ክርስቲያኖች መርዝ እንዲጠጡ ታዘዋልን?

ክርስቲያኖች መርዝ እንዲጠጡ ታዘዋልን?

 


ሙስሊሞች በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ የማርቆስ ወንጌል 16፡18 ላይ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች በመርዝ አለመጎዳታቸውን በተመለከተ የተነገረው ነው።

ጥቅሱ እንዲህ ይነበባ፦

ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፥ የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በድውዮች ላይ ይጭናሉ እነርሱም ይድናሉ። (ማርቆስ 16፡ 17-18)

ብዙ ጊዜ ሙስሊም ወገኖች በዚህ ጥቅስ ውስጥ “የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም” የሚለውን ቃል በመጥቀስ ክርስቲያኖችን መርዝ እንዲጠጡ ይገዳደሯቸዋል። ክርስቲያኖቹ የእንቢታ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ እምነት እንደሚጎድላቸው ወይንም ደግሞ ይህ ቃል ትክክል አለመሆኑን በመናገር ሊያሸማቅቋቸው ይሞክራሉ።

ይህ የሙስሊም ወገኖች ተግዳሮት ቃሉን በትክክል ካለመረዳት የመነጨ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዲያብሎስ ተመሳሳይ ፈተና በቀረበለት ጊዜ መልስ በመስጠት እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ እንዴት መመለስ እንዳለብን አሳይቶናል፦

ከዚህ በኋላ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር” አለው። ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው። (ማቴዎስ 4፡6-7)

ዲያብሎስ የጠቀሰው እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ የሰጠውን በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የተጻፈውን ቃል ነበር፡፡ እውነት ነው እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ ከአደጋ እንደሚጠብቃቸው ተስፋን ሰጥቷል ነገር ግን ይህ ተስፋ ስለተሰጠ ብቻ ከዲንጋይ ጋር እየተጋጩ ቢሄዱና ከፎቅ ላይ ራሳቸውን ቢወረውሩ እንዲህ ዓይነቶቹን ጥቅሶች ያለ አግባብ እንዳይጠቀሙ ከሚናገረው ሌላ የእግዚአብሔር ቃል ጋር መጋጨት ይሆንባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጌታችን ኢየሱስ ማርቆስ 16፡18 ላይ የሰጠው ተስፋ በየመንደሩ እየዞርን መርዝ እንድንጠጣና እባቦችን እንድንይዝ የተነገረ አይደለም፡፡ ያንን ማድረግ እግዚአብሔርን መፈታተን ነውና፡፡ ነገር ግን ከኛ ቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ አደጋ ቢገጥመን አምላካችን ጥበቃን እንደሚያደርግልን የሚያሳይ ነው፡፡ አደጋውን ራሳችን ፈልገን የምንሄድ ከሆነ ግን እግዚአብሔርን መፈታተን በመሆኑ ሙሉ ኃላፊነቱ የኛ ይሆናል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ሆነ በኛ ዘመን ከመርዝ ጉዳት የተረፉ ብዙ አማኞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ፖሊካርፕ የተሰኘ የቤተ ክርስቲያን አባት ሮማውያን መርዝ ባጠጡት ጊዜ መርዙ ሳይገድለው እንደቀረ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሰፍሯል፡፡ እኔ የማውቀው የቅርብ ወዳጄ የማያምኑ ሰዎች መርዝ አብልተውት ያለምንም ጉዳት ተርፏል፡፡ ከዚህም የተነሳ መርዙን ያበሉት ሰዎች ተገርመው ወደ ክርስትና መጥተዋል፡፡ እኔንም ተመሳሳይ ነገር ቢገጥመኝ ጌታ በተስፋ ቃሉ መሠረት እንደሚጠብቀኝ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን የመርዝ ቢልቃጦችን ሁሉ እየጨለጥኩና በየቦታው በመዞር እባቦችን እየጨበጥኩ አምላኬን እንዳልፈታተን የተነገረኝን ትዕዛዝ በመጣስ ኃጢኣትን አልሠራም፡፡

በሐዋርያት ሥራ 28 ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእባብ የመነደፍ አደጋ በደረሰበት ጊዜ የእባቡ መርዝ ሳይጎዳው እንደቀረ ተጽፏል፡-

በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንድትባል አወቅን። አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፤ ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም አሉ። እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤ እርሱም፦ ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ። ይህስ አምላክ ነው ብለው አሳባቸውን ለወጡ። (የሐዋርያት ሥራ 28፡1-6)

