የሙባሃላ እርግማንና የሙሐመድ ቤተሰብ እልቂት

የሙባሃላ እርግማንና የሙሐመድ ቤተሰብ እልቂት

ሙሐመድ ሐሰተኛ ነቢይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ


“ሙባሃላህ”  مُبَاهَلَة የሚለው የአረብኛ ቃል “በሀለ” እርግማን የሚል ትርጉም ካለው የአረብኛ ቃል የተገኘ ሲሆን ሁለት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ያልተግባቡበት ጉዳይ ካለ “ሐሰትን በተናገረው አካል ላይ የፈጣሪ እርግማን ይሁን” በሚል ቃል የሚረጋገሙበት እስላማዊ ስርዓት ነው። ሙሐመድ ሃይማኖቱን ከመሠረተ በኋላ በአረብያና በዙርያው የነበሩ የተለያዩ ማሕበረሰቦች እንዲሰልሙ የቻለውን በጂሃድ የማስገደድና ያልቻለውን ደግሞ ደብዳቤዎችን በመላክ ጥሪ የማድረግ ዘዴዎችን ይጠቀም ነበር። የሙሐመድ ደብዳቤ ከደረሳቸው ማሕበረሰቦች መካከል በደቡብ አረብያ የሚኖር ነጅራን የተሰኘ ክርስቲያን ማሕበረሰብ ይገኝበታል። ከሙሐመድ የደረሳቸውን ደብዳቤ ምክንያት በማድረግ ከሙሐመድ ጋር ለመወያየት የማሕበረሰቡ ተወካዮች ወደ መዲና እንደ ተጓዙ ከእስላማዊ ምንጮች እንረዳለን። ውይይቱ የክርስቶስ አምላክነትና ሥላሴን በመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ያጠነጠነ እንደ ነበረ እነዚሁ ምንጮች የሚናገሩ ሲሆን ባለመግባባት እንደተጠናቀቀ ተዘግቧል።

የውይይቱን ባለመግባባት መጠናቀቅ ተከትሎ ሙሐመድ “ሐሰትን የተናገረው ወገን እንዲቀሠፍ” በሚል እርስ በርስ የመረጋገም ስርዓት (ሙባሃላ) እንዲፈፅሙ ክርስቲያኖቹን የጋበዛቸው ሲሆን የክርስቲያኖቹ ምላሽ ግን አዎንታዊ አልነበረም። ከዚሁ ክስተት ጋር የተያያዘ አንቀፅ በቁርአን ውስጥ ይገኛል፦

“ዕውቀቱም ከመጣልህ በኋላ በርሱ (በዒሳ) የተከራከሩህን ሰዎች «ኑ፤ ልጆቻችንንና ልጆቻችሁን፣ ሴቶቻችንንና ሴቶቻችሁንም፣ ነፍሶቻችንንና ነፍሶቻችሁንም እንጥራ፡፡ ከዚያም አጥብቀን አላህን እንለምን፤ የአላህንም ቁጣ በውሸታሞቹ ላይ እናድርግ» በላቸው፡፡” (ቁርአን 3፡61)

