ግልጠተ መለኮት ወይንስ የአእምሮ ጤና እክል? [ክፍል 1]

ግልጠተ መለኮት ወይንስ የአእምሮ ጤና እክል? [ክፍል 1]

ዶ/ር ሻሎም መኮንን


መግቢያ

ወደ ጽሑፉ ሐሳብ ከመግባታችን በፊት የአእምሮ ህመም ልክ እንደሌሎች የሰውነት ክፍል ህመሞች መታመምን የሚወክል እንጂ “ሰዎችን  ማሽሟጠጫ” እንዳልሆነ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ። በአሳዛኝ ሁኔታ እንደ ማህበረሰብ ለህመሙ የሚሰጠ’ው ምልከታ የተሳሳተ በመሆኑ  የአእምሮ ህመም እንደ ስድብ ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ይቆጠራል። የአእምሮ ታማሚዎች  ታክመው ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው ሊመለሱ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፤ አብዛኞቹም የአእምሮ ህመሞች በህክምና እርዳታ መልካም ውጤት አላቸው። የአእምሮ ህመም የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚገጥማቸው ሳይሆን ሁላችንም ላይ ሊከሰት የሚችል እክል ነው።

ይህ ጽሑፍ በሀዘኔታ መንፈስ እውነትን ለማሳወቅ እንጂ ሙስሊም ወገኖቻችንን ለማስከፋት እንዲሁም ነቢያቸው ሙሐመድ ላይ የስድብ ጅራፍ ለማንሳት ታቅዶ የተዘጋጀ ፈፅሞ አይደለም። በእርግጥ ከአፍላነት ዕድሜው አንስቶ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ የሙሐመድን ልእለ-ሰብነት  ሲሰበክ ለኖረ ሰው ይሄ ጽሑፍ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል እረዳለሁ። የሆነው ቢሆን እንኳ የተሳሳተ አመለካከት  መሬት ላይ ያለን “መራር እውነት ” ሊቀይር አቅም ስለሌለው በሆደ-ሰፊነት እውነታውን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።

ይህንን የሚያነቡ ሙስሊም ወገኖቻችን “የአእምሮ ህመምን” ካለመረዳት አንፃር “ስሜታዊ” ከመሆን በመቆጠብ መሬት ላይ ያለውን እውነታ እንዲያጤኑ ከፍ ባለ ትህትና እጠይቃለው። በተመሳሳይም የዚህን ጽሑፍ ድምዳሜ ተገን በማድረግ ሙሐመድን “ለማንቋሸሽ” ሊጠቀሙበት ያሰቡ ሰዎችን ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

በእርግጥ እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን ለማንበብ እድሉን ያገኘ ሙስሊም  ከሌሎች ዓይነት ጽሑፎች በተለየ መልኩ እስልምና ላይ ያለውን ኢማን (እምነት) ሊሸረሽር እንደሚችል ይታመናል። እስልምና የተመሠረተው እንዲሁም ዋና ዋና ስራዓቶቹ የተቀረፁት በሙሐመድ አእምሮ  ላይ ብቻ እና ብቻ ተደግፈው በመሆኑ ምርመራውን ወሳኝ እና “የጥያቄዎች ሁሉ ካስማ” ያደርገዋል።

የሙሐመድ የአእምሮ ጤንነት ጥያቄ ውስጥ ከገባ በእርሱ ወረደ የተባለው ቁርአን እንዲሁም ጅብሪል ነገረኝ ብሎ የተናገራቸው የእርሱ ንግግሮች በሙሉ በአንድ የጥርጣሬ ቋት ውስጥ ይገባሉ። የሙሐመድ አእምሮ ካመነጫቸው ሐሳቦች ውጪ “የእስልምና መኖር” አለመታሰቡ ርዕሱን አንገብጋቢ ያደርገዋል። በመሆኑም ሙስሊም ወገኖቻችን በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ ያሳደሩትን ጭፍን እምነት ገታ በማድረግ ነቢይ ያሉት አካልን የአእምሮ ጤና ሀቅን፣ ህሊናንና ሚዛናዊነትን ተጠቅመው መመርመር ይገባቸዋል። ይህ ጽሑፍ ለሙስሊም አንባብያን በተለይም ሀቅን ለሚፈልጉ የእውነትን መንገድ ለመጠቆም ያለመ ነው። ስለዚህም የዚህን ጽሑፍ ሐሳብ በመያዝ የእስልምናን መዛግብት እውነትን በሚፈልግ ልቦና መፈተሽ ብልህነት ነው።

የአእምሮ ህመም በምን መልኩ ይታይ?

