እውን ሙሐመድ መርዝ በልቶ አልሞተምን? አላህ የልቡን ሥር ቆርጦ አልገደለውምን?

እውን ሙሐመድ መርዝ በልቶ አልሞተምን? አላህ የልቡን ሥር ቆርጦ አልገደለውምን?

ሙሐመድ መርዝ በልቶ መሞቱን በተመለከተ ለቀረበው ሙግት አንድ ሙስሊም ወገናችን “መልስ” ብሎ በሁለት ክፍል ያቀረበው የድምፅ መልእክት ደርሶኝ የማድመጥ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ ይህ “መልስ” እንደ ሌሎቹ እስላማዊ ሙግቶች ሁሉ በአመክንዮአዊ ተፋልሶዎችና ስሁት መረዳቶች የታጀበ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

እኔ ያቀረብኩትን ሙግት ለማስታወስ ያህል፡-

ሙሐመድ ሐሰተኛ ነገር በአላህ ስም የሚናገር ከሆነ አላህ የልቡን ስር በመቁረጥ እንደሚገድለው በቁርኣን ውስጥ ተጽፏል፡፡ ሙሐመድ በሞቱ አልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ በኸይበር ዘመቻ ወቅት አንዲት አይሁዳዊት ሴት ባበላችው መርዝ ምክንያት የልቡ ስር መቆረጡ እንደተሰማው እስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ ተጽፏል፤ ስለዚህ የዚህ ድምዳሜ ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ ነው የሚል ነው፡፡

ሙስሊሙ ወገናችን ለዚህ ሙግት የሰጠውን ምላሽ ነጥብ በነጥብ እንመለከታለን፡፡

  1. በመጀመርያ ይህ ወገናችን ሙሐመድ በመርዝ ሞቶ የነበረ ቢሆን አንኳ ነቢያት በሰዎች መገደላቸው አዲስ ነገር ባለመሆኑ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን እንደማያረጋግጥ ይሟገታል፡፡ ዳሩ ግን ነቢያት በሰው እጅ መሞታቸው ሐሰተኛ ነቢያት ያደርጋቸዋል የሚል ሙግት ስላልቀረበና ሙሐመድ በዚህ ሚዛን ስላልተመዘነ ይህ ምላሽ እኛ ካቀረብነው ሙግት ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ይህ በስነ አመክንዮ ሕግ Straw man fallacy ይሰኛል፡፡ ተፋላሚያችሁ ያላቀረበውን ደካማ ሙግት እርሱ ያቀረበው አስመስሎ በማቅረብ ማፈራረስ እንደማለት ነው፡፡ የኛ ሙግት ሙሐመድ በሰው እጅ መገደሉ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን ያረጋግጣል የሚል አይደለም፡፡
  2. ሁለተኛው የሰጠው ምላሽ ያቺ አይሁዳዊት ሴት መርዙን ለሙሐመድ ትክክለኛ ነቢይነት እንደ መፈተኛ ብታቀርብም አለመሞቱ ትክክለኛ ነቢይነቱን ያሳያል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ መርዙን ከበላ በኋላ ቢዘገይም በመርዙ ምክንያት በመሞቱ ፈተናውን ወድቋል፡፡ ዳሩ ግን ሴቲቱ እንደ ምልክት ወይንም ፈተና ያስቀመጠችው የሙሐመድን ሞት ብቻ ሳይን በመርዙ ምክንያት የሚመጣውን ማንኛውንም ጉዳት እንደነበር እስላማዊ ትውፊቶች ይናገራሉ፡- They replied, “We intended to learn if you were a liar in which case we would be relieved from you, and if you were a prophet then it would NOT HARM YOU.” (Sahih al-Bukhari, Volume 7, Book 71, Number 669) “ነቢይ ከሆንክ መርዙ አይጎዳህም” ነው ያለችው፤ ስለዚህ እየበላ ሳለ እንኳ የመርዙ ጉዳት አፉ አካባቢ ታይቶ ነበር፤ ከዚያ በኋላም መርዙ ለሕመም ዳርጎታል፤ በመጨረሻም ገድሎታል፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ ፈተናውን የወደቀው ገና እየበላ ሳለ ነበር፡፡
  3. ሙስሊሙ ወገናችን ሙሐመድ በጭራሽ በመርዙ ምክንያት አልሞተም ብሎ ይክዳል፡፡ ለሞት ሲቀርብ በመርዙ ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት የተነሳ እንደሆነ የተናገረው ራሱ ሙሐመድ በመሆኑ ሙሐመድ ውሸታም ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ማንን እንመን? ሙስሊሙን ወገናችንን ወይንስ ሙሐመድንና በዙርያው የነበሩ የዐይን ምስክሮችን? ሙሐመድ በመርዙ ምክንያት መሞቱን እስላማዊ ምንጮች የተናገሩትን ተቀብሎ እንደ ማብራራት “በጭራሽ በመርዙ ምክንያት አልሞተም” ብሎ መካድ ሙሐመድን ውሸታም ማድረግ ነው፡፡ የእስላማዊ ምንጮችን ተዓማኒነትም መቀመቅ መክተት ነው፡፡

