የአኢሻ  ትዳር

የአኢሻ  ትዳር

ዶ/ር ሻሎም መኮንን

የሙስሊም መምህራን “አታቅፈው እሳት፣ አትጥለው የአብራኳ ክፋይ” ከሆነባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሙሐመድና የአኢሻ “ትዳር” (ያለ-አቻ ጋብቻ) ነው። በተለያዩ የእስልምና ቤተ እምነቶች የሚገኙ አንዳንድ ሙስሊም ሰባክያን “ሙሐመድ ልክ እንደኛው ሰው ነው፣ ይሳሳታል” በሚል ይህንን ግዙፍ ችግር ሊወጡት ይሞክራሉ። እንደ እውነቱ ከኾነ ይህ [ስህተቱን አምኖ መቀበል] በቂም ባይሆን ትልቅ ነገር ነው ብዬ አምናለሁ።

ታድያ የስህተቱ ዳፋ ሄዶ ሄዶ በቀጥታ የሚያርፈው “ሙሐመድ አይሳሳትም፣ የሰው ልጆች ሁሉ የሥነ-ምግባር ተምሳሌት ነው” ብለው በሚሰብኩት ሙስሊም ሰባክያን ላይ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ገሚሶቹ  መሬት ላይ ያለውን እውነታ ሽምጥጥ አድርገው በመካድ “የድሮ የአረብያ ሴቶች በዘጠኝ ዓመታቸው ለትዳር ይደርሱ ነበር” ብለው ይሞግታሉ። ገሚሶቹ ደግሞ አኢሻን ከ18 በላይም ያደርጓታል። ነገር ግን እነዚህ ሰባክያን የሚሉትን ዕድሜ ከእስላማዊ መዛግብት ላይ ያገኙት ሳይሆን የአኢሻ ዕድሜ እንዲሆንላቸው የሚመኙት ነው።

በዚህ ዘመን የሚኖር አንድ ሰው አንዲት ፍሬ የስድስት ዓመት ሕፃንን በህልሜ አይቻታለውና ላግባት ቢል ቀጥታ ወደ አዕምሮ ኅክምና ማዕከል አልያም ሃይማኖታዊ ፈውስ ያስገኛሉ ተብሎ ወደሚታመኑባቸው ስፍራዎች መወሰዱ አይቀሬ ነው። በለስ ቀንቶት ድርጊቱን ቢፈጽም ደግሞ የሕግ አካል በቀጥታ ወደ ማረምያቤት ይወስደዋል።

ለምሳሌ ያኽል በምስሉ ላይ የሚታየው ጎልማሳ ሰው የሙሐመድን  ፈለግ (ሱና) እከተላለለሁ በሚል ህፃን ልጅን በሚያገባበት ወቅት “እጅ ከፍንጅ” በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ ውሏል። ምንጭ: https://www.lindaikejisblog.com/2016/06/police-in-pakistan-arrest-60-year-old.html

እንደ እውነቱ ከኾነ ይህንን ድርጊት (ግፍ) የፈፀመው በታሪክ ያለፈ አንድ ተራ ሰው ነው ቢባል ኖሮ በዚህ መልኩ ተካብዶ መታየት ላይኖርበት ይችላል። ነገር ግን ሚልየኖች የሰው ልጆች “የስነ-ምግባር ተምሳሌት ነው” ብለው የሚያምኑት አካል፣ ሚልየኖች የእሱን ፈለግ እንከተላለን ብለው ላይ ታች የሚሉለት አካል ይህንን ግፍ ሲፈጽም ሙስሊም ወገኖቻችን ለምን «አሜን» ብለው እንደተቀበሉ ሁሌም የማይገባኝ ጉዳይ ነው። ውድ ሙስሊም አንባቢ ሆይ! አንድ ሰው ወዳንተ በመምጣት “የስድስት አመት ልጅህን ላግባት” ቢል ምላሽህ ምንድን ነው? ውድ እንስት ሙስሊም አንባቢዬ ሆይ! አንቺስ ገና ከእቅፍሽ ያወረድሻትን ልጅ አንድ ጎልማሳ “በህልሜ ስላየኋት ዳሪልኝ “ቢል ምላሽሽ ምን ይሆን? መልሱ ግልጽ ይመስለኛል።

