ግልጠተ መለኮት ወይንስ የአእምሮ ጤና እክል? [ክፍል 2]

ግልጠተ መለኮት ወይንስ የአእምሮ ጤና እክል? [ክፍል 2]

ዶ/ር ሻሎም መኮንን


የሚጥል በሽታ (TLE) ወይንስ መገለጥ?

አንድ ሰው  መንገድ ላይ ወድቆ “ለመተንፈስ እየተቸገረ እንደ ግመል እያጓራ በላብ ተጠምቆ፣ ከንፈሩን ያለ ድምፅ እያንቀሳቀሰና አረፋ ደፍቆ” ብናገኝ ሁላችንም “አጋንንት ይዞታል” አልያም “የሚጥል በሽታ አለበት” ብለን እንደምናስብ ጥርጥር የለውም። ህመሙ እንዳለፈለትም በፍርሀት ውስጥ የልብ ምቱ ጨምሮ እያየን  ማናችንም ፈጣሪ ተገልጦ ምን አለህ?” ብለን አንጠይቀውም፤ የአእምሮ እክል ከሌለብን በስተቀር። ነገር ግን በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ይህ መረዳት ባለመኖሩ አልያም ህመሙን የግላዊ (ፖለቲካዊ) ፍላጎታቸው ሟሟያ አድርጎ ለመጠቀም በማሰብ ከህመሙ በኋላ “ጅብሪል ተገልጦ ሙሐመድን ምን እንዳለው” ለመስማት የሙሐመድ ተከታዮች በጉጉት ሲጠባበቁ በእስልምና  መዛግብት ላይ ሰፍሮ እንመለከታለን።

ሙሐመድ ላይ የተከሰተው ዓይነት የአእምሮ እክል በህክምናው አለም “ቴምፖራል ሎብ ኤፒለፕሲ” (TLE) በመባል ይታወቃል። ይህ ህመም የተከሰተው በሙሐመድ ላይ ብቻ ሳይሆን በዘመናት ሁሉ በብዙዎች ላይ የተከሰተና ሊከሰት የሚችል ነው። በዚህ ዘመንም የዚህ ህመም ተጠቂዎች ሲኖሩ ወደ ህክምና ተቋማት እየሄዱ የህክምና ክትትል ያገኛሉ። ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ግብ የሌለው ፕሮፌሰር ፍሪመን የተሰኘ የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስትና ኒውሮሎጂስት በሙሐመድ ሕይወት ላይ ሰፊ ጥናት በማድረግ የሰጠውን አስተያየት በማቅረብ ወደ ዝርዝር ማብራርያ እናልፋለን፦

“አንድ  [የዘርፉ ባለሙያ] ሰው [በሙሐመድ በሽታ/መገለጥ ላይ] የህክምና ምርምር እንዲያደርግ ከተገደደ፣ በቴምፖራል ሎብ ኢፒለፕሲ  የሳይኮ ሞተር የሚጥል ህመም ማጋጠሙ ወደ እውነታ በጣም የተጠጋ ማብራሪያ ይሆናል…” (Freemon FR. A differential diagnosis of the inspirational spells of Muhammad the Prophet of Islam. Epilepsia. 1976 Dec;17(4):423-7. doi: 10.1111/j.1528-1157.1976.tb04454.x. PMID: 793843.)

ቴምፖራል ሎብ ኢፒለፕሲ (TLE)  የሚጥል በሽታ ዓይነት ቢሆንም የአእምሮ እክል እንደመሆኑ ቀጥታ ከእብደት (ስኪዞፍሬኒያ)  ጋር ባይገናኝም በርካታ የስነ-አእምሮ ተፅእኖዎች አሉት። ታድያ “መሬት ወድቆ ማጓራቱን” ጨምሮ ይህ እክል የሚያስከትባቸውን የስነ-አእምሮ ተፅዕኖዎ አንድ በአንድ የሙሐመድ የሕይወት ታሪክ ውስጥ እናገኛቸዋለን። የኒውሮ-ሳይንቲስት  የሆነው ዶክተር ፓትሪክ ማክናማራ “The neuroscience of religious experience” በሚለው መፅሀፉ ገፅ 4 ላይ እንዲህ ይላል፦

“በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የሚጥሉ በሽታ (TLE) ዓይነቶች ላይ የሃይማኖተኝነት ውዥንብር በርከት ባሉ ታማሚዎች  መታየታቸውን አሳማኝ በሆነ መንገድ የሚያሳዩ በደርዘን የሚቆጠሩ ጥናቶች ተካሂደዋል። ህመሙ ከመነሳቱ በፊት (pre-ictal) እና በህመሙ ወቅት (ictal) ግለሰቡ በሚወድቅበት ወይንም ሊወድቅ ሲል የሃይማኖታዊ ምልክቱ ወደ “ቁም ቅዠትነት” ሊያድግ ይችላል። ታማሚዎቹ “እኔ አምላክ ነኝ” ወይም “አምላክን ፊት ለፊት አነጋገርኩ” ሊሉ ይችላል …” ዶክተሩ ይቀጥላል .. “የዚህ ህመም ታማሚዎች የሥጋት እንቆቅልሽ ውስጥ ሊገቡ ሲችሉ አንዲት ጸሎት እንኳ ለማድረግ በየሳምንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዓታት ሊያጠፋ ይችላሉ  ወይም ” አጋንንት እንደተቆጣጠራቸው አድርገው ሊቆጥሩ ይችላል። እነዚህ ሕመምተኞች ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ አካል ወይንም በክፉ መንፈስ እንደተያዙ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ሊሆኑ ስለሚችል ይጎዳሉ። አንዳንድ ህመምተኞች ከእነርሱ ውጪ ባለ አካል ቁጥጥር ስር የሆኑ ስለሚመስላቸው ለሕይወታቸው አስጊ ይሆናል።”

እ.ኤ.አ. በ1975 የነርቭ ሐኪሞች የሆኑት ስቴፈን ዋክስመን እና ኖርመን ጌሽዊንድ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚጥል በሽታ (TLE) ባለባቸው ታካሚዎቻቸው ላይ ያደረጉትን ክትትል በመመርኮዝ በዘርፉ ልሂቃን ሰፋ ያለ ቅቡልነት ያገኘ ትንታኔ አሳትመዋል። ጥናታቸው እንደሚያሳየው ከሆነ ብዙ ሕመምተኞች ወደ ሃይማኖተኛነት ይሳባሉ፣ ጥልቅ ስሜቶች ይኖሯቸዋል፣ ዝርዝር ሐሳቦችን ያብሰለስላሉ እንዲሁም ህመሙ “እንዲጽፉ” ወይንም “እንዲስሉ” ያስገድዳቸዋል።

