ምዕራፍ 9 እውን እነዚህ የአምላክ ባህሪያት ናቸውን? ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ

ምዕራፍ 9

እውን እነዚህ የአምላክ ባህሪያት ናቸውን?

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች ምላሽ ካቆምንበት እንቀጥላለን

  1. ጳዉሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 1፡25 ላይ “ምክንያቱም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል፤ ከሰውም ብርታት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል፡፡” ብሏል፡፡ እንደዚህ ጥቅስ አባባል እግዚአብሔርም ሞኝነት አለበት፤ ግን የእርሱ ሞኝነት ከሰው ጥበብ ይጠበባል፡፡ ድካምም አለበት፤ ነገር ግን ድካሙ ከሰው ብርታት ይበረታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው አምላክ ድካምና ሞኝነት ካለበት ምኑን አምላክ ሆነ? ወይስ ይህ ጥቅስ የጳውሎስ ፈጠራ ነው?

ሐዋርያው ምን እያለ እንደሆነ ለመረዳት አውዱን ማንበብ ያስፈልጋል፡-

“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፡፡ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና፡፡ ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን? በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና፡፡ መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፡፡ ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና፡፡” (1ቆሮንቶስ 1፡18-25)፡፡

የወንጌል መልእክት በፍልስፍና የተቀመመ ባለመሆኑ ግሪኮች እንደ ሞኝነት ይቆጥሩታል፡፡ አይሁድ ደግሞ መሲሁ እንደማይሞት ስለሚያምኑ እንደ ድካም ይቆጥሩታል፡፡ ሐዋርያው እነርሱ የተናገሩትን በመጥቀስ በምፀት እየመለሰላቸው ነው፡፡ በዘመናዊ አጻጻፍ ቢሆን ኖሮ “ሞኝነት” እና “ድካም” የሚሉት ቃላት የተቃዋሚዎች እንጂ የጳውሎስ ባለመሆናቸው ትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ ሐዋርያው “እናንተ ሞኝነት የምትሉት የክርስቶስ መስቀል ከሰው ጥበብ የተጠበበ ነው፤ እናንተ ድካም የምትሉት የክርስቶስ መስቀል ከሰው ኃይል የበረታ ነው” በማለት ምፀታዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እየሰጣቸው ነው፡፡ ጠያቂው ይህንን ሙግት ወደ መድረኩ ማምጣታቸው ስለመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ፍታቴ ያላቸው ዕውቀት ጥራዝ ነጠቅ መሆኑን ያሳያል፡፡

2. መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ላይ እንዲህ ይላል፦ “ቀኑ መሸትሸት ሲል፤ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሔዋን ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር  አምላክ ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ግን አዳምን ተጣርቶ፤ “የት ነህ”? አለው፡፡” አዳምም፤ “ድምጽህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ፡፡” ዘፍጥረት (3፡8-10)፡፡ እግዚአብሔር “ዕራቁትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ በላህን?” አለው፡፡” (ዘፍጥረት 3፡11)፡፡  ይህ አንቀፅ እውን የአምላክ ቃል ነውን? ከሆነስ አምላክ እንዴት የት እንደተደበቁ ማወቅ ተስኖት አዳምን “የት ነህ?” ሲል ይጠይቃል? የተከለከለውን ዛፍ ይብላ ወይም አይብላስ ጠይቆ ነው የሚያረጋግጠው?  

እግዚአብሔር አምላክ አዳም ያለበትን ቦታ በራሱ አንደበት እንዲናገር ፈልጎ እንጂ የት እንዳለ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ የተከለከለውንም ዛፍ ስለመብላቱ በገዛ አንደበቱ እንዲናዘዝ ፈልጎ እንጂ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው የፈፀሙትን ጥፋት እያወቁ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ማናዘዝ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጥፋታቸውን እንዲገነዘቡና እንዲፀፀቱ በማድረግ ረገድ በቀጥታ ከመውቀስ የተሻለ ነው፡፡ አሕመዲን እንደ ሙስሊምነታቸው ይህንን የሚጠይቁ ከሆነ አምላካቸው አላህም በተመሳሳይ መንገድ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ በተደጋጋሚ ስለሚታይ እርሱንስ ምን ሊሉት ነው?

ሱራ 38፡75 “(አላህም) «ኢብሊስ ሆይ! በሁለት እጆቼ (በኃይሌ) ለፈጠርኩት ከመስገድ ምን ከለከለህ? (አሁን) ኮራህን? ወይስ (ፊቱኑ) ከትዕቢተኞቹ ነበርክ?» አለው፡፡”

ምን እንደከለከለው እንዴት ማወቅ አልቻለም? የከለከለው ኩራት መሆን አለመሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን ተሳነው? ኩራት መች እንደጀመረው ጠይቆ ነው የሚያረጋግጠው?

