ያማረው ሙሐመድ?

ያማረው ሙሐመድ?

ዘላለም መንግሥቱ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙሐመድ ተተንብዮአል የሚሉትን ሙሐመድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለማግኘት ሙስሊሞች የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ቀደም ሲል ‘የሙሴ ወንድም ሙሐመድ’ እና ‘አጽናኙ ሙሐመድ’ በሚሉ ርእሶች ሁለት ስለ ሙሐመድ የተነገሩ ምንባቦች ናቸው የሚሏቸውን ተመልክተናል። ሙስሊሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅስና ምንባብ ለመፈንቀል የሚለፉት የኢስላም ነቢይ ሙሐመድ በተውራት (ኦሪት ወይም ብሉይ ኪዳን) እና ኢንጅል (ወንጌል ወይም አዲስ ኪዳን) ማለትም፥ በአይሁድ እና በክርስቲያኖች መጽሐፍት፥ ተደጋግሞ እንደተጻፈና እንደተተነበየ ስለሚመስላቸው ነው። ይህን የሚሉት በሱራ 61፥6 ዒሳ ከእርሱ በኋላ አሕመድ የተባለ መልእክተኛ እንደሚመጣ ስለ ተናገረ ነው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፤

“የመርየም ልጅ ዒሳም፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደእናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ» ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ በግልጽ ተዓምራቶች በመጣቸውም ጊዜ «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ፡፡”

ዛሬ የምንመለከተው ያማረው ሙሐመድን ነው። ይህ ስለ ሙሐመድ ተነገረ የሚሉት ክፍል በመኃ. 5፥16 የሚገኘው ነው፤ በአማርኛው ትርጉም ይህ ነው።

“አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ውዴ ይህ ነው፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው።”

ዕብራይስጥ ከቀኝ ወደ ግራ ነው የሚነበበውና አማርኛውንም ከቀኝ ወደ ግራ ስናነብበው እንዲህ ነው።

16 חִכֹּו מַֽמְתַקִּים וְכֻלֹּו מַחֲמַדִּים זֶה דֹודִי וְזֶה רֵעִי בְּנֹות יְרוּשָׁלִָֽם׃

“የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ባልንጀራዬ ይህ (ነው) ወዳጄ ይህ ያማረ ሁለመናው የሚጣፍጥ አፉ”

ወደ ግራ የተጻፈውን ከግራ ወደ ቀኝ ስንመልሰው፥ “አፉ የሚጣፍጥ፥ ሁለመናው ያማረ (ነው)፤ ወዳጄ ይህ፥ ባልንጀራዬም ይህ (ነው)፤ እናንተ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት (ሆይ)።”

የተፈለገው ቃል ያማረ የሚለው ነው። በዕብራይስጥ מַחֲמַדִּים (ማኽማዲይም) ሲሆን ምንጩ מַחמָד (ማኽማድ) ነው። ማኽማዲይም ሲበዛ ወይም ሲጋነን ነው። ሲጋነን የሚለውን ኢም ወይም ኢይም (ማኻማዲይም) አሳብ ሙስሊሞች የአክብሮት አጠራር ነው ብለውም ይከራከራሉ። የዕብራይስጥ አጻጻፍና አነጋገር እንዲህ ያለውን አጠራር በመጠቀም ለነገሮች አክብሮት አይጠቀምበትም። ዐውዱን እና ማን ስለ ማን እየተናገረ እንደሆነ እናቆየውና ቃሉን እንደ ቃል ብቻ እንውሰደው። 

ማኽማድ የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ አንድ ነገርን ገላጭ ቅጽል ነው፤ ስምም አይደለም። ቃሉ እንደ ቅጽል ከዚህ ከመኃልየ መኃልይ ሌላ 12 ጊዜያት ተጽፎ ይገኛል። እንድትመለከቷቸው ጥቅሶቹ እነዚህ ናቸው፤ 1ነገ. 22፥6፤ 2ዜና 36፥19፤ ኢሳ. 64፥11፤ ሰቆ. 1፥10 እና 11፤ 2፥4፤ ሕዝ. 24፥16፥21 እና 25፤ ሆሴ. 9፥6 እና 16፤ ኢዩ. 3፥5 ናቸው። በነዚህ ጥቅሶች፥ ማኽማድ ወይም ማኽማዲይም የተባሉት ቃላት፥ ደስ የሚያሰኝ፥ መልካም፥ ያማረ፥ የከበረ፥ የሚያምር፥ አምሮት፥ ጌጥ፥ ፍሬ የሚሉ ናቸው። አንዳንዶቹ እንደ ስም ቢመስሉም በተጠቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ እንደ ቅጽል ነው የተጠቀሱት።

