ኢሳይያስ 9፥6 እና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም – እውን ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተብሏልን?

ኢሳይያስ 9፥6 እና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም

እውን ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተብሏልን?

በወንድም ሚናስ


ራሳቸውን “የይሖዋ ምሥክሮች” በማለት የሚጠሩት የእምነት ቡድኖች፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሳይሆን  የመላእክት አለቃ ሚካኤል ነው በማለት ይናገራሉ፤  ይኽንን የእምነት አቋማቸውን ለማጽናት የኢሳይያስ 9፥6  ሰብዓ ሊቃናት ትርጉምን በዋቢነት የሚጠቀሙ ሲኾን፣ በክፍሉ መሲሑ በማሶሬቲክ ምንባብ  “ኃያል አምላክ” የተባለውን የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም “መልአክ” ብለው አስቀምጠውታል የሚል ነው። ጥቅሱም የሚከተለው ነው፦

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፥ አለቅነቱም በጫንቃው ላይ ነው፤ የሚጠራበት ስሙም የታላቁ ጉባኤ መልአክ ይባላል፤ በአለቆች ላይ ሰላምንና ጤናን አመጣለታለሁና።” (ትርጉም በአዘጋጁ)

ὅτι παιδίον ἐγεννήθη ἡμῖν, υἱὸς ἐδόθη ἡμῖν, οὗ ἡ ἀρχὴ ἐγενήθη ἐπὶ τοῦ ὤμου αὐτοῦ, καὶ καλεῖται τὸ ὄνομα αὐτοῦ Μεγάλης βουλῆς ἄγγελος· ἄξω γὰρ εἰρήνην ἐπὶ τοὺς ἄρχοντας καὶ ὑγείαν αὐτῷ.

ἄγγελος “አንጌሎስ” የሚል የጽርእ ቅጽል  ብዙ ጊዜ ሰማያዊ ፍጥረታትን ለመግለፅ ጥቅም ላይ ይውላል። ስለዚኽም የሰብዓ ሊቃናት ተርጓሚዎች መሲሑ፣ “ኃያል አምላክ” መባሉ፣ “መልአክ” ከሚለው ቅጽል የዘለለ ትርጕም እንደሌለው ተገንዝበዋል የሚል ሙግት ያቀርባሉ። ሆኖም ግን ይኽ የሐሰት መምህራን ሙግት ቢያንስ በሦስት መሠረታዊ ነጥቦች ውድቅ ይኾናል። ይኽውም በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።

፩. “የታላቁ ጉባኤ መልአክ” (ጽርእ፡ Μεγάλης βουλῆς ἄγγελος “ሜጋሌስ ቡሌስ አንጌሎስ”) የሚለው “ኃያል አምላክ” የሚለውን ቃል ለመተካት የገባ አቻ ቃል ነው ለማለት አይቻልም። ምክንያቱም በዚኽ ጥንታዊ የግሪክኛ ትርጕም “ድንቅ መካር” “ኃያል አምላክ” ፣ “የዘላለም አባት” እና “የሰላም አለቃ” የሚሉት የማዕረግ ስሞች በሙሉ ተጠቅሰው አይገኙም፤ ይልቁኑም እነዚኽ ኹሉ የማዕረግ ስሞች “የታላቅ ጉባኤ መልአክ” በሚለው ነጠላ የማዕረግ ስም ተጠቃለው እናገኛለን። ስለዚኽ “የታላቁ ጉባኤ መልአክ” የሚለው ቅጽል፣ “ኃያል አምላክ”  የሚለውን የተካ ነው ለማለት የሚያስደፍር አንዳች ምክንያት የለም። ምናልባትም ይኽ የሰብዓ ሊቃናት  ትርጕም የተተረጎመው አንዳንድ የዕብራይስጥ የእጅ ጽሑፎች ከጠፉበት ዕደ ክታብ ሊሆን ይችላል።

፪. በመግቢያው ላይ ያነበብነው የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም “የታላቁ ጉባኤ መልአክ” የሚል ቢሆንም በኵረ-ጽሑፍ የሆነውን የእብራይስጥ ንባብን መሠረት በማድረግ “ኃያል አምላክ” የሚለውን፣ ሳይቀንሱ ያስቀመጡ አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም የእጅ ጽሑፎች አሉ። ለምሳሌ፦

“…ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ ኃያል፣ የሰላም አለቃ ፣ የሚመጣውም የዓለም አባት…”

“…καὶ ὥς τινα τῶν ἀντιγράφων ἔχει, «θαυμαστὸς σύμβουλος, θεὸς ἰσχυρός, ἐξουσιαστής, ἄρχων εἰρήνης, πατὴρ τοῦ μέλλοντος αἰῶνος”

፫. የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም አዘጋጆች “የታላቁ ጉባኤ መልዐክ”  የሚለውን መጠሪያ የተጠቀሙት ይኽ ሕፃን መለኮታዊ መልዐክ መኾኑን ተገንዝበው ነው። በብሉይ ኪዳን “የእግዚአብሔር መልዐክ (መላክ ያህዌ)” ተብሎ የሚታወቅ ልዩ መልአክ፣ አምላክ ተብሎ በተደጋጋሚ ይጠራል፤ ለምሳሌ በዘፍጥረት 32፥24-30 ላይ ከያዕቆብ ጋር የታገለው አካል እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን ይነግረናል፡፡ ነብዩ ሆሴዕ ደግሞ፣ ያዕቆብ የታገለው፣ ታግሎ ያሸነፈውም መልአኩን መሆኑን ይነግረናል። ያዕቆብ አንዴ አምላክን ሌላ ጊዜ ደግሞ መልዐክን አልታገለም፤ ነገር ግን አንድ አካልን ነው አንዴ የታገለው፡፡ ከዝያም ገጠመኝ በኋላ ያዕቆብ የተገለጠለትን አካል “እግዚአብሔር” በማለት ጠርቶታል (ሆሴዕ 12፡4-6)፡፡ በተጨማሪም ኢሳይያስ 63፥9 ላይ የፊቱ መልአክ አዳናቸው የሚለውን የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም አዘጋጆች መልአክ ወይም እንደራሴ ሳይኾን ራሱ እግዚአብሔር አዳናቸው ብለው አስቀምጠውታል። ስለዚህ፣ ኢሳይያስ 9፥6  ላይ ይኽ የተለየ መልአክ መሆኑን በመግለጽ፣ የሰብዓ ሊቃናት ተርጓሚዎች ወልድ ሰማያዊ፣ አስቀድሞ የነበረ መለኮታዊ አካል መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።

ማጠቃለያ

በሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ውስጥ ኢየሱስ የመላእክት አለቃ ሚካኤል መኾኑን የሚያመለክት ኾነ፣ የጌታችንን የኢየሱስን መለኮትነት የሚሸረሽር አንዳች ምክንያት የለውም።


 

መሲሁ ኢየሱስ