ሱራ 2፡260 “ኢብራሂምም «ጌታዬ ሆይ! ሙታንን እንዴት ሕያው እንደምታደርግ አሳየኝ» ባለ ጊዜ (አስታውስ፡፡) አላህ ፡- «አላመንክምን?» አለው፡፡ «አይደለም (አምኛለሁ)፤ ግን ልቤ እንዲረጋ» ነው አለ፡፡

 ማመን አለማመኑን እርግጠኛ ስላልሆነ ይሆን ይህንን ጥያቄ የጠየቀው?

አሕመዲን ይህንን ደካማ የሆነ ጥያቄ ማንሳታቸው የገዛ መጽሐፋቸውን እንኳ በወጉ አለማወቃቸውን ያመለክታል፡፡

3. ዘፀአት 31፡17 “በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘለዓለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰማይ ምድርን በስድስት ቀን ሰርቶ፤  በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፎአልና” ይላል፡፡ እንዲሁም በሌላ ስፍራ “ስለ ሰባተኛውም ቀን በአንድ ስፍራ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሏልና፡፡” (ዕብራውያን 4፡4)፡፡ አምላክ እንደሰው ሥራ ሰርቶ ያርፋልን? ድካም ይሰማዋል እንዴ? አንዳንድ ክርስቲያኖች “አምላክ ሊያስተምረን ብሎ ነው” ይላሉ፡፡ አምላክ የሚያስተምረው ነቢያትንና መጻሕፍትን በመላክ ነው ወይንስ የደካማውን የሰው ልጅ ባህሪ በመላበስ?

በዚህ ቦታ ጥቅም ላይ የዋለው የዕብራይስጥ ቃል “ሻባት” የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ “ማቆም” ወይም “መተው” የሚል ነው፡፡ ቃሉ እንደየአውዱ በተለያዩ መንገዶች ሊተረጎም ቢችልም ከድካም የተነሳ እረፍት መውሰድን የግድ አያመለክትም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊያን ይህንን ቃል የተጠቀሙት እግዚአብሔር ደክሞት እንዳረፈ ለማመልከት ሳይሆን እግዚአብሔር የመፍጠር ሥራውን ስላጠናቀቀ ማቆሙን ለማመልከት ነው፡፡[1] ጠያቂው “አምላክ ሊያስተምረን ብሎ ነው” በማለት መልስ የሚሰጡ ክርስቲያኖች ስለመኖራቸው የተናገሯት ነገር ፈጠራ እንዳትሆን እጠረጥራለሁ፡፡ ግንዛቤው ያላቸው ክርስቲያኖች በዚህ መልኩ ምላሽ አይሰጡም፡፡ ጠያቂው የክርስትናን ትምህርት ለመገዳደር መጽሐፍ እስከጻፉ ድረስ ከግለሰቦች ከለቃቀሟቸው “ምላሾ” ሳይሆን ዕውቀቱ ባላቸው ክርስቲያኖች ከተሰጡት ምላሾች በመነሳት ሙግታቸውን ማቅረብ ነበረባቸው፡፡

4. መዝሙር 44፡23-24 “ጌታ ሆይ፤ ንቃ! ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፤ ለዘለዓለም አትጣለን፡፡ ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? መከራችንንና መጠቃታችንን ለምን ትረሳለህ” ይላል፡፡ አምላክ ተኝቶ ሰው “ንቃ”  ብሎ ይቀሰቅሰዋልን? ለመሆኑስ አምላክ ይረሳልን? ታዲያ ይህን አምላክ ነው ሙስሊሞች እንዲያምኑበት ክርስቲያኖች የሚጣሩት? ወይስ ይህ የአምላክ ቃል አይደለም?

ይህ መዝሙር በአሣቃቂ መከራ ውስጥ ሲያልፉ የነበሩ ሰዎች የዘመሩት ነው፡፡ እግዚአብሔር የተዋቸውና የጣላቸው የመሰላቸው ሰዎች እግዚአብሔር እንዲረዳቸው የተማፀኑበት ነው፡፡ “ንቃ፣ ስለምን ትተኛለህ፣ ተነስ” የሚሉት ቃላት ዘይቤያዊ ሲሆኑ በቀጥታ መተርጎም የለባቸውም፡፡ ዘማሪያኑ በመከራ ውስጥ መሆናቸውንና እግዚአብሔር እነርሱን ከመርዳት በመዘግየቱ ማዘናቸውን ብቻ የሚገልፁ ናቸው፡፡ እዚሁ መዝሙረ ዳዊት ውስጥ “እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም” ተብሎ ተጽፏል (121፡4)፡፡

5. መዝሙር 78፡65 “ጌታም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ፤ የወይን ጠጅ ስካር እንደ በረደለት ጀግናም ብድግ አለ” ይላል፡፡ አምለክ ከእንቅልፍ እንዴት ይነቃል? ኃያሉን አምላክ በዚህ መልኩ መግለጽ ተገቢ ነውን?

እግዚአብሔር ባልተጠበቀ ሰዓት ድንገት ክፉዎች ላይ እርምጃ መውሰወዱን ለማመልከት የተነገረ ዘይቤያዊ ገለፃ በመሆኑ በቀጥታ ካልተረጎምነውና ዘይቤያዊ አነጋገር መሆኑን ከተገነዘብን ንግግሩ ችግር የለበትም፡፡ “እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤ የዘለዓለምን ኀሣር ሰጣቸው፡፡” (ቁ.65-66)፡፡

ጠያቂው ዘይቤያዊ ንግግሮችን በቀጥታ የሚተረጉሙ ከሆነ ተከታዮቹን የቁርኣን ጥቅሶች ምን ሊሏቸው ነው?፡- “እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን (ሃይማኖቱን) ብትረዱ፤ ይረዳችኋል፡፡” (ሱራ 47፡7) – አላህ የኛን እርዳታ የሚሻ ደካማ አምላክ ነው ማለት ነውን? በቅንፍ የተቀመጠው (ሃይማኖቱን) የሚለው በተርጓሚዎቹ የተጨመረ እንጂ በአረብኛው ንባብ ውስጥ አይገኝም፡፡

“ለአላህ መልካም ብድርን ብታበድሩ (ምንዳውን) ለናንተ ይደራርበዋል፤ ለናንተም ይምራል፤ አላህም አመስጋኝ ታጋሽ ነው፡፡” (ሱራ 64፡17) – አላህ ኃጢአትን የሚምረው ለአበዳሪዎቹ ነው ማለት ነውን? የሚበደር አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው? እነዚህን ጥያቄዎች የጠየቅነው የአሕመዲን ዕይታ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ለማሳየት ያህል ነው፡፡ እነዚህ የቁርኣን ጥቅሶች ዘይቤያዊ በሆነ መንገድ የሚተረጎሙ ከሆነ ችግር የለባቸውም፡፡ በቀጥታ ከተተረጎሙ ግን በአላህ ባሕርይ ላይ ከባድ ጥያቄዎችን ያስከትላሉ፡፡ ጠያቂው የጠቀሷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም ልክ እንደእነዚህ የቁርኣን ጥቅሶች ሁሉ ዘይቤያዊ በመሆናቸው በቀጥታ መተርጎም የለባቸውም፡፡

6. ዘፍጥረት 32:22-28 “…አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው አደረ፡፡ ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤  በግብግቡም የያዕቆብ ጭን ከመገጠሚያው ላይ ተናጋ፡፡ በዚያን ጊዜ ሰውየው፤  “እንግዲህ መንጋቱ ስለሆን ልቀቀኝና ልሂድ” አለው፡፡ ያቆብም፤ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው፡፡ ሰውየውም፤  ከእግዚአብሔርም ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ ያዕቆብ አይባልም” አለው” ይላል፡፡ ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎዋልን? እንዴትስ ታግሎ አሸነፈ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው አምላክ ይህ ነው ማለት ነው?

