ምዕራፍ ሁለት
የመጽሐፍ ቅዱስ አዘጋገብ ክፍል 1 [ክፍል 2]
የቁርአን አዘጋገብ ምንም ተዓማኒነት የሌለውና የተጭበረበረ እንደሆነ በብዙ ማስረጃዎች አረጋግጠናል፡፡ በመሐመድ ዘመን ተጻፉ የተባሉት የቁርአን ክፍሎችና ከእነርሱ ላይ የተሰበሰበ እንደሆነ የተነገረው በሐፍሷ እጅ የነበረው ቁርአንም መቃጠሉን አይተናል፡፡ የፖለቲካ መሪዎች ጽሑፉን በመቆጣጠር በፈለጉት መንገድ ሲለዋውጡት መኖራቸው የታሪክ ሃቅ ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ግን እንደርሱ አይደለም፡፡ ከቁርአን በተፃራሪ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለያዩ ሰዎች ያለ ምንም ኦፊሴላዊ ቁጥጥር ይገለበጥ ስለነበር የተደራጁ ቡድኖች በፈለጉት መንገድ እንዲቀያይሩት የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም፡፡ በግልበጣ ሂደቱ መካከል ጣልቃ የሚገባ ስህተት ካለ ቀዳሚያን ቅጂዎች እንዲወድሙ ስለማይደረጉ ችግር ያለበትን ክፍል በቀላሉ ነቅሶ በማውጣት በትክክለኛው ንባብ መሠረት ማስተካከል ይቻላል፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ የግልበጣ ታሪክ ፍፁም ግልፅ ነው፡፡ ላለፉት 200 ዓመታት ደግሞ ምሑራን ዘመናዊ የጥናት ዘዴዎችን በመጠቀም በመመርመር ሃቀኝነቱን አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህ እውነታ ምስክርነታቸውን የለገሱ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ምሑራን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በፓሌኦግራፊ[1] ጥናት ዘርፍ እውቅናን ካተረፉ ሊቃውንት መካከል በአንድ ወቅት የብሪቲሽ ቤተ መዛግብት ተጠሪ እንዲሁም የብሪቲሽ አካዳሚ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሰር ፍሬደሪክ ጆርጅ ኬንዮን ይጠቀሳሉ፡፡ እኝህ ብዙ ዘመናቸውን የመጽሐፍ ቅዱስን ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች በመመርመር ያሳለፉ ስመ ጥር ሊቅ በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፡-
“የመጀመርያው ጽሑፍ በተጻፈበት ጊዜና በቀዳሚው ጽሑፍ መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት ምንም የለም እስኪያስብል ድረስ በጣም አናሳ ሆኗል፤ እናም ቅዱሳት መጻሕፍት መጀመርያ በተጻፉበት ይዘት እኛ ዘንድ በመድረሳቸው ላይ የነበረው የመጨረሻው የጥርጣሬ መሠረት ተወግዷል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ተዓማኒነትና አጠቃላይ ተግባቦት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደተረጋገጠ ሊቆጠር ይችላል፡፡”[2]
ዕውቅ የአዲስ ኪዳን ሊቅ የሆኑት ኤፍ ኤፍ ብሩስ፣ ሰር ፍሬደሪክ ጄ. ኬንዮንን “ስለ ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ስልጣናዊ ንግግር በማድረግ ረገድ ማንም የማይስተካከላቸው” ይሏቸዋል፡፡[3]
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችና ይዘት
ተቃዋሚዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት አጠራጣሪ ለማድረግ ብዙ ጊዜ የሚጠቅሱት በውስጡ የሚገኙትን መጻሕፍት ዝርዝር በተመለከተ በክርስቲያኖች መካከል የሚገኘውን ልዩነት ነው፡፡ አቶ ሐሰንም ይህንኑ ያረጀ የሙግት ሐሳብ ተጠቅመዋል (ገፅ 30-32)፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስን ቀኖና በተመለከተ በተለያዩ የክርስትና ቤተ እምነቶች መካከል ልዩነት መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ የወንጌላውን አብያተ ክርስቲያናትና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቀኖና 66 መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን 73፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ 81 መጻሕፍትን የያዙ ናቸው፡፡ በስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት ዙርያ በነዚህ የክርስትና ቤተ እምነቶች መካከል ስምምነት ያለ ሲሆን ልዩነቱ የተፈጠረው አፖክሪፋ በመባል በሚታወቁት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዙርያ ነው፡፡ ነገር ግን የአፖክሪፋ መጻሕፍት ከቀኖና መቆጠራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ መልዕክት ላይ የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ምንም ነገር የለም፡፡ በየትኛውም ቤተ እምነት ቀኖና የታተመውን መጽሐፍ ቅዱስ ያነበበ ሰው መሠረታዊ የሆኑ የክርስትና አስተምህሮዎችን በተሟላ ሁኔታ ያገኛል፡፡ የአፖክሪፋን መጻሕፍት እንደ ቃለ እግዚአብሔር የማይቆጥሩ አብያተ ክርስቲያናትም ቢሆኑ እነዚህን መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ ውድቅ የማያደርጉ ሲሆን መንፈሳዊ ትምህርቶችን እንደያዙ አስተማሪ መጻሕፍት ይቀበሏቸዋል፤ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጎን ለጎን ለተጨማሪ ዕውቀት ያጠኗቸዋል፡፡
የአፖክሪፋ መጻሕፍት ቀኖና መሆን አለመሆናቸው የክርስትናን ዋና ዋና አስተምህሮዎች በምንም መልኩ የሚነካ አይደለም፡፡ የተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መቀየራቸውንም አያሳይም፡፡ ሙስሊም ወገኖች ራሳቸው “ሐዲስ ቁድሲ” በማለት የሚጠሯቸው የሐዲስ ክፍሎች እንደ ቁርአን ሁሉ የአላህ ቃል ናቸው ወይስ አይደሉም? በሚለው ላይ ስምምነት የላቸውም፡፡
የተጻፉበት ዘመን
አቶ ሐሰን ክርስቲያን ምሑራን ሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ ማለትም ብሉይና አዲስ ኪዳናት የተጻፉበት ዘመን በትክክል እንደማይታወቅ መናገራቸውን ጽፈዋል (ገፅ 32)፡፡ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ትኩረት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተጻፈበት ሥፍረ ዘመን (Era) ላይ እንጂ በዓመቱ፣ በወሩ ወይም በቀኑ ላይ እንዳልሆነ አልተገነዘቡም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በነቢያትና በሐዋርያት ሥፍረ ዘመን የተጻፈ መሆኑ ከተረጋገጠ ለተዓማኒነቱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ዕድሜ ያለውና የተጻፈበት ቁርጥ ያለ ዓመት፣ ወርና ቀን የሚታወቅ ጥንታዊ መጽሐፍ የለም፡፡ ነገር ግን ጥንታዊ መዛግብትን የሚያጠኑ ሊቃውንት የተለያዩ ውጪያዊና ውስጣዊ መመዘኛዎችን በመጠቀም የተጻፉበትን ዘመን ይገምታሉ፡፡ ይህ ግምት ተራ ግምት ሳይሆን ምሑራዊ ጥናቶችን በመጠቀም ላይ የተመሠረተ ልሒቃዊ ግምት በመሆኑ አስተማማኝነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡
- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት
አቶ ሐሰን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከ13ኛው እስከ 1ኛው ክፍለ ዘመን ቅድመ ክርስቶስ መካከል እንደተጻፉ ዘመነኛ ምሑራን ግምት ማስቀመጣቸውን ጽፈዋል (ገፅ 32)፡፡ ለዚህ ዋቢ እንዲሆናቸው በማጣቀሻቸው ላይ ያስቀመጡት ደግሞ “The History of Quranic Text” የተሰኘ መጽሐፍ ነው፡፡ ነገር ግን የመጽሐፉ ጸሐፊ ማን እንደሆነ፣ መች እንደታተመና የት እንደታተመ ምንም ፍንጭ አልሰጡም፡፡ በዋቢ ምንጮቻቸውም ውስጥ አልተካተተም፡፡ ርዕሱም ቢሆን ቁርአንን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የተመለከተ አይደለም፡፡ እንዲህ ካለው ያልተጣራ ምንጭ ላይ ያመጡትን መረጃ መቀበል ባይቻልም ነገር ግን የጠቀሱት መረጃ ሙግታቸውን የሚያፀድቅ አይደለም፡፡ ሙሴ የኖረው በአሥራ አራተኛውና በአሥራ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን ቅ.ክ. መካከል እንደሆነ ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡[4] ነገር ግን አቶ ሐሰን ከላይ በጠቀሱት ግልፅነት በጎደለው ምንጭ ላይ ተመሥርተው እንዲህ የሚል አልተገናኝቶ ድምዳሜ አስቀምጠዋል፡-
“ይህም ማለት የመልእክቱ ባለቤት የሆነው ሙሣ ከሞቱ ከበርካታ ምእተ አመታት በኋላ የመጻፍ ሂደቱ በሌሎች ሰዎች ተወጥኖ የተጠናቀቀ መጽሐፍ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡” (ገፅ 32)
ሙሴ በአሥራ አራተኛውና በአሥራ ሦስተኛው ክ.ዘ. መካከል ኖሮ ከነበረና አቶ ሐሰን በጠቀሱት ምንጭ መሠረት ብሉይ ኪዳን በአሥራ ሦስተኛው ክ.ዘ. ከተወጠነ “እርሱ ከሞተ ከበርካታ ምዕተ ዓመታት በኋላ የመጻፍ ሂደቱ… ተወጥኖ ተጠናቀቀ” ሊባል የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው? በሙሴ የተጻፉት አምስቱ የሕግ መጻሕፍት (ፔንታቱክ) እንጂ ሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ባለመሆናቸው ብሉይ ኪዳንን የማሟላት ሂደቱ ከእርሱ ህልፈት በኋላ በሌሎች ቅዱሳን ሰዎች ለክፍለ ዘመናት ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን አቶ ሐሰን በጠቀሱት ያልተረጋገጠ ምንጭ መሠረት ብሉይ ኪዳን ሙሴ በኖረበት ዘመን በጽሑፍ መስፈር እንደጀመረ ስለተነገረ ሙሴ ከሞተ ከበርካታ ክፍለ ዘመናት በኋላ በሌሎች ሰዎች ተወጥኖ እንደተጠናቀቀ መናገራቸው ግጭት ነው፡፡ ለወደፊቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተቸት ከመጣደፋቸው በፊት የመረጃ ምንጫቸውንና ድምዳሜያቸውን እንዴት ማስማማት እንደሚችሉ ተረጋግተው ቢያስቡ መልካም ይመስለናል፡፡
- የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት
የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉበትን ዘመን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡-
በአብዛኞቹ ምሁራን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ሐሳብ እንደሚያመለክተው የመጀመሪያው ‹ወንጌል› እንደሆነ የሚታመነው የማርቆስ ወንጌል በ68 ዓመተ ልደት አካባቢ ማለትም እየሱስ ካረጉ ከ35 ዓመታት በኋላ እንደተጻፈ ይገመታል፡፡ የመጨረሻው ወንጌል የሆነው የዩሐንስ ወንጌል ደግሞ ከ100-125 ዓ.ል ማለትም እየሱስ ካረጉ ከ70-90 ባሉት አመታት ውስጥ መጻፉ ተገምቷል፡፡ የሉቃስ ወንጌል በ90 ዓ.ል ማለትም ከእየሱስ እርገት ከ57 ዓመታት በኋላ፣ የማትዮስ ወንጌል ከ95-112 ዓ.ል ማለትም ከእየሱስ እርገት ከ60-80 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ እንደተጻፉ በምሁራን ተገምቷል፡፡ … ሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎችም እስከ 150 ዓ.ል. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተዋቀሩ ይገመታል፡፡ (ገፅ 32-33)
አቶ ሐሰን የጠቀሱት ግምት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ባስቆጠረ በጣም ለዘብተኛ በነበረ ሰው ከተጻፈ መጽሐፍ የተገኘ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የሚገኙት አጥባቂ ሊቃውንት ተመሳሳዮቹ ወንጌላት ከ70 ዓ.ም. በፊት እንደተጻፉ የሚናገሩ ሲሆን ከለዘብተኛ ምሑራን መካከል የሚበዙቱ አራቱንም ወንጌላት ከ95 ዓ.ም. በፊት ያደርጓቸዋል፡፡ በለዘብተኛነታቸውና ክርስትናን በመቃወም የሚታወቁት የአዲስ ኪዳን ምሑር ባርት ኤህርማን እንኳ ማርቆስን 70 ዓ.ም. ገደማ፣ ማቴዎስንና ሉቃስን 80-85 ዓ.ም. ገደማ፣ ዮሐንስን ደግሞ 95 ዓ.ም. ገደማ ያስቀምጣሉ፡፡[5] አቶ ሐሰን የጠቀሱት ግምት መሠረተ ቢስ በመሆኑ በዚህ ዘመን በሚገኙት ምሑራን ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ የክርስትና ተቃዋሚ የነበሩት ኤ ቲ ሮቢንሰን የተሰኙ ዕውቅ ለዘብተኛ ምሑር እንዲያውም ማቴዎስን ከ40-60፣ ማርቆስን ከ45-60፣ ሉቃስን ከ57-60፣ ዮሐንስን ከ40-60 ዓ.ም. ባሉት መካከል አስቀምጠዋል፡፡[6]
