የዐዲስ ኪዳን ቀኖና ተኣማኒነት – ክፍል ፩

የዐዲስ ኪዳን ቀኖና ተኣማኒነት

ክፍል ፩

ወንድም ሚናስ


ብዙ ክርስቲያን ያልኾኑ የእምነት ቡድኖች እና ግለሰቦች፣  የቤተክርስቲያን አባቶች በዘፈቀደና ከግል የእምነት አቋማቸው ጋር ተስማሚ የኾኑትን አኹን በእጃችን ላይ የሚገኙትን ኻያ ሰባት የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት  በመምረጥ፣ ሌሎችን መጻሕፍት ከቀኖና ውጪ አድርገዋል፤ የሚል ክስ ሲያቀርቡ መስማት በእጅጉ የተለመደ ኾኖአል[1]፤ እኛም በዚህ መጣጥፍ የዚህን ክስ መሠረተ ቢስነት የምንመለከት ይኾናል። 

“ቀኖና” የሚለው ቃል κανών “ካኖን” ከሚለው የጽርእ ቃል የመጣ ሲኾን፣ ሕግ፣ ሥርዐት፣ ደንብ፣ ፍርድ፣ ቅጣት፣ መጠን፣ ልክ ማለት ነው[2]፤ “ቀኖናዊ የዐዲስ ኪዳን” መጻሕፍት ስንል ደግሞ፣ አንድ አማኝ ክርስቲያናዊ ሕይወቱን ለመለካት፣ የነገረ መለኮት ትምህርቱ ትኽክል መኾኑንና አለመኾኑን፣ ለመለየት የሚያገለግሉ፣ መጻሕፍት አምላካውያት ወይም በእስትንፋሰ መለኮት የተጻፉ መጻሕፍት ማለታችን ነው። የቃሉ ፍቺ ይህ ከኾነ ዘንዳ፣ የዐዲስ ኪዳን ቀኖና ማዘጋጀት ስለምን አስፈለገ? ቀኖናው በምን መሥፈርት ተለካ? የሚለውን ደግሞ በተከታይነት እንቃኛለን።  አስቀድመን ግን ቤተክርስቲያን ፣ የዐዲስ ኪዳን ቀኖና ለማዘጋጀት የተገደደችበትን፣ ሦስት ተግዳሮቶችን በእማኝነት እናቀርባለን።

1ኛ. የዐይን እማኞች በሕይወት አለመኖር

 ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በአካለ ሥጋ ዐብረው የነበሩ ሐዋርያት፣ ሐዋርያት አርድእት፣ እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በዐጸደ ሥጋ እስካሉ ድረስ፣ አከራካሪ የኾኑ የትኛውም የነገረ መለኮት ጒዳዮች በቀላሉ እልባት ሊሰጣቸው ይችላል። ለዚህም  በ 49 ዓ.ም ገደማ ላይ የተደረገው “የኢየሩሳሌሙ ጒባኤ”  ቊልፍ ማሳያ ነው፤ በዘመኑ አይሁዳዊ ያልኾኑ አማኒያን ይድኑ ዘንድ፣ የሙሴን ሥርዐት መፈጸም አለባቸው ወይም የለባቸውም፣ የሚል ክርክር በሕዝብ ክርስቲያኑ ዘንድ ተፈጥሮ ነበር፤ ጳውሎስ እና በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት እግዚአብሔር በአሕዛብ (እስራኤላዊ ባልኾኑ) አማኒያን ላይ እያደረገ ያለው ድንቅ ነገር፣ ከሐዋርያት ጋር ከተመካከሩ በኋላ፣ አሕዛብ የቤተክርስቲያን አካል እንደኾኑ፣ ነገር ግን ለወንጌል እንቅፋት እንዳይፈጥር፣ በጣዖት ከረከሰ ነገር፣ ከዝሙት ርኩሰት፣ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ ከመብላትና ደም ከመመገብ እንዲርቁ በማሳሰብ፣  ጒባኤው ፍጻሜውን አግኝቶአል(ሐዋ.15፥1-21)።  ነገር ግን በጌታችን አገልግሎት ዘመን በአካለ ሥጋ ዐብረውት የነበሩ ሐዋርያት፣  በተለያዩ ምክንያቶች በአካለ ሥጋ ሊኖሩ አይችሉም፤ ስለዚህ አማኒያን ምን ማመን እንዳለባቸው፣ ክርስቲያናዊ ሕይወታቸውንም በምን መልኩ መምራት እንደሚገባቸው፣ ሊያዝዛቸው፣ ሊመራቸው የሚችል፣ ዘመን ተሻጋሪ መለኮታዊ መጻሕፍት ያስፈልጋቸዋል፤ በዚህም ምክንያት ቀኖናው እንዲዘጋጅ ዐቢይ ምክንያት ኾኖአል። 