ሙስሊሙ ወገናችን ይህንን ክስተት ለሙሐመድ ነቢይነት ማረጋገጫ አድርጎ ለመጥቀስ ይሞክራል፡-

  1. በኦዲዮው ውስጥ እንደተናገረው ሙሐመድ መርዙን ከበላ ከ4 ዓመት በኋላ ነበር የሞተው፡፡ ነገር ግን እስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ እንደተዘገበው በ3 ዓመት ውስጥ ነበር የሞተው ፡፡
  2. ይሁንና ተናጋሪው ሙሐመድ በመርዙ ወዲያው አለመሞቱን በመርዙ ላለመጎዳቱ እንደ ማረጋገጫ ያቀርባል፡፡ “የትኛውም መርዝ ወዲያው ደምስርን በጣጥሶ ይገድላል” በማለት ከእውነት የራቀ ነገርንም ይናገራል፡፡ ከግምት ውስጥ ያላስገባው ነገር ቢኖር የመርዝ ገዳይነትም ሆነ ጉዳት እንደየሰውና እንደየሁኔታው እንደሚለያይ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ጥሩ ጤንነትና ጠንካራ አካላዊ ብቃት ካለው በንጽጽር ከሌላው ሰው በተሻለ የመርዝን ቅጽበታዊ ውጤት የመቋቋም አቅም ይኖረዋል፡፡ ወደ ሰውነት የገባው የመርዝ መጠንም የጉዳቱን መጠን ሊጨምር ወይንም ሊቀንስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ ቶሎ አለመሞቱ ቅጽበታዊውን የመርዙን ጉዳት መቋቋሙን እንጂ በረጅም ጊዜ ሒደት በመርዙ አለመጎዳቱን አያመለክትም፡፡ ይህንን መካድ እስላማዊ ሐዲሳትን ማስዋሸት ነው፡፡
  3. ሙሐመድ መልእክቱን ሳይጨርስ ወዲውኑ አለመሞቱ በአላህ ዕቅድ መኖሩንና መሞቱን እንደሚያሳይ ከተናገረ በኋላ እስልምና ትክክለኛ ሃይማኖት ለመሆኑ ማሳያ ነው ይላል፡፡ ነገር ግን፡-
    1. ሙሐመድ መትረፉ መርዙን አብዝቶ ባለመብላቱ ወይንም አካላዊ ብቃቱ ከመርዙ እንዲተርፍ ስለረዳው እንደተረፈ እንጂ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ ስለመትረፉ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ የለም፡፡ ብዙ ሰዎች በጋራ ሆነው የተመረዘ ምግብ በልተው አንዳንዶች ይሞታሉ አንዳንዶች ደግሞ ይተርፋሉ፡፡ ይህ በዘመናችንም ቢሆን የምናየው ነገር በመሆኑ ተዓምራዊ ክስተት ማስመሰል ኢ-አመክንዮአዊ ነው፡፡ የሙሐመድ ከዚህ የተለየ ስለመሆኑ ማስረጃ የለም፡፡ እንዲያውም ያሉን ማስረጃዎች ተቃራኒውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ከሙሐመድ ጋር የበሉ ብዙ ሰዎች እንደነበሩ በአልጠበሪ ታሪክ የተዘገበ ቢሆንም ወዲያውኑ እንደሞተ የተዘገበው ግን ቢሽር የተሰኘው ሰው ብቻ ነበር፡፡ በተጨማሪም ቢሽር አስቀድሞ እንደበላና ሙሐመድ አንዷን አጥንት ሲጀምር እርሱ ሁለተኛውን ጀምሮ እንደነበር ተጽፏል፤ ስለዚህ ወደ ቢሽር ሰውነት የገባው መርዝ መጠን ብዙ በመሆኑ የሞተ ሲሆን ወደ ሙሐመድ ሰውነት የገባው ግን ጥቂት በመሆኑ ለጊዜው ተርፏል፤ ኋላ ላይም ከመርዙ ባተረፈው ህመም ምክንያት ሞቷል፡፡ The Apostle of Allah, may Allah bless him, lived after this three years till in consequence of his pain he passed away.During his illness he used to say: I did not cease to find the effect of the (poisoned) morsel, I took at Khaybar and I suffered several times (from its effect) but now I feel the hour has come of the cutting of my jugular vein, which is a vein in the back… (Ibn Sa’ad’s Kitab Al-Tabaqat Al-Kabir Volume II, pp. 251-252)
    2. የኛ ሙግት ሙሐመድ በመርዙ ወዲያውኑ መሞት አለመሞቱ ሳይሆን የልቡ ስር እንደተቆረጠ እንደተሰማው መናገሩ ነው፡፡ ሙግታችን በጭራሽ በሙሐመድ በመርዝ መሞት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ወዲያውኑ አለመሞቱ ነቢይ አለመሆኑን አያሳይም፤ ዘግይቶ መሞቱም ነቢይ መሆኑን አያሳይም፡፡ ወዲያውኑ መሞቱ ወይንም አለመሞቱ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ነገር ግን ሊሞት ሲቃረብ የተናገረው ነገር በቁርኣን ውስጥ ከሚገኝ ሌላ ጥቅስ ጋር ሲስተያይ የሚሰጠን ትርጉም ነቢይነቱን አንድንጠራጠር ያደርገናል፡፡
    3. የሙሐመድ ሞት ብዙ ክፍተቶችን ያስከተለ እንደነበር የሚያሳዩ ብዙ ነገሮች በመኖራቸው ምክንያት “እስልምና ከተሟላ በኋላ ነው የሞተው” የሚል ሙግት ውድቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-
      1. ሙሐመድ ተተኪው ማን መሆን እንዳለበትና ከእርሱ በኋላ የሚኖሩት ሙስሊሞች ምን ዓይነት አስተዳደር መከተል እንደሚገባቸው ያስተላለፈው ትዕዛዝ ባለመኖሩ በኸሊፋዎች መተካካት ላይ ሙስሊሞች ትልቅ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ዑመር ተገደለ፣ ኡሥማን ተገደለ፣ ዐሊ ተገደለ፣ የዐሊ ልጅ የሙሐመድ ልጅልጅ ሁሴን ተገደለ፤ እስልምናም እስከ ዛሬ ድረስ ሱኒና ሺኣ ተብሎ ለሁለት ተከፈለ፡፡ የሙሐመድ ሚስት አይሻም የራሷን ፍላጎት ለማስፈፀም ጦር እያዘመተች ስትበጠብጥ ነበር፡፡
      2. ሙሐመድ ቁርኣንን ሳያጠናቅቅ በመሞቱ ምክንያት ሙስሊሞች ከእርሱ ህልፈት ከክፍለ ዘመናት በኋላ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ በመግባታቸው ሳብያ የሐዲስ መጻሕፍት እንዲሰበሰቡ ተደርጓል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በቁርኣን ውስጥ ያልተጻፉ ወሳኝ የሆኑ ትዕዛዛት በመኖራቸው ምክንያት ነው፡፡ ቁርኣን ለአንድ ሙስሊም በቂና የተሟላ መመርያን አይሰጥም፡፡
  • በቁርኣን አሰባሰብ ዙርያ ሙሐመድ የሰጠው መመርያ ባለመኖሩ በቁርኣን ቅጂዎችና ትክክለኛ ስብስቦች ዙርያ ሙስሊሞች ከፍተኛ የሆነ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም የተለያዩ የአረብኛ ቁርአኖች በዓለም ላይ እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