የአእምሮ ህመምተኛ ሲባል በእየመንገዱ እርቃናቸውን የሚገልጡ ሰዎች ብቻ ወደ ሐሳባችን የሚመጡ ከሆነ ስለአእምሮ ህመም የተዛባ ግንዛቤ እንደያዝን ማሳያ ነው። የአእምሮ ህመም ሲባል ከመቶ ዓይነት በላይ  ህመሞች እንዳሉ ማስታወስ ያስፈልጋል። የአንድ አእምሮ እክል የተጋነነ ገፅታ ሁሉንም የአእምሮ እክሎች ሊወክል አይችልም።

የአእምሮ ጤና ስሜታዊ፣ ስነልቦናዊ እና ማሕበራዊ  ደኅንነትን ያጠቃልላል። በውስጡ የሚያካትታቸው ነገሮች መጠነ-ሰፊ በመሆናቸው ሁሉን ያስማማ አንድ የጋራ ወጥ ትርጉም ባይኖረውም የአእምሮ ጤና:- ” መደረግ  ያለበትን በማድረግ ራስን መምራት መቻል፤ ኃላፊነትን ማወቅ እና መወጣት፤ ምክንያታዊ ካልሆነ ጭንቀት ነጻ መሆን እንዲሁም ከአካባቢው ማሕበረሰብ ጋር ተግባብቶ ተግባርን ማከናወንና በማሕበረሰቡ ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤን መከተልን“  ያመለክታል። ይህ በእንዲህ ቢሆንም አንድ ሰው  እነዚህን የጤንነት ምልክቶች ሟሟላት እየቻለ አእምሮው ሊታመም የሚችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አይኖሩም ማለት አይደለም።

የአለም የጤና ድርጅትን (WHO) ጨምሮ በዘርፉ ያሉ ታላላቅ ማዕከላት ለአእምሮ ህመም ያስቀመጡትን “መስፈርት” እንደ መመዘኛ የተጠቀምን እንደሆን  የሙሐመድ አእምሮ “ጤናማ ነው” ወይስ ” ጤናማ አይደለም” የሚለው አከራካሪ አይሆንምም። በዘመናዊው የስነ-አእምሮ ህክምና መመዘኛ መሰረት አንድ የአእምሮ ህመምተኛ ሊያሳያቸው ይችላል የሚባሉትን ምልክቶች በሙሉ አሳይቷል። ምናልባት ዘመናዊው የስነ-አእምሮ ህክምና ሽምጥጥ ተደርጎ ካልተካደ በስተቀር በሙስሊም ወገኖቻችን መነፅር ቢታይ እንኳ ሙሐመድ ምልክቶቹን ማሳየቱን መካድ አስቸጋሪ ነው። የአለም የጤና ድርጅት (WHO) የአእምሮ ህመምን በተመለከተ ባወጣው ኦፊሴያላዊ መጣጥፍ የአእምሮ ህመሞች “ብዙ ይነት” እንደሆኑ በመግለፅ ከተለምዶ የወጣ አስተሳሰብ፣ አመለካከት (መረዳት)፣ ያልተስተካከለ ስሜት ፣ ባህርይ እና ከሌሎች ጋር በሚኖር ትስስር በአጠቃላይ እንደሚገለፁ ይጠቁማል። https://www.who.int/news-room/fact-sheets/detail/mental-disorders

በተመሳሳይም የአሜሪካ የስነ-አእምሮ ህክምና ማሕበር (APA) “የአእምሮ መሞች የስሜት፣ የአስተሳሰብ ፣ የባህርይ ወይም የእነዚህ ጥምር ለውጦችን የሚያካትቱ የጤና ሁኔታዎች ናቸው።” በሚል ጠቅላላ መገ’ለጫቸውን ያስቀምጣል። https://www.psychiatry.org/patients-families/what-is-mental-illness

አሁን በምንኖርበት ዘመን ላይ የአእምሮ ህመም ምልክቶች ከተባሉት ውስጥ ሁለት ወይንም ከሁለት በላይ ከታየ ወደ ጤና ተቋም በፍጥነት መሄድ እንደሚገባ የዘርፉ ጠበብት ይመክራሉ።  https://www.psychiatry.org/patients-families/warning-signs-of-mental-illness  

https://www.webmd.com/mental-health/signs-mental-illness

https://www.mayoclinic.org/diseases-conditions/mental-illness/symptoms-causes/syc-20374968