2. በዘመኑ የነበረው የክርስቲያኖች ስደት

በዘመነ ሄሮድስ የዮሐንስ ወንድም የኾነውን፣ ቅዱስ ያዕቆብን በመግደል የተጀመረው(ሐዋ 12፥2) የክርስቲያኖች ስደት፣ በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ቄሣር ተባብሶ ቀጥሎ ነበር፤ ንጉሡም ክርስቲያኖች ምንም ዐይነት ቅዱሳት መጻሕፍት በእጃቸው፣ በቤታቸው፣ እንዲኖር አይፈቀድም ነበር፤ ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትንም ዶግ ዐመድ አድርጐአል፤ እናም ራሳችንን በ303 ዓ.ም እንደነበረ ክርስቲያን እናስብና፣ የዲዮቅልጥያኖስ ወታደር እቤታችን ቢበረብርና፣ የ“ሄርማስ ኖላዊ”[3] መጽሐፍን አገኘ እንበል፤ መጽሐፉን መያዝ የመንግሥቱን ሕግ የሚጻረር ነውን ? የሔርማስ ኖላዊ መጽሐፍ ምንም እንኳን የኑፋቄ ይዘት ባይኖረውም፣ በእስትንፋሰ መለኮት የተጻፈ ነውን ? 

 3. የሐሰት ትምህርት እና የእምነት ቡድኖች በእጅጉ መሠራጨታቸው 

የስሕተት ትምህርቶች እና የሐሰት ሰነዶች፣ በጳውሎስ ዘመን የነበሩ ሲኾን፣ በተሰሎንቄ የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን፣  “የጌታ ቀን መጥቶአል” (2ኛ ተሰ 2፥2) በማለት የሚያስተምሩ ሐሳዌ መምህራን መኖራቸውን ከሐዋርያው መልእክት ደርሶአት ነበር፤ ጳውሎስ ይህ ትምህርት ጤናማ አለመኾኑን በማሳየት፣ ምዕመኑን ከተኵላ መታደግ ችሎአል፤ ነገር ግን አስቀድመን እንዳነሣነው፣  እንደ ጳውሎስ ያሉ ሐዋርያት በአካለ ሥጋ በሌሉበት ኹኔታ፣ የተሰሎንቄ ቤተክርስቲያን እንደገጠማት ዐይነት ጠማማ ትምህርትን  ሊያቀና፣  አማኒያኑንም በቀናች እምነት ሊያጸና፣ የሚችል መመሪያ ማግኘት ግድ ይላል፤ በተለይ በኹለተኛው ክፍለ ዘመን የተነሡት ኖስቲክ የተባሉት የኑፋቄ የእምነት ቡድን፣ በስመ ሐዋርያት፣ ዐያሌ ጽሑፎችን ከማዘጋጀታቸው አንጻር፣ ገለባውን ከእንክርዳዱ ለመለየት፣ ቤተክርስቲያን ቀኖና ለማዘጋጀት የተገደደችበት ሌላኛው ምክንያቷ ነበር። 

 ሦስቱ መመዘኛዎች 

ቤተ ክርስቲያን የትኞቹ የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ቀኖናዊ  ሥልጣን እንዳላቸው የተቀበለችባቸው፣ ኢ-አማኒያን እንደሚሉት በዘፈቀደና ከራሳቸው የእምነት አቋም ጋር ተስማሚ ኾነው ስላገኛቸው አይደለም፤ ይልቁንም ተኣማኒ የኾኑ ሦስት መለኪያዎችን በማቅረብ ነበር፤ እነርሱም፦ ሐዋርያዊ፣ ርቱእ፣ ኵላዊ ናቸው [4]። ምንም እንኳን እነዚህ ሦስቱ መመዘኛዎች በይፋዊ የቤተ ክርስቲያን  መግለጫ ባይነገሩም፣ ታሪካዊ ዳራውን ስንቃኝ፣ በግልጽ የምንረዳው ሐቅ ኾኖ እናገኘዋለን። ትኽክለኛነታቸው አስመልክቶ ጥያቄ የተነሣባቸው መጻሕፍት ደግሞ፣ “ሰብዓቱ መልእክታት” [5]  በሚባሉት መጻሕፍት ዙሪያ ላይ ብቻ ሲኾን፣ የቀሩት  መጻሕፍት ላይ እዚህ ግባ የሚባል ጥያቄ  አልነበረም[6]። 