ስለዚህ ሙሐመድ ሃይማኖቱን ከሟላ በኋላ ነው የሞተው የሚለው አያስኬድም፤ ብዙ የጎደሉ ነገሮች ነበሩ፤ ባለመሟላታቸውም የሙስሊሙ ዓለም ውዝግብና ለክፍፍል ተዳርጓል፤ የሙሐመድ ሞት ድንገተኛ ስለነበር ብዙ ክፍተት በሃይማኖቱ ውስጥ ታይቷል፡፡

  1. ሙሐመድ መርዙን ከበላ በኋላ ጠንካራ እንደነበርና ፆምም ሲፆም እንደነበር እንደ ማስረጃ በማቅረብ መርዙ አልጎዳውም ይለናል፡፡ ሆኖም ስለ አሟሟቱ በተነገረው ሐዲስ ላይ በየጊዜው የሚነሳበት አደገኛ ህመም እንደነበረበት ተነግሮናል (Sahih al-Bukhari, Volume 5, Book 59, Number 723)፡፡ ከመርዙ በኋላ ሙሐመድ አንዴ ሲታመም አንዴ ሲሻለው ነበር በመጨረሻ ይህችን ዓለም በሞት የተሰናበተው፡፡ እንዲያውም አይሻ ስለ አሟሟቱ ስትናገር የሰው ልጅ እንዲህ ሲሠቃይ አይታ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡ ሙስሊም ጂሃዳውያን ሰዎችን እንደ በግ ሲያርዱ እያየች የኖረችው አይሻ የሙሐመድ ሥቃይ ግን ዓይታ ከምታውቀው ከየትኛውም ሥቃይ ጋር እንደማይነፃፀር ትነግረናለች (Sunan Ibn Majah 1622፡፡ በዚህ ኦዲዮ ምላሽ የሰጠው ሰው የእስልምናን ፆም ከፆም ቆጥሮ ለሙሐመድ ጥንካሬ እንደ ማስረጃ ማቅረቡ አስገራሚ ነው፡፡ የእስልምና ፆም የምግብ ሰዓትን ከቀን ወደ ሌሊት ማዛወር እንጂ ፆም አይባልም፡፡ ሙስሊሞች ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ የተመረጡ ምግቦችን የሚመገቡት በፆማቸው ወቅት ነው፡፡ በሙስሊሞች ፆም ጊዜ በተለይ ሙስሊሞች በሚበዙበት አካባቢ የምግብ ዋጋ ይወደዳል፤ አብዛኞቹም ሙስሊሞች ኪሏቸው ይጨምራል፡፡ ይህቺ እንኳን ከማስረጃ የምትቆጠር አይደለችም፡፡

