ግልጠተ መለኮት ወይንስ የሚጥል ህመም?
ለሙስሊሞች ምላሽ
ዶ/ር ሻሎም መኮንን
ሙሐመድ “ቴምፖራል ሎብ ኤፒለፕሲ” በተሰኘ የጤና እክል እንደተጠቃ ባቀረብኩት መጣጥፍ ላይ አንዳንድ ብዥታዎች ስላየሁ የተወሰነ ልበል። በቅድሚያ የሚጥል በሽታ ልጄ፣ ወንድሜ ወይንም አክስቴ ስላለባቸው ስለበሽታው በደንብ አውቃለው የሚባል ዓይነት እክል አይደለም። ኤፒለፕሲ በኒውሮኖች በአግባቡ አለመሥራት የሚመጡ እክሎች ስብስብ መጠርያ ነው።[1] ማናችንም እንደምናውቀው አእምሮ ውስብስብ ነው። በአእምሮአችን ውስጥ እጅግ ውስብስብ የኤሌትሪክ ሥራዎችን የሚሠሩት በቢልየን የሚቆጠሩ ኒውሮኖች አሉ። በተለያየ ዓይነት መንገድ የሚከፋፈሉ ሲሆን Excitatory Transmitter የሚባሉት የኤሌትሪክ ሲግናሎችን ይለቃሉ። Inhibitory Transmitter የሚባሉት የተለቀቀው ከመጠን እንዳይበዛ ይመልሳሉ። ይህ ሂደት ጤነኛ የአእምሮ ክዋኔ እንዲኖር ያደርጋል። ታድያ የሚጥሉ በሽታዎች የሚከሰቱት በዚህ አለመመጣጠን ነው። ይህ አለመመጣጠን የተወሰነ የአእምሮ ክፍል ላይ ሲያጋጥም Partial/ Focal Seizure ሲከሰት፣ ሁሉም የአእምሮ ክፍሎች ላይ ከሆነ ደግሞ Generalized Seizure ይከሰታል። Partial Seizure ካጋጠማቸው ውስጥ ንቁ የሚሆኑ አሉ የማይሆኑም አሉ። Simple Focal Seizure ያጋጠማቸው በአብዛኛው ንቁ ሲሆኑ Complex Focal Seizure የሚያጋጥማቸው ደግሞ በአብዛኛው በህመሙ ወቅት እራሳቸውን ይስታሉ። Generalized ከሚባለው ውስጥ የማይጥላቸው ግን እራሳቸውን የሚያስታቸው ሲኖሩ Absence Seizure ያጋጠማቸው ናቸው። እነዚህም ከንፈርን ያለንግግር ማንቀሳቀስ (Lip Smacking) ዐይን መገልበጥ(ወደሰማይ ማፍጠጥ) ወዘተ… በህመሙ ወቅት ሊያሳዩ ይችላሉ። ከGeneralized Seizure ውስጥ Atonic Seizure, Tonic Seizure, Myoclonic Seizure የሚባሉ ሲኖሩ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው Tonic-clonic የሚባለው አይነት Seizure ነው። ይኸውም መሬት ወድቆ መንደፋደፍ፣ እራስን አለማወቅ ወዘተ… ዓይነት ምልክቶች ናቸው።
እስካሁን በድርበቡ እንዳየነው የሚጥሉ በሽታዎች ዓይነቶቻቸው እንዲሁም ምልክቶቻቸው አንድ ብቻ አይደሉም። እንደ ፕሮፌሰር ፍሪመን ገለፃ “ሙሐመድ የሚጥል ህመም አልነበረበትም” ማለት ስለሚጥል በሽታ በቅጡ አለማወቅ ነው። አንዳንድ ሰዎች “አንድን ሰው Epileptic ነው” የምንለው በየቀኑ ሁለቴ ህመሙ ከጣለው ብቻ ነው የሚል ትንታኔ ሲሰጡ ተመልክቻለው። ሰዎቹ አንድም ለጉዳዩ አዲስ ስለሆኑ፣ ሁለትም ሙሐመድ ይህ በሽታ የለበትም ከሚል ጭፍን እምነት ብቻ ተነስተው መሆኑን ትንታኔውን ያየ ሰው ሁላ ይረዳል። ዓለም አቀፉ የሚጥል በሽታዎች ህክምና ህብረት (ILEA) እንዲሁም የተለያዩ የዘርፉ ማሕበራት “አንድ ሰው በሕይወት ዘመኑ በቀን(በሀያአራት ሰዓት ውስጥ) ሁለቴ ይህንን ምልክት ካሳየ” የሚል ነገር አስቀምጠዋል። ነገር ግን ያስቀመጡት መለያ አካታች እንጂ የግድ መሆን አለበት የሚል ይዘት የለውም ። አንድ ሰው በቀን አንዴ ብቻ ጥሎት በሌላ ጊዜ ከተደገመ Epileptic ሆኖ ሊኾን ይችላል፤ ከተቀመጠው ዘለግ ብሎም በቀን ሦስቴ ሊጥለው ይችላል። በመጣጥፉ ላይ እንዳስነበብኩት ሙሐመድ ከህፃንነቱ ጀምሮ የዚህ በሽታ ተጠቂ እንደሆነ ማሳያ ስለተገኘ ሙሐመድ በሕይወት ዘመኑ በቀን ሁለቴ ተገልጦለት (ታሞ) ሊሆን አይችልም ማለት አንችልም።
