እስላም እና ክርስትና ንጽጽራዊ አቀራረብ – ለዶ/ር ሙሐመድ ዓሊ አልኹሊ የተሰጠ ምላሽ – ክፍል ሦስት

እስላም እና ክርስትና – ንጽጽራዊ አቀራረብ 

የመጽሐፍ ሒስና ግምገማ

ዘላለም መንግሥቱ

ደራሲ፥ ዶ/ር ሙሓመድ ዓሊ ኣልኹሊ

ትርጉም፥ አይታወቅም

አሳታሚ፥ ሑዳ ፕሬስ ሊሚትድ

የገጽ ብዛት፥ 91 

የኅትመት ዘመን፥ 1989

ክፍል ሦስት

ባለፉት ሁለት ክፍሎች በዶ/ር ዓሊ ኣልኹሊ የተጻፈውን እስላምና ክርስትና (ንጽጽራዊ አቀራረብ) የተሰኘ መጽሐፍ በማሔስ ጸሐፊው መጽሐፍ ቅዱስን ስሕተት ሊያሰኝ የጣረበትን ነጥቦች ማየት ጀምረን ነበር። ያንን በመቀጠል በዚህ ክፍል ሌሎች የጸሐፊውን ነጥቦች ማየት እንቀጥላለን።

ትክክለኛነት?

‘ትክክለኛነት’ በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ኢየሱስ የተናገረው በአራማይስጥ ቋንቋ ሲሆን በዚያ ቋንቋ የተጻፈ ወንጌል አለመኖሩና በአንጻሩ ደግሞ የሙሐመድ ቋንቋ ዐረብኛ ሆኖ የተናገረው በቋንቋው መገኘቱን ይዘግባል።

እዚህ ላይ ሁለት ሰዎች ከፊታችን አሉ፡፡ በአንድ በኩል በአራማይክ (የሶርያ ቋንቋ) ተናጋሪ የነበሩና ስለሳቸው አንድም ነገር በአራማይክ ያልተዘገበ ኢየሱስ ሲሆኑ፤ እሳቸውን አስመልክቶ ዛሬ በእጃችን ያለው መረጃ የጠፉ ኦርጂናሎች የትርጉም ቅጂ ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዐረብኛ ተናጋሪ የነበሩና ስለሳቸው የቀረቡ ዘገባዎች በሙሉ ነቢዩ ይናገሩ በነበረው ዐረብኛ ቋንቋቸው ተጠናቅረው የምናገኛቸው ሙሐመድ ናቸው፡፡

እንግዲህ ጸሐፊው እንደ ንዑስ ርዕሱ ቃል ‘ትክክለኛ’ ሊል የፈለገው ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች በአራማይስጥ ያለመጻፋቸውንና የሙሐመድ ደግሞ በዐረብኛ ተጽፈው መገኘታቸውን ነው። ጸሐፊው ቋንቋን ብቻ እንጂ ዘመኑን የዘነጋ ይመስላል። በአራማይስጥ የተጻፈ ወንጌል ኖሮ ኦሪጂናሉ ጠፍቶአል ካለ ጸሐፊው እየቃዠ ነው። አራማይስጥ የንግግር ቋንቋ መሆኑና ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ይናገሩ የነበሩት በአራማይስጥ መሆኑ እውነት ነው።

አራማይስጥ ወይም ሱርስጥ ከዚያን ዘመን አራት መቶ ዓመታት በፊት በነበሩት ጊዜያት የአሶርንና የባቢሎንን ወረራ ተከትሎ የተስፋፋ ዋና ቋንቋ ነበረ። ከዚያ የትልቁ እስክንድርን ወረራ ተከትሎ ዋናው ቋንቋ ግሪክ ወይም ጽርዕ ሆነ። የሮም መንግሥት ሲገዛም እንኳ ሮማይስጥ የመንግሥት ሥራዎች ቋንቋ ሆነ እንጂ የስነ ጽሑፍንና የፍልስፍናን ቋንቋ ሊተካው አልቻለም። ይህ የሆነው የላቀ ቋንቋ ስለሆነ ነው። ስለዚህ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትም በግሪክ ቋንቋ መጻፋቸው ትክክልና ተገቢ እንጂ ስሕተት የለበትም። አራማይስጥ በዘመኑ የጽሑፍ ቋንቋ አልነበረም። ዕብራይስጥም ራሱ እንኳ በዚያን ዘመን ክልላዊና ሃይማኖታዊ የጽሑፍ ቋንቋ ነበር እንጂ ብሔራዊነት ያለው የጽሁፍ ቋንቋ አልነበረም። አይሁድም ራሳቸው በንግግርና በመግባቢያነት የዕብራይስጥ ሳይሆን የአራማይስጥ ተናጋሪዎች ነበሩ። ዕብራይስጥን የሚያነብቡና የሚናገሩ እንደ ፈሪሳውያን ያሉቱ ቀናተኛ ሃይማኖተኞች ብቻ ነበሩ።