በሁለተኛው ኦዲዮ ላይ ይህ ሙስሊም አፖሎጂስት በቁርኣን ውስጥ አላህ ሙሐመድ በእርሱ ላይ የሚዋሽ ከሆነ የልቡን ስር በመቁረጥ እንደሚገድለው ተናግሯል የተባለውንና በሐዲስ መሠረት ሙሐመድ ሊሞት ሲል “የልቤ ስር እንደተቆረጠ ይሰማኛል” ብሎ የተናገረውን ግጥምጥሞሽ ለማብራራት ይሞክራል፡፡ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፡-

“በኛ ላይም ከፊልን ቃላት (ያላልነውን) በቀጠፈ ኖሮ፤ በኅይል በያዝነው ነበር። ከዚያም ከርሱ የልቡን ስር (የተንጠለጠለበትን ጂማት) በቆረጥን ነበር። ከእናንተም ውስጥ ከርሱ ላይ ከልካዮች ምንም አይኖሩም።” (69፡44-47)

ሙሐመድ ሊሞት ሲል ምን አለ?፡-

“የቢሽር እናት ሆይ፥ በኸይበር ከልጅሽ ጋር ከበላሁት ምግብ የተነሳ የልቤ ስር እንደተቆረጠ ይሰማኛል።” (የአልጠበሪ ታሪክ ቅፅ 8፥ ገፅ 124)

“አይሻ ሆይ! በኸይበር ከበላሁት ምግብ የተነሳ እስከ አሁን ህመም ይሰማኛል፣ በዚህ ሰዓት ግን ከመርዙ የተነሳ የልቤ ስር እንደተቆረጠ እየተሰማኝ ነው፡፡” (ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 5፣ መጽሐፍ 59፣ ቁጥር 713)

ይህንን ግልፅ ጉዳይ እንዴት ለማስተባበል እንደሞከረ እስቲ እንመልከት፡፡

  1. “ይህ ትክክለኛው የአምላክ መገለጥ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?” የሚል ጥያቄን ያቀርባል፡፡ በርሱ እሳቤ መሠረት የምንጠቅሰውን የቁርኣን ጥቅስ ሁሉ የግድ ማመን ያስፈልገናል፡፡ ይህ አመክንዮ ለእርሱ ይሠራ ይሆን? አጭርና ግልፅ መልስ ይህ ጥቅስም ሆነ በቁርኣን ውስጥ የሚገኝ የትኛም ቃል ከጌታ እግዚአብሔር ዘንድ ነው ብለን አናምንም የሚል ነው፡፡ ታድያ ለምን ጠቀስነው? በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡
    1. ሙስሊሞች በሚያምኗቸውና በሚቀበሏቸው ምንጮች መሠረት እንኳ ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ሙሐመድ እውነተኛነቱን የምንፈትንበትን መስፈርት አስቀመጠ፤ “ሐሰተኛ ከሆንኩ አላህ የልቤን ሥር ቆርጦ ይገድለኛል” አለ፤ እንደዚያውም ሆነ፡፡ ስለዚህ በሙሐመድ መስፈርት መሠረት ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ ነው፡፡
    2. በቁርኣን ውስጥ የሚገኘው ጥቅስ ከጌታ እግዚአብሔር ዘንድ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ እንዲያውም ንግግሩ በራሱ ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን የሚያሳይ የሙሐመድ የራሱ ፈጠራ ነው፡፡ “እውነተኛ ነቢይ ካልሆንኩ ፈጣሪ ይገድለኛል” ካለ በኋላ “አያችሁ? ፈጣሪ ያልገደለኝ እውነተኛ ነቢይ ስለሆንኩ ነው” የሚል ሰው ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ በዓለም ታሪክ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ተነስተዋል፤ ነገር ግን ብዙዎቹ መዋሸት በጀመሩበት ቅፅበት አልሞቱም፡፡ ስለዚህ “ከዋሸሁ ፈጣሪ ይገድለኛል” የሚል ግድድር የሚያቀርብና በዚያ መንገድ ነቢይነቱን ለማረጋገጥ የሚሞክር ሰው ሐሰተኛ ነው፡፡ ዳሩ ግን ሙሐመድ ይህንን ምልክት ከሰጠ በኋላ ምን ሆነ? ብዙዎቹ ሐሰተኛ ነቢያት እንዲህ ያለ ግድድር ቢያቀርቡ እግዚአብሔር በዝምታ ሊያልፋቸው ቢችልም በሙሐመድ ሁኔታ ግን የተለየ ነገር ተከስቷል፡፡ “ከዋሸሁ ፈጣሪ የልቤን ስር በመቁረጥ ይገድለኛል” አለ፤ ሊሞት ሲቃረብ ደግሞ “የልቤ ሥር ተቆረጠ” እያለ እየጮኸ ሞተ፡፡ ለሐሰተኝነቱ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ ከየት ይመጣል?
  2. በቁርኣንና በሐዲስ ውስጥ ያሉት ቃላት እንደሚለያዩና የተለያየ ትርጉም እንዳላቸው በመናገር የቃላት ጫወታ ይጫወታል፡፡ በቁርኣን ላይ አል-ወቲን እንደሚልና በሐዲስ ደግሞ “አብሐር” የሚል ቃል እንደተጠቀሰ፤ የሁለቱ ትርጉም እንደሚለያይ ይነግረናል፡፡ “ወቲን” አንድ የልብ ስር እንደሆነና አብሐር ደግሞ ብዙ የደም ስሮችን የያዘ ከአንገት ጀምሮ እስከ ልብ ድረስ ያለ ደም ስር እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይህ ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ ዝነኛውን የሌን አረቢክ ሌግዚኮን ጨምሮ ብዙ የአረብኛ ዲክሺነሪዎች ሁለቱም ቃላት ተመሳሳይ ትርጉም እንዳላቸው ያሳያሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ኦንላይን የአረብኛ ዲክሺነሪ ሁለቱንም ቃላት ጎን ለጎን በማስቀመጥ ተመሳሳይ ትርጉም ሰጥቷቸዋል https://www.almaany.com/en/dict/ar-en/aorta/ ለዚህ ነው የቁርኣንም ሆነ የሐዲስ ተርጓሚዎች በእንግሊዘኛ አንዱን ቃል (Aorta) የተጠቀሙት፡፡ ቁርአኑ የወረደው በአማርኛ ቢሆንና አላህ “የልቡን ስር እቆርጠዋለሁ” ብሎ ሙሐመድ ደግሞ በሐዲስ “የልቤ ደም ቧምቧ ተቆረጠ” ቢል ልዩነቱ ምንድነው? ይህቺ እንኳ እየሰጠመ ያለ ሰው በውኀ ላይ የሚንሳፈፍ ገለባ በመጨበጥ ነፍሱን ለማትረፍ እንደሚፍጨረጨር ዓይነት ከንቱ ጥረት ናት፡፡ ማንንም አታሳምንም፡፡

