በእንተ ማቴዎስ 28፡19 – እውን ሰርጎ-ገብ ጽሑፍ ነውን?
ሰሞኑን ሳላህ ዘይን በተሰኘ ሙስሊም ጸሐፊ የተደረሰ የመጽሐፍ ቅዱስን የብራናዎች ታሪክና ተያያዥ ጉዳዮች የሚዳስስ መጽሐፍ ለማንበብ ዕድሉን አግኝቼ ነበር። ወጣቱ ጸሐፊ እስከ ዛሬ ካየኋቸው ሙስሊም ተሟጋቾች በተሻለ ሁኔታ ሙግቶቹን ያደራጀ ሲሆን በርካታ ምንጮችን የሚያጣቅስ ሥራ ለንባብ አብቅቷል። ለአጠቃላዩ መጽሐፍ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደፊት ምላሽ የምሰጥበት ቢሆንም አሁን ግን ትኩረቴ የሚያርፈው ጸሐፊው የማቴዎስ ወንጌል 28፡19ን ትክክለኛነት ለማጣጣል ባቀረበው ሙግት ላይ ይሆናል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የመጻፍ የረጅም ጊዜ ፍላጎት የነበረኝ ቢሆንም እስካሁን ድረስ በቂ ምላሽ የሚሻ የደረጀ ሙግት ከሌላ ወገን ገጥሞኝ አያውቅም ነበር። አንዳንድ የ”ኦንሊ ጂሰስ” እምነት ተከታዮች ይህንን ክፍል ለማጣጣል ቢሞክሩም ሙግታቸው በታሪክና በጽሑፍ ምርመራ (Textual Criticism) ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ ለምላሽ የሚበቃ ሆኖ አልታየኝም። ይህ ሙስሊም ወገናችን ግን በክፍሉ ላይ የሚነሱ ዋና ዋና ተቃውሞዎችን በማካተት ሙግት በማቅረቡ ተገቢውን ምሑራዊ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ጸሐፊው “ሰማዕቱ ብራና” በተሰኘው መጽሐፉ ገጽ 75-78 “ሥላሴያዊ ቅሰጣ” በሚል ርዕስ ሥር ሙግቱን እንዲህ ሲል ይጀምራል፦
ሙስሊም፦
-
- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” የማቴዎስ ወንጌል 28:19
ይህ የሦስትዮሽ የጥምቀት ቀመር በሁለተኛው ክ/ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጨመረ ሰርጎ-ገብ (Interpolation) ንባብ እንደሆነ በርካታ ሊቃውንቶች በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።
መልስ፦
የጸሐፊው ስህተት ከዚህ ይጀምራል። ይህ ዐረፍተ ነገር ከእውነት የራቀና በምሑራን ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ንግግር ነው። “በርካታ ሊቃውንት በአንድ ድምፅ ይስማማሉ” የሚለው አገላለጽ የተሳሳተ መረጃ (Misinformation) ነው። ለዚህም ዋና ዋናዎቹን ምክንያቶች በዝርዝር የምንመለከት ይሆናል።
ሙስሊም፦
ጥቅሱ ከጊዜ በኋላ እንደተጨመረበት ለማወቅ የሐዋርያት ጥምቀት በማን ስም እንደነበር መመልከት በቂ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድም ሰው በሦስት አካላት ስም አጥምቆ (ተጠምቆ) አያውቅም። ሐዋርያት ሲያጠምቁ የነበረው በኢየሱስ ስም ብቻ ነው። […የሐዋርያት ሥራ 2:38፣ 8:16፣ 10:48፣ 19:5…]
ከእነዚህ አንቀጾች በግልጽ እንደምንረዳው ጥምቀት በሦስት የተለያዩ አካላት ስም ሳይሆን “በኢየሱስ ስም” ብቻ ነው። ይህ የሐዋርያት ጥምቀት ከሆነ በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ የሚለው ባዕድ የሥላሴ የጥምቀት ቀመር ከየት መጣ? ብለን የጠየቅን እንደሆነ፤ ከመሠረቱ ጥቅሱ በሁለተኛው ክ/ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጨመረ ሰርጎ-ገብ የኋላ ጭማሪ (Later addition) ሆኖ እናገኘዋለን።
መልስ፦
ይህ ወገናችን ጥቅሱ ጭማሪ ነው የሚለውን መነሻውን ለማረጋገጥ ሲል የማያምንበትን ቅድመ ግንዛቤ ይዞ ተነስቷል። እንደ አንድ ሙስሊም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የሚገኙት ጥቅሶች በማቴዎስ ውስጥ ከተጻፈው ይልቅ ትክክል መሆናቸውን ያወቀው በምን መመዘኛ ነው? እንበልና ማቴዎስ ትክክል ሆኖ የሉቃስ ዘገባ አለመሳሳቱንስ በምን ተረዳ? ወይም ሁለቱም ጸሐፊያን የጻፉትን ጽፈው ግን እርስ በርሳቸው እንዳልተጋጩ እንዴት አወቀ? ማቴዎስ ጭማሪ ነው ለሚለው ድምዳሜው እንዲያመቸው ብቻ እየጻፈ እንጂ አንዳችም መመዘኛ ኖሮት ወይም የሚጽፈውን አምኖበት አይደለም። ትችቱ ካለ አንዳች ተጨባጭ የጽሑፍ ማስረጃ (Manuscript evidence) የቀረበ ከመሆኑም በላይ ተከራካሪው የሚጠቀምበትን መርጦ ተጠራጣሪነት (Selective Skepticism) ስህተት በግልጽ ያሳያል። (የጸሐፊውን ወጥነት የጎደለው አካሄድ ለማሳየት ያህል እንጂ ከሉቃስና ከማቴዎስ አንዳቸው ተሳስተዋል ወይም ይጋጫሉ ለማለት እንዳልሆነ ይሰመርበት።)
ሁለቱም መጻሕፍት በጥንቷ ቤተክርስቲያን እኩል ተቀባይነት የነበራቸውና ያለምንም መለዋወጥ ለዘመናት አብረው መቆየታቸው የሚያሳየው ቀደምት ክርስቲያኖች በሁለቱ መካከል ተቃርኖ እንዳላገኙ ነው። የሐዋርያት ሥራ ላይ “በኢየሱስ ስም ተጠመቁ” (ሐዋ. 2:38) ተብሎ ሲነገር የሚያመለክተው የመጠመቂያ ሥልጣንን (Baptismal Authority) እንጂ የመጠመቂያ ቀመርን (Baptismal Formula) አይደለም። በኢየሱስ ስም መጠመቅ ማለት በጥምቀቱ ላይ የክርስቶስን ባለቤትነትና ሥልጣን ማወጅ ማለት ነው። በወቅቱ የነበሩት አይሁድ በዮሐንስ ጥምቀት ይጠመቁ ስለነበር አሁን ግን የደህንነት ምንጭ በሆነው በኢየሱስ ሥልጣን ሥር መሆናቸውን ለመግለጽ “በኢየሱስ ስም” መጠመቅ ነበረባቸው። ለዚህ ነው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ አንድም ጊዜ አጥማቂዎች “በኢየሱስ ስም” እያሉ ሲያጠምቁ የማይታየው። ሁል ጊዜም ቢሆን በኢየሱስ ስም መጠመቅ ለተጠማቂዎች የሚሰጥ ትዕዛዝ ሆኖ ይታያል። ለዚህም ምክንያቱ ቀደም ሲል እንዳልነው በኢየሱስ ስም መጠመቅ ማለት የኢየሱስን ስልጣን ተቀብሎ መጠመቅ ማለት ስለሆነ ነው። ጌታ ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19 ላይ “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው” ሲል የሰጠው ትዕዛዝ ጥምቀቱ በምን ዓይነት ቃል መፈጸም እንዳለበት የሚያሳይ ለአጥማቂያን የታዘዘ ቀመር ነው። ሐዋርያት የጌታን ትእዛዝ የሚቃረን ተግባር አይፈጽሙም፤ ይልቁንም በኢየሱስ ሥልጣን የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን ስም እየጠሩ አጥምቀዋል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ያሉ ጥንታዊ የቤተክርስቲያን ሰነዶች ይህንን ግልጽ ያደርጉታል። በ1ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የተጻፈው ዲዳኬ (የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ትምህርት) እንዲህ ይላል፦
“ስለ ጥምቀት በሚመለከት እንዲህ አጥምቁ፦ እነዚህን ሁሉ ነገሮች (ትምህርቶች) አስቀድማችሁ ካስተማራችሁ በኋላ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በሕያው (በሚፈስ) ውኃ አጥምቁ።” (ዲዳኬ 7:1)
ሐዋርያት ተጠማቂዎች በኢየሱስ ስም እንዲጠመቁ ያዘዙት የእርሱን ሥልጣን ለመቀበላቸው ምልክት ሲሆን፣ ጥምቀቱን ግን እርሱ ባዘዘው መለኮታዊ ቀመር (በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም) ይፈጽሙት ነበር። እነዚህ ሁለት አገላለጾች አንዱ ሌላውን የሚጻረር ሳይሆኑ ተደጋጋፊ ናቸው። ይህ ጉዳይ ማቴዎስ 28፡19 ጭማሪ መሆኑን ለማሳየት የሚበቃ አይደለም። የጸሐፊውን የመረዳት እጥረት ብቻ የሚያሳይ ነው።
ሙስሊም፦
እንደሚታወቀው አብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት የተዘጋጁት በግሪክ ቋንቋ ቢሆንም የማቴዎስ ወንጌል ግን ከእነርሱ ተለይቶ በዕብራይስጥ (Hebrew) እንደተጻፈ በአጠቃላይ የክርስቲያን ምሁራን ዘንድ ይታመናል።
መልስ፦
በዘመናችን የሚገኙት አብዛኞቹ የክርስትና ምሑራን “የማቴዎስ ወንጌል መጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ ነው” የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉም። ይልቁንም በምሑራን ዓለም እጅግ የጎላውና ተቀባይነት ያለው ድምዳሜ ወንጌሉ መጀመሪያውኑ የተዘጋጀው በግሪክ እንጂ በዕብራይስጥ አይደለም የሚለው ነው። ጥንታዊት ቤተክርስቲያን ማቴዎስ በዕብራይስጥ (ወይም በአረማይክ) ጽፎ ነበር የሚል የሚመስል ወግ ቢኖራትም ጥልቅ የሆነ የጽሑፍና የቋንቋ ጥናት (Linguistic analysis) የሚያሳየው የወንጌሉ በኩረ ጽሑፍ ግሪክ መሆኑን ነው።
ሙስሊም፦
ከሐዋርያውነ-አበው (Apostolic fathers) መካከል አንዱ የሆነውና የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ተማሪ እንደነበር የሚነገርለት “ፓፒያስ ዘኤራጶሊስ” (140 CE) በመልእክቱ ላይ ማቴዎስ ወንጌልን በዕብራይስጥ ቋንቋ አዘጋጅቶ፤ ሌሎች ደግሞ እንደየአቅማቸው በሚችሉት ቋንቋ ከእርሱ ላይ እንደተረጎሙ ጽፏል። በተጨማሪ የፖሊካርፕ ተማሪ የነበረው ቅዱስ ሄራንዮስ (130 – 200 CE) በተመሳሳይ ሀሳቡን በመቀበል “ቅዱስ ማቴዎስ በዕብራውያን መካከል በራሳቸው (ቋንቋ) ዘዬ ወንጌልን ጻፈላቸው” በማለት የማቴዎስ ወንጌል የበኩር-ጽሑፍ ቋንቋ “Hebrew” መሆኑን ያፀድቃሉ።
በተመሳሳይ የሦስተኛው ክ/ዘመን የክርስቲያን ምሁር የነበረው አርጌንስ ዘአሌክሳንደርያ (185–255 CE)’ም በበኩሉ “ከሰማይ በታች የማያከራክሩ ግልጽ የሆኑ አራት ወንጌላት መካከል በአንድ ወቅት ቀራጭ የነበረው ማቴዎስ በዕብራይስጥ ቋንቋ ወንጌልን አዘጋጅቷል፤” በማለት የበኩር ሥራ (Original text) ቋንቋው ወንጌል እብራይስጥ መሆኑን በግልጽ ተናግሯል።
እንደ ኤጲፋንዮስ ያሉ የቤተክርስቲያን አባቶችም ይህንኑ አቋም ይደግፋሉ። በተጨማሪ ቅዱስ ጄሮምም እንዲሁ ማቴዎስ በዕብራይስጥ ቋንቋ ወንጌል ጽፎ እንደነበር ተናግሯል። የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን በእብራይስጥ ቋንቋ ማዘጋጀቱ በቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ በምልአት የሚታመንበት እውነታ ነው።
መልስ፦
ፓፒያስ “ማቴዎስ ንግርቶቹን (logia) በዕብራይስጥ ዘዬ ሰበሰበ፤ እያንዳንዱም እንደየአቅሙ ተረጎማቸው” ብሏል። ሆኖም እዚህ ላይ መነሳት ያለባቸው ነጥቦች አሉ። ፓፒያስ የተጠቀመው “ሎጊያ” የሚለው ቃል “የንግግሮች ስብስብ” ማለት እንጂ የግድ “ሙሉ ወንጌልን” ላያመለክት ይችላል። “የዕብራይስጥ ዘዬ” (Hebrew dialect) ማለቱ አረማይክን ሊያመለክት ይችላል። ስለዚህ ፓፒያስ የተናገረው አሁን በእጃችን ስላለው ቀኖናዊ የማቴዎስ ወንጌል ስለመሆኑ እርግጠኛ ማስረጃ የለም። ይህንን በተመለከተ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሙስሊሙ ወገናችን በማስረጃነት ከጠቀሳቸው ምንጮች መካከል አንዱ የሆነው የቲንዴል ማብራርያ እንዲህ ሲል ጽፏል፦
ስለዚህ ወግ [ማቴዎስ በዕብራይስጥ ጻፈ ስለሚለው] በእጃችን ካሉ የጽሑፍ ማስረጃዎች ሁሉ ቀዳሚው በ140 ዓ.ም አካባቢ የነበረው የሄራጶሊስ ጳጳስ ፓፒያስ የሰጠው ምስክርነት ነው። ይህ ምስክርነት በአውሳብዮስ የታሪክ መጽሐፍ (H.E. iii.39.16) ላይ እንዲህ ተብሎ ተጠቅሷል፦
Matthew compiled the oracles in the Hebrew dialect, and everyone translated them as best he could.
