ሙሐመድ ከአራት ሚስቶች በላይ ማግባቱ የቁርኣን ሕግ ጥሰት አይደለምን? ለሙስሊም ሰባኪያን ምላሽ

ሙሐመድ ከአራት ሚስቶች በላይ ማግባቱ የቁርኣን ሕግ ጥሰት አይደለምን? ለሙስሊም ሰባኪያን ምላሽ

በወንድም ትንሣኤ

ሙስሊሞች እንደሚሉን ቁርኣን ከአራት ሚስት በላይ ማግባት ከከለከለ ነቢያቸው ሙሐመድ በአንዳንድ ዘገባዎች መሰረት ዘጠኝ፣ በሌሎች አስራ አንድ፣ በሌሎች አስራ ሦስት በሌሎች ዘገባዎች ደግሞ አስራ አምስት ሚስቶችን ማግባቱ ወረደልኝ ያለው መገለጥ ላይ የፈጸመው ግልጽ ጥሰት መሆኑ አይካድም።[1] ሙስሊሞች ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡን መልስ ከአራት በላይ ማግባት የሚከለክለው ህግ (ሱራ 4:3) ነቢዩ ዘጠኝ አግብተው ከጨረሱ በኋላ የወረደ ነው የሚል ማስረጃ ቢስና በማስከተል እንደምናየው ከምንጮቻቸው ጋር የማይስማማ ሀሳብ ነው።

እንደ ሰይድ ቁጥብ ያሉ ሙስሊም ምሑራን እንደሚሉት ሱራ አል-ኒሳእ የወረደው ከሦስተኛው ዓመተ ሂጅራ ጀምሮ ነው።[2] ከአራት ሚስት በላይ ማግባትን የሚከለክለው ትዕዛዝ (ሦስተኛው አያህ) የወረደው ደግሞ በሦስተኛው አመተ ሂጅራ ሙሐመድ ከቁሬይሾች ጋር ዑሁድ ላይ ካደረገው ጦርነት (625 A.D/3 A.H) በኋላ ነው።[3][4] በዚህ ትርጉም መሠረት ይህ የቁርኣን ክፍል ብዙ ሙስሊሞች ዑሁድ ላይ ስለሞቱ ወላጅ አልባ ሴቶችና ህጻናት ላይ በደል እንዳይፈጸም የወረደ ነበር። እንደ ቴዎዶር ኖልዴኬ ያሉ በቁርኣን ክሮኖሎጂ ላይ ብዙ ጥናት ያደረጉ ምሁራንም በዚህ ይስማማሉ።[5]

ታዲያ ኢማሙ አልጠበሪና ኢብን ሰአድን የመሰሉ ሙስሊም ሊቃውንት እንደሚዘግቡት ሙሐመድ አምስተኛ (በጊዜው በሕይወት ያልነበረችው ከድጃ ሳትቆጠር አራተኛዋ) ሚስቱን ኡም ሳላማን እንኳን ያገባው በሦስተኛው (624AD) ወይም በአራተኛው ዓመተ ሂጅራ (626 A.D.) ነበር።[6][7]

ስለዚህ ሙሐመድ ከአራት በላይ ማግባትን የሚከለክለው መገለጥ በወረደበት ሰዓት ሳውዳ ቢንት ዛማህ፣ አይሻ ቢንት አቡበከርና ሐፍሷ ቢንት ኡማርን ጨምሮ ሦስት ወይም አራት ሚስቶች ብቻ ነበሩት ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ነው የሙስሊሞች ነቢይ የራሱን ትዕዛዝ በመተላለፍ ሰባት ተጨማሪ ሚስቶችን አከታትሎ ያገባው። አልጠበሪ የዘገበውን ብቻ ከወሰድን እንኳን ሙሐመድ በአራት ሚስት ተገደቡ ብሎ መስበክ ከጀመረበት ጊዜ በኋላ (3 A.H.) አራቱ ሚስቶቹ በሕይወት እያሉ ከሰባት በላይ ሴቶችን አግብቷል።[8] የዘመኑ ሙስሊም ምሁራን ግን ምንጮቻቸውን ጠንቅቀው እያወቁ “አራት ብቻ አግቡ የሚለው መገለጥ ሲወርድ ሙሐመድ ዘጠኝ ሚስቶች ነበሩት” ብለው ለመዋሸት ዓይናቸውን አላሹም።

