ኢየሱስ አብ ከሆነ እነሆ ስህተቱ ከእግዜሩ ሆነ
አማን እንዳለ
በክርስትና ላይ በየጊዜው ከሚነሱ ኑፋቄዎች ውስጥ በጥንታዌው ስሙ ሰባሊዮሳዊነት በአሁኑ ደግሞ በኢትዮጵያ ለወጉ ራሳቸውን የኢትዮጵያ “ሐዋርያዊት” ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ “ዋንነስ ፔንቴኮስታሊዝም” በማለት የሚጠሩት ቤተ-እምነቶች ይገኛሉ። እነዚህ ወገኖች በብሉይ ሆነ በአዲስ ኪዳን የተገለጠው አንዱ እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ ሦስት አካላት እንዳሉት የሚቃወሙ ናቸው ወይንም በሙያዊ ስያሜው የቅድስት ሥላሴ ትምህርትን የሚቃወሙ ናቸው። በቅዱሳት መጽሐፍት የተገለጡት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የአንዱ አምላክ የመገለጫ መንገዶች ናቸው ብለውም ያምናሉ። በኢትዮጵያ የቤተ እምነቱ መስራች የነበሩት ቄስ ተክለማርያም ገዛኸኝ እንዲህ ይላሉ፦ “መለኮት ከዘላለም በአካል በባሕርይ በስም በግብር አንድ እንጂ ሁለት ወይም ሦስት አልነበረም። በሦስት መንገድ ግን ራሱን ለሕዝቡ ገልጾአል። በሦስት መንገድ የተገለጸበትም ምስጢር በአብነት በሥጋ ዓይን ሳይታይ በወልድነት በሥጋ እየታየ በመንፈስ ቅዱስነት እስትንፋሱን በሕዝቡ ልብ ውስጥ በማሳደር ተገልጦአል” (ኢየሱስን ማን ይሉታል በቢሾፕ ተክለማርያም ገዛኸኝ ግንቦት 1978 ዓ.ም ዕትም ገጽ 8 ትምህርት 2)።
ከላይ እንደተመለከተው አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የሚሉ ስሞችን የዚህ እምነት በሀገራችን ቀዳሚው ጀማሪና በሕይወት እያሉ ደግሞ አጠቃላይ Chairman የነበሩት ቄስ ተክለማርያም ግልጽ የሆነ ክህደትን አስቀምጠዋል። ይህ አንድ አካል የተባለው በእኚህ ሰው በዚያው ገጽ ላይ አብ እንደሆነ ተገልጿል። ስለዚህ አብ ራሱን እንደ አባት እንደ ልጅና እንደ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ሲገለጥ ነበር ማለት ነው። ኢየሱስ ከአብ ያልተለየ ነገር ግን በሥጋ ዓይን ሳይታይ ይኖር የነበረው እርሱ ራሱ በሥጋ ዓይን ሲገለጥ የተገጠበት የአዲስ ኪዳን ስም እንጂ ሌላ ምንም አይደለም ብለው ያምናሉ፣ ያስተምራሉም። ስለዚህ ኢየሱስ ሁለት ነገሮች አሉት ያ ማለት የማይታየው ማንነት (አብነት) እና የሚታየው ማንነት (ወልድነት) ማለት ነው። ስለዚህ ወልድ ማለት አብ የተገለጠበት “የሥጋው ሰውነት” ማለት ነው። ኢየሱስ ሰው መሆኑን ሲያወሱ ኢየሱስ ወልድ ተብሎ እንደተጠራ ይነግሩናል፤ ደግሞም ኢየሱስ አምላክ ነው ሲሉ ኢየሱስ አብ ነው ማለታቸው እንደሆነ ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ከሚጠቀሟቸው መጽሐፎችና ስብከቶች እንረዳለን።
እነዚህ ወገኖች ከሚያስተምሩት በተጻራሪ ኢየሱስ አብ እንዳልሆነ፣ ወልድ በራሱ የመለኮት ባሕርይ (Devine Nature) እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ከሁሉም በላይ በወንጌላትም ሆነ በመልዕክታት ውስጥ በግልጽ የተቀመጡ አያሌ ምንባባት አባት ልጁን በመላክ እንዳዳነን እንጂ አባት የራሱን ንግግር (ማንነት የሌለውን ቃል) ራሱ ወዳዘጋጀው ሰማያዊ ሥጋ ቀይሮ በዚያ ሥጋ ውስጥ አብ መምጣቱን አያስተምርም። እነዚህ ወገኖች እንዲህ ያለ ተራ እና ግልጽ ማደናገሪያ በመጠቀም ብዙዎችን በማሳት ላይ ይገኛሉ።
ኢየሱስ አብ ነው ብሎ ለማለት መጽሐፍ ቅዱስ እኛ በምንረዳበት መንገድ በሰው ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ እንዳልሆነ አስቀድሞ ማመንን የሚጠይቅ ትርጉም አልባ ንግግር ነው። ለምሳሌ በሰዋሰው ሕግጋት ውስጥ የመጀመሪያ መደብ ነጠላ ሲባል ንግግሩን የሚናገረውን ሰው ንግግሩን ከሚያደምጠው/ከሚያደምጡት የሚለይ ነው። በዚህ የቋንቋ ሕግ መሠረት ጌታችን የተናገረውን እንመልከት፦
የዮሐንስ ወንጌል 14፥15-17 (አመት)
“ብትወድዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ አብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን ታውቁታላችሁ።”
