“አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ?” የኢየሱስ ንግግርና የሙስሊሞች ውዥንብር!

አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ?

የኢየሱስ ንግግርና የሙስሊሞች ውዥንብር!

በክርስቶስ ላይ ተቃውሞ መነሳት የጀመረው በእስልምና ሃይማኖት ዕድሜ ሳይሆን ራሱ ክርስቶስ ጌታችን በምድር ላይ ከነበረበት ዘመን አንስቶ ነው፡፡ በክርስቶስ ላይ ስለነበራቸው እምነት  ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው እስከመስጠት ድረስ የፀኑት ቅዱሳን ሐዋርያትና በየዘመናቱ የኖሩት አበው በጌታችን ላይ ለተነሱት ክሶች አጥጋቢ መልስ እየሰጡ የምሥራቹን ሰብከው አልፈዋል፡፡ መቼም ሰይጣን ሁል ጊዜ አለና ዛሬም ቢሆን በጌታችን ላይ ብዙ ጥያቄዎችንና ክሶችን መሰንዘሩን ቀጥሏል፡፡ እኛም ደግሞ በተራችን እንደቀደሙት የእምነት አባቶቻችን በጌታችን ማንነት ላይ ላነጣጠሩት ተቃውሞዎች ምላሽ እንሰጣለን፡፡

ሙስሊሞች በክርስቶስ ማንነት ላይ ከሚያነሷቸው የተለመዱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ እርሱ አምላክ ከሆነ ለምን በመስቀል ላይ “አምላኬ አምላኬ” ብሎ ጮኸ? የሚል ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ አብዛኛው ሙስሊም እውነተኛ የልቡ ጥያቄ ሆኖበት የሚጠይቅ ቢሆንም ጥቂት ሙስሊም የዳዕዋ አስፋፊዎች ደግሞ ትክክለኛውን ምላሽ እያወቁ ሆነ ብለው ሙስሊሙ ሕዝብ እውነቱን እንዳያውቅና ክርስቲያኑ እንዲወናበድ በማሰብ ይጠይቃሉ፡፡ የጥያቄያቸው መነሻ የሆነው ጥቅስ እንደሚከተለው ይነበባል፡-

“በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ፦ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም፦ አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው።”  (ማቴ 27: 46 እና ማር 15፡34)

ሙስሊም ሰባኪያን ጥቅሱ  ምን እያለ እንደሆነና ከአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አንጻር እንዴት እንደሚተረጎም ሳያገናዝቡ በጥሬው እያነበቡና እየፈቱ ሰዎችን ግራ ለማጋባት ይጥራሉ፡፡ ቁርአናቸውን በአስባብ እየፈቱ መጽሐፍ ቅዱስን በዘፈቀደ ይፈቱታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ማንም ተነስቶ በዘፈቀደ የሚፈታው መጽሐፍ ሳይሆን ራሱን በራሱ ለመፍታት ብቁ የሆነ የተሟላ አውድና የመልእክት ተያያዥነት ያለው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ጥቅስ ያነበበ እምነቱን የሚያውቅ ክርስቲያን ኢየሱስ ምን እያለ እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችል አንድ ቁልፍ ነጥብ መኖሩን ይገነዘባል፡፡ እርሱም ኢየሱስ ንግግሩን ከመዝሙረ ዳዊት እየጠቀሰ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ጥቅስ በመዝሙረ ዳዊት እንዲህ ይነበባል፡፡

“አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ።” (መዝ. 22: 1)

ይህንን ክፍል በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ማግኘታችን ኢየሱስ ምን እያለ እንደሆነ ግልፅ የሆነ ዕውቀት እንዲኖረን ይረዳል፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ሙስሊሞች በተሰበሰቡት ቦታ ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ “ቢስሚላሂ አር-ረሕማኒ ረሒም” ቢል በቦታው ያሉት ሙስሊሞች ከዚህ ንግግር ቀጥሎ አዕምሯቸው ውስጥ የሚመጣው ሌላ ንግግር “አል-ሐምዱ -ሊ- ላሂ ረብቢል- ዓለሚይን”  የሚል ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ “አር-ረሕማኒ ረሒም፣ ማሊኪ የውሚ ዲን..” የሚሉት ቃላት ይታወሷቸዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ተናጋሪው ሰውዬ አል-ፋቲሃን እየቀራ እንደሆነ ማወቃቸው ነው፡፡ በተመሳሳይ አንድ ሰው ክርስቲያኖች በተሰባሰቡበት ቦታ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ቢል በቦታው ያሉ ክርስቲያኖች “ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ…” የሚል ቃል ይታወሳቸዋል፡፡ ምክንያቱም ይህ በክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ ጌታችን ያስተማረው ጸሎት ነውና፡፡  