የትኛውም ዓይነት የዚህ ጽሑፍ ተነባቢ፣ ሙሐመድን ልደግፍ በሚል ካልሆነ ይህንን ፀያፍ ድርጊት በገዛ ልጁ፣ በዘመዱ እንዲሁም በሚያውቀው ሰው ሕይወት እንዲደገም አይፈልግም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህንን ከሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ በማካተት ይመድበዋል https://www.un.org/en/exhibits/page/un-remarks-9

“ያለ እድሜ ጋብቻ” ጎጂ መሆኑን እዚህ ዘመን ላይ ሆኖ መናገር ለዐቃቤ እምነት ብዙም አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። በሃምሳዎቹ  ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ጎልማሳ የስድስት ዓመት ሕጻንን “አላህ እንዳገባ’ት በህልሜ አሳየኝ” ማለቱን በመልካም ጎን የሚያይ አንድም ፊደል የቀመሰ አንባቢ አለኝ ብዬ አላስብም። በተሻሻለው የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምርያ ህግ መሰረት ከ16-18 አመት በታች የምትገኝ ህፃን ጋብቻ ቅቡልነት የለውም። ይህንን ድርጊት ፈጽሞ የተገኘ አካል በሀገሪቷ ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት ቅጣት ይተላለፍበታል።

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ይህን ድርጊት (ግፍ) ከሰባተኛው ክፍለ-ዘመን አንፃር ብቻ የምንመለከተው ከኾነ የማሕበረሰብ ንቃት እምብዛም ስላልሆነ ትችቱ አሁን በሆነበት ልክ ላይጮህ ይችላል። በርካታ የመካከለኛው ዘመን የእስልምና ኀያሲያን ሙሐመድ ብዙ ሚስቶች ማግባቱን ካልሆነ በቀር ይህንን ጉዳይ እምብዛም ሲነኩት አልታየም። ለዚህም ዋነኛው መንስዔ በወቅቱ ሙግት ማዋቀርያ ይኾን ዘንዳ የተስተካከለና የተሰመረ ዕይታ ባለመኖሩ ነው። ዛሬ ላይ ግን ይህ ፈፅሞ ስህተት ኾኖ በመገኘቱ በሀገራችን እንኳ ከጎጂ ልማዶች ተመድቧል። ከዚህም አልፎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ሊያገኛቸው ከሚገባቸው፣ ማንም ሊነጥቀው ከማይገባ ሰብአዊ መብቶች ጋር ተቀላቅሏል።

ወደ ሙሐመድ ስንመለስ ሙሐመድ በታሪክ ባለፉ ተራ ሰዎች መነፅር ሊታይ እንደማይገባ ከአንዳንድ አፈንጋጭ ሙስሊሞች በስተቀር ሕዝበ-ሙስሊሙ በጠቅላላ ምስክር ነው። ሙሐመድ የስነ-ምግባር አስተማሪ፣ የፈጣሪ ቃል ተቀባይ፣ ለሙስሊሞች ሁሉ ዘመን አይሽሬ የግብረ-ገብ መንገድ ጠቋሚ ስለሆነ በቀላሉ እንደሌሎች አካላት ይህ ዓይነቱ ጎጂ ልማድ “በታሪክም እኮ ነበር!” በሚል በቀላሉ የሚድበሰበስ ጉዳይ አይሆንም። ቁርአን እንዲህ ይላል፦

وَإِنَّكَلَعَلَىٰخُلُقٍعَظِيمٍ

“አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ፡፡”