ሙስሊም ወገኖቻችን እንደ እውነተኛ ነቢይ የሚቀበሏቸው ነቢዩ ሙሐመድ ይህንን መለኪያ ያልፉ እንደሆን እንጠይቃቸዋለን፡፡ ምክንያቱም በሐዲስና በሲራ ውስጥ በተጻፈው መሠረት ድግምት እሳቸው ላይ ከመሥራቱም ባለፈ የሞቱት አንዲት አይሁዳዊት ሴት ካበላቻቸው መርዝ የተነሳ ነውና፡-

በአንድ ወቅት ነቢዩ አስማት ተሠራባቸው፤ ከዚህ የተነሳም ያላደርጉትን ነገር እያደረጉ እንዳሉ በአእምሯቸው ውስጥ ይታያቸው ጀመር። (ሳሂህ አልቡኻሪ ቅፅ 4, መጽሐፍ 53, ቁጥር 400)

Once the Prophet was bewitched so that he began to imagine that he had done a thing which in fact he had not done. (Sahih Al-Bukhari Volume 4, Book 53, Number 400)

የአላህ መልዕክተኛ በሞቱበት ህመም ተይዘው ሳሉ የቢሻር እናት ልትጎበኛቸው መጣች፤ እሳቸውም እንዲህ አሉ፦ “የቢሻር እናት ሆይ፥ በኸይበር ከልጅሽ ጋር ከበላሁት ምግብ የተነሳ የልቤ ስር እንደተቆረጠ ይሰማኛል።” (የአልጠበሪ ታሪክ ቅፅ 8፥ ገፅ 124)

The messenger of God said during the illness from which he died – the mother of Bishr had come in to visit him – “Umm Bishr, at this very moment I feel my aorta being severed because of the food I ate with your son at Khaybay.” al-Tabari’s History, Volume 8, p. 124

ከላይ የተጠቀሰውን የነቢዩ ሙሐመድን አሟሟት የሚገልፀውን ታሪክ በቁርኣን ውስጥ ከተነገረ ሐሳብ ጋር ስናስተያይ ውጤቱ አስደንጋጭ ነው። ነቢዩ ሙሐመድ በእርሱ ላይ የሚዋሹ ከሆነ የልባቸውን ስር በመቁረጥ እንደሚገድላቸው አላህ በቁርኣን ውስጥ “ተናግሯል”፦

በኛ ላይም ከፊልን ቃላት (ያላልነውን) በቀጠፈ ኖሮ፤ በኅይል በያዝነው ነበር። ከዚያም ከርሱ የልቡን ስር (የተንጠለጠለበትን ጂማት) በቆረጥን ነበር። ከእናንተም ውስጥ ከርሱ ላይ ከልካዮች ምንም አይኖሩም። (ሱራ 69፡44-47)

በእስላማዊ ትውፊቶች ውስጥ የሰፈረውን የሙሐመድን የህልፈት ታሪክና በቁርኣን ውስጥ አላህ ተናገረው የተባለውን በማስተያየት የምንደርስበት ድምዳሜ የሚከተለውን ይመስላል፦

  1. አላህ በቁርአኑ እንደገለፀው ሙሐመድ ሀሰተኛ ሆነው ከተገኙ የልባቸውን ስር በመቁረጥ ይገድላቸዋል።
  2. ሙሐመድ ለሞት ሲቃረቡ የልባቸው ስር እንደተቆረጠ ተሰምቷቸው ነበር።
  3. ስለዚህ በቁርኣን መስፈርት መሠረት ሙሐመድ ሀሰተኛ ነቢይ ናቸው።

ውድ ሙስሊም ወገኖቻችን፤ ከላይ የሰፈረውን አመክንዮአዊ ድምዳሜ ያሳየናችሁ ሃይማኖታችሁን ለማብጠልጠል ወይንም ደግሞ እናንተ የምታከብሯቸውን ነቢያችሁን ለማንኳሰስ አይደለም። በገዛ መጻሕፍታችሁ ውስጥ የሌሉ የግል ሐሳቦቻችንን ስላልጨመርን ሃይማኖታችሁ እንደተነቀፈ ሊሰማችሁ አይገባም። ነገር ግን የሙሐመድን ነቢይነት ለማረጋገጥ በተጻፉት መጻሕፍት ውስጥ እንዲህ ያሉ አስደንጋጭ ነገሮች ስለምን ተገኙ? በማለት ትጠይቁ ዘንድ እናበረታታችኋለን።

ለእስልምና ሙግቶች ምላሽ