እነዚህ ሙስሊም ሰባኪያን እንደሚሉት ይህ ግልጽ የትዕዛዝ ጥሰት ከሙሐመድ ሥጋዊ ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን ክልከላው በጊዜው ስላልነበረ የተፈጸመ ስህተት ቢሆን እንኳን ከትዕዛዙ መውረድ በኋላ ሙሐመድ ሌሎቹን ሚስቶቹን ፈትቶ አራት እንዲያገባ እርሱ ራሱ ያስቀመጠው እስላማዊ ሕግ ያስገድደዋል።

ኢብን ዐባስ ለምሳሌ ሱራ 4:3ን ሲያብራራ እንዲህ ይላል፦

“(ይህ ትዕዛዝ የወረደው)…ወንዶቹ እስከ ዘጠኝና አስር ድረስ የፈለጉትን ሚስት ያህል ያገቡ ስለነበር ነው። ቃይስ ኢብን አል-ሃርት ለምሳሌ ስምንት ሚስቶች ነበሩት ፤ አላህ ግን ሁለትም ሶስትም አራትም አግቡ በማለት ከአራት በላይ ሚስቶች ከማግባት ከለከላቸው።”[9]

ኢብን ከሢር በተመሳሳይ አት-ቲርሚዚና ኢማም አሕመድ የዘገቡትን ሐዲስ ጠቅሶ እንዲህ ይላል-

“ጋሊን ቢን ሳላማህ እስልምናን ሲቀበል አስር ሚስቶች ነበሩት። ነቢዩም ‘አራቱን ያዝና ሌሎቹን ፍታ’ አሉት።”[10][11][12]

አሽ’ሻፊ ደግሞ ነውፋል ኢብን ሙኣዊያን ጠቅሶ እንዲህ ይላል፦

“ሙስሊም ስሆን አምስት ሚስቶች ነበሩኝ ፤ ነቢዩም አራቱን ያዝና ሌላዋን ፍታ አሉኝ።”[13]

እንግዲህ በነዚህና ሌሎች መሰል ሐዲሶች መሠረት ይህ መገለጥ ከወረደ በኋላ ከአራት በላይ ሚስት ያሏቸው ሰዎች አራቱን አስቀርተው የተቀሩትን እንዲፈቱ የግድ ይባሉ ነበር። ታዲያ ሙሐመድ ዘጠኝ ሚስት ያገባው የአራት ሚስት ገደብ በጊዜው ስላልነበረ ከሆነ መገለጡ ከተሰጠው በኋላ በተመሳሳይ አምስቱን ሚስቶች ፈትቶ በአራት ከመገደብ ምን ከለከለው? ይህ ተግባር ሙሐመድ የቁርኣንን ሕግ በሚገባ እንደሚያከብር በማሳየት ለሙስሊሙ ሕዝብ የተሻለ አርአያ ሊያደርገው የሚችል አልነበረምን?

ለዚህ ጥያቄ ሙስሊሞች የሚሰጡት የመጨረሻው መልስ ‘አላህ በቁርኣን ነቢዩ የፈለገውን ያህል እንዲያገባ ፈቅዶለታል’ የሚል ነው። ቁርኣን መለኮታዊ ግልጠት እንደሆነ የማያምን ሰው ያነሳውን ጥያቄ ቁርኣን መለኮታዊ ነው የሚል ቅድመ ግምት (Presumption) ወስዶ ለመመለስ መሞከር መሠረታዊ የአመክንዮን ሕግ ያልጠበቀ እንደሆነ ግልጽ ቢሆንም ቁርኣን የሙሐመድ ፈጠራ ሳይሆን መለኮታዊ መገለጥ ነው ብለን ብንነሳ እንኳን ይህ የመጨረሻ አማራጭ የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ የሚበቃ አይደለም።

ሙስሊሞች እንደሚሉት ከሆነ ሙሐመድ የፈለገውን ያህል ሚስት እንዲያገባ ፍቃድ የተሰጠው በሱረቱል አህዛብ 33:50 ላይ ነው። ይህ የቁርኣን ክፍል ግን የወረደው ሙሐመድ የአራት ሚስት ገደብን ጥሶ ከጨረሰ በኋላ እንደሆነ በቂ ማስረጃ አለን።