ወደ ሙሐመድ ስንመጣ ታሪኩን የሰማን ሁሉ በጋራ የሚያስማማ ቢያንስ አምስት ምልክቶችን አሳይቷል። እራሱን ለማጥፋት ሞክሯል፣ ለሌሎች የማይታይ ነገር አይቻለው ብሏል፣ ግዑዝ ነገር በተደጋጋሚ አዋርቷል፣ ብቻውን አውርቷል፣ ቀደም ከነበረው የባህርይ ለውጥ አሳይቷል፣ የወሲብ ህይወቱ ተቀይሯል፣ ከሰዎች ተገልሎ ለብቻው ሆኗል፣ ብዙ ጊዜ ይበሳጫል፣ ከሚስቶቹ ጋር ወሲብ ሳያደርግ እንዳደረገ ይቆጥራል፣ ለማሕበረሰቡ አደገኛ በሆነ ሁኔታ ያለ በቂ ምክንያት በሌሎች ላይ ጉዳት አድርሷል… በጣም ብዙ መጥቀስ ይቻላል።

የሙሐመድ የአእምሮ ህመም

የማንም ሰው የአእምሮ ጤና ይጣራል፤ እንደየ አስፈላጊነቱ ይፈተሻል። ስለዚህ ሙስሊሞች ይህ በጥንቃቄ ሊያዩት የሚገባ ወሳኝ ነጥብ እንጂ ሐሳቡን እንደ አይነኬ በመቁጠር ሊበሳጩበት አይገባም። ቁርአንም በተመሳሳይ የአእምሮ ጤናውን ማጣራት ተገቢ እንደሆነ ይናገራል።

«የምገስጻችሁ ባንዲት ነገር ብቻ ነው፡፡ (እርሷም) ሁለት ሁለት አንድ አንድም ኾናችሁ ለአላህ እንድትነሱ ከዚያም በጓደኛችሁ (በሙሐመድ) ምንም ዕብደት የሌለበት መኾኑን መርምራችሁ እንድትረዱ ነው፡ ፡ እርሱ ለእናንተ ከብርቱ ቅጣት በስተፊት አስጠንቃቂ ነው እንጂ ሌላ አይደለም» በላቸው። (የሳባ ምዕራፍ 46፡34)

በእርግጥ ይሄንን ክፍል የጠቀስኩት የአላህ ቃል ነው በሚል አይደለም። አላህ የሙሐመድን ጤንነትን ለተጠራጠሩ ሰዎች “የምገስፃችሁ በአንዲት ነገር ብቻ ነው” ብሎ በመለመን   ” ሁለት ሁለት እየሆናችሁ ጓደኛችሁ እብድ እንዳልሆነ መርምራችሁ ተረዱ”  የሚል ንግግር አደረገ ማለት ሰማዩን ምድር፤ ድንጋዩን ዳቦ እንደ ማለት ነው። አላህ ለፍጥረታት ሁሉ እዝነት አድርጎ የላከውን ሰው አእምሮው ጤናማ እንደሆነ የሚያረጋግጥበት መንገድ ሁለት ሁለት እየሆናችሁ እዩት በሚል ነውን? በፍፁም! ይህ ሙሐመድ የአእምሮ ጤናውን የተጠራጠሩ ሰዎችን “በአንዲት ነገር ብቻ ላስቸግራችሁ፣ እዩኝ እብድ እኮ አደለሁም ” ብሎ በአላህ ስም የተለማመጠበት መሆኑን ማንም አሳቢ አይስተውም።

አሁን የ21ው ክፍለዘመን ሰው የስነ-አእምሮ ህክምና ሳይንስን በመጠቀም የሙሐመድን አእምሮ ጤና ቢፈትሽ ምላሹ ምናልባት ሙስሊም ሆኖ ቀርቶ ከእስልምና ውጪ ቢሆን እንኳ የሚያስደነግጠው ነው። ሙሐመድ የአእምሮ ጤንነቱ የተዛባ ሰው ሆኖ ብናገኘው እንኳ “ሀሰትን በመናገር” ከእውነታነት ፈቀቅ ልናደርገው ስለማንችል ለእውነት እራሳችንን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል። የሙሐመድን “የአእምሮ ጤና” ተከታዮቹ ያረጋገጡበትን መንገድ በቀጣይ ክፍል የምናየው ይሆናል።

