የይሖዋ ምስክሮች የደም ልገሳ ፖሊሲ መጽሐፍ ቅዱሳዊና አመክንዮአዊ ነውን?

የይሖዋ ምስክሮች የደም ልገሳ ፖሊሲ መጽሐፍ ቅዱሳዊና አመክንዮአዊ ነውን?


የይሖዋ ምስክሮች ደም ላለመውሰድ የሚከፍሉት መስዋዕትነት በብዙዎች ዘንድ የጽናት ምሳሌ ተደርጎ ቢታይም የፖሊሲው ዝርዝር ይዘት ግን በውስጣዊ አለመጣጣሞች የተሞላና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቱ ደካማ መሆኑን እንረዳለን። ይህ ጽሑፍ ድርጅቱ በዚህ ረገድ ለተከታዮቹ የሚሰጣቸው መመሪያዎች አሳማኝ አለመሆናቸውንና ይልቁኑ የድርጅቱን ሐሰተኛነት የሚገልጡ መሆናቸውን በማስረጃዎች በማስደገፍ ያቀርባል።

  1. የፖሊሲው ውስጣዊ አለመጣጣሞች (Inconsistencies)

የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ደምን በተመለከተ የሚከተላቸው ሕግጋት በአመክንዮ (Logic) ሊደገፉ የማይችሉባቸው ዋና ዋና ነጥቦችን እንመልከት፦

ድርጅቱ “ሙሉ ደም” መውሰድን ይከለክላል፤ ነገር ግን ከደም የሚወጡ “ጥቃቅን ክፍልፋዮችን” (Fractions) መውሰድን ለግል ሕሊና ይተዋል። ድርጅቱ ደም መብላትን የሚከለክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ከጠቀሰ በኋላ ደም በደም ስር መውሰድ ልክ አለመሆኑን ለማሳመን እንዲህ የሚል ምሳሌ ይጠቀማል፦ “አንድ ሐኪም አልኮል መጠጣት አቁም ቢልህ አልኮሉን በቀጥታ ከመጠጣት ይልቅ በደም ሥር ብትወስድ ትዕዛዙን እንደጠበቅክ ይቆጠራልን?” በማለት ይጠይቃል። እስኪ ይህንኑ ምሳሌ በመጠቀም መልሰን እንዲህ እንጠይቅ፦   “አንድ ሐኪም አልኮል መጠጣት አቁም ቢልህ በውስጡ ያሉትን ንጥረ ነገሮች ለይተህ ብትወስድ ትዕዛዙን እንደጠበቅክ ይቆጠራልን?” ደም መውሰድ ትክክል ካልሆነ ክፍልፋዮቹን ነጣጥሎ መውሰድ ትክክል ሊሆን አይችልም።

ሌላውና የድርጅቱን መመሪያ መሠረተ-ቢስነት በግልጽ የሚያሳየው ነጥብ፣ ድርጅቱ ስለ ደም ክልከላ ያለው አቋም አምላክ ከፈጠረው የተፈጥሮ ሥርዓት ጋር በቀጥታ መጋጨቱ ነው። ድርጅቱ ነጭ የደም ሴሎችን (White Blood Cells) መውሰድን እንደ “ሙሉ ደም” በመቁጠር “የአምላክን ሕግ መጣስ ነው” ብሎ በጥብቅ ይከለክላል። ሆኖም ግን፣ ደም መብላትን የከለከለው ያው አምላክ አንዲት እናት ለልጇ የምታጠባው ወተት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነጭ የደም ሴሎችን እንዲይዝ አድርጎ ፈጥሮታል። በሳይንሳዊ ጥናት እንደተረጋገጠው የእናት ጡት ወተት በውስጡ ከፍተኛ መጠን ያለው ነጭ የደም ሴሎች (በተለይም ማክሮፋጅስ እና ሊምፎሳይትስ) ይዟል። እነዚህ የደም ሴሎች ከእናቲቱ ደም ውስጥ በቀጥታ ወደ ወተቱ የሚገቡ ሲሆን ዓላማቸውም የሕፃኑን በሽታ የመከላከል አቅም መገንባት ነው።

