ምዕራፍ 2: የኢየሱስ መወለድና የሚነሱ ጥያቄዎች

ምዕራፍ 2

የኢየሱስ መወለድና የሚነሱ ጥያቄዎች

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

79. በቁጥር 30 ላይ የተመለሰውን ጥያቄ ደግመው በመጠየቃቸው ምክንያት ታልፏል፡፡

80. ኢየሱስ ጅማሬ፤ ፍጥረት እና ዉልደት ከሌለዉ እንደ ክርስትና እሳቤ አንዱ “አምላክ” (ኢየሱሱ) “ልጅ/ወልድ” ሲባል ሌላኛዉ አምላክ (አብ) “አብ/አባት” ተብሏል፡፡ ታዲያ ለምንድነዉ ቅደም ተከተልን በሚገልጽ ቃላት የተጠሩት? “አባት” እና “ልጅ” ቅደም ተከተል ከሌላቸዉ ለምን እንዲህ ያለ መጠሪያ ኖራቸዉ? ካልሆነ ስያሜያቸዉን መቀያየር እንችላለንን?

አብና ወልድ የተባሉበት ምክንያት ኢየሱስ በዘለዓለማዊ መገኘት ከአብ የተገኘ በመሆኑ ነው (ለጥያቄ ቁጥር 74 የተሰጠውን መልስ ይመልከቱ)፡፡ እነዚህ ቃላት በመካከላቸው የሚገኘውን ጥብቅ ቁርኝት የሚገልፁ የትስስር ቃላት (Relational Terms) እንጂ የጊዜ ቅደም ተከተልን የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የዘለዓለም አባት”[1] ተብሎ የተጠራ ቢሆንም (ኢሳይያስ 9፡6) ነገር ግን ወልድ እንጂ አብ አይደለም፤ ስለዚህ ስያሜያቸውን በማቀያየር ኢየሱስን የአብ አባት ልንል አንችልም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ስያሜያቸው የተቀያየረበት ቦታ የለም፡፡

81. ማርያም ከመፀነሷ በፊት ኢየሱስ ነበርን? ከነበረ የትና እንዴት? እርሷ ከመንፈስ ቅዱስ ስትፀንስ እርሱ የት ነበር? ስትፀንስ ያ የነበረዉ ጠፋ ሊባል ነዉ? ወይስ ኢየሱስ እንደሚወለድ የሚገልጽ የአምላክ ቃል ብቻ ነበር? እስቲ በደንብ ያዉጠንጥኑት!

አሕመዲን የገዛ ጥያቄያቸውን በደንብ ያውጠነጠኑት አይመስልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ከአብ ጋር በሰማይ ይኖር እንደነበር በግልፅ ይናገራል (ዮሐንስ 1፡1-3፣ 3፡13፣ 6፡33-48፣ 6፡62፣ 8፡42፣ 56-58፣ 13፡3፣)፡፡

ዮሐንስ 1፡1 ላይ የተገለፀለው “ሎጎስ” (ቃል) አንዳንዶች እንደሚሉት ልበ እግዚአብሔር ውስጥ የተወሰነ ሐሳብ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ የነበረ ልዩ አካል ነው፡፡ ይህንንም ለማመልከት ሐዋርያው “ሁቶስ” (እርሱ) የሚለውን የግሪክ ተባዕታይ ተውላጠ ስም (Musculine Pronoun) እና “ዘንድ” ተብሎ የተተረጎመውን “ፕሮስ” የሚለውን ድርጊት ገላጭ (Proposition) ተጠቅሟል፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም ከአብ ጋር የነበረ፣ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ የሥላሴ አካል እንጂ በቅድስት ድንግል ማርያም ማህፀን በተፀነሰ ጊዜ መኖር የጀመረ አይደለም፡፡