ተፍሲራቱ ይህንን አንቀፅ ከዚሁ ክስተት ጋር የሚያያይዙ ሲሆን ሙሐመድ ለእርግማን ስርዓቱ የገዛ ቤተሰቡን፣ ማለትም ልጁ ፋጢማንና ሁለት ልጆቿን ሐሰንና ሁሴንን ይዞ እንደቀረበ ይናገራሉ።[1] ክርስቲያኖቹ እርግማኑ ላይ እንዲሳተፉ በተጠየቁ ጊዜ እንቢታን የመረጡ ሲሆን እስላማዊ ምንጮች እንደሚሉት እንቢታን የመረጡት “የሙሐመድን ነቢይነት ስለሚያውቁና እርግማኑ እንዳይፈፀመባቸው ስለ ፈሩ” ነበር። ታሪኩን የዘገቡልን እስላማዊ ምንጮች በመሆናቸው ምክንያት ሃቀኛ ዘገባ የማግኘት ዕድላችን አነስተኛ ቢሆንም ክርስቲያኖቹ ሰጡ የተባለው ምክንያት እውነት ሊሆን እንደማይችል እዝነ-ልቦናችን ይነግረናል። ይህንን ታሪክ የጻፉት ሙስሊሞች ክርስቲያኖቹ ለሙሐመድ የሚሰጡትን ምላሽ በተመለከተ የተነጋገሩትን ከወዴት እንደሰሙ ግልፅ አይደለም። ነቢይነቱን እያወቁ ሆነ ብለው አልተቀበሉትም የሚለው በጭራሽ ሊታሰብ የማይችል ነው። ምን ጥቅም ለማግኘት ብለው ይክዳሉ? ምድራዊ ጥቅም አስበው ነው እንዳይባል ይጠቅማቸው የነበረው ሙሐመድን ተቀብሎ የምድራዊ ጥቅም ተጋሪ መሆን እንጂ እርሱን ክዶ አዋራጅ የሆነውን የጂዝያ ግብር መክፈል አይደለም። ሙሐመድ እውነተኛ መሆኑን በሚያውቁበት ሁኔታ ይህንን ለምድርም ሆነ ለሰማይ የማይጠቅማቸውን ምርጫ መምረጣቸው የማይመስል ነው። ይልቅ በእርግማን ስርዓት ውስጥ መሳተፍ ክርስቲያናዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባለመሆኑ አለመቀበላቸው ትክክል ነበር። ተከታዩ መጽሐፍ ክርስቲያኖች ለምን በእርግማኑ ውስጥ መሳተፍ እንዳልፈለጉ ተጨማሪ ምክንያት ይሰጣል፤ እርሱም ሙሐመድ እርምጃ እንዳይወስድባቸው መፍራታቸው ነው፦

“ስለ ክስተቱ የተለያዩ ዝርዝር ዘገባዎች አሉ፤ ነገር ግን ለሁሉም ታሪኮች የጋራ የሆኑት ነጥቦች፦ ክርስቲያኖች እስልምናን ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸውና ስለ ኢየሱስ ያላቸውን እምነት አጥብቀው በመያዛቸው ምክንያት የፈጣሪ እርግማን በሚዋሹት ሰዎች ላይ ይሁን የሚል ግድድር ቀርቦላቸው ሁለቱም ወገኖች በቀጣይ ቀን ለመገናኘት ተስማሙ የሚለው ነው። ክርስቲያኖች በኋላ እርስ በርሳቸው በመመካከር ክርስቲያን ሆነው ለመቀጠል ስለፈለጉ ወደዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መግባት ምንም ዓይነት መልካም ነገር የለውም ብለው ደመደሙ። ሙሐመድ እውነተኛ ነቢይ ከሆነ የፈጣሪ እርግማን እንዳይወርድባቸው ፈርተው ሊሆን ይችላል ወይም ሙሐመድን በፖለቲካ ስለሚፈሩት ፖለቲካዊ ጠላቶቹ ለመሆን አልፈለጉም። አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ነብዩ ከልጃቸው ፋጢማና ከሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ሐሰንና ሁሴን ጋር በማግስቱ ወጡ። ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ የፋጢማ ባልና የነብዩ የአጎት ልጅ የሆነው ዓሊይም መጥቶ ነበር፤ በጥቅሱ መሠረት የተከራካሪዎቹ ልጆችና ሴቶች የግድድሩ አካል ናቸውና። ክርስቲያኖች ወደዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ከመግባት ይልቅ እንቢታን መረጡ፤ በአንዳንድ ምንጮች መሠረት “በፈጣሪ እንጠበቃለን!” አሉ። ከዚያም የነጅራን ልዑካን ክርስቲያን ሆነው እንዲቀጥሉና የራሳቸውን ጉዳይ እንዲመሩ፣ ነገር ግን ዚሚ በመሆን ለሙስሊሞች ዓመታዊ ግብር እንዲከፍሉ ከነቢዩ ጋር ስምምነት ላይ ደረሱ (ቁርአን 9፡29)።”[2]