ወደ ርዕሳችን ስንመለስ የሚጥል በሽታው የተነሳው ቴምፖራል ሎብ ከተሰኘ የአእምሮ ክፍል ከሆነ ቴምፖራል ሎብ ኤፒለፕሲ እንለዋለን። ይህ ዓይነቱም ቢሆን በርካታ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን አንድ ዓይነት ብቻም አይደለም። ከቴምፖራል ሎብ ኤፒለፕሲ ታማሚዎች ውስጥ Simple Focal Seizure የሚያጋጥማቸው ታማሚዎች አሉ፤ Complex Focal Seizure በቀደመ መጠርያው Psychomotor Seizure ወይንም በተሻሻለው መጠርያው Focal Impaired Awareness Seizures የሚያጋጥማቸው አሉ። እነዚህ በሚጥላቸው ወቅት ዙርያቸው የነበረን ነገር አያስታውሱም፣ ይህ ዓይነት እክል ያጋጠማቸው ጥቂት የማይባሉ ታማሚዎች “በዚህ ጊዜ ከፈጣሪ ጋር እንደተነጋገሩ፣ የተለየ ነገር እንዳዩ፣ በሰይጣን ቁጥጥር ስር እንደወደቁ” ሊቆጥሩ ይችላሉ።[2] የሚጥሉ በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች ህመሙ ከመጀመሩ በፊት የሚያዩት ምልክት (Aura) አለ። በዚህኛው ዓይነት የሚጥል ህመም የታመሙ ሰዎች ከተጠቀሱት ምልክቶች መካከል የደውል ድምፅ (Ringing) ጥዝዝ… የሚል ዓይነት ድምፅ (Buzzing) ወዘተ… መስማት ነው። ሙሐመድ መገለጡ ሊመጣለት ሲል የደውል ድምፅ ይሰማ ነበር። ሀቀኛ ሙስሊም መርማሪ ይህንን ድንገተኛ ግጥምጥሞሽ ነው እንዳይሉ ከደውሉ ድምፅ በተጨማሪም የንብ መንጋ ዓይነት ድምፅ(ጥዝዝዝ የሚል ድምፅ) ይሰማ ነበር [ቲርሚዝይ 3173]። በተጨማሪም ይህ ዓይነት የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች በርካታ የስነ-አእምሮ ተፅእኖ ሲኖርባቸው ከእነርሱ መካከል የጌሽዊንድ ምልክት የተሰኘው አንዱ ነው።[3] የጌሽዊንድ ምልክቶች ምንድን ናቸው? እነዚህ ታማሚዎች ሀይማኖተኛ ይሆናሉ (Hyper-religious)፣ እንዲሁም የሀይማኖት ውዥንብር ውስጥ ይገባሉ። የዚህ ህመም ተጠቂዎች አእምሯቸው ውስጥ የመጣውን ነገር የሚረሱት ስለሚመስላቸው ወደ አእምሮዋቸው የመጣውን ነገር ሰንደው ይይዛሉ (Hypergraphia)። ህመሙ እንዲጽፉ፣ እንዲሸመድዱ፣ እንዲስሉ ያስገድዳቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ ታማሚዎች Atypical Sexuality ያጋጥማቸዋል። የወሲብ ህይወታቸው ይቀየራል። Hypo Sexual ወሲብ ሊቀንስ ወይንም ሊጨምር (Hypersexuality) ይችላል። እንዲሁም እነዚህ ታማሚዎች በወቅታዊ ሁኔታዎች ይወሰናሉ (Circumstantiality)። ንግግራቸውና