የያዕቆብ ሕይወት ከመጀመርያው እስከዚያች ዕለት ድረስ በትግል የተሞላ ነበር፡፡ ያዕቆብ በተፈጠሮው እንደ ስሙ በማታለል ይኖር የነበረ ሰው ሲሆን ያንን ሁሉ ትግል ያደርግ የነበረው እውነተኛውን በረከት ፍለጋ ነበር፡፡ እውነተኛውን በረከት ሳያገኝ ዕድሜው ቢገፋም አሁን ግን ምንጩን አግኝቶታል፡፡ እግዚአብሔር በተመጠነ ኃይል ሆኖ በአካል ተገልጦ ተገዳደረው፡፡ ያዕቆብ ማንነቱን ስለተገነዘበ እንዲባርከው አጥብቆ ያዘው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በያዕቆብ አቅም ልክ የገለጠው ፅናቱን ለመፈተን ሲሆን ያዕቆብም የመጨረሻ እንጥፍጣፊ አቅሙን በመጠቀም በረከቱን ለማግኘት በመታገል ፅናቱን አሳይቷል፡፡ እግዚአብሔርም “ተሸነፈለት”፡፡ ይህ “መሸነፍ” ግን በያዕቆብ ኃይል የሆነ አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመመጠን ተገልጦ ለያዕቆብ ፅናት ማረጋገጫ ሲል መሸነፍን ስለፈቀደ ነበር፡፡ (አባቶች ልጆቻቸውን ፅናትና በራስ መተማመንን ለማስተማር የሆነ ነገር በእጃቸው ይዘው እንደሚታገሉትና በመጨረሻም ለልጆቻቸው እንደሚሸነፉት ዓይነት ማለት ነው፡፡) ይህ እግዚአብሔር አምላካችን ምን ያህል ለኛ የቀረበና እንደ አባት የሚወደን መሆኑን የሚያሳይ እጅግ ውብ ታሪክ ነው፡፡ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን ጥሎ ወደ ምድር በመምጣት ከእኛ ጋር እንዲኖርና እንዲሞትልን ያደረገው ለኛ ያለው ፍቅር ነው፡፡ ሙስሊሞች የሚያመልኩት አምላክ ከሰው ልጆች እጅግ ሩቅ የሆነና የግል ሕብረት ለማድረግ የማይፈቅድ በመሆኑ ምክንያት መሰል ታሪኮች ጥያቄ ቢፈጥሩባቸው አያስገርምም፡፡

7. ዘፍጥረት 6፡6 “እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተፀፀተ፤ በልቡም እጅግ አዘነ” ይላል፡፡ እግዚአብሔር እንደ ደካማው ፍጥረት እንደሰው ባደረገው ይፀፀታልን? በመሠረቱ “ጸጸት” ማለት አንድ ሰው አንድን ድርጊት ያደርግና በኋላ ያደረገው ድርጊት በጠበቀው መልኩ ሳይሆንለት ሲቀር ነው፡፡ ይህ ለሰው የተገባ ባህሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው አስቀድሞ የነገርን ፍጻሜ ማወቅ አይችልምና፡፡ አምላክ ግን ሁሉን የሚያውቅ ጌታ ስለሆነ በሚሰራው ሥራ አይጸጸትም፡፡ ታዲያ “አምላክ ሰውን በመፍጠሩ ተጸጸተ” ማለት አግባብነት አለውን? ሰውን ሲፈጥር ሰው ምን እንደሚያደርግ አስቀድሞ አያውቅምን? የማያውቅ ከሆነ ሁሉን አዋቂ አይደለም ማለት ነው፡፡ ታድያ ይህ አምላክ መሆን ይችላልን? ወይስ ይህ  የአምላክ ሳይሆን የሰው ቃል ነው?

ተከታዮቹም ጥያቄዎች ተያያዥ ናቸው፡-

8. 1ኛ ሳሙኤል 15:35 “ሳሙኤል ሳኦል ቢያለቅስለትም እንኳን እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ ዳግመኛ ሊያየው አልሄደም፡፡ እግዚአብሔርም ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተፀፀተ” ይላል፡፡ አምላክ ይፀፀታልን? ፈጣሪን ይፀፀታል ማለት ድፍረት አይሆንምን?

9. አሞፅ 7፡1-6 “ጌታ እግዚያብሔር በእሳት ሊፈርድ ተዘጋጀ ፤ እሳቱም ታላቁን ጥልቅ አደረቀ ፤ ምድሪቱንም በላ ፡፡ ከዚያም በኃላ ፤ “ጌታ እግዚያብሄር ሆይ! እንድትተወው እለምንሃለሁ ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ አልሁ ፡፡ 
እግዚአብሔር ስለዚህ ነገር ተፀፀተ ፤ ጌታ እግዚአብሔር፤ “ይህም ደግሞ አይፈፀምም” አለ” ይላል ፡፡ አምላክ ይፀፀታልን?