አዲስ ኪዳን በአራማይስጥ ሳይሆን በግሪክ የተጻፈ መሆኑ ከብዙ አንጻር ጠቃሚ ነው። አንደኛ፥ የዘመኑ ዋና መግባቢያ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዮቹ 200 ያህል ዓመታት በአገልግሎት የቆየ መሆኑ ለክርስትና መስፋፋት ጠቃሚ አስተዋጽዖ አድርጎአል። ሁለተኛ፥ የግሪክ ቋንቋ ያደገና የበሰለ ብቻ ሳይሆን የደረጀ ቋንቋ መሆኑ ለጠንካራ ክርስቲያናዊ ስነ መለኮት ጅማሬና ዕድገት አስተዋጽዖ አበርክቶአል። ሦስተኛ፥ ለቤተ ክርስቲያንም አንድነት ተገቢ ድርሻ ኖሮታል። የአዲስ ኪዳን ቋንቋ ዕብራይስጥ ቢሆን ኖሮ የአይሁድ ተጋቦት አሕዛብን ሁለተኛ ዜጋ ባደረጋቸውም ነበር።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ዋናው ነገር የአዲሱ ኪዳን ቋንቋ ሳይሆን መልእክቱ ነው። ወንጌሉን በአማርኛ ሰማን በቻይንኛ፥ በዐረብኛ ሰማን በፈረንሳይኛ ቋንቋው ሳይሆን የተላለፈው እውነት ነው ቁም ነገሩ። የእግዚአብሔር ቃል በአንድ ቋንቋ ተበይዶ የተቆለፈ ቃል አይደለም። ዋናዎቹን የዕብራይስጥ፥ የአራማይስጥ (ጥቂት የብሉይ ኪዳን ክፍሎች በአራማይስጥ ተጽፈዋል) እና የግሪክ ቋንቋ አውቀን በነዚህ ቋንቋዎች ብናነብብ ወይም በዘመናዊ ቋንቋ የተተረጎመልንን ብናነብብ መልእክቱ ሳይዛነፍ እናገኘዋለን። በመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች ማንበብ በጣም መልካም ቢሆንም እነዚያን አለማወቅ ደግሞ ጎዶሎነት አይደለም። ስለዚህ የኢየሱስ ቋንቋ አራማይስጥ ሆኖ በአራማይስጥ ወንጌል አለመገኘቱ ሊያስደንቅ አይገባም። ቀድሞ ኖሮ ግን አልጠፋም። ይህ ቅዠት ብቻ ሳይሆን ውሉን የሳተ ቅዠት ነው።

ተቃርኖዎች?

ቀጥሎ ‘ተቃርኖዎች’ በሚል ርዕስ ስር ዶ/ር ዓሊ እንዲህ ይላል፥

ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቃል ብትላቸውም አራቱ የሐዲስ ኪዳን ወንጌሎች በተመሳሳይ ሁነቶች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ልዩነቶች ያሳያሉ፡፡

በእስላም ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው ቁርኣን ግን አንዳች ውስጣዊ አለመጣጣምም ሆነ ተቃርኖ የለበትም፡፡

እንደ እግዚአብሔር የጠራ ቃል የትኛውን ነው የሚቀበሉት? ከአራቱ ተጻራሪ ወንጌሎች ጋር ሐዲስ ኪዳንን ወይስ ከማይናጋ ቋሚ ወጥነቱና የተሟላ ፍጹማዊ መጣጣሙ ጋር ቁርኣንን?

መቼም ምሳሌ አድርጎ በአንድም ስፍራ ተጨባጭ ነገር የማያቀርብ መሆኑ ባለፈው ክፍል እንደተመለከትነው አውቆ ለማወናበድ ወይም በጭፍን ለማምታታት ነው። እንጂ በወንጌላት ውስጥ እርሱ እንዳለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ልዩነቶች አለመኖራቸውን ዶክተሩም ሳያውቀው አይቀርም።

ያነሣቸውን ሁለት ነጥቦች ግን እንመልከት። አንዱ የወንጌላት ተቃርኖ ያለው ሲሆን ሁለተኛው የቁርኣን ተቃርኖ የሌለበት መሆን ናቸው። በመጀመሪያ የወንጌላትን “ተቃርኖ” እንይ። ወንጌላት፥ አራቱ ወንጌላት በአራት የተለያዩ ጸሐፊዎች የተጻፉ የጌታ ትምህርቶችና ታሪኮች ናቸው። አንዳንዶቹ ታሪኮች በአንዱ ወንጌል ብቻ ሲገኙ አንዳንዶቹ ደግሞ በአራቱም ይገኛሉ። የእግዚአብሔር ቃል እንዲጻፍ ዋናውን ሥራ የሠራው መንፍስ ቅዱስ መሆኑን እናስተውል። ቅዱሳን ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው ተናገሩት፤ 2ጴጥ. 1፥21። ይህ ሳይዘነጋ ታሪክ እንደ ተራኪውና እንደ ተመልካቹ መሆኑንም እናጢን። ጸሀፊው ከሚመለከትበት አንጻር የተጻፈ ነውና። አራት ምስክሮች ስለ አንድ ክስተት ሲናገሩ ቃል በቃልና ሐረግ በሐረግ ተመሳሳይ መሆን አለባቸው ብለን መጠበቅ የለብንም። ታሪኩና የታሪኩ ይዘት ግን አንድ መሆን ይጠበቅበታል። የዓይን ምስክሮች እዳኛ ፊት ቀርበው የሚናግሩት ቃል በቃልና ሐርግ በሐረግ አንድ መሆን አለበት ማለት ተላላንት ነው። ልክ እንደዚሁ አንዱ ወንጌል ውስጥ የተጻፈው ሌላው ውስጥ ስላልተጻፈ ያንን ልዩነት ብለን አንወስድም። ሁሉም ወይም ከፊሉ ጽፈውት ቢቃረን ግን ሊሰኝ ይችላል።

ለምሳሌ፥ ጌታ በሁለት ዓሣና በአምስት እንጀራ ብዙዎችን የመገበበት ታሪክ በአራቱም ወንጌላት ተጽፎአል፤ ማቴ. 14፤ ማር. 6፤ ሉቃ. 9፤ ዮሐ 6። አንዱ በሁለት ዓሣ ያለውን ሌላው በአሥራ ሁለት ዓሳ ካለ ተቃርኖአልና ይህንን ተቃርኖዎች ቢል እውነትነት ይኖረዋል። የመስቀሉ ስቃይ ሞቱና ትንሣኤውም በአራቱም ወንገላውያን ተዘግቦአል። አገላለጻቸው ፍጹም አንድ አይደለም። ልዩነት ግን የላቸውም። ቁርኣኑ ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከአራቱ አንዱ የጻፈውን እንኳ አይቀበልም። አራቱም ግን አንድ ነው ቃላቸው። አራቱም ወንጌላት አንዱ የሌላው ቅጅ እስኪመስል ወይም በፎቶ ኮፒ እንደተባዙ ተመሳሳይ ቢሆኑ አራት ወንጌላት ባልኖሩና ባላስፈለጉም ነበር።