“ማቴዎስ ንግርቶቹን በዕብራይስጥ ዘዬ ሰበሰበ (አቀናበረ)፤ እያንዳንዱም እንደየአቅሙ ተረጎማቸው።”
ይህ በአውሳብዮስ አማካይነት የተጠቀሰው አውድ አልባ ዓረፍተ ነገር (ምንም እንኳን አውሳብዮስ ፓፒያስ የሚናገረው ስለ ማቴዎስ ወንጌል እንደሆነ ቢያምንም) በውስጡ ብዙ አሻሚ ትርጉሞችን የያዘ ነው። በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ ያሉት ቁልፍ ቃላት በተለያየ መንገድ ሊተረጎሙ የሚችሉ ሲሆን ይህ ደግሞ የንግግሩን መልእክት በከፍተኛ ሁኔታ ይለውጠዋል፦
-
- ሰበሰበ (Compiled):- ‘አዘጋጀ’ ወይም ‘አደራጀ’ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።
- ዕብራይስጥ (Hebrew):- ለዕብራይስጥ ወይም ለአረማይክ ቋንቋ ሊያገለግል ይችላል።
- ዘዬ (Dialect):- አብዛኛውን ጊዜ ‘ቋንቋን’ የሚያመለክት ቢሆንም፣ አንዳንዶች ግን የጽሑፍ ‘ሥልትን’ (style) ለማመልከት እንደገባ ይከራከራሉ።
- ተረጎመ (Translated):- ‘ተነተነ’ ወይም ‘አብራራ’ (interpreted) ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።
እስከዚህ ድረስ ግልጽ የሆነው ነገር ፓፒያስ እየተናገረ ያለው ቀደም ብለው የነበሩ መረጃዎችን ስለ ‘መሰብሰብ’ (እንደ አዘጋጅ/editor) ወይም ደግሞ ራሱ ስለ ‘መጻፍ’ (እንደ ደራሲ/author) ሊሆን እንደሚችል ነው። ይህ አነጋገር ጽሑፉ የተዘጋጀው በአንዱ ሴማዊ ቋንቋ መሆኑንና በኋላም (ምናልባትም ወደ ግሪክ) መተርጎሙን የሚጠቁም ቢሆንም አንዳንዶች ግን ፓፒያስ እያለ ያለው “በዕብራይስጥ የጽሑፍ ሥልት” ስለተጻፈ የግሪክ ሥራ ነው ብለው ይከራከራሉ።
ከሁሉ በላይ ግን ትልቁ አሻሚ ቃል “ሎጊያ” (logia) የሚለው ሲሆን፣ ከላይ “ንግርቶች” ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ ቃል አብዛኛውን ጊዜ “ንግግሮች” ወይም “መግለጫዎች” ማለት ነው። አንዱ ብዙም ተቀባይነት የሌለው ግምት ቃሉ ስለ ኢየሱስ የተነገሩ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ስብስብን ያመለክታል የሚል ነው። ነገር ግን በምሑራን ዘንድ በብዛት የሚነሳው ጥያቄ፦ “ፓፒያስ እንዲህ ዓይነቱን ቃል አሁን በእጃችን እንዳለው ‘የማቴዎስ ወንጌል’ ላለ መጽሐፍ ሊጠቀምበት ይችላል ወይ? ወይስ እየተናገረ ያለው በኋላ ላይ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ስለተካተቱት ‘የኢየሱስ ንግግሮች ስብስብ’ ብቻ ነው?” የሚለው ነው። (Tyndale Commentary I by France, R. T. (1985). Matthew: an introduction and commentary (Vol. 1, pp. 33–34). InterVarsity Press.)
ይህ የምሁሩ አር. ቲ. ፍራንስ ትንተና የሚያሳየው የፓፒያስ ንግግር ሙስሊሙ ወገናችን እንደሚለው “የማቴዎስ ወንጌል ኦሪጅናል ቋንቋ ዕብራይስጥ መሆኑን” የሚያረጋግጥ የማያዳግም ማስረጃ አለመሆኑን ነው። ይልቁንም ንግግሩ በውስጡ ብዙ ጥርጣሬዎችንና ትርጉሞችን ያዘለ በመሆኑ ለድፍን ድምዳሜ እንደማይበቃ በግልጽ ያስረዳል።
ሄሬኔዎስ “ማቴዎስ በዕብራውያን መካከል በገዛ ቋንቋቸው ጻፈላቸው” ማለቱ ትክክል ነው። ነገር ግን መረጃው እንደ ፓፒያስ ባሉ ቀደምት ታሪኮች ላይ የተመሠረተ እንጂ ራሱ ያረጋገጠው የእጅ ጽሑፍ ማስረጃ ኖሮት አልጻፈም። ይህ አባባሉ በዕብራይስጥ የተጻፈን ዕትም፣ የሆነ ዓይነት የቀደመ ምንጭ ወይም አሁን ያለውን የግሪክ ወንጌል እንደሚያመለክት ግልጽ አላደረገም። ኦሪገንም ቢሆን ማቴዎስ ለአይሁድ በዕብራይስጥ እንደጻፈ ቢናገርም ራሱ አይቶ የመሰከረው ሳይሆን ከቤተክርስቲያን ወግ የሰማውን ዘገባ ነው ያስተላለፈው። ዞሮ ዞሮ ሁሉም ለብዙ ትርጉሞች ወደ ተጋለጠው አሻሚ ወደሆነው የፓፒያስ ንግግር ይመለሳል።
ጄሮም “የዕብራይስጥ ማቴዎስ” አይቻለሁ ብሏል፤ እንዲሁም መጽሐፉን ከአይሁድ-ክርስቲያን ወገኖች (ናዝራውያንና ኢብዮናውያን) ጋር ያያይዘዋል። ሆኖም ግን አብዛኞቹ ምሑራን ጄሮም ያየው አሁን በእጃችን ያለውን ቀኖናዊ ወንጌል ሳይሆን “የዕብራውያን ወንጌል” ተብሎ የሚታወቀውን የተለየ ጽሑፍ እንደሆነ ይስማማሉ። እስከ ዛሬ ድረስ የቀኖናዊው ማቴዎስ ወንጌል “የዕብራይስጥ ትክክለኛ” ቅጂ አልተገኘም።
አብዛኞቹ ምሑራን የማቴዎስ ወንጌል መጀመሪያ የተጻፈው በግሪክ መሆኑን የሚያምኑት በሚከተሉት ምክንያቶች፦
- የቋንቋው ጥራት፦ የግሪኩ ጽሑፍ የትርጉም ምልክቶች የማይታይበትና በራሱ የረቀቀ የግሪክ ቋንቋ አጠቃቀም ያለው ነው።
- ከማርቆስ ወንጌል ጋር ያለው ዝምድና፦ ማቴዎስ በግሪክ ከተጻፈው የማርቆስ ወንጌል ላይ በሰፊው ይጠቅሳል፤ ይህ ደግሞ ኦሪጅናሉ በዕብራይስጥ ተጽፎ ከነበረ የማይመስል ነው።
- የቃላት ጨዋታ (Wordplay)፦ በወንጌሉ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የቋንቋ ስልቶችና አወቃቀሮች በግሪክ እንጂ በዕብራይስጥ ትርጉም የማይሰጡ ናቸው። ስለዚህ የቀደመው የማቴዎስ ወንጌል በዕብራይስጥ ተጽፎ ነበር ማለት እምብዛም ትርጉም አይሰጥም።
ማቴዎስ አስቀድሞ በዕብራይስጥ ተጽፎ ነበር ቢባል እንኳ የውይይቱ መነሻ የሆነው ጥቅስ በዕብራይስጡ ውስጥ እንዳልነበረ ሙስሊሙ ወገናችን እንዴት እርግጠኛ ሊሆን ቻለ? ለዚህ ምላሽ እንዲህ ይለናል፦
ሙስሊም፡-
ይህ ግልጽ ከሆነ፤ ማቴዎስ ለዕብራውያን ሰዎች ያዘጋጀው ወንጌል ላይ በማቴዎስ 28:19 ላይ ልክ ዛሬ እንደምናገኘው የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳልተጠቀሰ ጥንታውያን የክርስትና ምንጮች እና የተለያዩ መድብለ እውቀቶች “Encyclopedias” ያትታሉ። ጥንታዊው የአዲስ ኪዳን ምሁር እና የግሪክ ቤተክርስቲያን ሊቅ የነበረው አውሳብዮስ ዘቂሳሪያ (270-320 CE) ሲሆን አብዛኛው የአዲስ ኪዳን ታሪክ የተወሰዱት ከዚህ ሊቅ መሆኑ በሁሉም ይታመናል⁶። ይህ የቤተክርስቲያኗ ታላቅ የግሪክ መምህር እና በወቅቱ የሃይማኖት ሊቅ የነበሩት አውሳብዮስ በመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን ፁሁፎች ላይ እምነት የነበረውና ለእነርሱ ቅርብ እንደነበረም ይነገርለታል።
የማቴዎስ ወንጌልን በዕብራይስጥ ቋንቋ ማዘጋጀት በአብዛኞቹ የቤተክርስቲያን አባቶች እና ታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ምንም ጥርጥር የሌለበት ጉዳይ ነው። ይህ በዕብራይስጥ የተጻፈው (Original text) ጹሁፍ ልክ የአዲስ ኪዳን የበኩር ጹሁፎች እንደጠፉት እርሱም የጠፋ ሲሆን እንደሌሎቹ ከጊዜ በኋላ ደግሞ የተዘጋጀ ሥራ ዛሬ በእጃችን ላይ ይገኛል። ታድያስ በዚህ በዕብራይስጥ ቋንቋ ተዘጋጅቶ የመጣ ወንጌል ላይ ማቴዎስ 28:19ን ከፍተን ስናየው በሚያስገርም መልኩ ከታች ያለውን ንባብ እናገኛለን፦
-
- Matthieu Shem Tov-Araméen (MT 28:17-20)
-
- When they saw him they worshipped him, but there were some of them who doubted him.
