ኢየሱስና ሰይፍ

ኢየሱስና ሰይፍ

ጥያቄ፦ በማቴዎስ ወንጌል 10፡34 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና” በማለት መናገሩ ትምህርቱ ሰላማዊ አለመሆኑን አያመለክትምን? በሌሎች ቦታዎች ላይ ስለ ሰላምና ስለ ፍቅር ከተናገራቸው መልዕክቶች ጋርስ አይጣረስምን?

መልስ፦

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቦታ ላይ እየተናገረ ያለው ክርስቲያኖች ስለሚመዙት ሰይፍ ሳይሆን በክርስቲያኖች ላይ ስለሚመዘዝ ሰይፍ ነው፡፡ አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ሲሆን በቤተሰቡ፣ በዘመዶቹና በጓደኞቹ ዘንድ ይጠላል፤ ስለዚህም ይሰደዳል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት የመጣው ሰይፍ የእርሱን የፍቅርና የሰላም መንገድ በሚከተሉት ሰዎች ላይ ሙስሊሞችን በመሳሰሉት የሐሰተኛ ነቢያትና ሃይማኖቶች ተከታዮች የሚመዘዝ እንጂ የኢየሱስ ተከታዮች የሚመዙት ሰይፍ አይደለም፡፡ ይህንን ከጥቅሱ አውድ መረዳት ይቻላል፡-

“ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል። እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ። ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ። በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤ ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል። ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።” ማቴዎስ 20፡28-39

ስለዚህ የጥቅሱ አውድ የሚናገረው አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ሲሆን ስለሚደርስበት ስደት እንጂ የኢየሱስ ትምህርት እንደ መሐመድ ትምህርት ሰይፍ ያስመዝዛል ማለት አይደለም፡፡ አንድ ሙስሊም ክርስቲያን ሆኖ ቢጠመቅ በሸሪኣ ሕግ መሰረት ስለሚመዘዝበት እስላማዊ ሰይፍ እንጂ እርሱ ስለሚመዘው ሰይፍ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ሰይፍን የሚመዙ በሰይፍ እንደሚጠፉ በመናገር ክርስቲያኖች ሰይፍ እንዳይመዙ ከልክሏል (ማቴዎስ 26:47-52)፡፡ የክርስቶስ መንገድ የሰላምና የፍቅር መንገድ እንጂ እንደ መሐመድ የሰይፍና የጥላቻ መንገድ አይደለም፡፡

መልሶቻችን