ሁለተኛው የቁርኣን ተቃርኖና ግጭት የሌለበት መሆን ነው። እውን በቁርኣን ውስጥ ግጭትና ተቃርኖ የለም? ሁሉን ለማቅረብ መጽሐፍ ይወጣዋል፤ እንደ ዶ/ር ዓሊ ቁርኣን ተቃርኖና ግጭት አለበት ብቻ ብሎ ምሳሌ ሳይሰጥ ላለመተው ጥቂት እነሆ፤

ሀ) ፍጥረት በስንት ቀን ተፈጠረ? በ6? በ7? በ8?

ጌታችሁ ያ ሰማያትንና ምድርን በስድስት ቀናት ውስጥ የፈጠረ፥ በዐርሹም ላይ ራሱን ያደላደለ (አምላክ)ነው። ነገሮችን (ሁሉ) ያስተናብራል፥ ይመራል። ከርሱ ፈቃድ በኋላ ካልሆነ በቀር (የሚያማልድ) አንድም አማላጅ የለም። ጌታችሁ አላህ ይህ ነው። ስለሆነም (በብቸኝነት) አምልኩት። አትገለፁምን? 10፥3 (በተጨማሪ 7፥54፤ 10፥3፤ 11፥7፤ እና 25፥59 ተመሳሳይ አሳብ አላቸው።)

ይህ በ6 ቀን መፈጠሩን ይጠቅሳል። በ41፥9-12 ያሉት ቀናት ድምር ደግሞ 8 ይሆናል። 

9፥ በላቸው፦ እናንተ በዚያ ምድርን በሁለት ቀኖች ውስጥ በፈጠረው አምላክ በእርግጥ ትክዳላችሁን? ለርሱም ባላንጣዎችን ታደርጋላችሁን? ያ (ይህንን የሠራው) የዓለማት ጌታ ነው።

10፥ በርሷም ከበላይዋ የረጉ ጋራዎችን አደረገ፤ በርሷም በረከትን አደረገ፤ በውስጧም ምግቦችዋን (ካለፉት ሁለት ቀኖች ጋር) በአራት ቀናት ውስጥ፣ ለጠያቂዎች ትክክል ሲሆኑ ወሰነ።

11፥ ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ሆና ሳለች አሰበ፤ ለርሷም ለምድርም ወዳችሁም ሆነ ወይም ጠልታችሁ፣ ኑ፤ አላቸው። ታዛዦች ሆነን መጣን አሉ።

12፥ በሁለት ቀኖችም ውስጥ ሰባት ሰማያት አደርጋቸው፤ በሰማያቱም ሁሉ ነገሯን አዘጋጀ፤ ቅርቢቱንም ሰማይ በመብራቶች አጌጥን፤ (ከሰይጣናት) መጠበቅንም ጠበቅናት፤ ይህ የአሸናፊው፣ የዐዋቂው (ጌታ) ውሳኔ ነው።

በቁጥር 10 ያለው ቅንፍ ማብራሪያ ነው እንጂ በቁርዓኑ ውስጥ የሌለ ነው። የሳሂ ሙስሊም ማብራሪያ ደግሞ ፍጥረት ቅዳሜ ተጀምሮ በያንዳንዱ ቀን እየተፈጠረ አዳም በ7ኛው ቀን ዐርብ ተፈጠረ ይላል፤ (ምዕራፍ 1155፤ ሐዲስ ቁጥር 6707)። ሰባት ቀን ማለት ነው።

ለ) ሰው ከምንድርነው የተፈጠረው? ከፍትወት ጠብታ? ከሸክላና ከሚገማ ጥቁር ጭቃ? ከአፍር? ከረጋ ደም? ወይስ ከምንም?

3፥59 አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ፥ እንደ አዳም ብጤ ነዉ፤ ከዐፈር ፈጠረዉ፤ ከዚያም ለርሱ (ሰዉ) ሁን አለዉ፥ ሆነም።

16፥4 ሰውን ከፍትወት ጠብታ ፈጠረው፤ ከዚያም እርሱ ወዲያውኑ (ትንሣኤን በመካድ) ግልጽ ተከራካሪ ይሆናል። [በዚህ ክፍል ስለ ሌሎችም ነገሮች መፈጠር ስለሚናገር ስለ አዳም ይመስላል።]

19፥67 ሰዉ፣ ከአሁን በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲኾን፣ እኛ የፈጠርነዉ መኾኑን አያስታዉስምን? የዩሱፍ ዓሊ የእንግሊዝኛ ትርጉም፥ We created him before out of nothing ይላል። ከእመ ዐልቦ እንደማለት ነው።

15፥26 ሰውንም ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጥቁር ጭቃ በእርግጥ ፈጠርነው፡፡

96፥2 ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)።

አንድ ሰው[1] ይህንን አፈጣጠር ሲያብራራ ይህ የአፈጣጠር ደረጃ መሆኑን ተናግሮአል። ማለትም፥ አፈሩ አፈር፥ ጭቃው ሲለወስ፥ ሸክላው ሲደርቅ፥ የረጋው ደም ደም ከገባበት በኋላ ወዘተ፥ እያለ ሊያብራራ ሞክሯል።

ሐ) በሃይማኖት ማስገደድ አለ? ወይስ የለም? ወይስ እንደ አስፈላጊነቱ?