እዚህ ጋር ልንጠይቅ የሚገባው መሠረታዊ ጥያቄ አለ፦ አምላክ ነጭ የደም ሴሎችን ወደ ሌላ ሰው አካል ማስተላለፍን የሚከለክል ቢሆን ኖሮ፣ ለምን ሕፃናት ገና እንደተወለዱ ከእናታቸው ወተት ጋር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነጭ የደም ሴሎችን እንዲወስዱ አድርጎ ፈጠረ? አምላክ የፈጠረው የተፈጥሮ ሥርዓት (ጡት ማጥባት) ነጭ የደም ሴሎችን ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍን (Transfusion of cells) የሚያካትት ከሆነ፣ ድርጅቱ “ነጭ የደም ሴል መውሰድ ኃጢአት ነው” የሚለው ትምህርት የፈጣሪን ጥበብና የተፈጥሮ ሕግ የሚቃረን ነው። ይህም ድርጅቱ የመጽሐፍ ቅዱስን የደም ክልከላ ዓላማ በትክክል እንዳልተረዳና መመሪያውም መለኮታዊ ሳይሆን ሰው ሠራሽ መሆኑን የሚያረጋግጥ ትልቅ ማስረጃ ነው።

ከዚሁ ጋር አያይዘን ልንመለከተው የሚገባው ጉዳይ የድርጅቱን አቋም መዋዠቅ ነው። ለምሳሌ ያህል ድርጅቱ ቀደም ሲል የክትባት መድኃኒቶችንና የአካል ክፍሎች ንቅለ ተከላን (Organ Transplant) ልክ እንደ ደም ሁሉ ይከለክል ነበር። በኋላ ግን እነዚህን ክልከላዎች አንስቷል። ይህም ድርጅቱ “መለኮታዊ መመሪያዎች” ብሎ ለተከታዮቹ የሚሰጣቸው ሕግጋት በሰዎች አስተያየት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ያሳያል። ይህንን ነጥብ ከአፍታ በኋላ አጠናክረን እንመለስበታለን።

  1. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሙግት

የይሖዋ ምስክሮች ደምን ለመከልከል የሚጠቀሙባቸው ጥቅሶች (ዘፍጥረት 9:4፣ ዘሌዋውያን 17:10፣ ሐዋርያት ሥራ 15:29) በትክክለኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አውድ ሲታዩ ደም መስጠትን አይከለክሉም። ምክንያቱም፦

  • መብላት ከሕክምና ይለያል (The Digestion Fallacy): መጽሐፍ ቅዱስ “ከደም ራቁ” ሲል ትኩረቱ “ደምን እንደ ምግብ መውሰድ” ላይ ነው። በሕክምና ሳይንስ ደም በደም ሥር መውሰድ (Transfusion) ማለት “መመገብ” ሳይሆን እንደ አንድ ሕያው የአካል ክፍል ንቅለ ተከላ (Organ Transplant) የሚቆጠር ነው። ደም በደም ሥር ሲሰጥ ወደ ሆድ ሄዶ አይፈጭም፤ ይልቁንም በቀጥታ ወደ ሥራ ይገባል። ስለዚህ “አትብላ” የሚለው ትእዛዝ “ለሕክምና አትጠቀምበት” ማለትን አያሲዝም።
  • ሕይወትን ማዳን ከሕግ ይበልጣል (Life Over Law): በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሕግጋት ሁሉ ዓላማ ሕይወትን ማዳን ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ቀን የታመሙትን በመፈወሱ በወቅቱ የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ሲተቹት፣ እርሱ ግን “ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?” (ማቴዎስ 12:11) በማለት ምላሽ ሰጥቷል። ትርጉሙም፦ አንድን ደንብ ወይም ሥርዓት ለመጠበቅ ሲባል የሰው ሕይወት መጥፋት የለበትም የሚል ነው። የይሖዋ ምስክሮች ግን ከሕይወት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ ተርጉመው ለፈጠሩት የድርጅቱ ሕግ ቅድሚያ ይሰጣሉ።
  • የብሉይ ኪዳን መሥዋዕትነት ትርጉም፦ በዘሌዋውያን ላይ ደም የተከለከለው “የነፍስ መገኛ” ስለሆነና ለመሥዋዕትነት ብቻ እንዲውል ስለታሰበ ነው። ዛሬ ግን ክርስቲያኖች ከእንስሳት መሥዋዕት ነፃ ናቸው። ደም መስጠት ደግሞ አንድ ሰው ሕይወቱን ለሌላው አሳልፎ የሚሰጥበት የፍቅር መገለጫ እንጂ አምላክን የመዳፈር ተግባር አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ፍቅሩን የገለጸው ደሙን ስለ እኛ በማፍሰስ ነው። በጌታ እራት ወቅትም ሥጋውንና ደሙን በወይኑና በሕብስቱ አማካይነት እንድንወስድ ትዕዛዝ ሰጥቶናል (ሉቃስ 22፡19)።
  1. ግብረ ገባዊና ሰብዓዊ ቀውስ