ይህ ወገናችን ለዚህ ሙግት ምላሽ ከየት እንዳገኘ ኢንተርኔት ላይ ፍለጋ ሳደርግ ባሰም ዘወዲ የተሰኘ ሙስሊም አፖሎጂስት የጻፈውን ምላሽ አገኘሁ፡፡ በዚህ ምላሽ ውስጥ ይህ ሙስሊም ወገናችን የጠቀሰው Taaj al-‘Aroos min Jawaahir Al-Qaamoos የአረብኛ ዲክሺነሪ የተጠቀሰ ሲሆን እርሱ ከተናገረው ጋር መሠረታዊ ልዩነት አለው፡፡ ዲክሺነሪው አል አብሐር ከጭንቅላት ተነስቶ እስከ እግር የተዘረጋ የደም ስር እንደሆነና ወደ ጀርባ እንደሚዘረጋ፣ ከዚያም አል-ወቲን ተብሎ እንደሚጠራ ይናገራል፡፡ የአርቲክሉ ጸሐፊ አል-ወቲን የአል-አብሐር ክፍል መሆኑንና በአንዳንድ ዲክሺነሪዎች ውስጥ ሁለቱም አንድ መሆናቸው መነገሩን አምኗል፡፡ ስለዚህ በርሱ ሙግት መሠረት እንኳ ከሄድን ወቲን የአብሐር ክፍል ከሆነ ሙሐመድ የእርሱ አብሐር እንደተቆረጠ ሲናገር ወቲን የተሰኘው ክፍሉ መቆረጡን ለማመልከት ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛ ብዙ የአረብኛ ዲክሺነሪዎች ሁለቱም አንድ እንደሆኑ ስለሚገልፁ በሙሐመድ ዘመን ሁለቱ ልዩነት እንደነበራቸው ምን ማረጋገጫ አለ? ይህንን የሚገልፅ ምንም ነገር የለም፡፡

Az-Zubaydee in his famous Arabic dictionary Taaj al-‘Aroos min Jawaahir Al-Qaamoos cites the scholar Ibn Athir as saying:

الأبْهَرُ عِرْقٌ مَنْشَؤُه مِن الرَّأْس ويَمْتَدُّ إلى القَدمِ

The Abhar is a vein that originates from the head and extends to the feet.

He then proceeds to say after assigning names to specific veins and their respective locations in the human body:

ويمتدُّ إلى الظَّهْر فيُسَمَّى الوَتِينَ

And it extends to the back and is called al-wateen.