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ተፀፀተ” ሲል እንደ ሰው ያለ ፀፀት አለመሆኑን በሌሎች ቦታዎች ላይ ግልፅ አድርጓል፡- “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፡፡” (ዘኍልቍ 23፡19)፡፡ “የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው፡፡” (1ሳሙኤል 15፡29)፡፡

በነዚህ ቦታዎች ፀፀትን ለማመልከት የገባው የእብራይስጥ ቃል “ናኻም” የሚል ሲሆን በተለያዩ አውዶች ውስጥ የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ ለምሳሌ ያህል ተከታዮቹን ጥቅሶች ተመልከቱ፡-

“እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ (ናኻም)፡፡” (ዘጸአት 32፡14)

“ግብፃውያንስ፦ በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ (ናኻም)፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ፡፡” (ዘጸአት 32፡12)

“እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳል፥ ስለ ባሪያዎቹም ያዝናል (ናኻም)” (ዘዳግም 32፡36)

“ምሕረትህ ለመጽናናቴ (ናኻም) ትሁነኝ፥ እንደ ቃልህም ለባሪያህ ይሁነው፡፡” (መዝሙር 119፡76)

“እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና (ናኻም)፥ ባሪያዎቹንም ይረዳልና፡፡” (መዝሙር 135፡14)

“በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል፡፡ እንግዲህ በዚህ ነገር አልቁጣምን (ናኻም)?” (ኢሳይያስ 57፡6)

“አጽናኑ (ናኻም)፥ ሕዝቤን አጽናኑ (ናኻም) ይላል አምላካችሁ፡፡” (ኢሳይያስ 40፡1)

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደ ሰው እንደማይፀፀት ከነገረን፤ ናኻም የሚለው የእብራይስጥ ቃል ደግሞ በብዙ መንገዶች ሊተረጎም ከቻለ (መራራት፣ መመለስ፣ ማዘን፣ መጽናናት፣ መፍረድ፣ መቆጣት)፤ ጠያቂው እግዚአብሔር “እንደተፀፀተ” የሚናገሩትን ጥቅሶች አጥብበው መተርጎማቸው ትክክል አይደለም፡፡ ዘፍጥረት 6፡6 እና 1ሳሙኤል 15፡35 ላይ የሚገኙት ጥቅሶች እግዚአብሔር ማዘኑን ለመግለፅ የተነገሩ ሲሆኑ (NIV ትርጉም “Grieved” ብሎ ተርጉሟቸዋል) አሞፅ 7፡1-6 ላይ የሚገኘው ደግሞ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ሊፈፅመው ከነበረው ፍርድ መታቀቡን ያመለክታሉ፡፡

10. ኢሳይያስ 7:20 “በዚያን ቀን ፤እግዚአብሔር ከወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ፤ የራሱንና የእግሩን ጠጉር ይላጨዋል፤ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይበላል” ይላል፡፡ አምላክ ምላጭ ይከራያልን? ሁሉን የፈጠረና ዓለሙ ሁሉ የርሱስ አይደለምን? ጸጉር ይላጫልን? ተራ የሰው ማህበራ ድርጊቶቹን ሁሉ የፈጣሪ እለታዊ ድርጊት እንደሆኑ አድርጎ መግለፅ ለፈጣሪ ያለንን እሳቤ በብዥታ የተሞላ አያደርግምን?

“ምላጭ” የተባለው የአሦር ንጉሥ መሆኑ በግልፅ እየታየ ይህ ጥያቄ መነሳቱ በራሱ በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡ ይህ ቃል እግዚአብሔር እርሱን በማያቀውቀው፣ ጣዖት አምላኪ በሆነው የአሦር ንጉሥ ተጠቅሞ የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ጠላት የሆነውን ኤፍሬምን እንደሚያዋርድ የተነገረ ዘይቤያዊ ንግግር ነው፡፡ (መላጨት የኀዘንና የውርደት ምልክት ነው 2ሳሙኤል 10፡4፣ ኤርምያስ 41፡5፡፡) ይህ ነጥብ የሙግት ሐሳብ ሆኖ መቅረቡ በራሱ እጅግ አስቂኝ ነው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ሙስሊም ወገኖች ይህንን ነጥብ “ከጠንካራ” ሙግቶቻቸው መካከል እንደ አንዱ በመቁጠር በተደጋጋሚ ማንሳታቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ብዙ ሙስሊሞች አንዱ የጻፈውን በመያዝ በደመነፍስና በድርቅና ከመከራከር በዘለለ ክፍሉን አውጥቶ የማንበብ ልማድ የላቸውም፡፡

  1. ምሳሌ 30:21-23 “ምድር በሦስት ነገር ትናወጣለች፤ እንዲያውም መሸከም የማትችላቸው አራት ነገሮች ናቸው፤ ባርያ ሲነግሥ፤ ሰነፍ እንጀራ ሲጠግብ፤ የተጠላች ሴት ባል ስታገባ፤ ሴት ባሪያ በእመቤትዋ እግር ስትተካ” ይላል፡፡ ምናለ ባርያ ቢነግሥ?ምናለ የተጠላች ሴት ብታገባ? ሴት ባሪያ በእመቤቷ ብትተካስ? ክርስቲያኖች የሚያመልኩት አምላክ በሰው እኩልነት አያምንምን? ወይስ ይህ የአምላክ ቃል አይደለምን?