ይህ ቃል የመነጨበት ግስም አለው፤ חָמַד (ኻማድ) ይሰኛል። መደሰት፥ ደስ መሰኘት፥ መውደድ፥ መመኘት ማለት ነው። እዚሁ መኃ. 2፥3 “ወድጄ ተቀመጥሁ” በሚለው “ወድጄ” የሚለው ያ ግስ ነው። ዘፍ. 2፥9፤ ደስ የሚያሰኝ፥ ዘጸ. 20፥17፤ ዘዳ፣ 7፥25፤ አትመኝ፥ መዝ. 68፥16፤ ወደደው፥ ወዘተ፥ የሚለው ይህ ግስ ነው።

ስለዚህ፥ ማኽማድ ወይም ማኽማዲይም የተለመደ የዕብራይስጥ ቃል ነው። የሰው ስም አይደለም፤ ከተጠቀሰባቸው ቦታዎች በአንዱም እንኳ የሰው ስም ሆኖ አልተጠቀሰም። እንዲያው ነው ብለን ብንወስድ እንኳ ሙሐመድ ከሚለው ስም ጋር በድምጸት (phonetics) ተቀራረበ እንጂ በዕብራይስጥ ካለው የቃሉ ትርጉም ጋር አይሄድም። ሙሐመድ ሀምድ ከሚል ቃል የመነጨ ሆኖ የተከበረ ማለት ነው። ይህኛው ደግሞ ከክብር ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው የማማር ጉዳይ ነው። ብሉይ ኪዳን በአማርኛ የተጻፈ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ቃል ስም ብናወጣ፥ መልካሙ ወይም አማረ ነበር የሚፈጠረው ስም የሚሆነው።

ይህ እንግዲህ ዐውዱን ሳንነካ ነው። ወደ ዐውዱ ስንመለስ መኃልየ መኃልይ በሁለት ፍቅረኞች መካከል የተደረገ ተውኔታዊ ንግግር ነው። ሦስተኞችም፥ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት የተባሉ አሉ። አንዳቸው ለሌላቸው ያላቸውን የጋለ ፍቅር የሚገልጡበት መጽሐፍ ውስጥ ይህቺን ጥቅስና በውስጧ የሚገኝ አንድ ቃልን አውጥቶ ይህ ስለ ሙሐመድ የተነገረ ነው ማለት መጽሐፍ ቅዱስን ከቶም አለማወቅ ነው። ለነገሩ እንዲህ የሚሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አያውቁትምም፤ አይቀበሉትምም። ቢያውቁም ጥራዝ ነጠቅ እውቀት ብቻ ነው። ጥቅስ መርጠው ግን ሊወስዱ ይሞክራሉ።

ሌላው የዚህ ጥቅስ አወሳሰድ ችግር፥ ሙስሊሞች ለሙሐመድ ብለው የሚወስዱት ይህንን ብቻ ጥቅስ ነው? ወይስ ሌሎቹንም ማኽማድ እና ማኽማዲይም ያሉበትን ጥቅሶች በሙሉ ነው? ከሆነ ሙሐመድን የቤት ዕቃ፥ ጌጥ፥ የመቅደስ ዕቃ፥ ቤተ መቅደስ፥ የነቢዩ ሕዝቅኤል ሚስት፥ ወዘተ. ሊያደርጉት ነው።

ስማችን ወይም ለስማችን የሚቀርብ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገኘ ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ስለኛ ተናገረ ማለት አይደለም። ዘላለም የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ500 ጊዜ በላይ ተጽፏልና፥ ‘ኢሳይያስ እኔን እያሰበ ነው የጻፈው፤ ሰሎሞንም ስለ እኔ ነው የተናገረው፤’ ብል መቀወሴን ማረጋገጤ ነው።

ሙሐመድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም። ለተጨማሪ ንባብ ይህንን ጽሑፍ ይመልከቱ፦ የሙሐመድ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ?


በወንድም ዘላለም የተዘጋጁ ጽሑፎች

ሙሐመድ