የኢየሱስ አምላክነት በይሁዳ መልዕክት

የኢየሱስ አምላክነት በይሁዳ መልዕክት

ወንድም ሚናስ


የይሁዳ መጽሐፍ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ካሉት እጅግ አጫጭር መጻሕፍት መካከል አንዱ ሲሆን አንድ አጭር ምዕራፍ ብቻ የያዘ አነስተኛ መጽሐፍ ነው፤ ሆኖም  በእነዚህ ጥቂት መስመሮች ውስጥ ይሁዳ ስለ ክርስቶስ መለኮትነት በአጽንዖት ሲገልጽ እናነባለን።

ቍጥር ዐራት፦

ረጅም ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና፤ እነርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ የአምላካችንን ጸጋ በርኵሰት የሚለውጡና እርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።” (አ.መ.ት)

παρεισεδύησαν γάρ τινες ἄνθρωποι, οἱ πάλαι προγεγραμμένοι εἰς τοῦτο τὸ κρίμα, ἀσεβεῖς τὴν τοῦ θεοῦ ἡμῶν χάριτα μετατιθέντες εἰς ἀσέλγειαν καὶ τὸν μόνον δεσπότην καὶ κύριον ἡμῶν Ἰησοῦν Χριστὸν ἀρνούμενοι.

ግራንቪል ሻርፕ የተሰኘ የግሪክ ቋንቋ ሊቅ ለይቶ ካስቀመጣቸው የግሪክ ሰዋስው ሕግጋት መካከል አንዱ በሆነው ሕግ  1 መሠረት ይሁዳ ከላይ ባነበብነው ጥቅስ፣ “ገዣችንና ጌታችን” ብሎ የሚገልጸው አንዱን አካል ይኸውም ኢየሱስን መሆኑን እንረዳለን። ሕጉ እንደሚለው “በዋናው የግሪክ አወቃቀር (ትርጉም ባልሆነ ግሪክ) “ካይ” በሚል መስተጻምር የተያያዙ ሁለት ስሞች አንድ መስተኣምር ከፊታቸው ከገባ እና ሁለቱም ባሕርይ ገላጮች (1) በሰዋሰውም ሆነ በቃል ደረጃ ነጠላ ከሆኑ (2) ማንነታዊ ከሆኑ (ህልውና ያላቸውን አካላት አመልካች ከሆኑ) እና (3) የወል ስሞች ከሆኑ (የተጸውዖ ስሞች ወይንም ቅደም ተከተላዊ ካልሆኑ) አንድን አካል ያመለክታሉ፡፡” በዚህ መሠረት τὸν μόνον δεσπότην καὶ κύριον ἡμῶν Ἰησοῦν Χριστὸν (ቶን ሞኖን ዴስፖቴን ካይ ኩሪዮን ሄሞን ኢዬሱን ክሪስቶን)  በሚለው ውስጥ “ዴስፖቴን” (ገዣችን) እና “ኩሪዮን” (ጌታችን) የሚሉት ባሕርይ ገላጮች “ቶን” በሚል አንድ መስተአምር የተቀደሙና “ካይ” በሚል መስተጻምር የተያያዙ በመሆናቸው ሕጉን ያሟላሉ፤ እናም በዚህ ቦታ “ገዣችን እና ጌታችን” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በተጨማሪም፣ በዐውደ-ምንባቡ ውስጥ  ብቸኛ አምላክ የተባለው አብ፣ በብቸኛው ጌታ  በክርስቶስ በኩል አኮቴት እንደሚቀርብለት ይናገራል (ቍጥር 25)፤ ይኽውም ይሁዳ ብቸኛ አምላክ የሚለውን ቅጽል ለአብ፣ “ብቸኛ ጌታ” የሚለውን ደግሞ ለወልድ ይጠቀማል ማለት ነው። ታዲያ በዚህ ጥቅስ ውስጥ “ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው” የሚለውን የመጨረሻ ሐረግ አሁንም በጥንቃቄ ማስተዋል አስፈላጊ ነው። “ገዣችን” ተብሎ የተተረጎመው የጽርእ ቃል δεσπότην “ዴስፖቴን” የሚል ሲሆን፣ δεσπότης “ዴስፖቴስ” ከሚል የጽርእ ቅጽል የመጣ ነው። በዚኽ ቅጽል የሚጠራ ግለሰብ፣ በአንድ ማሕበረሰብ ወይም ቤተሰብ የበላይ መሪ ወይም ከሁሉም የላቀ ሥልጣን ያለው አካልን ለማመልከት የሚገባ ቃል ነው[1]። በይበልጥ ደግሞ ይኼ ቅጽል በሮማውያን ባሕል ውስጥ ያለው ሥልጣን እጅግ የላቀ ነው፤ ይኸውም የአንድ ቤተሰብ ራስና ባለ ሙሉ ሥልጣን ከመሆኑ የተነሳ፣ የአብራክ ልጆቹ ምን ትልቅ እና ራሳቸውን የቻሉ ቢሆኑ እንኳ ሥነ ምግባራቸው ደስ ካላሰኘው እስከ መግደል የደረሰ ሕጋዊ መብት አለው[2]። ይሁዳ ይኽንን ቃል የተጠቀመው በብሉይ ኪዳን ስመ-ያህዌን ወክሎ ለእልፍ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለውን “ጌታ” በጽርእ  κύριος “ኩሪዮስ” ከሚል ቃል ጋር በማጣመር ነው። እነኚህ ኹለት ቅጽሎች ማለትም፣ δεσπότην “ዴስፖቴን” እና  κύριον “ኩሪዮን” በአንድ ላይ ተያይዘው የቀረቡት እውነተኛውን አምላክ ያህዌን ለመግለጽ መሆኑን የብሉይ ኪዳን የሰብዓ ሊቃናት ትርጉምን (LXX)  ስንመለከት እንገነዘባለን። ለምሳሌ፦