ልብ ሊባል የሚገባው ሌላው ነጥብ፣ እነዚህ መመዘኛዎች ቀኖናውን አልፈጠሩም፤ አላበጁም፤  ወይም ለመጻሕፍቱ መለኮታዊ ሥልጣንን አላቀናጁም፤ ሐዋርያት በክርስቶስ የተሰጠ  ሐዋርያዊ ሥልጣን አላቸውና፣ በመጻሕፍቶቻቸው ላይ  ቤተክርስቲያን ክርክር አልነበራትም፤ የቤተክርስቲያን መሠረቷ የሐዋርያት ትምህርት ስለኾነ፣ የጽሑፋቸውን ቅቡልነት ለማጽናት የቤተክርስቲያን ድጋፍ አያስፈልጋቸውም። 

1ኛ. ሐዋርያዊ

አንድ ሰነድ የዐዲስ ኪዳን የቀኖና አካል ለመኾን የመጀመሪያ መስፈርቱ፣ የመጽሐፉ ወይም የመልእክቱ ጸሓፊ ማንነት ነው፤ በዚህ ረገድ፣  አራቱ ወንጌላት፣ ዐሥራ ሦስቱ የጳውሎስ መልእክታት፣ 1ኛ ጴጥሮስ እና 1ኛ ዮሐንስ ያለ አንዳች ክርክር እና ተቃውሞ ተቀባይነት ያገኙ መጻሕፍት እና በየትኛውም የቤተክርስቲያን ታሪክ ክርክር ያልነበረባቸው መጻሕፍት ነበሩ፤ ከዚህ የምንረዳው ነገር ሉቃስ እና ማርቆስ ምንም እንኳን ሐዋርያት ባይኾኑም፣ ከሐዋርያት ጋር የነበራቸው ቅርበት የመጻሕፍቶቻቸው  ተቀባይነት አጽንቶታል።  የዕብራውያን መልእክት የጸሓፊ ማንነት በመልእክቱ ላይ ባለመገለጹ፣ የምዕራቧ ቤተክርስቲያን የቀኖና አካል አድርጋ ለመቀበል የተቸገረች ቢኾንም፣ የምሥራቋ ቤተክርስቲያን ግን የጸሓፊውን ማንነት ጳውሎስ ነው በማለት ተቀብላው ነበር፤ ከሐዋርያት አበው ጀምር የነበሩ የቤተክርስቲያን አባቶችም ከመልእክቱ ዐያሌ ምንባባትን አጣቅሰው ጽፈዋል። 2ኛ ጴጥሮስ ከ 1ኛ ጴጥሮስ በሰዋስው እና በሥነ ጽሑፍ ይዘቱ ልዩነት ስላለው፣ ቀኖናዊ መኾኑን ለመቀበል ቤተክርስቲያን ተቸግራ ነበር ፤ ኾኖም ግን ጴጥሮስ መልእክቱን በሌላ ጸሓፊ መጻፉ ከተረጋገጠ በኋላ(1ጴጥ. 5፥12) የሥነ ጽሑፍ ይዘቱን አስመልክቶ የነበረው ክርክር አብቅቶአል። የይሁዳ መልእክትም ከ ከአዋልድ መጻሕፍት በማጣቀሱ በመጽሐፉ ቀኖናነት ዙሪያ ጥያቄ ተነሥቶ ነበር፤ ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስም ቢኾን፣ ለትምህርት ማጠናከሪያነት ከአረማውያን ጽሑፍ ሐሳቡን አሰናዝሎ መጥቀሱ ስለተስተዋለ (ሐዋ.17፥23)፣ የመልእክቱ አከራካሪነት እልባት አግኝቶአል ። 

