉም የሆነው የ2008 የአማርኛ ዕትም በኋላ ላይ ቢለውጡትም ከነዚህ ትርጉሞች ጋር ይስማማል፦

“አብ ሕይወት የመስጠት ሥልጣን እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም ሕይወት የመስጠት ሥልጣን እንዲኖረው አድርጎታል” (2008 አዲሲቱ ዓለም ትርጉም)

ስለዚህ የጥቅሱ ሐሳብ ወልድ ለሌሎች ሕይወትን እንዲሰጥ ከአብ ዘንድ ሥልጣንን መቀበሉን እንጂ ለራሱ ሕያውነት ሕይወትን መቀበሉን አያመለክትም። ይህንንም ከአውዱ መረዳት ይቻላል፦

“አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።” (ቁ. 21)

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።” (ቁ. 24)

“መቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።” (ቁ. 29)

ስለዚህ አውዱ የክርስቶስን ለሰው ልጆች ሕይወት መስጠት የተመለከተ በመሆኑ የጥቅሱ ሐሳብ እነዚህ ትርጉሞች ባስቀመጡት መሠረት ሊታይ ይገባዋል።

ሙስሊም፦

አንድምታ፦ “ሕይወት የባሕርይው ይሆን ዘንድ ሕይወትን ሰጠው” ሲል የሂፓፑ አውጉስጢዮስ ደግሞ ሕይወት ሰጠው ማለት “እርሱ(አብ) ወልድን ወልዶታል” ማለት ነው በማለት ይናገራል፦

እንዲህ አለ፦ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልን? በአጭሩም እላለሁኝ፦ “እርሱ(አብ) ወልድን ወልዶታል” Augustine on the Gospel of John. Tractates (Lectures) 19 number 13

አብ ረቂቅ እና ምጡቅ ስለሆነ ለወልድ ሕይወት በመስጠት ፈጥሮታል ማለት ነው፥ ወልድ የአብ ግኝት ስለሆነ የአብ ጥገኛ ነው።

መልስ፦

ሙስሊሙ ጸሐፊ አውጉስጢኖስ በጭራሽ ያላሰበውን ትርጓሜ በመስጠት የአውጉስጢኖስን ሐሳብ ከግል ትርጓሜው ጋር ቀይጧል። ይህንን ነውረኛ ተግባሩን ለማጋለጥ አውጉስጢኖስ እዚያው ክፍል ላይ ምን እንዳለ እንመልከት፦

You are made a partaker of life; you were not that which you have received, but wast one who received: but it is not so with the Son of God as if at first He was without life, and then received life. For if thus He received life, He would not have it in Himself. For, indeed, what is in Himself? That He should Himself be the very life. (9)

“እናንተ ሕይወት ተቀባዮች ተደርጋችኋል፤ እናንተ የተቀበላችሁትን ያንን አይደላችሁም ነገር ግን ተቀባዮች ናችሁ። ነገር ግን መጀመርያ ሕይወት ያልነበረውና ከዚያ የተቀበለ ይመስል ለእግዚአብሔር ልጅ እንደርሱ አይደለም። ሕይወትን የተቀበለ ከሆነ በራሱ ሕይወት ሊኖረው አይችልምና። በእርግጥ በራሱ ያለው ምንድነው? እርሱ ራሱ ሕይወት እንዲሆን ነው።”

በግልፅ እንደሚነበበው በአውጉስጢኖስ አረዳድ የእግዚአብሔር ልጅ ሕያው ያልሆነ ነገር ሕይወትን እንደሚቀበል አልተቀበለም። የእርሱ የሕይወት አቀባበል እንደ ፍጡር አይደለም። ሙሉ ጽሑፉን ካነበብን የአውጉስጢኖስ ሙግት “በራሱ” በሚለው ራስን በራስ ማኖር (self-existence) የሚል መልእክት ባለው ለፍጡር ሊነገር በማይችለው አገላለጽ ዙርያ ያጠነጠነ ነው። ይህ አገላለጽ ለፍጡር የማይነገር በመሆኑ ጥቅሱ ከላይ ሲታይ “ሕይወትን ከአብ ተቀበለ” ከሚለው መልእክት የጠለቀ ትርጉም እንድናስተውል ያደርገናል፤ ይኸውም ክርስቶስ ራሱ ሕይወት መሆኑ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንደተናገረው ፍጡራን በራሳቸው ሕይወት የላቸውም፤ ሕይወትን ሰጪ በሆነው በእርሱ ላይ ጥገኞች ናቸው፦

“ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።” (ዮሐ 6:53)

በማስከተል እንደምንመለከተው ይህ ሊሆን የቻለው ክርስቶስ በዘላለማዊነት ከአብ የተወለደ ስለሆነ ከአብ ጋር አንድ ሕይወት ስላለው ነው። አውጉስጢኖስ ክርስቶስ ከአብ ጋር ዘላለማዊ መሆኑን በተመለከተ የተናገረውን ከመጥቀሳችን በፊት ሙስሊሙ ጸሐፊ በአውጉስጢኖስ ላይ የቀጠፈውን ሌላ ቅጥፈት እንመልከት።

ሙስሊም፦

ይህንን የሂፓፑ አውጉስጢዮስ ያጠናክርልናል፦

አብ በራሱ ሕይወት ያለው እንጂ ከወልድ አይደለም፥ ወልድ ግን በራሱ ሕይወት ያለው ከአብ ነው። ወልድ በራሱ እንዲኖር ከአብ የተወለደ ነው፥ ነገር ግን አብ በራሱ እንዲኖር አልተወለደም። Augustine on the Gospel of John. Tractates (Lectures) 19 number 13

አብ የማንም ጥገኛ ስላልሆነ በራሱ ሕይወት ያለው እንጂ ከወልድ ሕይወት አልተሰጠውም፥ ወልድ ግን ከአብ የተሰጠ ሕይወት ስላገኘ አብ ፈጥሮታል፦

ልክ እርሱ እንደሚለው፦ “አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ወልዶታል” ማለቱ ነው። Augustine on the Gospel of John. Tractates (Lectures) 19 number 13

መልስ፦

ሙስሊሙ ጸሐፊ እንደቀጠፈው አውጉስጢኖስ አንድም ጊዜ አብ ወልድን ፈጥሮታል የሚል ቃል አልተጠቀመም። አብ አባት ወልድ ልጅ በመሆኑ ወልድ ከአብ ሕይወትን ተቀብሏል እንላለን ነገር ግን ይህ መፈጠርን ወይም የጊዜ መቀዳደምን የሚያሳይ ሳይሆን ዘላለማዊ አባትነትና ልጅነትን የሚያሳይ ነው። ይህ አብና ወልድ አንድ ሕይወት አላቸው ማለት እንጂ ወልድ ፍጡር ነው ማለት አይደለም። ይህንንም ሲያስረዳ አውጉስጢኖስ እዚያው ክፍል ላይ እንዲህ ይላል፦

Before all time, He is co-eternal with the Father. For the Father has never been without the Son; but the Father is eternal, therefore also the Son co-eternal. (13)

“ከጊዜ ሁሉ አስቀድሞ እርሱ ከአብ ጋር አብሮ ዘላለማዊ ነው። አብ ያለ ወልድ የነበረበት ጊዜ አልነበረም፤ ነገር ግን አብ ዘላለማዊ እንደሆነ ወልድም ከእርሱ ጋር አብሮ ዘላለማዊ ነው።”

