መለኮታዊው ቃል – የዮሐንስ 1፥1 የጽርዕ ማብራሪያ

መለኮታዊው ቃል

የዮሐንስ 1፥1 የጽርዕ ማብራሪያ

በወንድም ሚናስ


“በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።”  — ዮሐንስ 1፥1
Ἐν ἀρχῇ ἦν ὁ λόγος, καὶ ὁ λόγος ἦν πρὸς τὸν θεόν, καὶ θεὸς ἦν ὁ λόγος.

ሀ. “በመጀመሪያ ቃል ነበረ”

Ἐν ἀρχῇ ἦν ὁ λόγος

የዮሐንስ 1፥1 ዋና ባለቤት (Subjective Nominative)  የሆነው፣ ቃል (ὁ λόγος “ሆ ሎጎስ”) መሙያን የወሰደው፣ ኢርቱዕ ተሳቢ ሙያ(Dative Case)  መስተዋድዳዊ ንኡስ ሐረግ ከሆነው ከ Ἐν ἀρχῇ “ኢን አርኬ” ነው፣ ትርጉሙም “በመጀመሪያ” የሚል ነው፤  ይኽ መጀመሪያ  ደግሞ የሎጎስ ህላዌ ነው። ህላዌውን የገለፀው ደግሞ ἦν “ሄን” በምትል የኑረት ግስ ነው፤ ትርጕሙም “ነበር” የሚል ይሆናል። ዮሐንስ የቃልን  ፍጡርነት ለማስተላለፍ ቢፈልግ ኖሮ፣ ἦν “ሄን” ከሚለው የኑረት ግስ ይልቅ፣ የ γίνομαι “ጊኖማይ” ማዕከላይ ግስ የሆነውን፣ ἐγένετο “ኤጌኔቶ”(ሆነ፤ተደረገ) የሚባለውን የድርጊት ግስን በተጠቀመ ነበር። ሆኖም ግን ቅዱስ ዮሐንስ  በቍጥር 3፤6፤ እና 14 ውስጥ ἐγένετο “ኤጌኔቶ” የሚለውን የድርጊት ግስ ሲጠቀም፣ የሎጎስን ኑረት በሚገልጽበት ቁጥሮች ማለትም፣ በቊጥር 1፤ 2፤4፤ እና10  ἦν “ሄን” የሚለውን፣ የኑረት ግስን ይጠቀማል። ይኽውም ቃል(λόγος) ሀልዎቱ ጅማሬ ያለው ፍጡር ሳይሆን ዘለዓለማዊ መሆኑን በግልጽ አመልካች ነው።

ለ. “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር”
   καὶ ὁ λόγος ἦν πρὸς τὸν θεόν

ይኽ ክፍል ደግሞ የሚነግረን፣ ቃል (ሎጎስ λόγος) እምቅድመ -ዓለም በዘለዓለማዊ ህላዌ ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ እንደነበር ነው። ይኽውም ፣ በአማርኛ “ዘንድ/ጋር” ያሉት በጽርዑ πρός “ፕሮስ” የሚለው ቃል በተሳቢ ሙያ በመቀደሙ ነው። የጽርዕ ሰዋስውን ዋቢ በማድረግ ሥላሴያውን የምናቀርበው ሙግት አማርኛ ተርጓሚዎች “ዘንድ/ጋር” ያሉት በእንግሊዘኛው “With”  በግሪኩ πρὸς “ፕሮስ” የምትለው ቃል በተሳቢ ሙያ (Objective case) ሲቀደም ሁልጊዜ አካላዊ አብርኦት/ግንኙነትን የሚያመለክት ነው።

No description available.