የድርጅቱ አባላት ደም ባለመውሰዳቸው ምክንያት ሕይወታቸው ሲያልፍ ድርጅቱ ይህንን እንደ “ታማኝነት” ይቆጥረዋል። ሆኖም ግን አንድ አባል በራሱ ሕሊና ደም ለመውሰድ ቢወስን ከቤተሰቡና ከጓደኞቹ እንዲገለል (Ostracism) ይደረጋል። ይህ ዓይነቱ አካሄድ “ነፃ ምርጫን” የሚጋፋና ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ የሥነ-ልቦና ተፅዕኖ ነው።

  1. የፖሊሲዎች መዋዥ መለኮታዊ መመሪያ ወይንስ የሰዎች ቃል?

የመጠበቂያ ግንብ ድርጅት የሚሰጣቸውን አዳዲስ መመሪያዎች “አዲስ ብርሃን” (New Light) በሚል ስያሜ ቢጠራቸውም በታሪኩ ውስጥ የታዩት እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ለውጦች ግን ድርጅቱ በሰዎች ፍላጎትና ግምት የሚመራ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። አምላክ የማይሳሳትና ትክክለኛ መመሪያን የሚሰጥ ከሆነ ዛሬ “ነፍሰ ገዳይነት” የተባለ ተግባር ነገ “ተፈቅዷል” ሊባል አይችልም። ድርጅቱ ግን በተደጋጋሚ እንዲህ በማድረግ በሰዎች ሕይወት ቁማር ሲጫወት ይታያል። ለምሳሌ ያህል፦

  • የአካል ክፍሎች ንቅለ ተከላ (Organ Transplants)
    • 1967 በፊት፦ እንደ ግል ውሳኔ ይታይ ነበር።
    • 1967–1980 ድርጅቱ የአካል ክፍል ንቅለ ተከላን “በላዔ ሰብነት” (Cannibalism) በማለት በጥብቅ ከለከለ። በነዚህ ዓመታት ውስጥ የኩላሊት ወይም የልብ ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ብዙ አባላት ይህንን መመሪያ አክብረው ለሞት ተዳርገዋል።
    • 1980 በኋላ፦ ድርጅቱ ድንገት ሐሳቡን ቀይሮ ንቅለ ተከላን ፈቀደ።
    • ጥያቄው፦ በእነዚያ 13 ዓመታት ውስጥ “ሰው በላነት ነው” ተብሎ የተሰጠው መመሪያ ከአምላክ ከሆነ፣ አምላክ በ1980 ሐሳቡን ቀየረ ማለት ነው? ወይንስ መመሪያው የሰዎች ስሕተት ነበረ? ስሕተት ከሆነስ በዚያ ስሕተት ምክንያት ለሞቱት ሰዎች ተጠያቂው ማን ነው?
  • የክትባት መድኃኒቶች (Vaccinations)
    • ድርጅቱ ከ1921 እስከ 1952 ድረስ ክትባትን ይከለክል ነበር። ክትባት “የአጋንንት ሥራ” እና “የአምላክን ሕግ መጣስ” እንደሆነም ይናገር ነበር። ዛሬ ግን ክትባት የግል ምርጫ ነው። አምላክ ስለ ጤና ሳይንስ ያለው እውቀት በ1952 ታደሰ ማለት ነው? ምን የሚሉት ቀልድ ነው?