የአውጉስጢኖስ አመለካከት ይህ ነው! ወልድ እንደ አብ ሁሉ ዘላለማዊ ነው። በሁለቱ መካከል የጊዜ መቀዳደም የለም። አብ ያለ ወልድ ወልድም ያለ አብ የነበሩበት ጊዜ የለም። አብ ለወልድ ሰጠው የሚለው በሥላሴ አካላት ግብር ውስጥ የሚታይ እንጂ በፈጣሪና ፍጥረት እሳቤ የሚገለጽ ፈፅሞ አይደለም። ሙስሊሙ ጸሐፊ ግን አውጉስጢኖስ ያልተናገረውንና የማያምነውን የግል አመለካከቱን ጨምሮ አንብቦታል። ለነገሩ ከላይ የጠቀሰውን ሐሳብ የሆነ ቦታ ከተጻፈ ምንጭ አግኝቶ እንጂ በርግጠኝነት ሙሉ ጽሑፉን አንብቦ አይደለም። አውጉስጢኖስ ዘሂፖ ማን እንደሆነ ራሱ የሚያውቅ አይመስልም። ቢያውቅ ኖሮ አውጉስጢኖስን “አውጉስጢዮስ” በማለት ተሰምቶ በማይታወቅ አጠራር ባልጠራ ነበር፤ ሂፖ የሚለውንም የከተማ ስም “ሂፓፕ” ብሎ ባልጻፈ ነበር። የሂፓፕ ሙዚቃ ስልት እያሰበ ይሆን? ይህንን ለይቶ ያላወቀ ሰው ነው እንግዲህ የአውጉስጢኖስን የጠለቀ ነገረ መለኮት ለማጣቀስ ቁም ስቅሉን የሚያየው። አሳፋሪ ነው! በቀጣይነት አሁንም ቃለ እግዚአብሔርን በማጣመም የቅጥፈት ዲስኩሩን ይቀጥላል፦

ሙስሊም፦

አብ ወልድን የፈጠረው ከማርያም ማኅፀን ነው፦

ግዕዙ፦ “ወለድኩከ እም ከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ”

መዝሙር 110፥3

ትርጉም፦ “ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከማኅፀን ወለድኩህ”

“ከማኅፀን ወለድኩህ” I have begotten thee from the womb” የሚለው ቃል ግሪክ ሰፕቱጀንት ላይ የሚገኝ ነው፥ “ከርሥ” ማለት “ማኅፀን” the womb” ሲሆን ከድንግል ማኅፀን መፈጠሩን ተናግሯል፦ ሃይማኖተ-አበው ዘቄርሎስ 76፥19
ግዕዙ፦ “ተፈጥረ እምከርሠ ድንግል”

ትርጉም፦ “ከድንግል ማኅፀን ተፈጠርኩኝ”

መልስ፦

አሁንም ሙስሊሙ ጸሐፊ እያጭበረበረ ነው። ቄርሎስ ይህንን ያለው መዝሙር 110ን በመጥቀስ አይደለም። መነሻ ሐሳቡን ያደረገው ምሳሌ 8 ላይ ስለ ጥበብ የተነገረውን በመጥቀስ ነው። ስለ ክርስቶስ የቤተልሔም ልደት ሲናገር ቅድመ ፍጥረት ከአብ የተወለደ የሚለውን በመካድ አይደለም። የቄርሎስ ትክክለኛ አቋም ለመላው ዓለም እየታወቀ እንዲህ መዋሸት ለምን አስፈለገ? እስኪ እዚያው ክፍል ላይ ምን እንዳለ እንመልከት፦

የመለኮቱ መገኘት ከድንግል አይደለም፤ ከአብ ከተወለደ በኋላ ጥንታዊ (ቀዳማዊ) ልደትን ሊወለድ አልወደደም፤ ከአብ ጋር ከዘመን ሁሉ አስቀድሞ የነበረ፤ ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ስለሚሆን ስለእርሱ ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ጥንታዊ ልደትን ሁለተኛ እንደሻ ይነገር ዘንድ፤ ይህ ሐሰት ክህደትም ነው፤ ዳግመኛ በሥጋ እንደ ተወለደ፤ ስለእርሱ እንዲህ ይነገራል፤ እንደ ሰው ሁሉ አስቀድሞ ቅርጽ የተፈጸመለት ሰው ተገኝቶ ከዚህ በኋላ ቃል ያደረበት አይደለም፤ በእመቤታችን ማሕፀን እርሱ ብቻ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ በሥጋም ይወለድ ዘንድ ወደደ፣ በሥጋ መወለድን ለእርሱ ብቻ ገንዘብ ኣደረገ። ዮሐ፡፩፡፲፬ ፡፲፬። ገላ፬፡፬” (ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ መዕራፍ 43፡5)።