ስለዚህ ክርስቲያኖቹ ይህ ድርጊት በመጽሐፍ ቅዱስ የማይደገፍ ከመሆኑም በተጨማሪ ከሙሐመድ ጋር መረጋገም ቁጣውን ከፍ በማድረግ እነርሱን ለጥቃት ሊያጋልጥ እንደሚችል በትክክል ተረድተዋል። የእርግማኑ ተካፋይ ከመሆን ይልቅ ከእንዲህ ያለ ክፋት እግዚአብሔር እንደሚጠብቃቸው መናገራቸው ክርስቲያናዊና በአስተውሎት የተሞላ ምላሽ ነበር።

እርግማኑ በሙሐመድ ላይ ነው የደረሰው!

ሙሐመድ የገዛ ቤተሰቡን አቅርቦ የእርግማኑን ቃል ሲናገር “አሜን” እንዲሉ በጠየቃቸው ጊዜ ክርስቲያኖቹ እምቢ እንዳሉ አል-ጃላላይን ይነግሩናል፦

“ከአል-ሐሰን፣ አል-ሁሴን፣ ከፋጢማና ዓሊይ ጋር የተጓዙትን ነብዩን (ሶ.ዐ.ወ) ለማየት በሄዱ ጊዜ (ለነጅራን ልዑካን) ነቢዩ እንዲህ አሏቸው፡- ‘እኔ ልመና ሳቀርብ እናንተ ‘አሜን’ ትላላችሁ። ነገር ግን ከዚህ የእርስ በርስ መረጋገም ተቆጥበው ጂዝያ ለመክፈል ከነብዩ ጋር የሰላም ስምምነት አደረጉ። አቡ ኑዓይም ዘግበውታል።”[3]

በጃሚ አል-ትርሚዚ ሐዲስ ውስጥ እንደተዘገበው ሙሐመድ የገዛ ልጁንና የልጅ ልጆቹን በማቅረብ “አላህ ሆይ የኔ ቤተሰብ ይህ ነው” በማለት ተናግሯል።[4] ውድ አንባቢያን፤ ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን ነገር ሙሐመድን እንደ እውነተኛ ነቢይ የተቀበሉት ወገኖች ላለማሰብ ቢፈልጉም ሃቁ ግን እጅግ አስደንጋጭ ነው። ሙስሊም ሊቃውንት እንደሚናገሩት የሙባሃላ እርግማን የፈፀመ ሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እርግማኑ ይደርሰውና ይሞታል። ኢብን ሐጀር አል-አስቀላኒ “ፈት አል-ባሪ” በተሰኘው የሳሂህ አል-ቡኻሪ ማብራርያቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፦

ومما عرف بالتجربة أن من باهل وكان مبطلاً لا تمضي عليه سنةٌ من يوم المباهلة

“በልምድ የሚታወቀው በሙባሃላ ወቅት ሐሰትን በመደገፍ የተሳተፈ ሰው ከአንደኛ ዓመቱ አያልፍም።”[5]

በኢብን ሐጀር መሠረት በሙባሃላ እርግማን ወቅት ሐሰተኛው ወገን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መቅሠፍት ይደርስበታል። በዚሁ ማብራርያቸው ላይ ከራሳቸው ልምድ ተነስተው ሲናገሩ ከርሳቸው ጋር እንዲህ ያለ ፉክክር ውስጥ የገባ አንድ አምላክ የለሽ ሰው በሁለት ወራት ውስጥ ሞቷል። ይህንን ይዘን የሙባሃላ እርግማን ማን ላይ ነው የደረሰው የሚለውን እንመልከት።