So here we observe that al-wateen is actually a part of al-abhar. This is why al-wateen is sometimes used synonymously with al-abhar in some dictionaries.

  1. ሙስሊሙ ወገናችን “የልቤ ስር ተቆረጠ” የሚለው ተምሳሌታዊ ንግግር እንደሆነና ቀጥተኛ ንግግር እንዳልሆነ ሊያሳምነን አንዳንድ እስላማዊ ምንጮችን ጠቅሶልናል፡፡ ስለዚህ በርሱ እምነት መሠረት ሙሐመድ “የልቤ ስር እንደተቆረጠ ይሰማኛል” ሲል ቀጥተኛ ንግግር ሳይሆን ልክ “ቆሽቴ አረረ” እንደምንለው ዓይነት ሲሰማው የነበረውን ከፍተኛ ህመም ለመግለፅ የተጠቀመበት ነው፡፡ በሚከተሉት ምክንያቶች ሙግቱ ውድቅ ነው፡-
    1. የሙሐመድ ንግግር ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ እንዲተረጎም ተደርጎ የተገለፀ አይደለም፡፡ “የልቤ ስር እንደተቆረጠ ይሰማኛል” ሲል የህመም ስሜቱን እየገለፀ ነው፡፡ የልብ ስር መቆረጥ ስሜት እየተሰማው ነው ማለት ነው፡፡ እየተሰማው የነበረውን የህመም ስሜት እየገለፀ የሚገኝ ሰው ንግግር “ተምሳሌታዊ ነው” ብሎ ማለት ትርጉም አይሰጥም፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ የተናደደ ሰው ጨጓራዬ ተቃጠለ” ቢልና አንድ እየታመመ ያለ ሰው “ጨጓራዬ ተቃጠለ” ቢል የሁለቱ ንግግር በፍፁም አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ የመጀመርያው ሰው ስሜቱን (emotion) ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ እየገለፀ ሲሆን ሁለተኛው ግን የህመም ስሜቱን (pain feeling) በቀጥታ እየገለፀ ነው፡፡
    2. በሌላ ሐዲስ “(መርዙ) የልቤን ስር የቆረጠበት ጊዜ ነው” በማለት ስለተናገረ በሐዲሱ መሠረት የመርዙን ውጤት እየገለፀ ነበር፡፡ መርዙ የልቡን ስር ቆርጦታል፤ የሙሐመድ የልቡ ስር ተቆርጧል፡፡
    3. ከመርዝ ውጤቶች መካከል አንዱ የልብን ስር (Aorta) መጉዳት ነው፡፡ ስለዚህ ሙሐመድ የልቡ ደም ቅዳ እንደተቆረጠ እንደተሰማው መናገሩ “ተምሳሌታዊ ነው” ሊባል እንዴት ይችላል? እንዲህ ያለ ተምሳሌታዊ ንግግር በአረብኛ አለ ቢባል እንኳ በሙሐመድ ሁኔታ ግን ተምሳሌታዊ ሊሆን አይችልም፡፡
    4. ከፍተኛ የህመም ስሜትን የሚገልፅ ተምሳሌታዊ ንግግር ነበር ቢባል እንኳ በቁርኣን ውስጥ የተጻፈውስ ንግግር ተምሳሌታዊ እንዳይሆን ምን ያግደዋል? ስለዚህ በቁርኣን ውስጥ አላህ ሐሰተኛውን ነቢይ በከፍተኛ ሁኔታ አሠቃይቶ እንደሚገድለው ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ከተናገረና ሙሐመድ በከፍተኛ ሥቃይ ከሞተ ንግግሩ ገቢራዊ ሆነም አይደል?
