ሙሐመድ የለምፅ ደዌን ይፈራ ነበር – ኢየሱስ ለምፃሞችን ያነፃል
የኢየሱስን ፈጣሪነትና የሙሐመድን ደካማነት የሚያረጋግጥ ታሪክ
ሙስሊም ወገኖቻችን የኢየሱስን አምላክነት ባይቀበሉም ከፍ ያለ ደረጃ ካላቸው ነቢያት መካከል እንደ አንዱ ይቆጥሩታል፡፡ ሆኖም ሙሐመድ ከኢየሱስ ብልጫ እንዳለውና ለሰው ልጆች ሁሉ ምርጡ ምሳሌ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከኢየሱስ ትምህርትና ምሳሌነት ይልቅ የሙሐመድን ትምህርትና ምሳሌነት ልንከተል እንደሚገባ ይነግሩናል፡፡ ነገር ግን የሙሐመድ ትምህርትና ምሳሌነት ከኢየሱስ በምን እንደሚልቅ ግልፅ መስፈርትም ሆነ ማስረጃ የላቸውም፡፡ በክርስቲያናዊ ቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በእስልምና መጻሕፍት ውስጥ የሰፈሩትን የሁለቱን ወገኖች ስብዕና ስናጠና በኢየሱስና በሙሐመድ መካከል የሚገኘው ልዩነት በፈጣሪና በፍጡር መካከል የሚገኝ ልዩነት ያህል የሰፋ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይህንን ከሚያስገነዝቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለ ለምፅ ህመም ሁለቱ ወገኖች የነበራቸውን አተያይና በበሽታው ላይ የነበራቸውን ኃይል አስመልክቶ በቁርኣን፣ በሐዲስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉት ታሪኮች ናቸው፡፡
እስኪ ሙሐመድ ስለ ለምፅ ህመም የነበረውን ግንዛቤና በበሽታው ላይ የነበረውን ኃይል በተመለከተ በእስላማዊ የሐዲስ መጻሕፍት ውስጥ የተነገሩት እንመልከት፡-
ሳሂህ አል-ቡኻሪ ውስጥ እንደተዘገበው ሙሐመድ እንዲህ ብሏል፡- “አንድ ሰው ከአንበሳ ሮጦ የሚሸሸውን ያህል ከለምፃም ሮጦ መሸሽ አለበት፡፡”[1]
ሙሐመድ በለምፅ ላይ የነበረውን ኃይል አስመልክቶ ሱናን አቡዳውድ ውስጥ እንዲህ ተብሏል፡- “ነቢዩ እንዲህ ሲል ይጸልይ ነበር፡- አላህ ሆይ ከለምፅ፣ ከእብደት፣ ከዝሆኔ በሽታና ከክፉ ደዌ በአንተ እሸሸጋለሁ፡፡”[2]
ከላይ ባነበብናቸው የሐዲስ ዘገባዎች መሠረት ሙሐመድ ለምፅን የመፈወስም ሆነ ከለምፅ የመትረፍ መንፈሳዊ ኃይል አልነበረውም፡፡ እንደ ማንኛውም የነቢይነት ስጦታ እንደሌለው ተራ ሰው ሁሉ ራሱንም ሆነ ሌሎችን ማዳን የማይችል፤ ደዌውንም በመፍራት የሚርድ ሰው ነበር፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የለምፅን ደዌ መፈወስ ብቻ ሳይሆን በበሽታው የሚሠቃዩትን ሰዎች በመዳሰስም ጭምር አምላካዊ ፍቅሩን ይገልፅ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ ተጽፏል፡-
“ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ ተንበረከከና፦ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው። ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፦ እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው። በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀውና ነጻ። በብርቱም ተናግሮ ወዲያው አወጣው፤ ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ አለው። እርሱ ግን ሲወጣ ብዙ ሊሰብክና ነገሩን ሊያወራ ጀመረ፥ ስለዚህም ኢየሱስ ተገልጦ ወደ ከተማ መግባት ወደ ፊት ተሳነው፥ ነገር ግን በውጭ በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ከየስፍራውም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።” (ማርቆስ 1፡40-45)
በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ሌላ አስደናቂ ታሪክ እናነባለን፡-
“ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ። ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤ እነርሱም እየጮኹ፦ ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ። አይቶም፦ ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው። እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ። እርሱንም፦ ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው።” (ሉቃስ 17፡11-19)
ጌታ ኢየሱስ እነዚህን ለምፃሞች ሳይዳስስ በቃሉ ብቻ ከፈወሳቸው በኋላ ከአሥሩ አንዱ ብቻ ለምስጋና ወደ እርሱ በመመለሱ ምክንያት በዘጠኙ ደስ አለመሰኘቱን ሲናገር እንመለከታለን፡፡ ሰውየው በእግሩ ስር ወድቆ ለአምላክ የሚገባውን ክብር ሲሰጠው መቀበሉና እርሱን ማመስገን እግዚአብሔርን ማመስገን መሆኑን መናገሩ የኢየሱስን አምላክነት ከሚያሳዩ የአዲስ ኪዳን ማስረጃዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስ ለምፃሞችን መፈወስ ብቻ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱም ለምፃሞችን እንዲፈውሱ ኃይልን ሰጥቷቸዋል፡-
“አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። … ሄዳችሁም፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ።” (ማቴዎስ 10፡1፣ 7)
ደቀ መዛሙርቱ ይህንን ሥልጣን ሲለማመዱና በኢየሱስ ስም ድውያንን ሲፈውሱ፣ አጋንንትንም ሲያስወጡ በብዙ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ እናነባለን (ማርቆስ 6፡7፣ 13፣ ሉቃስ 9፡1-2፣ 49-50፣ የሐዋርያት ሥራ 3፡1-16፣ 26፣ 4፡29-33፣ 5፡12-16፣ 9፡32-42፣ 13፡6-12፣ 16፡16-18፣ 1፡10-20) ከአምላክ በስተቀር ደዌን ለመፈወስ የሚያስችል ሥልጣን መስጠት የሚችል ማነው? ከአምላክ ስም በስተቀር ድውያንን ሊፈውስ የሚችል የማን ስም ነው?
ጌታ ኢየሱስ ለምፅን የመፈወስ ኃይል እንዳለው በቁርኣንም ውስጥም ጭምር ተፅፏል፡-
“ወደ እሥራኤልም ልጆች መልክተኛ የደርገዋል፤ (ይላልም) ፡-እኔ ከጌታዬ ዘንድ በታምር መጣኋችሁ። እኔ ለናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ፤ በርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል። በአላህም ፈቃድ ዕዉር ሆኖ የተወለደን፥ ለምጸኛንም፥ አድናለሁ፤ ሙታንንም አስነሳለሁ። የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት።” (ሱራ 3፡49-50)
በእስላማዊ ምንጮች መሠረት እንኳ ሙሐመድ ተከታዮቹን ለምፅ ከያዘው ሰው እንዲሸሹ በጥብቅ ያዘዘና ራሱም በፍርሃት ሲኖር የነበረ ሲሆን ኢየሱስ ግን ለምፃሞችን የሚያነፃ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ (ለሙስሊም ወገኖቻችን ግንዛቤ ስንል እንጂ ዒሳና ጌታ ኢየሱስ አንድ ናቸው የሚል አቋም እንደሌለን አንባቢያን እንዲገነዘቡልን እንፈልጋለን፡፡)
ውድ ሙስሊሞች፤ ታድያ ሙሐመድ ከኢየሱስ የተሻለ ሊሆን የሚችለው በምን መስፈርት ነው? ራሱንም ሆነ ተከታዮቹን ማዳን የማይችል በበሽታ ፍርሃት ተሸብቦ የኖረውን እንደኔና እንደናንተ ያለ ደካማ ሰው ከመከተልና በቃሉ ብቻ በሽተኞችን መፈወስ የሚችል፣ ለተከታዮቹም እንዲፈውሱ ሥልጣንን ያጎናፀፈውን ጌታ ከመከተል የትኛውን ትመርጣላችሁ? ሙሐመድ እንኳንስ ከጌታ ኢየሱስ ጋር ለንፅፅር ሊቀርብ ይቅርና የጌታ ሐዋርያ የሆነውን የቅዱስ ጳውሎስን የጫማ ጠፍር እንኳ ለመፍታት የሚበቃ ሰው አልነበረም፡፡
————————-
[1] Sahih al-Bukhari, Volume 7, Book 71, Numbers 608
[2] Sunan Abu Dawud, Book 8, Number1549