ተቂያ ገደብ አለውን?
ገደብ አልባው እስላማዊ ውሸት
በወንድም ትንሣኤ
ተቂያ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ አንድን በጎ ዓላማ ለማሳካት ተብሎ የተፈቀደ የውሸት ዓይነት ነው። እስልምና ይህንን የውሸት ዓይነት አንዳንዴ በድጋፍ መልክ የሚያጸድቀው ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ግዴታ ያደርገዋል። ሙስሊሞች “ምንስ ቢሆን እውነተኛው አምላክ እንዴት ውሸትን ይፈቅዳል?” የሚለውን ጥያቄ “ውሸቱ የሚፈቀደው በሦስት/አራት ሁኔታዎች ብቻ ነው” የሚል ማብራሪያ በማስቀመጥ ለማለፍ ሲሞክሩ ማየት የተለመደ ነው። ውሸት መጥፎ መሆኑ ከተረጋገጠ ለሦስት ወይም አራት ሁኔታ ቀርቶ ለአንድም ሁኔታ ቢሆን መፈቀድ የሌለበት ተግባር መሆኑ ግልጽ ቢሆንም እውን እስልምና ተቂያ ላይ ገደብ ያስቀምጣልን? የሚለውን ሐሳብ እንመልከት።
ሙስሊሞች ውሸት ለሦስት ሁኔታ ብቻ እንደሚፈቀድ ሙሐመድ ከተናገራቸው ሐዲሶች ተነስተው ይሞግታሉ።[1] በሐዲሶቹ መሠረት ሙሐመድ “ውሸት ሚስትን ለማስደሰት፣ ለጦርነት እና የተጣሉ ሰዎችን ለማስማማት ካልሆነ በስቀር አይፈቀድም” ብሎ ሦስት ተቂያ የሚፈቀድባቸውን ሁኔታዎች አስቀምጧል። ሙስሊም ወገኖች ይህንን ሐዲስ በመያዝ ተቂያ ከነዚህ ሁኔታዎች ውጪ እንደማይፈቀድ ቢናገሩም ሐዲሱን “ጥሩ ዓላማ ያለውን ውሸት ሁሉ የሚፈቅድ” አድርገው የተረጎሙ እንደ አቡ ሐሚድ አል-ገዛሊ ያሉ ሙስሊም ሊቃውንት አልጠፉም።[2] የተቀመጡት ሁኔታዎችም ቢሆኑ ለግል ትርጓሜ የተጋለጡ መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ለምሳሌ አንድ ገንዘብ አምጣ እያለች የምትጨቃጨቅ ሚስት ያለችው ባል “ሚስቱን ለማስደሰት” በሚል ሰበብ ይህንን የመዋሸት መብት ተጠቅሞ የእርሱ ያልሆነን ገንዘብ (ምናልባት በጉቦ) ሊወስድ ይችላል።
ተቂያ እስላማዊ ገደብ እንደሌለው የሚያሳየው የመጀመሪያው ነጥብ በብዙ ሐዲሶች መሠረት ሙሐመድና ሌሎች ነቢያት ከነዚህ ሦስት ሁኔታዎች ውጪ በሆኑ አጋጣሚዎች ጭምር ይህንን የውሸት መብት መጠቀማቸው ነው። ሙሐመድ ስለ ኢብራሂም ሲናገር እንደዚህ ይላል፦
“…ኢብራሂም አልዋሸም ፤ ከሦስት ጊዜያቶች ውጪ ፤ ሁለቱን ጊዜ ለአላህ ብሎ ዋሽቷል። (ሳይታመም) “ታምሜያለሁ” ብሏል ፤ ሁለተኛም “ይህንን እኔ አላደረኩትም ትልቁ ጣዖት እንጂ…” ብሏል።[3]