በቄርሎስ መሠረት ጌታችን ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደ መለኮት ሲሆን ከዚያ በተለየ ልደት በቤተልሔም ከድንግል ተወልዷል። ሁለቱ ልደቶች ለየ ቅል ናቸው። አንደኛው የአብ ባሕርይ ተካፋይ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን ሁለተኛው ወደ ፍጥረተ ዓለም በመግባት እኛን ለማዳን የመጣበት ነው። ከድንግል ማሕፀን የተገኘው ሥጋዊ ባህርዩ እንጂ መለኮቱ አይደለም። ይህንን ያልተረዳ ሰው ነገረ ክርስቶስ ላይ ለመጻፍ ብዕሩን ሲያነሳ ማየት አስቂኝ ነው። እዚያው ምዕራፍ ላይ ቄርሎስ እንዲህ ይላል፦

“ከፍጥረት ሁሉ በላይ በሆነ ባሕርይ ሞት እንደ ደረሰ የሚናገር ማንም ዐላዋቂ አይኑር ከቅድስት ድንግል ማርያም በተገኘ ሥጋ ሰው ሆነ ገንዘቡ ነውና ስለዚህ እኛ ተዋሕዶውን አምነን በመለኮቱ ሞት የሌለበት እርሱ ሰው እንደ መሆኑ በሥጋ ሞተ እንላለን። ዮሐ ፩፥፲፬። ሮሜ ፭፥፲። ፪፡ቆሮ ፭፥፲፬። አምላክ ሲሆን ሰው ሆነ ከጌትነቱም ክብር ፈጽሞ አልተለየም ምንም ሰው ቢሆን እርሱ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ነው፤ በመለኮቱ ሕግን የሠራ ሲሆን እነሆ ሕግን በመፈጸም ተገኘ ሕግን ሲሰጥ በነበረበት ባሕርይ ጸንቶ ኖረ። ገላ ፬፥፬። በመለኮቱ ገዥ ሊሆን የተገዥ ባሕርይን ገንዘብ አደረገ ግን የጌትነቱ ክብር ከእርሱ አልተለየም አንድ ሲሆን ለብዙዎች ምእምናን በኵር ሆነ (በትንሣኤ በዕርገት) በአንድነቱም ጸንተ ኖረ። ሮሜ ፰፥፳፱። ፊልጵ ፪፥፭-፰። ሰው እንደ መሆኑ በሥጋ ቢሞት የሚያስደንቅ አይደለም፤ እነሆ በመለኮቱ የማይሞት ነው ሐዋርያው ጳውሎስም በዚህ አንድ ጌትነት አብን በመምሰል ያለ ቃል እርሱ ለሞት እስከ መድረስ ደርሶ መከራውን እንደ ታገሠ ሞቱም በመስቀል እንደሆነ ተናገረ። ፊልጵ ፪፥፰ እና ፱። (ቁጥር 3-6)

በቄርሎስ ትምህርት መሠረት ክርስቶስ አምላከ-ወሰብ ነው። የተወለደው፣ መከራን የተቀበለውና የሞተው በሰውነቱ ነው። በመለኮቱ ግን ዘላለማዊና የከበረ ነው። እንዲህ የጌታችንን ክብር ከሚገልጽ ጽሑፍ አንዲት ሐረግ ቆንጥሮ በመውሰድ ማብራርያውን በመተው ቄርሎስ ክርስቶስን ፍጡር ያደረገ በማስመሰል መናገር በእውነቱ ከሆነ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው። ለመሆኑ ሙስሊም ኡስታዞች ሕዝባቸውን እንዲህ ማቄላቸው ተገቢ ነውን? ይህ ህሊና ቢስነት አይደለምን? መዋሸት ከሃይማኖት መምህር ይጠበቃልን? እኛስ ስለ እነርሱ አፈርን!

