መዝጊያ በአሕመድ ዲዳት

መዝጊያ በአሕመድ ዲዳት

ክቡር ሰብሳቢ፣ የችሎቱ ክቡራትና ክቡራን፤ ሰው በተፈጥሮ ፈሪ ነው፡፡ ታስታውሳላችሁ ከአዳም ጊዜ ጀምሮ ሲያመካኝ ነበር፡፡ “እኔ አይደለሁም ሴቷ ናት”፤ ሴቷም፣ “እኔ አይደለሁም እባቡ ነው” ሲሉ ነበር፡፡ ሰው በተፈጥሮው ፈሪ ነው፡፡ እናም ሌላ ሰው እዳችንን እንዲሸከምልን እንፈልጋለን፡፡ ታማሚዎቹ እኛ ሆነን ሳለን ሌላ ሰው መድኃኒቱን እንዲውጥልን እንፈልጋለን፡፡ የበሰበሰው የኛ ሆኖ ሳለ የሌላው ሰው ትርፍ አንጀት እንዲወገድ እንፈልጋለን፡፡ ሰው ባጠቃላይ እንዲህ ነው፡፡

ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ይህንን አይደለም፡፡ የራሳችሁን መስቀል ራሳችሁ እንድትሸከሙት ይፈልጋል – ራሳችሁ እንድትሰቀሉ፡፡ አድምጡኝ! እንዲህ አለ፡- “መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ የኔ ሊሆን አይችልም፡፡” መስቀላችሁን ተሸክማችሁ ተከተሉኝ፡፡ በሌላ ቋንቋ ራሳችሁ ተሰቀሉ [የሕዝቡ ሳቅ]፡፡ አይደለም፣ አይደለም፣ አይደለም፡፡ እንደርሱ ማለቱ አይደለም፡፡ እርሱ እያለ ያለው “እኔ የራሴን ኃላፊነት እንደምሸከመው ሁሉ እናንተም የራሳችሁን መሸከም ያስፈልጋችኋል፡፡ እኔ እንደምጸልየው እናንተም መጸለይ ያስፈልጋችኋል፡፡ እኔ እንደተገረዝኩት እናንተም መገረዝ ያስፈልጋችኋል፡፡ እኔ የማደርገውን እናንተም ታደርጋላችሁ፡፡ የራሳችሁን ኃላፊነት ራሳችሁ ትሸከማላችሁ” ነው፡፡

ይህንን ነው እያለ ያለው፡፡ እንግዲህ ያ እስላማዊው ስርኣት ነው! ይህ ኢስላም የሚያስተምረው ነው፡፡ አያችሁ? ከዓመታት የጠጪነት ሕይወት በኋላ፤ ለዓመታት 10 ሳንቲም ከመባ መሰብሰቢያ ላይ በጣቶች መሃል አድርጎ ከመውሰድ ሕይወት በኋለ ሊያድናችሁ የሚችል ስርኣት ነው፡፡ እዚህ ታነቡታላችሁ፤ በጆሽ መጽሐፍ ውስጥ፡፡ በየእሑዱ ከቤተ ክርስቲያን የሚያገኘው ነገር ቢኖር 25 ሳንቲም የመባ ዕቃ ውስጥ አስቀምጦ ወተት ለመናጥ የሚሆን 35 ሳንቲም መውሰድ ብቻ እንደነበር ይናገራል፡፡ ከዚያ በኋላም በሕይወት ውስጥ፤ የምንመረምር ከሆነ፤ በከፍተኛ የዕውቀት ደረጃ ላይ ከተደረሰ በኋላ እንኳ ተመሳሳይ የሆነ ነገር እየተሠራ እንደሆነ እንደርስበታለን፡፡ ነገር ግን ስለሱ በጥልቀት ለማውራት ጊዜ የለንም፡፡

በኢየሱስ መልእክት ልደምድም፡፡ እንዲህ አለ፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ ፅድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከጻፎች ፅድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ልትገቡ አትችሉም፡፡” መንግሥተ ሰማያትን አታገኙም፡፡ እነዚህ እርሱ የተናገራቸው ናቸው፤ እነዚህ ቃሎቹ ናቸው፡፡ እየሆነ ያለው ነገር ምንድነው፤ እናንተ የርሱን ቃል እየተቃረናችሁ አይደላችሁም፡፡ ይህ ኢስላም ነው! ከአይሁድ ካልተሻላችሁ በሰማይ ቦታ የላችሁም፡፡

“ደሙ ነው” አላለም፣ ነገር ግን “የናንተ ጽድቅ ነው” ያለው፡፡ ከአይሁድ መሻል ይኖርባችኋል፡፡ አይሁድ እንደሚፆሙት መፆም ያስፈልጋችኋል፣ ነገር ግን ከፍ ባለ ደረጃ፡፡ አይሁድ እንደሚጸልዩት መጸለይ ያስፈልጋችኋል ነገር ግን ከፍ ባለ ደረጃ፡፡ አይሁድ ምጽዋት እንደሚሰጡት ምጽዋት መስጠት ያስፈልጋችኋል ነገር ግን ከፍ ባለ ደረጃ፡፡ እናም  ኢስላም ነው፡፡

ስለዚህ ክቡር ሰብሳቢ፤ የችሎቱ ክቡራትና ክቡራን፤ እንዲህ ልበላችሁ፤ ይህ ትንሣኤ “ፈጠራ ወይንስ ታሪክ” በሚል ርዕስ በአሜሪካ በጆሽ እንደተነገረው እዚህ አንድ መቶ ሚሊዮን ሰዎች በመስቀል ላይ ሆነው እንዲጋልቡ ተወስደዋል ብዬ አጠቃልላለሁ፡፡ [ጆሽ በተቀመጡበት ሆነው ሊጠጡት ወደ አፋቸው ያስጠጉትን ውሃ በመተው አንድ ነገር የተገለጠላቸው ይመስል ከፍ ባለ ድምጽ “አሜን!” ሲሉ በቪድዮው ላይ ይታያል] በደርባን ውስጥ በየሳምንቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለግልብያ የሚወስዱ ፈረሶች አሉን፡፡ ነገር ግን እዚህ በመስቀል ላይ ሆናችሁ ለመጋለብ ነው የምትወሰዱት፡፡

ክቡራትና ክቡራን በጣም አመሰግናለሁ፡፡

[ሕዝቡ አጨበጨበ፣ ሚስተር ዲዳት ወደ ቦታቸው ተመልሰው ተቀመጡ፡፡]


ክርስቶስ ተሰቅሏልን? ማውጫ