ግብረ ገባዊ አሁናዊነት (Moral presentism) በበርካታ ዓለማዊ የታሪክ አጥኚዎች ከግምት ውስጥ ይገባል። ግብረ-ገብነት ከታሪክ ታሪክ፣ ከስፍራ ስፍራ ይለያያል የሚል ርዕዮት ካለ የሙሐመድ ጉዳይ እምብዛም ሊያሳስበን ባልተገባ ነበር። ነገር ግን የሙሐመድ ጉዳይ ከ”historian’s fallacy” ወይንም “presentism” ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። ምክንያቱም ከእነዚህ ውጪ የሆነው፣ በዘመን የማይለካው አላህ ስለ ሙሐመድ ባሕርይ በሙሉ ድምፅ ምስክርነት ሰጥቷልና። በበርካታ ሙስሊሞች ዘንድም የሙሐመድ የሕይወት ታሪክ ለሰው ልጆች ሁሉ የስነ-ምግባር ተምሳሌትና መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ስለ “ያለ ዕድሜ ጋብቻ” ጎጂነት እዚህ ዘመን ላይ እንደ ዐቃቤ-እምነት መናገርና መሞገት ብዙም አስፈላጊ አልነበረም። በሃምሳዎቹ ዓመት የሚገኝ አዛውንት የስድስት ዓመት ታዳጊ ሕጻንን አላህ ለትዳር እንድትሆነኝ በህልሜ አሳየኝ ማለቱን በመልካም ጎን የሚያየው አንድም ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። በሕግ አግባብም ቢኾን ቅቡልነት የለውም።

“አኢሻ እንደተረከችው፡- የአላህ መልእክተኛ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉኝ፡- ‹‹አንቺን ከማግባቴ በፊት ሁለት ጊዜ (በሕልሜ) ታይተሽኝ ነበር፤ መልአክ በሐር ጨርቅ ተሸክሞሽ አየሁ፣ እኔም “ግለጣት” አልኩት፤ እነሆ አንቺ ነበርሽ። ይህ ከአላህ ዘንድ ከሆነ መፈጸም አለበት አልኩ።” (Sahih al-Bukhari Vol. 9, Book 87, Hadith 140)

ያለ ዕድሜ ጋብቻ ጎጂነት አስቀድሞውኑ ሙግት መሆን አለበት ብዬ ስለማላምን ብዙም ወደውስጥ አልገባም። በዚህ ክፍለ- ዘመን የሚገኝ ዐቃቤ እምነት ነኝ ለሚል ሰው የዘጠኝአመትሴትልጅ ለአቅመ-ትዳር እንዳልደረሰች ማስረዳት “እሳት በእጅ መንካት ያቃጥላል” እንደ ማለት ነው። ይህንን ጽሑፍ ከመጻፌ አስቀድሞ የብዙ ሰዎችን ሐሳብ ለማየት ሞክሬያለሁ። ወደ አንድ ፍሬ ህፃን ልጅ ሲመለከት እደዚያ ዓይነት ልጅ መውለድ አልያ ማጫወት እንጂ “ከእርሷ ጋር መዳራትና ትዳር ለመመስረት” የሚያስብ አእምሮው ጤናማ የኾነ ሰው (የዚህ ጽሑፍ አንባቢ) ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። የሀገራችን  ሙስሊሞችም ቢሆኑ ይህ ፈፅሞ ስህተት መሆኑን እንደሚያምኑ ጥርጥር የለኝም። “የስድስት ዓመት ልጅሽ ጋር ትዳር ልመስርት፣ ዘጠኝ ዓመት ሲሞላትም ተራክቦ ላድርግ” ብትባል አሜን የምትል ሙስሊም እናት ትኖራለች ተብሎ አይታሰብም። ወንዶችም (አባቶች) ቢሆኑ ተመሳሳይ አቋም ሊኖራቸው እንደሚችል ጥርጥር የለውም።

ሙሐመድ በጉልምስና ዕድሜው ለትዳር  አዲስ አልነበረም። ከዚያቀደም (በወጣትነት ዘመን) በአስራ አምስት ዓመታት ያህል ከምትበልጠው ኸዲጃ ከተሰኘች ሴት ጋር በትዳር ተጣምሮ ነበር። በሃያ አምስት ዓመቱ ከአርባ ዓመት እንስት ጋር በጋብቻ ተጣምሮ ተራክቦ ሲፈፅም የኖረ ሰው ዕድሜው በሃምሳዎቹ ሲገኝ የዘጠኝ ዓመት ህፃንን ተራክቦ ሲፈፅምባት ለሕፃኗ ምን ያህል ሲቃ ሊኾን እንደሚችል የሚያጠያይቅ አይደለም። ይህ ብቻም ሳይሆን ከዘጠኝ ሚስቶቹ ጋር በአንድ ሌሊት ብቻ ተራክቦ የሚያደርግ ወጣ ያለ ወሲባዊ ፍላጎት ያለው ሰው መሆኑን ማስታወስ የልጅቷን ሲቃ ለመረዳት ያግዛል።

