መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 1]

መላክ ያሕዌ – ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ የተገለጠበት መንገድ [ክፍል 1]

Isaiah 48 Apologetics


የእግዚአብሔር መልአክ ወይንም ( מלן יהוה ) የሚለው መገለጫ በመላው ብሉይ ኪዳን ይገኛል። በዚህ መገለጫ የሚጠራው አካል ተራ መልዕክተኛ ሳይሆን መለኮታዊ አካል (person) መሆኑን ከእግዚአብሔር ቃል እንረዳለን።

ብዙ ከመሄዳችን በፊት መልአክ የሚለውን ቃል ትርጉም እንመልከት። ብሉይ ኪዳን በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ መልአክ የሚለው ቃል ትርጉም መልዕክተኛ ማለት ነው። ይህ ለፍጡራን መናፍስት ( መላእክት የምንላቸው ) ብቻ አይውልም። ለሰዎችም አንዳንዴም ለእግዚአብሔር ውሏል። በአጭሩ ያ አካል መልእክት ይዞ መላኩን ነው የሚያመለክተው። ይህ ደግሞ ከመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ ጋር ይስማማል ምክንያቱም እግዚአብሔር በእግዚአብሔር እንደተላከ የሚናገሩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ (ኢሳ 48:16 ዘካ 2:7-11)። ከዚህ የምንረዳው፥ እግዚአብሔር ነጠላ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን ይህ የእግዚአብሔር መልአክ ወይንም መልእክተኛ፣ መልአክ ተብሎ ስለተጠራ ብቻ ፍጡር አለመሆኑንም ጭምር ነው። ምክንያቱም በነቢያት መጽሐፍ እግዚአብሔር እንደላከው የሚናገረው መለኮታዊ አካል ( እግዚአብሔር ተብሎ ተጠርቷል ) እሱ ስለሆነ።

ታዲያ ለምንድነው ይህንን አካል መለኮት ነው የምንለው? ይህንን አካል መለኮት ብለን የምንጠራው በመላው ብሉይ ኪዳን እንደ መለኮት ሲናገር፥ ቃል ሲገባ፥ ሲያድን ስለነበረ ነው። በተጨማሪም ያዩት ሰዎች በሙሉ እንደ እግዚአብሔር ሲመለከቱት እና አንዳንዴም እግዚአብሔር ብለው ስለሚጠሩት ነው። ይህንን በስፋት እንመለከታለን። በተጨማሪ ይህ መለኮታዊ ልዑክ ከላኪው (ከአብ) የተለየ አካል (person) መሆኑን እንረዳለን። ምክንያቱም እሱ ራሱ እግዚአብሔርን ከራሱ በአካል ለይቶ ስለሚናገር ነው። ይህ በአዲስ ኪዳን የሚገኘውን ትምህርት በቀጥታ ያሳያል።

ይህ መለኮታዊ አካል ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠው በዘፍጥረት 16 ነው። በዚህ ክፍል አጋር እመቤትዋ ሦራ ከምታደርስባት ስቃይ ስትሸሽ እንመለከታለን። አጋር ከአብርሃም በመጸነሷ ምንም ልጅ የሌላትን ሶራ መናቅ ስለ ጀመረች ነበር። ሸሽታ በበርሃ ሳለች ይህ መለኮታዊ አካል (person) ይገለጥላታል። የሚናገራትን ነገር እንመልከት።

“የእግዚአብሔር መልአክም። ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት።” (ኦሪት ዘፍጥረት 16:10)

እዚህ ጋር ይህ ልዑክ የአጋርን ህዝብ እንደሚያበዛ ይናገራል። የትኛውም ፍጡር መልአክ #እኔ ህዝብን አበዛለሁ አይልም። ፍጡራን መላእክት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በማለት ይናገራሉ እንጂ በዚህ መልኩ አይናገሩም። እዚህ ጋር ግን እሱ ህዝብሽን አበዛለሁ በማለት እንደ መለኮት ቃል ኪዳንን ይገባል።  ይህ ልዑክ እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደተናገረው ነው የሚናገረው። እግዚአብሔር ለአብርሃም ሲናገር እንደዚህ ነበር የተናገረው (ዘፍ 13:16)። ከዚያም ጩኸቷን እግዚአብሔር እንደሰማት ይናገራል። ከዚህ የምንረዳው ይህ አካል መለኮት ቢሆንም በአካል (person) ከእሱ የተለየ ላኪ እንዳለው ነው።

” …ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና።” (ኦሪት ዘፍጥረት 16:11)

ይህ ደግሞ ከክርስትና ትምህርት ጋር ይስማማል፥ ምክንያቱም አብ አንዲያ ልጁን እንደላከው ወንጌል ይናገራልና። ከዚያም አጋር ይህ ያናገራትን አካል አንድ በጣም አስገራሚ በሆነ ስም ትጠራዋለች፦

“እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፤ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና።” (ኦሪት ዘፍጥረት 16:13)

አጋር ይናገራት የነበረውን አካል የሚያየኝ በማለት ገለጸችው። ሁሉንም ማየት የእግዚአብሔር ባህሪ ብቻ ነው። ይህንንም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፦

“የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ነውና፥ አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና። ” (መጽሐፈ ምሳሌ 5:21)

ይህንን አካል በዚህ መጠሪያ መጥራቷ እሱን እንደ መለኮት መመልከቷን ያሳያል። በተጨማሪም የሚያየኝን #አየሁት በማለቷ ይህ የሚመለከታት አካል ይመለከታት የነበረው እንደ ፍጡር እንዳለልሆነ መስክራለች፤ ተገልጦላታልና።

በስተመጨረሻም የዘፍጥረቱ ጸሐፊ ይህንን አካል እግዚአብሔር በማለት ይጠራዋል። አጋር ብቻ ሳትሆን እሱን እንደ መለኮት የምትናገረው፥ የዘፍጥረቱ ጸሐፊ ሙሴም ነው፦

“እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፤ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና።” (ኦሪት ዘፍጥረት 16:13)

አስተውሉ! ይናገራት የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ነው፥ ነገር ግን ጸሐፊው እሱን እግዚአብሔር በማለት ይጠራዋል። ይህ የዚህን አካል ማንነት በግልጽ ያሳየናል።  ስለዚህ በዚህ መሠረት ለአጋር የተገለጠው በአምሳለ መልአክ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ወልድ መሆኑን እናያለን።



መሲሁ ኢየሱስ