የዮሐንስ ወንጌል ዘግይቶ እንደተጻፈ የሚናገሩ የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ሊቃውንት የተጨበጠ የሰነድ ማስረጃ ኖሯቸው ሳይሆን ነገረ መለኮታዊ ይዘቱ ከፍ ያለ በመሆኑ እንዲህ ያለ የተደራጀ ነገረ መለኮት ያለው ጽሑፍ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን የተጻፈ ሊሆን አይችልም ከሚል የተሳሳተ ግምት በመነሳት ነው፡፡ ነገር ግን በሃምሳዎቹ ውስጥ በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተጻፈ ሊቃውንት በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት የሮሜ መልዕክት[7] ከዮሐንስ ወንጌል የጠለቀ ነገረ መለኮታዊ ይዘት የሚታይበት በመሆኑ ይህ ሙግት አሳማኝ አይደለም፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ በግብፅ አገር ነግ ሐማዲ በተባለ ቦታ የተገኘው p52 ወይም “ጆን ሪላንድ ፐፓይረስ” የሚል መጠርያ የተሰጠው የዮሐንስ ወንጌል ቁራጭ ወንጌሉ ዘይግይቶ በሁለተኛው ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የገመቱትን ወገኖች መላ ምት ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጓል፡፡ ዮሐንስ 18፡31-33፣ 37-38 የያዘው ይህ ጽሑፍ መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ዕድሜው በ114-138 ዓ.ም. መካከል መሆኑ ስለተረጋገጠ ወንጌሉ በአንደኛው ክፍለ ዘመን የተጻፈ መሆኑን ከጥርጣሬ በፀዳ ሁኔታ ያረጋግጣል፡፡ በትንሹ ኢስያ የተጻፈ መጽሐፍ በ114-138 ዓ.ም. መካከል በወዲያኛው የሜድትራንያን ባሕር ጫፍ በሚገኙ ትንንሽ ከተሞች ውስጥ የሚዘዋወር ከሆነ በአንደኛው ክፍለ ዘመን ለመጻፉ ምንም ጥርጥር የለውም![8]
ምንጮቻቸው
ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ተመሳሳይነት ስላላቸው “ተመሳሳዮቹ ወንጌላት” (Synoptic Gospels) በመባል ይታወቃሉ፡፡ ዮሐንስ የተጠቀመው የአጻጻፍ ስልትና የታሪክ አወቃቀር ከእነርሱ እንደሚለይ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ልዩነት ማለት ተቃርኖ ማለት ባለመሆኑ ከሌሎቹ ወንጌላት ጋር የሚጣረስበት ምንም ዓይነት ነጥብ የለም፡፡ ለዘብተኛ ምሑራን “በተቃርኖነት” የፈረጇቸው አንዳንድ ነጥቦች በቂ መልስ ያላቸው ናቸው፡፡
አቶ ሐሰን ገፅ 33-34 ላይ በወንጌሉና በተመሳሳዮቹ ወንጌላት መካከል “እስከ ተቃርኖ የሚደርስ ልዩነት” መኖሩን የሚገልፅ ሐሳብ ከኢንሳይክሎፒድያ አሜሪካና ላይ ማግኘታቸውን “ሾላ በድፍን” በሆነ መንገድ መጥቀሳቸው ማስረጃ ያለው ባለመሆኑ ቦታ የምንሰጠው አይደለም፡፡ ኢንሳይክሎፒድያዎች ብዙ ጊዜ የለዘብተኛ ምሑራንን አመለካከቶች እንደሚያንጸባርቁ ይታወቃል፡፡ ሙስሊም ወገኖች ትርጉም ያለው ውይይት ማድረግ ከፈለጉ “እገሌ የተባለ ሰው እንዲህ ብሏል”፣ “እንትን የተባለ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተብሏል” ከሚለው ድፍን ሙግት በመውጣት ተጨባጭ ማስረጃዎችን በማቅረብ መወያየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አቶ ሐሰን ከሜሪል ሲ. ቴኒ መጽሐፍ ላይ ተከታዩን ይጠቅሳሉ፡-
“በዩሐንስ ወንጌልና በሌሎች ሦስት ወንጌላት መካከል በግልጽ የሚታይ ልዩነት በመኖሩ የወንጌሉ ተአማኒነት አጠያየቂ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡” (ገፅ 34)
ልዩነቱን መነሻ በማድረግ ተዓማኒነቱን አጠያያቂ ለማድረግ የሞከሩት ለዘብተኛ ምሑራን ናቸው፡፡ ነገር ግን ቴኒ የዮሐንስ ወንጌል ተዓማኒ መሆኑንና በዮሐንስ በራሱ የተጻፈ መሆኑን በተመለከተ የደረሱበትን ድምዳሜ እንዲህ በማስቀመጥ ይህንን ሐሳብ ውድቅ አድርገዋል፡-
“አራተኛው ወንጌል የተጻፈው በሐዋርያው ዮሐንስ ሳይሆን ስሙ ዮሐንስ ተብሎ በሚጠራ አንድ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መሠረት የለሽ ነው፡፡ ከኢራንየስ ዘመን ጀምሮ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አበው እንደመሰከሩት የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው፡፡ የእስክንድርያው ቀለሜንጦስ (190 ዓ.ም.)፣ አርጌንስ [ኦሪጎን] (220 ዓ.ም.)፣ ሂፓላይትስ [ሂጶሊጦስ] (225 ዓ.ም.)፣ ተርቱልያንና [ጠርጡሊያኖስ] (200 ዓ.ም.) የሙራቶራውያን ጽሑፍ (170 ዓ.ም.) በአንድነት የሚስማሙት የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ መሆኑን ነው፡፡”[9]
በተጨማሪም ዶ/ር ቴኒ የወንጌሉ ጸሐፊ የኢየሱስ ደቀመዝሙር የነበረ መሆኑን የሚያሳዩ አራት ማስረጃዎችን ከወንጌሉ ይዘት በመነሳት አስቀምጠዋል፡፡[10] የወንጌሉ ጸሐፊ ዮሐንስ ስለመሆኑ ፅኑ እምነት መኖሩንም አበክረው ይናገራሉ፡፡[11] ስለዚህ አቶ ሐሰን የቴኒን ሐሳብ ለዓላማቸው እንዲመች ቆርጦ የመጥቀስና የማጣመም ወንጀል ፈጽመዋል፡፡
ብዙ የለዘብተኛ ሥነ መለኮት ሊቃውንትና ጥቂት አጥባቂዎች የማርቆስ ወንጌል ለማቴዎስና ለሉቃስ በምንጭነት እንዳገለገለ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በማርቆስ ውስጥ የማይገኙና የማቴዎስና የሉቃስ የጋራ ያልሆኑ መረጃዎች ደግሞ M እና L በማለት ከሰየሟቸው ንድፈ ሐሳባዊ ምንጮች ተገኝተው ይሆናል ይላሉ፡፡ አቶ ሐሰን ሁለቱንም ሐሳቦች ጠቅሰዋል፡፡ ይህ አመለካከት በወንጌላት ተዓማኒነት ላይ ምንም ዓይነት ችግር የማይፈጥር ቢሆንም ግምት ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
ሌላ ከአራቱ ወንጌላት የሚቀድም የኢየሱስ ትምህርቶች ስብስብ የሆነ፤ ነገር ግን ታሪኩንና ተዓምራቱን ያላካተተ Q የተሰኘ ንድፈ ሐሳባዊ ሰነድ ይኖር ይሆናል የሚልም ግምት አለ፡፡ Q – “Quelle” የሚለው የጀርመንኛ ቃል የመጀመርያ ፊደል ሲሆን “ምንጭ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ ይህ ትወራ መጀመርያ የቀረበው ፍሬድሪክ ሽሌይርማከር (Friedrich Schleiermacher (1768–1834)) በተሰኘ ጀርመናዊ ምሑር ሲሆን ይህ ሰው “የዘመናዊው ለዘብተኛነት አባት” በመባል ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ትወራ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በታላላቅ የነገረ መለኮት ምሑራን ተቃውሞ ደርሶበታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድና አንድ ነው፤ Q የተባለ ሰነድም ሆነ እርሱን የሚመስል ነገር ስለመኖሩ ሊጠቀስ የሚችል ቅንጣት ታክል የታሪክ ማስረጃ የለም! ይህንን ትወራ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እያቀነቀነ የሚገኘው Jesus Seminar የተሰኘው ህልውናው ለማክተም ጫፍ ላይ የደረሰ የለዘብተኞች ማሕበር ነው፡፡[12]
አቶ ሐሰን “ይህ Q የተባለ ምንጭ የበርናባስ ወንጌል ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምት የሰነዘሩ ምሑራንም አልጠፉም” በማለት እጅግ አስቂኝ ነገር ጽፈዋል (ገፅ 34)፡፡ ነገር ግን ለዚህ ማስረጃ የሚሆን ምንም ዓይነት ምንጭ አልጠቀሱም፤ ሊጠቅሱም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም “ውሸት” በሚለው ቃል ሊገለፅ የማይችል ነጭ ውሸት ነውና!
“የበርናባስ ወንጌል” የተሰኘው አናሳ ዕውቀት ባላቸው ሙስሊሞች ዘንድ የሚወደሰው የተጭበረበረ ድርሳን በመካከለኛው ዘመን በአንድ ሙስሊም የተጻፈ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ከአንደኛው ክፍለ ዘመን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ “ወንጌሉ” ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቁርአንም ጋር በእጅጉ ይጣረሳል፡፡ ከዚህ የተነሳ ብዙ ሙስሊም ምሑራን የተጭበረበረ መሆኑን አምነው ተቀብለዋል፡፡ ማስረጃዎቹን ለአሕመዲን ጀበል በጻፍኩት የመልስ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት አስፍሬያለሁ፡፡ ለአንባብያን ጥቅም ስል ከጥቂት ገፆች በኋላ እደግማለሁ፡፡[13]
የ “Q ምንጭ” አቀንቃኞች አጥብቀው ከሚናገሯቸው ነገሮች መካከል አንዱ ምንጩ የኢየሱስን ንግግሮች ብቻ እንጂ ልደቱን፣ ተዓምራቱንና በምድር ላይ ያሳለፋቸውን የመጨረሻ ቀናት ጨምሮ የትኛውንም ታሪኩን እንደማይናገር ነው፡፡ ነገር ግን የበርናባስ “ወንጌል” እነዚህን ሁሉ ይናገራል፡፡ ታድያ ሁለቱ አንድ ሊሆኑ የሚችሉት በምን ስሌት ነው? ሰውየው ሁለቱ አንድ መሆናቸውን መገመታቸው ስለ Q ምንም ዕውቀት እንደሌላቸውና በአጋጣሚ ከመጽሐፍ ላይ ያገኙትን ግርድፍ ሐሳብ ሳያጣሩ መገልበጣቸውን ያመለክታል፡፡
የጸሐፊያን ማንነት
አቶ ሐሰን የብሉይ ኪዳን ሁሉም መጻሕፍት ጸሐፊያን ማንነት በውል እንደማይታወቅ የክርስቲያን ምሑራን መመስከራቸውን አስፍረዋል (ገፅ 35)፡፡ ነገር ግን ለዚህ አባባላቸው ማስረጃ አልሰጡም፡፡
የተወሰኑ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዕድሜ ጠገብት ከመሆናቸው የተነሳ በማን እንደተጻፉ መናገር አዳጋች ቢሆንም የሁሉንም ማወቅ እንደማይቻል መናገር ግን ስህተት ነው፡፡ እንዲህ ብሎ የጻፈ ክርስቲያን ምሑርም የለም፡፡
የመጽሐፈ ኢያሱ፣ መሳፍንትና ሩት ጸሐፊያን ማንነት እንደማይታወቅ የሚገልፁ ሐሳቦችን በክርስቲያኖች ከተጻፉ መጻሕፍት ጠቅሰዋል (ገፅ 35)፡፡ ነገር ግን በነዚሁ መጻሕፍት ውስጥ በአይሁድ ትውፊት መሠረት መጽሐፈ ኢያሱ በራሱ በኢያሱ እንደተጻፈ፤ መሳፍንትና ሩት ደግሞ በነቢዩ ሳሙኤል እንደተጻፉ የሚገልፁ ሐሳቦች ሰፍረዋል፡፡[14] የዘመናችን ምሑራን እነዚህን ትውፊቶች ችላ በማለት ግምቶችን ማብዛታቸው ተቀባይነታቸውን ቢሸረሽርም ይህን ያህል የሚያሳስብ ነገር የለም፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ዋና ትኩረታችን መሆን ያለበት በጸሐፊያኑ ማንነት ላይ ሳይሆን በመልዕክቱ ሰጪ ማንነት ላይ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ብሉይ ኪዳን እውነተኛ ቃለ እግዚአብሔር መሆኑን ስላረጋገጡልን ውጪያዊ ማስረጃዎች ተጨማሪና ትርፍ እንጂ የግድ አስፈላጊ አይደሉም፤ ስለዚህ የጸሐፊያኑን ማንነት በእርግጠኝነት መናገር መቻልና አለመቻል ‹የማወቅ ጉጉታችንን› ከማርካት በዘለለ የሚጨምርልን ፋይዳ እምብዛም ነው፡፡ የብሉይ ኪዳንን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ለክርስቲያን ከእግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስና ከቅዱሳን ሐዋርያቱ ምስክርነት የላቀ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሊኖር አይችልም፡፡ (ዮሐ. 10፡35፣ ማቴ. 5፡18፣ 15፡3፣ 21፡16፣ 22፡31 ማር. 7፡13)፡፡
የኡስታዙ ምስክሮች
አቶ ሐሰን አራቱ ወንጌላት ተዓማኒነት እንሌላቸው ይገልፃሉ፡፡ ዋቢ ይሆኗቸው ዘንድ በቀዳሚነት የጠቀሱት ዴቪድ ስትራውስ (1808-1874) እና አዶልፍ ሐርናክ (1851-1930) የተሰኙ ሁለት ምሑራንን ነው (ገፅ 36)፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ግለሰቦች የለዘብተኛ ሥነ መለኮት አቀንቃኞች የነበሩ ሲሆን ድምዳሜያቸው ከቅርብ ጊዜ ጥናቶች ጋር የሚስማማ አይደለም፡፡
ለዘብተኛ ሥነ መለኮት መሠረቱ ልዕለ ተፈጥሯዊ ክስተቶችን መካድ በመሆኑ ለቁርአንም ቢሆን የሚመለስ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል የተጠቀሱት ሁለቱ ምሑራን የክርስቶስን ከድንግል መወለድ “የፈጠራ ታሪክ” እንደሆነ በመግለፅ ክደዋል፡፡[15] አቶ ሐሰን የነዚህ ምሑራን አቋም እውነት መሆኑን ካመኑ በቁርአን የተገለፀውን የክርስቶስን ከድንግል መወለድ መካዳቸውንም ሊቀበሉ ነው ማለት ነው? ካልተቀበሉ እኛ እንድንቀበል ስለምን ይጠብቁብናል? አቶ ሐሰን የግለሰቦቹን ማንነት በትክክል ሳያጣሩ ያገኙትን ፈረንጅ ስም በግብታዊነት መጥቀስ ምሑራዊ ጥናት ማድረጋቸውን እንደማያረጋግጥ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል፡፡
የኡስታዙ ጠማማ ብዕር
ኡስታዙ ተዓማኒ ያልሆኑ ምስክሮችን ካስደመጡን በኋላ የሃቀኛ ክርስቲያን ምሑራንን ሐሳቦች በመቆራረጥና በማጣመም በወንጌላት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው በማስመሰል ጽፈዋል (ገፅ 36-37)፡፡ የአቶ ሐሰንን ቅጥፈት ለማጋለጥ እሳቸው የጠቀሱትንና ትክክለኛውን ሐሳብ በሠንጠረዥ ጎን ለጎን በማድረግ እናሳያለን፡፡