- Jesus drew near to them and said to them: “To me has been given all power in heaven and earth.
- Go
- and (teach) them to carry out all the things which I have commanded you forever.” ⁸
ከላይ በግልጽ እንደምናየው በዕብራይስጡ ማቴዎስ 28:17-20 ድረስ ሙሉ ገጽ ላይ “ሂዱና በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው።” የሚል አንድም ሐረግ የለም። ለመጀመሪያ ጊዜ በራሳቸው በዕብራውያን ቋንቋ ተጽፎ በትውፊት (Oral tradition) የተላለፈው ወንጌል ላይ የመጨረሻዎቹ ትእዛዛት እነዚህ ብቻ ናቸው። በሥላሴ ወይም በሦስቱ አካላት ስም የታዘዘው የጥምቀት ቀመር በቃሉ ላይ ፈጽሞ አይገኝም። ይህ በጥንታዊያን ክርስቲያኖች በሁለተኛው ክ/ዘመን ሥነ-መለኮታዊ አስተምህሮ ለማዋቀር ሰርጎ የገባ ጭማሪ (Interpolation) ነው።
መልስ፦
የ”ሸም ቶብ” (Shem Tov) “የዕብራይስጥ ማቴዎስ” የተዘጋጀው በ14ኛው ክፍለ ዘመን (Middle Ages) ነው።ይህ ሰነድ የተጻፈው ወንጌሉ ከተጻፈ ከ1300 ዓመታት በኋላ ነው። በአሥራ አራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረን ሰነድ መሠረት አድርጎ በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩትን እጅግ ጥንታዊ የግሪክ ቅጂዎች “ስህተት ናቸው” ማለት በታሪክና በሳይንሳዊ ምርምር ተቀባይነት የለውም። ይህንንም መሠረት አድርጎ የሚሞግት ነፍስ ያለው ምሑር የለም። ይህንን እውነታ እንደሚከተለው ሰፋ አድርገን እናብራራዋለን።
የሸም ቶብ የዕብራይስጥ ማቴዎስ ወንጌል ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበረና በጥንታውያን “የዕብራውያን ወንጌል” ተብሎ የሚታወቀው ኦሪጅናል ጽሑፍ ነው የሚለው አባባል በታሪክና በጽሑፍ ምርመራ (Textual Criticism) ሚዛን ሲመዘን ፍጹም መሠረተ ቢስ መሆኑ ተረጋግጧል። በሆሴ-ቪሴንቴ ኒክሎስ አልባራሲን (José-Vicente Niclós Albarracín) ጥናት መሠረት፣ ይህ ጽሑፍ በ13ኛው እና በ14ኛው ክፍለ ዘመን በደቡብ ፈረንሳይና በሰሜን ስፔን አካባቢ የተዘጋጀ የመካከለኛው ዘመን ስብስብ (Medieval composite) ነው። ጽሑፉ የተቀዳው ከጥንታዊ ዕብራይስጥ ሳይሆን መጀመሪያ ከላቲን ቩልጌት (Latin Vulgate) ወደ ፕሮቬንሳልና ካታላን (Provençal/Catalan) ቋንቋዎች ከተተረጎሙ የካቶሊክ የሥርዓተ አምልኮ መጻሕፍት መሆኑን በውስጡ የሚገኙት ቃላት በግልጽ ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት እንደ “liri”፣ “feno” እና “pan sagrat” ያሉ ቃላት በዚያ ዘመን በነበሩት የአካባቢው ቋንቋዎች (Romance languages) ይነገሩ የነበሩ እንጂ በጥንታዊ ዕብራይስጥ የሚታወቁ አይደሉም።
በተጨማሪም በሸም ቶብ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኙት ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎች (Glosses) በቀጥታ ከመካከለኛው ዘመን የላቲን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜዎች (Glossa Ordinaria) የተወሰዱ ናቸው። ይህም የሚያሳየው ጽሑፉ የተዘጋጀው በ14ኛው ክፍለ ዘመን በነበረ አይሁዳዊ ጸሐፊ ሲሆን ዓላማውም በወቅቱ ከነበሩ የክርስትና ሰባኪያን ጋር ለሚደረግ የሃይማኖት ክርክር (Polemics) እንዲያገለግል መሆኑን ነው። ሂደቱም ከላቲን ወደ ካታላን፣ ከዚያም የካታላን ቋንቋ ተናጋሪዎች በነበሩ ወደ ይሁዲነት በተመለሱ ሰዎች (Jewish converts) አማካኝነት ወደ ዕብራይስጥ የተተረጎመ መሆኑን በጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት የቃላት አወቃቀርና አገላለጾች ምስክሮች ናቸው። ስለዚህ የሸም ቶብ ማቴዎስ የወንጌሉ የበኩር ጽሑፍ ሳይሆን ከአንድ ሚሊኒየም በኋላ ከተለያዩ የላቲንና የሮማንስ ቋንቋዎች የተውጣጣ የመካከለኛው ዘመን ትርጉም በመሆኑ ይህ ሐሰተኛ ሰነድ የማቴዎስ 28፡19ን ትክክለኛነት ለማጣጣል እንደ ታሪካዊ ማስረጃ ሊቀርብ አይችልም። (José-Vicente Niclós Albarracín, “The Hebrew Gospel of Matthew in Shem Tob’s Eben Boḥan: Particular Features and Medieval Sources,” Revue des études juives 181, no. 1–2 (2022): 138-157).