በእስላማዊ ምንጮች መሠረት ክርስቲያኖቹ ከሙሐመድ ጋር የተገናኙት በ10 ዓመተ ስደት ሲሆን[6] ሙሐመድ የሞተው ደግሞ በ11 ዓመተ ስደት ነው። የሙሐመድ ህልፈት በፈረንጅ አቆጣጠር ጁን 7፣ 632 ዓ.ም. ይሆናል።[7] የሙሐመድን አሟሟት ስንመለከት እጅግ ከባድና የቅሥፈት ዓይነት እንደነበረ ከእስላማዊ ምንጮች እንረዳለን፦

የአላህ መልዕክተኛ በሞቱበት ህመም ተይዘው ሳሉ የቢሽር እናት ልትጎበኛቸው መጣች፤ እሳቸውም እንዲህ አሉ፦ “የቢሽር እናት ሆይ፥ በኸይበር ከልጅሽ ጋር ከበላሁት ምግብ የተነሳ የልቤ ስር እንደተቆረጠ ይሰማኛል::[8]

አይሻ እንዳወራችው፡- ነቢዩ በሞቱበት ህመም ሲታመሙ ሳሉ እንዲህ ብለው ይናገሩ ነበር፤ “አይሻ ሆይ! በኸይበር ከበላሁት ምግብ የተነሳ እስከ አሁን ህመም ይሰማኛል፣ በዚህ ሰዓት ግን ከመርዙ የተነሳ የልቤ ስር እንደተቆረጠ እየተሰማኝ ነው፡፡”[9]

አይሻ ስለ አሟሟቱ ስትናገር የሰው ልጅ እንዲህ ሲሠቃይ አይታ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡ የሙስሊም ጂሃዳውያንን ግፍና ጭካኔ ስታይ የኖረችው አይሻ የሙሐመድን ሥቃይ ዓይታ ከምታውቀው ከየትኛውም ሥቃይ ጋር እንደማይነፃፀር ትነግረናለች።[10] ከዚህ በመነሳት ሙሐመድ የሞተው ተቀሥፎ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም። ስለዚህ የሙባሃላ እርግማን በሙሐመድ ላይ ደርሷል። በክርስቲያኖቹ ላይ እንዲከሰት የተመኘው እርግማን በራሱ ላይ ደርሶ ሐሰተኛነቱን አረጋግጧል።

የሙሐመድ ቤተሰብስ ከዚህ እርግማን ተርፎ ይሆን?

በፍጹም። ሙሐመድ ከዚህ ዓለም በሞት በተለየበት በዚያው ዓመት (632 ዓ.ም.) ልጁ ፋጢማ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየች ከእስላማዊ ታሪክ እንረዳልን።[11] አሟሟቷን በተመለከተ በሱኒና ሺኣ ሙስሊሞች መካከል ክርክር ያለ ሲሆን በሺኣ ሙስሊሞች መሠረት የሰማዕትነት ሞት እንደሞተች ይታመናል። ይኸውም ከሙሐመድ ሞት በኋላ የሙስሊሞች ተተኪ ማን ይሁን በሚለው ላይ በተፈጠረ ጭቅጭቅ በዓሊይና በፋጢማ ቤት ላይ ከበባ ተፈፅሞ ነበር። በዚህ ጊዜ ዓሊይ ለአቡበክር ሹመት አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ለማስገደድ የቤታቸውን በር በኃይል ሰብረው በሚገቡበት ወቅት በሩ ስለወደቀባት እንደ ተጎዳችና ክፉኛ እንደቆሰለች ይህም ለሞቷ ሰበብ እንደሆነ ነው።[12] ሌሎች ደግሞ ነፍሰጡር እንደነበረችና ፅንሱም እንደጨነገፈ የሚናገሩ ሲሆን ከዚህ ጋር የማይስማሙም አሉ።[13] የሆነው ሆኖ ፋጢማ እንደ አባቷ ሁሉ እርግማኑ እንደደረሰባት ግልፅ ነው።