የደም ፖሊሲውም እንደዚሁ ወጥ ያልሆነና በየጊዜው የሚለዋወጥ ነው፦

  • መጀመሪያ (1945) ማንኛውም ዓይነት የደም ንክኪ የተከለከለ ነበር።
  • በኋላ (2000) “ጥቃቅን የደም ክፍልፋዮች” (Blood Fractions) ተፈቀዱ።
  • አመክንዮአዊ ስሕተቱ፦ አንድ ድርጅት “ደም ክልክል ነው” እያለ ደሙን በፋብሪካ አቀነባብሮ ክፍልፋዮቹን መውሰድ ይቻላል ማለቱ “ዝሙት ክልክል ነው፣ ነገር ግን ዝሙትን በከፊል (ጥቃቅን ድርጊቶችን) መፈጸም ይቻላል” እንደማለት ነው። ደም መብላትን የሚከለክለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሕይወት አድን ለሆነ ተግባር ደም መውሰድን የሚከለክል አድርጎ የተረጎመው ድርጅቱ ክፍልፋዮችን መውሰድ እንደሚቻል የፈቀደው በየትኛው ትዕዛዝ መሠረት እንደሆነ ግራ ይገባል። ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም መለኮታዊ ትዕዛዛትን ሳይሆን የሕግ ጠበቆችን (Lawyers) መመሪያ ይመስላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና ስለ እውነተኛ ነቢያት የሚናገረው ከዚህ በተቃራኒ ነው፦

  • አምላክ አይለወጥም፦ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በባሕርዩ የማይለዋወጥ መሆኑን ስለሚናገር (ሚልክያስ 3:6፣ ያዕቆብ 1:17) በባሕርዩ ላይ የተመሠረቱት የአምላክ መመሪያዎችም በየአሥር ዓመቱ አይለወጡም።
  • የሐሰተኛ ነቢያት መለያ፦ ኦሪት ዘዳግም 18:22 ላይ አንድ ነቢይ “በአምላክ ስም” የተናገረው ነገር ሳይፈጸም ቢቀር ከአምላክ እንዳልሆነና “በድፍረት” እንደተናገረ ይገልጻል። የመጠበቂያ ግንብ በአምላክ ስም ተደጋጋሚ የሐሰት ትንቢቶችን በመናገር የሚታወቅ ከመሆኑም በተጨማሪ ተለዋዋጭ ትዕዛዛትን በአምላክ ስም በማስተላለፍ የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ እየጣለ የሚገኝ የሐሰተኞች ስብስብ ነው።
  • የሰዎች ወግ፦ ጌታ ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የሰው ሥርዓት የሆነውን ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል” (ማቴዎስ 15:9)። የመጠበቂያ ግንብ ድርጅትም መጽሐፍ ቅዱስን ሳይሆን የራሱን “ሥርዓት” (Policy) በሰዎች ላይ በመጫን ሰዎችን ለከንቱ መሥዋዕትነት እየዳረገ ነው።

ማጠቃለያ

አንድ ድርጅት ዛሬ ሕይወት የሚቀጥፍ መመሪያ ሰጥቶ፣ ነገ ደግሞ “ተሳስቼ ነበር” ወይም “ብርሃን በራልኝ” ካለ ያ ድርጅት የሚመራው በመለኮታዊ መንፈስ ሳይሆን በሰዎች ግምት፣ ፍርሃትና ድፍረት ነው። እውነተኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና ግን በሰው ልጆች ደንብ ላይ ሳይሆን፣ በክርስቶስ ፍቅርና በቃሉ የማይለወጥ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው። የይሖዋ ምስክሮች የደም ፖሊሲ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን፣ ጥቅሶችን ባልተገባ መንገድ ከአውድ ውጭ በመተርጎም ላይ የተመሠረተ ነው። ደም መውሰድ መብላት አይደለም፤ ሕይወትን ማዳን ደግሞ የአምላክ ትዕዛዛት ዋነኛ ትኩረት በመሆኑ ከማንኛውም ሃይማኖታዊ ሥርዓት በላይ በአምላክ ዘንድ የተወደደ ነው። አማኞች የድርጅት መመሪያዎችን ከመከተል ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ይመረምሩ ዘንድ የተገባ ነው።


መልስ ለአርዮሳውያን