“አብራምም፣ “ገዢ ጌታ ሆይ (Δέσποτα Κύριε)፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለሁ?” አለ።”
  — ዘፍጥረት 15፥8 LXX

“እኔም፣ “ጌታ ገዢ ሆይ (δέσποτα Κύριε)   ፤ ሰይፍ አንገታቸው ላይ ተቃጥቶ ሳለ፣ ‘ሰላም ይሆንላችኋል’ ብለህ ይህን ሕዝብና ኢየሩሳሌምን ለምን እጅግ አታለልህ?” አልሁ።”
  — ኤርምያስ 4፥10 LXX

“ስለዚህ የሠራዊት ገዢ (δεσπότης)  ጌታ (Κύριος) እንዲህ ይላል፦ ለእስራኤል ኃያላን ወዮላቸው። ቍጣዬ በጠላቶቼ ላይ አይወገድምና፥ በጠላቶቼም ላይ ፍርድን አደርጋለሁ” ኢሳይያስ 1፥24 LXX

ኢየሱስ የኛ ብቸኛ ገዢ እና ጌታ ሊሆን የሚችልበት ብቸኛው መንገድ እርሱ ያህዌ አምላክ ከሆነ ብቻ ነው።

ቍጥር አምስት፦

“ምንም እንኳ አስቀድማችሁ ይህን ሁሉ የምታውቁ ቢሆንም፣ ኢየሱስ  ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዴት እንዳወጣ፣ በኋላ ግን ያላመኑትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።”
  — ይሁዳ 1፥5 (ESV)
Ὑπομνῆσαι δὲ ὑμᾶς βούλομαι, εἰδότας ἅπαξ πάντα ὅτι Ἰησοῦς  λαὸν ἐκ γῆς Αἰγύπτου σώσας τὸ δεύτερον τοὺς μὴ πιστεύσαντας ἀπώλεσεν,

አንዳንድ የግሪክ የእጅ ጽሑፎች “ኢየሱስ” የሚለውን “ጌታ ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዴት እንዳወጣ” ይላሉ፤ ነገር ግን በቍጥር 5 ላይ ጌታ ብለው  የጠቀሱት ክርስቶስ መሆኑን በመካድ አይደለም፤ ምክንያቱም፣ በቍጥር 4 ላይ፣ ብቸኛ ጌትነቱ የተነገረለት ኢየሱስ ነው፤ ሆኖም ግን በቊጥር 5 “ጌታ” የሚለው ቀዳማይ የግሪክ ዕደክታብ ኮዴክስ ሳይናቲከስ ሲሆን፣ ከእርሱ በዕድሜም ሆነ በጥራት ቀዳማይና ተመራጭ የሆነው ኮዴክስ ቫቲካነስ “ኢየሱስ” ይላል። ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ ላይ እንደገለጥነው በአዲስ ኪዳን የምንባባዌ ሕያሴ ሊቃውንት (New testament textual critics ) ዘንድ ከሳይናቲከስ ይልቅ ቫቲካነስ ይበልጥ ተቀባይነት አለው[3]፤ እንዲሁም፣ እንደ አርጌንስ፣ ቆጵርያኖስ፣ ጀሮሜ፣ ወዘተ. ያሉ ቀደምት የቤተክርስቲያን አበው ይሁዳ 1፥5ን በሚጠቅሱበት ጊዜ “ጌታ” ከሚለው ቃል ይልቅ “ኢየሱስ” የሚለውን በጽሑፋቸው ውስጥ ተጠቅመዋል። ይበልጡኑ ደግሞ ፓፒረስ 72 በመባል የሚታው የይሁዳ መልዕክት የመጀመሪያው የእጅ ጽሑፍ፣  “አምላክ ክርስቶስ” (θς χρς) በማለት “ኢየሱስ” ለሚሉት ዕደክታባት  ጥሩ ግብአት ሆኗቸዋል።