በግርጌ ማስታወሻ ላይ የሰፈሩትን የአዲስ ኪዳን ግሪክ የሰዋስው መማሪያ መጻሕፍት[1] እንዲመለከቱ እየጋበዝኩ በመጽሐፍ ቅዱስም አማርኛ ተርጓሚዎች “ዘንድ/ጋር” ያሉት በግሪኩ πρὸς “ፕሮስ” የሚለው ቃል በተሳቢ ሙያ(Objective Case) ከተቀደመ እንዴት አካላዊ መስተጋብርን እንደሚያመለክት  መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማሳያዎችን አቀርባለሁ፦

ማሳያ አንድ፦
“በርግጥ በእናንተ ዘንድ በነበርንበት ጊዜ መከራ እንደሚደርስብን በየጊዜው እንነግራችሁ ነበር፤ እንደምታውቁትም እንዲሁ ደግሞ ሆኖአል።”
  — 1ኛ ተሰሎንቄ 3፥4
καὶ γὰρ ὅτε πρὸς ὑμᾶς ἦμεν, προελέγομεν ὑμῖν ὅτι μέλλομεν θλίβεσθαι, καθὼς καὶ ἐγένετο καὶ οἴδατε.

ይህንን ዓረፍተ ነገር የተናገረው ቅዱስ ጳውሎስ ነው። “እኛ በእናንተ ዘንድ ሳለን” እያለ ነው፡፡ እኛ የሚለው እራሱንና  ከእርሱ ጋር የነበሩትን አገልጋዮች መሆኑ እሙን ነው። “እናንተ” የሚለው ደግሞ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖችን ነው። ስለዚህ እያወራ ያለው ስለ ኹለት ወገኖች መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ማሳያ ሁለት፦
1ኛ ቆሮ 2፥3፦“እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ”

κἀγὼ ἐν ἀσθενείᾳ καὶ ἐν φόβῳ καὶ ἐν τρόμῳ πολλῷ ἐγενόμην πρὸς ὑμᾶς

በዚህም ምሳሌ “ዘንድ” የሚለው ቃል የተተረጎመው ፕሮስ (πρὸς) ከሚለው የጽርዕ ቃል ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ በእናንተ ዘንድ ነበርሁ” በማለት ይናገራል። ስለዚህ ይኽ ምንባብ የሁለት አካላትን አብሮነት በሚያሳይ መልኩ ግልጋሎት ላይ እንደዋለ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። በተጨማሪም በዚህ ክፍል ላይ “እኔ በእናንተ ዘንድ ነበርሁ” የሚለው ዓረፍተ ነገር ዮሐንስ 1፥1 ላይ ካለው “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ከሚለው ዓረፍተ ነገር ጋር  ተመሳሳይ መሆኑን ልብ ይሏል።

ማሳያ ሦስት፦
ዮሐንስ በወንጌሉ ብቻ ሳይሆን በመጀመሪያ መልዕክቱም ሎጎስ ከአብ የተለየ አካል መሆኑን፣ πρὸς “ፕሮስ” + ተሳቢ ሙያ፣ በመጠቀም የዮሐንስ 1፥1ን ሐሳብ በደንብ ያረጋግጥልናል።

በመጀመሪያ (ἀρχῇ) ቃል(λόγος) ነበረ(ἦν)፤ ቃልም በእግዚአብሔር (አብ) ዘንድ (πρὸς τὸν θεόν)ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ።”
  — ዮሐንስ 1፥1

1ኛዮሐንስ 1፥1-2 “ስለ ሕይወት ቃል (λόγου) ከመጀመሪያው (ἀρχῆς)  የነበረውን (ἦν)፣ የሰማነውን በዓይኖቻችን ያየነውን፤ በአብ ዘንድ የነበረውን (πρὸς τὸν πατέρα)፣ ለእኛም የተገለጠልንን የዘላለም ሕይወት እንነግራችኋለን”

ከላይ ባሉት ትይዩ ጥቅሶች ዮሐንስ በወንጌሉ እና በመልዕክቱ ተመሣሣይ የሰዋስው አወቃቀር በመጠቀም የሎጎስን ቅድ ህልውና እየገለፀ መሆኑን ያስተውሉ፤ በሁለቱም ቦታዎች ἀρχῇ “አርኬ” የሚለውን መስተዋድድ በማያቋርጥ የኅላፊ ግስ (ἦν “ሂን”) ጋር በመታጀብ የሎጎስ አካላዊ ቅድመ-ህልውና ይነግረናል። እንዲሁም በሁለቱም ጥቅሶች πρὸς “ፕሮስ” የሚለውን ቃል ከተሳቢ ሙያ ጋር በመጠቀም ሎጎስ ከአብ (እግዚአብሔር የተለየ) አካል መሆኑን ይናገራል። በተጨማሪም በዮሐንስ 1፥1 ላይ የተጠቀሰው ቃል (λόγος) በመልዕክቱ ላይ ክርስቶስ ኢየሱስ መሆኑን በግልጽ እንረዳለን።