ሙሐመድ ” አእምሮው ጤናማ አልነበረም” የሚል አመለካከት ዛሬ ላይ ድንገት ብቅ ያለ ሳይሆን በወቅቱ ሙሐመድ አካባቢ  በነበሩ ሰዎች ሳይቀር በስፋት ሲያውጠነጠን የነበረ ነው። 

(ኑን)፤ በብርእ እምላለሁ በዚያም (መልአኮች )  የተጎናጸፍክ ስትኾን እብድ አይደለህም፡፡ (የቀለም ምዕራፍ 1፡68)

በቲርሚዝይ ዘገባ  መሠረት ሙሐመድ እንዳለው ከሆነ በዚህ የቁርአን ክፍል ላይ  የሙሐመድን የአእምሮ ጤና ለማሳመን በአላህ የተማለባት ብዕር የፍጥረታት በኩር ስትሆን አፍ አውጥታ አላህን ምን ላድርግ ብላ ታናግራለች።  ብእሯ ላይ ብዙ ጥያቄ ቢነሳም ከርእሳችን ላለመውጣት ነገረ – ብእሯን ትተን የመሀላው ትርጉም አልባነት ላይ እናተኩር።

ወደ መሀላው አላማ ስንመለስ ሙሐመድ መሀላውን የአእምሮ ጤናውን ጥያቄ ውስጥ ያስገቡት ሰዎችን ለመርታት የተጠቀመበት መንገድ  መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ንግግሩ ሲጠቀለል ” አላህ ምሎ እና ተገዝቶ ጤነኛ መሆኔን ነገረኝ” የሚል ሐሳብ ለማስተላለፍ ነው።

ንግግሩ የአላህ ነው ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ሙሐመድን እብድ ያሉት ሌሎች ሆነው ሳለ ለእራሱ ለሙሐመድ እብድ አደለህም ብሎ መማል “አራምባ” እና “ቆቦ” ነው። ተናጋሪው አላህ ቢሆን ኖሮ “እብድ አይደለህም” ብሎ ለሙሐመድ ከመማል ይልቅ ጤነኛነቱን በሌላ ውጤታማ መንገድ ማረጋገጥ ይችል ነበር።  በአጭር ቃል “ያለው ችግር ሌላ፤ የተቀመጠው መፍትሄው ሌላ” ነው። የሙሐመድን የአእምሮ  ጤና የጠየቁ ሰዎች ሌሎች ሆነው  ሳለ  የሙሐመድን እብድ አለመሆን ለእራሱ ለሙሐመድ በመሃላ እና በግዘታ  መንገር እንዴት ያለ ፈሊጥ ነው?

እዚህ ጋር በሙሐመድ ላይ የተፈጠረው ግልፅ እንዲሆን አንድ ምሳሌ ልስጥ:-  በአንድ የአእምሮ ህክምና ተቋም ውስጥ ሀኪም ናችሁ እንበል።  አንድ በአእምሮ ህመም የተጠረጠረ ሰው እናንተ ደህንነቱን እንድታረጋግጡለት ወደ እናንተ መጣ። ታድያ እናንተ ጤንነቱን ለማረጋገጥ “በለበስኩት ጋውን፣ በያዝኩት እስኪብርቶ” እምላለው ጤነኛ ነህ ትሉታላችሁ? እንኳን ሁሉን የሚያውቅ ፈጣሪ ይቅርና እኛ ተራ ሰዎች ይሄንን ስህተት አንፈፅምም። ይህንኑ ምሳሌ አዟዙረን እንይ። በአንድ መስርያ ቤት አለቃ ናችሁ እንበል። በአእምሮ ህመም አንድ ሠራተኛችሁን ጠረጠራችሁት እንበል፤ እናም የአእምሮ ህመም እንደሌለበት ማረጋገጫ እንዲያመጣ ጠየቃችሁት። እርሱም ትንሽ ቆየት ብሎ  እገሌ የሚባል ዶክተር “በእስኪብርቶው፣ በጋውኑ ምሎ ጤነኛ ነህ አለኝ” ብሎ ወደ እናንተ ቢመጣ አይ በቃ ጤነኛ ነው ትላላችሁ? በፍፁም። ጤነኛ ያለመሆኑን ማረጋገጫ እንዳገኛችሁ ነው የምትቆጥሩት!