የራእይ መጽሐፍ ቀኖናነት እስከ ኋለኞቹ መቶ ክፍለዘመን ድረስ ምንም ዐይነት ጥያቄ ያልነበረበት ሲኾን፣ ከጊዜ በኋላ በምሥራቅ አብያተክርስቲያናት ዘንድ፣  የመጽሐፉ ቅቡልነት ላይ የተወሰነ ክርክር ቢኖርም፣ ይህ ዐጪር ጊዜ የቈየ እና በዅሉም አብያተክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መጽሐፍ ነበር።  የሐዋርያት መጻሕፍትን እንደ መለኮታዊ ቃል  አድርጐ መቀበል እንደሚገባ፣ በዐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ የሰፈረ እውነት ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸውን ዅሉ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስታውሳቸው እና እንደሚመራቸው ተናግሮአል(ዮሐ. 14፥26)፤ ሐዋርያት የሚያስተምሩት በክርስቶስ ሥልጣን ነው (1ቆሮ.  14፥37፤    

1ቆሮ7፥10-12፤ ገላ. 1፥1፤ 1ተሰ. 2፥13፤ 2ጴጥ 3፥2፤ ራእይ 1፥1-2) ቤተክርስቲያን የሐዋርያትን ትምህርት እንደ ክርስቶስ ንግግር አድርጋ ትቈጥራለች፤ ሐዋርያው ጳውሎስ የሉቃስን ወንጌል ከዘዳግም መጽሐፍ ጋር በማሰናዘል ጠቅሶአል(1ኛ ጢሞ.5፥18)፤ ሐዋርያውም  የክርስቶስ ትእዛዝ ከተናገረ በኋላም(1ቆሮ 7፥10) የራሱን ትእዛዝ በማስቀመጥ (1ቆሮ 7፥12) ምእመናን ከክርስቶስ ትእዛዝ ጋር የርሱም ትምህርት በእኵልነት ማየት እንዳለባቸው አመልክቶአል። 

ከዐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ውጪም በኹለተኛው ክፍለዘመን የነበሩት የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ዐያሌ ምንባባት ከዐዲሳት መጻሕፍት ማጣቀሳቸው እና  ለሐዋርያት መጻሕፍት ዕውቅና መስጠታቸው ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ነው። 

  • ፓሊካርፐስ (155 ዓ.ም) የሰምርኔስ ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ የነበረውና የሐዋርያት ዮሐንስ ደቀመዝሙር የኾነው ፓሊካርፐስ የጳውሎስን መጻሕፍት “ቅዱሳት” ሲል ይጠራቸዋል(To the Philippians 12.1)።
  • ·ቀለምንጦስ ዘሮም(96 ዓ.ም)  እግዚአብሔር ክርስቶስን፣ ክርስቶስ ደግሞ ሐዋርያትን እንደላከ ተናግሮአል((First Epistle of Clement 47:1–3)። 
  • አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ (107 ዓ.ም)  ሐዋርያት የክርስቶስ አንደበት መኾናቸው ዘክሮአል(To the Magnesians 7.1)። 
  • ዮስጢኖስ ሰማዕት(165 ዓ.ም) ሐዋርያት በእግዚአብሔር የተላኩ መኾናቸውን አትቶአል(First Apology 39)።
  • ሔሬኔዎስ(200 ዓ.ም)  ሐዋርያት ለሕይወታችን መርሕ እና አዕማድ የኾነውን ወንጌል እንደጻፉልን ገልጾአል(Against Heresies 3.1.1)።

የአንድ ሰነድ ቀኖናዊነት ለመቀበል ሐዋርያዊ መመዘኛ መቀመጡ፣ ሐሳዌ መጻሕፍትን ለመለየት አንዱ መሣሪያም ነበር፤ ለምሳሌ የሙርትሪያን ቀኖና ላይ የሎዶቅያ መልእክት(ቈላ 4፥16)  በመባል የሚታወቅ ሰነድ ነበር፤ ምንም እንኳን ይህ ሰነድ በትምህርቱ ርቱእ ቢኾንም፣ በሐዋርያት የተዘጋጀ አለመኾኑ ስለታወቀ፣ ተቀባይነቱ ውድቅ ኾኖአል። 3ኛ ቆሮንቶስ በመባል የሚታወቅ ሌላኛው ሰነድ፣ ጳውሎስን በእጅጉ የሚያወድስና ምንም የስሕተት ትምህርት የሌለው መጽሐፍ ቢኾንም፣ በሐዋርያት ያልተዘጋጀ ሐሰተኛ ሰነድ መኾኑ ከታወቀ በኋላ በቤተክርስቲያን ጒባኤ እንዳይነበብ ተደርጐአል፣ ጸሓፊውም ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ታግዶአል[7]።  ሰራፒዮን ዘአንጾኪያ የተባለ የቤተክርስቲያን አባትም “ራእየ ጴጥሮስ” የተባለ መጽሐፍ በሐዋርያው ጴጥሮስ የተዘጋጀ መጽሐፍ አድርጐ ይቈጥር  የነበረ ቢኾንም፣ መጽሐፍ ሐሳዌ ሰነድ መኾኑን ሲረዳ በቤተክርስቲያን ዅሉ እንዳይነበብ አድርጐአል[8]። በአጠቃላይ ቤተክርስቲያን “ሰብዓቱ መልእክታት” በሚባሉት ላይ የተወሰነ ክርክር የነበራት ቢኾንም፣ በሚከተሉት መጻሕፍት ላይ ግን ምንም ዐይነት ክርክር ኾነ ጥያቄ ተነሥቶ አያውቅም። 