ሙስሊም፦
ይህንን በተመለከተ አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ መደበኛ ትርጉም (New Revised Standard Version) በግርጌ ማስታወሻው ላይ እንዲህ ይላል “የዘመናችን ኋያሲያን ይህ (በማቴዎስ 28፥19) ላይ የተጠቀሰው ቃል በውሸት የኢየሱስ ንግግር ተደርጎ የተጨመረበትና በኋላ ላይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መግለጫ ተደርጎ የቀረበ እንጂ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ በየትኛውም መፅሐፍ ውስጥ በእነዚህ ሦስቱ ስሞች ጥምቀት የታዘዘበት አንድም ሥፍራ የለም ይለናል። ዓለማቀፋዊው የመጽሐፍ ቅዱስ መድብለ-እውቀትም (Encyclopedia) ማቴ 28፥19 ለሥላሴ ማስረጃ ይሁን ዘንድ ከግዜ ቡኋላ እንደተጨመረበት አስረግጦ ጽፏል።
የዊሊያም ቴንደል “William Tyndale” (1490 CE) የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በሐዲስ ኪዳን ላይ በሰጠው ማብራሪያ ማቴዎስ ወንጌል ላይ የሚከተለውን ጽፏል፦ “በአብ፣ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚሉ ቃላት ከኢየሱስ የወጣ ትክክለኛ ንግግር ሳይሆን ቡኋላ ላይ የተጨመረበት ጭማሪ ነው። በማለት እርግጡን ያምናል። ይህ ሰርጎ-ገብ (Interpolation) መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጨመረው በሁለተኛው ክ/ዘመን ላይ መሆኑን ዘመናዊያን ምሁራን ይስማማሉ።
በተጨማሪ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ (270-320 CE) ማቴዎስ 28፥19’ን ጠቅሶ ሲያብራራ ለደቀ መዛሙርቱ “ሂዱና በስሜ አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲላቸው ከሕዝቡ መካከል በስውር የኃይሉን በጎነት አሳይቷል።” በማለት ነው የጠቀሱት።
ይህ የቤተክርስቲያን አባት በታላቁ ተልዕኮ (The Great Mission) ወቅት ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “አሕዛብን እያጠመቃችሁ ደቀመዛሙርት አድርጉ” በማለት ባዘዛቸው ጊዜ ጥምቀትን “በስሜ” ብሎ እንጂ በሦስት አካላት (በሥላሴ) ስም አለማዘዙን በግልጽ ጽፏል። ምንም እንኳን በሌላ ስፍራ ላይ ተስተካክሎ በሦስቱ አካላት ስም እንዲያጠምቁ መታዘዛቸውን የጻፈ አድርገው በኋላ ቢጨምሩበትም ቀዳማዊያን መዛግብት ላይ ሐዋርያት የታዘዙት “በኢየሱስ ስም” መሆኑን አውሳብዮስ ተናግሯል። ከላይ ቀደም ብለን እንደገለጽነው ጥቅሱ የተጨመረው በሁለተኛው ክ/ዘመን ላይ በመሆኑ በወቅቱ የነበሩ ጥቂት አባቶች የተስተካከለውን ንባብ ጠቅሰዋል። በማቴዎስ ወንጌል የዕብራይስጡ ጽሑፍ ላይ ግን ፈጽሞ አልተገኘም። ይህም ክፍሉ ሰርጎ ገብ መሆኑን ያመክታል።
መልስ፦
ሙስሊሙ ወገናችን “አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ መደበኛ ትርጉም (New Revised Standard Version) በግርጌ ማስታወሻው ላይ እንዲህ ይላል” በማለት የጻፈው በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ፈፅሞ የማይገኝ የተሳሳተ ጥቅስ ነው። ይህ አባባል መጀመሪያ ኢንተርኔት ላይ በኦንሊ ጂሰስ እምነት ተከታዮች የተነገረ ይመስላል። አንዳንዶችም ምንጩን ሳያውቁ እያጣቀሱ የሚገኙ ሲሆን በNRSV በየትኛውም ህትመት ላይ አይገኝም። ሙስሊሙ ወገናችን ምንጩን ሳያረጋግጥ በግድ የለሽነት በመጥቀሱ ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ሠርቷል። ሲጀመር አሁን በእጃችን በሚገኙት ማቴዎስ 28ን በያዙ የእጅ ጽሑፎች ሁሉ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ እንዲህ ያለ ንግግር ሊናገር የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የለም። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በተፋፋመው የላዕላይ ሕያሴ (Higher Criticism) ሳብያ ይህ ንግግር በኢየሱስ ሊነገር ይችላል ወይስ አይችልም የሚል መላ ምታዊ ክርክር ነበር። ይህ ማለት ጽሑፉ የማቴዎስ ወንጌል አካል አልነበረም የሚል የታህታይ ሕያሴ (Lower Criticism) ጉዳይ አልነበረም ማለት ነው። ሙስሊሙ ወገናችን በሁለቱ መካከል የሚገኘውን ልዩነት ባለማወቅ ሲጽፍ ይታያል።
The International Standard Bible Encyclopedia, Vol. 4 page 2637 የሚያሳየው ሙስሊሙ ወገናችን ምንጮችን እንዴት “ቆርጦ በመቀጠል” (Selective quoting) ለራሱ እንዲመች አድርጎ እንደተጠቀመባቸው ነው። ጽሑፉን በጥንቃቄ ስናነበው መድብለ-ዕውቀቱ (ISBE) ተከራካሪው ያለውን ሳይሆን የተቃራኒውን ሐሳብ እንደደገፈ እንረዳለን።

ልዩነቱን እንዲህ እንመልከት፦
- “ይባላል” (It has been argued) vs “እውነታው ግን” (It is evident, however)
በምስሉ ላይ የሚታየው ጽሑፍ በሁለት ይከፈላል፦
- የመጀመሪያው ክፍል (ሙግት አቅራቢው የጠቀሰው)፦ ጽሑፉ “እንደሚከራከሩት ከሆነ…” (It has been argued that…) በማለት ይጀምርና የለዘብተኛ ምሑራንን (እንደ Harnack ያሉ) ትችት ይዘረዝራል። እነዚህ ሰዎች “ማቴዎስ 28፡19 በኋላ የመጣና ከኢየሱስ አፍ ያልወጣ ነው” ይላሉ።
- ሁለተኛው ክፍል (መድብለ–ዕውቀቱ የሰጠው ምላሽ)፦ መድብለ-ዕውቀቱ ወዲያውኑ እንዲህ ይላል፦ “ሆኖም ግን እነዚህ ተቃውሞዎች ልዕለ-ተፈጥሯዊ ነገሮችን ካለመቀበል ጥላቻ የመነጩ እንደሆኑ ግልጽ ነው“ (It is evident, however, that some of these objections rest upon anti-supernatural presuppositions…)።
- የመድብለ–ዕውቀቱ (ISBE) ድምዳሜ
ጽሑፉ በስተመጨረሻ የሚሰጠው ድምዳሜ ሙግት አቅራቢው ካለው ፍጹም ተቃራኒ ነው፦
- ጽሑፉ እንዲህ ይላል፦ “ጥምቀት ከክርስትና የመጀመሪያ ቀናት ጀምሮ የነበረ መሆኑን… እና ጳውሎስ እንኳ አስፈላጊነቱን ተጠራጥሮ አለማወቁን ስናይ… ይህ ትእዛዝ በራሱ በጌታ ያልተሰጠ ነው ብሎ ማሰብ ይከብዳል” (On any other supposition than that of its appointment by Our Lord Himself it is difficult to conceive…)።
- የሙግት አቅራቢው ስህተት