2፥256 በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡ ቅኑ መንገድ ከጠማማው በእርግጥ ተገለጠ፡፡ በጣዖትም የሚክድና በአላህ የሚያምን ሰው ለርሷ መበጠስ የሌላትን ጠንካራ ዘለበት በእርግጥ ጨበጠ፡፡ አላህም ሰሚ ዐዋቂ ነው፡፡

9፥3 (ይህ) ከአላህና ከመልክተኛዉ በታላቁ ሐጅ ቀን የወጣ አላህ ከአጋሪዎቹ ንጹሕ ነው፣ መልክተኛዉም (እንደዚሁ)፤ (ከክሕደት) ብትጸጸቱም እርሱ ለናንተ በላጭ ነዉ (ከእምነት) ብትሸሹም እናንተ አላህን የማታቅቱት መሆናችሁን ዕወቁ፤ በማለት ወደ ሰዎች የሚያደርስ ማስታወቂያ ነው፤(1) እነዚያን የካዱትንም በአሳማሚ ቅጣት አብስራቸው። [የአማርኛው ቁርኣን የግርጌ ማስታወሻው፥ ከዚህ ዓመት በኋላ ከሐዲ ከዕባን አይጎበኝም፤ ራቁቱንም አይዞርም ይላል።]

9፥5 የተከበሩትም ወሮች ባለቁ ጊዜ አጋሪዎቹን በአገኛችሁባቸው ሰፍራ ግደሉዋቸዉ፤ ያዙዋቸዉም፤ ክበቡዋቸውም፤ ለነሱም (መጠባበቅ) በየመንገዱ ተቀመጡ፤ ቢጸጸቱም፤ ሶላትንም በደንቡ ቢሰግዱ፣ ግዴታ ምጽዋትንም ቢሰጡ፣ መንገዳቸውን ልቀቁላቸዉ አላህ መሐሪ አዛኝ ነውና።

9፥29 ከነዚያ መጽሐፍን ከተሰጡት ሰዎች፣ እነዚያን በአላህ በመጨረሻዉ ቀን የማያምኑትን፣ አላህና መልክተኛዉ እርም ያደረጉትንም እርም የማያደርጉትንና እዉነተኛዉንም ሃይማኖት የማይቀበሉትን እነርሱ የተዋረዱ ሆነዉ ግብርን በእጆቻቸው እስከሚሰጡ ድረስ ተዋጉዋቸው።

አንዴ ማስገደድ የለም ይልና ኋላ ደግሞ ግደሉአቸው፥ አዋርዱአቸው፥ ተዋጉአቸው ይላል። ይህ ቅራኔ ካልሆነና ካልተባለ ምንድርነው? እነዚህ ጥቂት ናሙና ቅራኔና ግጭቶች ናቸው። ዶ/ር ዓሊ፥

በእስላም ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል የሆነው ቁርኣን ግን አንዳች ውስጣዊ አለመጣጣምም ሆነ ተቃርኖ የለበትም፡፡

ሲል ፍጹም እብለት መሆኑ መታወቅ አለበት። ስለ ቁርኣንን ውስጣዊና ውጪያዊ ተቃርኖዎችና ግጭቶች በርካታ መጻሕፍትና ድረ-ገጾች ይገኛሉ። ይህን ለማንበብ ለናሙና እኒህን ከግርጌ የተጠቀሱ ሁለት ድረ-ገጾች ተመልከቱ።[2]

 ምርጫውን ማን አካሄደው?

‘ምርጫውን ማን አካሄደው?’ በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ከላይ ግጭት አለባቸው የሚላቸው አራቱ ወንጌላት ከብዙዎች ወንጌላት መካከል እንዴት እንደተመረጡ ሲጽፍ፥ ወንጌላት ከብዙ መካከል አራቱ በድምጽ ብልጫ እንደተመረጡና የቀሩት በሙሉ ተሰብስበው የተቃጠሉ መሆናቸውን በድፍረት ይጽፋል።

በአንድ ወቅት ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ወንጌሎች እንደነበሩና ከነኚህ ውስጥ ቤተክርስቲያን አራቱን ማለትም የማቴዎስን፣ የማርቆስን፣ የሉቃስንና የዮሐንስን ወንጌሎች ብቻ እንደመረጠች ክርስትና ይናገራል፡፡ ቀሪዎቹ ወንጌሎች እንዲቃጠሉ ወይም እንዲጠፉና እንዲወድሙ ተደርገዋል፡፡

በአስገራሚ ሁኔታ ደግሞ ስለ ቁርኣን የዚህ ተቃራኒ ስለመሆኑ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፥

እስላም ደግሞ ምንጊዜም ቢሆን አንድ ነጠላ የቅዱስ ቁርኣን ቅጂ ብቻ መኖሩንና ተመሳሳይ የማማረጥ ሂደት አለመደረጉን ወይም አለማስፈለጉን ይናገራል፡፡

ሁለቱንም አሳቦች፥ የወንጌልትን መቃጠልና የቁርኣንን አለመቃጠል እንመልከት። መጀመሪያ ወንጌላት ተሰብስበው የተቃጠሉ ከሆኑ መቃጠላቸውን በምን አወቀ? የነበረ ምስክር የጻፍውን አነበበ? ዛሬ ያሉት ሌሎች “ወንጌላት” ተብለው የሚጠሩ ጽሑፎችስ (የቶማስ ወንጌል፥ የበርናባስ ወንጌል፥ ወዘተ) ከተቃጠሉበት አመድ እንዴት ባለ ተአምር ትንሣኤ ሊያገኙ ቻሉ? ወይስ ሳይቃጠሉ የተረፉ ናቸው? እውነቱ ግን እነዚህ ሌሎቹ “ወንጌላት” ሳይቃጠሉ የተረፉ ሳይሆኑ በኋላ ተፈጥረው የተጻፉ ናቸው።