ጌታ ኢየሱስ በዚህ ስፍራ ራሱን “እኔ” በማለት በመጀምሪያ መደብ ነጠላ ሲጠቅስና ወደ አብ እንደሚጸልይ ሲናግር፤ አብንም “እርሱ” እያለ ሲጠቅስ እናያለን። መንፈስ ቅዱስንም ልክ እንደዚያው “እርሱ” ብሎ በሁለተኛ መደብ ነጠላ ስለጠቀሰና በአብ የሚላክ መሆኑን ስለተናገረ ኢየሱስ አብም መንፈስ ቅዱስም እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ከዚህ ንግግር በመነሳት የሦስቱን አካላት ልዩነት ካልተገነዘብን ከላይ እንዳልነው መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ዓይነት የስነ ቋንቋ ሕግጋትን የማይከተል የአላዋቂ ሰው ጽሁፍ ነው እንደማለት ነው። እንዲህ ያለ መረዳት ወንጌላት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውን ተግባቦት በተመለከተ በግልጽ ያስቀመጧቸውን ምንባባትን መቃወም ነው። ሌላ ጥቅስ እንመልከት፦
የማቴዎስ ወንጌል 3:16-17 (አመት)
“ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። 17እነሆ፤ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።”
በዚህ የወንጌላዊው ማቴዎስ ትረካ ውስጥ ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ የወረደ ሲሆን ይህንንም አስከትሎ ከተከፈተው ሰማይ አባት ስለ ልጁ የተናገራቸው ቃላት “በእርሱ” በሚል ሁለተኛ መደብ ተውላጠ ስም ተቀድመዋል። በዚህም ተናጋሪውና የሚነገርለት ሁለት አካላት እንዳሉ ከቋንቋ ሕግ እንረዳለን። “በእርሱ ደስ የሚለኝ” እና “የምወደው” በማለት ልጁን የገለጸው አካል እንዴት መልሶ ደግሞ ያንኑ ልጅ ሊሆን ይችላል? አባት ልጅን በእርሱ ደስ እንደሚለው ከተናገረና ቀጥሎ “የምወደው” ብሎ ካለ በእነዚህ ሁለት አካላት መካከል ግልጽ የሆነ ግንኙነት አለ ማለት ነው። ይህም ማለት አባት በልጅ ደስ ይሰኛል ደግሞም ይወደዋል ማለት ነው። በተጨማሪም አባት የሚታወቅበት የራሱ ማንነት እንዳለው ሁሉ ልጅም የሚታወቅበት የራሱ ማንነት አለው ማለት ነው። አብና ወልድ አንድ ማንነት ብቻ ከሆኑ እንዴት አብ ወልድን “የምወደውና በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ” ሊለው ይችላል? እንደ ሰባልዮሳውያን ከተረዳነው ይህ ንግግር ለራስ የተነገረ ማሞካሻ መሆኑም አይደል? አንድ ተጨማሪ ጥቅስ እንመልከት፦
የማቴዎስ ወንጌል 11:27 (አመት)
“ሁሉ ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም።”
ወልድ የሚታወቅበት ማንነት አለው፤ ይህንን የሚያውቀው አብ ብቻ ነው (ሌላ የለም ተብሏል)። አብ የሚታወቅበት የራሱ ማንነት አለው፤ በዚህ ማንነቱ ወልድና ወልድ በራሱ ፈቃድ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን ማንም አያውቅም። ወልድ አብ የተገለጠበት ሥጋ ከሆነና የራሱ ማንነት የሌለው ነገር ከሆነ አብ ብቻ ስለወልድ ያውቃል፤ ወልድ ፈቅዶ አብን ይገልጣል የሚለውን የጌታን ንግግር እንዴት እንረዳው? ይህ እጅግ ከባድና ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አለን ማለት አይሆንምን?
ቅዱሳት መጽሐፍት ዋና አላማቸው ቅዱሳን ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው የጻፉትን የእግዚአብሔርን ፈቃድ፣ ሐሳብና ማንነት እንድንረዳ በመሆኑ ሳብያ የሰው ልጆች መግባቢያ በሆኑት ቋንቋዎች ተጽፈውልናል። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል በሰው ቃል የተባለው። የቅዱሳት መጻሕፍት የቃላት አጠቃቀምና ሰዋሰው ፊት ለፊት በሚታየው ሁኔታ ትርጉም የሚሰጥ ካልሆነና “ኢየሱስ የአብ ልጅ ነው” ተብሎ የተጻፈውን “ኢየሱስ የገዛ ራሱ ልጅ ነው” ብለን መረዳት ትክክል ከሆነ፤ “ኢየሱስ አብ ነው” የሚለው “የኢየሱስ ብቻ” ትምህርት ተሳስቶ ያሳሳተን እራሱ እግዚአብሔር ነው እንድንል የሚያስገድድ ነው። ይህ ደግሞ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፤ ሰዎች ሁሉ መዳንን ያገኙ ዘንድ መልካም ፈቃዱ የሆነው የእግዚአብሔር ባሕርይ አይደለም። ሁሉን አዋቂ ከሆነው ከእርሱ ዘንድ የመጣው ቃሉም በዚህ ልክ ሰዎችን ግራ ወደ መጋባት የሚመራ የሰዋሰው ችግር ያለበት ጽሑፍ ሊሆን ከቶ አይችልም። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ልጅ እንጂ የገዛ ራሱ ልጅ አይደለም።
2ዮሐንስ 1፡3 (አመት)
“ከእግዚአብሔር አብና የአብ ልጅ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናል።”