አቶ ሐሰን የጠቀሱት ምሑራን ሉቃስ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ መሆኑን መጠራጠር የጀመሩት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ … እንደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሁሉ ስለ ሉቃስም ያለን መረጃ የተወሰነ ነው፡፡” (ቲም ፌሎስ፣ የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ በትምህርተ መለኮት ማስፋፍያ (ት.መ.ማ) መልክ የተዘጋጀ፣ 2ኛ መጽሐፍ፣ ገጽ 336) | በመጽሐፉ ውስጥ የሠፈረው ሙሉ ሐሳብ “የጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት ባልደረባ የነበረው ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ መሆኑን ሁሉም የጥንት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል፡፡ ምሑራን ሉቃስ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ መሆኑን መጠራጠር የጀመሩት ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ምሑራን ጥርጣሬያቸውን ያቀረቡት ከሉቃስ ዘመን በኋላ ስለ ተነሱት የቤተ ክርስቲያን ችግሮች የሚዘግቡ አሳቦች በመጽሐፉ ውስጥ እደሚገኙ በመግለፅ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ አለመሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ መረጃ አልተገኘም፡፡ እንደ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሁሉ ስለ ሉቃስም ያለን መረጃ የተወሰነ ነው፡፡ ከሦስቱ የጳውሎስ መልእክቶች እንደምንረዳው፣ ሉቃስ በሙያው ሐኪም የነበረ ሲሆን፣ የጳውሎስ የቅርብ ጓደኛና የሥራ ባልደረባ ነበር፡፡ ሉቃስ ሌሎች ስደትን ፈርተው ገሸሽ ባሉ ጊዜ ከጳውሎስ ያልተለየ ሰው ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ ስለ ሉቃስ የምናውቃቸውን ነገሮች የምናገኘው ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ነው፡፡ (ቲም ፌሎስ፣ የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ በት.መ.ማ መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገጽ 336) |
ምርመራ
- ከአንደኛ መጽሐፍ የጠቀሱትን ከሁለተኛ መጽሐፍ እንደሆነ በመግለፅ የምንጭ ስህተት ፈፅመዋል፡፡
- ሉቃስ የዚህ ወንጌል ደራሲ አለመሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ መረጃ አለመገኘቱን የሚናገረውን አረፍተ ነገር ሆነ ብለው ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሉቃስ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የቅርብ ወዳጅና በሙያው ኀኪም እንደነበረ የሚናገረውን ክፍል ቆርጠው በማስቀረት የማይታወቅ ሰው ለማስመሰል ጥረት አድርገዋል፡፡
ሐሰን የጠቀሱት ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን የሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡ (ቲም ፌሎስ የአዲስ ኪዳን መምሪያና ማብራሪያ በትምህርተ መለኮት ማስፍፊያ (ት.መ.ማ.) መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገፅ 440) | በመጽሐፉ ውስጥ የሠፈረው ሙሉ ሐሳብ በ115 ዓ.ም. ኢግናቲየስ የተባለ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከዮሐንስ ወንጌል ጠቅሶ ጽፎአል፡፡ ከእርሱ በኋላ መጽሐፍ የጻፉት ሌሎች ሰዎች ሐዋርያው ዮሐንስ ይህንን ወንጌል በኤፌሶን ሆኖ እንደጻፈው ገልጸዋል፡፡ በጥንት ጽሑፎች ውስጥ ዮሐንስ ይህንን መጽሐፍ እንደጻፈ የሚያጠራጥር ነገር የለም፡፡ ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን ያልሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡ ምክንያታቸውም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመሆኑ የቀረበው ትምህርት በጣም የጠነከረ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በ100 ዓ.ም. ላይ ከዚህ ደረጃ መድረስ አትችልም የሚል ነው፡፡ … የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስ ይህንን መጽሐፍ እንደጻፈው የሚያስቡ ሰዎች የዘብዴዎስ ልጅ የሆነው ዮሐንስና ሽማግሌው ዮሐንስ አንድ ሰው ነው የሚል አሳብ አላቸው፡፡ ይህ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ያስተማረችው አሳብ ሲሆን ለመጠራጠር የሚያበቃ ምክንያት የለንም፡፡ (ቲም ፌሎስ የአዲስ ኪዳን መምሪያና ማብራሪያ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ት.መ.ማ.) መልክ የተዘጋጀ፣ 1ኛ መጽሐፍ፣ ገፅ 440) |
ምርመራ
- ኢግናጢዮስ በ115 ዓ.ም. ከወንጌሉ ጠቅሶ መጻፉን፣ ከእርሱ በኋላ የነበሩት ሰዎች ዮሐንስ ወንጌሉን በኤፌሶን እንደጻፈ መግለፃቸውን፣ ወንጌሉ በዮሐንስ የተጻፈ መሆኑን የሚያጠራጥር ነገር እንደሌለ፣ ወዘተ. የሚናገሩትን አረፍተ ነገሮች ሆነ ብለው ቆርጠው አውጥተዋል፡፡
- ሐሰን ታጁ ወንጌላውያን ምሑራን እንኳ ሳይቀሩ የዮሐንስ ወንጌል በዮሐንስ እንደተጻፈ የማያምኑ ለማስመሰል “ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን የሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ” በማለት ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን “የሆኑ” የምትለዋ ቃል ራሳቸው ፈጥረው የተኳት እንጂ በቦታው ላይ እንደሌለች ልብ ይሏል፡፡ ጽሑፉ በትክክል የሚለው እንዲህ ነው፡- “ዛሬ ግን ብዙ ወንጌላውያን ያልሆኑ ምሁራን ይህንን ወንጌል ዮሐንስ እንደጻፈው ይጠራጠራሉ፡፡”
የማቴዎስን ወንጌል በተመለከተ ተከታዩን አባባል በትዕምርተ ጥቅስ በማስቀመጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ላይ እንዳገኙ ገልፀዋል፡-
‹የማቲዮስ ወንጌል፡- “ወንጌሉን የጻፈው ማቲዮስ ነው” ያሉት የቀደሙ የቤተክርስቲያን አባቶች ናቸው እንጂ የጻፈው ስም አልተጻፈበትም፡፡ መች እንደተጻፈ አልታወቀም፡፡› (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 41)
ነገር ግን እንዲህ የሚል ነገር በጠቀሱት የመዝገበ ቃላቱ ገፅ ላይ የለም፡፡ “ማቴዎስ” የሚለው ማውጫ ገፅ 52-53 ላይ የሚገኝ ሲሆን ሐሰን ከጠቀሱት የተለየ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“እንደ ጥንት ቤ.ክ. ትውፊት የመጀመርያውን ወንጌል የጻፈው ማቴዎስ ነው፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሊቃውንት ይህን ሐሳብ ባይቀበሉትም የወንጌሉ አጻጻፍ በጥንቃቄ ከሚጽፍና ከሚሠራ ወደ ወንጌላዊነት ከተለወጠ ቀራጭ አሠራር ጋር ይስማማል፡፡ የማቴዎስ ወንጌል የተጻፈባቸው ዘመናት በብዙ ሊቃውንት የተለያዩ እንደሆኑ ቢጠቀስም አንዳንዶች ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ከ50 ዓ.ም. በፊት እንደሆነ ሲያመለክቱ ሌሎች ግን ጸሐፊው የማርቆስን ወንጌል ተመልክቶ ኢየሩሳሌም ከወደቀችበት ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንዳዘጋጀው ይናገራሉ፡፡”[16]
ስለ ማርቆስ ደግሞ ከቴኒ መጽሐፍ ላይ ተከታዩን ጠቅሰዋል፡-
‹ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ስለዚህኛው ወንጌል ጸሐፊ ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ መጽሐፉ በየትኛውም ሥፍራ ስሙን አይጠቅስም፡፡› (ሜሪል ሲ ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት ገፅ 236)
ነገር ግን ቴኒ ስለ ማርቆስ ወንጌል የተናገሩት ይህንን ብቻ አይደለም፡፡ ማርቆስን የተመለከተ በ115 ዓ.ም. የተነገረ ከፓፒያስ የተገኘ መረጃ ኢዮስቢዮስ (375 ዓ.ም.) በጻፈው ጽሑፍ ውስጥ ተጠብቋል፡፡ ይህ መረጃ በቀዳሚነት የተላለፈው ከሽማግሌው ከዮሐንስ (ከሐዋርያው ዮሐንስ) ሲሆን፤ ማርቆስ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ደቀ መዝሙር ባይሆንም የጴጥሮስ አስተርጓሚ የነበረ መሆኑን፤ መረጃዎቹን ሳይጨምርና ሳይቀንስ ያለ አንዳች ስህተት በታላቅ ጥንቃቄ መጻፉን እንደመሰከረ ቴኒ ጽፈዋል፡፡[17] የጸሐፊውን ማንነት በተመለከተ አበው ስለሰጡት መረጃ ተዓማኒነት ቴኒ እንዲህ ይላሉ፡-
“የእነኚህ ታሪኮች አስተማማኝነት አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ የሁለተኛው ወንጌል ጸሐፊ ማርቆስ መሆኑን ሁሉም ተስማምተዋል፤ ወንጌሉንም ከጴጥሮስ ስብከት ጋር ያያይዙታል፡፡”[18]
አቶ ሐሰን ምሑራዊ ምንጮችን የሚጠቅሱበት መንገድ ፍፁም የተጭበረበረና ታዓማኒነት የጎደለው ነው፡፡ እንዲህ ያለ የሸፍጥ አካሄድና አንባቢን ለማሳሳት የሚደረግ ቅጥፈት ከአንድ የሃይማኖት አስተማሪ የሚጠበቅ አይደለም፡፡
የኒቅያ ጉባኤና ቀኖና
እንዲህ በማለት የቅጥፈት ዲስኩራቸውን ይቀጥላሉ፡-
ከኒቃያ ጉባኤ በፊት ከ270 ያላነሱ የተለያዩ የወንጌል አይነቶች እንደነበሩ የታሪክ ጸሐፍት ይገልጻሉ፡፡ በተለይ የእየሱስን አምላክነት በማይቀበሉ አሐዳውያን ክርስትያኖች እጅግ ጠቃሚ የታሪክና የስነ መለኮት ምንጮች ነበሩ፡፡ ጣኦት አምላኪው የወቅቱ የሮም ገዥ በጠራው ጉባኤ ላይ ግልጽ ባልሆነ መስፈርት አሁን በክርስትያኖች እጅ የሚገኙት የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ተመርጠው ሌሎች እንዲቃጠሉና እንዲወገዱ፣ ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደረገ፡፡ (ገፅ 37)
“ኒቃያ” ያሉት ኒቅያ ለማለት ነው፡፡ አቶ ሐሰን ይህንን መረጃ ከየት እንዳመጡ ምንጭ አልጠቀሱም፡፡ ሊጠቅሱም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ቅጥፈት ነውና፡፡ (በዚሁ ገፅ ላይ የኒቅያን ጉባኤ ውሳኔዎች በተመለከተ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይሰጡ ከያዙት ርዕስ ጋር የማይገናኙ ሌሎች ቅጥፈቶችንም አክለዋል፡፡)
በኒቅያ ጉባኤ ላይ የቅዱሳት መጻሕፍት ምርጫ መደረጉን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ማስረጃ እደግመዋለሁ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም! ይህንንም ሐሳብ የሚቀበል የታሪክም ሆነ የሥነ መለኮት ምሑር የለም! አቶ ሐሰንና መሰሎቻቸው ይህንን ተራ የመንደር አሉባልታ በማናፈስ የተሳሳተ መረጃ የመገቡትን ሕዝባቸውን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፡፡
ቅድመ ኒቅያ በሁለተኛውና በሦስተኛው ክፍለ ዘመናት የተጻፉ በክርስቲያኑ ማሕበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያጡ ጽሑፎች መኖራቸው ቢታወቅም በሐሰት የጌታ ሐዋርያት ስም የተለጠፈባቸው የተጭበረበሩ ጽሑፎች ነበሩ፡፡ ይህንን ሃቅ ለዘብተኛም ሆኑ አጥባቂ፣ ሃይማኖተኛም ሆኑ ከሃዲ ሊቃውንት ይስማሙበታል፡፡[19] አብዛኞቹ በኖስቲሳውያን የተጻፉ ሲሆኑ ኖስቲሳውያን አሐዳውያን አልነበሩም፡፡ እነዚህን የተጭበረበሩ ጽሑፎች ክርስቲያኖች የመጠበቅም ሆነ የመንከባከብ ግዴታ ባይኖርባቸውም ብዙዎቹ በክርስቲያናዊ ጽሑፎች ውስጥ ተጠቅሰው እንዲሁም የእጅ ጽሑፎቻቸው ተጠብቆ ለዚህ ዘመን ስለበቁ ይዘታቸው ምን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአጭር ቃል ቁምነገር የሌላቸው የተረታ ተረት መጻሕፍት ናቸው፡፡ አስገራሚው ነገር ግን የእነዚህ መጻሕፍት ተረታ ተረቶች በቁርአን ውስጥ ሰፍረው መገኘታቸው ነው፡፡ ይህ ለምንና እንዴት ሊሆን እንደቻለ በምዕራፍ ሦስት መልሳችን የምንመለከተው ይሆናል፡፡
የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና በአንድ ጀንበር የተከናወነ ሳይሆን ለክፍለ ዘመናት የዘለቀ በጥንቃቄና በፈሪሃ እግዚአብሔር የተከናወነ ሂደት ነበር፡፡ አንድ ቡድን የግል ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ተነስቶ መጻሕፍትን በመምረጥ ክርስቲያኖች እንዲቀበሉ አላስገደደም፡፡ ነገር ግን በሐዋርያት የተጻፉት መጻሕፍት ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በመጣ ተያያዥነት በሕዝበ ክርስቲያኑ አጠቃላይ መግባባት በሂደት ነጥረው በመውጣት ተቀባይነት ለማግኘት በቅተዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ጥንቃቄና ታማኝነት እንጂ ማጭበርበርም ሆነ ሸፍጥ አልነበረም፡፡ ከዚህ አንፃር አቶ ሐሰን በመጽሐፋቸው ገፅ 38 ላይ “በሂደቱ የታየ ማጭበርበር” በሚል ርዕስ ስር “ምሑራን” ተናግረውታል በሚል የጠቀሷቸው ክሶች መሠረት የላቸውም፡፡
የአዳዲስ መረጃዎች መገኘት
አቶ ሐሰን እንዲህ በማለት ጽፈዋል፡-
የእየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው ሐዋርያው በርናባስ አዘጋጀው የተባለው ወንጌል መገኘቱ፣ የሙት ባሕር ጥቅሎች (The Dead Sea scrolls) እና ሌሎችም መረጃዎች የምእራባዊ ምሁራንን ቀልብ መሳባቸው አልቀረም፡፡ እናም ስለ እየሱስ ማንነትም ሆነ ስለ እውነተኛ ትምህርቱ አስደናቂ መረጃዎች መገኘት ቀጥለዋል፡፡ ከነዚህ መረጃዎች በመነሳት የታሪክ ምሁራን ስለ እየሱስ ማንነት የወንጌል ጸሐፍት ካቀረቧቸው የተለዩ መረጃዎችን እያገኙ ነው፡፡ (ገፅ 38-39)
ይህ እውነቱን ለመናገር እጅግ አሳፋሪ ቅጥፈት ነው፡፡ የበርናባስ “ወንጌል”ም ሆነ የሙት ባሕር ጥቅሎች እስላማዊ አቋማቸውን የሚያፈርሱ መሆናቸውን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
የበርናባስ “ወንጌል” የፈጠራ ጽሑፍ ወይስ እውነተኛ ወንጌል?