  2. ሙስሊሙ ወገናችን የቁርኣን አንቀፁና ሐዲሱ አምክንዮአዊ ግንኙነት እንደሌላቸው ይነግረናል፡፡ “አላህ ሙሐመድን የልቡን ስር በመቁረጥ የገደለው በእርሱ ላይ ስለዋሸ ነው የሚል ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም” ይለናል፡፡ ይህ በጣም ደካማ ሙግት ነው፡፡ አላህ በቁርኣን ሙሐመድ ከዋሸ የልቡን ስር ቆርጦ እንደሚገድለው ከተናገረና ኋላ ላይ ሙሐመድ የልቡ ስር ተቆርጦ ከሞተ ምልከታው ግልፅ ነው፤ ሙሐመድ በእርሱ ላይ ዋሽቷል ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው “እኔ ሐሰተኛ ነቢይ ከሆንኩ የልቤ ስር ተቆርጦ እሞታለሁ” በማለት ከተናገረና በተናገረው በዚያው መንገድ ሞቶ ከተገኘ ክስተቱ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን አያሳይም እንዴት ሊባል ይችላል? ከቋንቋ አንፃር ያቀረበው ሙግት ትንሽም ቢሆን ያስኬዳል፤ ይኸኛው ሙግት ግን ቢቀርበት ይሻለው ነበር፡፡
  3. ሌላ አስገራሚ ሙግትም ያቀርብልናል፡፡ “ሙሐመድ በአላህ ላይ ዋሽቶ ከነበረ አላህ ሙሐመድ መዋሸቱን ከመግለፅ ይልቅ ከዚያ በኋላ የሚገኙትን የቁርኣን አንቀፆች ለምን አወረደ?” የሚል ዓይነት ሐተታ አቅርቧል፡፡ ይህ ግን ቁርኣን ትክክለኛ የአላህ ቃል ነው ከሚል ቅድመ ግንዛቤ የመነጨ ከንቱ ሙግት ነው፡፡ ሲጀመር ቁርኣን የፈጣሪ ቃል አይደለም፤ የልቡን ስር ስለመቁረጥ የሚናገረው ቃልም ቢሆን የፈጣሪ ቃል ሳይሆን ሙሐመድ መልእክተኛነቱ ተቀባይነት እንዲያገኝለት በፈጣሪ ስም የተናገረው “ራስን የማፅደቅ” ንግግር ነው፤ “ሐሰተኛ ከሆንኩ ፈጣሪ ይገድለኛል፤ ስለዚህ ስላልሞትኩ እውነተኛ ነቢይ ነኝ” ዓይነት ራስን እውነተኛ አድርጎ የማቅረን ንግግር ነው፡፡ ሙሐመድ ከእውነተኛው ፈጣሪ ዘንድ የሆነ ምንም ነገር ተናግሮ አያውቅም፤ በፈጣሪ ስም የተናገረው ሁሉ የግል ፈጠራውና የልቡ ምኞት ነው፡፡ ነገር ግን ሐሰተኛ መሆኑ ለዓለም ግልፅ ይሆን ዘንድ “ሐሰተኛ ከሆንኩ የልቤ ስር ተቆርጦ እሞታለሁ” ባለው መሠረት እውነተኛው አምላክ የልቡ ስር ተቆርጦ እንዲሞት አደረገው፡፡ ዳሩ ግን ሙስሊም ወገኖች እግዚአብሔር አምላክ የሙሐመድን ሐሰተኛነት እንዲህ ግልፅ አድርጎ በአደባባይ አሳይቷቸው ሳለ በግድ እውነተኛ ነቢይ ሊያደርጉት ይደክማሉ፡፡
  4. ሙስሊሙ ወገናችን ጥቅሱ ሙሐመድ በአላህ ላይ መዋሸቱን አይናገርም ይለናል፡፡ “በኛ ላይም ከፊልን ቃላት (ያላልነውን) በቀጠፈ ኖሮ…” ስለሚል “አድርጎ ቢሆን ኖሮ” እንጂ “አድርጓል አይልም” የሚል መከራከርያ ያቀርባል፡፡ ይህ ሙግት በሁለት ምክንያቶች ውድቅ ነው፡-
    1. ጥቅሱ ስላልተደረገ ነገር ማለትም ሙሐመድ ስላለመዋሸቱ የሚናገር ቢሆን እንኳ እስከዚያች ሰዓት ድረስ አለመዋሸቱን እንጂ ከዚያ በኋላ ላለመዋሸቱ ዋስትና አይሆንም፡፡ ሙሐመድ ከዚያ ቀደም አልዋሸም ቢባል እንኳ በጥቅሱ ውስጥ የተነገረው መቅሠፍት ስለደረሰበት ከዚያ በኋላ ዋሽቷል ማለት ነው፡፡ የሙስሊሙ ወገናችን ሙግት ሙሐመድ የሆነ ጊዜ ላይ እውነተኛ ነቢይ እንደነበረ እንጂ ዕድሜ ልኩን እውነተኛ ነቢይ ሆኖ እንደኖረ አያመለክትም፡፡
    2. ሙሐመድ ከፈጣሪ የሆነ አንድም መገለጥ ተናግሮ አያውቅም፡፡ ጥቅሱ ሙሐመድ ራሱን ለማፅደቅ የተናገረው የግል ፈጠራው ነው፡፡ ነገር ግን ሙሐመድ ራሱን ለማፅደቅና ለእውነተኛነቱ ማስረጃ አድርጎ የተናገረው ንግግር በስተመጨረሻ ሐሰተኛነቱን የሚያረጋግጥ ሆኖ ተገኘ፡፡