ፓፒረስ 72

ክርስቶስ ሕዝቡን ከግብፅ ማውጣቱን በተመለከተ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ተመሳሳይ ሐሳብ አንጸባርቋል፦

“ወንድሞች ሆይ፥ ይህን ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። አባቶቻችን ሁሉ ከደመና በታች ነበሩ ሁሉም በባሕር መካከል ተሻገሩ፤ ሁሉም ሙሴን ይተባበሩ ዘንድ በደመናና በባሕር ተጠመቁ፤ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መብል በሉ፥ ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና፥ ያም ዓለት ክርስቶስ ነበረ።” (1ቆሮ. 10፥1-4)

በብሉይ ኪዳን ሕዝቡን ከግብፅ ምድር ያወጣው፣ የእስራኤል አምላክ ጌታ እግዚአብሔር መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ደጋግመው የሚነግሩን እውነት ነው፤ የተወሰኑትን ለመመልከት ያህል፦

“የከነዓንን ምድር ልሰጥህና አምላክህ (ኤሎሂም) ልሆን፣ ከግብፅ ያወጣሁህ እኔ ያህዌ ኤሎሂም ነኝ።”
  — ዘሌዋውያን 25፥38

ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ በዓመት በዓላችሁ ቀን ታደርጉ እንደ ነበረው ሁሉ፣ እንደ ገና በድንኳኖች እንድትቀመጡ አደርጋችኋለሁ።”
  — ሆሴዕ 12፥9

““እኔ ግን ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፤ ከእኔም በቀር ሌላ አዳኝ የለም።”
  — ሆሴዕ 13፥4

ክርስቶስ ጌታችን ሕዝቡን ከግብፅ ያወጣው ያህዌ ነው!


ሥላሴ በይሁዳ መልዕክት

ሐዋርያው ይሁዳ ስለ ኢየሱስ ያህዌ መኾን ሲናገር ልክ ዘመነኞቹ “የሐዋርያት ቤተክርስቲያን” እንደሚያምኑት ኢየሱስ አብ ነው እያለ አለመሆኑን በዚሁ ምዕራፍ አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስን ለይቶ በመግለጽ የሐሰተኞቹ የእምነት አቋም ትክክል አለመሆኑን ግልጽ አድርጓል።

ይሁዳ 1፥20-21 “እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፤ እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ (ἐν πνεύματι ἁγίῳ προσευχόμενοι) ። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሳችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት (τὸ ἔλεος τοῦ κυρίου ἡμῶν Ἰησοῦ Χριστοῦ)  ስትጠባበቁ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር (ἐν ἀγάπη θεοῦ) ራሳችሁን ጠብቁ።”

ይሁዳ አብ፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ለይቶ መግለጽ ብቻ ሳይሆን፣ ዘለዓለማዊው  ቅዱሱ እምነታችን በእነዚህ መለኮታዊ አካላት ላይ የተመሠረተ መሆኑንም እየነገረን ነው። ስለዚህ የይሁዳ መልዕክት የክርስቶስ የጌታችን መለኮትነት የሚክዱትን ወገኖች ብቻ ሳይሆን ሦስቱን የሥላሴ አካላት (ማንነቶች) በመካድ አንድ ማንነት ብቻ የሚሉትንም ወገኖች ትክክል አለመሆናቸውን የሚያሳይ ታሪካዊውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የሥላሴ አስተምህሮ የሚያጸና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው።


ማጣቀሻዎች
[1] Richard Bauckham, Jude and the early relative of Jesus in the Early Church ገጽ 303-304
[2] Ann Shelton, As the Romans Did: ገጽ 17
[3]J.K.Elliot, New Testament Textual Criticism: The Application of Thoroughgoing Principles, ገጽ 65

መሲሁ ኢየሱስ