ፕሮፌሰር ሰይድ ሁሴን ናስር ባዘጋጁት ሰፊ የቁርኣን ትንታኔ መጽሐፋቸው እንደሚሉት ይህ ሱራ የወረደው የመካ ቁሬይሾችና ባኑ ቁራይዟ የተባሉት የአይሁድ ጎሳዎች ሙሐመድ ላይ በማበር መዲናን የከበቡበት ጦርነት ከተፈጸመ (5A.H./627A.D.) በኋላ ነው።[14] እንዲያውም እኒህ ምሑር እንደሚሉን ከሆነ በ 33:50 ላይ “እጅህ የጨበጣቸውን ምርኮኞች…” ተብለው የተጠቀሱት ሳፊያ ቢንት ሁያይ እና ጁዋሪያህ ቢንት ሃሪሣ የተባሉት ሙሐመድ ከጦርነት ምርኮ ያገኛቸው ሚስቶቹ ናቸው።[15]

ይህ ከሆነ ደግሞ ሙሐመድ ጁዋሪያን በ 6 A.H. (628 A.D.) ሳፊያን ደግሞ በ 7 A.H. (629 A.D.) እንዳገባት ከኢብን ኢሳቅ ዘገባዎች መረዳት ስለምንችል ሱራ 33:50 ከዚያ በፊት ሊወርድ እንደማይችል ግልጽ ነው።[16][17]

እንግዲህ ችግሩ እዚህ ጋር ነው። ሙሐመድ በአራተኛው ዓመተ ሒጅራ (626 A.D.) እንኳን በረመዳን ወር ላይ ዘይነብ ቢንት ኩዛይማህ የተባለች እንስት አግብቶ የሚስቶቹን ብዛት ወደ አምስት አሳድጎ ነበር።[18] ነቢዩ የፈለገውን ያህል እንዲያገባ የሚፈቅድለት አያህ ከ 627A.D. ወይም 629 A.D. በፊት ሊወርድ እንደማይችል እርግጥ ስለሆነ ሙሐመድ የአራት ሚስት ገደብን የተላለፈው በአላህ ፍቃድ ሊሆን አይችልም ማለት ነው። ይልቅ ከዚህ የምንረዳው ሙሐመድ ሌሎቹን ሙስሊሞች በአራት ሚስት እንዲገደቡ አዝዞ ሲያበቃ የራሱን ትዕዛዝ ከሥጋዊ ፍላጎቱ ጋር ማስማማት ተስኖት የገዛ መጽሐፉ ላይ ትልቅ መተላለፍ እንደፈጸመ ነው። ሙስሊም ወገኖች ለዚህ ከነቢይ ለማይጠበቅ የዘቀጠ ሥጋዊ ባሕርይ ሌላ ትርጉም ለመስጠት መሞከር አቁመው ትክክለኛውን የሙሐመድን ገጽታ ይመለከቱ ዘንድ እንመኛለን። እግዚአብሔር አምላክ የልብ ዓይኖቻቸውን በማብራት ንጹህና ቅዱስ ወደሆነው ወደ ልጁ መንግሥት ይመራቸው ዘንድ የዘወትር ጸሎታችን ነው።


[1] The History of Al-Tabari, volume 9, p.126.

[2] Sayyid Qutb. (2002). In the shade of the Quran. Vol 3 p.1. Kube publishing.

[3] Neal Robinson. (1996). Discovering the Quran: a Contemporary Approach to a Veiled text. p.80. SCM Press LTD.

[4]https://web.archive.org/web/20160423001304/http://www.commongroundnews.org/article.php?id=27379&lan=en&sp=0  . Retrieved December 2021.

[5] Noldeke and Schwally. (1860). Geschichte des Qorans. volume 1, pp.74-234. Olms publishers.

[6] The History of Al-tabari, Volume 9, p.132.

[7] Ibid.

[8] Ibid. pp.133-139.

[9] Tafsir Ibn Abbas, p.99.

[10] Tafsir Ibn-kathir 4:3.

[11] Muwatta Malik, Book 29, Hadith 76.

[12] Sunan Abi-Dawud, 2241.

[13] Sayyid Qutb. (2002). In the Shade of the Quran. Vol 3 p.26. Kube publishing.

[14] Seyyed Hossein Nasr. (2017). The Study Quran: a New Translation and Commentary. p.1865. Harper one publishers.

[15] Ibid., p.1897.

[16] Ibn Ishaq, Sirat Rasulullah. p.493.

[17] Ibid., p.516.

[18] The History of Al-tabari volume 7, p.150.


ሙሐመድ