የበርናባስ “ወንጌል” በመባል የሚታወቀው ጽሑፍ በመካከለኛው ዘመን በአንድ ሙስሊም የተጻፈ የፈጠራ ጽሑፍ ሲሆን የአንደኛው ክፍለ ዘመን ሽታ እንኳ የለውም፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጡ ብዙ ነጥቦች በውስጡ ይገኛሉ፡-
- “ክርስቶስ” የሚለው የግሪክ ቃልና “መሲህ” የሚለው የእብራይስጥ ቃል “የተቀባ” የሚል ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው ሲሆን በአንደኛው ክፍለ ዘመን የኖረ የትኛውም አይሁዳዊ ሁለቱ ቃላት ተመሳሳይ ትርጉም እንዳላቸው ያውቃል፡፡ በርናባስን የመሰለ የግሪክ ቋንቋ ከሚነገርባት ከአሌክሳንደርያ የመጣ አይሁዳዊ ይህንን ቀላል እውነታ ይዘነጋል ተብሎ በፍፁም ሊታሰብ አይችልም፡፡ ነገር ግን የበርናባስ “ወንጌል” ገና ሲጀምር ኢየሱስን “ክርስቶስ” ብሎ የጠራው ሲሆን (ገፅ 2)፤ ነገር ግን ምዕራፍ 42 ላይ ኢየሱስ መሲህ መሆኑን መካዱን ይነግረናል፡፡
- ምዕራፍ 3 ላይ ሄሮድስና ጲላጦስ በአንድ ዘመን የይሁዳ ገዢዎች እንደነበሩ ይናገራል፡፡ ነገር ግን ሄሮድስ ከ37-4 ዓ.ዓ. ይሁዳን ብቻውን የገዛ ሲሆን ጲላጦስ ደግሞ ከ26-36 ዓ.ም. ነበር የገዛው፡፡[20] በርናባስ ይህንን የታሪክ ቅጥፈት ሊፈፅም የሚችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡
- በምዕራፍ 20-21 ላይ ኢየሱስ በጀልባ ወደ ናዝሬት ከተማ እንደሄደና የከተማይቱ ጀልባ ቀዛፊዎች እንደተቀበሉት ይናገራል፡፡ ነገር ግን ናዝሬት ከገሊላ ባሕር 14 ኪ.ሜ. ርቃ በተራሮች ተከባ የምትገኝ መሆኗ ይታወቃል፡፡[21] በዚሁ ቦታ ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ሽቅብ እንደወጣ የሚናገር ሲሆን ይህም ሌላ ጂኦግራፍያዊ ስህተት ነው፡፡ የቅፍርናሆም ከተማ አቀማመጥ ከናዝሬት በላይ ከፍታ ላይ ሳይሆን ታች የገሊላ ባሕር አጠገብ ነው፡፡ ኢየሱስ በተደጋጋሚ ወደ እነዚህ ከተሞች በመሄዱ ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ በሚገባ ያውቋቸዋል (ማቴዎስ 2:23፣ 4:13፣ 8:5፣ 11:23፣ 17:24፣ 21:11፣ 26:71፣ ሉቃስ 4:16 )፡፡ ነገር ግን የበርናባስ “ወንጌል” ጸሐፊ ይህንን ስህተት በመስራት አጭበርባሪነቱን ይፋ አውጥቷል፡፡
የበርናባስ “ወንጌል” የእስልምናን ትምህርቶች የሚደግፍባቸው ብዙ ቦታዎች ቢኖሩም ነገር ግን ደግሞ ሙስሊሞች በእርሱና በቁርአን መካከል እንዲመርጡ የሚያስገድዱ የሚጣረስባቸው ብዙ ነጥቦች በውስጡ ይገኛሉ፡-
- ቁርአን መርየም ዒሳን የወለደችው በምጥ እንደሆነ የሚናገር ሲሆን (ሱራ 19፡22-23) የበርናባስ “ወንጌል” ግን ያለ ምንም ምጥ እንደወለደችው ይናገራል (ም. 3)፡፡
- ቁርአን ዒሳ መሲህ መሆኑን በተደጋጋሚ የሚናገር ሲሆን (ሱራ 3፡45) የበርናባስ “ወንጌል” ግን ዒሳ መሲህ መሆኑን መካዱን (ም. 42) እና መሐመድ መሲህ መሆናቸውን መመስከሩን ይናገራል (ም. 97)፡፡ በቁርአን ውስጥም ሆነ በየትኛውም እስላማዊ ጽሑፍ ውስጥ መሐመድ መሲህ መሆናቸው አልተጻፈም፡፡
- ቁርአን አንድ ሙስሊም ወንድ እስከ አራት ሚስቶች እንዲያገባ የሚፈቅድ ሲሆን (ሱራ 4፡3) የበርናባስ “ወንጌል” ግን ድርብ ጋብቻን አጥብቆ በመቃወም አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያንጸባርቃል (ም. 115)፡፡
- ቁርአን ሰባት ሰማያት ብቻ እንዳሉ የሚናገር ሲሆን (ሱራ 17፡44) የበርናባስ “ወንጌል” ዘጠኝ መኖራቸውን ይናገራል (ም. 178)፡፡
የበርናባስ “ወንጌል” የመካከለኛው ዘመን ፈጠራ መሆኑን የሚያሳዩ ጠቋሚ ምልክቶች በውስጡ ይገኛሉ፡፡
- በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ኢዮቤ ልዩ በየ ሃምሳ ዓመቱ እንዲከበር ትዕዛዝ የተሰጠ ሲሆን (ዘሌዋውያን 25፡10-11) በ1300 ዓ.ም. የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ የነበሩት ቦኒፌስ ስምንተኛ በየ መቶ አመቱ እንዲከበር አውጀው ነበር፡፡ ነገር ግን ቀጣዩ ጳጳስ ክሌመንት አራተኛ አዋጁን በመሻር ተመልሶ በየ ሃምሳ ዓመቱ እንዲከበር ስላወጁ በ1350 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡[22] የበርናባስ “ወንጌል” ግን ይህንን የጳጳሱን የተሳሳተ አዋጅ በመቀበል በምዕራፍ 82 ላይ የኢዮቤ ልዩ በዓል በየ መቶ ዓመቱ እንደሚከበር ይናገራል፡፡ ይህም መጽሐፉ በመካከለኛው ዘመን የተጻፈ ስለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡
- ይህ መጽሐፍ የመካከለኛው ዘመን ፈጠራ መሆኑን የሚያመለክተው ሌላው ነጥብ ከዘመኑ ጸሐፊ ከዳንቴ ሥራዎች ላይ የተቀዱ ሐሳቦች በውስጡ መገኘታቸው ነው፡፡[23] ለምሳሌ ያህል ከገነት በፊት ዘጠኝ ሰማያት መኖራቸውን ጸሐፊው ከዳንቴ ልበ ወለድ ላይ መውሰዱ ግልፅ ነው (ም. 178)፡፡
- የበርናባስ “ወንጌል” ቀዳሚያን የእጅ ጽሑፎች በጣልያንኛና በእስፓኒሽ የተጻፉ ሲሆኑ ምርመራ ተደርጎባቸው ከአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የተጻፉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡[24] እውነተኛው በርናባስ ጽፎት ቢሆን ኖሮ በእብራይስጥ፣ በግሪክ ወይም በአረማይክ ነበር መጻፍ የነበረበት፡፡
የጠለቀ ዕውቀት የሌላቸው ሙስሊሞች ይህንን መጽሐፍ እንደ ተዓማኒ ወንጌል ቢያራግቡትም ነገር ግን ጉዳዩን በጥንቃቄ ያጠኑ ሙስሊም ሊቃውንት ሳይቀሩ ሀሰተኛ መጽሐፍ መሆኑን ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡[25] አቶ ሐሰን ይህንን የፈጠራ መጽሐፍ ለሙግታቸው እንደ ግብአት መጠቀማቸው ምሑራዊ ጥናት አለማድረጋቸውን ያመለክታል፡፡
የሙት ባሕር ጥቅልሎች የእስልምና ስጋቶች
“የቁምራን ጥቅልሎች” ወይም “የሙት ባህር ጥቅልሎች” በመባል የሚታወቁ ጥንታውያን የብሉይ ኪዳንና ሌሎች ጽሑፎች መገኘት ከሃያኛው ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ስኬቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ እነዚህ ጽሑፎች ክርስቲያኖችና አይሁድ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እምነት ትክክል መሆኑንና እስልምና ስህተት መሆኑን ከሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መካከል ግንባር ቀደምት ናቸው፡፡
ቁምራን በሙት ባህር አካባቢ የሚገኝ እሴናውያን የተሰኙ ኃይማኖተኛ ማህበረሰቦች ይኖሩበት የነበረ አካባቢ ነው፡፡ ጥቅልሎቹን ለመጀመርያ ጊዜ ያገኘው አንድ የፍየል እረኛ አረብ ወጣት ሲሆን ጊዜው ደግሞ 1947 ነበር፡፡ ይህ አረብ ወጣት ያገኛቸውን ጥቅልሎች ወደ ከተማ በመውሰድ የጥንታዊ መዛግብት ሻጭ ለነበረ ካንዶ ለተባለ ሰው ሰባት ጥቅልሎችን ሸጠለት፡፡ ይህም ሰው ከጥቅልሎቹ መካከል ሦስቱን ለአንድ የእስራኤል ዩኒቨርስቲ መምህርና የተቀሩትን አራቱን ደግሞ በገዳም ውስጥ ለሚኖሩ ማር አትናሲውስ ለተሰኙ አንድ ሦርያዊ መነኩሴ ሸጠ፡፡ መነኩሴው እነዚህን ጥቅልሎች ወደ አሜሪካን ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ሪሰርች ባመጡበት ወቅት ነበር የቁምራን አካባቢ የምዕራባውያን ምሑራንን ትኩረት ማግኘት የቻለው፡፡ የመጀመርዎቹ ጥቅልሎች የተገኙበት ዋሻ በ1949 ዓ.ም. “አንድ ቁጥር ዋሻ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በ1949 እና በ1956 መካከል የተለያዩ ጥንታዊ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የመጻሕፍት ጥቅልሎችና ቁርጥራጮችን የያዙ አስር ተጨማሪ ዋሻዎች ተገኝተዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በተገኙ በነዚህ ዋሻዎች ውስጥ በ250 ዓ.ዓ. እና በ68 ዓ.ም. መካከል የተጻፉ ወደ 800 የሚሆኑ በእብራይስጥ፣ በግሪክና በአራማይክ ቋንቋ የተጻፉ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት፣ የአፖክሪፋ መጻሕፍት፣ የተለያዩ መዝሙሮች፣ የእሴናውንን እምነት የሚገልጹ ጽሑፎችና ዋጋቸው በገንዘብ ሊተመን የማይችል ሌሎች ጥንታውያን መዛግብት ተገኝተዋል፡፡ ከመጽሐፈ አስቴር በስተቀር ሁሉንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሚወክሉ የእጅ ጽሑፎችና ቁርጥራጮች የተገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል የትንቢተ ኢሳይያስን ሙሉ መጽሐፍ የያዘውና ከክርስቶስ ልደት በፊት 200 ዓመታትን በመቅደም እንደ ተጻፈ የተረጋገጠው አስደናቂ የብራና ጥቅልል ይገኝበታል፡፡
ከ2000 ዓመታት በላይ እድሜ ያለው የኢሳይያስ ጥቅልል መጽሐፍ፡፡ ይህ ጥቅልል በቁምራን ዋሻ ውስጥ ከተገኙ ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የፎቶ ምንጭ፡ bible-researcher.com |
ሌላው አስደናቂ ነገር ደግሞ ጆሴ ኦ’ክላሃን የተሰኙ እስፔናዊ ፓሌኦግራፈር የማርቆስ፣ ሐዋርያት ሥራ፣ ሮሜ፣ 1ጢሞቴዎስ፣ 2ጴጥሮስ እና ያዕቆብ መልዕክት ክፍሎችን በተወሰኑ ቁርጥራጮች ላይ ማንበብ መቻላቸውን መናገራቸው ነው፡፡ ስለ ጉዳዩ ኒውዮርክ ታይምስ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር ፡- “የአባ ኦ’ክላሃን መላምት ተቀባይነት ካገኘ በጥቂቱ የቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ከኢየሱስ ሞት በኋላ ጥቂት ዓመታትን ብቻ በመዘግት መጻፉን ያረጋግጣል፡፡”[26]
የኢሳይያስ ጥቅልል ሁለተኛው ገጽ፤ ከኢሳይያስ 1፡26-2፡21 ድረስ ያለውን ክፍል ይዟል፡፡ የፎቶ ምንጭ፡ bible-researcher.com |
ኮዴክስ ሲናይቲከስ – እስልምናን ያስደነገጠ ግኝት
አቶ ሐሰን እንዲህ በማለት ጽፈዋል፡-
The Guardian በሰኞ July 6,2009 እትሙ Worlds Oldest bible goes online በሚል ርእስ ከየትኛውም መጽሐፍ ‹ቅዱስ› የቀደመ የተባለለትን ጥንታዊ መጽሐፍ ‹ቅዱስ› አስተዋውቆናል፡፡ እድሜው 1600 ዓመታት ሲሆን ይዘቱ አሁን በክርስትያኖች እጅ ከሚገኙ መጽሐፍ ቅዱሶች በከፊል ይለያል፡፡ (ገፅ 39)
አቶ ሐሰን በዘጋርዲያን ዘገባ ላይ ቅጥፈት አክለዋል፡፡ የመጣጥፉ ሙሉ ቃል በጋዜጣው ድረ-ገፅ ላይ የሠፈረ ሲሆን ይዘቱ አሁን በክርስቲያኖች እጅ ከሚገኘው መለየቱን አልዘገበም፤ ሊዘግብም አይችልም፡፡[27] ምክንያቱም አሁን በክርስቲያኖች እጅ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህና በሌሎች ጥንታውያን የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ነውና!