ከዚህ ቀደም ባስነበብኩት መጣጥፍ ላይ ሙሐመድ ለምን እንዲህ ዓይነት ባሕርይ (ልቅ ወሲባዊ ባሕርይ) ያሳይ እንደነበር ለመጠቆም ሞክሬያለው። ከላይ እንደጠቀስኩት ሙሐመድ የወጣትነት ዘመኑን በዕድሜ ከምትበልጠው እንስት ጋር በነጠላ ጋብቻ ተጣምሮ ቆይቷል። ታድያ ምን ተገኝቶ ነው በጉልምስና ዕድሜው እንዲህ ልቅ የሆነ ወሲባዊ ሕይወትን የመረጠው? ለዚህ ጥያቄ ቀላል መልስ አለው።

ሙሐመድ ባጋጠመው የሚጥል በሽታ (TLE) ምክንያት እነዚህን ባሕርያት እንዳሳየ ብንገምት ስህተት የመኾን እድላችን ጠባብ ነው። አኢሻን ማግባቱን እንደ ታሪካዊ ስህተት ብንወስድ እንኳ በዕድሜው መባቻ ሳለ ጡት የምትጠባ አፍላ ህፃንን ተመልክቶ ለትዳር መመኘቱ ጤንነቱን የሚያስጠረጥር ሆኖ እናገኘዋለን።

“የአባስ ልጅ  ኡም ሐቢባ ጡት  በመጥባት ዕድሜ ላይ ሳለች በዳዴ ስትሄድ ተመልክቷት ነቢዩ እንዲህ አለ፡- ወሏሂ እኔ በሕይወት እያለሁ የምታድግ ከሆነ አገባታለሁ፡፡” (Musnad Ahmed, Number 25636)

ቴምፖራል ሎብ በሚባለው የአእምሮ ክፍል ላይ እክል የገጠማቸው ታማሚዎች ላይ በተደረገው ጥናት መሠረት ከህፃናት ጋር ግንኙነት ከማድረግ ጋር በሰፊው ተያያዥነት አለው። https://psycnet.apa.org/record/1987-34736-001

(Kaitlyn Goldsmith. Pedophilia and Brain Function.Department of Psychology, University of British Colombia. (2012). p. 3.)

https://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov/19927260/

በተመሳሳይም ከሕፃናት ጋር ተዳርተው ወንጀል በፈፀሙ ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት የጊዜያዊ የአይምሮ ክፍል ወይንም የቴምፖራል ሎብ፣ እንዲሁም የፍሮንታል ሎብ እክሎች ተገኝተዋል። https://pubmed.ncbi.nlm.nih.gov/25116710/

ስለ ቴምፖራል ሎብ ኤፒለፕሲ ያስነበብኩትን መጣጥፍ ለማግኘት እዚህ ጋር ጠቅያድርጉ። የዚህን ጽሑፍ ክፍል አንድ ለማግኘት እዚህ ጋር ይጫኑ።

ይሁን እንጂ ለሙግት መቅረብ የማይገባውን ነጥብ በሕይወታቸው ከቶውኑ እንዲፈጠር የማይፈልጉትን ነገር በሰው ህይወት “ትክክል” ለማድረግ የሚሞክሩ ከአእምሯቸው የተጣሉ ሰዎች አሉ። ከእነዚኞቹ “የሙሐመድና የአሁኑ ዘመን ይለያያሉ፣ ምንም እንኳ አሁን ስህተት ቢሆን በወቅቱ የተለመደ ነው” የሚሉቱ ሳይሻሉ አይቀሩም። እነዚህኞቹ ካዳሚዎቻቸውም (ተማሪዎቻቸው) ሆነ እራሳቸው ከዕውቀት እጅግ የራቁ መሆናቸውን ሙግታቸውን የሚያዋቅሩበትን መንገድ (ቪድዮ፣ ጽሑፍ) ማየት ብቻ በቂ ነው። ለሀገር ውስጥ ተሟጋቾች አዲስ ሆኖባቸው ካልሆነ በስተቀር ከሃያ ወይን ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ከሽፎ የተጣለ ውዳቂ ሙግትነው።