ጠያቂው ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት የሌላቸውና በዕውቀት ያልበቁ ሰዎች በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ቢወጡ ችግር የለውም እያሉ ነውን? በእርግጥ ጥቅሱ ባርያ መንገሥ የለበትም፣ የተጠላች ሴት ማግባት የለባትም ወይም ሴት ባርያ በእመቤቷ መተካት የለባትም እያለ አይደለም ነገር እነዚህ ሰዎች ይህንን ክብር ሲያገኙ ከመጠን በላይ ራሳቸውን እንደሚቆልሉና የተናጋ ስነ ልቦና ስላላቸው ለበቀል እንደሚነሳሱ ለመግለፅ የተነገረ ግነታዊ ዘይቤ ነው፡፡ እንዲያ ያሉ ሰዎች ይህንን ክብር ሲያገኙ ችግር ስለሚፈጥሩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ስለ እኩልነት ሊሰብኩን የሚዳዳቸው ጠያቂያችን የገዛ ሃይማኖታቸው በሰው ልጆች እኩልነት እንደማያምን ልባቸው ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ በቁርኣን መሠረት ወንዶች ከሴቶች ብልጫ አላቸው (2፡228)፣ የአንድ ወንድ ምስክርነት ከሁለት ሴቶች ጋር እኩል ነው (2፡282)፣ የወንዱ የውርስ ድርሻ ከሴቷ እጥፍ ነው (4፡11)፡፡

12. በትንቢት ኢሳይያስ 54፡4-5 ላይ “አታፍሪምና አትፍሪ ፤ አትዋረጂምና አትደንግጪ፤ የሕፃንነትሽንም እፍረት ትረሺዋለሽ፤ የመበለትነትሽንም ስድብ ከእግዲህ ወዲህ አታሥቢው ፤ ፈጣሪሽ ባልሽ ነው ፤ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው ፡፡” ይላል፡፡ እግዚአብሔር ሚስት ያገባልን? ይህ ለዓለም ፈጣሪ አምላክ የሚገባ ነገር ነውን?

ጥቅሱ እየተናገረ ያለው ስለ ሴት ሳይሆን ስለ እስራኤል ነው፡፡ እግዚአብሔር የእስራኤል ተንከባካቢ፣ አስተዳዳሪና ጠባቂ መሆኑን ለመግፅ የተነገረ ተለዋጭ ዘይቤ ነው፡፡ ጠያቂው ጥቅሶችን በአውዳቸው ውስጥ ያለማንበብ አባዜ በእጅጉ ተጠናውቷቸዋል፡፡

13. ዘፍጥረት 18፡20-21 “የሰዶምና ገሞራ ሕዝቦች የሚፈፅሙትን በደል ሰምቻለሁ፤ ኃጢአታቸውም እጅግ ከባድ ነው፤ ስለ እነርሱ የሰማሁት ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ወደ እነርሱ እወርዳለሁ” ይላል፡፡ እንዲሁም ዘፍጥረት 11፡5 እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ” ይላል፡፡ ምን ለማለት ተፈልጎ ይሆን ? ታዲያ እግዚአብሔር የሰማውን ለማረጋገጥ  እንደ ሰው በቦታው መገኘት ካስፈለገው ምኑን አምላክ ሆነ? ሁሉን ማወቅ ተስኖት? በዚህ አምላክ ነው ክርስቲያኖች የሚያምኑት?

የ1954 ዕትም እንዲህ ይላል፡- “እግዚአብሔርም አለ፦ የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥ እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ፡፡”

ይህ ጥቅስ የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት አጠያያቂ የሚያደርግ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው፡፡ ነገር ግን በሰዎች ሁኔታ ውስጥ እንደሚሳተፍና ሰዎች ወደ እርሱ ስለጮኹ ብቻ በስሜት ተነሳስቶ እንደማይፈርድ ነገር ግን ነገሮችን ከስር መሠረታቸው መርምሮ እንደሚፈርድ ለማሳወቅ የገባ ዘይቤ ነው፡፡