82. ከሥላሴ አንዱ አብ ለሌላኛዉ (ለኢየሱስ) አባት ነዉ ይባላል፡፡ ሌላኛዉ የሥላሴ አባል የሆነዉ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ እናቱ ማርያን አስፀንሷል (ማቴዎስ 1፡1-20 ፤ ሊቃስ 1፡35) ታዲያ ኢየሱስ ስንት አባት ነዉ ያለዉ?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ተሠግዎ ከአብ ጋር እንደነበር በቁጥር 81 ላይ በማስረጃዎች አስደግፈን ገልጠናል፡፡ ወደ ዓለም የመጣው ተዓምራዊ በሆነው ልደቱ አማካይነት ቢሆንም አብ አባቱ የሆነው ወደዚህች ምድር እንደ ሰው ተወልዶ በመምጣቱ አይደለም፡፡ ብፅዕት እና ንፅህት ከሆነችው ከማርያም የመወለዱን ተዓምራዊ ሂደት መንፈስ ቅዱስ መከወኑ መንፈስ ቅዱስን የኢየሱስ አባት ካሰኘው ከሞላ ጎደል ፈጠራ በሆነው የቁርኣን ታሪክ መሠረት ዒሳ ከመርየም እንዲወለድ የማድረጉን ተግባር የከወነው ጂብሪል በመሆኑ ጂብሪል የዒሳ አባት ሊሆን ነው (ሱራ 19፡21-22)፡፡ ቁርኣን በግልፅ እንዳስቀመጠው ጂብሪል በእስትንፋሱ አማካይነት ዒሳ እንዲፀነስ አድርጎ ሳለ አሕመዲን ጂብሪልን የዒሳ አባት ብለው ካልጠሩት የጌታችንንም ልደት በዚያው መልኩ መረዳት ስለ ምን ተሳናቸው? በሁለት ሚዛን በመመዘን ማወናበድ ለምን ይሆን ያስፈለጋቸው?

83.የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ቁጥር 21 ላይ “ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ” ይላል፡፡ ኢየሱስን የገረዙት ሰዎች ሲገርዙት “የዓለምን ፈጣሪ ኃያሉን አምላክ ገረዝን” ብለዉ ነበር ያሰቡት? እንደ ክርስቲያኖች እምነት አምላክ የኢየሱስን ስጋ ተዋህዶታል፡፡ ያቺ በግርዛት የተቆረጠችዉ የኢየሱስ ቁራጭ ስጋስ የአምላክ ቁራጭ ልትሆን?

ጌታችን ፍፁም ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣቱ ምክንያት ከኃጢአት በስተቀር እንደ እኛው ሰው ነበር፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ ቤዛችን በመሆን የኃጢአት እዳችንን ለመክፈል ባልቻለም ነበር፡፡ ከሕግ በታች እንደመወለዱ እና የአብርሃም ዘር እንደመሆኑ መጠን መገረዝ አስፈልጎታል፡፡ በስምንተኛው ቀን የገረዙት ሰዎች ማንነቱን ማወቅ አለማወቃቸው ማንነቱን ስለማይለውጥ ጠያቂያችንን ሊያሳስባቸው አይገባም፡፡ የሰው ሥጋ ቁራጭ የነፍሱ ቁራጭ እንዳልሆነው ሁሉ የኢየሱስም የሥጋው ቁራጭ የመለኮቱ ቁራጭ አይደለም፡፡

84. ማርያም ፀንሳ ሳለ “ኢየሱስ” የሚለዉን ስያሜ እንደምታወጣለት ተገልጧል፡፡ በእርሷ ይህንን ስያሜ ከመሰጠቱ በፊት እዉን ኢየሱስ ከነበር ማን ነበር ስሙ?

ለዚህ ጥያቄ ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው መልስ ይሰጣል፡- “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ… ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን፡፡” (ዮሐንስ 1፡1-3፣ 14)

ሥጋ ከመሆኑ በፊት ኢየሱስ “እግዚአበሔር” እና “ቃል” (ሎጎስ) ተብሎ መጠራቱን ሐዋርያው ይነግረናል፡፡ “ኢየሱስ” የሚለውን ስም እና “ክርስቶስ” የሚለውን ማዕርግ ያገኘው ከተሠግዎ በኋላ ነው፡፡

85. በሉቃስ ወንጌል 2፡41-48 ላይ “ወላጆቹም በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ነበር፡፡ የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ፥ እንደ በዓሉ ሥርዓት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ቀኖቹንም ከፈጸሙ በኋላ፥ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፥ ዮሴፍም እናቱም አላወቁም ነበር፡፡ ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤ የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ፡፡ ዮሴፍና ማርያም በቤተ መቅደሱ ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም “ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብኝ? እነሆ፥ አባትህና እኔ ተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርኮ” አለችው” ይላል፡፡ ማርያም ልጇ ኢየሱስ የዓለም ፈጠሪ ኃያሉ አምላክ ነዉ ብላ ታምን ነበርን? አምላክ መሆኑን ብታዉቅ “አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር እኮ!” ትል ነበርን? አምላክነቱን ካወቀች ምን ያስጨንቃታል? ታዲያ ወላጅ እናቱ ማርያም ልጇ አምላክ ነዉ ብላ ካላመነች ክርስቲያኖች እንዴት አምላክ ሊሉት ቻሉ?