እነዚህ ሰዎች “Puberty (ኩርድና) የሚጀምረው በዚህ በዚህ ዕድሜ ነው ስለዚህ አኢሻ በዘጠኝ ዓመቷ በሃምሳዎቹ ከሚገኝ ጎልማሳ ጋር ተራክቦ መፈፀሟ ምንም ዓይነት የግብረ-ገብ ስህተት የለበትም” ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ምናልባት ይህንን ማለታቸው በሕግ የሚያስቀጣቸውም ጉዳይ ይመስለኛል። ለምሳሌ ከዚህ ስሁት እሳቤ በመነሳት በየመን አንድ ጎልማሳ ሰው የዘጠኝ ዓመት ልጅን በማግባት ሕይወቷን ሊያሳልፍ ችሏል። እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች አንድ ብቻ ሳይሆኑ በየቀኑ፣ በየጊዜው የሚፈፀሙ ናቸው።

ምንጭ:- https://www.theguardian.com/global-development/2013/sep/11/yemen-child-bride-dies-wedding

የእስልምና ደሴት የምትባለው ሳዑዲ አረብያ እንኳን አንዲት እንስት የማግባት ዝቅተኛው ዕድሜ አስራ ስምንት በሚል አፅድቃለች https://www.arabnews.com/node/1613691

አብዛኞቹ ሙስሊም-በዝ ሀገራትም ቢሆኑ እንደዚያ አድርገዋል፣ እያደረጉም ነው። ሙስሊም-በዝ በሆኑት ሀገራት ሥልጣን ላይ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎችና ሹመኞች በከፍተኛ ተቃውሞ ውስጥ ሳሉ ይህንን ውሳኔ የወሰኑት ዝም ብለው ከመሬት ተነስተው ሳይሆን የሙሐመድን ሱና (ፈለግ) በመከተል ህፃናት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ራስ ወዳድ በመብዛቱ ነው።

አንድ በሀገር ውስጥ እራሱን ዐቃቤ-እሥልምና በሚል የሚጠራ ሰው በኩራት የጻፈውን አስተውዬ እጅግ አዘንኩኝ። «Matrimony የሚባል የስነ-ጋብቻ ጥናት ሴት ልጅ በዘጠኝ አመቷ ደርሳለች ይላል። የዘጠኝ ዓመት እንስት ሳይንስም ለዐቅመ ጋብቻ እንደደረሰች ያረጋግጣል» በማለት ሰብዓዊነት ተሰምቷቸው እንዲህ ያለውን ትዳር የሚኮንኑ ሰዎች ይዘልፋል። [ጽሑፉን ቃል በቃል ሳይሆን አጠቃላይ ሐሳቡን ነው የጠቀስኩት]

ሲጀመር “Matrimony” ማለት የሥነ-ጋብቻ ጥናት ማለት አይደለም። “ዐቃቤው” በዚህ ጉዳይ የተወሰነ ቅኝት ቢያደርግ ኖሮ የሙግት አካሄዱን ሊቀይር ይችል ነበር። ነገር ግን እንኳንስ ጥናቱን በመቃኘት ሊያመሳክር ቀርቶ የእንግሊዝኛውን ቃል ትርጓሜ እንኳ ምን እንደሆነ አልተረዳም። በአማርኛ ትርጓሜው “በትዳር መታሰር” በእንግሊዝኛ ደግሞ “Matrimony” ከመች ጀምሮ የጥናት ዘርፍ እንደሆነም ከእርሱ ውጪ የሚያውቅ ሰው ያለ አልመሰለኝም። ምናልባት ዐቃቢውን እንደ biology, chemistry, theology, ሁሉ ቃሉ በ”Y” ስለሚጨርስ የተምታታበት ይመስላል። ነገር ግን ዐቃቢው ቢያመሳክር ኖሮ በስማበለው «እንዲህ የሚባል ጥናት እንዲህ ብሏል» በሚል በY የሚጨርስ ስም በአቦሰጥ  እየጠቀሰ  ሙግት ከማዋቀር ይድን ነበር። ነገር ግን ይህ ጽሑፍ ምላሽም ሆነ ሙግት የማዋቀር ይዘት ስለሌለው “የዐቃቤውን” ጉዳይ እዚህ ላይ ላቁም። ይህንን ሰው እዚህ ጋር ያነሳሁበት ዋና ምክንያቴ አንድ ብልህ አንባቢ የማይመስሉ ነገሮችን ሲመለከት «የሰውየው መረዳት ምንድን ነው? እስከምንስ ያውቃል? እንዲህ እንዲደመድም ያደረገው ምንድን ነው?» ብሎ መጠየቅ ያስፈልገዋል የሚል ምክር ለመለገስ ነው። «ሃይማኖቴ ተደፈረብኝ፣ ነቢዬ ተሰደቡብኝ» በሚል እልህ በታጀበበት መነሻ የባጥ የቆጡን የሚያውቁትንም የማያውቁትንም እንዲያው የመጣላቸውን ኹሉ በስድብ እያዋዙ «ሚሽነሪ መጣብህ» እያሉ በባዶ ሜዳ ሕዝበ-ሙስሊሙ ላይ ሽብር የሚፈጥሩ አካላት ብዙ ናቸው። ይህንን የሥነልቦና ችግር በሰፊው ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ወደ ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስ።