14. ዘጸአት 12:12-13 “እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ሀገር አልፋለሁ፤ በግብጽም ሀገር ከሰው እስከ እንስሳት ድረስ በኩርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብጽም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንሞ ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ” ይላል፡፡ እስራኤሎች በግብጻውያን ባርነት ውስጥ ለ400 ዓመታት ቆይተዋል፡፡ በስተመጨረሻም እግዚአብሔር እስራኤሎችን በማዳን ግብፃዊያንን ሊያጠፋ ፈለገ፡፡ ይህን ዓላማውን ለማሳካት የተጠቀመበት መንገድ እስራኤሎችን የራሳቸውን ቤት ለይቶ ማሳየት የሚችል የደም ምልክት ደጃፉን እዲቀቡና እርሱም ደሙን ባየ ሰዓት ከነርሱ እያለፈ ሌሎች ሊያጠፋ ነው፡፡ ፈጣሪ ሁሉን አዋቂ አይደለምን? እንዴት የደም ምልክት ካልተጠቀመ አያውቅም እንላለን?

የደሙ ምልክት እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን ቤት ለይቶ እንዲያውቅ ሳይሆን ኃጢአታቸውን በመሸፈን ከእግዚአብሔር ፍርድ እንዲያድናቸው ነው፡፡ የደሙ ምልክት የሌላቸው ቤቶች ስላልተዋጁ የእግዚአብሔርን ፍርድ ያስተናግዳሉ፡፡ ይህ የፋሲካ በግ የክርስቶስ ምሳሌ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (1ቆሮንቶስ 5፡7)፡፡ ክርስቶስ ራሱ የተሰቀለው የፋሲካው በግ በሚታረድበት የፋሲካ ዋዜማ ነበር፡፡

15. 2ኛ ሳሙኤል 22:9-11 “በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ወደ አምላኬም ጮህኩ፤ እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም ከጆሮው ደረሰ፡፡ ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤ በሰማያትም መሠረቶች ተናጉ፤ እርሱ ተቆጥቶአልና ራዱ፡፡ ከአፍንጫው የቁጣ ጢስ ወጣ፤ ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤ ከውስጡም ፍሙ ጋለ፡፡ ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ፡፡ በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ መጠቀ” ይላል፡፡ ይህ የአምላክ ባሕሪ ነውን?

የእግዚአብሔርን ቁጣ ለመግለፅ የተነገረ ግነታዊ ዘይቤ እንጂ ቀጥተኛ ንግግር ባለመሆኑ ቃል በቃል መተርጎም ትክክል አይደለም፡፡

16. ኢሳይያስ 7:18 “በዚያን ቀን እግዚአብሔር ራቅ ካሉት ከግብጽ ወንዞች ዝንቦችን፣ ከአሦርም ምድር ንቦችን “በፉጨት ይጠራል፡፡” ይላል፡፡ እንደዚሁም “የእግዚያብሔር ቁጣ በህዝቡ ላይ ነዶአል፤ እጁን አንሥቶ መቶአቸዋል፤ ተራሮች ራዱ፤ ሬሳዎችም በመንገድ ላይ እንደ ተጣለ ጥራጊ ሆኑ፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቁጣው ገና አልተመለሰም፤ እጁም እንደ ተነሣ ነው፡፡ ከሩቅ ያሉትን ሕዝቦች የሚጠራበትን ምልክት ያቆማል፤ ከምድር ዳርቻም  በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እነርሱም እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ፡፡” (ኢሳይያስ  5:25-26)፡፡ እውን ይህ የአምላክ ባህሪ ነውን?

እግዚአብሔር የአሦራውያንና የግብፃውያንን ሰራዊት በቅፅበት ትዕዛዝ ወደ ምድረ እስራኤል በማምጣት አመፀኞችን እንደሚቀጣ የተነገረ ዘይቤ እንጂ እግዚአብሔር የፏጫል ማለት አይደለም፡፡ ጠያቂው ስለ ዘይቤያዊ አነጋገሮች ምንም ዕውቀት የሌላቸው መሆናቸውን በተደጋጋሚ አሳይተዋል፡፡

17. ምሳሌ 31፡5-7 “ለሚጠፉት የሚያሠክር መጠጥ፣ በስቃይ ላሉትም የወይን ጠጅ ስጧቸው፤ ጠጥተው ድህነታቸውን ይርሱ፤ ችግራቸውንም ከእንግዲህ አያስቡ” ይላል፡፡ በመጠጥ ውስጥ በመደበቅ ችግርን መርሳት ዘላቂ መፍትሄ ነውን? ወይስ ጥፋት? እውን ይህ የአምላክ መጽሐፍ የሚያዘው ነገር ነውን? አምላክ ወደ ጥፋት ያዛልን?