ሐሳባቸው የሚመነጨው ዙርያቸው ባዩት ነገር ነው። የሙሐመድን ሁኔታ ስንመለከት መገለጦቹን ጨምሮ ስለነገሮች ሲያብራራ በአካባቢው ሁኔታ ታጥሮ ነው። ፀሐይ ሲመለከት “ፀሐይ ወዴት እንደምትገባ አያችሁ?” ብሎ ትንታኔ ይሰጣል፤ ግመል ሲያይ “ወደ ግመል እንዴት እንደተፈጠረች አይመለከቱምን?” ይላል፤ መገለጦቹን ሁሉ የሚናገረው እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት አስቀድሞ ሳይሆን ከክስተቶቹ በኋላ (After the Facts) ነው፤ ብዙ መጥቀስ ይቻላል። የሙሐመድን የሕይወት ታሪክ ለሚያውቅ ሰው የዚህ በሽታ ተጠቂ እንደነበር ብዙም አሻሚ አይሆንበትም። ስለህመሙ ጭራሽ ዕውቀቱ የሌላቸው ሰዎች አልያ አውቀው የግድ ሙሐመድ ነቢይ መሆን አለበት ከሚል ጨለምተኝነት መነሾ ካልሆነ የሙሐመድ የሕይወት ታሪክ መዛግብት የዚህ በሽታ ተጠቂ እንደነበር እማኝ ናቸው።
በህክምናው ዓለም ከታማሚ ታሪክ ብቻ ተነስቶ ሙሉ ድምዳሜ መውሰድ ትክክል ተደርጎ አይታሰብም። ከታማሚውና ከታማሚው የቅርብ ሰዎች የሚወሰዱት መረጃዎች (Symptoms) ይባላሉ። ከታማሚውና የታማሚው የቅርብ ሰዎች በምንሰማው ታሪክ ተነስተን በሽታዎችን እንገምታለን (Hypothesize)። እኛ በአካላዊ ምርመራም ሆነ በሌላ መንገድ ታማሚው ላይ የምናያቸው ምልክቶች Signs ሲባሉ በእነርሱም ቢሆን ተነስተን ከድምዳሜ አንደርስም። እዚህ ላይ ሊሆኑ የሚችሉ በሽታዎችን (Differential Diagnosis) ነቅሰን እናወጣና ተጨማሪ ማረጋገጫ ምርመራዎችን እናክላለን። የሙሐመድን ታሪክ በህክምና መነፅር ስናጠና ሊሆን የሚችለው የተለየ መገለጥ (Divine Inspiration) ሳይሆን “ቴምፖራል ሎብ ኤፒሊፕሲ” (TLE) ነው። ይህቺን ጫፍ ይዘው አንዳንድ ሙስሊም መምህራን ሙሐመድ TLE እንዳለበት በህክምና እርግጠኛነት መስፈርት እርግጠኞች መሆን ስለማንችል የለበትም የሚል ሙግት ያነሳሉ። የህክምና ሳይንስ በሚጠይቀው እርግጠኛነት ዓይነት ሚዛን ነገሮችን እንለካ የምንል ከሆነ ሙሐመድ የሚባል ሰው በተባለበት ዘመንና ቦታ ስለመኖሩም እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በህክምና እርግጠኛነት ሚዛን ሙሐመድ ይህ ህመም እንደሌለበት ወይንም እንዳለበት እርግጠኛ ለመሆን የEEG የMRI ምርመራዎች ያስፈልጋሉ። ይህን ማድረግ ደግሞ አይቻልም። ነገር ግን ሙሐመድ ከነበሩበትና ካሳያቸው ምልክቶች ተነስተን የሙሐመድ ተከታዮች ሙሐመድን ነቢይ ያደረጉት “ሙሐመድ ያሳየቸውን ህመሞች (ምልክቶች) ” በቅጡ ሳይረዱ ቀርተው ስለመሆኑ ማወቅ እንችላለን።
[1] Chang BS, Lowenstein DH (September 2003). “Epilepsy”. The New England Journal of Medicine. 349 (13): 1257–66.
[2] Patrick McNamara: The Neuroscience of Religious Experience, p. 4
[3] https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC5565695/