ይህ ህመም ጊዜያዊ ነገሮችን የሚቆጣጠር የአእምሮ ክፍል (temporal lobe ) የሚነሳ ሲሆን አእምሮአቸው ወደ እነርሱ የሚመጣውን ሐሳብ የሚረሳ ስለሚመስለው ሰንዶ መያዝ የህመምተኞቹ ምርጫ ይሆናል። ወደ ሙሐመድ ስንመለስ ጅብሪል “አንብብ” እያለ ያስገደደ የመሰለው እንዲሁም የተናገራቸውን ነገሮች እንዳይጠፉ እራሱ ሲሸመድድ፣ ሰዎችን ሲያስሸመድድ፣ ድንጋይ፣ ቅጠል፣ አጥንት፣ ቆዳ፣ ሰሌን፣ ወዘተ. ላይ ሲያስጽፍ የነበረው ከዚህ የህመም ምልክት ጋር በተገናኘ ሁኔታ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በቁርአን በተደጋጋሚ “አስታውስ!” የሚሉ ከበሽታው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ንግግሮችን እናገኛለን። ይሄ ምልክት የጌሽዊንድ ምልክት በመባል በስፋት በስነ-አእምሮ ህክምና  ይታወቃል።

ከቀዳሚው መገለጥ እንጀምር፦

[አኢሻ እንደተረከችው] … ሙሐመድ በሂራ ዋሻ ውስጥ  [ከሰው ተገልለው ለብቻቸው] እያሉ ድንገት እውነቱ ወደእርሳቸው ወረደ።  መልአክ  ለእርሳቸው ተገልጦ እንዲያነቡ ጠየቃቸው። እሳቸውም  “ማንበብ አላውቅም ብለው መለሱለት።” በኋላም መልአኩ በሀይል ተጫነኝና በጣም አስጨነቀኝ ” አሉ። በመቀጠል ለቆኝ  እንዳነብ በድጋሚ ሲጠይቀኝ  ‘ማንበብ አላውቅም’ ብዬ መለስኩለት። እንደገና ያዘኝ እና መቋቋም እስኪያቅተኝ ለሁለተኛ ጊዜ ጨመቀኝ እና እንዳነብ  ጠየቀኝ እኔም  ‘ማንበብ አላውቅም አልሁት። ‘ በመጨረሻም ለሦስተኛ ጊዜ ተጭኖ ለቀቀኝና ‹አንብብ በጌታህ ስም፣ ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው። አንብብ! ጌታህም በጣም ቸር ሲሆን።” ( የረጋ ደም ምእራፍ 1-3  ) ከዚያም የአላህ መልእክተኛ የተገለጠለትን ይዞ  “ልቡ ክፉኛ እየመታች ” ወደ ኸዲጃ ቢንት ሑወይሊድ (ሚስታቸው) ዘንድ በመሄድ ፡- ሸፍኑኝ! ሸፍኑኝ! ” አለ። እነርሱም  ፍርሃቱ እስኪያልፍለት  ድረስ ሸፈኑት።  ፍርሀቱ ሲያልቅ የሆነውን ሁሉ በመናገር  “አንድ ነገር እንዳይደርስብኝ እፈራለሁ” አለ። (ሳሒህ አል-ቡኻሪ 9/111)

ጅብሪል መልአክ ከሆነ ሙሐመድ ማንበብ እንደማይችል ያውቃል። ካወቀ ደግሞ በግድ አንብብ ብሎ በተደጋጋሚ ሊሞት እስኪመስለው ማስገደድ አልነበረበትም። በተጨማሪም እንዲያነብ ያቀረበለት ምንም ዓይነት ነገር የለም። ነገሩ ግን ወዲህ ነው! ኢቅረዕ ﺃﻗﺮﺃ የሚለው ቃል መነሻው ቀ-ረ-አ ق ر ء የሚል ሲሆን  ማንበብ፣ ማጥናት፣ መሳል፣ መሸምደድ የሚሉ ትርጉሞችንም ይይዛል። https://en.m.wiktionary.org/wiki/أقرأ

ሀይፐር ግራፊያ (hypergraphia) የሚባለው የበሽታው ምልክት ህመምተኞች በማናቸውም ሰዓት ወደ ሐሳባቸው የመጣውን ተራ ነገር ሁሉ ሰንደው እንዲይዙ ያስገድዳቸዋል። ሙሐመድ  መሬት ላይ በሚወድቅ ሰአት የተከሰተው የሙሐመድንና የጅብሪል “አንብብ/ማንበብ አልችልም”  የሚለው ግብግብ አንዱ የህመሙ መገለጫ ነው። ኢብን ኢሳቅ በከተበው ሲራ እንዲህ ይገልፀዋል

…እንዳለኝ ሳደርግ [ሳነበንብ]  ከእኔ ተለየ (ጅብሪል) ከዚያም ከእንቅልፌ ስነቃ ቃሎቹ ልቤ ላይ ተፃፉ ( ኢብን ኢሳቅ ገጽ 71-72)

የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ህመሙ ከጣላቸው በኋላ የሚሆኑበት ሁኔታ (post ictal state) ሙሐመድ ከመገለጡ በኋላ ከሆነበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። ከህመሙ በኋላ የልብ ምት መጨመር፣ ፍርሀት፣ ላበት፣ መደናገጥ፣ መደናገር፣ ድካም ይታያል።   አል-ቡኻሪ በዘገበው በሌላ የሐዲስ ክፍል ላይ ወደቤቱ የተመለሰበትን አኳዃን እንዲህ ያስቀምጠዋል፦

የአላህ መልእክተኛም መገለጡን ተቀብሎ ሲመለስ ከድጃ ጋር እስኪገባ ድረስ በፍርሃትና የአንገቱ ጡንቻዎቹ በመንቀጥቀጥ ይብረከረኩ ነበር፡፡ እርሷ ጋ ሲደርስም “ሸፍኑኝ ሸፍኑኝ” አለ፡፡ እነርሱም ፍርሃቱ እስኪለቀው ድረስ ሸፈኑት፡፡ እርሱም “ከድጃ ሆይ ምን እየሆንኩ ነው; ብሎ ጠየቃት፡፡ የገጠመውንም ነገር ሁሉ ከነገራት በኋላ “የሆነ ነገር ሳልሆን አልቀርም” አላት፡፡ (አል-ቡኻሪ፣ 4953)