ሙሐመድ እዚህ ጋር እየተናገረ ያለው ኢብራሂም በጊዜው የነበሩ ጣዖት አምላኪያንን ጣዖታት ካፈራረሰ በኋላ “እኔ ሳልሆን ያፈረስኳቸው ትልቁ ጣዖት ነው” ብሎ የዋሸበትን ክስተት ነው (ቁርዓን 21፡57-63 ይመልከቱ): እንደምናስተውለው የኢብራሂም ውሸት ሙሐመድ ካስቀመጣቸው ሦስቱም ምድቦች የሚመደብ አይደለም።(ኢብራሂም ከማንም ጋር ጦርነት ላይ አልነበረም፤ ሚስቱን ለማስደሰት ብሎ አላደረገውም፤ ወይም የተጣሉን ለማስማማት አይደለም የዋሸው)።
ኢብራሂም እንደ ሁሉም ነቢያት ከኃጢአት የነጻ መሆኑንና ሙሐመድም የእርሱን ተግባር ደግፎ በዚህ መልኩ ማስተማሩን ከግምት ስናስገባ ተቂያ በሦስት ሁኔታዎች ብቻ ይገደባል የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት እንደሌለው ግልጽ ነው።
ሙሐመድም ቢሆን ከነዚህ ገደቦች ባለፈ መልኩ ተከታዮቹ እንዲዋሹ ፍቃድ ሰጥቷል። ካዕብ ቢን አሽራፍ የተባለው ሙሐመድና ተከታዮቹ ላይ ግጥም በመግጠሙ የሞት ትዕዛዝ የተላለፈበትን ሰው ታሪክ ስናነብ ይህንን እናገኛለን፦
“የአላህ መልእክተኛ አሉ፦ ‘አላህንና መልእክተኛውን የጎዳውን ካዕብ ቢን አል አሽራፍን ለመግደል ፍቃደኛ የሆነ ማነው?’ በዚህ ጊዜ ሙሐመድ ቢን መስላማ “የአላህ መልእክተኛ ሆይ እኔ እንድገድለው ይፈልጋሉ?” ብሎ ጠየቀ። ነቢዩም አዎ ብለው መለሱ። ሙሐመድ ቢን መስላማም “እንግዲያውስ (ካዕብን ለማታለል) አንድ ውሸት እንድናገር ፍቀዱልኝ” አለ፤ ነቢዩም “ትችላለህ” አሉት።”[4]
ኢብን ኢስሐቅ እንደሚነግረን ከሆነ ኋላ ላይ የሙሐመድ ተከታዮች ሰውየውን ለማታለል እስልምናን እንደለቀቁ ከነገሩት በኋላ እነርሱን ለመገናኘት ከቤቱ ሲወጣ በስለት ወግተው ገድለውታል።[5] አንባቢው ማስተዋል ያለበት በዚህ ታሪክ ላይ ሙሐመድ ለተከታዮቹ የሰጠው የውሸት ፍቃድ ከሦስቱም ገደቦች የሚመደብ አለመሆኑን ነው። ካዕብ ሙሐመድ ላይ ሰይፍ አላነሳም፤ ሙሐመድም ለሕይወት የሚያሰጋ ሁኔታ ላይ አልነበረም። ሆኖም ግን ካዕብ ሙሐመድን ይተች ስለነበር ብቻ ከነብያቸው የመዋሸት ፍቃድ የተሰጣቸው ተከታዮቹ የጭካኔ ሰለባ ሆኗል።
ሌላው ሳይነሳ ሊታለፍ የማይገባው ጉዳይ ተቂያ ቀድሞውኑ የተፈቀደው ጥሩ አላማ ለማሳካት በሚል ሽፋን ከሆነ በሦስት ሁኔታዎች ብቻ የሚገደብበት ምንም ምክንያት አይኖርም። መልከ ጥፉ ብለህ የምታስባትን ሚስትህን ለማስደሰት “እጅግ ቆንጆ ነሽ” ብሎ መዋሸት ከተፈቀደ የሰውን ሕይወት ለማትረፍ፣ የተቸገሩን ለመርዳት ወይም እስልምናን ለማስፋፋት ወዘተ. ውሸት የሚከለከልበት ምንም መሠረት የለም፤ እነዚህ ሁሉ “ሰናይ” ዓላማ ናቸውና። ለምሳሌ ኢማሙ አል-ሚስሪ በሸሪዓ ትንታኔ መጽሐፋቸው ላይ አል-ገዛሊን ዋቢ አድርገው “አንድ በጨቋኝ መንግሥት የሚተዳደር ሙስሊም ሌላ ሙስሊም ወዳጁ በአደራ የሰጠውን እቃ ለጨቋኙ ገዢ አሳልፎ ላለመስጠት መዋሸት እንዳለበት” ይናገራሉ።[6] ታዲያ ሚስትን ለማስደሰትና የሰውን አደራ ላለመብላት ተብሎ መዋሸት ከተፈቀደ እስልምናን ለማስፋፋት ተብሎ ሐሰተኛ ስብከቶችን መንዛት የሚከለከልበት ምክንያት ምንድነው? አል-ሚስሪ የጠቀሱት የመካከለኛው ዘመን ሙስሊም ፈላስፋ አል-ገዛሊ እንዲህ ብሏል፡-