በአጠቃላይ “ፕሮስ” (πρὸς) የሚለው፣ የጽርዕ መስተዋድድ በተሳቢ ሙያ ተቀድሞ አብሮነትን የሚያሳይ መሆኑን ለማሳየት ከዚህ በላይ መድከም አያስፈልግም። ከላይ ባየናቸው ምሳሌዎች ውስጥ “ፕሮስ” የሚለው የጽርዕ መስተዋድድ፣ በሁለት የተለየዩ አካላትን አብሮነት ለማሳየት እንዴት ግልጋሎት ላይ እንደሚውል ተመልክተናል። በአጠቃላይ ከዚህ ክፍል የምንረዳው፣ ቃል(ሎጎስ) አካል መሆኑንና፣ ከእግዚአብሔር ጋር እምቅድመ-ዓለም ያለ ጅማሬ የነበረ መሆኑን ነው[1]። 

ሐ.“ቃልም እግዚአብሔር ነበር”
καὶ θεὸς ἦν ὁ λόγος.

በ “ሀ”  እና “ለ” ጥናታችን ቃል (λόγος “ሎጎስ”) ያለ ጅማሬ እንደነበረ፣ ይኽም ሀልዎት ከአባቱ ጋር እምቅድመ-ዓለም እንደሆነ ተመልክተናል። በዚህኛው ጥናታችን ደግሞ፣  ከአባቱ ጋር ያለ ጅማሬ የነበረውን ቃል ልክ እንደ አባቱ አምላካዊ ባሕሪይ፣ የተላበሰ መሆኑን እንመለከታለን፦

καὶ θεὸς ἦν ὁ λόγος.
“ካይ ቴኦስ ሄን ሆ ሎጎስ”

የአማርኛ ቅጆች “እግዚአብሔር” ብለው የተረጎሙት ቃል፣ θεὸς “ቴኦስ” የሚል ሲሆን፣ ከፊቱ ላይ ምንም አይነት አመልካች መስተኣምር (Definite article) የለውም፤ ቃል (ሎጎስ λόγος) ላይ ደግሞ ὁ “ሆ” የምትል አመልካች መስተኣምር (Definite Article) ከፊቱ ተቀምጧል። ስለዚህ የዓረፍተ ነገሩ ዋናው ባለቤት(Subjective Nominative) ቃል  (λόγος ሎጎስ) ሲሆን፣ አምላክ ተብሎ የተተረጎመው “ቴኦስ” θεὸς ደግሞ፣  ስለ ቃል (ሎጎስ) ተጨማሪ ማንነት የሚናገር መሙያዊ ባለቤት(Predicate Nominative) ነው። በቀላል አማርኛ ὁ “ሆ” የምትለው የግሪክ መስተኣምር (በእንግሊዘኛው ‘The’) የገባው ከ λόγος  “ሎጎስ” ፊት ለፊት ብቻ ነው። Θεὸς“ቴዎስ” ፊት ለፊት ምንም አይነት መስተኣምር አልገባም። ስለዚህ በግሪክ ሰዋሰው ህግ ዓረፍተ ነገሩ መተርጎም ያለበት “እግዚአብሔርም ቃል ነበረ” ሳይሆን “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ተብሎ ነው። ለምሳሌ በዮሐ 4፥24 “እግዚአብሔር መንፈስ ነው (ግሪክ Πνεῦμα ὁ Θεός, “ፕኔውማ ሆ ቴኦስ”) በሚለው ክፍል፣ በቀጥታ የግሪኩ አቀማመጥ ከተረጎምነው   “መንፈስ እግዚአብሔር ነው” የሚል ነው። ሆኖም ግን፣ “መንፈስ እግዚአብሔር”  ነው ብለን መተርጎም የማንችልበት ምክንያት ὁ “ሆ” በእንግሊዘኛው “the” የምትለዋ አመልካች መስተኣምር የገባችው ከእግዚአብሔር (ቴዎስ “Θεός”) ፊት ለፊት ብቻ ነው። ስለዚህ በጽርእ የሰዋስው ሕግ መሠረት፣ ቃሉ መተርጎም ያለበት “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ተብሎ ነው፣ እንጂ “መንፈስ እግዚአብሔር ነው” ተብሎ ሊተረጎም አይችልም፤ ስለዚህም፣ በዮሐንስ 4፥24 የምንረዳው፣ ማንነቱ (Subjective Nominative) እግዚአብሔር ሲሆን፣ ምንነቱ (Predicate Nominative) ደግሞ መንፈስ ይሆናል። በተመሣሣይ በዮሐንስ 1፥1 ላይም ያለው ዓረፍተ ነገር “እግዚአብሔርም ቃል ነበረ” ተብሎ ሊተረጎም የሚችልበት ምንም አይነት ሰዋስዋዊ አገባብ የለም። ምክንያቱም የግሪኩ ሰዋስው እንደሚነግረን ማንነቱ ቃል (Subjective Nominative)፣ ምንነቱ (Predicate Nominative) ደግሞ አምላክነት ይሆናል[3]። ይህን የግሪክ ሰዋስውን ዋቢ ያደረገ ትንታኔ የማይዋጥላቸው፣ አርዮሳውያን (ለምሳሌ፣ “የይሖዋ ምስክሮች”) ያለ ምንም ተጨባጭ ሰዋስዋዊ ማስረጃ፣  ቃል (ሎጎስን) የሚያመለክተው “ቴኦስ” (አምላክ) ምንም አይነት መስተኣምር (Definite article)  የለውም፤ ይኸውም ገላጭነትን አሊያም ወኪልነት እንጂ ቃል በኑባሬው አምላክ አለመሆኑን ያሳያል ይላሉ። የሥላሴ አማኒያን ከላይ ያቀረብነውን የሰዋስው ሙግት በደንብ እንዲያጤኑ በመጋበዝ አብ  ልክ እንደ ዮሐንስ 1፥1 ላይ ኢየሱስ አምላክ እንደተባለ ያለ ምንም መስተኣምር ቴኦስ የተባለበትን ከታች የሚገኙትን ጥቅሶች እንዴት እንደሚረዱት እንጠይቃለን፦