አራቱ ወንጌላት ግን ጸሐፊዎቹ ስማቸውን ባይጽፉም በሐዋርያት ወይም ከሐዋርያት ጋር በነበሩት ምስክሮች በመጀመሪያው ምዕት ዓመት የተጻፉ ናቸው። የዮሐንስ ወንጌል የዮሐንስ ስም ባይጻፍበትም የዓይን ምስክር የጻፈው መሆኑ በገጾቹ ውስጥ ይስተዋላል። ወንጌላት ሌሎች ተቃጥለው እነዚህ የተመረጡ ሳይሆኑ ከሌሎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጋር በመንፈስ ቅዱስ ምሪነት የተጻፉና በቀኖና (መስፈርት፥ መለኪያ ማለት ነው ቃሉ) ተፈትሸውና አልፈው የተሰባሰቡ ናቸው እንጂ ከመቃጠል የተቤዡአቸው መጻሕፍት አይደሉም።

ደግሞ ጸሐፊው ሳያፍር የቃጠሎን ነገር መጻፉ አስገራሚ ነው። የቁርኣንን አሰባሰብ ታሪክ ከሐዲስ (የሙሐመድ ታሪኮች ስብስቦች)  ስናጠና ይልቅ አንድ ቅጅ ብቻ እንዲቀር ተደርጎ የቀሩት እንዲቃጠሉ የተደረገው ወንጌላት ሳይሆኑ ቁርኣን ነው። በሳሂ አልቡኻሪ መጽሐፍ ቅጽ 6 መጽሐፍ 61 አንቀጽ 4657 እና 4658 ይህ በግልጽ ተጽፎአል። የመጀመሪያው አንቀጽ የሚናገረው በጀማማ ጦርነት ጊዜ ብዙ ቁርኣንን በቃላቸው የሚያውቁ ሰዎች በመሞታቸው ሌሎቹም ሁሉ እንደነዚህ ከሞቱ ቁርኣንም አብሮ ሊጠፋ በመሆኑ ተጽፎ እንዲቀመጥ በኡመርና በአቡ በከር መካከል የተደረገውን ንግግር ነው። ከዚያ በኋላ ከተለያዩ ሰዎች፥ ከጠፍጣፋ ድንጋዮችና ከተምር ዛፍ ቅርንጫፍ ከተከተቡት ተውጣጥተው ተጻፉና መጀመሪያ አቡ በከር ዘንድ፥ እርሱ ከሞተ በኋላ ኡመር ዘንድ፥ እርሱ ከሞተ በኋላ የኡመር ልጅና ከሙሐመድ ሚስቶች አንዷ በሆነችው በሐፍሳ ዘንድ ኖረ። በ634 መሪ ወይም ከሊፍ በነበረው በኡስማን ዘመን ኢስላም በጉልበትና በጦርነት ተስፋፍቶ ተንሰራፋ። በዚሁ ጊዜ የተለያዩ ቁርዓኖች በተለያዩ ሰዎች ሲነገሩ የሰማ ሁዳይፋ የተባለ ሰው ወደ ኡስማን ቀርቦ ስጋቱን ይገልጣል። ስጋቱም አገሪቱ እየሰፋችና ሕዝቡ እየበዛ ቁርዓኑ ከተለያየ ሊፈጠር የሚችለው መከፋፈል ነው። በዚህ ጊዜ ትልቁ ስብስብ የሚገኘው ከሙሐመድ ሚስቶች አንዷ በሆነችው በሐፍሳ ዘንድ ነበርና ያ እንዲመጣ አድርጎ አራት ሰዎች መርጦ እንዲጻፍ አደረገ። ልዩነት ከኖረ ከአራቱ አንዱ የቁረይሽ ተወላጅና የሙሐመድ ቋንቋ (ዘዬ) ተናጋሪ ስለሆነ የእርሱን ቃል እንዲቀበሉም በትእዛዝ ተናገረ። ይህ ተሠርቶ በየአገሩ ከተላከ በኋላ ከዚያ በፊት በምንም ነገር ላይ ተጽፈው የነበሩት የቁርኣን ቁራጮችም ሆኑ ሙሉ ቅጅዎች ተሰብስበው እንዲቃጠሉ አዘዘ። ይህ በሐዲስ ውስጥ የትጻፍ እውነት ነው።

ዶ/ር ዓሊ ወጌሎች እንዲቃጠሉና እንዲወድሙ ተደርገዋል ሲል ይልቁን የተቃጠለው መጽሐፍ የትኛው ስለመሆኑ ይህን ታሪክ ሳያውቅ ቀርቶ አይመስለኝም። በለመደው ዘዴ ማረጋገጫ ባለማቅረብ የማያምኑት በሩቅ እንዲቆሙና ያመኑት ግራ እንዲጋቡ ለማድረግ ነው። በፈረንጆች ቆጠራ በማርች ወር 2011 የፍሎሪዳው ፓስተር ቴሪ ጆንስ ቁርኣን አቃጠለ ተብሎ በርካታዎች የሞቱበት ግርግር በአፍጋኒስታንና በሌሎችም አገሮች ሆኖ ነበር። የመጀመሪያዎቹ የቁርኣን አቃጣዮች ግን ሙስሊሞች ራሳቸው መሆናቸው በሐዲሳቸው ተጽፎአል። ፓስተር ጆንስ ቁርኣንን ማቃጠሉ በኔ እይታ ጅልነት ነው። የሰውየው አሳብ የመጽሐፉን መልእክትና የመጽሐፉ ተከታዮች የሆኑቱ ጽንፈኞች የሚወስዱትን ጸረ አሜሪካ አቋም ለማጋለጥ ቢሆንም አንድ ጊዜ እንኳ ከዳር እስከ ዳር አንብቦ ያልተወጣውን መጽሐፍ ከሚያቃጥል አንብቦ ስሕተቶቹን ቢያሳይ የተሻለ ውጤት ይኖረው ነበር። እርሱም ሆነ ሌሎች ክርስቲያኖች ማድረግ ያለባቸው ማንበብና መመርመር ነው።