መዝሙር 110ን በተመለከተ የጥንት አበው የነበራቸው መረዳት ዘላለማዊ ልደቱን የሚገልጽ መሆኑን ነው። “ከሆድ ወለድሁህ” የሚለው አገላለጽ የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሚገልጽ ተምሳሌታዊ አገላለጽ ሲሆን ይህ ልደት ፍጥረትን የቀደመ መሆኑ “ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ” በሚለው አባባል ተገልጿል። አጥቢያ ኮኮብ የቀንን መምጣት የምታበስር በመሆኗ ቀድሞ መምጣትን ታሳያለች። በዘፍጥረት 1፡14 መሠረት ከዋክብት የጊዜ መለኪያዎች በመሆናቸው ከከዋክብት መቅደም የሚለው ለዘላለማዊነት ተምሳሌታዊ አገላለጽ ነው። ስለዚህ አባባሉ ቅድመ ፍጥረትን የሚያስገነዝብ ዘይቤ መሆኑ ግልጽ ነው። ጥቅሱ የሚለው “ወለድሁህ” እንጂ “እንድትወለድ አደረግሁህ” ባለመሆኑ ወላጁ ራሱ እግዚአብሔር ነው። እውነታው ይህ ከሆነ ደግሞ ኢየሱስ ቅድመ ፍጥረት በዘላለም ውስጥ ከአብ ባሕርይ የተገኘ ነው የሚለውን ትምህርት የሚደግፍ ክፍል መሆኑ ሊታበል የማይችል ነው። የጌታችን የቤተልሔም ልደት በሌሊት መሆኑ ሉቃስ ላይ ስለተጠቆመ “ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ” የተባለው ወደ ዓለም በመጣበት አመጣጡም ተገልጿል። ይህ ቅዱስ አውጉስጢኖስና ኢላርዮስን በመሳሰሉት ቀደምት አበው የሚደገፍ መረዳት ነው። ሙሉ ምዕራፉ ደግሞ የጌታችንን መለኮትነት የሚገልጽ መሆኑን ለማወቅ ይህንን ጽሑፍ ያንብቡ፦ አዶናይ የኾነው መሲሕ

ሙስሊም፦

ኢየሱስ ማሕፀን ውስጥ ሕይወት የተሰጠው ፍጡር ስለሆነ በሕይወት የሚኖረው በእግዚአብሔር ኃይል ነው፦

ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። 2 ቆሮንቶስ 13፥4

ኢየሱስ አብ ሕይወት ከሰጠው በኃላ ይሞት እና ድጋሚ ሕይወት እንደሚቀበል እራሱ ተናግሯል፦

ሕይወቴን “ዳግም” እወስድ ዘንድ አኖራታለውና ስለዚህ አብ ይወደኛል። διὰ τοῦτό με ὁ Πατὴρ ἀγαπᾷ ὅτι ἐγὼ τίθημι τὴν ψυχήν μου, ἵνα πάλιν λάβω αὐτήν. ዮሐንስ 10፥17

“ፓሊን” πάλιν ማለት “ድጋሚ” “ሁለተኛ” “ዳግም”again” ማለት ነው፥ ድጋሚ ሕይወቱን እንደሚቀበል መናገሩ በራሱ መጀመሪያ ሕይወት እንደተሰጠው አመላካች ነው። “አኖራታለውና” ማለቱ ወልድ ሕይወቱን በጽድቅ ለሚፈርደው ለአብ እንደሚሰጥ ነው፥ ነፍሱን ከሰጠ በኃላ ይሞታል። ከሞተ በኃላ “ድጋሚ” ሕይወትን ከአብ ይቀበላል፦

እኔ “በራሴ”(of Myself) አኖራለው እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ “ዳግምም” ልቀበላት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ። οὐδεὶς ἦρεν αὐτὴν ἀπ’ ἐμοῦ, ἀλλ’ ἐγὼ τίθημι αὐτὴν ἀπ’ ἐμαυτοῦ. ἐξουσίαν ἔχω θεῖναι αὐτήν, καὶ ἐξουσίαν ἔχω πάλιν λαβεῖν αὐτήν· ταύτην τὴν ἐντολὴν ἔλαβον παρὰ τοῦ Πατρός μου. ዮሐንስ 10፥18

ለወልድ ሕይወትን የሰጠው አብ እስከሆነ ድረስ ከአብ ውጪ ማንም ሕይወቱን አይወስዳትም፥ ወልድ ከአብ የተሰጠውን ሕይወት ለአብ፦ “ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለው” ብሎ ማኖር(መስጠት) ሆነ በትንሳኤ ዳግም(ድጋሚ) ሕይወትን መቀበል ስልጣን የተቀበለው ከአብ በትእዛዝ ነው። ወልድ ከራሱ ምንም ማድረግ የማይችል እና ሕይወት አልባ የነበረ ሆኖ ሳለ ሕይወት የተሰጠው ፍጡር ነው፥ አብ አስገኚ ወልድ ደግሞ ግኝት ከሆነ ከፈጣሪ ሕይወት የተሰጠው ማንነትና ምንነት እንዴት ይመለካል?