የጡንቻ መንቀጥቀጥ ከመገለጥ ጋር ሳይሆን ከነርቭ ጋር የተያያዘ ሲሆን የዚህ ህመም ተጠቂዎች ከህመሙ በኋላ ሲከሰትባቸው ይስተዋላል።

በመቀጠል ሙሐመድ ህመሙ [መገለጡ] ሲነሳበት ሌላ የሚያየውን ምልክት በእንዲህ መልኩ በኢስላማዊ መዛግብት ሰፍሮ እናገኛለን።

አል-ሃሪሳ ቢን ሒሻም ነቢዩን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፡- ራዕዩ ሲወርድለዎት በምን ሁኔታ ነው? እርሳቸውም ሲመልሱ መልአኩ አንዳንድ ጊዜ የደዎል ድምጽ በሚመስል ድምጽ እየተናገረ ይመጣል፤ ይህ አይነቱ የራዕይ አወራረድ ለእኔ በጣም ልቋቋመው የማልችለው ከባድ አይነት ነው፡፡ መልአኩ ትቶኝ ከሄደ በኋላ የተቀበልኩትን ራዕይ አስታውሰዋለሁ፡፡ አንዳንዴ ሰው በመምሰል ወደ እኔ ይመጣና ያናግረኛል እኔም ምን እንዳለኝ እረዳዋለሁ፣ አስታውሰዋለሁም፡፡ አኢሻ ጨምራ መልአኩ በእርሳቸው ላይ በወረደ ጊዜ በከባድ ብርድ ሰዓት ግንባራቸው ላብ በላብ ይሆናል፡፡ (አል-ቡኻሪ፣ ቅጽ 2 ሐዲስ 934)

የቴምፖራል ሎብ ኤፒለፕሲ ታማሚዎች የህመም ምልክቶች ውስጥ አንዱ የሚያቃጭል ድምፅ መስማት ነው። ሙሐመድም በግልፅ መገለጡ አንዳንዴ እንደ ቃጭል ድምፅ መሆኑን ተናግሯል። የዘጋቢዎቹ ወገንተኝነትና ስለህመሙ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ስለነበረ  ሙሐመድ ያጋጠመው የአእምሮ ህመም መሆኑን ከመገንዘብ ከልክሏቸዋል። የኢስላም ተራኪዎች ህመሙን  “መገለጥ” እንደሆነ ቢገልፁም “የመገለጥ ናቸው” ያሏቸውን ምልክቶችን እየነጠልን በማውጣት በህክምና ሚዛን ብንመዝናቸው ሙሐመድ በዚህ ህመም [TLE] እንደተጠቃ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንደ ሙሐመድ ሁሉ ይህ የሚያቃጭል ድምፅ ከባድ ውጥረት እንደሚፈጥርባቸው የዚህ በሽታ ታማሚዎች ይናገራሉ። ቅጭል… ቅጭል ከሚል ድምፅ በተጨማሪ ጥዝዝ… የሚል ድምፅ፣ ሽሽሽ… የሚል ድምፅ እንደየ ህመምተኛው  ሊሰማ ይችላል።  ሙሐመድ የመንጋ ንቦች አይነት ድምፅ (ጥዝዝ… የሚል ድምፅ) እንደሚሰማ ቲርሚዝይ በዘገበው ሐዲስ ተዘግቦ እናገኛለን (ሐዲስ ቁጥር 3173)። አኢሻ በዘገባው እንዳከለችው ሙሐመድ መገለጡ (ህመሙ) በሚያልፍለት ሰዓት ላብ በግንባሩ ተመልክታለች። በተመሳሳይም የዚህ ህመም ተጠቂዎች የአካባቢውን የሙቀት ሁኔታ ያላገናዘበ  ላበት ይኖራቸዋል። እንደላይኛው ሁሉ በዚህም ሐዲስ ሙሐመድ ያሳያቸው ምልክቶች በጠቅላላ የቴምፖራል ሎብ ኤፕለፕሲ ናቸው። የዘገባዎቹ ለሙሐመድ መገለጥ ያላቸው ወገንተኝነት እንዳለ ሆኖ ሙሐመድ ላይ መገለጥ ተብሎ ያየነው ምልክት ዛሬም የህመሙ (TLE) ተጠቂዎች የሚያሳዩት ነው። 

ነቢዩ በጂራና ሳሉ አንድ ሰው መጣ፡፡ ሰውየው ኻሉቅ ወይንም ሱፈራ በሚባል ሽቱ የተቀባ ካባ ለብሶ ነበር፡፡ ሰውየው ነቢዩን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፡- በኡምራየ ወቅት ላደርገው የሚገባ የሚያዙኝ ነገር ምንድን ነው? ከዛ በጨርቅ መጋረጃ በተጋረደ ቦታ ሆነው አላህ ለነቢዩ መልእክት ይሰጣቸው ጀመር፡፡ እኔም አላህ ለነቢዩ መገለጥ ሲሰጣቸው እንዴት እንደሚሆኑ ለማየት ጓጓሁ፡፡ ኡመርም እንዲህ አለኝ፡- ና! አላህ ለነቢዩ መገለጥ ሲሰጣቸው እንዴት እንደሚሆኑ ማየት ትፈልጋለህ? እኔም አዎን ስል መለስኩለት፡፡ ኡመርም የመጋረጃውን አንዱን ጎን አነሳልኝ፣ እኔም ነቢዩ ሲያንኮራፉ አየሁ፡፡ (ሌላ ተናጋሪ እንዲህ እንደተናገረ አስቧል፡- ኩርፊያው የግመል ይመስል ነበር)። (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅጽ 3፣ ሐዲስ 17)

የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች የተለየ ሽታ ሲሸታቸው ህመሙ የማገርሸት ባህርይ አለው። ይህ ማለት ግን ሁሌም የተለየ ሽታ ሲሸታቸው ይነሳባቸዋል ማለት ሳይሆን ሽታው ህመሙ እንዲያገረሽ የማድረግ ፀባይ አለው። በዚህ የሐዲስ ክፍል ላይም ሙሐመድ ህመሙ ተነስቶበት እንጂ ደጋፊዎቹ  እንደሚሉት መገለጥ እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ያእላ የተባለው የዚህ ሐዲስ ባለታሪክ ያየው ምስክርነት በቂ ነው። ያእላ የሙሐመድ ፊት ቀልቶ እንዳየው ምስክርነቱን ሰጥቷል። በሌሎች ሀዲሶች ላይ በህመሙ  [መገለጥ] ወቅት የሙሐመድ ፊት እንደሚገረጣ ተናግረዋል።