ኦሪጂናል ቋንቋ

ዶ/ር ዓሊ በመቀጠል ‘ኦሪጂናል ቋንቋ?’ በሚል ንዑስ ርዕስ ስር፥

ማቴዎስ መጀመርያ የተጻፈበት ኢሪጅናል ቋንቋ የዕብራይስጥ ቋንቋ መሆኑን ክርስትና ይናገራል፡፡ ግና የዕብራይስጥ ኢሪጅናል ቅጂው የትም የለም፤ ፈጽሞ ጠፍቷል፡፡ ዛሬ የሚገኘው ከዚህ ከጠፋው ቅጂ በሌላ ቋንቋ የተተረጎመ የትርጉም ቅጂ ብቻ ነው፡፡

ይላል። ይናገራል የሚለው ክርስትናን ነው። ይህ ምሑራዊ አጠቃቀስ አይደለም። ሰው ተናገረ ካለ “ማን?” እንዳይባል ይሆናል እንዲህ ያለ “ክርስትና ይናገራል” የሚል ቋንቋ መጠቀሙ። የማቴዎስ ወንጌልም ሆነ ሌላ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በመጀመሪያ በዕብራይስጥ አልተጻፉም። ቀደም ሲል ስለ አራማይስጥ በተነገረው ክፍል እንዳልኩት የዘመኑ የደረጀ የጽሑፍ ቋንቋ ግሪክ በመሆኑ ማቴዎስንም ጨምሮ አዲስ ኪዳን በመላው በግሪክ ቋንቋ ነው የተጻፈው እንጂ በዕብራይስጥ አልተጻፈም። ክርስትና የተባለው ተናጋሪ ይህንን አላለም። የመናገሪያ ቋንቋቸው አራማይስጥ ስለሆነ ኦሪጂናሉ ጽሑፍ ዕብራይስጥ ነው ብሎ መገመትና መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ማቅረብ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ይህ ጸሐፊ አስረጅ ስለማያቀርብባቸው ጉዳዮች በግድ የለሽነት አባባሎችን መወርወሩ መጽሐፍ ቅዱስን ለማቆሸሽና ለማስነወር ነው። የሚያሳዝነው ይህንን እርሱ የሚያንቋሽሸውን መጽሐፍ የራሱ ነቢይ አንቋሽሾት ነበር ወይ? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ አይደለም ነው። ይህንን በቀጣዩ ክፍል እንመለከታለን።

ከዚሁ ጋር በማነጻጸር (መጽሐፉ ራሱ የንጽጽር አይደል?) ስለ ቁርኣን ሲናገር እንዲህ ይላል፥

ከትክክለኛተን መመዘኛ አኳያ የትኛው መጽሐፍ ነው ይበልጥ አስተማማኙ? ኦርጂናሉ የጠፋ መጽሐፍ ወይስ ኦርጂናሉ ዛሬም የሚገኝ መጽሐፍ? ለትክክለኛነቱና ለተኣማኒነቱ የትኛውን የበለጠ ይመርጣሉ?

አሉ የሚባሉት ጥንታዊ የቁርኣን ቅጂዎች ከሙሐመድ ሞት በኋላ ከ100 እስከ 200 ያህል ዓመታት በኋላ የተጻፉ ናቸው። በታሽኬንት የሚገኘው የስማርካንድ ጽሑፍ ጥንታዊ የሚባለው ሆኖ በ800 ዓ. ም. ገደማ የተጻፈ ነው። ዶ/ር ዓሊ “ኦሪጂናሉ ዛሬም የሚገኝ” ሲል ሽንገላ ነው። ኦሪጂናል የሚለው ይህንን ከሆነ ይህ ኦሪጂናል አይደለም። ኡስማን ያስጻፈውም እንኳ የለም እንጂ ኦሪጂናል ሊሰኝ አይችልም። ኦሪጂናል መሰኘት የነበረባቸው የሉም እንጂ እንዲቃጠሉ የተደረጉት በድንጋይም፥ በልጣጭም፥ በብራናም የተጻፉት የመጀመሪያዎቹ ነበሩ። እነዚያ ቢኖሩና ቢተያዩ ታሪኩ ሌላ ሊሆን ይችል ነበር። ጸሐፊው ኦሪጂናል የሚለው ይህንን ጥንታዊ የሚባለውን ወይም በራሱ ቋንቋ “ኦሪጂናሉ ዛሬም የሚገኝ መጽሐፍ” የሚለው የስማርካንድ ጽሑፍ መሆን አለበት።

ቅጂዎች?