ሳይንስ «የዘጠኝ ዓመት ሴት ለትዳር ደርሳለች ይላል» ማለት እራስን በእጅጉ ማስገመትነው። ይህ ጥያቄ የሚፈጥርበት ሰው በእርግጠኝነት የስድስተኛ ወይን የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎችን ጠይቆ በሚገባ መረዳት ይችላል። እንደ እውነቱ ከኾነ ግን የዘጠኝ ዓመት ልጅ ለተራክቦ አለመድረሷን ለመረዳት ሳይንስ ጋር መሄድም አያስፈልግም፤ የዘጠኝ አመት ልጅ መመልከት ይበቃል።

በእርግጥ «ኮረዳነት» ወይንም ጉልምስና የሚጀምረው በአስራዎቹ ውስጥ ነው። ይህ ግን ለተራክቦ እንደ መስፈርት ሊቀመጥ አይችልም። የአንድ ዓመት ወይንም የስድስት ወር ህፃን አንድ ሁለት ጥርስ አብቅሏልና አጥንት ይጋጥ እንደማይባለው ሁሉ «የኮረዳነት ምልክት ማሳየት ስለ ጀመረች ለተራክቦ ዝግጁ ነች» አይባልም። አንዲት እንስት የኮረዳነት ምልክት ጅማሬዎችን ማሳየት ጀመረች ማለትን «ሕጻንነቷን አበቃች፣ ለትዳር ምስረታ ደረሰች» ብሎ መረዳት ከእውኑ ዓለም የተፋታ መሠረታዊ ችግር ያለበት አረዳድ ነው። ምንም እንኳ አከራካሪ ባይሆንም የተወሰነ ሐሳብ ልጨምር።

ሁለተኛ ደረጃ የሚባለው የፆታዊ ለውጥ ዓመታትን የሚወስድ እንጂ “በአንድ ሌሊት” የሚጠናቀቅ አይደለም። ሁለተኛ ደረጃ ፆታዊ ለውጥ (secondary sexual characterstics) የዕድገት አንዱ አካል ነው። የሴት ልጅ ፆታዊ ለውጥ በአምስት ደረጃዎች ተከፍለው ይታያሉ።

አንደኛው እና የመጀመርያው ደረጃ ምንም ዓይነት አካላዊ ለውጥ ሳይታይ «ለፆታዊ ለውጥ ዝግጁ የሚኮንበት» ደረጃ ነው።

ሁለተኛ ጡት የተወሰነ ማጎጥጎጥ፣ እንዲሁም ሌሎች ጥቃቅን አካላዊ ለውጦች መታየት ይጀምራሉ።

ሦስተኛ ዳሌ መስፋት፣ በመራብያ አካላት አካባቢ ፀጉር ጠቁሮ መታየት፣ እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ የጀመረው አካላዊ ለውጥ ይቀጥላል።