ኡመር እንዲህ አለኝ፡- የአላህ መልእክተኛ ራዕይ ሲወርድላቸው ማየት ትፈልጋለህ? እርሱም የመጎናጸፊያቸውን ጠርዝ ከፊታቸው ላይ ሲያነሳው ጅራና ላይ ነበር ራዕዩን ይቀበሉ የነበረው፣ ፊታቸው ደም መስሎ ቀልቶ ነበር፤ አዲስ እንደተወለደ ጥጃም ያቃስቱ ነበር፡፡ (Al-Sira Al-Nabawiyya, vol 1, p. 107)

በተጨማሪም እንደ ያእላ ምስክርነት በሃይል ይተነፍሳል። የዚህ ህመም ተጠቂዎች በህመሙ ወቅት የደረት ጡንቻዎች (thoracic muscles) እና አውታረ ድምፆች (vocal cords) ስለሚኮማተሩ ታማሚዎች አየር እንደ ልብ እንዳይወስዱ ያደርጋቸዋል። በዚህም ምክንያት ለመተንፈስ መቸገር፣ ማልቀስ፣ ማጓራት በብዛት በሚጥላቸው ወቅት ይታያል። በተጨማሪም የዚህ ትንቅንቅ አረፋ እንዲደፍቁ ሊያደርጋቸው ይችላል። ቀደም ሲል በተቀስነው ሐዲስ (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅጽ 3፣ ሐዲስ 17) ያእላ የተሰኘ ሰው በሙሐመድ ላይ ያየውን ካያቸው የመገለጥ ምልክቶች መካከል አንዱ እንደ ግመል ማጓራት ነበር። እንደ ግመል ማጓራት የመገለጥ ምልክት ተደርጎ እንዴት  እንደታሰበ ባይገባኝም የTLE ህመምተኞች ህመማቸው ሲነሳባቸው ለመተንፈስ በመቸገር ሊያጓሩ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ሙሐመድ  በመገለጥ ወቅት አረፋ ይደፍቅ ነበር፦

ነብዩ (ሶ.ዐ.ወ) ጅብሪልን በመጀመሪያው መልክ ሲያዩት ራሳቸውን ስተው ወደቁ። ጅብሪል ወርዶ ነብዩን አነቃ  እና ምራቅ ከጉንጮቻቸው ላይ ጠራረገ። (ተፍሲር ኢብን ከሢር 53:6-7)

እራሱን ስቶ አረፋ መድፈቅ ከመገለጥ ጋር ግንኙነት አለው ማለት ያስቸግራል። ቢሆንም ግን የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች አረፋ መድፈቅ እንዲሁም ከቁጥጥር ውጪ መሆናቸው የተለመደ ነው።

መገለጡ (ወህይ) ወደ ነቢዩ ሲመጣ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁንና) በጣም  ይሠቃያሉ በተጨማሪም ፊታቸው አመድማ ይሆናል (ይገረጣል)። (ኢብን ሳድ፣ ኪታብ አል-ጠቃባት አል-ከቢር 1:47:4)

ያእላ ያየው በአቡ ዳውድ ሐዲስ ላይ ሙሐመድ የተለየ ሽታ ሸቶት ህመሙ [መገለጡ] እንደ ግመል ካስጓራው በኋላ በቀስታ ወደ ሰውየው እንደመጣ ያስቀምጣል። (አቡዳውድ 1819)። ይህ የሚያሳየው ከህመሙ በኋላ በድካም ውስጥ እንደነበር ነው። በተጨማሪም ቁርአን “የልብስ ደራቢው ምዕራፍ 1-5 (ሱራ 74)” ሲወርድ የነበረውን ክስተት አል-ቡኻሪ በዚህ መልኩ አስቀምጦታል፦

ጃቢር ኢብኑ አብደላህ እንደተረከው ነቢዩ እንዲህ አሉ፡- “መለኮታዊ  መገለጥ ለአጭር ጊዜ ዘግይቶ ነበር። ነገር ግን ስጓዝ በድንገት  ከሰማይ ድምፅ ሰማሁ፤ በአግራሞት ወደ ሰማይም ቀና ብዬ ስመለከት በሂራ ዋሻ ውስጥ ሳለሁ  ወደ እኔ የመጣውን መልአክ  በሰማይና በምድር መካከል ባለው ወንበር ላይ ተቀምጦ አየሁኝ። በጣም ፈርቼው መሬት ላይ ወድኩኝና  ወደ ቤተሰቦቼ በመሄድ ” ሸፍኑኝ! (በብርድ ልብስ) ሸፍኑኝ!” አልኩ።  ከዚያም አላህ ራዕዩን ላከ፤ ቁርአን የልብስ ደራቢው ምዕራፍ [74:1-5] ( አል-ቡኻሪ  3238)።

የጅብሪል ገፅታ

እንደ እስልምና ዘገባ መሠረት ጅብሪል እንደ ሰው እየተገለጠ ይታየዋል፣ ድምፁን ብቻ ይሰማል እንዲሁም የመጀመርያ መገለጡን ጨምሮ ሁለቴ በትክክለኛ ገፅታው አይቶታል። የመጀመርያው መገለጥ ላይ ያየው እጅግ ግዙፍ ሰማይና ምድር መካከል መቀመጥ የሚችልና  ባለ ስድስት መቶ ክንፍ ባለቤት የሆነ መልአክ ነው። ክንፎቹ ከትልቅነታቸው የተነሳ ደመናውን ሰንጥቀው ያልፋሉ በተጨማሪም በክንፎቹ ላይ ቀያይ ጌጣጌጦች፣ እንቁ  የመሳሰሉ ነገሮች አሉባቸው። ሙሐመድ ያጋጠመው ቅዠት ካልሆነ እያዳፋና እየጨመቀው በነበረበት ሁኔታ የእሱን ስድስት መቶ ክንፎች አንድ ሁለት እያለ ቆጥሮ ያውቃል ማለት አስቸጋሪ ነው። በቀላል አማርኛ የቁም ቅዠት ነው። አስገራሚው የሙሐመድ ወዳጅ ከጆሮ ግንዱ እስከ ትከሻው ድረስ ያለው ርቀት ብቻ የሰባት መቶ አመት መንገድ ነው። (ሱነን አቡ ዳውድ 4727)።