ማሳያ አንድ፦
“ሁሉም ለእርሱ ሕያዋን ስለሆኑ፣ እርሱ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አይደለም።””
  — ሉቃስ 20፥38 (አዲሱ መ.ት)
θεὸς δὲ οὐκ ἔστιν νεκρῶν ἀλλὰ ζώντων, πάντες γὰρ αὐτῷ ζῶσιν.

ማሳያ ሁለት፦
“ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ራሴን ባከብር፣ ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ ግን እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው።”
  — ዮሐንስ 8፥54 (አዲሱ መ.ት)

… ὃν ὑμεῖς λέγετε ὅτι θεὸς ὑμῶν ἐστιν,

ከላይ በሚገኙት ሁለት ማሳያዎች ልክ ዮሐንስ 1፥1 ላይ ቃል (ሎጎስ) አምላክ በተባለበት አገባብ ማለትም ምንም አይነት ውስን መስተኣምር (Definite Article) ሳይኖር ለአብ ግልጋሎት ላይ ውለው እናገኛለን። የአብ አምላክነት በገላጭነት ወይም በወኪልነት ነው ይሉን ይሆን?

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ በዮሐንስ 1÷1 ላይ ለማለት የተፈለገው፣ ቃል በእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደ ነበረ፣ እንዲሁም ቃል ራሱ የእግዚአብሔር ባሕርይ (Essence) እንዳለው ነው፡፡


[1] Greek Grammar Beyond the Basics: An Exegetical Syntax of the New Testament ገጽ 381,  A Manual Grammar of the New Greek Testament H.E. Dana , Julius R. Mantey ገጽ 110
[2] Greenlee, Exegetical Grammar, 39.
[3] Daniel B. Wallace, Greek Grammar Beyond the Basics: An Exegetical Syntax of the New Testament, Zondervan, 1996,  pp. 41-46. William D. Mounce. Basics of Biblical Greek. Zondervan, 1993, p. 28-29.


መሲሁ ኢየሱስ