በመቀጠል ‘ብዙ የተለያዩ ቅጂዎች ወይስ አንድ ብቸኛ ቅጂ?’ በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ጸሐፊው እንዲህ በማለት ይጀምራል፥

የክርስትና መጽሐፍ ቅዱስ አያሌ የተለያዩ ቅጂዎች ያሉት ከመሆኑም ባሻገር በማያቋርጥ የመለዋወጥ ሂደት ውስጥ ያለና ከጊዜ ወደ ጊዜ ክለሳና ማሻሻያ የሚካሄድበት መጽሐፍ ነው፡፡

በተለይ ክለሳ፥ ማሻሻያ፥ እና የማያቋርጥ የመለዋወጥ ሂደት የሚሉት ቃላት የሐሰት ክስ ናቸው። በምሑራዊ አቀራረብ ማስተያየት ማዳላት መሆን የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስን፥ ለምሳሌ፥ አዲስ ኪዳንን ማስተያየት የሚፈልግ ሰው የአሁኑን የዐረብኛ ቁርኣን በ800 ዓ. ም. ከተጻፈው ጋር እንደሚያስተያይ ሁሉ በዐረብኛ ወይም በእንግሊዝኛ ወይም በአማርኛ የተጻፈውን ትርጉም ሳይሆን ዛሬ ያለውን የግሪክ አዲስ ኪዳን ከቀዳሚ ቁርጥራጭ ጽሑፎች ሰነዶች ጋር ነው ማስተያየት ያለበት። ጸሐፊው ይህን አድርጎ ስሕተቶች አገኘሁ ካለ አላቀረበም። ከአጻጻፉ እንደሚታየው የማድረጉ ብቃትም የለውም። በማያቋርጥ የመለዋወጥ ሂደት እያለፉ የሚላቸው የተለያዩ ቅጅዎች ቅጅዎች ሳይሆኑ ትርጉሞች ናቸው። እነርሱም በማያቋርጥ የመለዋወጥ ሂደት እያለፉ ሳይሆኑ የተተረጎሙበት ቋንቋ ነው ሳያቋርጥ የሚለዋወጠው። በቁርኣንም ስላሉት ልዩነቶች በዝርዝር ከታች ባለው ድረ ገጽ[3] ተመልከቱ። ወደ እንግሊዝኛ በተለያዩ ጊዜያት የተተረጎሙ የቁርኣን ትርጉሞችም ቁጥር ከ20 ሳይበልጥ አይቀርም። እኔ 16 ቆጥሬአለሁ። እና የሁሉም ቃል አንድ ነው? አይደለም። ይህ የትርጉም ጉዳይ ነው።

ጸሐፊው የተለያዩ ቅጂዎች የሚለው የተለያዩ ትርጉሞችን ከሆነ ቅጅ ማለት የለበትም። በአማርኛ ብቻ እንኳ አሁን ወደ አምስት ያህል ትርጉሞች አሉ። በእንግሊዝኛ በመቶዎች ይቆጠራሉ። ይህ የሆነው ቋንቋ በዘመናት ውስጥ እንደ ሐውልት ቆሞ የሚቀር ሳይሆን የመለወጥ፥ የማደግ፥ የመስፋት፥ የመሸብሸብና የመጥፋት ባህርይ ስላለው ነው። ቁርኣንም ወደ ሌላ ቋንቋ ሲተረጎም ይህ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ያለዚያ አሁን በየቋንቋው ትርጉሞች እንደሚደረገው በቅንፍና በግርጌ ማስታወሻ ማብራሪያ መጻፍና፥ ‘ይህን ሲል ይህን ማለቱ ነው’ ብሎ ማብራራት የተለመደ ይሆናል። በአማርኛው ቁርኣንም ቅንፎችና የግርጌ ማስታወሻዎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው። ይህ የሆነው ራሱ ዐረብኛውም ከሺህ አራት መቶ ዓመት በተጻፈበት ቋንቋ ደርቆ አለመቅረቱን የሚመሰክር ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ክለሳና ማሻሻያ የሚደረግበትና በማያቋርጥ የለውጥ ሂደት ውስጥ ያለ መጽሐፍ ሳይሆን ቋንቋ ነው በለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፈ የሚኖረው። መልእክቱ እንዲተላለፍ ከተፈለገ ቋንቋ ሲለወጥ ቃላት ሊስተክካከሉና ሊለወጡ የግድ ነው። ያለዚያ በቅንፍ ውስጥ `እንዲህ ማለት ነው` እያሉ ሲጽፉ መኖር ነው። ጸሐፊው ምሳሌ ቢሰጥና፥ `የቆየው የግሪኩ ጽሑፍ 12 ሐዋርያት የሚለውን የዘንድሮው ደግሞ 36 ሐዋርያት በማለት ከልሶታል፤ አሻሽሎታል` የሚል ወይም ይህን የሚመስል ክስ ወይም ማስረጃ ቢያቀርብ እውነትም መጽሐፍ ቅዱስ ክለሳ ይደረግበታል ሊባል ይችላል። ግን በዘመናት ውስጥ ቀድሞ ከተጻፈው በቋንቋ መግለጫ እንጂ በይዘት የተለየ ነገር ማቅረብ ስለማይችለው ነገር ሲጽፍ ጸሐፊው የራሱን ስንፍና ማጋለጡ ነው።

ሐዋርያ ወይስ ነቢይ?

ጸሐፊው ሐዋርያ ወይስ ነቢይ በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ኢየሱስ ነቢይ አለመሆኑን ክርስትና ስለማስተማሩ ይህን ይላል፤

ዮሐንስ፣ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ወንጌሎቻቸውን ለመጻፍ ከእግዚአብሔር ራእይ የተገለጸላቸው ሲሆን የክርስትና እምብርት የሆኑት ኢየሱስ ራሳቸው ግን ከእግዚአብሔር ምንም ራእይ እንዳልተገለጸላቸው ክርስትና ይናገራል፡፡

ይህ ‘ክርስትና ይናገራል’ እያለ ጸሐፊው ለሚለጥፈው ነገር ይኸው ማስረጃው እያለ ቢያቀርብ ጥሩ ነበር። ለነገሩ ንዑስ ርእሱ ራሱ ግራ የገባው ነው። ኢየሱስ ነቢይ መሆኑን ጸሐፊውና ሃይማኖቱ ይቀበላል። ግልጽ ባይሆንም እንደተረዳሁት ግን ነቢዩ (ኢየሱስ) ቃል ሳይቀበል ሐዋርያቱ ስለ እርሱ ጻፉለት ማለቱ ይመስላል።  እዚህም ላይ ሁለት ስሕተቶችን እናጢን።