ቀደም ሲል ያቀረብነው ሙግት ሙሐመድ በመርዝ በመሞቱ ምክንያት ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን የተመለከተ አይደለም፡፡ ሆኖም ክስተቱ የሙሐመድን ሐሰተኛነት እንደሚያረጋግጥ የሚያሳዩ ተከታዮቹን ነጥቦች እናቀርባለን፡፡

  1. ክስተቱ ለሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይነት እንደ ማስረጃ የሚቀርብበት አንዱ ምክንያት ሙሐመድ በምግቡ ውስጥ መርዝ መኖሩን አስቀድሞ በማወቅ ራሱንም ሆነ ወዳጆቹን መታደግ አለመቻሉ ነው፡፡ ይልቅስ መርዙን ከበላ በኋላና ወዳጆቹም በልተው ከተጎዱ በኋላ “የፊየል እግር መርዝ በውስጡ መኖሩን ነገረችኝ” በማለት የማይመስል ታሪክ በመፍጠር “ነቢይ” ለመምሰል ሞክሯል፡፡ ከእንዲህ ዓይነት አስደንጋጭ ክስተት በኋላ ተዓምራዊ የሚመስሉ ትርክቶችን በመፍጠር ስብዕናቸውን ለማደስ መሞከር የሐሰተኛ ነቢያት ባሕርይ ነው፡፡
  2. በሐዲስ ውስጥ እንደተዘገበው ቢሽር ገና ምግቡን እንደቀመሰ ነበር መርዝ በውስጡ መኖሩን ያወቀው፡፡ ነገር ግን በሙሐመድ ነቢይነት በመተማመኑ ምክንያት ሙሐመድ ምግቡን መብላት እስኪያቆም ድረስ ዝም ብሎ መብላቱን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን ይህ በሙሐመድ ላይ የነበረው መተማመን ሕይወቱን አሳጥቶታል፡፡ በምድራዊ ሕይወት ያልታመነው ሙሐመድ እንዴት ለዘላለም ሕይወት ሊታመን ይችላል?
  3. ይህ ክስተት የሙሐመድን ሐሰተኛ ነቢይት የሚያረጋግጥበት ሌላም ምክንያት አለ፡፡ ሙሐመድ ጠዋት ሰባት የአጁዋ ተምር የበላ ሰው በዚያን ዕለት በመርዝም ሆነ በድግምት ሊጎዳ እንደማይችል ተናግሮ ነበር (Sahih al-Bukhari, Volume 7, Book 71, Number 671)፡፡ ሙሐመድ በመርዝ መሞቱ ብቻ ሳይሆን በድግምት ቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበርም በሐዲሳት ተዘግቧል (Sahih al-Bukhari, Volume 7, Book 71, Number 660)፡፡ ስለዚህ ሙሐመድም ሆነ ወዳጆቹ የአጅዋ ተምር ሲበሉ የኖሩና ከመርዙም በኋላ በልተው የመዳን ዕድል የነበራቸው በመሆኑ በመርዙ አማካይነት መሞታቸው የሙሐመድ አባባል ሐሰት መሆኑን ያሳያል፤ እናም ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ ነው፡፡
  4. በሌላ ሐዲስ ላይ ደግሞ ሙሐመድ ጥቁር አዝሙድ ከሞት ውጪ የማይፈውሰው የበሽታ ዓይነት እንደሌለ ተናግሯል፡፡ ታድያ ለምን ጥቁር አዝሙድ በልቶ እርሱም ሆነ ወዳጁ ከጉዳትና ከሞት አልተረፉም? Sahih al-Bukhari Vol. 7, Book 71, Hadith 592
  5. ብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ነቢያትና ቅዱሳን ሰዎች ከመርዝ በመትረፍና ተከታዮቻቸውን በማትረፍ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

“ኤልሳዕም ዳግመኛ ወደ ጌልገላ መጣ፥ በምድርም ላይ ራብ ነበረ፤ የነቢያትም ልጆች በፊቱ ተቀምጠው ነበር፥ ሎሌውንም፦ ታላቁን ምንቸት ጣድ፥ ለነቢያት ልጆችም ወጥ ሥራ አለው። አንዱም ቅጠላቅጠል ያመጣ ዘንድ ወደ ሜዳ ወጣ፥ የምድረበዳውንም ሐረግ አገኘ፤ ከዚያም የበረሀ ቅል ሰበሰበ፥ ልብሱንም ሞልቶ ተመለሰ፥ መትሮም በወጡ ምንቸት ውስጥ ጨመረው ምን እንደ ሆነ ግን አላወቁም። ሰዎቹም ይበሉ ዘንድ ቀዱ ወጡንም በቀመሱ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ በምንቸቱ ውስጥ ሞት አለ፤ ብለው ጮኹ ይበሉም ዘንድ አልቻሉም። እርሱም፦ ዱቄት አምጡልኝ አለ፤ በምንቸቱም ውስጥ ጥሎ፦ ይበሉ ዘንድ ለሕዝቡ ቅዱ አለ። በምንቸቱም ውስጥ ክፉ ነገር አልተገኘም።” (2ነገ. 4፡38-41)

“በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንድትባል አወቅን። አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፦ ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም አሉ። እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤ እነርሱም፦ ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ፦ ይህስ አምላክ ነው ብለው አሳባቸውን ለወጡ።” (ሐዋ. 28፡1-6)

ታድያ ሙሐመድ የነቢያት መደምደምያ ከሆነ ከነቢዩ ኤልሳዕና ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሊያንስ እንዴት ቻለ?

“Muhammad is the most obvious false prophet in history!” Dr. David Wood

 

የሙሐመድ አሟሟት ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን ያረጋግጣል