ኮዴክስ ሲናይቲከስ ወይም አሌፍ በመባል የሚታወቀው ይህ ጥንታዊ ጽሑፍ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘው በሲና ተራራ ላይ በሚገኘው ቅድስት ካትሪን ገዳም ውስጥ በ1844 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሎቤጎት ፍሬድሪክ ኮንስታንቲን ቮን ቲሼንዶርፍ (1815-1874) የተሰኘ ሰው ገዳሙን በጎበኘበት ወቅት የገዳሙ መነኮሳት ማገዶ በሚያስቀምጡበት ቅርጫት ውስጥ አርባ ሦስት የብራና ቅጠሎችን አገኘ፡፡ እነዚህ የብራና ቅጠሎች 1ዜና፣ ትንቢተ ኤርምያስ፣ መጽሐፈ ነህምያና አስቴርን የያዙ ነበሩ፡፡ ይህንን የሰብዓ ሊቃናት (ሰብቱጀንት) ጽሑፍ በጀርመን አገር ወደሚገኘው የሌይፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት አመጣው፡፡ ኮዴክስ ኦገስታኑስ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት እዚያው ቆየ፡፡
ኮዴክስ ሲናይቲከስ (አሌፍ)፡፡ የፎቶ ምንጭ www.codexsinaiticus.net |
ቲሼንዶርፍ በ1853 ለሁለተኛ ጊዜ ገዳሙን በመጎብኘት የተቀሩትን የመጽሐፉን ክፍሎች ማፈላለግ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ምንም ሳያገኝ በመቅረቱ ምክንያት ወደ አገሩ ለመመለስ ሲዘጋጅ ሳለ በ1859 የገዳሙ አበምኔት ግማሽ የሰብዓ ሊቃናት (ብሉይ ኪዳን) ክፍልና ማርቆስ 16፡1-20 እንዲሁም ዮሐንስ 7፡53-8፡11 ሲቀር ሁሉንም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የያዘ መጽሐፍ አሳየው፡፡ ይህ ጽሑፍ 364 ገፆች ያሉት ሲሆን በ1933 ዓ.ም. የብሪቲሽ መንግሥት በግዢ የራሱ አድርጎታል፡፡[28] ኮዴክስ ሲናይቲከስ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ተጠብቆ መቆየቱን በማረጋገጥ የእስልምናን ሙግት ውድቅ ከሚያደርጉ ማስረጃዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ግኝቱ ለእስልምና መጥፎ ዜና ነው፡፡
የኡስታዙ የተጭበረበረ ምንጭ አጠቃቀስ
አቶ ሐሰን ገፅ 39 ላይ “የታሪክ ተመራማሪው” ጆሐነስ ሌህማን የተናገሩት ነው በሚል የጠቀሱት ሐሳብ የምንጭ አጠቃቀሳቸው ምን ያህል ደካማና የተጭበረበረ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ሐሳቡ ሲጠቀለል የታሪክ ተመራማሪዎች የሚያምኑበት ኢየሱስና የወንጌል ጸሐፍት ያቀረቡት ኢየሱስ የተለያዩ መሆናቸውን እንዲሁም የክርስቲያን ሥነ መለኮት ሊቃውንት መዋሸታቸውን መናዘዛቸውን የሚገልፅ ነው (ገፅ 39)፡፡
አቶ ሐሰን ይህንን ፈረንጅ ለክርስትና ቀናዒ የሆነ ምሑርና የታሪክ አዋቂ አድርገው ቢያቀርቡትም ስለሰውየው ምንም ነገር እንደማያውቁ፣ በእርሱ የተጻፈ አንድ መስመር እንኳ እንዳላነበቡና ስሙን የሆነ ቦታ ስላዩ ብቻ እንደጠቀሱት ግልፅ ነው፡፡ የጠቀሱትን መጽሐፍ እንኳ በወጉ አላነበቡትም፡፡ ሐሳቡን የወሰዱት “Jesus the Prophet of Islam” በሚል ርዕስ ተጽፎ “ኢየሱስ የኢስላም ነቢይ” ተብሎ ወደ አማርኛ ከተመለሰ ሀተታ ባልቴት ሲሆን በመጽሐፉ መሠረት ሌህማን የተሰኘው “የታሪክ ተመራማሪ” ሔንዝ ዛህርንት በተባለ ሌላ ሰው የተነገረውን ጠቅሶ እንዳቀረበ እንጂ አቶ ሐሰን እንዳሉት የራሱ ንግግር እንደሆነ አልተጠቀሰም፡፡[29] ሌህማን የተባለው ሰው ራሱ ይህንን ሐሳብ የወሰደው በቀጥታ ከሔንዝ ዛህርንት ሳይሆን የእርሱን ሐሳብ ከጠቀሰ ክሬውዝ ቬርላግ ከተሰኘ ሰው እንደሆነ በመጽሐፉ ላይ በዋቢነት የተጠቀሰው ምንጭ ያመለክታል፡፡[30]
እስኪ የዘገባ “ሰንሰለቱን” ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፡፡ ዛህርትን የተባለ ሰው የጻፈውን ቬርላግ የተባለ ሰው ጠቀሰ፡፡ ቬርላግ የጠቀሰውን ሌህማን የተባለ ሰው ጠቀሰ፡፡ ሌህማን የጠቀሰውን መሐመድ ዓታ ኡር-ረሂምና ባልደረባቸው ጠቀሱ፡፡ እነርሱ የጠቀሱትን ሌሎች ሰዎች ወደ አማርኛ ተረጎሙት፡፡ አቶ ሐሰን ደግሞ ከዚህ የአማርኛ ትርጉም ላይ ጠቀሱ፡፡ የተጠቃሾቹ ብዛት ከሐዲስ አዘጋገብ ጋር አልተመሳሰለም? ይህ ኢስናድ ዶኢፍ ወይም መውዱዕ አለመሆኑንና ሳሂህ መሆኑን ኡስታዙ ሊያረጋግጡልን ይችሉ ይሆን?
ወንጌላት ተበርዘዋልን?
አቶ ሐሰን “ወንጌላት ተበርዘዋል” ለሚለው እምነታቸው ዋቢ ይሆኑ ዘንድ በአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕትመቶች ውስጥ የተገለጹትን የንባብ ልዩነቶች (Textual Variants) “ኢትዮጵያዊ ናሙናዎች” በሚል ርዕስ ስር ጠቅሰዋል (ገፅ 40-41)፡፡ የጠቀሷቸው ነጥቦች ስድስት ሲሆኑ የመጨረሻዎቹ ሦስት ነጥቦች የማርቆስ ወንጌልን መዝጊያ የተመለከቱ በመሆናቸው ከሦስት ጥያቄ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የቀረቡት ጥያቄዎች ሲጠቀለሉ አራት ናቸው፡፡
ላቀረቧቸው ጥያቄዎች አስቀድመን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት የንባብ ልዩነቶች አጠቃላይ ማብራርያ በመስጠት ምላሽ እንሰጣለን፤ በማስከተል ደግሞ ያነሷቸውን ምሳሌዎች አንድ በአንድ እንመለከታለን፤ በመጨረሻም የገዛ ሙግታቸውን ወደ ቁርአን በማዞር መመዘኛውን ያልፍ እንደሆን እናያለን፡፡
የንባብ ልዩነቶች መነሻ ምክንያትና ተፅዕኖ
በጥንት ዘመን የጽሕፈትና የኮፒ ማሽኖች ስላልነበሩ መጻሕፍት ይገለበጡ የነበሩት በጽሑፍ ባለሙያዎች ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በሚገለብጡበት ወቅት ፊደላትን መግደፍ፣ ቃላትን መዝለል፣ ቦታ ማቀያየርና የመሳሰሉትን ስህተቶች ይፈጽማሉ፡፡ የኃይማኖት መጻሕፍትን ጨምሮ የትኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ ከንደነዚህ ዓይነት ችግሮች የፀዳ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ስልጣን ከርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከተጻፉት ጥንታዊ መዛግብ ሁሉ የላቀ በመሆኑ የግልበጣ ስህተቶች ተዓማኒነቱን አጠራጣሪ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በአንዱ ብራና ውስጥ የተዘለለ ወይንም ደግሞ የተገደፈ ክፍል ቢኖር በሌሎች ብራናዎች ውስጥ ተስተካክሎ ይገኛል ወይንም ደግሞ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመነሳት ትክክለኛውን አጻጻፍ ማወቅ ይቻላል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ ከተባሉት የግልበጣ ስህተቶች መካከል አብዛኞቹ እዚህ ግቡ የሚባሉ ካለመሆናቸው የተነሳ ሊተረጎሙ እንኳ የማይችሉ ናቸው፡፡ የከፉ የሚባሉቱ ደግሞ የስምና የቁጥር ስህተቶችን እንዲሁም የቃላትና የአረፍተ ነገሮች መዘለልን የመሳሰሉ ዋናውን መልዕክት ሊነኩ የማይችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል አቶ ሐሰን በቀዳሚነት የጠቀሷቸውን ሁለት ነጥቦች እንመልከት፡፡
የሐዋርያት ሥራ 15፡34 ላይ “ሲላስ ግን በዚያ ይኖር ዘንድ ፈቀደ” የሚለው በአንዳንድ የጥንት ቅጂዎች ውስጥ እንደማይገኝ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም እዚያው የሐዋርያት ሥራ 28፡29 ላይ “ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ” የሚለውም በአንዳንድ የጥንት ቅጆች ውስጥ እንደማይገኝ ተገልጿል፡፡ የጥቅሶቹን ሐሳቦች ከምንባቦቹ አውዶች ማግኘት ስለሚቻል መካተት አለመካተታቸው የምንባቡን ትርጉም አይለውጥም፤ የትኛውንም የክርስትና አስተምህሮ የሚጠቅስ ሐሳብም አላዘሉም፡፡ እነዚህን የሚመስሉት ምንባቦች የተለያዩ የእጅ ጽሑፎችን ጎን ለጎን በማስተያየት ትክክለኛዎቹ ምንባቦቻቸው ሊታወቁ የሚችሉ በመሆናቸው እንደነዚህ ባሉ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት የትኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ ተዓማኒነት እንደሚጎለው አይታሰብም፡፡ በዘርፉ እውቀት ያላቸው ምሑራን እነዚህን ችግሮች እንደ አሳሳቢ ችግሮች አይቆጥሯቸውም ነገር ግን ስለጉዳዩ እውቀት የሌላቸው ወገኖች ግራ ሊጋቡ ይችላሉ፡፡
በሊቃውንት እጅ የሚገኙት አብዛኞቹ ብራናዎች በስደት ዘመን የተገለበጡ በመሆናቸው ጸሐፍቱ ሌሊት መብራቶችን በመጠቀም ወይም ዋሻዎች ውስጥ በመደበቅ ነበር ሲገለብጡ የነበሩት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ጸሐፍት በአንድ ክፍል ውስጥ ይሰበሰቡና አንድ አንባቢ ከፊት ሆኖ እያነበበላቸው ይገለብጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ስህተቶች የመፈጠራቸው ሁኔታ ይሰፋል፡፡ ነገር ግን ሊቃውንት በዚህ ሁኔታ ችግር እንዳለበት ያረጋገጡት የአዲስ ኪዳን ክፍል ከሁለት በመቶ ያነሰ ነው፡፡ 98.33 ከመቶ የሚሆነው የአዲስ ኪዳን ክፍል ከመሰል ችግሮች የፀዳ ነው፡፡ ከእነዚህ በጣት ከሚቆጠሩት ችግሮች መካከል ዋናውን የእምነት መሠረት የሚነካ አንድም እንኳ የሌለ ሲሆን ወሳኝ የሆኑ ልዩነቶችን በመጽሐፍ ቅዱስ የግርጌ ማስታወሻዎች በማስቀመጥ አንባቢያን እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡
የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት በነዚህ ምንባቦች ውስጥ የተጠበቀ በመሆኑ በእውነቱ ከሆነ መሰል ችግሮች ሊያሳስቡን የሚገቡ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ የማድረግ ኃይል ቢኖረውም ነገር ግን ቅዱስ ቃሉ በተፈጥሯዊ መንገድ ተጠብቆ እንዲኖር መርጧል፡፡
ብሩስ መዝገር የተሰኙ ዕውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ የንባብ ሕየሳ (Textual Criticism) ሊቅ አዲስ ኪዳን 99.5 ከመቶ የተጠበቀ መሆኑን በማረጋገጥ ጽፈዋል፡፡[31] ቁርአንን ጨምሮ በዚህ የጥራት መጠን እንደተጠበቀ የተረጋገጠ ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ መጽሐፍ በሰው ልጆች ታሪክ አይታወቅም!
ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ተጠብቆ መቆየቱን እንጂ እያንዳንዱ በእጅ የተገለበጠ ብራና የፊደል ግድፈትና ጣልቃ ገብ ጽሑፎችን የመሳሰሉ እንከኖች በሌሉበት ሁኔታ ተጠብቆ መቆየቱን ተናግረው አያውቁም፡፡ በያንዳንዱ ብራና ላይ እንዲህ ያሉ እንከኖች ለምን እንደተገኙ የሚጠይቅ ሙስሊም ካለ የቁርአንን 10 ገፆች ያህል በእጁ በመገልበጥ ከስህተት በጸዳ ሁኔታ ገልብጦ እንደሆን ጓደኛውን አስነብቦ እንዲያረጋግጥ እናበረታታዋለን፡፡ እንኳንስ የማተሚያ ማሽን ባልነበረበት ዘመን ይቅርና በዚህ በኛ ዘመን እንኳ አንድን መጽሐፍ እንከን በሌለው ሁኔታ ማሳተም ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡
ዋና ዋና የንባብ ልዩነቶች
በምንዝር የተያዘች ሴት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የንባብ ልዩነቶች መካከል በተደጋጋሚ የሚነሳው በአመንዝራነት ተይዛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር ስላላት ሴት የተጻፈው ነው (ዮሐ. 7፡53-8፡11)፡፡ በነገረ መለኮት ምሑራን ዘንድ “The Pericope de Adultera” የሚል ቴክኒካዊ መጠርያ ያለው ይህ ታሪክ በብዙ ጥንታውያን የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ እንደማይገኝ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ይታያል፡፡ ይህ ማለት ግን የታሪኩን ትክክለኛነት የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ማለት አይደለም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ላቲን ቋንቋ የተረጎመው ቅዱስ ጀሮም (415 ዓ.ም.) ይህ ታሪክ በእርሱ ዘመን በነበሩት ብዙ የግሪክና የላቲን የዮሐንስ ወንጌል የእጅ ጽሑፎች ውስጥ እንደሚገኝ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ምሑራን “D” በማለት በሰየሙት በአምስተኛው ክ.ዘ. በተገለበጠ የግሪክ የእጅ ጽሑፍ ውስጥም ይገኛል፡፡[32] ድድስቅሊያና ሥርዓተ ሐዋርያትን በመሳሰሉት (3ኛውና 4ኛው ክ.ዘ.) ጥንታዊያን የአበው ጽሑፎች ውስጥ መገኘቱም ለጥንታዊነቱ ሌላው ማስረጃ ነው፡፡[33]
ይህ ታሪክ ብዙ ጥንታዊያን የቤተ ክርስቲያን አበው ምንዝርናን በሚፈፅሙት ወገኖች ላይ ይወስዱ ከነበሩት ጥብቅ እርምጃ በተጻራሪ ይቅርታና ምህረትን የሚያበረታታ በመሆኑ “ምንዝርናን ያበረታታል” በሚል የተሳሳተ ዕይታ ምክንያት በጸሐፍት ዘንድ በጥርጣሬ መታየቱን ጉዳዩን ያጠኑት ምሑራን ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ አውጉስጢኖስ (400 ዓ.ም.) ዋና ዋና በሚባሉት የአዲስ ኪዳን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ያለመገኘቱን ሚስጥር ሲያብራራ የሰጠው ምክንያት ተመሳሳይ ሲሆን ለታሪኩ ትክክለኛነት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡[34] የሚላን ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አምብሮስ (374 ዓ.ም.) የታሪኩን ሐቀኝነት የሚጠራጠሩት ወገኖች ትክክል አለመሆናቸውን ተናግሯል፡፡[35]
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው የሃይማኖት መሪዎች “ኃጢአተኞችና አመንዝሮች ናቸው” በማለት ካገለሏቸው ወገኖች ጋር ነበር (ማቴ. 9፡9-13፣ ማር. 2፡15፣ ሉቃ. 5፡32፣ 7፡36-50፣ 15፡2፣ 19፡7)፡፡ ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ በመሆኑ ምክንያት ማንም በማንም ላይ የመፍረድ ብቃት እንደሌለው ተናግሯል (ማቴ. 7፡1-5፣ ሉቃ. 6፡37-42)፡፡ በኃጢአተኞች ላይ ለመፍረድ ሳይሆን ኃጢአተኞችን ለማዳን መምጣቱንም አውጇል (ሉቃ. 19፡10)፡፡ ስለዚህ ይህ ታሪክ በአዲስ ኪዳን ላይ የሚጨምረው ወይም የሚቀንሰው የተለየ ትምህርት ስለሌለ የመጽሐፍ ቅዱስ አካል ተደርጎ መወሰድ አለመወሰዱ የእስልምናን የብረዛ ክስ አያረጋግጥም፡፡
የማርቆስ መዝጊያ
ሌላው አቶ ሐሰን የጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ማርቆስ 16፡9-20 ላይ የሚገኘው ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ማርቆስ 16፡9-20 ድረስ የሚገኘውን ክፍል ተዓማኒነት በተመለከተ ወጥ አቋም የላቸውም፡፡ ገሚሶቹ በአብዛኞቹ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ስለተካተተ ተዓማኒ እንደሆነ ሲናገሩ የተቀሩት ደግሞ ይህንን ክፍል ላለመቀበል ተከታዮቹን ምክንያቶች ያቀርባሉ፡-
- እነዚህ ቁጥሮች ቀዳሚና ይበልጥ ተዓማኒ በሆኑት የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡ በተጨማሪም በቀደመው ላቲን፣ ሢርያክ፣ አርመንያ እና ኢትዮጵያ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አይገኙም፡፡
- ቀለሜንጦስ፣ ኦሪጎን እና ኢዮስቢዮስን የመሳሰሉት ብዙ የጥንት አባቶች እነዚህን ቁጥሮች አያውቋቸውም፡፡ ቅዱስ ጀሮም ከሞላ ጎደል በእርሱ ዘመን በነበሩት በሁሉም የግሪክ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡
- ይህንን ክፍል የሚያጠቃልሉት ብዙ የእጅ ጽሑፎች አጠራጣሪ መሆኑን ለማሳየት ምልክት ያደርጉበታል፡፡
- በአንዳንድ የእጅ ጽሑፎች ውስጥ ሌላ አጠር ያለ የማርቆስ ወንጌል መዝጊያ ይገኛል፡፡
- አንዳንዶች ደግሞ አጻጻፉና የሰዋሰው ይዘቱ ከተቀረው የማርቆስ ወንጌል ጋር እንደማይመሳሰል ይናገራሉ፡፡
ይህ ክፍል በኦሪጅናል የማርቆስ ወንጌል ውስጥ መገኘት አለመገኘቱ አጠያያቂ እንደሆነ ቢቀጥልም ነገር ግን የያዘው እውነት ከተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚስማማ ነው፡፡ ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢወጣ ምንም የሚጎድል ትምህርት የለም፡፡ ያዘለው ትምህርት በሌሎች ክፍሎች እንደመገኘቱ መጠን ደግሞ ባለበት ቦታ ቢቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የሚጨምረው ነገር የለም፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱት በልሳን የመናገር ስጦታ፣ የጥምቀት ሥርዓትና በእባብ መርዝ ያለመጎዳት ተዓምር በሌሎች ክፍሎች ላይ ተጠቅሰዋል (ሐዋ. 2፡1-21፣ 10፡44-48፣ 19፡1-7፣ 28፡3-5)፡፡[36]
በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙት ሰፋፊ ምንባቦች መካከል በዚህ ሁኔታ በምሑራን ዘንድ ክርክር ያስነሱት ክፍሎች ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ብቻ ሲሆኑ መሠረታዊውን የአዲስ ኪዳን መልእክት የሚለውጡና የእስልምናን የብረዛ ክስ የሚያረጋግጡ አይደሉም፡፡ እነዚህ ክፍሎች የዲስ ኪዳን ክፍል ተደርገው መቆጠር አለመቆጠራቸው በአዲስ ኪዳን ትምህርት ላይ የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ምንም ነገር የለም፡፡
የቁርአን የንባብልዩነቶች
ክርስቲያን ምሑራን የአዲስ ኪዳንን የእጅ ጽሑፎች ታሪክ በተመለከተ ያሳዩትን ግልጸኝነትና ሐቀኝነት ሙስሊም ጸሐፊያን በመጠምዘዝ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ማየት በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ከሙስሊም ምሑራን በተጻራሪ ክርስቲያን ምሑራን ከሕዝባቸው የሚሰውሩት ምንም ነገር የለም፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን የንባብ ልዩነቶች ያለምንም መሸፋፈን ያሳውቃሉ፡፡ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎችንም ሙዚየሞች ውስጥ ከማስቀመጥ ባለፈ ገፅ በገፅ ፎቶግራፍ አንስተው በመጽሐፍና በበይነ መረብ በማሳተም ለመላው ዓለም ያሳያሉ፡፡ በእያንዳንዱ የእጅ ጽሑፍ ውስጥ የሚገኘውን የፊደል ግድፈትና ጭረት ሳይቀር ጥልቅ የሆኑ ማነጻጸርያዎችን (Critical Editions) በማዘጋጀት በየጊዜው ያሳትማሉ፡፡
በእስልምና ግን እንዲህ ያለ ነገር አይታወቅም፡፡ ክርስቲያን ምሑራን መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ በሚያዘጋጁት ሁኔታ የቁርአንን የንባብ ታሪክ የሚያሳይና የብራና ጽሑፎቹን የሚገመግም ምንም ዓይነት ጥልቅ ማነጻጸርያ (Critical Edition) አይገኝም፡፡ ነገር ግን ቁርአን ሙስሊሞች ከሚሉት በተጻራሪ በትክክል ያልተጠበቀና ብዙ መለዋወጦችን ያስተናገደ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡
ሙስሊም ምሑራን በቁርአን ጥንታዊያን የእጅ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን ግድፈቶች ዕውቅና ሰጥተው ለሕዝባቸው ይፋ በማድረግ ሃይማኖታቸውን በእውነት ላይ ከመመስረት ይልቅ ቁርአን በእጅ ሲገለበጥ በኖረባቸው ክፍለዘመናት የተጻፉት የብራና ጽሑፎች ሁሉ ፍጹም እንከን የለሽ በሆነ ሁኔታ የተገለበጡ በማስመሰል ይናገራሉ፡፡ “ከነቢዩ ዘመን ጀምሮ አንዲት ጭረት አልተጨመረበትም ከላዩ ላይም አልተቀነሰም” በማለት ይወሸክታሉ፡፡ አከራካሪ የሆኑ የቁርአን የንባብ ልዩነቶች የሌሉ በማስመሰልም ሕዝባቸውን ያታልላሉ፡፡ እውነቱ ግን እንደርሱ አይደለም፡፡ በማስከተል በቁርአን ውስጥ የንባብ ልዩነቶችና የግልበጣ ስህተቶች መኖራቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን እናቀርባለን፡፡ ሙስሊም ወገኖቻችንም ከስሜታዊነት በጸዳ ሁኔታ ማስረጃዎቹን እንዲያጤኑ እንጠይቃቸዋለን፡፡
- በትውፊት የተዘገቡ የንባብ ልዩነቶች
ቀዳሚያን ሙስሊሞች በቁርአን ውስጥ የነበሩ ለቁጥር የሚያታክቱ የንባብ ልዩነቶችን ዘግበው አልፈዋል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
- የማሊክ ሙዋጣዕ በተሰኘ የሐዲስ ስብስብ ውስጥ ተከታዩ ተዘግቧል፡-
ያህያ ከማሊክ፣ ከዘይድ ኢብን አስለም፣ ከአል-ቃቃ ኢብን ሐኪም የተላለፈውን እንደነገረኝ የአማኞች እናት የሆነችው የአይሻ ጸሐፊ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “አይሻ ቁርአንን እንድጽፍላት አዘዘችኝ፡፡ ‹‹በሶላቶች (በተለይ) በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ›› የሚለው አንቀጽ ጋር ስትደርስ አሳውቀኝ፡፡ እኔም አንቀጹ ጋር ስደርስ አሳወኳት፡፡ ከዚያም እንዲህ ብዬ እንድጽፍ ነገረችኝ ‹‹በሶላቶች በመካከለኛይቱ ሶላት እንዲሁም በአስር ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡›› አይሻ ይህንን ከአላህ መልእክተኛ መስማቷን ተናግራለች፡፡”[37]
ይህ አንቀጽ በዛሬው ቁርአን ውስጥ ሱራ 2፡238 ላይ የሚገኝ ሲሆን እንዲህ ይነበባል፡- “በሶላቶች (በተለይ) በመካከለኛይቱም ሶላት ላይ ተጠባበቁ፡፡ ታዛዦች ኾናችሁም ለአላህ ቁሙ፡፡” በአይሻ ቁርአን ውስጥ የነበረው “እንዲሁም በአስር ሶላት” የሚለው ሐረግ ተቀንሷል ማለት ነው፡፡ የዘመናችን ሙስሊም ምሑራን ሐቀኞች ቢሆኑ ኖሮ በቁርአን የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ “የአይሻ ቅጂ ‹‹እንዲሁም በአስር ሶላት›› የሚል ሐረግ ይጨምራል” የሚል መረጃ ለአንባቢያን መስጠት ነበረባቸው፡፡
- ሳሂህ ሙስሊም ውስጥ ተከታዩ ተዘግቧል፡- “አቡ ሀርብ ቢን አቡ አል-አስዋድ አባታቸውን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት አቡ ሙሳ አል-ሸዐሪ የበስራ ቁርአን አነብናቢዎችን አስጠሯቸው፡፡ ቁጥራቸው ወደ ሦስት መቶ የሚሆኑቱ መጡ፡፡ ቁርአንን አነበነቡት፤ እርሳቸውም እንዲህ አሏቸው ‹‹እናንተ አነብናቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን ከበስራ ነዋሪዎች ሁሉ ምርጦች ናችሁ፡፡ ማነብነባችሁን ቀጥሉ፡፡ (ነገር ግን) ለረጅም ጊዜ ማነብነባችሁ ከናንተ በፊት የነበሩትን ሰዎች ልቦች እንዳደነደነ ልቦቻችሁን እንዳያደነድን ተጠንቀቁ፡፡ በርዝመትና በጥንካሬ ከሱራ በረዓት ጋር የሚነፃፀር ሱራ እናነበንብ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹የአደም ልጅ በኃብት የተሞሉ ሁለት ሸለቆዎች ቢኖሩት ሦስተኛውን ይመኛል፡፡ ከአፈር ውጪ የአደምን ልጅ ሆድ የሚሞላ ምንም ነገር የለም፡፡›› ከሱረት ሙሰቢሃት መካከል ከአንዱ ጋር የሚመሳሰል ሌላ ሱራም እናነበንብ ነበር ነገር ግን ከተከታዩ ውጪ የተቀረውን ረስቼዋለሁ፡- ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ የማትፈፅሙትን ነገር ስለምን ትናገራላችሁ? እርሱም በናንተ ላይ ምስክር እንዲሆንባችሁ በአንገቶቻችሁ ላይ ተጽፏል፤ በዕለተ ትንሣኤም ከእርሱ ትጠየቃላችሁ፡፡››” [38]
በኛ ዘመን የሚገኙት ሙስሊም ሊቃውንት በያንዳንዱ የቁርአን መቅድም ላይ በዘመናችን የሚገኘው ቁርአን ያልተሟላ መሆኑንና ረጃጅም ምዕራፎች ከውስጡ መጉደላቸውን ማሳወቅ ነበረባቸው፡፡
- ሳሂህ አል-ቡኻሪ ውስጥ እንደተዘገበው አብደላህ ኢብን መስዑድ የተሰኘው የመሐመድ ወዳጅ ሱራ 92፡3 ላይ የሚገኘውን “ወንድንና ሴትን በፈጠረውም (አምላክ እምላለሁ)” የሚለውን አንቀጽ ሲያነብ “በወንድና በሴት እምላለሁ” በማለት ነበር፡፡ አቡ ደርዳ የተሰኘ ሌላ የመሐመድ ወዳጅ ይህንኑ ንባብ ከነቢዩ መስማቱን በመሐላ በማረጋገጥ የኡሥማንን ንባብ እንደማይቀበል ተናግሯል፡፡[39]
የዘመናችን ሙስሊም ምሑራን ሐቀኞች ቢሆኑ ኖሮ በቁርአን የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ የአብደላህ ኢብን መስዑድ ቅጂ “ወንድንና ሴትን በፈጠረውም (አምላክ እምላለሁ)” በሚለው ቦታ “በወንድና በሴት እምላለሁ” እንደሚል ማሳወቅ ነበረባቸው፡፡
በሕትመት ላይ የሚገኙት የንባብ ልዩነቶች
ሙስሊም ወገኖች በዚህ ዘመን በዓለም ላይ አንድ ዓይነት የአረብኛ ቁርአን ብቻ እንደሚገኝና ምንም ዓይነት ልዩነት እንደማያሳይ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ፍጹም የተሳሳተና ከተጨባጩ እውነታ ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ በዚህ ዘመን በዓለም ላይ እጅግ ብዙ የንባብ ልዩነቶች ያሏቸው ቁርአኖች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ ቁርአን በምን ሁኔታ እየተላለፈ ለዚህ ዘመን እንደበቃ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡
በመሐመድና በተከታዮቻቸው ዘመን የነበረው የአረብኛ ቋንቋ ተነባቢ ፊደላት እንጂ አናባቢ ስላልነበረው በጽሑፍ የሰፈረው ቁርአን በብዙ መንገዶች መነበብ የሚችልና ቋሚ ንባብ ያልነበረው ግራ አጋቢ ጽሑፍ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሙስሊሙ ማሕበረሰብ ግራ ስለተጋባ በተነባቢ ፊደላት ላይ ተቀፅለው ትክክለኛ ድምፃቸውን የሚያመለክቱ እንዲሁም እርስ በርሳቸው የሚመሳሰሉ ተነባቢ ፊደላትን ለይተው የሚያሳዩ ቋሚና ወጥ መልክ ያላቸው ምልክቶች (Diacritical Marks) እንዲፈጠሩ ተደረገ፡፡ ሙስሊም ገዢዎች ከላይ በተጠቀሰው ችግር ምክንያት የተፈጠሩትን የንባብ ልዩነቶች ለማፈን ቢሞክሩም እነዚህን ንባቦች ለማጥፋት አልቻሉም ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ በአራተኛው የእስልምና ክፍለ ዘመን ቀደም ሲል ተፈጥረው የነበሩትን ሰባት ቁርአኖች ኦፊሴላዊ ለማድረግና ልዩነቶቹን ለማቻቻል ጥረት ተደረገ፡፡ ሰባቱ የንባብ መንገዶች (ቂርአት) ከሰባት ታዋቂ አነብናቢዎች (ቁረ) የተላለፉ ሲሆኑ ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ ሁለት ሁለት አስተላላፊዎች (ሩዋህ) ተመረጡ፡፡ ከእነዚህ አስተላላፊዎች የተገኙት ቁርአኖች ደግሞ መጠነኛ ልዩነቶችን በሚያሳዩ ሁለት ሁለት ቅጂዎች (ሪዋያተን) እየተላለፉ ለዚህ ዘመን በቅተዋል፡፡[40] “ከሰባቱ” በተጨማሪ “ሦስቱ” በመባል የሚታወቁ ሌሎች ቁርአኖች ስለተገኙ የቂርአት ቁጥር ወደ አሥር ከፍ ብሏል፡፡
በመላው ዓለም በብዛት ተሰራጭቶ የሚገኘው ቁርአን የንጉሥ ፈሐድ ዕትም በመባል የሚታወቀው የሐፍስ ንባብ ሲሆን ተፎካካሪ ተደርጎ የሚወሰደው የዋርሽ ንባብ ደግሞ አልጄርያ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ፣ ሱዳንና ምዕራብ አፍሪካን በመሳሰሉት አካባቢዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ በሁለቱ መካከል ከሚገኙት ልዩነቶች መካከል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እናያለን፡፡
رواية ورش عن نافع – دار المعرفة –دمشق የዋርሽ ንባብ – ደር አል ማሪፋህ ደማስቆ | رواية حفص عن عاصم – مجمع الملك فهد- المدينة የሐፍስ ንባብ – የንጉሥ ፈሐድ ጥራዝ መዲና | አንቀፅ |
يُغْفَرْ ይምራልና | نَّغْفِرْ እንምራለንና | 2:58 |
لَوْ تَرَى الذِينَ ظَلَمُواْ እነዚያን የበደሉትን ሰዎች ባያችሁ ጊዜ | لَوْ يَرَى الَّذِينَ ظَلَمُواْ እነዚያም የበደሉት ሰዎች … ባዩ ጊዜ | 2:165 |
ድኾችን ማብላት አለባቸው | ድኻን ማብላት አለባቸው | 2፡183 |
فَنُوَفِّيهِمُ ምንዳዎቻቸውን እንሞላላቸዋለን | فَيُوَفِّيهِمْ ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል | 3:57 |
تَبْغُونَ ትፈልጋላችሁን | يَبْغُونَ ይፈልጋሉን | 3:83 |
تُرْجَعُونَ የምትመለሱ ስትኾኑ | يُرْجَعُونَ የሚመለሱ ሲኾኑ | 3:83 |
نُدْخِلْهُ እናገባዋለን | يُدْخِلْهُ ያገባዋል | 4:14 |
نُفَصِّلُ እናብራራለን | يُفَصِّلُ ያብራራል | 10:5 |
يُوحى የሚያወርድላቸው | نُّوحِى የምናወርድላቸው | 12:109 |
تُوقِدُونَ የምታነዱበትም | يُوقِدُونَ የሚያነዱበትም | 13:17 |
مَا تَنَزِّلُ አታወርድም | مَا نُنَزِّلُ አናወርድም | 15:8 |
تّقُولُونَ እንደሚሉት | يَقُولُونَ እንደምትሉት | 17:42 |
قُل በል | قَالَ አለ | 21:4 |
ከላይ የተጠቀሱት ልዩነቶች በሁለቱ ቁርአኖች መካከል ከሚገኙ 1354 ከሚሆኑት ልዩነቶች መካከል ለናሙናነት የተወሰዱ ናቸው፡፡[41] እነዚህ ልዩነቶች የምንባቡን አጠቃላይ ትርጉም የሚለውጡ ባይሆኑም በዓለም ላይ የሚገኙት ቁርአኖች ፍፁም አንድ እንደሆኑ ሲነገር የምንሰማውን እስላማዊ ተአብዮ ከንቱ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ልዩነቶች በንባብ ወቅት የሚፈጠሩ ልዩነቶች ሳይሆኑ በጽሑፍ የሰፈሩ ንባቦች በመሆናቸው ልዩነቶቹ በአነባብ ስልት ወይም በአረብኛ ዘዬ ምክንያት ብቻ የተፈጠሩ ናቸው የሚለው የሙስሊም አቃቤ እምነታውያን ማስተባበያ የሚያስኬድ አይደለም፡፡
የሙስሊም ምሑራን ኑዛዜ
በቁርአን ውስጥ የሚገኙትን የንባብ ልዩነቶችና ስህተቶች ዕውቅና ሰጥቶ ለሕዝብ የማሳወቅ ድፍረትና ዝግጅት በሙስሊም ምሑራን ዘንድ ባይታይም ዝምታውን በመስበር ይህንን ለማድረግ የሞከሩ ጥቂቶች አልጠፉም፡፡ ለምሳሌ ያህል አብዱላህ ዩሱፍ አሊ የተሰኘው ዕውቅ የቁርአን ተርጓሚ ሱራ 33፡6 የንባብ ልዩነት እንደሚያሳይ ጠቅሷል፡፡ የኡሥማን ቅጂ እንደሆነ የሚታመነው በኛ ዘመን የሚገኘው ቁርአን እንዲህ ይነበባል፡-
“ነቢዩ በምእምናን ከነፍሶቻቸው ይበልጥ ተገቢ ነው፡፡ ሚስቶቹም እናቶቻቸው ናቸው፡፡”
ዩሱፍ አሊ የኡበይ ቢን ካዕብ ቅጂ “እንዲሁም እርሱ አባታቸው ነው” የሚል ሐረግ እንደሚጨምር በግርጌ ማስታወሻው ላይ ገልጿል፡፡[42]
የአብዱላህ ዩሱፍ አሊ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
ረሺድ ኸሊፋ የተሰኘ ሌላ የቁርአን ተርጓሚ ሱራ 9፡128-129 ላይ የሚገኙት ሁለት አንቀፆች ነቢዩ መሐመድ ከሞቱ ከዓመታት በኋላ በኡሥማን ዘመን በቁርአን ላይ የተጨመሩ መሆናቸውን በመግለፅ ከራሱ ቅጂ ውስጥ አስወግዷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአክራሪ ሙስሊሞች ተገድሏል፡፡[43]
ቁርአን ሲለዋወጥ የኖረ መጽሐፍ መሆኑን በተናገሩ ሙስሊም ባልሆኑ ምሑራን ላይም ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ያህል ገርድ ሩዲጀር ፑዊን የተሰኘ ጀርመናዊ የአረብኛ ቋንቋ ሊቅ “የሰነዓ የእጅ ጽሑፎች” ተብለው በሚታወቁት የቁርአን ጽሑፎች ላይ ጥናትና ምርምር እንዲያደርግ በየመን መንግሥት ጥሪ ተደርጎለት ነበር፡፡ ነገር ግን ቁርአን የተለዋወጠ መጽሐፍ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማግኘት ሲጀምር የየመን መንግሥት ሥራውን አስቁሞታል፡፡ ጽሑፎቹንም ድጋሜ እንዳያገኛቸው እገዳ ጥሎበታል፡፡ ዶ/ር ፑዊን ጽሑፎቹን ቀደም ሲል በፎቶ ፊልም ወስዷቸው ስለነበር ወደ አገሩ በመመለስ ጥናቱን ቀጥሏል፡፡ የጥናቱን ውጤት በመጽሐፍ አንደሚያሳትም ማሳወቁ በሙስሊሞች ዘንድ ቁጣና ተቃውሞን ሊያስነሳ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡[44]
ሙስሊም ወገኖቻችን ሆይ፤ በሃይማኖት መሪዎቻችሁ የተነገራችሁን ነባር አስተምህሮ የሚገዳደሩ ድምፆችን በዚህ ሁኔታ ለማፈን የምትሞክሩ ከሆነ ቁርአን መሰል ተግዳሮቶችን መቋቋም እንደሚችል ከልባችሁ አታምኑም ማለት ነው፡፡ ካልተጠናና ካልተመረመረ ታድያ ያለምንም እንከን ተጠብቆ ለዚህ ዘመን እንደበቃ ስትናገሩ ምን ማስረጃ ይዛችሁ ነው? ጥንታውያን ቁርአኖች እንደሆኑ የሚነገርላቸው በቱርክ ቶፖካፒ ቤተ መዘክርና በኡዝቤኪስታን ታሽኪን ቤተ መዘክር የሚገኙት ቁርአኖች ታትመው ለሕዝብ ይፋ አልሆኑም፡፡ እነዚህ ቁርአኖች ልክ እንደ ኮዴክስ ሲናይቲከስና ኮዴክስ ቫቲካነስ ታትመው ለሕዝብ ይፋ የማይሆኑት ለምንድነው? ሙስሊም መሪዎች ከሕዝባቸው ሰውረው በሚስጥር መያዝ የፈለጉት በመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኝ ችግር ምን ይሆን?
የመጀመርያዎቹ የእጅ ጽሑፎች አለመኖራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ተዓማኒነት ይቀንሳልን?
አቶ ሐሰን “የማመሳከርያው መጥፋት” በሚል ርዕስ ስር እንዲህ ይላሉ፡-
አሁን በምድር ላይ ያሉ ወንጌሎችን ከኦሪጅናል ጸሐፊዎች ስራ ለማመሳከር እንዳይሞከር በባለቤቶቹ የእጅ ጽሑፍ የተጻፉ መጽሐፍት ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፡፡ ሁሉም የወንጌል መጽሐፍት ከግሪክ የተቀዱ ናቸው፡፡ አሳሳቢው ነገር ግን ይህም የግሪክ እናት መጽሐፍ መጥፋቱ እና የክርስቲያኑ ዓለም ያለ ማጣቀሻ መቅረቱ ነው፡፡ (ገፅ 42)
ይህንን አባባል ይደግፍልኛል ያሉትን ሐሳብ እንደተለመደው ከኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ላይ ጠቅሰዋል (ገፅ 42-43)፡፡ ነገር ግን በጽሑፋቸው ውስጥ ሁለት ሐሰተኛ ምልከታዎች ይገኛሉ፡፡ የመጀመርያው ወንጌላት በቀዳሚነት በግሪክ ቋንቋ ሳይሆን በሌላ ቋንቋ የተጻፉ በማስመሰል መናገራቸው ነው፡፡ ይህ አባባላቸው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ዕውቀት እንደሌላቸው አመላካች ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት መጀመርያ የተጻፉት በግሪክ ቋንቋ እንደሆነ ለማወቅ ምሑራንን መጥቀስ አያሻም፡፡ አቶ ሐሰን እኔ ወደማገለግልባት ቤተ ክርስቲያን እሑድ ጠዋት በመምጣት የሰንበት ትምህርት የሚማሩትን ህፃናት ቢጠይቁ በጥሩ ሁኔታ ሊያስረዷቸው ይችላሉ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በኩረ ጽሑፉ ከሌለ አንድ መጽሐፍ ተዓማኒነት እንደሚጎድለው በማስመሰል መናገራቸው ነው፡፡ እውነት ነው የአዲስ ኪዳን በኩረ ጽሑፎች ዛሬ በእጃችን አይገኙም፡፡ የተጻፉባቸው ቁሶች እስከ እኛ ዘመን መቆየት ለመቻል እንደ ቁምራን ባለ ከባቢያዊ ሁኔታው ለዚህ ምቹ በሆነ ስፍራ መቀመጥ ነበረባቸው፡፡ እንደርሱ ባለመሆኑ በዘመን ርዝማኔ የተፈጥሮ ሂደት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ምክንያት የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት ተዓማኒነት የሚጠራጠር ምሑር የለም፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ዕድሜ ያለው የመጀመርያው ጽሑፍ የተጻፈበት ቁስ ተጠብቆ ለዚህ ዘመን የበቃ አንድም ጥንታዊ መጽሐፍ መጥቀስ አይቻልም፡፡ ቁርአን እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጠናቀቀ ከስድስት ክፍለ ዘመናት በኋላ የተጻፈ ቢሆንም የመጀመርያዎቹ ጽሑፎቹ ጠፍተዋል፡፡ ጽሑፎቹ በተፈጥሯዊ ምክንያቶች ጠፍተው ቢሆን ኖሮ አሳሳቢ ባልሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን በኡሥማን ትዕዛዝ እንዲቃጠሉ በመደረጋቸው ምክንያት የሆነ ዓይነት ሸፍጥ አለመኖሩን ሙስሊሞች እርግጠኛ መሆን አይችሉም፡፡
ምሑራን የአንድን ጥንታዊ መጽሐፍ ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ነፃ በሆነ መንገድ የተገለበጡትን ኮፒዎች ብዛት፣ ጥራትና በመካከላቸው የሚገኘውን ስምምነት ይገመግማሉ እንጂ የመጀመርያው ጽሑፍ የግድ መገኘት አለበት አይሉም፡፡ እንደርሱ ዓይነት መመዘኛ ቢጠቀሙ ኖሮ ከጥንት መጻሕፍት መካከል አንዱም ተዓማኒ ባልሆነ ነበር፡፡
በኮፒዎች ብዛት አዲስ ኪዳን ከእርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከተጻፉት ጥንታውያን ጽሑፎች ጋር ሊነፃፀር በማይችልበት ሁኔታ በእጅጉ የላቀ በመሆኑ ለተዓማኒነቱ አስተማማኝ ዋስትና ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ዕውቅ ክርስቲያን አቃቤ ዕምነት የሆኑት ፕሮፌሰር ጆሽ ማክዱዌል እንዲህ ይላሉ፡-
ከ5,686 በላይ የሚሆኑ የታወቁ የአዲስ ኪዳን የግሪክ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች አሉ፡፡ በተጨማሪም 10,000 የላቲን ቩልጌቶችና ሌሎች 9,300 ቀዳሚያን ቅጂዎች፣ በአጠቃላይ ከዚያ ካልበለጡ ወደ 25,000 የሚሆኑ ጥንታውያን የእጅ ጽሑፎች አሉ፡፡ ከጥንት መዛግብት መካከል አንዱም እንኳ ይህንን ያህል ቁጥርና የማረጋገጫ ብዛት ወደ ማስመዝገብ የቀረበ የለም፡፡ በንፅፅር 643 የእጅ ጽሑፎች ብቻ ያሉት የሆሜር ኢሊያድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡[45]
ከነዚህ እውነታዎች በመነሳት ለአቶ ሐሰን ተከታዮቹን ጥያቄዎች እናቀርባለን፤ በማስረጃ የተደገፈ ምላሽም እንዲሰጡን እንጠይቃቸዋለን፡-
- የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ዕድሜ ያለው በኩረ ጽሑፉ (autograph) ተጠብቆ ያለ አንድ መጽሐፍ ይጥቀሱልን፡፡
- በእጅ ጽሑፎች ሥልጣን ከመጽሐፍ ቅዱስ የላቀ ጥንታዊ ጽሑፍ የሚያውቁ ከሆነ ይጥቀሱልን፡፡
- የመጀመርያው ጽሑፍ መኖሩ ተመራጭ መሆኑን ከማመን በዘለለ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ተዓማኒ ለመሆን የመጀመርያው ጽሑፍ መኖሩን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያነሳ አንድ የታሪክ ምሑር ይጥቀሱልን፡፡
- በመሐመድ ዘመን ከተጻፉት ቀዳሚያን የቁርአን ጽሑፎች መካከል እስከ እኛ ዘመን የኖረ አንድ ቁራጭ እንኳ ካለ ያሳዩን፡፡
- በመሐመድ ዘመን የተጻፉትን ማሳየት ካልቻሉ ጥያቄውን ቀለል እናድርግሎት፡፡ በአቡበከር ዘመን ተሰብስቦ በሐፍሷ ቤት ተቀምጦ የነበረው ሙሳሒፍ ካለ ያሳዩን፡፡
- እርሱንም ማድረግ ካልቻሉ አሁንም እናቅልልሎት፡፡ ከኡሥማን አምስቱ ኮፒዎች መካከል እስከዚህ ዘመን የዘለቀ ካለ ያሳዩን፡፡
- ኡሥማን ቀዳሚያን ጽሑፎችን የእሳት ሲሳይ ማድረጉን በዚሁ መጽሐፍዎ ገፅ 25 ላይ አምነዋል፡፡ የሐፍሷ ቅጂ በማርዋን መቃጠሉን ቢክዱም በማስረጃ አስደግፈን ቅጥፈትዎትን አጋልጠናል፡፡ ስለዚህ የቁርአን ጽሑፎች እንደ መጽሐፍ ቅዱስ በተፈጥሯዊ ሂደት ሳይሆን ሆነ ተብለው እንዲወድሙ የመደረጋቸው ምክንያት ምስጢር ለመደበቅ የተደረገ ሸፍጥ አለመሆኑን በማስረጃ ያረጋግጡልን፡፡
አቶ ሐሰን ኦሪጅናል ቁርአን አለመኖሩን ልባቸው እያወቀ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ያለውን ሙግት ማቅረባቸው የግብዝነት መገለጫ ካልሆነ ሌላ ምን ይባላል? የገዛ ንግግራቸውን ወደ ራሳቸው ብንመልስና እንዲህ ብንላቸውስ ይቀበሉ ይሆን?