ይህ ንግግር ማርያም ኢየሱስ አምላክ ከመሆኑም በተጨማሪ ፍፁም ሰው መሆኑን ማመኗን እንጂ አምላክ መሆኑን አለማወቋን አያመለክትም፡፡ በልደቱ ወቅት እረኞች የተወለደው ህፃን የዓለም መድኃኒትና ጌታ መሆኑን መላእክት እደነገሯቸው መስክረው ነበር (ሉቃስ 2፡8-20)፡፡ “የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር፡፡” (ቁ. 19-20)፡፡ ከጥቅሱ እንደምንረዳው ማርያም ስለ ኢየሱስ የምታውቀውን ሁሉ በልቧ ለመያዝ መርጣ እንጂ በብሉይ ኪዳን ትንቢት የተነገረለት መሲህ፣ ጌታ እና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሳታውቅ ቀርታ አይደለም፡፡ መጨነቋ ደግሞ የኢየሱስ ሰብዓዊ ባሕርይ እንደማንኛውም ሰው እንክብካቤ የሚሻ መሆኑን መገንዘቧን ያመለክታል፡፡ ማርያም በወቅቱ የኢየሱስን ማንነት ሙሉ በሙሉ አልተገነዘበችም ቢባል እንኳ የእርሷ አለመገንዘብ ማንነቱን የሚለውጠው እንዴት ሆኖ ነው? ነገር ግን አሕመዲን እንደልማዳቸው ቆርጠው ያስቀሩት የኢየሱስን ምላሽ የያዘው የጥቅሱ ቀጣይ ክፍል እንዲህ ይላል፡- “እርሱም፦ ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው፡፡” (ቁ. 49)፡፡ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ነው “የአባቴ ቤት” በማለት የጠራው፡፡ ነገር ግን ጠያቂያችን አንባቢያኖቻቸው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መናገሩን እንዲያውቁ ስላልፈለጉ ለአላማቸው ብቻ የሚመቸውን በመጥቀስ ሌላውን ቆርጠው አስቀርተውታል፡፡

86. ክርስቲያኖች እንደሚሉት ኢየሱስ “ሰዋዊ” ባህሪዉን ከማርያም (ከእናቱ) መለኮታዊ ባህሪዉን ደግሞ ከአባቱ (ከአብ) ነስቶ ተወለደ፡፡ ታዲያ አንዱን ባህሪዉን ከአባቱ ሌላዉኛዉን ደግሞ ከእናቱ ከነሳ አባቱ እና እናቱ ምን እና ምን ናቸዉ??

አብ የኢየሱስ አባት የተባለው ኢየሱስ ከማርያም በመወለዱ ምክንያት ባለመሆኑ ይህ ጥያቄ አሕመዲን ክርስቲያናዊውን አስተምህሮ ባለማወቃቸው ምክንያት መደነጋገራቸውን ከማሳየት የዘለለ ቁምነገር የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ በማርያም ማህፀን አድሮ ከእርሷ ሥጋን በመንሳት ፍፁም ሰው ሆኖ መወለዱን እንጂ ግማሽ ባሕርዩን ከእግዚአብሔር ግማሽ ባሕርዩን ከሰው ነስቶ እንደተወለደ የሚያምን ክርስቲያን የለም፡፡ ቁርኣን ግን ዒሳ ከአላህ የሆነ መንፈስ መሆኑን ይናገራል፡፡ ስለዚህ ዒሳ አንዱን ባሕርዩን ከአላህ ሌላ ባሕርዩን ከመርያም ካገኘ አላህ እና መርየም ምንና ምን ናቸው? በተጨማሪም “የመጽሐፉ እናት” በመባል የምትታወቀው በአላህ ዘንድ የምትገኘው ያቺ ነገር ለአላህ ምኑ እንደሆነች ቢብራራልን? ይህንን የጠየቅንበት ምክንያት አሕመዲን የጠየቁት ጥያቄ ምን ትርጉምና ስሜት እንደሚሰጥ ሙስሊሞች በክርስቲያኖች ቦታ ሆነው እንዲያውቁ ያህል እንጂ የሙስሊሞች መልስ ምን ሊሆን እንደሚችል ጠፍቶን አይደለም፡፡

87. ኢየሱስ ያለ አባት በመወለዱ “አምላክ” ከሆነ ያለ አባትና እናት የተፈጠረዉን አዳም ትልቅ “አምላክ” ልንለዉ ለምን አልደፈርንም?