የተቀሩት የሙሐመድ ቤተሰቦችስ ምን ሆኑ? የሙሐመድ የልጅ ልጅ ሐሰን በገዛ ሚስቱ ተመርዞ እንደሞተ ከእስላማዊ ታሪክ እንረዳለን። የሐሰን ወንድም የነበረው ሁሴን ደግሞ ከተወሰኑ ተከታዮቹ ጋር በሙስሊሞች እንደተገደለ፤ አሟሟቱም በጦር ተወግቶ መሬት ላይ ወድቆ ሳለ ሲናን ኢብን አነስ በተሰኘ ሙስሊም አንገቱ ተቆርጦ እንደሆነ፤[14] አስክሬኑም ጭምር በሙስሊሞች እንደተቆራረጠ ታሪክ ይናገራል።[15] በአል-ጠበሪ ዘገባ መሠረት ሁሴን ሲገደል ሠላሳ ሦስት የተወጉ ቁስሎችና ሠላሳ አራት ድብደባዎች በሰውነቱ ላይ ነበሩ። የሙሐመድ ልጅ የፋጢማ ባል፣ የሐሰንና ሁሴን አባት የነበረው ዓሊይ ከዚያ ቀደም ብሎ አብዱልረህማን ኢብን ሙልጃም በተባለ ሙስሊም እንደተገደለ፤ አሟሟቱም ግንባሩ ለሁለት እስኪከፈል ድረስ መርዝ በተነከረ ሰይፍ ከባድ ምት አርፎበት እንደነበር ምንጮች ይነግሩናል።[16] በርግጥ የተቀሩት የሙሐመድ ቤተሰቦች (አማቹ ዓሊይ እና የልጅ ልጆቹ ሐሰንና ሁሴን) ከሙባሃላ ክስተት ከብዙ ዓመታት በኋላ የሞቱ ቢሆንም አሟሟታቸው አሳቃቂ ከመሆኑ አንጻር እርግማኑ እንደደረሰባቸው መደምደም እንችላለን። የሙሐመድ ሁለቱ የልጅ ልጆች እርግማኑ ሲፈፀም ህፃናት ስለነበሩ የህሊና ተሳትፎ አልነበራቸውም። ነገር ግን ካደጉ በኋላ የሙሐመድን ውርሶች ለማስቀጠል ሲሞክሩ እርግማኑ እንደ ደረሰባቸው ማሰብ እንችላለን። የሆነው ሆኖ በሙሐመድ ዘር ማንዘር ላይ እንዲህ ያለ አሠቃቂ ነገር መድረሱ የፈጣሪ ቁጣ ከማለት ውጪ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

ማጠቃለያ

ሙሐመድ የክርስቶስን አምላክነት በተመለከተ ከክርስቲያኖች ጋር ሙግት በገጠመበት ወቅት ማሸነፍ ሲሳነው ያቀረበው ግድድር «ኑ፤ ልጆቻችንንና ልጆቻችሁን፣ ሴቶቻችንንና ሴቶቻችሁንም፣ ነፍሶቻችንንና ነፍሶቻችሁንም እንጥራ፡፡ ከዚያም አጥብቀን አላህን እንለምን፤ የአላህንም ቁጣ በውሸታሞቹ ላይ እናድርግ» የሚል ነበር (ቁርአን 3፡61)። በእርግማኑ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያሰለፈው ደግሞ ልጁ ፋጢማ፣ ባሏ ዓሊይን እንዲሁም በወቅቱ ህፃናት የነበሩትን ሐሰንና ሁሴንን ነበር። የዓሊይ በቦታው ላይ መገኘት በሙስሊሞች ዘንድ አከራካሪ ጉዳይ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። እርግማኑ በሙሐመድና በልጁ በፋጢማ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሆነን መናገር እንችላለን። ሐሰንና ሁሴን በወቅቱ ህፃናት በመሆናቸው የእርግማኑ ውጤት ወዲያው ባያገኛቸውም ካደጉና የሙሐመድን ውርስ ለማስቀጠል ጥረት ማድረግ ከጀመሩ በኋላ የእርግማኑ ውጤት አግኝቷቸዋል። ከእነርሱ ቀደም ብሎ አባታቸው ዓሊይ ለብዙ ዘመናት በሰላም ከኖረ በኋላ ሥልጣን ተረክቦ የሙስሊሞች ኸሊፋ በሆነ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እርሱም አሳዛኝ የሆነ አሟሟት ሞቷል።