የወረቃ አረዳድ እና የኸዲጃ ፈተና

የሙሐመድን መገለጥ ትክክለኛ መሆን አለመሆኑን ዘመዶቹ የለዩበት መንገድ ትንሽ ፈገግታን የሚያጭር ስለሆነ ሳልጠቅሰው ባልፍ ትልቅ ነገር እንደማጉደል ነው። ወረቃ ክርስቲያን ነበር ቢባልም በሙሐመድ ዘመን ንስጥሮሳውያን በአረብያ ባህረሰላጤ በስፋት ተሰራጭተው ስለነበር የስህተት ትምህርት ውስጥ የነበረ ሊሆን ይችላል። የሆነው ቢሆን እንኳን ሙሐመድ በድንጋጤ፣ የልብ ምቱ ጨምሮ “ልብስ ደርቡልኝ” በሚል ሰአት “አይ ያየኸው ሙሴ ያየውን ጅብሪልን ነው” የሚል ትምህርት በሰማይም በምድርም በክርስትና መጽሐፍትም ተሰምቶ የማይታወቅ ምልከታ ሰጥቶታል። ይህንን እሳቤውን በመመርኮዝ ወረቃ በዕድሜ መግፋት የሚመጣ የአእምሮ እክል (መጃጀት)  ደረሰበት ብለን ብናስብ እንኳ የኸዲጃ  ግን  የባሰ ነው፦

የአላህ መልዕክተኛ ” ኸዲጃ ሆይ! ድምጾችን ሰማሁኝ ፤ ብርሃንንም አየሁ  እኔ ሰጋሁ እብድ ሆኛለው።  ኸዲጃም  “የአብደላህ ልጅ (ሙሐመድ)  ሆይ! አላህ ባንተ ላይ  እንዲህ አያደርግም”  ብላ ወደ ወረቃ ኢብኑ ነውፈል ጋር በመሄድ የተፈጠረውን አስረዳችው። ወረቃም፡- እውነቱን ከሆነ ይህ ሙሴን ያጋጠመው “ናሙስ” ነው። እኔ በሕይወት ካለሁ (በነቢይነት) በተሾመ ጊዜ እደግፈዋለሁ፣ እረዳዋለሁ  በእርሱም አምናለሁ። (ኢብን ሳድ፣ ኪታብ አል-ጠበቃት አል-ከቢር 1:45:5)

በዚህ የሙሐመድ ንግግር ውስጥ ምንም ስህተት የለም። ድምፅ ከሰማ ዓይኖቹ ብልጭ ካሉበት የሚጥል በሽታ ምልክት ሆኖ ሊመጣ ይችላል። የሙሐመድን አለማበድ ወይንም በሰይጣን አለመያዝ ያረጋገጠችበት በኢብን ይስሐቅ በተጻፈው ሲራ ውስጥ እናገኛለን።

ኸዲጃ ነገረችኝ ብሎ የዙበይር አገልጋይ የነበረው እስማኤል አቡ ሀኪም አንደተረከው ሙሐመድ ጅብሪል ወደእርሱ ሲመጣ እንዲነግራት በማሳሰብ ልክ ጅብሪል ሲመጣ ያሳውቃታል። መገለጡ ከአላህ “እንደሆነ” እና “እንዳልሆነ” ማጣራቷን ትቀጥላለች…

የአጎቴ ልጅ (ሙሐመድ) ሆይ፣ ‘በግራ ጭኔ ተቀመጥ’ አለቻቸው። መልእክተኛውም እንዲሁ አደረጉ፣ እርስዋም  ታየዋለህን?’ ‘አዎ’ አሉ።  ዙርና በቀኝ ጭኔ  ተቀመጥ› አለቻቸው። እንዳለችው አደረጉ፣ እሷም ‘አሁንስ ታየዋለህ?’ አለቻቸው። እሳቸውም  “አዎን” ሲሏት (የእግሯ) እቅፍ ውስጥ እንዲቀመጡ ጠየቀቻቸው። እግሮቿ መካከል ከተቀመጡ በኋላ ዳግመኛ ያዩት እንደሆነ ጠየቀቻቸው። እርሳቸውም “አዎ” ሲሏት የእግሯ እቅፍ ውስጥ እንዳሉ ልብሷን(ቀሚሷን) ገልጣ ወደ ጎን አደረገች ከዚያም ‘ አሁንም ታየለዋለህን?’ አለቻቸው። እሳቸውም መልሰው “አይ” አሏት። እርስዋም የአጎቴ ልጅ ሆይ ደስ ይበልህ! አይዞህ መገለጡ ከአላህ ዘንድ የሆነ መልአክ እንጂ ሰይጣን አይደለም። (Ibn Ishaq, The Life of Muhammad, tr. Guillaume, 1967, p.107 )

እንዲህ ያለ ነገር በአረቦች ባሕል ሊሆን ይችላል እንጂ በክርስትናም ሆነ በስነ-አእምሮ ህክምና ውስጥ ባዕድ ነው።

ሙሐመድ በህመም (መገለጥ) ላይ  በሚሆንበት ሰዓት ሌሎች ተከታዮቹ የሚያደርጉትን በእስልምና መዛግብት የተመለከተ ሰው ምናልባት የኸዲጃ ፈተና ሊራቀቅበት ይችላል። ከንፈርን ያለ ንግግር ማንቀሳቀስ (lip smacking) አንዱ የቴምፖራል ሎብ ኢፒለፕሲ ምልክት ነው። ሙሐመድ በህመሙ ወቅት ከንፈሩን ያለ ንግግር ሲያንቀሳቅስ ተከትለውት እነርሱም እንደእርሱ ያደርጋሉ። እየተገለጠልኝ ነው ብሎ አንገቱን ሲዘቀዝቅ አብረውት አንገታቸውን ይዘቀዝቃሉ። ምናልባት በዚህ የአስተሳሰብ ደረጃ ሙሐመድን ነቢይ ማድረጋቸው ብዙም ሊደንቀን አይገባም። ሙሐመድ አኢሻ አጠገብ ተቀምጦ  አሁን ጅብሪል እያዋራኝ እኮ ነው “አንቺንም ሰላም ብሎሻል”  ሲላት እርሷም “ኦ! ሙሐመድ ታመሀል፣ እውነት ጅብሪል አጠገብህ ሆኜ እኔን ለማውራትና ሰላም ማለት ቢፈልግ እኔን ቀጥታ ነበር የሚያወራኝ ”  ከማለት ይልቅ “አንተ እኮ እኛ የማናየውን ታያለህ” ብላ መልሳለታለች።

የመጀመርያው የአላህ ወሕይ (መገለጥ )