አሁን በምድር ላይ ያሉት ቁርአኖች ከኦሪጅናል ጸሐፊዎች ሥራ ለማመሳከር እንዳይሞከር በባለቤቶቹ የእጅ ጽሑፍ የተጻፉት መጽሐፍት ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል፡፡ ሁሉም የቁርአን መጽሐፍት በአረብኛ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው፡፡ አሳሳቢው ነገር ግን ይህ የአረብኛ እናት መጽሐፍ በኡሥማንና በአል-ሐጃጅ ዘመን ተቃጥሎ መጥፋቱና የሙስሊሙ ዓለም ያለ ማጣቀሻ መቅረቱ ነው፡፡
“ከመስታወት በተሠራ ቤት ውስጥ የምትኖር ከሆነ በሌላ ሰው ላይ ድንጋይ አትወርውር” የሚለው የፈረንጆቹ አባባል ልብ ላላቸው ሙስሊሞች ጥሩ ምክር ነው፡፡
አወቅሽ ሲሏት …
በመጽሐፉ ገፅ 43 ላይ እንዲህ ይላሉ፡-
ወንጌላት ከእየሱስ ሞት በኋላ 120 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ተጽፈዋል የሚለው ሐሳብ በታሪክነት ደረጃ እንጅ በዚያ ዘመን የተጻፉ ወንጌሎች አሉ ማለት አይደለም፡፡ በ The Guardian ዘገባ መሠረት የጥንቱ ወንጌል ከእየሱስ ልደት ከ300 ዓመታት በኋላ የተጻፈ ሲሆን የሲያትል ጽሑፍ (Codex sinaticus) ይባላል፡፡ ከ330-360 ዓ.ል. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፈ ይነገራል፡፡ ቋንቋው ግሪክኛ ነው፡፡ በአንድ የብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ ይገኛል … ከዚህ የቀደመ መጽሐፍ ‹ቅዱስ› በምድራችን ላይ የለም፡፡ (ገፅ 43)፡፡
ይህንን ካሉ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በድንግዝግዝ የተሞላ መሆኑን፣ ጸሐፊያኑ፣ የተጻፈበት ቦታና ዘመን አለመታወቃቸውንና በማሕበራዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ሲለዋወጥ መኖሩን ያለማስረጃ በመለፈፍ ይደመድማሉ (ገፅ 43)፡፡
ከላይ በተቀመጡት ጥቂት አረፍተ ነገሮች ውስጥ ከአረፍተ ነገሮቹ የበዙ ያፈጠጡ ያገጠጡ ስህተቶችና ቅጥፈቶች ይገኛሉ፡፡ በይቅርታ ሊታለፉ ከሚችሉት ቀላል ስህተቶች እንጀምር፡-
- በመጽሐፋቸው መጀመርያ አካባቢ የሐመረ ተዋሕዶ አዘጋጆች አንዳንድ የአረብኛ ቃላትን በትክክል መጻፍ አልቻሉም በሚል የከረረ ትችት ሰንዝረዋል (ገፅ 14-15)፡፡ ይህም የጸሐፊያኑን ስህተት አስቀድሞ በማሳየት መረጃዎቻቸውን ለማንኳሰስ የተደረገ ዘዴ ነው፡፡ ነገር ግን ራሳቸው በቆፈሩት ጉድጓድ ሲቀበሩ ማየት አስገራሚ ነው፡፡ Codex Sinaiticus የሚለውን “የሲያትል ጽሑፍ” ብለውታል፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ አነባበቡ “ኮዴክስ ሲናይቲከስ” ነው፡፡ የአሜሪካዋን ሲያትል እዚህ ጋር ምን እንዳመጣት አልገባኝም፡፡
- የእንግሊዘኛውንም ቃል ቢሆን አንድ ፊደል አጉድለው ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ነጥቦች እንደ ትልቅ ስህተት በመቁጠር ልንወቅሳቸው አንሻም፡፡ ነጥቦቹን ያነሳንበት ምክንያት ጸሐፊው መሰል ስህተቶችን መነሻ በማድረግ የሐመረ ተዋሕዶን አዘጋጆች በመዝለፋቸው ምክንያት ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ተከታዮቹ ቅጥፈቶች በይቅርታ የሚታለፉ አይደሉም፡፡
- ወንጌላት ከኢየሱስ ሞት በኋላ 120 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደተጻፉ መናገራቸው ቅጥፈት ነው፡፡ እጅግ ለዘብተኛ በተባሉት ሊቃውንት መሠረት እንኳ የወንጌላት ጽሑፎች ጌታችን ወደ ሰማይ ባረገ 40-60 ባሉት ዓመታት ውስጥ ተጽፈው ተጠናቀዋል፡፡ ራሳቸው አቶ ሐሰን ወንጌላት የተጻፉበትን ዘመን በተመለከተ የሰጡት እጅግ የተጋነነ መሠረተቢስ ግምት 125 ዓ.ም. ነው (ገፅ 33)፡፡ የጌታ ስቅለት 33 ዓ.ም. አካባቢ በመሆኑ የጊዜ ክፍተቱ 92 ዓመት እንጂ 120 አይደለም፡፡ ቀጣዩን መጽሐፋቸውን ከመጻፋቸው በፊት ኡስታዙ የሒሳብ ማሽን እንዲገዙ እንመክራቸዋለን፡፡
አቶ ሐሰን ከኮዴክስ ሲናይቲከስ የሚቀድም መጽሐፍ ቅዱስ አለመኖሩን ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው አይመስልም፡፡ እውነት ነው እስከ አሁን ባለው መረጃ መሠረት ኮዴክስ ሲናይቲከስ በዕድሜ ከሁሉም የሚቀድም ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንድ ላይ የያዘ ጥራዝ ነው፡፡ (በዚህ ረገድ ኮዴክስ ቫቲካነስ ተፎካካሪ ጽሑፍ ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል)፡፡ ይህ ማለት ግን በዕድሜ ከእርሱ የሚቀድሙ የብሉይና የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል በግብፅ ነጅ ሐማዲ በተባለ ሥፍራ የተገኘው p52 ወይም “ጆን ሪላንድ ፐፓይረስ” የሚል መጠርያ የተሰጠው የዮሐንስ ወንጌል ቁራጭ ዕድሜው በ114-138 ዓ.ም. መካከል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡[46] “ቦድመር ሁለት” የሚል ስያሜ የተሰጠው በ200 ዓ.ም. የተጻፈ የዮሐንስ ወንጌል ሌላ ጽሑፍም በእጃችን ይገኛል፡፡[47] ከኮዴክስ ሲናይቲከስ በአንድ ክፍለ ዘመን የሚቀድሙ የፓፒረስ ጽሑፎችን የያዘ አብዛኛውን የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ያካተተ ቸስተር ቢቲ የተሰኘ ሌላ ጽሑፍም ተገኝቷል፡፡[48] ወደ ብሉይ ኪዳን ደግሞ ስንመጣ መጽሐፈ አስቴር ሲቀር ሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሙት ባሕር አካባቢ ቁምራን በተሰኘ ሥፍራ ተገኝተዋል፡፡ ትንቢተ ኢሳይያስን የያዘው ጥቅልል ከክርስቶስ ልደት 200 ዓመታትን በመቅደም እንደተጻፈ ተረጋግጧል፡፡ ሌሎቹም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከ200 ዓ.ዓ. እስከ 70 ዓ.ም. ባሉት ዘመናት መካከል የተጻፉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡[49] ስለዚህ ከኮዴክስ ሲናይቲከስ የሚቀድሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች የሌሉ በማስመሰል መናገራቸው አንባቢያንን ለማሳሳት የፈፀሙት ተንኮል ነው፡፡ ሁሉንም የቁርአን ክፍል ያካተተ ቀዳሚው ቁርአን በ393 ዓ.ስ./ 1002 ዓ.ም. የተጻፈው በኩዌት አገር ራጃብ ቤተ መዘክር ውስጥ የሚገኘው ቁርአን መሆኑን አቶ ሐሰን ያውቁ ይሆን? የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ “የራሷ አሮባት…” ይሏል ይሄ ነው![50]
ማጣቀሻዎች
[1] ጥንታውያን መዛግብትን የማጥናት ሳይንስ ነው፡፡
[2] FF Bruce. The New Testament Documents, Are They Reliable?, 1959, p. 11
[3] Ibid.
[4] Britannica: Encyclopedia of World Religions; By Encyclopædia Britannica, Inc., 2006, p. 751, Entry: Moses
[5] Bart D. Ehrman. Jesus, interrupted : Revealing the Hidden Contradictions in the Bible (and Why We Don’t Know About Them); New York, HarperOne, 2009, pp. 144-145
[6] Norman Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, pp. 389
[7] John Barton & John M.: The Oxford Bible Commentary, Oxford University Press, 2001, p. 1084 (በጣም ለዘብተኛ በሆኑ ሊቃውንት የተጻፈ ነው፡፡)
[8] Craig L. Blomberg: Jesus and the Gospels, Broadman & Holman Publishers, Nashville, Tennesse, 1997, p. 74; Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, pp. 389
[9] ሜሪል ሲ.ቲኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተክርስታን የኮሚዩኒኬሽንና ስነ ጹሑፍ መምሪያ፣ ገጽ 282
[10] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 282-283
[11] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 83
[12] Geislere: Encyclopedia of Christian Apologetics, pp.
[13] ኑረዲን ኢብን አል-መሲህ፡፡ ክርስቶስ ማነው? ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ፤ 1ኛ ዕትም፣ ግንቦት 2008፣ ገፅ 103-104
[14] ቲም ፌሎስ፡፡ የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራርያ 2ኛ መጽሐፍ፤ ገፅ 342-343፣ 370፣ 399
[15] http://www.newworldencyclopedia.net/entry/David_Friedrich_Strauss
http://www.newworldencyclopedia.net/entry/Adolf_Harnack
[16] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ ገፅ 53
[17] ቴኒ፣ የአዲስ ኪዳን ቅኝት፣ ገፅ 239
[18] ዝኒ ከማሁ
[19] Bart D. Ehrman. Lost Christianities: the Battles for Scriptures and the Faiths We Never Knew; Oxford University Press, 2003, p. 9
[20] FF Bruce, Israel and the Nations, Exeter: Paternoster Press, 1973, p. 240.
[21] “Nazareth”, New Bible Dictionary, England: IVP, 1987, p. 819
[22] Herbert Thurston, The Holy Year of Jubilee, London: Sands & Co., 1900, p. 5
[23] Dante Alighieri. The Divine Comedy, section: Paradiso
[24] Geislere. Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 67
[25] As regards the “Gospel of Barnabas” itself, there is no question that it is a medieval fnetery … It contains anachronisms which can date only from the Middle Ages and not before, and shows a garbled comprehension of Islamic doctrines, calling the Prophet the “Messiah”, which Islam does not claim for him. Besides it farcical notion of sacred history, stylistically it is a mediocre parody of the Gospels, as the writings of Baha Allah are of the Koran. (Cyril Glassé, The Concise Encyclopedia of Islam, San Francisco: Harper & Row, 1989, p. 65)
[26] Geisler፡ Ensyclopedia of Christian Apologetics, pp. 188
[27] www.theguardian.com/world/2009/july/06/codex-sinaiticus-oldest-bible-online
[28] Geisler፡ Ensyclopedia of Christian Apologetics, pp.
[29] Muhammad ‘Ata’ur-Rahim and Ahmad Tomson. Jesus Prophet of Islam, Revised Edition; Taha Publishers Ltd. Uk, 1995, p. 7-8
[30] Ibid., p. 321
[31] “Most other ancient books are not so well authenticated. New Testament scholar Bruce Metzger estimated that the Mahabharata of Hinduism is copied with only about 90 percent accuracy and Homer’s Illiad with about 95 percent. By comparison, he estimated the New Testament is about 99.5 percent accurate.” (Geisler. Baker Encyclopedia of Christian Apologetics, p. 532)
[32] Edward F. Hills. The King James Version Defended; 4th edition (Des Moines: Christian Research Press, 1984), pp. 151-152
[33] Ibid., p. 52
[34] Ibid., p. 50
[35] Ibid.
[36] Norman L. Geisler & Thomas Howe. When Critics Ask: A Popular Hand Book on Bible Difficulties, Victor Books, p. 321-322 (pdf)
[37] Malik’s Muwatta, Book 8, Number 8.8.26; Book 8, Number 8.8.27
[38] Sahih Muslim 5:2286; Jalal al Din `Abdul Rahman b. abi Bakr al Suyuti. Al Itqan fi `ulum al Qur’an; Halabi, Cairo, 1935/1354, part 2, p. 25
[39] Sahih Al-Bukhari, Volume 5, Book 57, Number 105; Volume 6, Book 60, Number 468; Volume 5, Book 57, Number 85
[40] Cyril Glassé, The Concise Encyclopedia of Islam, p. 324
[41] ለበለጠ መረጃ፡- www.answering-islam.net/Green/seven.htm
በተከታዩ ድረ-ገፅ ላይ በሁለቱ ቁርአኖች መካከል የሚገኙ ብዙ ልዩነቶች ተዘርዝረዋል፡- www.answering-islam.net/Quran/Text/warsh_hafs.html
[42] Abdullah Yususf Ali, The Holy Qur’an, p. 1104, foot note. 3674
[43] http://masjidtusco.net/quran/appendices/appendix24.html
[44] https://www.theguardian.com/education/2000/aug/08/highereducation.theguardian
[45] Josh McDowell, Evidence That Demands a Verdict, p. 34
[46] Craig L. Blomberg: Jesus and the Gospels; Broadman & Holman Publishers, Nashville, Tennesse, 1997, p. 74
Geislere. Encyclopedia of Christian Apologetics, pp. 711, 962 (pdf)
[47] FF Bruce. The New Testament Documents, Are They Reliable?, 1959, pp. 7-9 (pdf)
[48] Ibid.
[49] Geisler. Ensyclopedia of Christian Apologetics, pp. 18-19 (pdf)
[50] የዚህ ቁርአን ፎቶግራፍ በዚህ ድረ ገፅ ላይ ይገኛል፡- http://www.usna.edu/users/humss/bwheeler/quran/kufi_393.html