አንደኛ፥ ‘ክርስትና ምንም ራእይ እንዳልተገለጸላቸው ይናገራል’ ያለው ጸሐፊው ውሸቱን ነው። ክርስትና ወይም አዲስ ኪዳን እንዲያውም የሚናገረው ኢየሱስ እንደ ብሉይ ወይም አዲስ ኪዳን ነቢያት ነቢይ ሳይሆን እርሱ ሰው የሆነ፥ ሥጋን የለበሰ አምላክ መሆኑን ነው። ደግሞም ነቢይም ሐዋርያም መሰኘቱም በእርግጥ ተጽፎአል። እነዚህ ግን በማንነቱ ላይ የተጨመሩ ሥራውን የገለጡ ቃላት ናቸው እንጂ እርሱ ከቀድሞ የነበረ ሥጋ የለበሰ ቃል ነው። ለነገሩ ኢየሱስ ቃል የተሰኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ አይደለም። ጸሐፊው ልብ ያላለው ወይም አውቆ የደበቀው እውነት በቁርኣንም ኢየሱስ የአላህ ቃል እና የአላህ መንፈስ መሰኘቱን ነው። በ4፥171 ያለው ቃል ይህንን ያረጋግጣል።

እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም ከርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው፤ በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ (አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉም፤ ተከልከሉ ለናንተ የተሻለ ይሆናልና፤ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው። ለርሱ ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው። በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው። መመኪያም በአላህ በቃ።

ጥቅሱ አማልክት ሦስት ናቸው አትበሉ፤ አላህ ልጅ ያለው ከመሆን የጠራ ነው በማለት ክርስቲያኖችን ሦስት አማልክት አምላኪ አድርጎ ያቀርባል። ሙሐመድ ሥላሴን የተረዳው እንደዚያ ስለሆነ ነው። ቀደም ሲል እንዳየነውም ሦስቱ ያላቸው እግዚአብሔር፥ ኢየሱስ እና ማርያም ናቸው። ልጅ ያለው ሲባልም የሥጋ ልጅን፥ ማለትም እግዚአብሔርና ማርያም በሥጋ ተገናኝተው እንደተወለደ ልጅ ማለቱ ነው። ሌላው ይህ አንቀጽ የሚለው ኢየሱስ ቃል መሆኑን ነው፤ ወደ ማርያም የጣላት ቃል። ቃሉ፥ ‘ቃሊማቱላህ’ ኢየሱስ የአላህ ቃል መሆኑን መግለጡ ነው። በዚህ ጥቅስ ቃሉ ብቻ ሳይሆን የአላህ መንፈስም (ሩሁላህ) ተሰኝቶአል፤ የይህ ቃል በሌሎችም የቁርኣን ክፍሎች ተጠቅሶአል፤ 2፥87 እና 253፤ 16፥102።

ኢየሱስ ቀድሞ የነበረው ቃል ከሆነ ጸሐፊው እንዳለው ኢየሱስ “ከእግዚአብሔር ምንም ራእይ እንዳልተገለጸላቸው” ክርስትና አይናገርም። እግዚአብሔርን ማንም ያየው የለም፤ አንድ ልጁ ግን እርሱ ግን ተረከው፤ ይላል፤ ዮሐ. 1፥18። ሥጋ ከለበሰው የቀደመ ቃል በላይ ማን ይተርከው? ራሱ ቃል ቢሆንም ቃልን መቀበሉን ደግሞ ራሱም ተናግሮአል። በዮሐ. 17፥8 ደግሞ ጌታ፥ የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ አለ። የተቀበለውና የሰጠው ቃል አለ ማለት ነው። ይህንን ነው ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውና እነርሱም የተቀበሉት። ይህንን ነው እነርሱም የጻፉትና ያስተላለፉት። ነቢዩ ምንም አለመቀበሉ የሚለው አባባል ቅጥፈት ነው።

ሁለተኛው ስሕተት፥ እርሱ አስተማረ፤ ደቀ መዛሙርቱና ከዓይን ምስክሮች የሰሙቱ ያስተማረውንና ያደረጋቸውን ነገሮች ጻፉ የሚለው ነው። ጸሐፊው ዶክተር ዓሊ ሚዛኑን የሳተበትን ነገር ተመልከቱ፤ ሙሐመድም እኮ ጅብሪል ተናገረኝ ያለውን ሌሎቹ ሰሙና ሸምድደው ቆይተው ኋላ ያ የሸመደዱት ቃል በቅጠልም፥ በዛፍ ልጥም፥ በድንጋይም፥ በአጥንትም፥ በብራናም ተጻፈ እንጂ እርሱ ራሱ አልጻፈውም። እርሱ ራሱ እንዳልጻፈው እያወቀ ስለ ሙሐመድ ሌሎች ከእርሱ የሰሙትን መጻፋቸውን በአድናቆትና በአንክሮ እየተቀበለ ስለ ኢየሱስ ከእርሱ የሰሙትና ያዩት የጻፉትን አለመቀበሉ ነው የሚያስደንቀው ስሕተት። ይህ ይደንቃል። ሙሐመድ አለመጻፉ ከኢየሱስ አለመጻፍ ልዩነቱ ምንድርነው?

————-

[1] ሙሐመድ ሰዲቅ (የዲቪዲ ስርጭት በአማርኛ)።

[2]http://www.answering-islam.net/Quran/Contra/   http://wikiislam.net/wiki/Contradictions_in_the_Qur’an.

[3] http://www.answering-islam.net/Green/seven.htm/

 

———–

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ

መጽሐፍ ቅዱስ