ሁሉን አዋቂ የሆነው አምላክ ለፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ በላከው መገለጥ ላይ “ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው” ብሎ ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ ንግግር ይጀምራል ማለት እርሱን ማንጓጠጥ ነው (ሱራ 96:1-6)። የረጋ ደም ማለት ሙት ስብስበ-ቁስ ሲሆን የሙሐመድ ዘመንን ጨምሮ ለረጅም ጊዜ የሰው ልጅ አንዱ የፅንስ ደረጃ እንደሆነ በተሳሳተ መልኩ ሲታመን ቢኖርም እውነታው ግን የሰው ልጅ ከረጋ ደም አይፈጠርም። በስነፅንስ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራርያ ካፈለጉ እዚህ ጋር ጠቅ ያድርጉ። ከዚህም በመቀጠል የመጡ ንግግሮች ከሰው ተፈጥሮ በላይ ያለ አካል ማለትም የጅብሪል ወይንም የአላህ ናቸው ብሎ ማመን ቀርቶ “የጤነኛ ሰው” ናቸው ብሎ ማሰብ ያስቸግራል። ሙሐመድ ተገለጠልኝ ከማለቱም በላይ የመጀመርያው ወሕይ በማለት ይዞት የመጣው ንግግር የባሰ ጤንነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። በእርግጥ በህመሙ ሰዓት የተፈጠረውን እያንዳንዷን ንግግር በአግባቡ ቃል በቃል አስታወሰው ለማለት ባያስደፍርም ተገለጠልኝ ብሎ ጨማምሮ ያመጣውን ንግግር በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን። አንዱ ኢ-ሳይንሳዊ ነገር እየጠራ ሰው ከዚህ (ከረጋ ደም) በፈጠረው ጌታ ስም አንብብ ያለበት ነው። (ቁ. 1-2) “አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም፡፡ ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)”፡፡ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ አንብብ (ኢቅራእ) ማለቱ እንደቀጠለ ሆኖ “አላህ ቸር እንደሆነ፣ በእስኪብርቶ መጻፍ ያስተማረ፣ እንዲሁም ሁሉን ያስተማረ ሲሆን ሰው ግን ወሰኑን ያልፍበታል” የሚል ንግግር ነው። (ቁ. 3-6) “ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲኾን፡፡ በእውነቱ ሰው ወሰንን ያልፋል፡፡ ራሱን የተብቃቃ (ባለ ሀብት) ኾኖ ለማየቱ፡፡ መመለሻው ወደ ጌታህ ብቻ ነው፡፡”

በመቀጠል የምናገኘው የሱራው ክፍል በአንዳንድ ተፍሲሮች እንደተዘገበው ከመጀመርያው ወሕይ ስድስት ወራት ዘግይቶ የመጣ ነው። በሚቀጥለው ክፍል ላይ ሙሐመድ በአላህ ስም በማሳበብ ቁጣውን የሚያዥጎደጉድበት ሰው አጎቱ ሲሆን “ሲሰግድ አንገቱ ላይ እንደቆመበት፣ እንዲሁም በተደጋጋሚ “የጨረቃው አምላክ” (አል-ላህ) ልጆችን (አል-ላት፣ አል-ኡዛ እና አል-መናትን) መለማመን አትተው” በሚል ጫና እዳደረሰበት የእስልምና መዛግብት ያመላክታሉ። አንድ የሰፈር ጎረምሳ ትንሽ ልጅን ሲያንገላታ አልያ ህፃን ልጅ ሲያባብል የሚጠቀመው ዓይነት ንግግርን ይመስላል። አየህ? ንገረኝ! የሚሉ ቃላትን አስምሮባቸው በተደጋጋሚ ይጠቀምባቸዋል። በመቀጠልም አላህ የሚያስተባብሉትንና ከእምነት የሚሸሹትም እንደሚያይ አያውቁምን ብሎ ይጠይቃል። (ቁ. 7-13) “አየህን? ያንን የሚከለክለውን፡፡ ባሪያን በሰገደ ጊዜ፤ አየህን? ንገረኝ (ተከልካዩ) በትክክለኛ መንገድ ላይ ቢኾን፤ ወይም (ፈጣሪውን) በመፍራት ቢያዝ፤ አየህን? ንገረኝ (ከልካዩ) ቢያስተባብልና (ከእምነት) ቢሸሽ፤ አላህ የሚያይ መኾኑን አያውቅምን?” በቀጣይ የሚመጣው የንግግሩ ክፍል ላይ አናቱን የሚለውን ቃል አስምሮበት ደግሞ ሲጠቅሰው እናያለን። በመቀጠልም በሸንጎ ሰብሰብ ብሎ ከመጣ [ብቻውን አቅቶት?] “እኛም ዘበኞቻችንን እንጠራለን” የሚል ንግግር አለ። አንድ ግለሰብ ለመዋሸት አስቦ ካልሆነ በስተቀር የእውነቱን ይህንን “የአምላክ ንግግር ነው” ካለ የአእምሮ ጤናውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ንግግር ነው። በመጨረሻም “አትፍራው ተወው” የሚመስል ዓይነት ንግግር እናገኛለን። (ቁ. 14-18) “ይተው ባይከለከል አናቱን ይዘን እንጎትተዋለን፡፡ ውሸታም ስሕተተኛ የኾነችውን አናቱን፡፡ ሸንጎውንም #ይጥራ፡፡ (እኛም) ዘበኞቻችንን እንጠራለን፡፡ ይከልከል አትታዘዘው፡፡ ስገድም፤ (ወደ አላህ) ተቃረብም፡፡” ሙሐመድ የለየለት እብደትና ከባድ የስብእና እክል እንዳጋጠመው ከተለያዩ የእስልምና መዛግብ እንደዚሁ እያገላበጥን እንቃኛለን ።

ሌሎች አጋጣሚዎች

ሙሐመድ ላይ በሽታው በድንገት የተከሰተበት ሳይሆን ከህፃንነቱ ጀምሮ እንደሆነ በእስልምና መዛግብት እናገኛለን። እንደ እስልምና መዛግብት ሙሐመድ የተወለደበት የአወላለድ መንገድ ጤናማ የሚባል አይደለም። ፊቱን ወደ ሰማይ አድርጎ መወለዱን የእስልምና መዛግብት ልብ ወለድ የፈጠራ ተአምርን ጣል አድርገው አቅርበዋል። ቢሆንም ትክክለኛ የፅንስ አመጣጥ የጭንቅላቱ የጀርባ ክፍል ወደላይ (OA) መሆን ሲኖርበት የሙሐመድ አወላለድ ግን በተቃራኒው ነው። ይኸውም በመወለድ ወቅት የሚፈጠር አደጋ ተፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው። በዚህ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ይችላል ብሎ ማሰቡ ተገቢ ነው። በዚሁ በተረት በታጀበ ዘገባ ሙሐመድ ሲወለድ የመውደቅ አደጋ ደርሶበት ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ ትረካ አለ https://muslimvillage.com/2020/11/02/60844/prophet-muhammad-s-birth-real/ 

