መዝጊያ፡ በጆሽ ማክዱዌል
[ጆሽ ማክዱዌል የመናገርያ ቦታቸውን ሲይዙ ሕዝቡ በጭብጨባ ተቀበላቸው]
ሚስተር ዲዳት በእግዚአብሔር በተገለጠው በክርስቲያን አዲስ ኪዳን ውስጥ በአንድም ቦታ ላይ ክርስቲያኖች እንዲሰቀሉ አልታዘዙም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ሆነን መሰቀላችንን ዕውቅና እንድንሰጥ ነው የታዘዝነው፡፡ [ሕዝቡ “አሜን!” በማለት አጨበጨበ]
በሮሜ 8፡32 ላይ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ሲናገር፡- “ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችንም አሳልፎ… የሰጠው” ይላል፡፡ በአገሬ ውስጥ ከተፈቀደ ፍጥነት በላይ በማሽከርከር የተያዘች ወጣት ልጅ በዳኛ ፊት ቀረበች፡፡ ዳኛውም “ወንጀለኛ ነሽ አይደለሽም?” በማለት ጠየቃት፡፡ እርሷም “ወንጀለኛ ነኝ” አለች፡፡ ዳኛውም የ100 ዶላር ወይንም የ10 ቀን ቅጣት ጣለባት፡፡ ከዚያም የሚያስደንቅ ነገር ሆነ፡፡ ደኛው ተነስቶ ቆመ፤ ካባውን አውልቆ ከወንበሩ በስተጀርባ ካስቀመጠ በኋላ ወደ ታች ወርዶ ቅጣቱን ከፈለ፡፡ የዚህ ትርጉም ምንድነው? ዳኛው አባቷ ነበር፡፡ እርሱ ፍትሃዊ ዳኛ ነበረ፡፡ ልጁ ህግ ተላልፋለች፡፡ ምንም ያህል ቢወዳት 100 ዶላር ወይንም 10 ቀን ማለት ነበረበት፡፡ ነገር ግን በጣም ስለሚወዳት ወደታች ወርዶ ቅጣቱን በራሱ ላይ በመውሰድ ለመክፈል ፍቃደኛ ነበር፡፡ ይህ ያሕዌ እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ ውስጥ የገለጠውን የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይወደናል፡፡ ክርስቶስ ሞቶልናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኃጢኣት ደመወዝ ሞት መሆኑን በግልፅ ያሳየናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ፍርድ ማስተላለፍ አለበት፡፡
ነገር ግን ክቡራትና ክቡራን፤ በጣም ስለሚወደን የዳኝነት ካባውን በመተው ኢየሱስ ክርስቶስ በተባለው ሰው መልክ መጣ፡፡ ከዚያም ወደ መስቀል በመሄድ እዳችንን ከፈለ፡፡ ስለዚህ አሁን “እነሆ በሕይወታችሁ ደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፡፡ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ” ብሎ ለመናገር ይችላል፡፡
አዎን ሚስተር ዲዳት፣ አንድ ቢልዮን ክርስቲያኖች በመስቀል ላይ ሆነው እየጋለቡ ነው፡፡ እንድንጋልብ ተወስደናል፡፡ [የሕዝቡ ጭብጨባ] እግዚአብሔር በፈሰሰው መለኮት በሆነው ልጁ ደም አማካይነት መስቀሉን ወደ ሰማይ የሚወስድ ሰረገላ አድርጎ እንደሰጠን አምናለሁ፡፡
ክቡራትና ክቡራን የሌላ አገር ሰው እንደመሆኔ መጠን እዚህ እንድመጣ ስለሰጣችሁኝ እድል በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ሚስተር ዲዳት፤ ስለዚህ እድል የርሶ ታላቅ ባለ እዳ ሆኛለሁ፡፡ ወደ አገሬ ቢመጡ አብረን ምሳ እንበላለን፡፡ አኔ እጸልያለሁ እርሶ ደግሞ ሂሳቡን ይከፍላሉ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ [የሕዝቡ ሳቅና ጭብጨባ]
ሚስተር አህመድ ዲዳት እና ጆሽ ማክዱዌል ተጨባብጠው ክርክሩ ተጠናቀቀ፡፡