መጽሐፍ ቅዱስ ስካርን አጥብቆ ይከለክላል (1ቆሮንቶስ 6፡10)፡፡ ነገር ግን አልኮልን ለመድኃኒትነት መጠቀም አይከለክልም (1ጢሞቴዎስ 5፡23፣ ሉቃስ 10፡34)፡፡ በጥንት ዘመን ማደንዘዣ መድኃኒቶች ስላልነበሩ በህመም ለሚሰቃዩ ሰዎችና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ለደረሱባቸው ሰዎች የወይን ጠጅ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የህመም ስቃያቸውን ስለሚያስታግስላቸው ሰናይ እንጂ እኩይ አይደለም፡፡ “ድህነታቸውን” ተብሎ የተተረጎመው የእብራይስጥ ቃል “አማል” የሚል ሲሆን ሥቃይ፣ መከራ፣ ድካም፣ የሚሉ ትርጉሞች አሉት፡፡[2]

18. መሳፍንት 1፡19 “እግዚአብሔር ከይሁዳ ሰዎች ጋር ነበር፤ ስለዚህ ኮረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለነበሯቸው ከዚያ አሳደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም” ይላል፡፡ የይሁዳ ሰዎች እግዚአብሔር ከነርሱ ጋር ስለሆነ ኮረብታማውን አገር ከያዙ እግዚአብሔር አብሯቸው እያለ እንዴት ከረባዳው ምድር ማስወጣት ተሣናቸው? ጥቅሱ እንደ ሚለው ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለነበሯቸው? አምላክ “ከብረት የተሰሩ ሰረገሎች” ይበግሩታልን? እውን አምላክ የሚሳነው ነገር አለን?

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አለ ማለት ሁሉንም ነገር ማድረግ እንችላለን ማለት አይደለም፡፡ የይሁዳ ሕዝቦች በእግዚአብሔር እርዳታ ኮረብታማውን አገር ይዘውታል፡፡ ነገር ግን ረባዳውን አገር ላለመያዛቸው የብረት ሰረገሎች እንደ ምክንያት ቢጠቀሱም እንዲይዙት የእግዚአብሔር ፈቃድ አልሆነም፡፡ ምክንያቱን ደግሞ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለሕዝቡ አስታውቋል፡- “አምላክህም እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያወጣቸዋል፤ የምድረ በዳ አራዊት እንዳይበዙብህ አንድ ጊዜ ታጠፋቸው ዘንድ አይገባህም፡፡” (ዘዳግም 7፡22)፡፡

19. ትንቢት ሆሴዕ 1፡2 “እግዚያብሔር በሆሴዕ መናገር በጀመረ ጊዜ፣ እግዚአብሔር “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ተለይታ ታላቅ ምንዝርና እያደረገች ስለ ሆነ፣ ሄደህ አመንዝራ ሴት አግባ፤ የምንዝርና ልጆችንም ለራስህ ውሰድ” አለው ይላል፡፡ አምላክ በአመንዝራነት ያዛልን? በዝሙት ላይ የፈጣሪ አቋም ይህ ነውን?

እግዚአብሔር የሆሴዕን ሕይወት ለእስራኤል ማስተማርያ ለማድረግ ስለፈለገ አመንዝራ ሴት እንዲያገባ አዘዘው እንጂ አመንዝር አላለውም፡፡ ሆሴዕ ያገባት ሴት አመንዝራና ምግባረ ብልሹ ብትሆንም እርሷን የሚወድበትና የሚታገስበትን ፀጋ ሰጥቶታል፡፡ ዛሬም በማሕበረሰባችን ውስጥ ከእንደዚህ ዓይነት ሴቶች ጋር በመጋባት የሚኖሩ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ የግለሰቦቹን ጥንካሬና ታጋሽነት የሚያሳይ እንጂ በፍፁም የሚያስወቅስ አይደለም፡፡ የሆሴዕ ታሪክ እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ሌሎች አማልክትን ቢያመልኩም እንደታገሳቸውና እንደወደዳቸው የሚያሳይ ትዕምርታው ትንቢት ነው፡፡ ታሪኩ ዘይቤያዊ እንጂ በተግባር የተፈፀመ እንዳልሆነም የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ብዙዎች ናቸው፡፡

ማጣቀሻዎች


[1] Vines Complete Expository Dictionary of Old and New Testament Words, P. 203

[2] Vines Complete Expository Dictionary of Old and New Testament Words, p. 131

ለአሕመዲን ጀበል 303 ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ ማውጫ