ሙሐመድ የአራት ዓመት ህፃን እያለም ይሄው መገለጥ (ህመም) አጋጥሞት ነበር። ይህ ቢሆንም ኸዲጃም ሆነ ወረቃ ባለመኖራቸው አሳዳጊ እናቱ ሀሊማም ሆነች እሱን የሚያውቁ “አጋንንት ወይንውም የመካ በሽታ” አድርገው በመውሰድ ወላጅ እናቱ ልትጠይቀው ስትመጣ ሀሊማ ውሰጂልኝ ብላ በፍርሀት መልሳዋለች። ሙሐመድ መሬት ወድቆ እንዲህ የሚል ቅዠት (መገለጥ ) እንዳየ ተነግሮናል፦

ሁለት መላእክት ወደ እርሱ መጥተው ደረቱን ከፍተው ጥቁር የረጋ ደም በማውጣት እርሱን ጥለው ልቡን  በወርቅ ትሪ ላይ  አጠቡ። በመቀጠል ከአንድ ሺ ተከታዮቹ ጋር ሲመዝኑት የእርሱ በለጠ። አንደኛውም መልአክ “ተወው ከመላው ኡማው (ተከታዩ) ቢመዘን እንኳ የእርሱ ይመዝናል” አለ።

አብረውት ከሄዱት መካከል  ወንድሙ የሙሐመድን ሁኔታ (ህመም) ካየ በኋላ እያለቀሰ ወደ እናቱ ጋር በመሄድ የቁረይሹ ወንድሜን ተንከባከቢው አላት። እርሷም ከባሏ ጋር በመሆን እየሮጠች ሙሐመድ ጋር ስትደርስ “ግርጥት” ብሎ አገኘችው። (ኢብን ሳድ ኪታብ አል-ጠቃባት አል-ከቢር 1:27:15 )

ይህ ክስተት ሐሊማና ቤተሰቧን እጅግ ከመረበሹ የተነሳ ሙሐመድን ለእናቱ እንደመለሰችው ታሪኩ ይናገራል፡፡ የሐሊማን ስጋት በኢብን ይስሐቅ በተጻፈው ሲራ ውስጥ እንደሚከተለው እናነባለን፡-

“(የሙሐመድ ጓደኛ) አባት እንዲህ አለኝ “ይሄ ልጅ የልብ በሽታ እንዳለበት እሰጋለው፡፡ የከፋ ነገር ሳይከሰት ወደ ወላጆቹ መልሱት” የሙሐመድም እናት ምን እንደተከሰተ እና አጋንንት ይዞት እንደሆን አጥብቃ ጠየቀችኝ፡፡ እረፍትም አልሰጠችኝም፡፡ እኔም በእርግጥ እንደምጠረጥር ነገርኳት፡፡” (ኢብን ኢሳቅ፣ ገጽ 72)

በተመሳሳይ የፍየል ጠባቂ እያለ ፍየሎቹን ለጓደኞቹ በመስጠት የሰርግ ጭፈራ ሲመለከት መገለጡ (ህመሙ) አጋጥሞት ነበር። [al-Raheeq al-Makhtume, The Sealed Nectar, by Sheikh Safi-ur-Rahman al-Mubarkpuri, p. 82 ]  አሁንም ቢሆን ኸዲጃ እና ወረቃ ከጎኑ ስለሌሉ ከህመም በዘለለ እንደ መገለጥ አልተቆጠረም።

ይሄም ብቻ አይደለም እድሜው ወደ 38 ገደማ ሳለ ለካዕባ እድሳት ድንጋይ ሲሸከም በሽታው ራሱን አስቶ ጥሎት ነበር።

ጃቢር ብን አብደላህ እንደተረከው፡- ካዕባ እንደገና በተገነባ ጊዜ ነቢዩና አባስ ድንጋይ ሊሸከሙ ሄዱ። አባስ ነብዩን (ሶ.ዐ.ወ) ድንጋዮቹ እንዳይጎዱህ የወገብህን አንሶላ በአንገትህ ላይ አድርግ። (ግን ከወገቡ አንሶላ እንዳወለቀ) በሁለቱም አይኖቹ ወደ ሰማይ አንጋጦ ራሱን ስቶ መሬት ላይ ወደቀ። ወደ ቀልቡ ሲመለስ  “የወገቤን አንሶላ! የወገቤን አንሶላ!” አለ። ከዚያም የወገቡን አንሶላ (በወገቡ ዙሪያ) አሰረ። (አል-ቡኻሪ፣ 3829)

ይህንን አጋጣሚ ኢብን አባስ ሲገልፀው ነቢዩ “ያበዱ መስሎኝ ነበር” ብሎ ነው።  ሙሐመድ ሌሎች ሰዎች የማይሰሙትን ድምፅ ይሰማ ነበር። በተመሳሳይ የዚህ ህመም ተጠቂዎች የማይሰማ ድምፅ እንደሰሙ (auditory hallucination) የማይታይ አካል እንዳዩ (visual hallucination) አድርገው ያስባሉ። ይሄ መገለጥ ሳይሆን የ ህመሙ (TLE) ክፍል ነው።

ሙሐመድ የወደቀባቸውን ሌሎች ብዙ አጋጣሚዎች ከእስላማዊ ምንጮች ውስጥ መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በአንድ አጋጣሚ ከፈረስ ላይ ወድቆ ጉዳት አጋጥሞት እንደነበር ተነግሯል (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅጽ 1፣ መጽሐፍ 12፣ ሐዲስ ቁጥር 699)። እነዚህ አጋጣሚዎች የሚጥል በሽታ ውጤት ተደርገው በእስላማዊ ምንጮች ውስጥ ባይጠቀሱም በተደጋጋሚ ከመውደቁ አንጻር የዚያው ችግር ውጤት ሊሆኑ እንደሚችሉ ብንገምት ከእውነት የራቅን አንሆንም።

የሙስሊም መምህራን ምላሽ

የሙስሊም መምህራን በዚህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በማናቸውም ጉዳይ ለምላሽ ይፈጥናሉ። በሁሉም ጉዳዮች የሚያቀርቡት ምላሽ ተደማጩን ወቅታዊ ሆይ ሆይታ ያማከለ እንጂ ቋሚ  ምላሽ አይደለም። የእስልምና ሀይማኖት ሰባክያን ስለሚጥል በሽታ (TLE) ምንም ግንዛቤው ሳይኖራቸው እንደ ወትሮ ሲተነትኑ የሙስሊም የስነ-አእምሮ ሀኪሞች  እንኳ ይታዘቡናል ብለው አይጠብቁም።