“ንግግር ዓላማን የማሳክያ መንገድ ነው፡፡ እውነትን በመናገርና በመዋሸት በሁለቱም መንገዶች ምስጋና የተገባው ግብ ከተመታ በመዋሸት ማሳካት የተፈቀደ አይደለም ምክያቱም መዋሸት አስፈላጊ አይደለምና፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱን ዓላማ ማሳካት የሚቻለው እውነት በመናገር ሳይሆን በመዋሸት ከሆነና ያ ግብ የተፈቀደ ግብ (ሐላል) ከሆነ በመዋሸት ግቡን መምታት የተፈቀደ ነው… እንዲሁም ግቡን መምታት ግዴታ ከሆነ በመዋሸት ግቡን መምታት ግዴታ ነው፡፡”[7]
ጽሑፉን ስናጠቃልል ተቂያ በሦስት ሁኔታዎች ብቻ ይገደባል የሚለው ትርክት ከራሱ ከሐዲሱ ትርጓሜ ጀምሮ ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው። ሐዲሱ ያስቀመጣቸው ገደቦች ግልጽ አለመሆን፣ በእስላማዊ ታሪኮች መሠረት ሙሐመድን ጨምሮ ሌሎች ነቢያት ገደቦቹን ተላልፈው መዋሸታቸው (ለውሸት ፍቃድ መስጠታቸው)፣ ውሸት ለሦስቱ ሁኔታዎች ብቻ ተፈቅዶ ለሌሎች የተሻለ “ቅዱስና አስፈላጊ” ለሆኑ ሁኔታዎች የሚከለከልበት ምክንያት አለመኖሩ፣ ወዘተ. ተቂያ ገደብ አለው የሚለውን ሐሳብ ስህተትነት ያሳያል። ይልቁን የተሻለው አመክንዮአዊ ድምዳሜ የሚሆነው አል-ሚስሪ አል-ገዛሊን ጠቅሰው እንዳሉት “ዓላማው ሐላል (የተፈቀደ) ከሆነ መዋሸቱም ሐላል ይሆናል” የሚለው ነው።[8] ይህ ደግሞ እስልምና የእውነተኛውን አምላክ ባሕርይ ያልተገነዘበ ምድራዊ ፖለቲካ ብቻ መሆኑን በማሳየት ቋሚ የግብረ ገብነት መርህ የሌለውና የዘላለምን ሕይወት የማይሰጥ ሰው ሠራሽ ንፅረተ ዓለም መሆኑን ያረጋግጣል።
[1] Riyad as-Salihin, 249. https://sunnah.com/riyadussalihin:249
[2] Imam al-Misri , Reliance of the Traveller , page 745.
[3] Jami at-Tirmidhi 3166 https://sunnah.com/tirmidhi:3166
[4] Sahih al-bukhari 4037. https://sunnah.com/bukhari:4037
[5] Ibn Ishaq, Sirat Rasulullah, p. 368.
[6] Imam al-Misri,‘Umdat al-Salik “The Reliance of the Traveller”, p. 745
[7] Ibid.
[8] Ibid.