ሙስሊሙ ወገናችን ያደረገው ነገር በትምህርት ዓለም “Quote Mining” ይባላል። ይህም ማለት አንድ ጸሐፊ ሌሎችን ለመሞገት የጠቀሰውን “ተቃራኒ ሐሳብ” ወስዶ የጸሐፊው የራሱ ድምዳሜ አስመስሎ ማቅረብ ነው።
- ተከራካሪው ጥቅሱን የቆረጠው መድብለ-ዕውቀቱ ውስጥ ከሰፈረው የሌላ ሰው ትችት (Objection) ላይ ነው።
- መድብለ-ዕውቀቱ የሰጠውን ምላሽ (Refutation) ግን ሆን ብሎ ዘልሎታል። ምናልባትም ምንጩን በቀጥታ ሳያነብ ከሌላ ሁለተኛ ምንጭ ላይ ስለወሰደ ለስህተት ተዳርጓል። ሆን ብሎ ከዘለለ ማጭበርበር ፈፅሟል፤ ሳያጣራ ከሌላ የተጭበረበረ ምንጭ ላይ ከወሰደ ደግሞ ኃላፊነት የተሞላበት ጥንቃቄ ባለመውሰዱ ተወቃሽ ይሆናል። በሁለቱም ጥፋተኛ በመሆኑ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባዋል።
ባጭሩ ይህ ኢንሳይክሎፔዲያ ማቴዎስ 28፡19 “ጭማሪ ነው” አይልም፤ ይልቁንም “ጭማሪ ነው የሚሉት ሰዎች መረጃ የላቸውም፣ ትእዛዙ ከጌታ የመጣ ነው” ብሎ ነው የሚደመድመው። ሲጀመር ጭማሪ ነው ባዮቹ የማቴዎስ ወንጌል ሲጻፍ አብሮ አልተጻፈም የሚል የንባብ ሕየሳ ሙግት ሳይሆን የታሪካዊ ሕየሳ ሙግት እያቀረቡ ነው። ሙስሊሙ ጸሐፊ የሚናገረውና የጽሑፉ ሐሳብ አራምባና ቆቦ ነው።
የቲንዴል መጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያን (Tyndale New Testament Commentary) መነሻ በማድረግ “ማቴዎስ 28፡19 በኋላ የመጣ ጭማሪ ነው” የሚለን ወገናችን አሁንም በምሑራዊ ዓለም እጅግ ነውር የሆነውን ተግባር ፈፅሟል። ጽሑፉን የሚያነብ ሰው የቲንዴል ኮሜንተሪ ተጻራሪውን ሐሳብ ለመደገፍ ሳይሆን ውድቅ ለማድረግ መጻፉን በቀላሉ መረዳት ይችላል።

ተከራካሪው የፈጸመውን የማስረጃ ማጭበርበር እንመልከት፦
- የጸሐፊውን ድምዳሜ ሆን ብሎ መደበቅ
ተከራካሪው የቲንዴል ኮመንተሪ ስለ አውሳብዮስ (Eusebius) አጭር ጥቅስ የጠቀሰበትን ክፍል ብቻ ወስዶ ጸሐፊው ጥቅሱን “ጭማሪ ነው” እንዳለ አድርጎ አቅርቧል። ነገር ግን የዚህ የቲንዴል ኮሜንተሪ ቅጽ ጸሐፊ (R.T. France) ይህንን ትወራ ውድቅ የሚያደርግበትን ተከታይ ዓረፍተ-ነገር ሆን ብሎ ዘልሎታል። ጸሐፊው በግልጽ እንዲህ ይላል፦
“…በእጃችን ያለ አንድም (No extant) የማቴዎስ ወንጌል የእጅ ጽሑፍ ይህንን [የአውሳብዮስን] ንባብ አለመያዙ የሚያሳየው ይህ የአውሳብዮስ የራሱ ማሳጠሪያ (abbreviation) እንጂ በእጅ ጽሑፎች ውስጥ ያገኘው ቃል አለመሆኑን ነው።“
ይህ ማለት የቲንዴል ኮሜንተሪ “ጥቅሱ ጭማሪ ነው” ለሚለው ግምት መልስ እየሰጠ እንጂ ግምቱን እየደገፈ አይደለም።
የሚገርመው ነገር ሙስሊሙ ጸሐፊ “ምንም እንኳን በሌላ ስፍራ ላይ ተስተካክሎ በሦስቱ አካላት ስም እንዲያጠምቁ መታዘዛቸውን የጻፈ አድርገው በኋላ ቢጨምሩበትም…” በማለት ክርስቲያኖችን የአውሳብዮስን ጽሑፍ በመበረዝ ለመክሰስ ይሞክራል። ነገር ግን ጽሑፎቹ የራሱ የአውሳብዮስ መሆናቸው በምሑራን ዘንድ በእጅጉ የታመነ ነው። አውሳብዮስ በኋለኞቹ ጽሑፎች ውስጥ ሥላሴያዊ ቀመርን መጥቀሱ የገዛ ሙግቱን ውድቅ ስለሚያደርግበት ብቻ እንዲህ ያለ ማስረጃ የሌለው ክስ ማቅረብ ትዝብት ላይ ይጥላል።
- “ኢየሱስ መሠረተው” የሚለውን ክፍል ባላየ ማለፍ
ማብራሪያው ገና ሲጀምር እንዲህ ይላል፦ “Jesus now institutes one [baptism] with a fuller meaning.” ጸሐፊው ኢየሱስ ይህንን የሥላሴ ስም ያለበትን የጥምቀት ሥርዓት “መሠረተ” (Institutes) ብሎ በግልጽ ጽፏል። ተከራካሪው ግን ጸሐፊው “ኢየሱስ አልተናገረውም” እንዳለ አድርጎ ማቅረቡ ጽሑፉን ጨርሶ አለማንበቡን ወይም ሆን ብሎ እውነታውን ማጣመሙን ያሳያል።
- የሥላሴን አንድነት የሚገልጸውን ትንተና መሸፈን
ቲንዴል በማብራሪያው ላይ ማቴዎስ 28፡19 ስለ ሥላሴ አንድነት የሚሰጠውን ትምህርት እንዲህ ያጠናክራል፦
- “Name” (ስም) የሚለው ቃል በነጠላ ቁጥር (Singular) መጠቀሱ የሦስቱን አካላት አንድነት (Unity of the three Persons) እንደሚያሳይ፤
- ኢየሱስ ራሱ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የአምልኮ (Worship) ማዕከል መሆኑን ያብራራል።
ተከራካሪው “ቲንዴል ጥቅሱ ጭማሪ መሆኑን እርግጠኛ ሆኖ ያምናል” ማለቱ ጸሐፊው ለሥላሴ አስተምህሮ የሰጠውን ይህን ጥልቅ ድጋፍ ሆን ብሎ ከመደበቅ የመጣ ነው።
ተከራካሪው ያደረገው ነገር የጸሐፊውን ተቃዋሚ ሐሳብ ወስዶ እንደ ጸሐፊው አቋም አድርጎ ማቅረብ ነው። ቲንዴል በማያሻማ ሁኔታ የሚከተሉትን ነጥቦች አረጋግጧል፦
- ጥቅሱ በሁሉም የእጅ ጽሑፎች ላይ ይገኛል፤
- የአውሳብዮስ ጥቅስ ማሳጠሪያ (Abbreviation) እንጂ ሌላ ጽሑፍ አይደለም፤
- ትእዛዙ ከራሱ ከኢየሱስ የመጣ (Instituted by Jesus) ነው።
ተከራካሪው የጸሐፊውን ምላሽ ደብቆ ጸሐፊው የነቀፋቸውን ሰዎች ሐሳብ እንደ ጸሐፊው ድምዳሜ አድርጎ ማቅረቡ ምንጮችን በታማኝነት የማያነብ ወይም እውነታውን ለማጣመም የሚጥር መሆኑን ያሳያል። ይህ ካልሆነ ግን ዋናውን መጽሐፍ ገልጦ ሳያነብ ከሌላ የተጭበረበረ ምንጭ በመውሰድ ለስህተት ሊዳረግ ችሏል። በእኔ ግምት ግን ቀደም ሲል NRSV ውስጥ የሌለ አባባል በመጻፉ የጠቀሳቸውን ምንጮች ሳያነብ ከሌላ የተሳሳተ ጸረ-ሥላሴያዊ ምንጭ ያለ ጥንቃቄ ወስዷል። እንዲህ ያለ የጥንቃቄ ጉድለት ልፋቱ ላይ ጥላ ስለሚያጠላበት ለወደፊቱ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ። እርሱ ከተናገረው በተጻራሪ የቲንዴል ማብራሪያ ማቴዎስ 28፡19 የኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ ቃል መሆኑን በጽኑ ያረጋግጣል።
ሌላው “ይህ ሰርጎ–ገብ (Interpolation) መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጨመረው በሁለተኛው ክ/ዘመን ላይ መሆኑን ዘመናዊያን ምሁራን ይስማማሉ” በማለት ብሪታኒካን በመጥቀስ የተናገረው ሐሰት ነው። መድብለ ዕውቀቱ ስለ ማቴዎስ ጽሑፍ ጭማሪ መሆን ምንም የተናገረው ነገር የለም። ይልቁኑ ይህ ጊዜው ያለፈበት ምንጭ (በ1910 ዓ.ም የታተመ ነው) በዘመኑ ትልቅ ቦታ የተሰጠውን የላዕላይ ሕያሴ (Higher Criticism) አካሄድ በመጠቀም ሥላሴያዊ ጥምቀት ቀደምት አይደለም የሚለውን ግምት ያንጸባርቃል። ይህም የማቴዎስ ወንጌል ሲጻፍ ጥቅሱ አልነበረም በሚል እሳቤ ላይ የተመሠረተ ሙግት አይደለም።