አራተኛ የወር አበባ ማየት ትጀምራለች፣ ሌሎች አካላዊ ለውጦችም ይቀጥላሉ።

አምስተኛው ፆታዊ ለውጦች የሚያበቁበት ደረጃ ነው። ከሰው ሰው ቢለያይም ከ16-23 ባለው ውስጥ እንደሚያበቃ ይገመታል። ታድያ ግን ይህም ዕድሜ ቢሆን ለአቅመ-ጋብቻ ሳይሆን ሰውነቷ እኩያዋ፣ በዕድሜዋ፣ በአቅሟ ለሆነ ተራክቦ ደረሰ እንጂ ለተሟላ ትዳር ደርሳለች የሚያስብልበት ደረጃ አይደለም። ከላይ እንዳልኩት ፆታዊ ለውጦችን ማሳየት ጀመረች ማለት ለትዳርም ሆነ ለተራክቦ ዝግጁ ነች ማለት አይደለም። አንዳንድ ሰዎች የሰባተኛ ክፍል መማርያ መጽሐፍ ላይ እንኳ ያለን ነገር መረዳት አቅቷቸው ለሙግት ሲያቀርቡት ማየት አሳፋሪ ነው።

መደምደምያ

የተወደዳችሁ ሙስሊም አንባብያን! የሙሐመድን  ፈለግ መከተል ለማንወጣቸው ችግሮች ይዳርጋል። የአፍላ ዕድሜ ጋብቻ  ከስነ-ልቦናዊ ችግሮች ባሻገር ፌስቱላ፣ በግንኙነት ጊዜ ጉዳት መከሰት (sex injury)፣ ደም መፍሰስ (internal bleeding)፣ የማህፀን መገልበጥ፣ የማህፀን ግርግዳ መላላጥ፣ የፅንስ ጭንገፋ፣ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ደም ግፊት (pre eclampsia, Gestational hypertension) የእንግዴ ልጅ አለጊዜው መላቀቅ (Placental abruption)፣ የእንግዴ ልጅ አላግባብ ቦታ ማረፍ (Placental previa)፣ ከማህፀን ውጪ የሚፈጠር እርግዝና (ectopic pregnancy) ጤነኛ አካል ያለው ልጅ አለመውለድ፣ የሰውነት መቀንጨር፣ የአጥንት መዛባት፣ የአእምሮ መቀንጨር፣ (በአጠቃላይ) የድኅረ ወሊድ ደም መፍሰስ (PPH)፣ (በአጠቃላይ) የቅድመ ወሊድ ደም መፍሰስ (APH)፣ የማህፀን መተርተር (Uterine rupture)፣ እንዲሁም በወሊድ ጊዜ የሚከሰትን ሞት ጨምሮ ብቻውን ረጅም ጽሑፍ ሊወጣው የሚችል እጅግ በርካታ ችግሮችን በእንስቷና በሚወለደው ልጅ ላይ ያስከትላል። ይህም ብቻ ሳይሆን ኤችአይቪ፣ አባላዘር እንዲሁም በርካታ በግብረሥጋ ግንኙነት አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎች ስርጭትን በእጅጉ ያባብሳል።

ብዙዎቻችሁ “አንድ በፈጣሪ እንደተላከ የሚያምን ሰው እንዴት ይህንን ያደርጋል?” እያላችሁ እየጠየቃችሁ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ከሙሐመድ ድርጊት (ግፍ) እጅግ ትንሹ የሚባለው ነው። ከዚህ ጽሑፍ በመቀጠል “አዛኙ ሙሐመድ” በሚል ርዕስ በሙሐመድ አማካኝነት በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ የተደረጉትን ሰዎች ታሪክ ከእስላማዊ ምንጮች ለማሳየት እሞክራለሁ። ሙሐመድ ያሳያቸው ባሕርያት ለግብረ-ገብነት ተምሳሌት ሊሆኑ ከቶ አይችሉም። ሙሐመድን የመልካም ባሕርያት ተምሳሌት አድርጎ መከተል ለአንድ ህሊናው በትክክል ለሚሠራ ሰው ተገቢ ሆኖ አይታየውም። ይልቁኑ የክርስቶስንና የሐዋርያቱን የላቀ ግብረ ገባዊ ሕይወት ለተመለከተ ሰው ሙሐመድን የመልካም ባሕርያት ምሳሌ አድርጎ ማቅረብ ምንኛ ስላቅ ነው!

ሴቶች በእስልምና