ኢየሱስ አምላክ የሆነው ያለ አባት በመወለዱ ምክንያት እንደሆነ ክርስትና ስለማያስተምር ይህ የአሕመዲን ጥያቄ ዕውቀት ከማጣት የመነጨ ነው፡፡ ኢየሱስ አምላክ በመሆኑ ያለ አባት ተወለደ እንጂ ያለ አባት ስለተወለደ አምላክ አልሆነም፡፡ አዳም የመጀመርያው ሰው በመሆኑ ምክንያት ያለ እናት እና አባት እንደ ተፈጠረ ያስማማናል፡፡ ነገር ግን ዒሳ ያለ አባት ከእናት ብቻ መወለዱ ለምን ይሆን? ሙስሊሞች ምናልባት ለሰው ልጆች ምልክት እንዲሆን ነው የሚል መልስ ይሰጡ ይሆናል፡፡ በእምነት እንጂ በተግባር ሊረጋገጥ የማይችለውን መንገድ መጠቀም ለሰው ልጆች ምልክት ሊሆን የሚችለው እንዴት ሆኖ ነው?

88. ማቴዎስ 1፡23 ላይ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው፡፡” ይላል፡፡ ድንግል ምን ትወልዳለች ተባለ? ወንድ ልጅ! ታዲያ ‹‹ድንግል አምላኳን ወለደች›› የሚለዉ ከየት መጣ?

ድንግል የወለደችው ወንድ ልጅ አማኑኤል (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) ተብሏል፡፡ ለዚህ ነው ክርስቲያኖች ድንግል አምላኳን እንደወለደች የሚናገሩት፡፡ የተጠቀሰው ጥቅስ ራሱ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ያሳያል፡፡

89. ሉቃስ 2፡6-7 ላይ “በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው” ይላል፡፡ ክርስቲያኖች እንደሚሉት ድንግል አምላኳን ነዉ የወለደችዉ? ጥቅሱ “ወንድ ልጅ” ነዉ የሚለዉ? ኢየሱስን ስትወልድ ማርያም “አምላኬን ወለድኩ” ብላ ነበር ያሰበችዉ ወይስ “ወንድ ልጅ”? ታዲያ “ድንግል አምላኳን ወለደች” የሚለዉ ከየት መጣ? ከጉባኤ? በሐዋርያት ዘመንስ ይህ ‹‹ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች›› የሚለዉ እምነት ነበርን? ታዲያ ከየት መጣ? ከጉባኤ!! የሚከተለዉ ይህንን ያረጋግጣል፡- ቤተክርስቲያን በ431 ዓ.ል በኤፌሶን በተካሄደዉ ጉባኤ ድንግል ማርያም ቴዎቶኮስ (የአምላክ) እናት መሆዋን እንደ ሃይማኖት ህግ አወጀች፡፡ (ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዉ አብ ቃል እና የዓለም መድሃኒት፤ በኢት/ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጽ/ጠ/ጽ/ቤት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ የተዘጋጀ፤ አዲስ አበባ ፤ ማስተር ማተሚያ ቤት ገፅ 159)

ጠያቂያችን በጠቀሱት በዚያው ክፍል ውስጥ ኢየሱስ የዓለም መድኃኒት እና ጌታ መሆኑ ስለተነገረ ድንግል ፈጣሪዋን እንደወለደች መነገሩ ትክክል ነው (ሉቃስ 2፡10-11)፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ የሚወለደው ልጅ አምላክ መሆኑን መሲሁ ከመወለዱ ከ700 ዓመታት በፊት ትንቢት ተናግሯል (ኢሳይያስ 9፡6)፡፡ ስለዚህ “ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች” የሚለው ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እስከሆነ ድረስ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተጠቀሰው እውነት ኦፊሴላዊ በሆነ ጉባኤ እውቅና በመስጠት እንደ እምነት አቋም መያዟ ስህተቱ ምኑ ላይ ነው?

ማስታወሻ


[1] “አቪ ያድ” የሚለው የእብራይስጥ ሐረግ ቀጥተኛ ትርጉም ኢየሱስ ለዘላለማዊነት (Eternity) ለራሱ አባት መሆኑን (አስገኚ መሆኑን) የሚያመለክት ነው፡፡

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