ጸሐፊው ጥቅሱ በ2ኛው ክፍለ ዘመን የገባ ጭማሪ ነው የሚል መላ ምት ቢያቀርብም የታሪክ መዛግብት ግን ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ እውነታን ይነግሩናል። ጥቅሱ በኒቅያ ጉባኤ ጊዜ ለሥነ-መለኮት ፍጆታ ተብሎ የገባ ሳይሆን ገና ከ1ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ በተለያዩ አህጉራት በሚገኙ የቤተክርስቲያን አባቶች ዘንድ የታወቀና በጥምቀት ሥርዓት ውስጥ ይሠራበት የነበረ ነው። ቀደም ሲል ከጠቀስነው ዲዳኬ ከተሰኘው የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ጽሑፍ በተጨማሪ ተከታዮቹ የአበው ጽሑፎች ክፍሉ ቅድመ ኒቅያ ምን ያህል ታዋቂ እንደ ነበረ ይመሰክራሉ፦
ዮስጢኖስ ሰማዕት (Justin Martyr – 160 ዓ.ም አካባቢ)
ዮስጢኖስ ሰማዕት በጻፈው የመጀመሪያው የመከላከያ ጽሑፉ (First Apology 61) ላይ ጥምቀት የሚከናወነው “በሁሉም ጌታና አባት በሆነው በእግዚአብሔር፣ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ስም” መሆኑን ገልጿል። ዮስጢኖስ በሌላ ቦታ (Dialogue with Trypho) ላይ “በክርስቶስ ስም ደቀመዛሙርት ማድረግ” የሚለውን አህጽሮተ ቃል መጠቀሙ፣ ከሥላሴያዊው የጥምቀት ቀመር ጋር ይጋጫል ማለት አይደለም። ይልቁንም ቀዳማይቷ ቤተክርስቲያን እነዚህን ሁለት አገላለጾች እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች አጣጥማ ትረዳቸው እንደነበር ያሳያል።
ቀለሜንጦስ ዘእስክንድርያ እና ቴዎዶተስ (Clement of Alexandria – 150-215 ዓ.ም)
ቀለሜንጦስ ዘእስክንድርያ፣ ቴዎዶተስ የተባለውን ኖስቲካዊ (Gnostic) መምህር ዋቢ በማድረግ እንደጻፈው ጌታ ለሐዋርያቱ “ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ” የሚል ትእዛዝ እንደሰጣቸው ገልጿል (Excerpta ex Theodoto 76)። ይህም የሚያሳየው ሥላሴያዊው ቀመር በትክክለኛ አማኞች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከቤተክርስቲያን በወጡ ቡድኖች ዘንድ እንኳ ሳይቀር የታወቀና ተቀባይነት የነበረው መሆኑን ነው።
ጠርጡለስ (Tertullian – 160-225 ዓ.ም)
ጠርጡለስ በሦስት የተለያዩ መጻሕፍቱ ላይ ይህንን ጥቅስ በዝርዝር ጠቅሶታል። በተለይም “ስለ ጥምቀት” (On Baptism 13) በተባለው መጽሐፉ ላይ፦ “የጥምቀት ሕግ ታውጇል፣ ቀመሩም ተደንግጓል፤ ሂዱና አሕዛብን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ አስተምሯቸው ይላል” በማለት ጥቅሱን እንደ መለኮታዊ ትእዛዝ (Prescribed law) ያቀርበዋል። ጠርጡለስ ይህንን ሲጽፍ ጥቅሱ “ሊጨመር ወይም ሊቀነስ” የማይችል የቤተክርስቲያን መሠረታዊ ሕግ መሆኑን አስምሮበታል።
ቆጵሪያኖስ (Cyprian – 258 ዓ.ም የሞተ)
በ3ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የነበረው ቆጵሪያኖስ በማቴዎስ 28፡19 የሚገኘውን ሥላሴያዊ ቀመር ደጋግሞ ተጠቅሞበታል። በተለይም በ258 ዓ.ም በተካሄደው በሰባተኛው የካርቴጅ ጉባኤ ላይ ከቤተክርስቲያን ውጭ የሚደረጉ ጥምቀቶች ዋጋ የላቸውም የሚለውን ሙግት ለማጠናከር ይህ ጥቅስ እንደ ዋና ማስረጃ ቀርቧል (Epistles of Cyprian 24)። በወቅቱ የነበሩት ጳጳሳት ሁሉ ጥቅሱ “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” የሚል መሆኑን ያለምንም ጥርጥር ተቀብለውታል።
ኢግናጥዮስ ዘአንጾኪያ (Ignatius of Antioch – ከ107–112 ዓ.ም አካባቢ)
ኢግናጥዮስ የሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር እንደነበረ የሚታወቅና በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እጅግ ቀዳሚ ከሚባሉት አባቶች አንዱ ነው። ቤተክርስቲያን በምትቀበላቸው አንዳንድ ጽሑፎቹ ውስጥ ጥቅሱን በቀጥታ የጠቀሰ ቢሆንም ስለ ትክክለኛነታቸው በምሑራን ዘንድ ስምምነት የለም። ቢሆንም ግን ጽሑፎቹን ከግምት ውስጥ ማስገባት አይከፋም።
ቪክቶሪነስ (Victorinus – 270-303 ዓ.ም አካባቢ)
በ3ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የነበረውና በሰማዕትነት ያለፈው ቪክቶሪነስ በዮሐንስ ራእይ ትርጓሜው ላይ ለማቴዎስ 28፡19 ጥንታዊ ምስክርነት ሰጥቷል።
-
በዮሐንስ ራዕይ ማብራሪያው (ምዕራፍ 1፡15) ላይ፦ “ድምፁም እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ነበረ” የሚለውን ቃል ሲተረጉም፣ “ብዙ ውኃዎች” የተባሉት ወንጌልን የተቀበሉ ሕዝቦች ወይም ሐዋርያት የተላኩበት “የጥምቀት ጸጋ” መሆኑን ይገልጻል። ይህንን ሐሳብ ለማጠናከርም ጌታ ለሐዋርያቱ፦ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ አስተምሯቸው” ማለቱን እንደ ዋና ማስረጃ ይጠቅሳል። ይህም ጥቅሱ ከኒቅያ ጉባኤ በፊት በነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች (Commentaries) ውስጥ ሳይቀር ሥር የሰደደ መሆኑን ያሳያል።
ከላይ የቀረቡት ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ማቴዎስ 28፡19 ከመጀመሪያው ጀምሮ በሮም (ምዕራብ)፣ በሰሜን አፍሪካ (ካርቴጅ) እና በእስክንድርያ (ምሥራቅ) በስፋት የታወቀ ነበር። ይህ ሰፊ መልክዓ ምድራዊ ስርጭት ጥቅሱ “በኋላ ላይ የተጨመረ” ነው የሚለውን ግምት ውድቅ ያደርጋል። ይልቁንም ጥቅሱ ወንጌሉ ከተጻፈበት ጊዜ ጀምሮ የነበረና የቤተክርስቲያን የሥርዓተ አምልኮና የትምህርተ መለኮት ማዕከል መሆኑን ያረጋግጣል።
ማጠቃለያ
የማቴዎስ ወንጌል 28፡19 ትክክለኛነትና በውስጡ የያዘው ሥላሴያዊ የጥምቀት ቀመር ከጥንት ጀምሮ የነበረ እንጂ በኋላ ላይ የተጨመረ አለመሆኑን የሚያሳዩ ምሑራዊና ታሪካዊ ማስረጃዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ጥቅሱ “ሰርጎ-ገብ” ነው የሚለው ክስ በቂ ማስረጃ የሌለውና በብራና ጥናት (Textual Criticism) ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ነው። ይህ ጥቅስ ‘ሰርጎ-ገብ’ ነው የሚለው ሙግት እንደ ከርትና ባርባራ አላንድ፣ ብሩስ መዝገር፣ ባርት አህርማን እና ዳንኤል ዋላስ ካሉ የንባብ ሕየሳ ዓለማቀፍ ሊቃውንት ዘንድ የሚቀርብ አይደለም። ይልቁንም ይህ አቋም የሚስተዋለው በምሑራዊው ዓለም ተቀባይነት በሌላቸውና በቅድመ-ግምት በሚመሩ ጸረ-ሥላሴያዊ ግለሰቦች ዘንድ ብቻ ነው። እስካሁን ያነሳናቸውን ሐሳቦች በተከታዮቹ ነጥቦች እናጠቃለላለን፦