በዚህ ጉዳይ መጠነኛ ዕውቀት ያላቸው በህመምተኞቻቸው የሚያውቁት ስለሆነ እንደ ሰባክያኑ ሽምጥጥ አያደርጉም። ነገር ግን የሙሐመድ ጉዳይ በተለየ መነፅር እንዲታይላቸው እንዲሁም የሚጥል በሽታ አለበት ብሎ እርግጠኛ ለመሆን ተጨማሪ  ምርመራዎች ማድረግ ያስፈልጋል በሚል  ጥረት ያደርጋሉ። የሙሐመድ ታሪክ በተለየ መልኩ ለምን እንደሚታይ ከአማኙ በቀር ለሌላው ግራ ነው። ሙሐመድ የዚህን ህመም ምልክቶች አንድ በአንድ ካሳየ የአላህ መልእክተኛ በመሆኑ አላህ ስለሚጠብቀው በሽታው አይኖርበትም ማለት ከሰባክያኑ የባሰ ጭፍንነት ነው። ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛነት ሹመት ያገኘው በህመሙ ምክንያት በመሆኑ ጥረታቸው ብዙም መንገድ አያስኬድም። በእርግጥ አንድ ሁለት ሰዎች ባቀረቡት ሀተታ መሠረት አንድን ሰው ይህ በሽታ አለበት ብሎ እርግጠኛ በመሆን  ወደ ህክምናው ለመግባት EEG እና MRI ምርመራዎች ማድረግ አለበት። ነገር ግን ይሄንን ጥያቄ የሚያነሱ ሙስሊም ወገኖች “ሙሐመድ መትረፍ አለበት” በሚል ጨለምተኛ ፍላጎት ብቻ ነው። ሙሐመድ በዚህ በሽታ እንደተጠቃ ጅብሪል የሚባለውን የሙሐመድ አእምሮ የፈጠረው ሊሆን እንደሚችል ከታሪኩ ተነስተን መገንዘብ እንችላለን። ነገር ግን “ሌሎች የሕመሙ ተጠቂዎች የሚያሳዩትን ምልክቶች ሙሐመድ በተመሳሳይ ማሳየቱ ከህመሙ ጋር ዝምድና የለውም፣ ሙሐመድን ከሌሎች ታማሚዎች በተለየ መነፅር እንየው፣ ለሙሐመድ የተገለጠለት ጅብሪል ነው” በሚል ዘላለሙን ሊሰዋ ዝግጁ ከሆነው ሕዝበ-ሙስሊም ዘንድ ማጣራት የሚጠበቅ ነው።  ሙሐመድ በሽታው ኖረበትም አልኖረበትም እኛ የምናጣው ነገር የለንም። ስለዚህ እኛ እንድናደርግ የሚጠይቁንን እራሳቸው ማለትም  ሙሐመድን በአካል አግኝተው “የEEG ፣ የMRI” ምርመራዎችን ማድረግ የሚጠበቀው ከእነርሱ ነው።

ሌላው እነዚሁ በሙሐመድ ፍቅር የታወሩ  ሰዎች  የሚጠቀሙት መንገድ  ተአምራቶቹን ማብዛትና በአጠገቡ ያሉ ሰዎች ክስተቱን እንዳዩ መናገር ነው። ሙሐመድ በቁርአን ላይ አንዲትም ተአምር እንዳላደረገ ሲናገር “ዲንጋይ ሲያወራ አየ፣ ጨረቃን ከፈለ፣ ዛፍ ላይ ጥምጥም ብሎ ከዛፍ ጋር ተነጋገረ” ወዘተ. ከሚሉ ሙሐመድ ከሞተ ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ የተዘገቡት ሐዲሳት ጋር ማስታረቅ ይጠበቅባቸዋል። ሐዲሳቱ ፅንፍ ይዘው ስለሚተርኩ ፍፁም ተዓማኒ አይደሉም። ነገር ግን መገለጥ ናቸው ብለው የሚያቀርቧቸው ምልክቶች ሙሉ በሙሉ የቴምፖራል ሎብ ኤፒለፕሲ (TLE) ምልክቶች ሆነው እናገኛቸዋለን።

የመጨረሻ ሙሐመድን ማስመለጫ መንገዳቸው ደግሞ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ስለሚጥል በሽታ በቂ ዕውቀት ስላላቸው “ህመሙን መገለጥ” ብለው እንደማይሸወዱ ለማሳመን ጥረት ማድረግ ነው። ይህንን ለማስረገጥ የሚጠቅሱት ሐዲስ ደግሞ ሙሐመድ ጋር መጥታ እንዲፀልይላት የጠየቀችውን ጥቁር ሴት ነው።  በሚያሳዝን መልኩ ለማጭበርበር  ፈልገው ካልሆነ የሙሐመድና የሴትየዋ ምልልስ እነሱን የሚደግፋቸው ሳይሆን ሙሐመድ የሚጥል በሽታ አለበት የሚሉትን ሰዎች ነው። በሚጠቅሱት ሐዲስ ላይ  ሙሐመድን “ፈውሰኝ” ብላ የመጣችው ሴት ከሚጥል በሽታዋ ጋር ከኖረች “ገነት እንደምትገባ” የሚጥል በሽታዋ ከተፈወሰላት ደግሞ “እርሱ እንደሚቀርባት” ነግሯታል። (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅጽ 7፣ መጽሐፍ 70፣ ሐዲስ 555)

ወደ ክፍል ሦስት ከማለፋችን በፊት ለሙስሊም አንባብያን የምለው አለኝ። እስከዚህ ድረስ በትዕግስት ማንበባችሁን እጅግ አደንቃለሁ። ምናልባት ከእስልምና ለመውጣት “ደረጃ አንድ” ላይ እንደምትሆኑ አስባለው። ስለ እስልምና ለመረዳት በመወሰን በእስልምና ላይ ሂስ የሚያቀርቡ ጽሑፎችን በተረጋጋ ሁኔታ ማንበብ እስልምናን የመልቀቅ ደረጃ አንድ መሆኑን ከእስልምና የወጡ  ሰዎች ይናገራሉ። እናንተስ ምን ታስባላችሁ? እስከመች ለድንግዝግዝ ነገር ዘላለማዊ ሕይወታችሁን ትሰዋላችሁ? የሕይወት ብርሃን ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ ትመጡ ዘንድ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ።

ይቀጥላል… 


 

ሙሐመድ