  • አራቱ ወንጌላት(ማቴዎስ፣ ሉቃስ፣ ማርቆስ፣ ዮሐንስ)
  • የሐዋርያት ሥራ
  • ዐሥራ ሦስቱ የጳውሎስ መልእክት 
  • 1ኛ ጴጥሮስ 
  • 1ኛ ዮሐንስ 
  • የዮሐንስ ራእይ

2ኛ. ርቱእ

ኹለተኛው መስፈርት በቀኖናነት ለመካተት የቀረበው መጽሐፍ በይዘቱ ርቱእ መኾን አለበት፤ ይኸውም ትምህርቱ አስቀድመው ቅቡልነት ካላቸው  መጻሕፍት ጋር  ስምም(consistent) መኾን ይጠበቅበታል፤ በዚህ ረገድ ቤተክርስቲያን በ50 ዓ.ም ገደማ የተጻፉት የጳውሎስ መልእክታት(32,471 የጽርእ ቃላት)  እና የማርቆስ ወንጌል(11,314) አላት፤ እነኚህ ዐሥራ አራት መጻሕፍት፣  138,213 ከኾነው የዐዲስ ኪዳን ቃላት፣  43,785 ከመያዛቸው አንጻር ቤተክርስቲያን የትኛው መጻሕፍት በትምህርቱ ቀናኢ ነው ወይም አይደለም ለማለት በቂ ምስክር መኾን ይችላሉ፤ የሉቃስ ወንጌል(19,497 ቃላት) ከሐዋርያት ሥራ በፊት ስለተጻፈ እና የሐዋርያት ሥራ(18,472 ቃላት) ጳውሎስ በሸንጐ ከመቅረቡ በፊት ያለው ኩነት ላይ ትረካው ስለሚያቆም፣  ከ70 ዓ.ም በፊት የተጻፈ፣ እንዲሁም መለኪያ ከኾኑት መጻሕፍት መኻከል መኾኑ አያጠያይቅም፤ ስለዚህ እነኚህ ዐሥራ ስድስት መጻሕፍት 138,213 ከኾኑት የዐዲስ ኪዳን ቃላት፣ 81,754 ይዘዋል፤ ይኸውም በቀመር ስናስቀምጠው 59% የሚኾኑት መጻሕፍት አስቀድመውም ቅቡልነት ያገኙ እና ሌሎች መጻሕፍትን ለመዘዘን በቂ መለኪያ ነበሩ። ቤተክርስቲያን ሙራቶሪያን እና ግኖስቲክ የተባሉትን የስሕተት የእምነት ቡድኖችን አውግዛ የለየቻቸው፣ አስቀድሞውም እነዚህ ርቱእ መጻሕፍት በእጇ ስለነበሩ ነው። 

3ኛ. ኵላዊ

ሦስተኛው መመዘኛ የኾነው በቀኖናነት ለመካተት የቀረቡት መጻሕፍት፣ በዅሉም አብያተክርስቲያናት እና ምእመናን፣ እሙን እና ቅቡል መኾን አለባቸው፤ መጻሕፍቱ በተወሰነ አካላትና የእምነት ቡድኖች ብቻ  የሚታወቅ ከኾነ፣  ቅቡልነት አይኖረውም፤ በዚህ ረገድ የዕብራውያን መልእክት እና የዮሐንስ ራእይ ጥሩ ማሳያ ናቸው፤ ኹለቱም መጻሕፍት በኹሉም አብያተክርስቲያናት ከመታወቃቸው አንጻር በቀላሉ በቀኖናነት ሊካተቱ ችለዋል። 