ንግግሩ የሙሐመድ ከሆነ ግን ጤነኛ መሆኑን ለማሳመን ማድረግ የሚችለው ይህንን ብቻ ነው። ብዙ የአእምሮ ህመምተኞች መታመማቸው አምነው አይቀበሉም። ህመሙ ተረጋግጦ እንኳ መድኃኒት ውሰዱ ሲባሉ ” አላመመኝም እኮ!  እንዴ ምን ሆናችኋል! መች አመመኝ!?” ማለት የተለመደ ነው። ይህ የታማሚዎች ሁኔታ አኖሶግኖሺያ  ሲባል በርካታ  የአእምሮ ህመምተኞች ላይ የሚታይ ነው።  በቁርአን የአላህ ቃል ተብሎ በመሀላ የታጀበው ንግግር ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ ሳይሆን ሙሐመድ አእምሮ ህመሙን ለመካድ የሚያደርገው ትንቅንቅን በግልፅ የሚያሳይ ነው።  ሙሐመድ “እብድ ነኝ” ብሎ ካላሰበ አልያ “እብድ” ያሉትን ሰዎች በአላህ ስም ምሎ  ለመርታት ካላሰበ “ፈጣሪ ምሎ ጤነኛ ነህ አለኝ” አይልም። በዚሁ የቁርአን ሱራ ላይ ዝቅ ብለን ስንመለከት  የሙሐመድን የአእምሮ ጤና የጠየቁ ሰዎችን “እስኪ ማን እብድ እንደሆነ እናያለን” የሚል አይነት የብሽሽቅ መንፈስ ያዘለ ንግግር እናገኛለን (5-6)። ወረድም ሲል ዲቃላ፣ ወራዳ፣ ልበ-ደረቅ የሚሉ አፀያፊ ቃላቶችን ለእነርሱ ውለው እናገኛለን (10-13)።

በቁርአን ሌሎች ክፍሎች ላይም በወቅቱ የሙሐመድን የአእምሮ ጤና የሚጠይቁ ሰዎች እንደነበሩ ተዘግቦ እናገኛለን።

«አንተ ያ በእርሱ ላይ ቁርአን የተወረደለት ሆይ! አንተ በእርግጥ እብድ ነህ» አሉም፡፡ «ከእውነተኞቹ እንደ ሆንክ በመላእክት (መስካሪ) ለምን አትመጣንም» አይደሉም፡፡ መላእክትን በእውነት (በቅጣት) እንጂ አናወርድም፡፡ ያን ጊዜም የሚቆዩ አይደሉም፡፡” (የድንጋያማ መሬት ምዕራፍ 6፡8-15 )

“እኛ ለእብድ ባለቅኔ ብለን አማልክቶቻችንን የምንተው ነን? ይሉም ነበር፡፡ (የተሰላፊዎች ምዕራፍ 36፡38-37)

“(ሰዎችን) አስታውስም፡፡ አንተም በጌታህ ጸጋ ምክንያት ጠንቋይም እብድም አይደለህም፡፡(የተራራ ምዕራፍ 29፡52)

“ነብያችሁ በፍፁም እብድ አይደለም።” (የመጠቅለል ምዕራፍ 22፡81)

ሙሐመድ ኖሮ ካለፈም በኋላ  ለዘመናት የአእምሮ ጤናው ጥያቄ እየቀረበበት ዛሬ ላይ ደርሷል። በቀጣይ የጽሑፉ ክፍሎች የሚቀርቡት መረጃ የጠገቡ ምልከታዎች  የጸሐፊው የግል አስተያየት ሳይሆን ብዙ ምሁራን የሚጠይቁት “መሬት ላይ ያለ እውነታ” መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በመካከለኛው ዘመን የአይሁድ ታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ሙሐመድን መሹጋዕ ( מְשֻׁגָּע ) ወይንም “እብዱ” ብሎ መጥራት የተለመደ ነበር። በተመሳሳይም በእየዘመኑ ሙሐመድን አጋንንት እንደያዘው፣ የሚጥል በሽታ እንዳለበት እንዲሁም አእምሮው ልክ እንዳልሆነ ሲያሳውቁ የነበሩ ሰዎች ጥቂት አልነበሩም። ሙሐመድም ቢሆን በመጀመርያው መገለጥ [ህመም] ወቅት  ያጋጠመውን ክስተት  “የአእምሮ ህመም አልያ አጋንንታዊ ልክፍት” በሚል እንጂ እንደ መገለጥ  አልቆጠረውም። በቀጣይ የሚቀርበው የጽሑፉ ክፍል ከስሜታዊነት በራቀ መንፈስ ተሁኖ በእርጋታ እንዲነበብ ግብዣዬ ነው።

ይቀጥላል …


ሙሐመድ