መልስ፦

ሙስሊሙ ጸሐፊ የግሪኩን ጽሑፍ ኮፒ አድርጎ የለጠፈ ቢሆንም የአማርኛ ትርጉም ያልተጠቀመውን ፍቺ የሰጠው ከምን ተነስቶ እንደሆነ አልገለጸም። እስካላብራራው ድረስ ግሪኩን መጥቀስ ለምን አስፈለገው? Λάβω (ላቦ) የሚለው ቃል “አንስቶ መውሰድ” ወይም “መቀበል” (take or receive) ተብሎ ሊተረጎም ቢችልም በአውዱ መሠረት መውሰድ የሚለው ፍቺ ነው የሚያስኬደው፤ ምክንያቱም ወልድ ሕይወቱን አሳልፎ መስጠትም ሆነ ዳግመኛ መውሰድ ሥልጣኑ እንደሆነ ይናገራልና፦

“ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” (ቁ. 17-18)

ጌታችን ይህንን የማድረግ ሥልጣን እንዳለው እየተናገረ ነው። በፈጣሪው ውዴታ የሚኖር ፍጡር በነፍሱ ላይ ሥልጣን እንዳለው እንዲህ በድፍረት ሊናገር ይችላልን? ሌሎች ፍጡራን ሲናገሩት አስደንጋጭና የአምላክን ሥልጣን ከመጋፋት የሚቆጠር ንግግር ለክርስቶስ ሲሆን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ቀላል መስሎ የሚታየው ለምን እንደሆነ ሊያስገርም ይችላል። ይህንን ሙስሊም ጸሐፊ የመሳሰሉት ግለሰቦች በምንም መንገድ የክርስቶስን አምላክነት ውድቅ ለማድረግ ጥረት ስለሚያደርጉ እንዲህ ያሉ ከባባድ ንግግሮችን እንደ ቀላል ለማለፍ በክህደት የጠየመው ህሊናቸው እምብዛም አይቸገርም። ለእውነት የወገነ ህሊና ያለው ግን እውነታውን ይገነዘባል። ክርስቶስ በዚህ ቦታ ነፍሱን በፈቃዱ አሳልፎ የመስጠትና መልሶ የማንሳት ሥልጣን እንዳለው ነው እየተናገረ ያለው። በገዛ ነፍሱ ላይ ሥልጣን የሌለው ፍጡር እንደሌለ ከተስማማን ክርስቶስ በገዛ ነፍሱ ላይ ሥልጣን እንዳለው የተናገረውን እንደ ማንኛውም ፍጡር ንግግር የምንቆጥረው ለምንድነው? ጌታችን የገዛ ነፍሱን ከሞት በኋላ እንደሚያስነሳ ሲናገር ይህ የመጀመርያው አይደለም፦

“ስለዚህ አይሁድ መልሰው። ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ። ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።” (ዮሐ 2፡18-22)

በዚህ ክፍል ጌታችን አይሁድ ቢገድሉት በሦስተኛው ቀን ራሱን እንደሚያስነሳ በመቅደሱ ምሳሌ ተናግሯል። ጌታችን ራሱን ማስነሳት ብቻ ሳይሆን በመጨረሻው ቀን ሙታንን የሚያስነሳው እርሱ እደሆነ በግልፅ ተናግሯል፦

“ኢየሱስም። ወንድምሽ ይነሣል አላት። ማርታም። በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው። ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።”

“ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና። ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው። ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። እንግዲህ አይሁድ። ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና። አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ። ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም። እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።” (ዮሐ. 6፡38-44)