ውድ ሙስሊሞች፣ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በሙሐመድና በቤተሰቡ ላይ የተከሰተውን አሳቃቂ እልቂ በመዘርዘር እናንተን ማሳዘን ወይም ማሳጣት አይደለም። ይህ የዘላለም ሕይወት ጉዳይ ስለሆነ የእርስ በርስ ብሽሽቅ ወይም አንዳችን ሌላችንን የማበሳጨት ጉዳይ አይደለም። ይህንን ሁሉ ካነበባችሁ በኋላ ምን ሊሰማችሁ እንደሚችል እንረዳለን፤ መከፋታችሁ ደግሞ ያሳዝነናል። ነገር ግን የእውነት አምላክ በገዛ ታሪካችሁ ውስጥ እውነቱን ታውቁ ዘንድ ያስቀራቸውን እነዚህን ምልክቶች እንድታስተውሉና ነፍሳችሁን እንድታተርፉ እንሻለን። የክርስቶስን አምላክነት ለመገዳደር ክርስቲያኖች ላይ እርግማን የጠራው የነቢያችሁና የቤተሰቡ ታሪክ እንዲህ ተደምድሟል። የናንተ ታሪክ በምን ዓይነት ሁኔታ እንዲደመደም ትሻላችሁ? ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳው ከእግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለዘላለም ለመኖር የምትሹ ከሆነ ለሙሐመድና ለቤተሰቡ እልቂት ሰበብ ከሆነው እርግማን ራሳችሁን አርቁ። ጊዜ ሳትሰጡ የነፍሳችሁ እረኛ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ታረቁ፦

“በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አሁን ነው።” (2ቆሮንቶስ 6፡2)።


ማጣቀሻዎች

[1] https://quranx.com/tafsirs/3.61

[2] Nasr, S. H., et al. (2015). The Study Quran, pp. 313-314.

[3] አል-ጃለላይን የሱራ 3፡61 ተፍሲር

[4]  Jami` at-Tirmidhi Volume 5, Book 44, Hadith 2999

[5] Fath al-Bari 12/195 

[6] Ibn Kathir. 1998. The Life of the Prophet Muhammad, Al-Sira al-Nabawiyya. Translated by Professor Trevor Le Gassick, pp. 73-75.

[7] http://www.itsislam.net/articles/life_of_Prophet_Muhammad.asp

[8] የአልጠበሪ ታሪክ ቅፅ 8፥ ገፅ 124

[9] ሳሂህ አል-ቡኻሪ ቅፅ 5፣ መጽሐፍ 59፣ ቁጥር 713

[10] Sunan Ibn Majah 1622

[11] https://www.worldhistory.org/Fatimah_bint_Muhammad/

[12] https://www.al-islam.org/story-holy-kaaba-and-its-people-smr-shabbar/story-hazrat-fatima-sa-daughter-holy-prophet

[13] https://www.islamicity.org/82787/death-of-fatimah-bint-muhammed-controversy-and-tragedy/

[14] The History of al-Ṭabarī Vol. 19. State University of New York Press, 1990, pp. 160-161

[15] https://www.britannica.com/event/Battle-of-Karbala

[16] https://erfan.ir/english/5813.html


 

ሙሐመድ