 የቶማስ “ወንጌል” ሲመዘን

የቤተክርስቲያን አባቶች ከቀኖናነት ኾን ብለው አስወግደዋቸል ከሚባሉት መጻሕፍት መኻከል በብዛት የሚጠቅሰው የቶማስ “ወንጌል”፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ሦስት መለኪያዎች ያልፍ እንደኾን እንመልከት። 

1ኛ.በዘርፉ ያሉ ሊቃውንት እንደሚናገሩት፣ መጽሐፉ  ከ175 እስከ 180 ዓ.ም ገደማ ከመጻፉ አንጻር፣ በሐዋርያው ቶማስ ያልተጻፈ መኾኑ ግልጽ ነው፤ ስለዚህም  “ሐዋርያዊ” መስፈርትን ሊያሟላ አይቻለውም። 

2ኛ. ሴት ልጅ መግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ፣ ወንድ መኾን አለባት፤ የሚለው የኑፋቄ ትምህርቱ ከ “ርቱእ” መሥፈርትም ይወድቃል።

3. ለዘመናት ሳይታወቅ በ1945 ዓ.ም የተገኘበት ምክንያት፣ ተነባቢቱ ያነሰ እና በመላዋ ቤተክርስቲያን ስለማይታወቅ ነበር፤  አርጌንስ እንዳለው የቶማስ ወንጌል በቤተክርስቲያን ዘንድ አንዳች ቅቡልነት እንዳልነበረው ነግሮናል፤ ስለዚህ “ኵላዊ” የሚለውንም መስፈርት አይሞላም ማለት ነው።

ማጠቃለያ

ቤተክርስቲያን በሊቃውንቱ ዘንድ “ዋና” ተብለው በሚጠሩት ኻያ አንድ መጻሕፍት ላይ በየትኛውም ዘንድ ክርክር ያልነበራትና እንደተጻፉ ቅቡልነት ያገኙ መጻሕፍት ሲኾኑ፣ የተወሰነ ክርክር የነበረባቸው “ሰብዓቱ መልእክታት” ላይ ብቻ ነበር፤ ቤተክርስቲያንም ከላይ በዘረዘርናቸው መለኪያዎች፣  የትኞቹ መጻሕፍት፣  አምላካውያት መኾናቸውን መለየት ተችሎአታል፤  አንድ መጽሐፍ “ሐዋርያዊ” ወይም “ርቱእ” መሥፈርትን ሊያልፍ ቢችል እንኳ (ለምሳሌ ፦ ለቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ከተላኩት አራቱ ደብዳቤዎች ኹለቱ) በመላዋ ቤተክርስቲያን ካልታወቀ፣ “ኵላዊ” የሚለውን መለኪያ አያልፉምና ውድቅ ይኾናል፤ ሌላኛው መጽሐፍ ደግሞ “ርቱእ” እና በዅሉም ቤተክርስቲያን የተሠራጨ “ኵላዊ” ቢኾን እንኳ(ለምሳሌ የሔርማስ ኖላዊ መጽሐፍ)፣ በሐዋርያት አልተጻፈምና እስትንፋሰ መለኮት ተደርጐ አይቈጠርም። በድጋሚ በእነዚህ ሦስቱ መሥፈርቶች፣  ቤተክርስቲያን የትኞቹ መጻሕፍት እግዚአብሔራዊ መኾናቸውን መዝና ተቀብላለች።


ዋቢ ምንጮች

[1] ለምሳሌ፦ Bart Ehrman, Lost Scriptures: Books that did not Make it into the New Testament; እንዲሁም  Dan Brown, The DaVinci Code 

[2] መጽ.ሰው.ወግ.ወመ.ቃላት ሐዲስ ገጽ 799-800

[3] በእንግሊዝኛው The Shepherd of Hermas 

[4] በእንግሊዝኛው ፦ apostolicity, orthodoxy, እና  universality በመባል ይጠራሉ። 

[5] “ሰብዓቱ መልእክታት” ወይም General epistles የሚባሉት፦ የዕብራውያን እና የያዕቆብ መልእክት፣ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ፣ 1ኛ 2ኛ 3ኛ ዮሐንስ ናቸው። 

[6] William D. Mounce. Why I Trust the Bible: Answers to Real Questions and Doubts People Have about the Bible:  p.125

[7] Tertullian, On Baptism

[8] Eusebius, Ecclesiastical History 6.12.3.


መጽሐፍ ቅዱስ