ውድ አንባቢያን፣ እነዚህ አባባሎች በፍጡር ሊነገሩ የሚችሉ ናቸውን? በመጨረሻው ቀን ሙታንን የሚያስነሳው አምላክ ብቻ አይደለምን? በፍጥረት ሁሉ ነፍስ ላይ ሥልጣን ያለው ክርስቶስ እኛን ለማዳን በተካፈላት የሥጋ ሕይወቱ ላይ ሥልጣን የለውም ማለት ሐሰት መሆኑ ግልፅ አይደለምን? ክርስቶስ ጌታችን በድምጹ ብቻ ሙታንን መቀስቀስ የሚችል ሃያል መለኮት መሆኑን ይህ ሙስሊም ጸሐፊ ለሙግቱ መነሻ ያደረገው ያው ክፍል በግልፅ ይናገራል፦

ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ። አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና። የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”

ክርስቶስ አምላክ ካልሆነ አብ ሊከበርበት በሚገባው በዚያ ክብር ሊከበር እንደሚገባው ስለምን ተናገረ? ሙታንንስ በድምጹ ብቻ ሊቀሰቅስ የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው? ምናልባት “አብ ሥልጣን ስለሰጠው” የሚል ምላሽ ቀላል መስሎ ሊታይ ይችላል። ነገር ግን በአምላክ አንድነት የሚያምን ሰው የዚህ ምላሽ ድክመት ይገባዋል። አምላክ ሙታንን የማስነሳት የመጨረሻውን ተግባርና ፍርድ ለፍጡር ይሰጣል ብሎ ማለት በእስልምናም ሆነ በክርስትና ተቀባይነት የሌለው የክህደት ቃል ነው። ክርስቶስ መለኮታዊ ወልደ እግዚአብሔር ስለሆነ ብቻና ብቻ ነው ይህ ሥልጣን ሊኖረው የቻለው!

ማጠቃለያ

ክርስቶስ ጌታችን በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣቱ ሳብያ የኛን ድካም ተካፍሎ “በድካም ተሰቅሎአልና”፤ ስለ እኛ ሲል ደካማ መስሎ ቢመጣም “ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል” (2ቆሮ. 13፡4)፤ ምክንያቱም እርሱ የአብ የባሕርይ ልጅና ከእርሱ ጋር አንድ ሕይወት ያለው ነውና፦ “እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።” (1ዮሐ 5፡11-12)። ለዚህ ነው ቅዱሳት መጻሕፍት አምላክነቱን የሚያውጁት (ዮሐንስ 1፡1፣ ዮሐንስ 10፡30፣ 20፡28፣ ሮሜ 9፡5፣ ዕብራውያን 1፡8፣ ቆላስይስ 2፡9፣ ቲቶ 2፡13)። እርሱ ከአብ እኩል የሚመለክ መለኮት እንጂ ሙስሊሞች ሊክዱት እንደሚሞክሩት እንደ ማንኛውም ፍጡር አይደለም፦

“አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፥ በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ። በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ። አራቱም እንስሶች። አሜን አሉ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።” (ራዕይ 5፡11-14)።

በመለኮታዊ ክብር እንዲህ የከበረውን ጌታ ቅዱሳት መጻሕፍትን ባልተገባ ሁኔታ በማጣመም ለማቃለል የሚሞክር ሰው ምንኛ ምስኪን ነው! ከዚህ የከፋ የነፍስ ኪሳራ ከወዴት አለ? ውድ ሙስሊም ወገኖቼ፣ አንድ ጥቅስ እንኳ በአግባቡ ለመጥቀስ ሃቀኝነት በሚጎድላቸው እንደዚህ ባሉ ወገኖች ከመታለል ወጥታችሁ የእግዚአብሔርን ልጅ በሙሉ ክብሩ ተመልክታችሁ የነፍሳችሁ እረኛ ወደሆነው ወደ እርሱ ትመለሱ ዘንድ ጥሪ እናደርግላችኋለን! እግዚአብሔር አምላክ ይረዳችሁ ዘንድ የዘውትር ጸሎታችን ነው።


“አብ በራሱ ሕይወት እንደለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታል” የሚለው ከኢየሱስ አምላክነት አኳያ እንዴት ይታያል?


መሲሁ ኢየሱስ