ልክ እንደዚሁ ኢየሱስ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ” (አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ) ብሎ ሲናገር ብሉይ ኪዳንን የሚያውቁት አይሁድ  የመዝሙር ሃያ ሁለትን የመጀመርያውን ስንኝ እየተናገረ እንደሆነ ስለሚያውቁ የመዝሙሩን ሙሉ ቃል ያስታውሳሉ፡፡ ኢየሱስ “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ” ሲል በመስቀል ላይ በመሰቀሉ ምክንያት እየጸለየ ሳይሆን በቦታው ለነበሩት አይሁድ “ትንቢታዊ መዝሙሩን አስታውሱ” ማለቱ ነበር፡፡

እንግዲህ አይሁድ መዝሙር ሃያ ሁለትን እንዲያስታውሱ ለምን ፈለገ? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ አይሁድ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ ከመስቀል ወርዶ በማሳየት እንዲያረጋግጥላቸው ሲጠይቁትና ሲሳለቁበት እንደነበር ልብ ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ መዝሙር ሃያ ሁለት መሢሃዊ መዝሙር በመሆኑ በወቅቱ እየሆነ የነበረው ነገር ሁሉ አስቀድሞ የተተነበየ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ማለት ያ ክፍል መሲሁ እንደሚመጣና በሰዎች እጅ እንደሚንገላታ ከዚያም እንደሚሰቀል ትንቢታዊ መልዕክትን ያዘለ ነው ማለት ነው፡፡ እስኪ በመዝሙሩ ውስጥ የተካተቱትን አስደናቂ ትንቢቶች በወቅቱ ሲሆን ከነበረው ሁኔታ ጋር አስተያይተን እንመልከት፡-

“የሚያዩኝ ሁሉ ይላገዱብኛል፤ ራሳቸውን እየነቀነቁ በከንፈሮቻቸው እንዲህ ይላሉ፦ በእግዚአብሔር ተማመነ፥ እርሱንም ያድነው፤ ቢወድደውስ ያድነው። (መዝ 22፡6-8)

“የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና፡- ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን። በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው። ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር። (ማቴ 27፡39-44)
“ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፤ የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ።”(መዝ 22: 16) “በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ።” (ማር 15: 25)
“ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ።” (መዝ 22:18)

“ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ።” (ማር 15: 24)

“ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥” (ማቴ 27: 35)

ከላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ለአይሁድ “በነቢዩ ዳዊት የተነገረው ትንቢት ይኸው እየተፈፀመ እያያችሁ አታስተውሉም ወይ” የሚል የማንቂያ ጥሪ መሳይ አጠቃቀስ በቀጥታ ከምንጩ ጠቅሶ እየነገራቸው ነበር፡፡ ስቅለቱ በዝርዝርና በጥልቀት የተተነበየበትን ትንቢት የሚያስታውሰውን  የጌታችንን ንግግር ከዓላማው ውጪ በመጥቀስ በማንነቱ ላይ ላነጣጠረ የክህደት አስምህሮ መጠቀም አግባብ አይደለም፡፡

ውድ ሙስሊም ወገኖቼ! ልክ እንደዚህ ክፍል መምህሮቻችሁ እየጠመዘዙ የሚያስተምሯችሁ እልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ እናንተ እውነትና ሕይወት ወደሆነው ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳትመጡ እንቅፋት እየሆነባችሁ ነው፡፡ መዳን ትፈልጋላችሁን? የዘላለም ሕይወትንስ ትሻላችሁን? ከማንም ይልቅ ሊያስተምራችሁና ወደ ሕይወት ሊመራችሁ የሚችለውን እጅግ የተወደደውንና ቅዱስ የሆነውን ታላቁን መምህር ኢየሱስ ክርስቶስን አድምጡ፡፡ እርሱ ምን አስተማረ? ስለራሱ ምን አለ? ስለ ዘላለም ሕይወት ምን ተናገረ? ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምትፈልጉ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ፡፡ እኛ ደግሞ ልንረዳችሁ እጅግ በጣም ፈቃደኞች ነን፡፡ ለዚህም እንተጋለን፡፡

ውድ ሙስሊም ኡስታዞች! ሰዎችን ወደ ጥፋት መምራት የማይሰለቸው ሰይጣን በየዘመናቱ ተወካዮች አሉት፡፡ ጌታችንን ሲቃወም እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ተቃውሞውን በመቀጠል እስከ የውም አል-ቂያማ ይኖራል፡፡ ለዚህ የሰይጣን ተቃውሞ ዋና መሣርያዎች ደግሞ እናንተ መሆናችሁ እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ እንግዲህ ማንም በፍርድ ቀን ከታላቁ ጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቁጣ ያመልጥ ዘንድ ያደነደነውን ልቡን ከፍቶ፣ የያዘውን የፉክክርና የከማን አንሼ ሥራ አቁሞ ራሱን ይመርምር፡፡ ወደ እውነትም ይምጣ!

 

መሲሁ ኢየሱስ