የብራና ጽሑፎችና የታህታይ ሕያሴ (Lower Criticism) ማስረጃ
በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት “ታህታይ ሕያሴ” ወይም የብራና ምርመራ (Textual Criticism) የሚባለው ዘርፍ የሚያተኩረው በቀጥታ በብራናዎቹ ይዘት ላይ ነው። በዚህ ረገድ የማቴዎስ 28፡19 ትክክለኛነት ፍጹም ነው። እስካሁን ድረስ በተገኙ እልፍ የግሪክ የብራና ጽሑፎች ላይም ሆነ በትርጉም ሥራዎች ውስጥ ይህ ጥቅስ ያለምንም ልዩነት ተመዝግቦ ይገኛል። ከነዚህም መካከል በ4ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉትና እጅግ ጥንታዊ የሆኑት ኮዴክስ ሲናይቲከስ (Codex Sinaiticus) እና ኮዴክስ ቫቲካነስ (Codex Vaticanus) ሙሉውን ሥላሴያዊ ቀመር ይዘዋል። ጥቅሱ በ2ኛው ክፍለ ዘመን ወይም ከዚያ በኋላ የገባ ጭማሪ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ በጥንታዊ የግሪክ፣ የላቲን ወይም የሶርያ ቅጂዎች መካከል ልዩነት መታየት ነበረበት፤ ነገር ግን በሁሉም ቋንቋዎችና ቅጂዎች ውስጥ ጥቅሱ ወጥ ሆኖ ይገኛል።
የጥንት አባቶችና የዲዳኬ ምስክርነት
ጥቅሱ በኒቅያ ጉባኤ (325 ዓ.ም) ጊዜ ለሥነ-መለኮት ፍጆታ ተብሎ የገባ ነው የሚለውን ክስ የሚያፈርሱ ከኒቅያ በፊት የነበሩ በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። ከነዚህም መካከል በ1ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ (ከ90–100 ዓ.ም) የተጻፈው “ዲዳኬ” (Didache) የተሰኘው ጥንታዊ የክርስቲያኖች መመሪያ “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ” በማለት የማቴዎስን ቃል በቀጥታ ይጠቅሳል ። በተጨማሪም በ2ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት ቅዱስ ሄሬንዮስ በታወቀው “Against Heresies” መጽሐፉ ላይ ጥቅሱን ሙሉ በሙሉ ጠቅሶታል። ዮስጢኖስ ሰማዕትና ጠርጡለስ በተመሳሳይ በ2ኛው እና በ3ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ጥቅሱንና ሥላሴያዊ ጥምቀትን እንደ ቤተክርስቲያን መመሪያ ጠቅሰውታል። ይህም የሚያሳየው ትምህርቱና ቃሉ ገና ከመጀመሪያው የነበረ መሆኑን ነው።
የተቺዎች ግራ መጋባት፦ ላዕላይ ሕያሴ እና ታህታይ ሕያሴ
ምሑራንን አጣቅሰው ክፍሉ ትክክለኛ አይደለም የሚሉ ወገኖች (በዚህ ሙስሊም ጸሐፊ እንዳየነው) ትልቁ ስህተታቸው በ”ላዕላይ ሕያሴ” (Higher Criticism) እና በ”ታህታይ ሕያሴ” (Lower/Textual Criticism) መካከል ያለውን ልዩነት አለማወቃቸው ነው ።
- ታህታይ ሕያሴ (Textual Criticism): በብራናው ላይ ቃሉ አለ ወይስ የለም? የሚለውን ይመረምራል፤ በዚህ መስክ ቃሉ በሁሉም ብራናዎች ላይ መኖሩ ተረጋግጧል። ይህንን በተመለከተ በምሑራን ዘንድ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የለም።
- ላዕላይ ሕያሴ (Higher Criticism): ይህ ደግሞ ስለ ጽሑፉ ሥነ-ጽሑፋዊ መዋቅርና ሥነ-መለኮታዊ እድገት የሚመረምር ነው። ጸሐፊው አንዳንድ ምሑራን ስለ “ሥላሴ አስተምህሮ እድገት” ያነሱትን የላዕላይ ሕያሴ ጥያቄዎች እንደ ብራና ስህተት (Textual corruption) አድርጎ ተረድቶታል። ምሑራኑ “ይህ አስተምህሮ እንዴት ዳበረ?” ብለው ሲጠይቁ ጥቅሱ በብራና ላይ የለም ማለታቸው አይደለም። ተቺው እነዚህን ሁለት የተለያዩ የምርምር ዘርፎች በማቀላቀል ምሑራኑ ያላሉትን “ጥቅሱ ሐሰተኛ ነው” የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሷል።
የአውሳብዮስና የሸም ቶብ መከራከሪያዎች ውድቅነት
ጸሐፊው አውሳብዮስን እንደ ማስረጃ ቢጠቅስም አውሳብዮስ ጥቅሱን በአህጽሮት “በስሜ” ማለቱ ለጽሑፉ አመቺነት ሲል የጠቀሰው (Paraphrasing) እንጂ ጥቅሱ በወቅቱ በነበሩት ብራናዎች ላይ ስላልነበረ አይደለም። አውሳብዮስ ራሱ በሌሎች የኋለኛ ጽሑፎቹ ላይ ሙሉውን ሥላሴያዊ ቀመር መጠቀሙ ተመዝግቧል። አውሳብዮስ ጥቅሱን የሚያሳጥረው ለጽሑፉ ምቾት እንጂ ጥቅሱ በብራናው ላይ ስለሌለ እንዳልሆነ የሚያረጋግጡ ግልጽ ማስረጃዎች አሉ። አውሳብዮስ ማርሴለስን ለመሞገት በጻፈው “ኮንትራ ማርሴለም” (Contra Marcellum 1.1.9 እና 1.1.36) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ማቴዎስ 28፥19ን “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” የሚለውን ሙሉ ሥላሴያዊ ቀመር በመጥቀስ ተጠቅሞበታል። በተጨማሪም “ዴ ኤክሌዚያስቲካ ቲዎሎጊያ” (De Ecclesiastica Theologia) በተባለው ሥራው ላይም ይህንኑ ሙሉ ቀመር ደግሞታል። ጥቅሱን በአህጽሮት የሚጠቅሰው በ”ታሪክ” ወይም በ”ምልሰት” (Commentary) ጽሑፎቹ ላይ ሲሆን ስለ “ሥነ-መለኮት” (Theology) እና ስለ “ሥርዓተ አምልኮ” (Liturgical Order) በሚጽፍባቸው ሥራዎቹ ላይ ግን ሙሉውን ቃል ይጠቀማል። ይህ የሚያሳየው አውሳብዮስ ሙሉውን ጥቅስ በሚገባ ያውቀው እንደነበርና ትክክለኛ የወንጌል ቃል መሆኑን ይቀበል እንደነበር ነው። ስለዚህ አውሳብዮስን “ጥቅሱ የለም ለማለት” እንደ ማስረጃ ማቅረብ የአውሳብዮስን ሌሎች ጽሑፎች ካለማወቅ ወይም እውነታውን ሸፍኖ ለማለፍ ከመፈለግ የሚመጣ ስህተት ነው።
በሌላ በኩል “ሸም ቶብ” (Shem Tov) የተባለው የዕብራይስጥ ማቴዎስ በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተገኘ የመካከለኛው ዘመን የተጭበረበረ ሰነድ ነው። ይህን ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ ዘግይቶ በክርስትና ተቃዋሚ አይሁድ የተጻፈን ሰነድ መሠረት አድርጎ ጥንታዊ የግሪክ ብራናዎች “ስህተት ናቸው” ማለት ከሳይንሳዊ የታሪክ ምርምር ውጭ የሆነ ፍጹም ስህተት ነው። ይህ መጽሐፍ “የበርናባስ ወንጌል” በሚል ርዕስ በመካከለኛው ዘመን ሙስሊሞች ከጻፉት ሐሰተኛ ጽሑፍ የተሻለ ዋጋ የለውም።
ስንደመድም የማቴዎስ 28፡19 ትክክለኛነት በውስጣዊ የወንጌሉ ይዘት (Internal Evidence)፣ በውጫዊ የብራና ምስክሮች (External Evidence) እና በጥንት አባቶች ሰነዶች (Patristic Evidence) የተረጋገጠ ነው። ጸሐፊው ያቀረባቸው ነጥቦች በምሑራን መካከል ያለውን የአጠናን ዘዴ ካለማወቅና የታሪክ ሰነዶችን በቅደም ተከተላቸው ካለመረዳት የመነጩ ናቸው።
